ጃፓን የዳግም ልደት ብስራት ሆኖ የተቆጠረላት የ18ኛውን ኦሊምፒያድ ጨዋታዎች ባዘጋጀችበት ጊዜ ነበር፡፡ መዲናዋ ቶኪዮ በሁሉም የውድድር ዓይነቶች በርካታ ተወዳዳሪዎች ማስተናገዷ ብቻ አይደለም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ዐቢይ ስኬት የተቆጠረው፤ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በሳተላይት አማካይነት በቴሌቪዥን መተላለፋቸው ጭምር እንጂ፡፡
ከሃምሳ ስድስት ዓመት ቆይታ በኋላ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዳግም ወደ ቶኪዮ ተመልሰዋል፡፡ ለላቀ ስኬትም መዲናዋ ተዘጋጅታለች፡፡ ከሐምሌ 17 እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚካሄደው የ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ 32ኛው ኦሊፒያድ ነው፡፡ የዘንድሮው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርካታ ውድድሮች የሚከናወኑት እ.ኤ.አ. የ1964 ኦሊምፒክ የተስተናገደባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡
ታይም መጽሔት እንደዘገበው፣ አዲሱ የቶኪዮ ብሔራዊ ስታዲየም በመክፈቻና መዝጊያ ሥነ በዓሎች ባሻገር የአትሌቲክስ ውድድሮች ሩውዝ (ሩጫ፣ ውርወራ፣ ዝላይ) ይደረጉበታል፡፡ አዲሱ ስታዲየም ታኅሣሥ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ተመርቋል፡፡ ስታዲየሙ ለአጠቃላዩ ኅብረተሰብ ከታኅሣሥ 11 ጀምሮ ክፍት የሆነ ሲሆን፣ ይፋዊ ውድድር የሚጀመረው ደግሞ ታኅሣሥ 22 (በጎርጎርዮሳዊው ቀመር በአዲሱ ዓመት 2020 መባቻ ጃንዋሪ 1) የአፄ ዋንጫ (Emperor’s Cup) በሚሰኘው የጃፓን የእግር ኳስ ሊግ ነው፡፡

ጃፓን ‹‹የኦሊምፒክ ምድር›› የሚል ቅጽል ያተረፈላት የበጋ ጨዋታዎችን እ.ኤ.አ. 1964 በማስተናገድ የመጀመሪያዋ የእስያ አገር በመሆኗ ብቻ አይደለም፡፡ ዘንድሮ (2020) አራተኛውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ታዘጋጃለች፡፡ ይህም የክረምት ኦሊምፒክ በሳፖሮ (እ.ኤ.አ. 1972) እና በናጋኖ (1998) ያስተናገደቻቸውን ጨምሮ ማለት ነው፡፡
ከሃምሳ ስድስት ዓመታት በፊት በተደረገው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ከስኬት ጫፍ ከደረሱት በርካታ አትሌቶች መካከል የሚጠቀሰው ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ጎዳናዎች ልዕልናን የጨበጠበት የማራቶን ድሉ ከጃፓናውያኑ ኅሊና እንዳይሰወር አድርጎታል፡፡
የአበበ ቢቂላ የቶኪዮ ትውስታና ገጠመኝ
“አበበ ቢቂላ በ1960 የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ተአምራዊ አሸናፊ ከሆነ ወዲህ የማራቶንን ሩጫ በ2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ የሚጨርስ ቢኖር ሻምፒዮን ይባላል፡፡ በ2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ የሚፈጽም ከተገኘ ደግሞ ድንቅ ሻምፒዮን ይባላል፡፡ አበበ ቢቂላ ግን በቶኪዮ ኦሊምፒክ 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11.2 ሰከንድ በማምጣቱ ምን ብዬ እንደምለው ቃላት አጥቼለታለሁ፡፡” ከ56 ዓመታት በፊት አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ ታላቁን የኦሊምፒክ ሩጫ ማራቶንን አሸንፎ ወርቅ ሲያጠልቅ ‹‹የበርሊን ማራቶን መጽሔት›› ዘጋቢ የጻፈው ነው፡፡
ረቡዕ ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. ነበር፤ ቦታው ጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ በተለይ 15 አትሌቶች የኦሊምፒኩን የወርቅ ሜዳሊያ ለማግኘት ቋምጠዋል፤ ለመፎካከር አፍጥጠዋል፡፡ የሮም ኦሊምፒክ ባለወርቅ አበበ ቢቂላ የትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምና ማድረጉና ሳያገግምም ከውድድር ሥፍራ መድረሱም የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ካልሲ አጥልቆ፣ ጫማውን ለተጫማው አበበ ውድድሩ አስቸጋሪ አልሆነበትም፡፡ እስከ መጀመሪያዎቹ 10 ኪሎ ሜትር የአውስትራሊያው ሮን ክለርክ ቢፎካከረውም ጥሎት በመሔድ ያለአንዳች የቅርብ ተቀናቃኝ በ2 ሰዓት 12 ደቂቃ 11.2 ሰኮንድ በድል አድራጊነት ፈጸመ፡፡ ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድል ፈጸመ፡፡
ይኸም ብቻ አይደለም ባሸናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባሲል ሔትሌይ በ2 ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሰኮንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን በ1 ደቂቃ 43 ካልዒት (ሰከንድ)፣ 8 ሣልሲት (ማይክሮ ሰከንድ) የሰበረበት ነው።
‹‹እንደ በረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ
ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ››
ብለው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914-1979) እንዲቀኙለት አድርጓቸዋል፡፡
አበበ በቶኪዮ ማራቶን ከመወዳደሩ 36 ቀናት በፊት ረቡዕ መስከረም 6 ቀን 1957 ዓ.ም. ቀዶ ሕክምና አድርጎ ስለነበር እንኳን ሊያሸንፍ ውድድሩን ይፈጽማል ብሎ ያሰበ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ 70,000 የሚሆነው የቶኪዮ ስታዲየም ተመልካች ማን ያሸንፍ ይሆን? እያለ ውድድሩን በጉጉት ሲጠባበቅ ማሸነፍን ምሱ ያደረገው ሸንቃጣው አበበ የ30 ደቂቃ የሰውነት ማሟሟቂያ አድርጎ ከመናፈሻ እንደወጣ አትሌት እየተዝናና ከስታዲየሙ ሲደርስ ተመልካቹ ዓይኑን ማመን አቅቶት ነበር፤ ከዚያም ውድድሩን አጠናቆ ወዲያውኑ እንደ ጠዋት የአምስት ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጅምናስቲክ መሥራት ሲጀምር ተመልካቹ መጀመሪያ ፈገግ አለ፡፡ ከዚያም በመገረም ዘግየት ብሎ አድናቆቱን በከፍተኛ ጭብጨባ ገለጸለት፤ ይላል ገድሉን የዘገበው የባሕር ማዶ መጽሔት፡፡
ዴቪድ ዎልቺንስኪ በኦሊምፒክ ድርሳኑ (The Complete History of Olympics 2004 Edition) እንደጻፈው፣ አበበ አካሉን ሲያፍታታ ላየው ‹‹አዝናለሁ፣ ማራቶን አጭር ሆኖብኛል›› ያለ አስመስሎበታል፡፡ እንዲያውም ለጋዜጠኞች በዚያን ጊዜ በሰጠው ምላሽ ለሌላ 10 ኪሎ ሜትር የሚያስሮጠኝ ኃይል አለኝ ነበር ያላቸው፡፡
በሽልማት ሥነ ሥርዓቱም አንድ ያልተጠበቀ፣ ከዚያም በፊትም ያልታየ ሌላ አስደናቂ ነገር ተከሰተ፡፡ አበበ ቢቂላ በሮም እንዲሁም ከቶኪዮ በኋላ ማሞ ወልዴ በሜክሲኮ ማራቶንን ሲያሸንፉ የተዘመረላቸው
‹‹ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ፣
ባምላክሽ ኃይል በንጉሥሽ››
የሚለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር የጃፓን ባለሥልጣኖችም ሆኑ የሙዚቃ ባንዱ አያውቁትም ነበር፡፡ እናም ዘየዱ፤ የማርሽ ባንዱ አጋጣሚውን ተጠቀመ፡፡ የጃፓንን ሕዝብ መዝሙር ለኢትዮጵያ ድል ማብሰሪያ አደረገው፤ ሕዝቡም ፈነደቀ፡፡ 17 ቁጥር መለያን ያጠለቀው አበበም በጃፓን ሕዝብ ልቡና ውስጥ ታተመ፡፡ ማራቶን በጃፓን ውስጥ እንዲህ ተወዳጅ ሊሆን የቻለው ከአበበ ቢቂላ ድል በኋላ ነው፡፡
ለአፈ ታሪክ የበቃው አበበ ቢቂላ
በኩሩ አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት ያስመዘገባቸው ተደጋጋሚ ድሎቹና ስኬቶቹ ለአፈ ታሪክነትም የበቁበት አንዳንድ አጋጣሚዎችን እዚህ ላይ ማንሳት ይገባል፡፡
አበበ የአትሌቶች በኩር በመሆኑ፣ የመጀመሪያ ውድድሩንም በባዶ እግሩ በመሮጥ የተፈጸመ በመሆኑ ክንውኑን ከታሪካዊ እውነታ ባሻገር አፈ ታሪክ ውስጥም እንዲገባ አስችሎታል፡፡ ኅብረተሰቡ የራሱን አፈ ታሪክ ፈጥሮለታል፡፡ ጀግንነቱን ለማጉላትና ለማወደስ ከተፈጠሩት አፈ ታሪኮች መካከል በባዶ እግሩ የመሮጡ ምክንያትና ሮም ከነበረው የአክሱም ሐውልት ጋር የተያያዙ ተረኮች ይገኙበታል፡፡
አበበ ‹‹እኔ በባዶ እግሬ የምሮጥበት ምክንያት ጫማ አጥቼ ሳይሆን ኢትዮጵያ አገሬ ከጥንት ጀምሮ የጀግንነት ሙያ በድፍረትና በቆራጥነት የምትፈጽም መሆኑን ለዓለም በይፋ ለማሳወቅ ነው፤›› ማለቱ በዘመኑ የተወሳ ነው፡፡ ሰዉ ደግሞ በአፈ ታሪኩ ለየት ያለ የራሱን ተረክ እየተቀባበለ አወጋው፣ ተረከው፡፡ እንዲህም አለ፡-
‹‹አበበ ቢቂላ በሮም የማራቶን ሩጫውን ሲጀምር ጫማ ተጫምቶ ነው፡፡ ሩጫውን እያጋመሰ ሳለ ‹እንዴ የአገሬን ዳገት ቁልቁለቱን የወጣሁት የወረድሁት በባዶ እግሬ አይደለም እንዴ፣ ሶላቶ ጣሊያን ባለበት አገር ጫማዬን አውልቄ ነው የምሮጠው ብሎ አሽቀንጥሮ ጥሎ በመሮጥ ድሉን ፈጸመ፤›› አሁንም በተለይ ወግና ተረቱ ላይ በሚያተኩሩት ዘንድ መወሳቱ አልቀረም፡፡
አበበ ቢቂላና አበበ ዋቅጅራ (እርሱም በባዶ እግሩ ነበር የሮጠው) ከአሠልጣኞቻቸው ስዊድናዊው ኦኒ ኒስካነን ጋር ከውድድሩ ቀናት በፊት የመወዳደሪያ ሥፍራውን መመልከታቸው አበበም ከአቅራቢያው የሚገኘውን ታሪካዊውን የአክሱም ሐውልትን ማስተዋሉ እውነት ነው፡፡
‹‹አበበም አክሱም ሐውልቱን ተመልክቶ ወኔው ተቀሰቀሰ፡፡ የዘመኑን ታላቅነትና ኃያልነት አስተዋለ፡፡ ከኢትዮጵያ ተዘርፎ ሮም መቆሙ ቆጭቶታል፤ አስከፍቶታል፡፡ ግን እንደ አክሱም የዓለም ገናና ታሪክ እርሱም መግነን፣ መንገሥ ሽቷል፡፡ እጅ ላለመስጠት፣ ላለመረታት ቃል ገባ፤›› አፈ ታሪክ ነው፡፡
አበበ ቢቂላና አበበ ዋቅጅራ በባዶ እግር ለምን ሮጡ?
በሮም ኦሊምፒክ አበበ በባዶ እግሩ የሮጠበት ምክንያት በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ሲንፀባረቁ ኖረዋል፡፡ የኦሊምፒክ ድረ ገጽን ጨምሮ የተለያዩ ምንጮች ‹‹ለአበበ የሚስማማ ጫማ በመጥፋቱና የሞከረውም ጫማ ስለጠበበው ያለጫማ መሮጥን መርጧል፤›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡ ጸሐፊዎቹ ሰባተኛ ስለወጣው አበበ ዋቅጅራም በባዶ እግሩ ስለመሮጡ እንኳ ያነሱት ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ እውነታውን በተመለከተ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑካን መሪ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ የገለጹት እውነታ፣ ከኦኒ ማስታወሻ አግኝቶ ሰሎሞን ሐለፎም በስዊድን በቅርቡ ባሳተመው፣ ‹‹ኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ ከ1910 – 1984›› በሚለው መጽሐፉ ከጻፈው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
‹‹ከውድድሩ በፊት ሮም በነበርንባቸው ቀናት አበበ ቢቂላና አበበ ዋቅጅራ የማራቶን መሮጫውን ጎዳና እንዲለማመዱት አድርጌ ነበር፡፡ አራት አምስት ጊዜ ተለማምደውበታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመካከለኛውንና የመጨረሻውን ክፍል እየለዋወጥን መሮጫውን አስቀድመው እንዲያጠኑት አድርገናል፡፡ በጫማም ያለጫማም ሞክረውታል፡፡ ከአበበ ቢቂላ ኋላ ኋላ በመኪና እየተከታተልኩ የአሯሯጡን ሥልት የርምጃውን ፍጥነት ወዘተ. ስቆጣጠርና ስለካም ነበር፡፡ በጫማ ሲሮጥ በባዶ እግሩ ከሚሮጠው በደቂቃ አምስት ስድስት ዕርምጃ ያህል ይቀንሳል፤ አሯሯጡም በባዶ እግሩ እንደሚሮጠው የቀለጠፈ እንዳልሆነ ልብ አልኩ፡፡ እኔን ጥየቃና እግረ መንገዱንም ውድድሩን ለመመልከት ከስዊድን የመጣው ታናሽ ወንድሜ አርነ ደግሞ በሌላ መኪና አበበ ዋቅጅራን እየተከተለ እንዲሁ ሲያጠና ነበር፡፡ ከዚሁ ግምገማ በኋላ ከነሱ ጋር ተመካክረን ሁለቱም ሯጮች በባዶ እግራቸው እንዲሮጡ ወሰንን፡፡
አበበ ቢቂላ ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም. በሮም ኦሊምፒክ ድሉን ዘከረ፡፡ ባለ 11 ቁጥር መለያው ሹራቡን ለብሶ ከነፈ፡፡ የመጀመርያው ጥቁር አፍሪካዊ የማራቶን ባለወርቅ ሆነ፡፡
‹‹በባዶ እግሩ! በእውነት እናስብ! ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ መሮጥ ጨርሶ ያልተለመደ፣ ከእነሱ በፊትም ሆነ ኋላ ተደርጎም ተተርኮም የማይታወቅ›› እንዳለው የኦሊምፒክ ሪቪው አዘጋጅ፡፡ ከሮም አራት ዓመት በኋላ ቶኪዮ ማራቶንና አበበ ዳግም በድል ተገናኙ፡፡
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ክብር ዘበኛ ሠራዊት ሻምበል የነበረው አበበ ቢቂላ፣ ከአፈ ታሪክ ሌላ በሕዝባዊ ዘፈንም ሲነሳ ኖሯል፡፡ አንዱ ከበኩር ድምፃዊው የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ጋር የተዛመደበት ነው፡፡
‹‹ያገባሻል ያገባሻል
አበበ ቢቂላ ያገባሻል
ይድርሻል ይድርሻል
ጥላሁን ገሠሠ ይድርሻል››
በ1960ዎቹ ሲዘፈን የነበረው ኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ በሜክሲኮ ኦሊምፒክ (1961 ዓ.ም. መስከረም) በማሞ ወልዴ ድል አድራጊነት ስትቀዳጅ የተዜመ ነበር፡፡
በቀጣዩ አራት ዓመት አበበ ቢቂላ ለሦስተኛው ድል ሜክሲኮ ላይ ቢሮጥም፣ 17ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ባጋጠመው የጡንቻ መሸማቀቅ አቋርጦ ወጥቷል፡፡ ቢሆንም ድሉ ከኢትዮጵያ አላፈተለከም፡፡ በመስከረም 1961 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1968) የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ማሞ ወልዴ በኦኒ አሠልጣኝነት ኢትዮጵያን ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ ያደረጋትን ድል አስመዘገበ፡፡ መርአዊ ገብሩም ስድስተኛ ሆነ፡፡ ማሞ በ10,000 ሜትር ሩጫም ከኬንያዊው ናፍታሊ ቲሙ ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር አድርጎ የብር ሜዳሊያ ለማጥለቅ ችሏል፡፡ የማሞ የማራቶን ድልም በሰሎሞን ተሰማ ገጣሚነት እንዲህ ቀረበ፤

‹‹ማራቶን ማራቶን ማራቶን ልዕልቷ
አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ
ማራቶን ደንግጠሽ አቤን ብትቆጪ
ዞሮም አልቀረልሽ የትም አታመልጪ፤
ሮም በባዶ እግሩ ቶኪዮ በጫማ
ድል ነሺው አበበ በሁለቱ ከተማ፤
አበበ ቢወጣ በእግር ወለምታ
ማሞ ድልን ነሳ በሞቀ ሰላምታ…›› ተብሎም ተዘፈነ፡፡
20ኛው ኦሎምፒያድ የጀርመኗ ሙኒክ ከተማ በ1964 ዓ.ም. (1972) ስታዘጋጅ የተካፈለችው ኢትዮጵያ ለወርቅ ባትታደልም በነሐስ ሜዳሊያ ለመታጀብ ችላለች፡፡ ማሞ ወልዴ በ40 ዓመት ዕድሜው ማራቶንን ሮጦ ሦስተኛ በመሆኑ፣ አንጋፋው የኦሊምፒክ ማራቶን ባለሜዳሊያ ተሰኝቷል፡፡
በመጽሐፉ የተጠቀሱትና ስለኦኒ ኒስካነን ትውስታቸውን ያጋሩት ማሪያነ ሳውተር፣ ኦኒ በፊንላንድኛ መልካም ዕድል ማለት ነው ይላሉ፡፡ እንዳሉትም ከዕድለኛነታቸው መገለጫዎች መካከል የበኩር አትሌት አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ ስኬቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹…ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንዲሉ እሱም ዕድለኛም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዓለም ላይ ብዙ ቦታዎችን ጎብኝቷል፡፡ የልጅነትና የወጣትነት አፍላ ጊዜውን ያሳለፈበት ሶልናና ለሁለት ዓመት ኮንትራት ሄዶ የዕድሜውን እኩሌታ ያህል የኖረባት አዲስ አበባ ግን በኦኒ ልብ ውስጥ እጅግ ላቅ ያለ ሥፍራ ነበራቸው፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡
‹‹ማራቶን ማራቶን
ማራቶን ልዕልቷ
አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ››
አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ተፎካካሪዎቹን ጣጥሎ ለድል እየገሰገሰ የተመለከተች አንዲት ጃፓናዊት ‹‹አይ ላቭ ዩ›› ስትለው፣ ‹‹የላቡን ነገር ተዪው›› ማለቱ አፈ ታሪኩ ያወሳል፡፡
የ32ኛው ኦሊምፒያድ ተስፋ
ኢትዮጵያ በዘመናዊ ኦሊምፒክ የስድሳ አራት ዓመት የተሳታፊነትና የተፎካካሪነት ታሪኳ የድል ጎህ የቀደደችው በአትሌቲክስ በተለይም በረዥም ርቀት ነው፡፡ ፋና ወጊውም በኩሩ አትሌት አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ በማራቶን ያስመዘገበው የወርቅ ሜዳሊያ ነው፡፡ በተከታታይ ሦስት ኦሊምፒያዶች (ሮም፣ ቶኪዮ፣ ሜክሲኮ) የተገኙት ወርቆች ሁሉም የማራቶን ናቸው፡፡ ይህም የኢትዮጵያና የማራቶን ስም በዓለምና ኦሊምፒክ መንደር እንዲተሳሰር አድርጓል፡፡
በሙኒክ ኦሊምፒክ ማሞ ወልዴ የነሐስ ሜዳሊያ ካገኘ በኋላ እስከ ሲድኒ ኦሊምፒክ ድረስ ኢትዮጵያና የወንዶች ኦሊምፒክ ማራቶን ተፋተው ነበር፡፡ ከሠላሳ ሁለት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ድሏ የተመለሰችው ገዛኸኝ አበራ የአሸናፊነቱን አክሊል ከደፋ በኋላ ነው፡፡ በአትላንታና በለንደን ኦሊምፒክ ሴቶች ማራቶን ፋና ወጊዋ ፋጡማ ሮባ እና ቲኪ ገላና እንደ አበበና ማሞ ስማቸው ከፍ ብሏል፡፡
በዘንድሮው 32ኛው ኦሊምፒያድ በወንዶች ማራቶን ለ20 ዓመት የራቀን፣ በሴቶች ማራቶን ለ8 ዓመት የራቀን ወርቅ ሜዳሊያን ማን ያስመልስልን ይሆን?