Ethiopian Reporter Magazine
Wednesday, March 29, 2023
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት
Ethiopian Reporter Magazine
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
Ethiopian Reporter Magazine
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ

ምርጫ 2012 ሥጋቶቹና ተስፋዎቹ

በ ታምሩ ጽጌ
February 2020
ምርጫ 2012 ሥጋቶቹና ተስፋዎቹ
0
ያጋሩ
602
ዕይታዎች
Share on FacebookShare on Twitter

ኢሕአዴግ አሐዳዊውን የደርግ ‘ኢሕዲሪ’ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) አስተዳደር በፌዴራላዊው ‘ኢፌዴሪ’ (የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) አስተዳደር ከተካ በኋላ በአገራችን አምስት ምርጫዎች ተካሂደዋል። እንዳለመታደል ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢሕአዴግ “ነፃና ፍትሐዊ” ሲል ቅጥያ ስም ከሰጣቸው ከእነዚህ ምርጫዎች አንዳች ያተረፈው ነገር የለም። እያንዳንዱ ምርጫ የኢሕአዴግን የሥልጣን ዕድሜ ከማስረዘምና በተለጠጠ ዕቅድ አገሪቱን አርባ ዓመታት ለመግዛት ዳር ዳር እንዲል ከማድረግ የተሻለ የአስተዳደር ለውጥም አላመጣለትም። ይባስ ብሎ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ከነበረው፣ ነገር ግን አጨራረሱ ካላማረው ምርጫ 97 ያተረፈው ነገር ቢኖር በአምባገነንና ‘እኔ ብቻ አውቅልሃለሁ’ በሚል አመራር ሥር መውደቅ ነው። ኅብረተሰቡ “ኢሕአዴግ የይስሙላ ምርጫ እያደረገ ሕገወጥ አካሄዱን ሕጋዊ መልክ ለማስያዝ ከሚጥር ይልቅ አንደኛውን ያለ ምርጫ አገሪቱን ቢገዛ ቢያንስ ‘በዴሞክራሲ ለምድ የመጣ አምባገነን ተኩላ’ ተብሎ ከመወቀስ ይድን ነበር” ይላል። እንዲያም ሆኖ ኢሕአዴግ ቀን ሳያዛባ በ27 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ አምስት አገር አቀፍ ምርጫዎችን አካሂዷል።

እነሆ ኢሕአዴግ ከውጭ ተጠራቅሞ በመጣ የሕዝብ ተቃውሞ ተገፍቶና ከውስጥ በተነሳበት የለውጥ እንቅስቃሴ ተጨምቆ መጋቢት 2010 ዓ.ም. አዲስ አስተዳደር ሲወልድ በውስጠ ታዋቂ ህልውናውም በዚያው አከተመ። 27 ዓመት የኖረው ‘አይበገሬ መሳዩ ኢሕአዴግ’ በስም ሰፍኖ፣ በተግባር ግን ከስሞ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ያህል ሲያዘግም ቢቆይም ህልውናው ክስመት ላይ ደርሷል። ዕንቁላሉን ሰብሮ ከውስጡ የወጣው “ብልፅግና ፓርቲ” በላዩ ላይ ቆሞ አዲስ ተክለ ሰውነቱን እየገነባበት ነው። ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫም በዚህ ጅምር የፖለቲካ ለውጥ ሒደት ላይ በመጪው ግንቦት ወር 2012 ዓ.ም. ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለታል። ለዚህ ምርጫ የቀሩት ጊዜያት ከመንፈቅ ከፍ አይሉም።

አሁን ባለንበት ወቅት (ይህ ጽሑፍ ማተሚያ ቤት እስኪገባ ድረስ) ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡም፣ በምዝገባ ሒደት ላይ ያሉም ሆነ ያልተመዘገቡ ቁጥራቸው ከ150 የሚልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱ ነው። በአወቃቀራቸው ክልላዊና አገር አቀፍ የሆኑ፣ ቢሯቸውን በኢትዮጵያና በውጭ አገሮች አድርገው ሲንቀሳቀሱ የኖሩ፣ ትግላቸውን በሰላማዊ መንገድና በትጥቅ ሲያካሂዱ የቆዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ 2012ን በተስፋም፣ በጉጉትም፣ በሥጋትም እየጠበቁ ነው።

ምርጫ 2012 ዓ.ም. መለያ ቀለሙ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መተንበይ አስቸጋሪ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በአንድ ወቅት “ጥቂት ፓርቲ፣ ከባድ ፉክክርና ነፃ ምርጫ” ብለው እንደገለጹት ዓይነት ባህሪ ይላበሳል ወይስ በተቃራኒው  “ብዙ ፓርቲ፣ ውል አልባ ፉክክርና አወዛጋቢ ምርጫ” ይሆናል? … አሁን ድረስ አይገመቴ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፎች

አቶ ጃዋር መሀመድ

አቶ ጃዋር መሀመድ “በማላውቀው ሀኪም መነካት አልፈልግም” በማለቱ በግል ሀኪም እንዲታከም ጥብቅ ትእዛዝ ተሰጠ

August 2020
C:\Users\IT\Documents\A01\pics

የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውኃ ሙሌትና መቆሚያ ያጣው የግብፅ ሩጫ

July 2020

የጸጥታው ምክርቤት አባል አገራት በሕዳሴው ግድብ ላይ ለመወያየት ተስማሙ

June 2020

አደም ፉራን ወ/ሮ ኬሪያን ኢብራሔምን ተክተው የፌደሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ ሆነው ተመርጠዋል

June 2020

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያመሰቃቀለው የትምህርት ሥርዓት

May 2020

ከኃያላን እስከ ታዳጊ ላሉ የዓለም ሀገራት ፈተና የሆነው ኮቪድ-19

April 2020

ከሁሉም በላይ በምርጫው ዙሪያ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚነሳው የሁለት ጠርዝ ክርክር “ምርጫው ይካሄድ፣ አይካሄድ” በሚለው ሐሳብ ላይ የሚያጠነጥን ሆኖ ይታያል። የአገሪቱ የሰላምና መረጋጋት ትንበያ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት በሚገባው መልኩ አለመጠናከር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅት አናሳነት፣ የምርጫ ቦርድና የፓርቲዎች ውዝግብን ዕልባት አለማግኘት፣ የሽግግር መንግሥትን አስፈላጊነት፣ ወዘተ በምክንያትነት የሚያነሱ ወገኖች “ምርጫው መዘግየት አለበት” ሲሉ በሌላ በኩል የሕገ መንግሥታዊነት መሸርሸርን፣ ሥልጣን ላይ ያለውን አዲስ ፓርቲ ሕጋዊ ቅቡልነት፣ የሕዝቡን ድምፅ መከበርና ሌሎችንም አካሄዶች የሚያነሱ ወገኖች ደግሞ “ምርጫው በጊዜው ይካሄድ” እያሉ ነው። የፖለቲካው ምኅዳር በእነዚህ ሁለት ጽንፎች ተወጥሮ ባለበት በዚህ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ መንግሥት የሀዋሳውን ጉባዔ ውሳኔ በመንተራስ ምርጫው በጊዜ መካሄድ አለበት ሲል፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አገም ጠቀም ሲል ቆይቶ በቅርቡ በቦርድ ሊቀመንበሩ አማካይነት “ምርጫው በጊዜው መካሄዱ አይቀርም” የሚል መግለጫ ሰጥቷል።

ይህንን መነሻ በማድረግም ኢዜማና ኢሕአፓን የመሳሰሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ምርጫ ቅስቀሳ ገብተዋል። ገዥውና ሕጋዊ ሰውነቱን ከምርጫ ቦርድ የሚጠብቀው ብልፅግና ፓርቲም ፕሮግራሙን  ማስተዋወቅ ጀምሯል። አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫው ቢካሄድም ባይካሄድም በዋናነት የምንሠራው የአገራችን ሰላም እንዲከበር ነው በማለት በምርጫው ጉዳይ ላይ ያላቸውን ዝግጁነት ከመግለጽ ሲቆጠቡም እየተስተዋለ ነው።

በዚህ መካከል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና ምሁራንን “የ2012 ምርጫ ተስፋና ሥጋቶች ምን ይሆኑ?” ብሎ የጠየቀው ሪፖርተር መጽሔት “አንኳር” ጉዳዩ በዚሁ ርዕስ ላይ እንዲያጠነጥን አድርጓል።

የምርጫ ዋጋው ስንት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዋጋ ቢያስከፍልም ምርጫው ይካሄዳል ብለዋል፡፡ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝተው ከተመዘገቡና ለምርጫው ይወዳደራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ቁጥራቸው ከሰባ በላይ የሚሆኑ ተፎካካሪ ፓረቲዎች ደግሞ “ሕይወት የሚያስከፍል ምርጫ መንግሥተ ሰማያት ማስገቢያ ባለመሆኑ መካሄድ የለበትም፤” እያሉ ነው፡፡ የምርጫው ተዋናዮች ምርጫ መካሄድ አለበት የለበትም እያሉ ያሉት በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመርያው ብልፅግና ፓርቲና የተወሰኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫው መካሄድ አለበት የሚሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የምርጫ ጊዜ የሚያበቃው በዚህ ዓመት በመሆኑና የሕገ መንግሥቱን አስገዳጅ ድንጋጌ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛውና ምርጫው መካሄድ የለበትም የሚሉት ደግሞ በአገሪቱ አብዛኛው አካባቢ ብጥብጥ፣ ሞትና መፈናቀል ባለበት ሁኔታ መረጋጋት ሳይፈጠር ምርጫ ማድረግ ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር የሚያስገኘው ፋይዳ የለውም በሚል ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ
አቶ ሙሉጌታ አበበ
አቶ የሺዋስ አሰፋ

በኢትዮጵያ ካለው አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ‹‹ምርጫ መካሄድ ይችላል ወይስ አይቻልም?›› የሚለው ክርክር ሌሎች ከሕግ ውጪ የሆኑ አንድምታዎች ቢኖሩትም፣ ከሕግ አንፃር ግን ‹‹አንድ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ምን ማሟላት አለበት?›› የሚለውን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና በአገር ውስጥም በተለያየ ቦታ ከሚሠራባቸው ተቀባይነት ካገኙ መርሆዎች አንፃር፤ ሕጎች ተቃኝተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መቋቋሙን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሳይ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ ነፃ፣ ተዓማኒና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ በሚያስችል መልኩ፣ ቀደም ብለው በሥራ ላይ የነበሩ የምርጫ ሕግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ሕግና የሥነ ምግባር ሕግ ክለሳ ተደርጎባቸው በአንድ ሕግ ተጠቃለው መውጣታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ነፃና ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ ገለልተኛና ተዓማኒ የምርጫ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ የሕግ ማዕቀፍም ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማካሄድ ከሚያስፈልጉ ነባራዊ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ፀጥታ ነው፡፡ ከሕጉ ብንነሳ፣ ሕጉ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ማድረግ እንደሚያስችል ሕግ ነው፡፡ ሕጉ ከመወጣቱ በፊት ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫ እንዳይካሄድ የሚያደርጉ ማነቆዎችን ማየት መቻሉን የጠቆሙት ዶ/ር ሲሳይ፣ የምርጫ አስፈጻሚ አካሉ ገለልተኛ ሆኖ አለመታየቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሚያስፈጽምባቸው ሁኔታዎችም፣ ምርጫ አስፈጻሚዎችን የሚመለምልበት መንገድ ነፃና ግልጽ አለመሆኑንና ያለውን በጀት የሚጠቀምበት መንገድ የቦርዱን አቋም የሚያጋልጥ ነው የሚለውን መመልከት እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የቦርዱ አባላትን አመራረጥ ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ ሲቪክ ማኅበራት ድረስ ከተሳተፉበት በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማወያየት እንዲመረጡ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ አስፈጻሚዎችን በሚመለከት ቀደም ብሎ ይሠራበት የነበረውን 120 ሺሕ የሚሆኑ አስፈጻሚዎች ከመንግሥት ተቋማት ለቦርዱ ይመደቡለት የነበረው አሠራር ቀርቶ ራሱ ቦርዱ እያየ፣ ገለልተኛነታቸውን፣ ብቃታቸውን፣ ነፃነታቸውን እያየና እየመዘነ ቦርዱ የሚመለምልበት አሠራር በሕግ ተካቷል፡፡ ቦርዱ ቀደም ብሎ በጀት የሚመድብለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይሆን ገንዘብ ሚኒስቴር ስለነበር፣ የሚለቀቅለት ቦርዱ በፈለገ ጊዜ ሳይሆን ምርጫ ከደረሰ በኋላ የነበረውን አሠራር የሚያስቀርና በቀጥታ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወስኖለትና በፈለገ ጊዜ ተለቆለት በራሱ አሠራር እንዲጠቅምም በአዲሱ አዋጅ መስተካከሉን ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል፡፡ በዚህና ሌሎች ከተካተቱት ድንጋጌዎች አንፃር ሕጉ ምርጫ ለማካሄድ በቂ ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋሙም ገለልተኛ ሆኖ ሊሠራ በሚችልበት መልኩ እንዲቋቋም መሠረት የጣለ ሕግ መኖሩንና የተመረጡትም የቦርድ አባላትም በነፃ እንደተመረጡም ዶ/ር ሲሳይ መስክረዋል፡፡ ወደ ምርጫ አፈጻጸም ሲገባ ወይም ከመገባቱ በፊት ቦርዱ ሕጉን ማስፈጸሚያ መመርያዎችን ማውጣት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የምርጫው ወቅት ካለው አጭር ጊዜ አንፃር ‹‹ለዝግጅት ያለው ጊዜ ምን ያህል ነው? የመራጮች ምዝገባና ተመራጭ ዕጩዎችን ማቅረቢያ ጊዜና የፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገቢያ መሥፈርት የሚከለሰው መቼ ነው?›› የሚለውን ስሌት ውስጥ አስገብቶ ቦርዱ መናገር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የምርጫ ‘መቼና እንዴት’?

የምርጫው ቀን አስፈጻጸም ፖለቲካዊና ሕጋዊ አንድምታ እንዳለው የጠቆሙት የሕግ ባለሙያው፣ ሕጉ ቀዳሚ ቢሆንም፣ አንዳንድ አገሮች ላይ ከሕግ በላይ የሆነ ነገር ሲያጋጥም ምርጫ የሚተላለፍበት የሕግ ማዕቀፎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ግን በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ ያለው በየአምስት ዓመቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ ይካሄዳል ከማለቱ በስተቀር ስለሚቀየርበት ሁኔታ ምንም ያለው ስለሌላ ለሕግ ትርጉም ክፍተት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የወጣው አዋጅ ያለ ስምምነት ስለመፅደቁና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅሬታ እያቀረቡበትና እስከ ረሃብ አድማ ለማድረግ ጭምር እንቅስቃሴ እየተደረገበት ስለመሆኑ ዶ/ር ሲሳይ እንደገለጹት፣ በሕጉ ላይ ብዙ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተሳትፈዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመመዝገብ ሦስት ሺሕ አባላትና አሥር ሺሕ አባላት በሚለው ድንጋጌ ላይ ተቃውሞ አንስተዋል፡፡ የተሻሻለው ሕግ በአንድ የምርጫ ክልል ላይ 12 ተወዳዳሪ ዕጩዎች ብቻ ይቀርባሉ ይላል፡፡ ቅደም ተከተላቸውንም ሲያስቀምጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያላቸው ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ይላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመመዝገብ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመሆን 1,500 ፊርማ ይበቃል ይላል፡፡ በዚያ ሕግ መሠረት ቢሠራ 1,500 ፊርማ ይዞ ይመዘገባል፡፡ ዕጩ ለማቅረብ ደግሞ 12 ብሎ ገድቦታል፡፡ ከ12 ‹‹ስንት ያልፋልና ቅደም ተከተል እንዴት ይሰጣል?›› የሚለው ትልቅ ቀውስ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ በትንሽ ፊርማ ቁጥር ከተሄደ ትልቁ ቀውስ ይፈጥራል፡፡ የምርጫ ቦርዱን ገለልተኛነትም ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከታል፡፡ ሌሎች አገሮች ‹‹በአንድ ምርጫ ክልል ይኼንን ያህል ሰው ይወዳደር ብለው መጠን አያስቀምጡም›› ነገር ግን የመወዳደሪያ መግቢያውን ጠንከር ያደርጉታል፡፡ ለኢትዮጵያም የተሻለ ሆኖ የተገኘው ይኼ ስለሆነ ፓርቲዎቹ በአዋጁ የተጠቀሰውን አሟልተው እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለበት አገር የአሥር ሺሕ ሰዎች ፊርማ ማሰባሰብ በጣም ትንሽ ነው፡፡ የሌሎች አገሮችን ልምድ ብናይ ጎረቤት አገር ኬንያ እስከ 24 ሺሕ ፊርማ ማቅረብን ይጠይቃል፡፡ ቁጥሩ በዝቶ ሳይሆን አሁን ላይ አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ፓርቲዎቹ እንደፈለጉ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ማስፈረም እንደማይችሉ ቢናገሩም፣ ሕግ ሲቀረፅና ሲወጣ ዘላቂነት ያለውና ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ እንጅ ‹‹ሰላም ካለ አሥር ሺሕ፣ ሰላም ከሌለ አንድ ሺሕ›› እየተባለ ሊቀመጥ እንደማይችል ዶ/ር ሲሳይ ተናግረዋል፡፡ አፈጻጸሙን በውይይትና በድርድር ማድረግ እንጂ የወጣው ሕግ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሕጉ ላይ ፀጥታዎችን ያገናዘቡ አንቀጾች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ምርጫ እየተካሄደ የፀጥታ ችግር ቢፈጠር ምርጫው ተቋርጦ ሌላ ጊዜ ሊደረግ የሚችልበት ሁኔታ መቀመጡንና ቆጠራ ላይም ችግር ቢፈጠር ምን መደረግ እንዳለበት በሕጉ መደንገጉን አስታውሰዋል፡፡ ቦርዱም ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በየምርጫ ጣቢያውና በየምርጫ ክልሉ ምን ማድረግ እንዳለበት በሕጉ ስለተቀመጠ፤ ምርጫው ሕጉን መሠረት አድርጎ መካሄድ እንደሚችል የሕግ ምሁሩ ዶ/ር ሲሳይ ይናገራሉ፡፡

የሥልጣን ምንጭ ማነው?

የኢትዮጵያ ሕዝብ በመረጠው መሪ መተዳደር አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ሌሎች ጥያቄዎች የሚመጡት ሕዝብ የመረጠው መሪ ከምርጫ በፊት የገባውን ቃል ማሟላት ሲያቅተው ወይም ለመመረጥ ያቀረበውን የመወዳደሪያ ሐሳብ ወይም ፕሮግራም መተግበር ሲያቅተው የሚቀየር ይሆናል፡፡ ላለፉት ሦስት አሠርታት ሕዝቡ ‹‹በመረጥኩት መሪ ልተዳደር›› ሲል፣ ኢሕአዴግ ሕዝብ የሚያነሳውንና የሚፈልገውን ትቶ ያልተጠየቀውን ‹‹መልካም አስተዳደር፣ ልማት፣ የውኃ፣ የመብራት፣ . . .›› እያለ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ ዝቅ ሲያደርገው ኖረ እንጂ ጥያቄው ‹‹በምፈልገውና በምመርጠው መሪ ልተዳደር የሚል ነው፤›› የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ናቸው፡፡ ሊቀመንበሩ እንደተናገሩት፣ የሕዝቡ ጥያቄ እንደ አገር ሲታይ የሥልጣን ባለቤት ልሁን ነው፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በሚሰጠው ድምፅ አገሩን ማስተዳደር እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የኢዜማም እምነት ‹‹ምርጫ መደረግ አለበት›› የሚል ነው፡፡ ኢዜማ ብዙ ጊዜ ‹‹ቀጣዩ ምርጫ›› እያለ ያወራል እንጂ ቀኑ መቼ ይሁን ወይም በዚህ ቀን ይሁን የሚል ውስን ያለ ጊዜ አለማስቀመጡን ይናገራሉ፡፡ ቀጣዩ ምርጫ ቀደም ብለው ለአምስት ጊዜያት እንደተደረጉት ‹‹የይስሙላ›› ምርጫዎች ሳይሆን የተለየና የተሻለ ምርጫ መሆን እንዳለበት የኢዜማ እምነት መሆኑን አቶ የሺዋስ ይገልጻሉ፡፡ ቀደም ብለው የተደረጉ ምርጫዎች ከንጉሡ ወይም ከደርግ ሥልጣን ማስቀጠያ አካሄዶች የተለየ ዓላማ እንዳልነበራቸው የሚናገሩት አቶ የሺዋስ፣ ቀጣዩ ምርጫ ግን ከዚያ የተለየ መሆን አለበት ይላሉ፡፡  

ምርጫውን የተለየ ምርጫ ለማድረግ ደግሞ የተለየ ሥራ መሥራት እንዳለበት  በምሳሌ ይገልጻሉ፡፡ በአገር ውስጥ የምርጫው ባለቤት የሆነው ሕዝቡ በተረጋጋና በሰላም መኖር አለበት፡፡ አማራጮችን በደንብ ማየት በሚችልበት ሥነ ልቦና ላይ መሆን መቻል አለበት፡፡ ከዚህ በመቀጠልም ተቋማት በደንብና በሥርዓት መገንባት አለባቸው፡፡ ምርጫ ቦርድ፣ የፍትሕ ተቋማትና የፀጥታ ተቋማት ገለልተኛ መሆን አለባቸው፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ሥነ ምግባሩን በጠበቀና በኃላፊነት መሠራት አለበት፡፡ ምርጫ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ የተለፋበትን የምርጫ ሒደት ተግባራዊ የሚደረግበት እንጂ ‹‹አብረን እንኑር ወይስ እንለያይ?›› ብሎ የራስን ዕድል በራስ የሚወስንበት ውሳኔ ሕዝብ (ሪፈረንደም) አለመሆኑን አቶ የሺዋስ ተናግረዋል፡፡ ተቋማቱ ከሌሉ፣ ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ምርጫው ምርጫ ሊሆን እንደማይችልና የሚፈለገውንም ግብ ሊያመጣ እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡

አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)

ኢዜማ ምርጫ መደረግ አለበት ቢልም፣ ትኩረቱ ሽግግሩ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለሽግግሩ ከምርጫው የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጡ የገለጹት አቶ የሺዋስ፣ በ1953 ዓ.ም.፣ በ1967 ዓ.ም.፣ በ1983 ዓ.ም. እና በ1997 ዓ.ም. የዴሞክራሲ ሽግግሮች ተሞክረው መጨንገፋቸውን አስታውሰዋል፡፡ የሚቀጥለው ምርጫም ለታሪክ ብቻ ‹‹እንደዚህ ተደርጎ ነበር›› ተብሎ በመደርደሪያ ላይ መቀመጥ እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ግን ግራ የሚያጋባ ነገር መኖሩን የሚገልጹት አቶ የሺዋስ፣ እንኳን ምርጫ ለማካሄድ አገር እንደ አገር የመቀጠሉም ሁኔታ እንደሚያሠጋ ጠቁመዋል፡፡ ቀደም ብለው ለይስሙላ እንደተደረጉና ውድቀታቸውን ማውራት የተቻለ ቢሆንም፣ አሁን ግን አገር ያለችበት ሁኔታ ለማውራትም የሚያስችል እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ ነገር ግን የአገር ሰላም ተጠብቆና ሕዝቡ ነፃነቱ ተረጋግጦለት ቀጣዩ ምርጫ እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚሠፍንበት እንዲሆን ግን የኢዜማ ምኞትና ፍላጎት መሆኑን አቶ የሺዋስ ገልጸዋል፡፡ ቀጣዩ ምርጫ መቼም ይደረግ መቼ ካለፉት የይስሙላ ምርጫዎች የተሻለ መሆኑ ላይ ስምምነት መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

 

ምርጫ የሥልጣን ደም ሥር መቀጠያ?

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ቅቡልነቱን ማጣቱን የገለጹት አቶ የሺዋስ እንዳብራሩት፣ በ2007 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ ኢሕአዴግ መቶ በመቶ ማሸነፉን ባወጀ በስድስት ወራት ውስጥ ቅቡልነቱን አጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ሌሎች በርካታ ነገሮች ተቀያይረዋል፡፡ ይኼ የሆነው በአዋጅ፣ በሕግ ወይም በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት አይደለም፡፡ ከሕጉም ሆነ ከሕገ መንግሥቱ በላይ የሆነ ሕዝብ አለ፡፡ ሕዝብና አገርን ማስቀደም ከተቻለ ተወስነው በተቀመጡ ሕጎች ላይ (ሕገ መንግሥቱ ምርጫ በየአምስት ዓመት ይካሄዳል ብሎ መደንገጉን ልብ ይሏል) መወያየት የሚከለክል ምንም ምክንያት የለም፡፡ አምስት ጊዜ የተካሄዱ ምርጫዎች ሕጋዊ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ በሚመስል ሁኔታ የገዥውን መንግሥት ዘመን ያስረዘሙ ናቸው፡፡ ውጤቱን በየምርጫው እያሻሻለው መጥቶ በ2007 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ መቶ በመቶ ማሸነፉን ገልጿል፡፡ ይኼ ምርጫ እንኳን ለታሪክ ሊነገር ቀርቶ ለማውራትም ያሳፍራል፡፡ መጪው ምርጫ ግን እንዳለፉት ምርጫዎች እንዲሆን ሳይሆን፣ በትክክለኛው የምርጫ ሕግና ሒደት ተከናውኖ ሕዝብ ትክክለኛ መሪውን በካርድና ካርድ ብቻ እንዲሰይም መሆኑን አቶ የሺዋስ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የይስሙላ ምርጫ ማካሄድ እንደሌለበትና የሚታመን፣ ሙሉ በሙሉ ፅድት ያለ ምርጫ መካሄድ እንዳለበት የኢዜማ እምነት መሆኑንና ለዚያም እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢሕአዴግ ይለው እንደነበረው መቶ በመቶ ውጤት የሚመዘገብበት ሳይሆን ስድሳና ሰባ በመቶ አሸናፊነት የሚመዘገብበት ፅድት ያለ የምርጫ ሒደት እንዲኖር መሥራት ያስፈልጋል፡፡

የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር ሕገ መንግሥቱን እንደጠበቃ አድርገው የሚያወሩ ሰዎች ሕገ መንግሥቱን ሲጥሱ የኖሩ ናቸው፡፡ ምርጫ ይደረግ የሚሉ ሰዎች ምርጫ እንዳይኖር በአካባቢያቸው አመፅ የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

‹‹ምርጫው በዚህ ዓመት ካልተደረገ ወይም መደረግ አለበት የሚሉት ሕወሓትና ኦነግ ናቸው›› ብለዋል፡፡ ሕወሓትን ብንወስድ ሕዝቡ ሌላ አማራጭ እንዳይኖረው እያደረገ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ደርጅቶችም ሕዝቡ ተረጋግቶ የሚጠቅመውን ለመምረጥ የሚችልበትን ጊዜ ትርምስ በመፍጠር ግራ እያጋቡት ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫ ይደረግ እየተባለ ያለው አማራጭ ሳይኖር ነው፡፡ ሕዝብን ጭንቅ ውስጥ ከትቶና ‹‹አዳኝህ እኔ ብቻ ነኝ›› ብሎ ሕዝቡ ሳይወድ በግድ ድምፁን እንዲሰጥ በማድረግ ‹‹ተመርጫለሁ›› ለማለት ካልሆነ በስተቀር፤ ሕዝቡ ላቡንም ደሙንም የሰጠበት፣ ሕይወትም በገበረበት ዓይነት ወደ ዴሞክራሲ የሚሻገርበት ምርጫ ለማድረግ የተዘጋጁ እንደማይመስላቸው አቶ የሺዋስ ገልጸዋል፡፡ አሁን በአገሪቱ እያስቸገሩ ያሉት የኢሕአዴግ ስባሪዎች (ቀሪ በሥልጣን ላይ ያሉ) ናቸው እያስቸገሩ ያሉት፡፡ ከውጭ አገርም፣ ከበረሃም፣ ሆነ እዚህ የነበረው አገር ለማናጋት የሚያስችል አቅም ያለው አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በመንግሥት መዋቅር ካሉ ርዝራዦች ጋር ሲደመር ግን ችግር ይፈጥራል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንዳሉት፣ የኢሕአዴግንና የኢትዮጵያን ህልውና አያይዞ መንቀሳቀስ ትክክል አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ መቀጠል ካልቻለና ካልተስማማ፣ ለሌሎች ኃይሎች በምርጫ መንግሥት እንዲመሠርቱ ዕድል መፍጠር አለበት፡፡ እሱም ጠፍቶ አገርን ማጥፋት ተገቢ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ከመንግሥት ተቃራኒና ከአገር ተቃራኒ (Against the State and Against the Government) መሆን የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውንም የኢዜማ ሊቀመንበር ተናግረዋል፡፡ ከፕሬዚዳንቱ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ከሚኒስትሮች ተቃራኒ መቆም ይቻላል፡፡ መተቸት፣ መቃወምና ከሥልጣን ማውረድም ይቻላል፡፡ ከአገር በተቃራኒ መቆም ግን ክህደት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ስለሚመለከት አገሩን የማዳን ግዴታ አለበት፡፡ በየአካባቢውና ባለበት ቦታ ሁሉ በሚችለው አቅም ለአገሩ በመሥራት መጠበቅ እንዳለበትም አቶ የሺዋስ ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት አገርን ለመጠበቅና ሕዝቡን ለመጠበቅ ከሆነ የቆመው የማስተባበር ግዴታ አለበት፡፡ ሰላምን ማስከበር የመጀመርያ ሥራ መሆን አለበት፡፡ ቀጣዩ ምርጫ ኢዜማም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች እንዲካሄድ ይፈልጋሉ፡፡

ነገር ግን ጥይት እየተተኮሰና ሰው እየተገደለ እንዴት ይሆናል? ምርጫ ሒደት ነው፡፡ ምርጫው የሚደረግበት ዕለትና ካርድ የሚሰጥበት ብቻ አይደለም፡፡ ሒደቱ ማለትም ቅስቀሳው፣ ማስተማሩ፣ አማራጭ ማቅረቡ፣ ፕሮግራምን ይፋ አድርጎ ማስተዋወቁ፣ ወዘተ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ በአገሪቱ ላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሕግና ሥርዓት እንዲከበርና ሰላም እንዲሠፍን ማድረግ መሆኑን አቶ የሺዋስ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ይኼንን ማድረግ ካልቻለ በግልጽ ተናግሮ ሕዝብን ማስተባበርና ሰላሙን እንዲያስከብር ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ የመንግሥትም ኃላፊነት ነው፡፡ መንግሥት አንዱን እየለቀቀ ሌላውን መምታት ወይም ማስመታት ጦሱ ለራሱ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ከምርጫው በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ሰላም ማስፈን መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ መምህራን፣ የሕግ ባለሙያዎችና ሌሎችም በጣም ብዙ ሰላምና መረጋጋት ላይ ቢሠሩ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ አሉ፡፡ ነገር ግን መንግሥት ይኼንን ማስተባበር አለመቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ ከሩቅም ከቅርብም ጭምር ከኢትዮጵያ ጎን ለመቆም የሚፈልጉ አገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይኼንን ማስተባበርና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ አለበት፡፡ ኢዜማ ቀጣዩ ምርጫ መደረግ እንዳለበት እምነቱ ቢሆንም፣ ከፊት ለፊቱ የተገተረውን ተራራ የሚህል እውነት መካድ እንደሌለበት አቶ የሺዋስ ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምንም ዓይነት ሕግና መርህ ቢቀመጥ ፖለቲካን ከነባራዊ ሁኔታው በላይ የሚመራው እንደሌለ ጠቁመው፣ እሱ ላይ ትኩረት ማድረግ ግድ እንደሚል ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ሌትም ቀንም በርብርብ በመሥራት በሕዝቡ ላይ ሰላም እንዲሠፍን በማድረግና ተቋማት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ለቀጣዩ ምርጫ ካደረሰ፣ በሰው ሀብትም፣ በዕውቀትም ሆነ በሀብት እንደ ኢዜማ የተዘጋጀ ፓርቲ ይኖራል የሚል እምነት እንደሌላቸው አቶ የሺዋስ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡ ኢዜማ ሲመሠረት ጀምሮ በምርጫ ወረዳዎች ላይ መሥራቱን፣ 400 ወረዳዎች ላይ ዕጩ፣ ታዛቢና የምርጫ ዘመቻ ማድረግ ምንም ችግር እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ ኢዜማ ከ20 በላይ የፖሊሲ ሰነዶችን ማዘጋጀቱን በውጭ አገር ከ72 ከተሞች በላይ የድጋፍ ማኅበሮችን ማዋቀሩንና በአጠቃላይ በሠለጠነ መንገድ ፖለቲካ ሊራመድበት በሚችል አኳኋን መዘጋጀቱንም አሳውቀዋል፡፡ ግን ሜዳው የኢዜማ ብቻ አለመሆኑን ጠቁመው፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና አስፈጻሚ ተቋማት መኖራቸውንና ከሁሉም በላይ ግን ሕዝብና አገር መኖሩን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ አንድ ሆነውና ተስማምተው መሄድ አለባቸው እንጂ፣ እንደ ኢዜማ ‹‹አንደኛው ይካሄድ ሌላኛው ይዘግይ›› እየተባባሉ ምርጫው መካሄድ የለበትም የሚል እምነት እንደሌለው አክለዋል፡፡

“የሽግግር” ሐሳቦች

“ሽግግር ሲባል እስከ መቼ ነው ሽግግር የሚባለው? ለዓመታት፣ ለወራት ወይስ እስከ መቼ?” በግልጽና በስምምነት መታወቅ እንዳለበት አቶ የሺዋስ ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሠሩትን፣ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም የሚሠራውንና የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የሚያደርጉትን በዝርዝር አስቀምጦ ሥራውን መጨረስ ቢቻል ምርጫው በቀኑም ቢደረግ ኢዜማ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ግን አይመስለኝም›› የሚለት አቶ የሺዋስ እንደገለጹት፣ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ እንድትገባና ሁሉም ነገር ሥርዓት ይዞ እንዳይሄድ እያደረጉ ያሉት ‹‹ምርጫው መተላለፍ የለበትም መካሄድ አለበት›› የሚሉት አካላት ናቸው፡፡ ኢዜማ ነገሩ ሁሉ ተቃራኒ ሆኖበታል፡፡ ሁሉም ወደ ቀልቡ ተመልሶ ሌት ተቀን ከሠራና ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ኢዜማ አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ ዝግጁ መሆኑን አቶ የሺዋስ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡ በፓርቲዎች ድክመት ምክንያት ምርጫ መራዘም የለበትም፡፡ የተዘጋጀ ፓርቲ በምርጫው ይሳተፋል፡፡ ያልተዘጋጀው በሚቀጥለው ይሳተፋል፡፡ ምርጫ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት በየአምስት ዓመቱ ይካሄዳል፡፡ በመሆኑም ያልተዘጋጀ ፓርቲ ካለ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ተዘጋጅቶ ይሳተፋል፡፡ ሽግግር ግን በአምስት ወይም በአራት ዓመት አይባልም፡፡ በየ15 ዓመታትና ከዚያም ባለፈ ጊዜ የሚመጣ ወይም የሚከሰት ነው፡፡ ምን ያህል ደም አፋሳሽ ሆኖ እየመጣ እንደሆነ እያየነው ያለ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ትኩረታቸው ሽግግሩ ላይ እንዲሆን ኢዜማ እየሠራ መሆኑን አቶ የሺዋስ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የትኛውም ዘመን ቢጠራ ይኼንን ያህል የቆየችው በአምባገነናዊ ሥርዓት መሆኑን የሚናገሩት አቶ የሺዋስ፣ ሕወሓትም ደርግም ሆነ ንጉሣውያኑ አምባገነኖች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ በራሱ ፍላጎት የሚመራውን መርጦ የተዳደረበት ጊዜ የለም፡፡ እንደ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ሳይሆን እንደ አፍሪካ አገሮች እንኳን መሆን እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ ሥልጣን በጠብመንጃ ሳይሆን በካርድ ወደ ሕዝባዊ ሥልጣን መሸጋገር የሚቻልበትን ሥርዓት የሽግግር ሥርዓት እንደሚሉትም የኢዜማ ሊቀመንበር አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አሁን መታየት ያለበት ይኼንን ሽግግር ማድረግ የሚችሉ መሆናቸውን እንጂ የፓርቲዎች መቻል አለመቻል ጉዳይ አይደለም፡፡ ሕዝቡ አሁን በጣም ንቁ መሆኑንና እያንዳንዱ ነገር በአንድ ወይም በሁለት ነገር ሊሰማ የሚችል ቢሆንም፣ ችግሩ ግን ‹‹አንዳንድ  ኃይሎች እየሠሩ ያሉት በምርጫ ሊወዳደሩ ነው? በፍፁም አይደለም፡፡ እኔ እምልህን ብቻ ስማ፡፡ አንተ ስለራስህ አታውቅም፤›› በማለት የማይሆን ነገር ሲሠሩ እየታዩ መሆኑን አቶ የሺዋስ ጠቁመዋል፡፡ ፕሮግራሞቻቸውን ለማስተዋወቅ ከበቂ በላይ ጊዜ መኖሩንና ዋናው የሚያሳስበው የተቋማት ጉዳይ መሆኑንም አክለዋል፡፡ መታሰብ ያለበት ነገር ለዘመናት መከራ፣ ጭንቅ፣ ግድያ፣ ስደት፣ መፈናቀልና ወዘተ ሲያይ የከረመው ሕዝብ ግን አሁን ደኅንነት እንደማይሰማውም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ነፃነት ተሰምቶትና ሳይታፈን የፈለገውን መምረጥ በሚያስችለው ሁኔታ ላይ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ጊዜም ይሁን በማንኛውም ግርግር ጊዜ ውስጥ ሌባውንና ደህናውን መለየት አይቻልም፡፡ እንኳን የተሻለ ሐሳብ የሚያቀርበውን ቀርቶ ማን እንደሚጎዳና ማን እንደሚጠቅም ማወቅ አይቻልም፡፡ የገበያ ግርግር ውስጥ በግና ቀበሮን መለየት በማይቻልበት ሁኔታ እንዴትም ብሎ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል አቶ የሺዋስ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሰላም ማስከበር አለበት፡፡ ሌላውም ግርግሩንና ሁከቱን ትቶ ለተቋማት ነፃነትና ለራሱም ሆነ ለሌላ የሚያስፈልገውን መሥራት እንዳለበት አክለዋል፡፡ ይኼ ከተሠራ ፓርቲዎች ራሳቸውን የማዘጋጀት ጉዳይ የራሳቸው የቤት ሥራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የኢሕአዴግ መክሰምና ወደ አንድ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲነት መምጣትን በሚመለከት አቶ የሺዋስ እንደገለጹት፣ በአገር ላይ የሚመጣው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ቢዋሃዱ አጠቃላይ ለፖለቲካው ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡ ውህደት ግን እንደሚወራው ቀላል አይደለም፡፡ እነሱ ብዙ ውህደቶችን ሲያፈርሱ ኖረዋል፡፡ ወደ ራሳቸው ሲመጡ ያንን ሲሠሩት የነበረውንና ተሸክመውት የነበረውን ኃጢአት ያገኙት ይመስላል፡፡ ሕወሓት የሁሉም ድርጅቶች ፈጣሪ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አሁን ሁሉም አጋር ድርጅቶች የሚባሉትም ‹‹እኩል እንሁን›› ሲሉ፣ እንዴት ‹‹እኔ ከሠራኋቸው ጋር እኩል እሆናለሁ?›› ማለት ጀምሯል፡፡ ከነበሩበት ሙቀት መውጣት የማይፈልጉ ቡድኖች ቢኖሩም፣ እንደ ድርጅት መቀጠል ስለማይችሉ፣ መዋሃዱ ይጠቅማቸዋል፡፡ የመዋሃዱ ጥቅም አንዱ የዘር መጓተቱን እንደሚያስቀርም አቶ የሺዋስ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ፖለቲካውን እያጦዙት ያሉት ‹‹እከሌ በእናቱ የዚህ ዘር ነው፣ እከሌ በአባቱ የዚህ ዘር ነው፤›› የሚለው እንዳይታወቅ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ልክ እንደ ሒትለር፡፡ ሒትለር ጀርመናዊ ስላልሆነ ጀርመናዊ መስሎ ለመታየት ብዙ ይለፈልፍ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ ልክ እንደዚህ ሁሉ ‹‹‹የትኛው ነው የበለጠ ኦሮሞ፣ የትኛው ነው አማራ፣ የትኛው ነው የበለጠ ትግራይ፣ የትኛው ነው ሲዳማ፣ ወዘተ …›› እየተባባሉ የጦዘ ፉክክር እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ለመገላገልና ኢሕአዴግ ያረጀ ድርጅት በመሆኑም ካልተዋሃደ፣ ራሱን ካልቀየረ ስብርብሩ እንደሚወጣ ተንብየዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በደም፣ በገንዘብና በተለያየ ነገር የተነካካ ቡድን ያለበት መሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አሁን በመሪነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችም እንዴት በኢሕአዴግ ውስጥ እንደበቀሉ ግርምትም ፈጥሮባቸዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በማለት ማንም ምንም መናገር በማይችልበትና ሁሉ ሚስጥር በሆነበት ድርጅት ውስጥ መሆኑን ሲያስቡ የአሁኑ መሪዎች መውጣት አስገርሟቸዋል፡፡ ይኼንን ጨቋኝ ድርጅት ‹‹አይዋሃድ›› ማለት የጤንነት ባለመሆኑ ለራሳቸው ሲሉና የእነሱ ችግርም ከአገር ጋር የተጣበቀ በመሆኑ ተነጋግረው መፍታት እንዳለባቸው ወይም ሙሉ በሙሉ መልቀቅ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡ ሕዝብን እርስ በርስ እንዲባላ ማድረግ ግን ከተጠያቂነት እንደማያድንም አቶ የሺዋስ አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን ያለና በድህነት፣ በጦርነት፣ በጋብቻ፣ በባህልና በተለያዩ ነገሮች ተጋምዶና ተጣብቆ የኖረ ሕዝብ በመሆኑ አንዳንድ ጽንፈኛ እንደሚመስለው ‹‹ነጠላዬን አቀብዪኝ›› ተብሎ የሚሄድበት ሁኔታ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ እየታየ ያለው ደም መቀባባት መቀጠል እንደሌለበትና እናቶች እንደገና እንዲያለቅሱ ማድረግ ተገቢ ባለመሆኑ መጪው ምርጫ እነዚህ ሁኔታዎች ሳይፈቱ መካሄድ እንደሌለበት አቶ የሺዋስ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡    

 

“እባብ ያየ በልጥ በረየ”

ምርጫ ሁሉም የሚፈልገው ቢሆንም በኢሕአዴግ አገዛዝ እስካሁን የተደረጉትን አምስት ዓይነት ምርጫ ግን ማንም እንደማይፈልገው የሚናገሩት ደግሞ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ፓርቲ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ቆንስላ አባል አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ሕወሓት/ኢሕአዴግ በበላይነትና በአምባገነንነት አገሩን ሲገዛ የተካሄዱ ምርጫዎች ዴሞክራሲዊና ፍትሐዊ እንዳልነበሩ ይታወቃል፡፡ ብዙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ኢዲኅ፣ መድኅን፣ ኅብረ ሕዝብና ሌሎችም ድርጅቶች ተገልለው መሳተፍ ካለመቻላቸውም ሌላ በስደት ላይ ነበሩ፡፡ ትዴትን ጨምሮ ከስደት ሲመጡ ፣ ሰላም ስለሚኖር በምርጫ ለመወዳደር መሆኑን ዶ/ር አረጋዊ ተናግረዋል፡፡ ሲጀመር ማለትም በ2010 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሰላማዊ ሒደት ያለ ቢመስልም፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን እንኳን ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ ቀርቶ አገር እንደ አገር ለመቀጠል አጣብቂኝ ውስጥ የተገባበት ሁኔታ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የሐሳብ ነፃነት ካለ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች መንቀሳቀስ ይቻላል፡፡ አሁን ላይ በሌሎቹ አካባቢዎች በተወሰነ ደረጃ መንቀሳቀስ ቢቻልም፣ በትግራይ ግን እንደማይቻል ይታወቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሕወሓት ከሥልጣን ከተገፋ ጀምሮ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የነበሩ ባለሥልጣናት በሙሉ ትግራይ ሄደው በመመሸግ የድሮውን የአምባገነን አካሄድ እያራመዱ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የትግራይ ሕዝብን አግኝቶ አማራጭ እንዳለው ለመቀስቀስና የሚፈልገውን መሪ በካርድ ብቻ እንዲመርጥ ማድረግ አይቻልም፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኖ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡ ትርጉም የለሽም መሆኑንም ዶ/ር አረጋዊ ተናግረዋል፡፡ በሌላው አብዛኛው ሊባል በሚቻል ሁኔታ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ በዚህ ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ  ሊሆን አይችልም፡፡ ምርጫ ሲካሄድ መሟላት ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመው፣ የቤትና ሕዝብ ቆጠራ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት በየአሥር ዓመት የቤትና ሕዝብ ቆጠራ መካሄድ እንዳለበት አስታውሰው፣ አሁን ምርጫ መካሄድ አለበት በሚባልበት ወቅት ቆጠራ መካሄድ የነበረበት ጊዜ ማለፉንና የሕዝቡም ብዛት አይታወቅም ብለዋል፡፡ ነፃና ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊም ምርጫ ለማካሄድ ዋናውና አንዱ ተግዳሮት መሆኑንም አክለዋል፡፡ በአዲስ አበባ አካባቢ መሟላት ቢቻልም (ከተቻለ)፣ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ግን ማሟላት እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ይኼ ሁሉ መስተካከል ስላለበት፣ እንደ ትዴት ምርጫው መካሄድ እንደሌለበት መወሰናቸውን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ከምርጫ ቦርድ ጋር በመወያየት መሻሻል ያለባቸውና መሰረዝ የሚኖርባቸው የምርጫ ሕጎችም እንዳሉ በመግለጽ ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በድሮው የሚቀጥል እንጂ፣ ተፎካካሪ ድርጅቶቹ ያቀረቡትን ሐሳብ የተቀበለው እንደማይመስልም ተናግረዋል፡፡ እነዚህና በመሳሰሉት ነጥቦች ቀጣዩ ምርጫ ነፃ፣ ተዓማኒ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል የሚል እምነት ስለሌላቸው መደረግ እንደሌለበት አቤቱታቸውን ለሚመለከተው አካል ሁሉ እያቀረቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ምርጫው መቼ መካሄድ እንዳለበት መወሰን ወይም አቅጣጫ ማስቀመጥ ሳይሆን፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓማኒና ነፃ ምርጫ እንዲካሄድ የሚያስችልን ሒደት መፍጠር መሆኑንም ዶ/ር አረጋዊ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ሁኔታው አሁን ከተፈጠረም በደስታ ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል፡፡ ከዓመት በኋላም ሁኔታው የሚፈጠር ከሆነ በዚያን ጊዜ ይካሄዳል፡፡ አንድ ነገር መገንዘብ ያለብን፣ የትዴት እምነት የይስሙላ ምርጫ ማካሄድ ሳይሆን የእውነት ምርጫ ማድረግ መሆኑን ዶ/ር አረጋዊ ገልጸዋል፡፡ ያለፉት ምርጫዎች ኢሕአዴግ መቶ በመቶ ማሸነፉን ሲገልጽበት እንደነበረው ዓይነት የይስሙላ ምርጫ ወይም ቴአትር መደረግ እንደሌለበት የእሳቸውም የድርጅታቸው እምነት አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሁሉም አካላት መንግሥት፣ ምርጫ ቦርድና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በትጋት ሠርተው የወሰደውን ያህል ጊዜ ወስዶ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መካሄድ እንዳለበት አክለዋል፡፡

 

“ከምርጫው በፊት ድምፃችን ይሰማ”

አዲስ በፀደቀው የምርጫ ሕግ ላይ ባሉ ድንጋጌዎች (አንቀጾች) ላይ ያቀረቧቸው መቃወሚያዎች ተቀባይነት ቢያገኙና ቢሻሻሉ ምርጫው መካሄድ እንደሚችልም የጠቆሙት ዶ/ር አረጋዊ፣ ፓርቲዎች በፈለጉበት ክልል እንደልባቸው ገብተው መውጣት የሚችሉበትና መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር ምርጫው መካሄድ እንደሚችልም አክለዋል፡፡ ሕዝቡን የሚያደራጁበት፣ የሚያስተምሩበትና የሚቀሰቅሱበት ጊዜ ቢኖራቸው ምርጫው በተፈለገበት ጊዜ መካሄድ እንደሚችልም አክለዋል፡፡ በምርጫ ሕጉ ላይ ከ33 አንቀጾች በላይ መቀየር አለባቸው የሚሉት፣ ምርጫ ተመጣጣኝ ውክልናን በሚመለከት ፓርቲዎች ባገኙት ድምፅ መጠን የፓርላማ ድርሻ ማግኘት አለባቸው የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ 51 ለ49 አንድ ፓርቲ ቢሸነፍ፣ 51 መቀመጫ ያሸነፈው ብቻ ጠቅልሎ ፓርላማውን መያዝ የለበትም፣ 49ኙ ያገኘው ውጤት ባዶ መሆን የለበትም፡፡ የ49ኙም ድምፅ መሰማት አለበት የሚል አቋም እንዳላቸውም  ገልጸዋል፡፡ ሌላው ለክልል ፓርቲዎች 4,000 ተመዝጋቢዎች የሚለውን ምርጫ ቦርድ በራሱ ስሌት ያቀረበው ተገቢ አለመሆኑን፣ የፖለቲካ ድርጅቶች መቃወሚያ ማቅረባቸውንም ዶ/ር አረጋዊ ሲገልጹ የቁጥሩ ጉዳይ ችግር ባይፈጥርም፣ ይኼንን ቁጥር ወይም ከዚያ በላይ ለማሟላት መጀመርያ በሰላም የመንቀሳቀሱ ዕድል ይስተካከል ብለዋል፡፡ ይኼ ባልሠፈነበት አካባቢ የተጠቀሰውን ቁጥር ማስቀመጥ ተገቢ አለመሆኑንም የፖለቲካ ድርጅቶቹ ገልጸዋል፡፡ ሌሎች መስተካከል ያለባቸው ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ለሁሉም በሚጠቅም ሁኔታ ማቅረባቸውን ዶ/ር አረጋዊ አስረድተዋል፡፡ ተቃውሞ ያቀረቡባቸው የምርጫ አንቀጾች ከተስተካከሉ፣ ሰላም ከወረደና በፈለጉበት ቦታ መንቀሳቀስ ከቻሉ፤ ምርጫው ቢካሄድ ደስተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የቀሩት አምስት ወራት አጭር ቢመስልም፣ ከላይ የተጠቀሱት ዕድሎች ከተመቻቹ ግን ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል፡፡ ብዙ አባላትና ብዙ የሚደግፋቸው ሕዝብ ስላለ በአጭር ጊዜ ቅስቀሳና ፕሮግራም በማስተዋወቅ ምርጫውን ማካሄድ እንደሚቻል አክለዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለበት ሁኔታ ጽሕፈት ቤት እንኳን መክፈት አለመቻሉን በትግራይ የገጠማቸውን ኢ-ዴሞክራሲ የሆነ ድርጊት የሕወሓት ካድሬዎች በትዴት ላይ የፈጸሙትን በምሳሌነት በመጥቀስ ዶ/ር አረጋዊ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጦርነት አለ፡፡ ተከበናል፡፡ በሰሜን ሻዕቢያ፣ በደቡብ ምዕራብ አማራ፣ በምሥራቅ አፋር፣ ወዘተ… ›› እያሉ ሕዝቡን የጦርነት ሥነ ልቦና እንዲያድርበት አድርገው ችግር እየፈጠሩበት ባሉበት ሁኔታ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ መንቀሳቀስ ከባድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይኼንን አስተካክሎ ምርጫ ማካሄድ ያለው ዕድል በጣም ጠባብ በመሆኑ፣ አሁን ምርጫ ለማካሄድ ያለው ዕድል በጣም ጠባብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምርጫው ተካሄደም አልተካሄደ ትዴት ከትግራይ ክልል ውጪ ያሉ የትግራይ ተወላጆችንና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ለማግኘት፣ ለማደራጀትና ለማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ዶ/ር አረጋዊ ተናግረዋል፡፡ ሰላምና ፀጥታ እንዲሠፍን፣ ደጋፊዎቻቸውን ከመምከር ባለፈ በተግባር ያደረጉት ነገር እንደሌለ የሚናገሩት ዶ/ር አረጋዊ፣ በዋናነት በዚህ ዙሪያ መሥራት ያለባቸውና ኃላፊነቱም የመንግሥትና ምርጫ ቦርድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር፣ ለሰላም ተግዳሮቶች የሆኑ ነገሮች እንዲፈቱና ግጭቶች እንዳይኖሩ ፈጥኖ መንቀሳቀስና ማስተካከል የፌዴራል ሥርዓቱ ቢሆንም፣ ተባብረው ለመሥራት ግን ፈቃደኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በተደጋጋሚ ከገዥው ፓርቲ ጋር ጭምር ተሰብስበው፣ ለአገርና ሕዝብ ቅድሚያ ለመስጠትና በአገር ላይ ሰላም እንዲሰፍን ተስማምተው በመፈራረም ጭምር የቻሉትን ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተው እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡ አሁንም በጽሑፎቻቸውና በመገናኛ ብዙኃን ጭምር ለመርዳት ጥሪ እያደረጉ መሆኑንና ሕዝቡ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ መግባት እንደሌለበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችንም ራሳቸው መፍታት እንዳለባቸው ጭምር እያስተማሩና እየመከሩ መሆኑንም አክለዋል፡፡ አገርና ሕዝብን ያስቀደመ ሥራ ለመሥራት ገዥው ፓርቲ ጭምር ስለተፈራረሙ እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመንግሥት ላይ ጫና ያደርጉ እንደነበር የጠቆሙት ዶ/ር አረጋዊ፣ አሁን ጊዜው የፖለቲካ ፓርቲዎች እሽቅድምድም የሚያደርጉበት ሰዓት ሳይሆን፣ በአገሪቱ ሰላም መሥፈንና የተረጋጋ ሁኔታ እንዲኖር ተቋማትን መዘርጋት፣ ማለትም የሕግ የበላይነት፣ የፀጥታው ክፍል መጠናከርና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን መስመር የሚያሲይዙ ተቋማት መፍጠር እንዳለባቸው ድርጅቶቹ ሲያሳስቡ መቆየታቸውንም የገለጹት ዶ/ር አረጋዊ፣ መንግሥት ምርጫው እንደሚካሄድ እየተናገረ ቢሆንም፣ የሚደረገው ምርጫ ግን ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡ ባልተረጋጋ ሁኔታና ሰላም በሌለበት ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መወዳደር ባልቻለበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ትርጉም የለሽ ወይም ለይስሙላ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በምርጫ ምክንያት አገር ወደ ቀውስ እንድትሄድ ትዴትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አይፈልጉም፡፡ ምርጫው ባይሆንላቸው እንኳን ግጭት እንዳይፈጠር ተግተው እንደሚሠሩ፤ ሰላም እንዲመጣ እየጣሩ መሆኑንና እንደሚቀጥሉበትም ተናግረዋል፡፡ ግን ምርጫው ከተካሄደ ቀውስ አይፈጠርም ማለት አይቻልም፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ያልተስማሙበትና ያልፈለጉት ምርጫ ከተካሄደ ተቃውሞ መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ከትዴት ጀምሮ ተቃውሞውን በሰላማዊ ሠልፍ ለመግለጽ ዝግጁ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ ወዴት እንደሚያመራ ግን ወደፊት የሚታይ መሆኑን ዶ/ር አረጋዊ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ምርጫው መካሄድ አለበት ብሎ በአቋሙ ከቀጠለ ትዴትም መንቀሳቀስ ባይችልም (በተለይ በትግራይ ክልል) ቅስቀሳ በመቀጠል ሕዝቡን ባላደራጀበት ሁኔታ ቢሆንም ‹‹በምርጫው እንሳተፍ ወይስ አንሳተፍ የሚለው በመጨረሻ ላይ የምንወስንበት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡  

ጎርባጣ የምርጫ መንገዶች

እንደ ሌሎቹ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ አገራዊ ምርጫ 2012 ዓ.ም. መደረግ የለበትም ብሎ የሚከራከረው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ነው፡፡ የድርጅቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ እንደገለጹት፣ አገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ሊያሰኝ በሚችል ደረጃ ችግሮች አሉ፡፡ ሰሜን አካባቢ የአዴፓና ሕወሓት ፍጥጫ እስካሁን ሳይፈታ የሕዝብ ሥጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች ሕዝቡን የሚወክሉ ባይሆንም፣ አብረው የኖሩና የወለዱ የተጋመዱም ሕዝቦች እንዲለያዩ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ጥቂት ባለሥልጣኖች እያደረጉት ያለው የፖለቲካ ጥቅም ሩጫ የፈጠረው ችግር መጀመርያ መፈታት አለበት፡፡ በኦሮሚያ (ኦዴፓ) እና ሶማሌ ክልሎች መካከል ያለው ችግርም ሳር ለብሶ የተቀመጠ ነው፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ አካባቢ ያልተፈታ ችግር አለ፡፡ በወለጋ ውስጥ ያለውን ገጽታ በሚመለከት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት፣ ‹‹ሳንወድ በግድ የገባንበት ጦርነት ነው፤›› ማለታቸውን ያስታወሱት አቶ ሙሉጌታ፣ አገሪቱ ውስጥ ያለው ችግር ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነና አገሪቱ የጥፋት አፋፍ ላይ መደረሱን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በምሥራቅም በኩል ተመሳሳይ ችግሮች መኖራቸውንና በቅርቡ ደግሞ በአፋርና በሶማሌ መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች፤ ውኃ በማይቋጥሩ ምክንያቶች ዜጎች እየሞቱ ባለበት ሁኔታና እነዚህን ሁሉ ችግሮች ሳይፈቱ፣ እንዲሁም በርካታ የጥፋት ኃይሎች እጆች በትጋት እየሠሩበት ባለበት ሁኔታና አገር ባልተረጋጋበት ወደ ምርጫ መግባት፤ ለበለጠ ትርምስ ያጋልጣል፡፡ ምርጫ መደረግ የለበትም ማለት፣ አያስፈልግም ወይም ወደ ምርጫ አለመግባት ሳይሆን፣ መኢአድ ከሃያ ዓመታት በላይ የሠራውና የታገለው፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ፣ ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲኖር መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ይናገራሉ፡፡ አሁን የምትታየውን የመወዳደሪያ ምኅዳር ጭራሹን ለማጥፋት የሚሯሯጡ አካላት ባሉበት ወደ ምርጫ መግባት አስፈላጊ አይደለም፡፡ አገር በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና ስለምርጫ ማሰብ፣ ወይም ‹‹ምርጫ መደረግ አለበት የሚሉት ወገኖች ምን አስበው ነው? ይህቺን አገር ወዴት ሊወስዷት አስበው ነው? መጀመርያ የምንቆምበት ምድር አለች ወይ?›› የሚለውን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ሕግጋትም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አሳማኝ ነገሮች በተፈጠሩ ጊዜ ማለትም ችግር በተከሰተ ጊዜ ምርጫ እንደሚራዘም መደንገጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ለአብነት ያህል መጥቀስ ቢያስፈልግ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ሁለት ጊዜ መራዘሙን ጠቁመዋል፡፡ መኢአድ ምርጫው መካሄድ የለበትም ሲል ግን፣ ፓርቲው በምርጫው አይሳተፍም ማለት እንዳልሆነ አስገንዝበው፣ መጀመርያ ችግሩ ይፈታና ምርጫው ቀጥሎ ይደረግ የሚል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ፓርቲዎቹ የተመሠረቱትና ወደ ፊትም የሚመሠረቱት ዓላማቸው ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተደርጎ ሥርዓቱን በካርድ ቀይሮ መንግሥት መሆን እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡ ዓላማውም አገርን ማስተዳደር ሕዝብ መምራት ነው፡፡ ነገር ግን በአገር ላይ የተደቀነው ቀውስና ሁከት መቆምና መስተካከል ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚለው የመኢአድ ፍላጎት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሥልጣን የመያዝ ሥርዓት የመቀየርና ገዥ ፓርቲ የመሆን ህልምና ዕቅድ ከአገር በላይ አለመሆኑን አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡ ሌላው በቅርቡ የፀደቀው የምርጫ አዋጅም እንከን ብዙ መሆኑም በመግለጽ የትዴት ሊቀመንበር የዶ/ር አረጋዊ ሐሳብን ተጋርተዋል፡፡ አዋጁ በችግር የተመላ በመሆኑ ፍትሐዊ ምርጫ እንዳይደረግ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ምርጫ ቦርድም ቢሆን ገና ዳዴ እያለ ያለ ገለልተኝነቱም ያልተረጋገጠና ገንዘብና ጡንቻ ያለው ወደፈለገበት እያወዛወዘው ያለ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በምርጫ ቦርድ በኩል በአዲስ አበባም ይሁን በክልል ያሉ አጠቃላይ ምርጫ አስፈጻሚዎችም ባሉበት የቀጠሉ ከመሆኑ አንፃር ምርጫን ከላይ ያሉ ሰዎች ሳይሆኑ የበታች አስፈጻሚዎች መሆናቸው ካለፉት ምርጫዎች የበለጠ አረጋጋጭ ነገር ስለሌለ፤ ይኼ ሁሉ ባልተስተካከለበት ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት ለይስሙላ ከመሆን ያለፈ ጥቅም ስለሌለው በዚህ ወቅት መደረግ እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

“ለመንግሥት አስተዳደር ወይስ ለመንግሥተ ሰማያት?”

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በቅርቡ በፓርላማ ተገኝተው ስለምርጫ ከተናገሩት ውስጥ ሁለት ነገር እንዳስደነገጣቸው አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ ከሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በቁጥር ደረጃ አስቀምጠው ‹‹ሰው ሊሞት ይችላል፡፡ ምርጫው ግን ይደረጋል፤›› ማለታቸው መጀመርያ ያስደነገጣቸው ነገር ነው፡፡ ‹‹ሰው ከሞተ ምርጫ የሚደረገው ለማን ነው? መሪ ሆነውና በመንግሥት ደረጃ ሰው እንደሚሞት መረጃ እያላቸው፣ ችግሮች እንዳሉ መረጃው እያላቸውና እያወቁ እንደዚያ ማለታቸው ለምንድነው? በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ምርጫ እኮ መንግሥተ ሰማያት ማስገቢያ አይደለም ወይም የመጨረሻው ነገር አይደለም፤›› የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ምርጫን ሊያመጣ የሚችለው ትግል ወይም ዴሞክራሲ ነው እንጂ፣ ምርጫ በራሱ ዴሞክራሲን ሊያመጣ እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ የአገዛዝ ሥርዓቱ የተሸነፈበትና የተንበረከከበት የምርጫ ሒደትን ጨምሮ የተደረጉ አምስት ምርጫዎችንና የቅርቡ የ2007 ዓ.ም. መቶ በመቶ ውጤት የተመዘገበበት ምርጫ የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡ ፈጥሮ የሚኖር እግዚአብሔር እንኳን መቶ በመቶ ተመርጧል ማለት በማይቻልበት ማለትም፣ ‹‹የሚያምነው አለ፣ የሚያምነው፣ የሚከተለው፣ የማይከተለው፣ የሚያማርረው፣ የሚያመሠግነው፣ ወዘተ አለ፤›› በሚባልበት ሁኔታ ኢሕአዴግ ግን መቶ በመቶ እንደተመረጠ መናገሩን ጠቁመዋል፡፡ ይኼንን ያየች አገር ችግሮቿን ሳታስተካክል ሰው ይሞታል እየተባለ ምርጫ ይደረግ ማለት ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድጋሚ ያስደነገጧቸው በፓርላማ ተገኝተው፣ ‹‹ችግሮች አሉ፡፡ ምርጫው ግን ይካሄዳል፤›› ማለታቸው መሆኑን ነው፡፡ ችግሮችን መፍታት ነው መቅደም ያለበት፣ ወይስ ሰው እንደሚሞትና ችግር እንዳለ እያወቁ ምርጫ ማካሄድ? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ምርጫ ፓርላማ የሚገባበት፣ ሥርዓት የሚለወጥበት፣ መንግሥት መሆን የሚቻልበት ነው ምርጫ፡፡ ግን በመሪ ደረጃ ችግር ይደርሳል እየተባለ ምርጫ መካሄዱ የመጨረሻ ምርጫ መሆን የለበትም የሚል አቋም የመኢአድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በምርጫ ምክንያት አንድ ሰውስ ቢሆን ለምን ይሞታል? ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ሙሉጌታ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱም አነጋገራቸው እንዳስደነገጣቸው ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት ደረጃ፣ ‹‹ሰው ሊሞት ይችላል ነገር ግን ምርጫው ይካሄዳል፤›› ማለት ስህተትና ፍፁም ትክክል አለመሆኑን አክለዋል፡፡ ሰው እንዳይሞት መጀመርያ መነጋገርና ችግር ካለ መፍታት ይቀድማል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም መንግሥትም፣ ‹‹ችግር አለ፤›› እያሉ ወደ ምርጫ መግባት ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ያለውን ችግር ሳይፈቱ ወደ ተጨማሪ ችግር ውስጥ መግባት ሌላ የማይፈታ ችግር መፍጠር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከምርጫ በፊት መግባባት ላይ መድረስ መጪውን ምርጫና ውጤቱን ጥሩ ስለሚያደርገው፣ በቅድሚያ መስማማት ላይ መሠራት ብዙ አላስፈላጊ ጥፋቶችን ማስቀረት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም በየዘሩ ተከፋፍሎ የሚፈልግውን ነገር ማራመድ እንጂ፣ ሰከን ብሎና ጊዜ ወስዶ በስምምነት ላይ የሚሠራ ስለሌለ፣ ቅድመ ምርጫ የሚባለው ሁሉም ‹‹ያገባኛል›› የሚል ሁሉ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸው አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡ ተዓማኒና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሂዶ የፈለገው የፖለቲካ ድርጅት ቢያሸንፍ ሁሉም ተሸናፊ ተወዳዳሪዎች ‹‹እንኳን ደስ አለህ›› ብለው የደስታ መግለጫ ማውጣት ይችላሉ፡፡ ይኼ የሚመጣው ግን አሁን በተያዘው ‹‹በአመፅ ጉተታ›› አለመሆኑን አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡ እንደ መኢአድ ምርጫው መቼና እንዴት መደረግ እንዳለበት ለመናገር መጀመርያ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ‹‹ችግር አለ›› እያሉ ስለሆነ፣ መጀመርያ በችግሮቹ ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

“የብሔራዊ ዕርቅ” ፍላጎቶች

መኢአድ ምርጫው አሁን መካሄድ የለበትም ሲል፣ አማራጭ ሐሳብ እንዳለው የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ፣ ‹‹እንዴትና በምን ሁኔታ ምርጫው ይሸጋገር?›› ሲባሉ ሊያቀርቡ እንደሚችሉም አውስተዋል፡፡ ከምርጫ በፊት መነጋገር እንዳለበት መኢአድ ሲናገር ያለ ምክንያት ሳይሆን ምክንያቶችን በግልጽ ማስቀመጡን አክለዋል፡፡ መጀመርያ ከምርጫ በፊት አገራዊ ዕርቅ መደረግ እንዳለበትና መኢአድ በቅድሚያ የሚያሳስበው የኢትዮጵያ አንድነት ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ መኢአድ አገራዊ ዕርቅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ሲል ምክንያቱ ደግሞ ምርጫው የሚካሄደው ለኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያ በመሆኑ፣ ያለ ስምምነት ያ ሊሆን ስለማይችል መሆኑንም አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡ በሚረጨው መርዝ ላይ ዕርቅ በመፈጸም ማስወገድ ግድ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማድረግ እስከ ታች ድረስ ወርደው መነጋገርና መደማመጥ መቻል እንዳለባቸውም አውስተዋል፡፡ ይኼ ‹‹የርዕዮተ ዓለም›› ጉዳይ ሳይሆን አገርን የማስቀደም ጉዳይ መሆኑንም አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከመንግሥት የተውጣጣ ጥምር ኃይል ተቋቁሞ እስከ ታች ድረስ ወርዶ አገራዊ ዕርቅ መፈጸሙ በመጀመርያ ደረጃ አገርን እንደሚያድንና ሌላው ቀጥሎ እንደሚደርስ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡ ያልታረቁ፣ ጽንፍ የወጡና ያልታረቁ ፖለቲካዎች ስላሉ መታረቅ እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡ ፖለቲካው እርስ በርስ ሲታረቅ ሕዝብ ለሕዝብ ስለሚታርቅ አንድ ዓይነት አገራዊ ራዕይ፣ የተለያዩ ፖለቲካዊ አተያይ ሊኖር እንደሚችልና ተፎካክሮ አሸናፊው ድርጅት አገር ሊመራ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ መንግሥት የያዘው አቋም ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ ሰው እንደሚሞት እየታወቀ ምርጫ ይካሄዳል ብሎ መወሰን ግን ለሕዝብ ሆነ ለአገር እንደማይጠቅም አክለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ‹‹ሰው ሊሞት ይችላል›› ብቻ ሳይሆን ወደ እርስ በርስ መጠፋፋት፣ አገር አለመረጋጋትና መፍረስ ሊያስከትል እንደሚችል መታሰብ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ሌላው መኢአድ በሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች አዲስ የፀደቀውን የምርጫ ሕግ እንደሚቃወም የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፣ ሕገ መንግሥት የፈቀደውን የመደራጀት መብት መገደቡ የመጀመርያው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አዋጁ አሥር ሺሕ አባላት በድርጅቱ ውስጥ አባል መሆን እንዳለባቸው ሲደነግግ፣ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ አዋጁ ተግባር ላይ ሊውል አይገባም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ሕገ መንግሥቱን የሚጣረስ ሕግ በተግባር ላይ አይውልም›› ብሎ ሕገ መንግሥቱ ስለደነገገ ነው ብለዋል፡፡ የመደራጀት መብትን የሚገድብ አዋጅ በመሆኑ መኢአድ እንደሚቃወም ተናግረዋል፡፡ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ለበርካታ ጊዜያት ውይይት ሲደረግ ስምምነት ላይ የተደረሰበት አገር አቀፉ 3,000 አባላት እንዲያቀርብና ክልሉ 1,500 አባላት እንድያቀርብ ነበር፡፡ ይኼ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመዘን እንጂ፣ ሌላ ትርጉም ስለማይኖረው በሚል ተማምነው የነበረ ቢሆንም፣ ከውይይትና ስምምነት ውጪ ግን ሦስት ሺሕና አሥር ሺሕ የሚል ቁጥር በአዋጁ ተካቶ መውጣቱ ከተስማሙበት መርህ ውጪ በመሆኑ ተቃውሞ እያሰሙ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡ መኢአድ አዋጁን በሦስተኛ ደረጃ የሚቃወመው ወቅቱን ያገናዘበ አይደለም በሚል ሲሆን፣ ቀድሞ ከ25 ዓመታት በፊት ተግባር ላይ የዋለው አዋጅ ቁጥር አንድ (ሕገ መንግሥቱ) ባልተከበረበት በአሁኑ ወቅት አባላትን ለማስፈረም የማይቻል መሆኑን እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡ ትግራይ ክልልና ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢን በምሳሌነት ጠቁመዋል፡፡ በዋናነት ደግሞ አሥር ሺሕ የፖለቲካ አባላትን መዝግቦ ለምርጫ ቦርድ ከእነ አድራሻው ማስገባት፣ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የአባላትን ደኅንነት ሥጋት ላይ ይጥላል የሚል ሥጋትም እንዳለ አክለዋል፡፡ አዋጁ የጠቀሷቸውንና ሌሎችንም ነገሮች ያላገናዘበ በመሆኑ እንጂ በተለይ እንደ መኢአድ የቁጥር ጉዳይ መቼም ሥጋት ሆኖበት እንደማያውቅና በአንድ አስተባባሪ ብቻ በአንድ ቀን ከተጠቀሰው በላይ ማሰባሰብ ትንሹ ሥራ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡ አዋጁን ዋና ዋና ነጥቦች መጠቆም ለሕዝቡም ግንዛቤ ስለሚረዳ ጥቂቶቹን ድንጋጌዎች የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፣ ዕጩ ፓርቲውን ቢለቅና በሞት ቢለይ ‹‹መልሶ ማስፈረም አለበት›› ይላል፡፡ ይኼ ‹‹ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ›› የሆነና ዴሞክራሲን ሊያሰፋ የማይችል ውስብስብ ሕግ ነው፡፡ አገሪቱን ወደ ትርምስ ሊመራ የሚችል ድንጋጌ ደግሞ ውጤት አስቀድሞ የሚበይን ቁጥር ነው፡፡ አንድ ዕጩ ከምርጫ ጣቢያው 3,000 አባላት ካስፈረመ፣ እንዳሸነፈ ማረጋገጥ የሚችልበትን ሒደት ስለሚያረጋግጥ፤ አስቀድሞ የምርጫውን ውጤት ስለሚበይንና በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ ይኼ ውጤት ካለ ‹‹ተሸንፈሃል›› ቢባል ወዳልተፈለገ ትርምስና ብጥብጥ የሚከት ሕግ መሆኑንም አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡ ሌላው የአዋጁ አስገራሚ ክፍል በምርጫ የሚወዳደር የመንግሥት ሠራተኛ ‹‹ሥራውን መልቀቅ አለበት›› የሚለው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፣ ይኼ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተወዳዳሪውን ብቻ ማሰብ ሳይሆን ቤተሰቡን ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 25 ሁሉም ዜጋ በሕግ ፊት እኩል መሆኑን ስለደነገገ፣ በምርጫ የሚሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ሌሎች ባለሥልጣናት ‹‹ሥራ ሊለቁ ነው? ሥራ ከለቀቁ አገሪቱ መንግሥት በሌለበት ነው ምርጫ የምታካሂደው? ወይስ አይወዳደሩም?›› የሚል ጥያቄ ሕጉ ረቂቅ ደረጃ ላይ እያለ ጥያቄ በመነሳቱ፣ አዋጁ ሲፀድቅ እስከ ሚኒስትር ዴኤታ ድረስ ሥራውን ሳይለቅ መወዳደር የሚችል አንቀጽ በማስገባት መፅደቁ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይኼ ሕዝቦች በሕግ ፊት እኩል ናቸው የሚለውን የጣሰ መሆኑንና ሌሎች በርካታ አግባብነት የሌላቸውን አንቀጾች ያካተተ አዋጅ መሆኑ በመጥቀስ ተገቢ አለመሆኑን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ መኢአድ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ሳይስተካከሉ ምርጫው መካሄድ የለበትም የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ እንጂ የአባላት ቁጥር ማነስና መብዛት እንዳልሆነ ሕዝብ ሊረዳው እንደሚገባ አክለዋል፡፡ ከሦስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተፈናቃይ ባለበት፣ አገርና ዘርን መሠረት አድርጎ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ተገብቶ መረጋጋት ሳይፈጠር ምርጫ ይደረግ ማለት፤ ሌላ ዓላማ ከሌለ በስተቀር ፍትሐዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊሆን ስለማይችል መካሄድ እንደሌለበትም ጠቁመዋል፡፡ አሁን አገር የማዳን ጉዳይ ስለሆነ መጀመርያ አገራዊ ዕርቅ፣ ቀጥሎ ‹‹አገር እንዴት ትቀጥል?›› በሚለው ላይ አማራጭ ሐሳቦችን በማቅረብ መደራደርና ሁሉንም ማዕከል ያደረገ አካሄድ ማስቀመጥ ተገቢና ግድም መሆኑንና ሌሎችም ጊዜው ሲሆን ይፋ የሚደረጉ የመኢአድ ስትራቴጂዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

 

ሕገ መንግሥቱ እንደ ዋና ችግር

 አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ግን የዚህ አገራዊ ችግር ዋነኛ ምክንያት፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ›› መሆኑን የመኢአድ እምነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ 86 ብሔር ብሔረሰቦች ያሉ ሲሆን፣ ሕገ መንግሥቱ ለሁሉም ፓርቲ እንዲሆን፣ መንግሥት እንዲሆኑ ይፈቅዳል፡፡ ይህ አገር የሚበትን ሕገ መንግሥት ነው፡፡ 86 አገር እንዲሆንም ይፈቅዳል፡፡ የመገንጠል መብትን ስለሚፈቅድ፡፡ ትልቁ የአገር በሽታ ሕገ መንግሥቱ መሆኑንና ሉዓላዊነትን ጭምር የሚጋፋ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡ ለአንድ አገር ሉዓላዊነት ሰንደቅ ዓላማ አንዱ በመሆኑ ትልቋ ኃያል አገር አሜሪካ ከ50 በላይ ክልሎች ቢኖራትም፣ የሚያውለበልቡት ግን አንድ ዓይነት ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን ዘጠኝ ሰንደቅ ዓላማ ዘጠኝ ሕገ መንግሥት አላት፡፡ ይኼ አፍራሽ ነው፡፡ አገር እንዳትረጋጋ ያደረገ አንዱ ተግዳሮት ሕገ መንግሥቱ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ዋናው ሕገ መንግሥት በሁሉም ክልሎች ሀብት ንብረት ማፍራት እንደሚቻል ቢደነግግም፣ የክልሎቹ ግን፣ ከክልሉ ተወላጅ በስተቀር ሌላ ዜጋን ስለሚከለክል በምክንያት እያፈናቀሉ መሆኑን ከብዙ ጥቂቶቹን በማንሳት ተናግረዋል፡፡ ይህ የተፈጠረው ደግሞ ክልሉ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ክልል ‹‹የትኛውንም ዓይነት ሕግ የማውጣት መብት አለው›› ስለሚል መሆኑን አክለዋል፡፡ በአጠቃላይ ሕገ መንግሥቱ ዜጎችን በዘር የከፋፈለና አገር በታኝ በመሆኑ መኢአድ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የዘወትር ጥያቄው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የመኢአድ ፍልስፍናና የሚከተለው ‹‹ሊብራል ዴሞክራሲ መሆኑን፤ የሚምኑትና የሚያስፈጽሙትም ፌዴራሊዝም መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፣ በዘር ላይ የተመሠረተና አንድነትን የሚበትን ፌዴራሊዝም ሳይሆን መልክዓ ምድርን መሠረት ባደረገ ፌዴራሊዝም እንዲተካ እንጂ ሌሎች እንደሚሉት አሐዳዊ ሥርዓት መመሥረት ፍላጎትም ሆነ ትልም እንደሌለው አስረድተዋል፡፡  

ሲጠቃለል የ2012 ምርጫ እንዲህ ባሉ የተለያዩ ፍላጎቶችና አመለካከቶች መካከል ተሰንጎ፣ ይካሄድበታል የተባለበት ግንቦት ወር በሥጋትና በተስፋ እየተጠበቀ ነው። ከምርጫው ጊዜ መቃረብ፣ ፓርቲዎች ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ መዳከምና ከምርጫው ርዕሰ ጉዳይ ይልቅ ቀዳሚ የሆኑ አገራዊ አጀንዳዎች መግዘፍ ጋር ተያይዞ “መጪው ምርጫ ምን መልክ ይዞ ይካሄድ ይሆን?” የሚለው ጥያቄ የሁሉም ነው። አብዛኛው ሰው በአንድ ነገር ላይ ይስማማል። ምርጫው የተሻለ አገር ለመፍጠር ምክንያት እንዲሆን አንጂ አገርን ቀውስ ውስጥ ለመክተት ሰበብ መሆን እንደሌለበት። ቀሪውን ቀን ሲቀርብ የምንታዘበው ይሆናል።

ShareTweetShare

ተዛማጅ Posts

አቶ ጃዋር መሀመድ
አንኳር

አቶ ጃዋር መሀመድ “በማላውቀው ሀኪም መነካት አልፈልግም” በማለቱ በግል ሀኪም እንዲታከም ጥብቅ ትእዛዝ ተሰጠ

በ ታምሩ ጽጌ
August 2020
0

አቶ ጃዋር መሀመድ "በማላውቀው ሀኪም መነካት አልፈልግም" በማለቱ በግል ሀኪም እንዲታከም ጥብቅ ትእዛዝ ተሰጠ _ የዓቃቤ ሕግ ምስክርሮችን መሰማት ጀመረ አቶ ጃዋር መሀመድ ከአራት ቀን በፊት ነሐሴ 11 ቀን...

ተጨማሪ ያንብቡ
C:\Users\IT\Documents\A01\pics

የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውኃ ሙሌትና መቆሚያ ያጣው የግብፅ ሩጫ

July 2020
በሕዳሴው ግድብ

የጸጥታው ምክርቤት አባል አገራት በሕዳሴው ግድብ ላይ ለመወያየት ተስማሙ

June 2020
አደም ፉራን ወ/ሮ ኬሪያን ኢብራሔምን ተክተው የፌደሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ ሆነው ተመርጠዋል

አደም ፉራን ወ/ሮ ኬሪያን ኢብራሔምን ተክተው የፌደሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ ሆነው ተመርጠዋል

June 2020
ትምህርት ሚኒስቴር

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያመሰቃቀለው የትምህርት ሥርዓት

May 2020
Addis Disinfecting By Petros Teka

ከኃያላን እስከ ታዳጊ ላሉ የዓለም ሀገራት ፈተና የሆነው ኮቪድ-19

April 2020
ከህዳሴው ግድብ ድርድር በስተጀርባ

ከህዳሴው ግድብ ድርድር በስተጀርባ

April 2020

በብዛት በመነበብ ላይ ያሉ መጣጥፎች

ዶ/ር ቅድስት

“አንድ ሰው ምልክቱ ስላልታየበት በኮሮና ቫይረስ አልተጠቃም ብሎ መደምደም አይቻልም”

May 2020
C:\Users\IT\Documents\A01\pics

የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውኃ ሙሌትና መቆሚያ ያጣው የግብፅ ሩጫ

July 2020
የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ

የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ

May 2020
ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

May 2020
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ

ከጦር ጀግኖች ባሻገር . . .

May 2020

Follow us on Facebook

  • ዶ/ር ቅድስት

    “አንድ ሰው ምልክቱ ስላልታየበት በኮሮና ቫይረስ አልተጠቃም ብሎ መደምደም አይቻልም”

    384 shares
    Share 384 Tweet 0
  • የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውኃ ሙሌትና መቆሚያ ያጣው የግብፅ ሩጫ

    21 shares
    Share 21 Tweet 0
  • የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ

    0 shares
    Share 0 Tweet 0
  • ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

    44 shares
    Share 44 Tweet 0
  • ከጦር ጀግኖች ባሻገር . . .

    169 shares
    Share 169 Tweet 0
Ethiopian Reporter Magazine

ሪፖርተር ሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተር

(+251) 116 61 61 81

(+251) 116 61 61 85

[email protected]

የኢትዮጵያ ሪፖርተር መጽሔት

የኢትዮጵያ ሪፖርተር መጽሔት በሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተር እየታተመ የሚወጣ ወርኃዊ መጽሔት ሲሆን፣ የሚያተኩረውም በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር መጽሔት በ ኢሜይል ለማግኘት

  • Ethiopian Reporter
  • The Reporter Ethiopia
  • Reporter Tenders
  • Ethiopian Reporter Jobs

© 2020 Ethiopian Reporter Magazine - By Media And Communications Center.

ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
  • የፊት ገጽ
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት

© 2020 Ethiopian Reporter Magazine - By Media And Communications Center.

Login to your account below

Forgotten Password?

Fill the forms bellow to register

All fields are required. Log In

Retrieve your password

Please enter your username or email address to reset your password.

Log In