- የሰው ዘር አመጣጥ ሙዚየም ዕቅድ እምን ደረሰ?
ከካዛንቺስ ስድስት ኪሎ ተሳፋሪዎችን ይዞ ሚኒባስ ታክሲ እያመራ ነው፡፡ በሚያዝያ 27 አደባባይ በኩል አራት ኪሎንና ቅድስት ማርያምን ሲያልፍ ከተሳፈሩት ሁለቱ ወጋቸውን ቀየሩ፡፡ ‹‹አንተዬ ብሔራዊ ሙዚየም ስሙ ተቀይሯል፣ የለም እየተባለ ነው›› ይለዋል፡፡
‹‹ምን እያልክ ነው ይኸው በሩ ላይ ያለው ሰሌዳ ‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም› ይላል አይደለም እንዴ?›› ይመልሳል ሌላው፡፡ ‹‹የተንቀሳቃሽ ቅርስ ምናምን ነው ያሉት ስሙን አልያዝኩትም፣ ዓመታት አልፎታል፣ ስሙ ደብሯቸው ሳይሆን አይቀርም ያልለጠፉት›› ተሳፋሪዎች ይሳሳቃሉ፡፡
አንድ ጠና ያሉ ተሳፋሪ ‹‹ምነው ሰዎቹ ባከኑ ስም መቀየር ከፈለጉ የድሮው የጃንሆይ ዘመኑ ወመዘክር ምን አላቸው? የኢትዮጵያ ቤተ መዘክር በአማርኛ፣ የኢትዮጵያ ሙዚየም በእንግሊዝኛ በሚል ቢሰይሙት ምን ይላቸዋል!›› ሰዉ ራሱን በመነቅነቅ መስማማቱን ገለጸላቸው፡፡
ባለፉት ዓመታት በቅርስና ሙዚየም ቤተሰብ ዘንድ መነጋገሪያ በተወሰኑ ሚዲያዎች ደግሞ አጀንዳ ሆኖ የነበረው ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም›› ሕጋዊ ስሙና ቁመናው ተለውጦ ሌላ ስም ማግኘቱ ነው፡፡
በአገሪቱ ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ ተንሰራፍቶ የነበረው ‹‹ቢፒአር›› በመባል የሚታወቀው መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ንቅናቄ ካተኮረባቸው ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ነበር፡፡
በአንድ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በቢፒአሩ አደረጃጀት መሠረት ባለሥልጣኑ በተለያዩ ዳይሬክቶሬቶች ሲዋቀር በዋና ሥራ አስኪያጅ ይመራ የነበረው ሙዚየሙ የባለሥልጣኑ አንድ ዳይሬክቶሬት ሆኖ ተደራጅቷል፡፡ ስሙም ከብሔራዊ ሙዚየምነት ወደ ‹‹የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማት ኤግዚቢሽን ዳይሬክቶሬት›› ተለውጧል፡፡ ኃላፊውም በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሥር ሆኖ ዳይሬክተር ተብሏል፡፡
ይህ አዲሱ ስያሜ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮና ከሙዚየሞች ወካይነት አኳያ ብዙም የማያስኬድ ስያሜ በመሆኑ በየጊዜው በመድረኩ ትችትና ተቃውሞ እየተሰነዘረበት መጥቷል፡፡
ነባሩ ሙዚየም ባሁን አጠራሩ ‹‹…ዳይሬክቶሬት›› ስለ ሰው ዘር አመጣጥና ሌሎችም የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል የሚያንፀባርቁ እነ ሉሲ፣ ሰላም፣ አርዲ ወዘተ ቅርሶች የሚጎበኝበት ቢሆንም ብሔራዊ ሙዚየም የሚለውን ዕውቅና የማጣቱ ጉዳይ የበርካቶች መጋገሪያ ከመሆን አላመለጠም፡፡
በየዓመቱ ግንቦት 10 ቀን (ሜይ 18) የሚከበረውን የዓለም ሙዚየም ቀን ኢትዮጵያ ስታከብር፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብሔራዊ ሙዚየም ስያሜ ጉዳይ ሳይነሳ ያለፈበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ለምን? ተብሎ ሲጠየቅም “እየተጠና ነው” የሚል ምላሽም ሲሰማበት ኖሯል፡፡
እንዲያውም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የሚለው መጠርያ ሳይኖራትና የሙዚየምነት ዕውቅና ሳትሰጥ የሙዚየም ቀንን በየዓመቱ ማክበሯን ተቃርኖ (ፓራዶክስ) ነው የሚሉም አልታጡም፡፡
ከዓመት በፊት የዓለም ሙዚየም ቀን፣ “Museums and. contested histories: Saying the unspeakable in museums” በሚል መሪ ቃል ሲከበር ኢትዮጵያ ‹‹ያልተነገሩና አሻሚ ታሪኮች በሙዚየም›› በሚል አቻ ትርጉም አክብራለች፡፡ ያኔ መሪ ቃሉ ሙዚየምን በተመለከተ ያልተነገሩ ሐሳቦችን ወደ አደባባይ ማምጣት እንደመሆኑ በወቅቱ የነበሩ የውይይት ተሳታፊዎች ያለ ብሔራዊ ሙዚየም የሙዚየም ቀንን ማክበር ፋይዳ እንደሌለው ማመልከታቸው ይታወሳል፡፡
ከብሔራዊ ሙዚየምነት ወደ ተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማት ኤግዚቢሽንነት መለወጡን ያስተዋሉ አንድ ባለሙያ ድርጊቱን ‹‹ብሔራዊ ሙዚየምን ማንኳሰስ፣ ማንነትን ማንኳሰስ ነው፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የሙዚየም ባለሙያ ‹‹ብሔራዊ ሙዚየሟን ከመዋቅር የሠረዘች አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት›› በማለት ጎረቤት አገር ኬንያ ለአገራዊ ሙዚየም የሰጠችውን ቦታ በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡
በኬንያ የብሔራዊ ሙዚየሞችና ቅርስ ድንጋጌ (ሕግ) ራሱን ችሎ የቆመ ነው፡፡ የኬንያ ብሔራዊ ሙዚየሞች (The National Museums of Kenya-NMK) መንግሥታዊ ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ በኬንያ የሚገኙ ሙዚየሞች፣ መካነ ቅርሶችንና ሐውልቶችን ያስተዳድራል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዎሎጂና ቅርስ አስተዳደር ረዳት ፕሮፌሰር ተመስገን ቡርቃ (ዶ/ር)፣ በአንድ ወቅት ባቀረቡት ጥናታቸው በቢፒአር ምክንያት ህልውናውን ያጣው ሙዚየሙ፣ በራሱ የሚንቀሳቀስ ነፃ ተቋም መሆን እንደሚገባውም ይመክራሉ፡፡ ሙዚየሙ ያሉበት ጥያቄዎች በአፋጣኝ መልስ አግኝተው፣ የተሰመረበትም በየአካባቢው ላሉ ሙዚየሞች ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም መሆን እንደሚያሻው ነው፡፡
እንደ ምሁራን አገላለጽ ሙዚየሞች የመገናኛ ቦታ፣ ሐሳብ መለዋወጫና ችግርን የመቅረፊያ መድረኮች ናቸው፡፡ ባላቸው ስብስብ በመገናኘትና ታሪክና ባህልን ብቻ በማሰባሰብ ሳይወሰኑ ሌሎች ዘርፎችን ማካተት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሙዚየም በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለምሳሌ በኤችአይቪ፣ በሥነ አካባቢ፣ በማኅበረ ፖለቲካ ዙሪያ የሚነጋገሩበት መድረክም እንዲሆንም ይጠበቃል፡፡
ሙዚየም ኅብረተሰብን የማገናኘት በማኅበረሰቡ ውስጥም አንድነትና ግንኙነት ማድረግ ትልቁ ተግባሩ በመሆኑ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚኖረው ተቋም ተገቢ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ በአዲስ አቀራረብ፣ በአዲስ ርዕይና ሐሳብ መታጠቅ እንደሚገባውና ለዚህም ባለሙያዎች መነሳሳት ይገባቸዋል ሲሉም ያክላሉ፡፡
በአንድ ጥናታዊ ጽሑፋቸው አንጋፋው አርኪዮሎጂስት ብርሃኔ አስፋው (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ ሙዚየም እንደ ትምህርት ቤት የሚታይ የመረጃ ማዕከል ነው፡፡ ዋና ሥራው ቅርሶችንና ታሪካዊ እሴቶችን ጠብቆ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ዜጋን የሚቀርጽ፣ ባህልን የሚያስተምር፣ ታሪክን የሚያስረዳ ተቋም ነው፡፡ ከሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋሞች የተለየ የሚያደርገው ሙዚየም ጊዜን የጠበቀ መረጃ ማቀበል መቻሉ ነው፡፡
ብሔራዊ ሙዚየም ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ታሪክ፣ ከባህል፣ ከታሪክ፣ ከኤትኖግራፊ (የሕዝብ ባህል) አንፃር ቁስ አካላዊና ቁሳዊ ያልሆኑ እሴቶችን በማቅረብ ኃላፊነት ያለበት ከተመራማሪዎች ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን ነው፡፡
“የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን” ሙዚየምን መተካት ይችላልን?
ከዓለም አቀፉ የሙዚየም ድርጅት (አይኮም) የሙዚየም ትርጓሜ በመነሳት “የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን” በምን ስሌት ነው የሙዚየምን ጽንሰ ሐሳብና ተልዕኮ በምልዓት ሊተካ የሚችለው? የሚሉ ጠያቂዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
መንግሥት የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን በ1992 ዓ.ም. ያቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 209/1992 ስለ ቅርስ ጥናትና አጠባበቅ የሚናገር ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 12 ድንጋጌ ሙዚየምን እንዲህ ተርጉሞታል፡፡ “ሙዚየም ማለት ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ያልሆነ ቅርሶችን የሚሰበስብ፣ የሚጠብቅና የሚጠግን ለምርምርና ለጥናት፣ ለማስተማሪያና ለመዝናኛነት ስብስቦችን በሚገባ አዘጋጅቶ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡” ለዚህ የሙዚየም ትርጓሜ መሠረት ነው ተብሎ የሚታሰበው በቀዳሚው የአይኮም ድንጋጌ ላይ የወጣው የሙዚየም ምንነት ነው፡፡
“ሙዚየም ማለት ዓላማው በትርፍ ላይ ያልተመሠረተ ለማኅበረሰብ ዕድገት አገልግሎት የሚያበረክትና ለኅብረተሰቡ ክፍት የሆነ፣ ለጥናት፣ ለትምህርትና ለኅሊናዊ ዕርካታ ሊውሉ በሚችሉበት ሁኔታ የሰው ልጅና የአካባቢውን ቁሳዊ መረጃዎች የሚያሰባስብ፣ የሚያከማች የሚንከባከብ ምርምር የሚያካሂድ በኤግዚቢሽን ወይም አግባብነት ባለው መንገድ የሚያስተዋውቅ ተቋም ነው፡፡”
እ.ኤ.አ. በ1946 የተመሠረተው አይኮም የሙዚየም ትርጓሜን በየዐረፍተ ዘመኑ ማሻሻሉን አልተወም፡፡ በኦስትሪያ ቪየና ነሐሴ 18 ቀን 1999 ዓ.ም. ባደረገው 22ኛው ጠቅላላ ጉባዔው ነባሩን ድንጋጌ እንዲህ አድርጎ ዘርዘር በማድረግ አሻሽሎታል፡፡
““ሙዚየም ማለት ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ለኅብረተሰብ አገልግሎትና ለልማቱ የተሰማራ፣ የሰው ልጆች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን (tangible and intangible heritage) የሚጠብቅ፣ የሚንከባከብ ምርምርና ጥናት የሚያደርግ፣ ለሕዝቡ ክፍት ሆኖ በዐውደ ርዕይ የሚጎበኝ ብሎም ለትምህርት፣ ለጥናትና ለተድላ ደስታ (ለመዝናኛ) የሚያውል ቋሚ ተቋም ነው፡፡”
አይኮም ያደረገውን የትርጉም ማሻሻያ ኢትዮጵያ አለመመልከቷ ወይም አለማሻሻሏ የሚያሳየው፣ በቀደመው ትርጉም ብቻ በመመሥረት ብሔራዊ ሙዚየምን “የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን ዳይሬክቶሬት” ብላ መሰየሟ ነው፡፡ ዳይሬክቶሬቱ የማይንቀሳቀሱ (የሚዳሰሱ) እንዲሁም የማይዳሰሱ ቅርሶችን አይመለከትም ማለት ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የሙዚየም ድርጅት ከአሥራ ሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ የሙዚየምን ትርጉም ዳግም አሻሽሎታል፡፡ የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ ባለፈው ሐምሌ 2011 ዓ.ም. በፓሪስ ባደረገው 139ኛው ስብሰባው በደረሰበት ውሳኔ አዲሱን የሙዚየም ብያኔ ይፋ አድርጓል፡፡
“ሙዚየሞች ዲሞክራሲያዊ፣ ሁሉን አካታች ስላለፉት ዘመናትም ሆነ ስለ መጪው ዘመን የሚያወሱ፣ የሒሳዊ (ክሪቲካል) ውይይቶች መድረክ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ያሉትን ግጭቶችና ተግዳሮቶች በመገንዘብ በመፍትሔነት በማኅበረሰቡ ውስጥ እምነት የሚያሳድሩ የዕደ ጥበባት ውጤቶችንና ናሙናዎችን ይይዛሉ፡፡ ለመጪው ትውልድ ብዝኃ ትውስታዎችን በመጠበቅ ለሁሉም ሕዝብ ያለ ልዩነት በእኩል መብቶችና በእኩል ተደራሽነት ያስተናግዳሉ፡፡ ዋስትናም ይሰጣሉ፡፡
“ሙዚየሞች በትርፍ ላይ ያልተመሠረቱ አሳታፊና ሥራቸው ግልፅ የሆነ ነው፡፡ እንዲሁም ለሰው ልጅ ክብርና ማኅበራዊ ፍትሕ፣ ለዓለም አቀፍ እኩልነትና ለዓለም ደኅንነት ንቁ አስተዋጽዖ የሚያደርጉት ብዝኃነትን ባማከለ መልኩ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን ቅርስ የመሰብሰብ፣ የመጠበቅ፣ ጥናትና ምርምር የማድረግ፣ የመተርጐም፣ በዐውደ ርዕይ በማሳየት ነው፡፡
ይህ አዲሱ ማሻሻያ ከመውጣቱ ከአሥራ አንድ ዓመታት በፊት የዓለም ሙዚየም ቀን በኢትዮጵያ «ሙዚየሞች ለማኅበራዊ ለውጥና ዕድገት አጋዥ ኃይሎች» በሚል መሪ ቃል ሲከበር በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ የሙዚየም ተልዕኮ መስፋት እንደሚገባው በኢትዮጵያውያን ምሁራን ተንፀባርቆ ነበር፡፡
በወቅቱ የታሪክና አርኪዮሎዢ ምሁሩ ካሳዬ በጋሻው (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ሙዚየም ብዙ ጊዜ የሚታወቀው ሥራው መሰብሰብ፣ መሰነድ፣ መጠበቅ፣ ጥናትና ምርምር በየዕለቱ ማከናወን ናቸው፡፡ አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሙዚየም ምን ሆኖ መገኘት ይገባዋል፣ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ይኖረዋል የሚለው ተተኳሪ ነጥብን አንስተዋል፡፡ ሙዚየሞች ምን ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ የሙዚየም ብያኔ ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ ይዳስሳል ወይ፣ ነባሩ ብያኔ ግማሽ ምዕት ዓመት አሳልፏል፡፡ አሁን የምንለውን መሸከም ይችላል ወይ፣ ሙዚየሞች የመገናኛ ቦታ፣ ሐሳብ መለዋወጫ ችግርን የመቅረፊያ መድረኮች ናቸው፡፡ ባላቸው ስብስብ በመገናኘትና ታሪክና ባህልን ብቻ በማሰባሰብ ሳይወሰኑ ሌሎች ዘርፎችን እንደ ማዕድን፣ ኢነርጂን ማካተትና ገንዘብን የማስገባት ለቱሪዝም ዕድገት የሚበጁ መሆናቸውን ማወቅ ይገባል ይላሉ፡፡
ሙዚየም የአገሪቷን ችግር በኤችአይቪ፣ በሥነ አካባቢ፣ በፖለቲካ ቀውሶች ዙሪያ የሚነጋገሩበት መድረክ መሆን እንደሚገባው የሌሎችን አገሮችን ተሞክሮ በምሳሌነት በማቅረብ ያብራራሉ፡፡
ለማኅበራዊ ለውጥ በምናስብበት ጊዜ ሕንፃውን፣ ቅርሶችን ብቻ ሳይሆን የሚያንቀሳቅሰው ክፍልንም ጭምር ነው፡፡ በሁለተኛነት የሚያሳየው ሙዚየሙ ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት አቅም አለው ወይ፣ ራሱስ ሳይለወጥ ሌላውን መለወጥ ይችላል ወይ፣ ለለውጥስ ተዘጋጅተዋል ወይ፣ ይኸንን የሚሸከም ኅብረተሰብ አለ ወይ፣ መንግሥትስ ይኸን ሐሳብ ይገነዘባል ወይ፣ እነዚህን መገንዘብ እንደሚስፈልግ ምሁሩ በወቅቱ አጽንዖት ሰጥተውበት ነበር፡፡
ብሔራዊ ሙዚየም ዳግም ይመለስ ይሆን?
ብሔራዊ ሙዚየም በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የተቋቋመው በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዘመን በ1936 ዓ.ም. ሲሆን በአሁኑ ወቅት ስሙ ባይኖርም 76ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሲቋቋም መጠርያው የነበረው ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ተብሎ ነው፡፡ ቤተ መጻሕፍቱ በአንድ በኩል፣ መዘክሩ (ሙዚየም) በሌላ በኩል ሆኖ የሙዚየሙን ሥራ ማከናወን የጀመረው ንጉሠ ነገሥቱ፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ ባበረከቷቸው 209 ቅርሶች መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ቢፒአሩን ተከትሎ ሕጋዊ ስሙን ያጣው (በየድረ ገጹና በሰሌዳ ላይ ስሙም ቢኖርም) እና በ“የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን ዳይሬክቶሬት” የተተካው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም፣ በየመድረኩ በተለይም በየዓመቱ በሚከበረው የሙዚየም ቀን ትችትና ነቀፌታ ማስከተሉን ተከትሎ ስሙን ለመመለስ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል፡፡
ሃቻምና የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን ዳይሬክተር የነበሩትና ቅድመ ቢፒአር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ት ማሚቱ ይልማ፣ በወቅቱ የብሔራዊ ሙዚየሙን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ እንደተቋቋመና በቅርቡ ለውጥ እንደሚኖር መግለጻቸው የተዘገበ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት የተተገበረ ነገር እንደሌለ ነው፡፡
ሪፖርተር በአሁኑ ወቅት የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን ዳይሬክተሩን አቶ ኤፍሬም አማረን አነጋግሮ ያገኘው ምላሽ የብሔራዊ ሙዚየም የአደረጃጀት ጉዳይ ተጠንቶ ለሚመለከተው አካል መተላለፉን ነው፡፡ እንዲህም አሉ፡፡ ‹‹ጥናቱን አዘጋጅተን በመጨረስ ለሚኒስትሮቹ አስተላልፈናል፤ ወደ ሕግ ክፍልም ተልኳል፡፡ ወደፊት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መድረክ ፈጥረን እናወያያለን፡፡››
የሰው ዘር አመጣጥ ሙዚየም ግንባታ ዕቅድ እምን ደረሰ?
በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥን የሚያሳዩ የ12 ቅሪተ አካላትን ሪከርድ እንደ ኢትዮጵያ የያዘ እንደሌለ ይወሳል፡፡ “ማንም ስለቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ማወቅ የፈለገ ኢትዮጵያ መምጣት ነው ያለበት” የሚለውን ብሂል ተከትሎ፣ ለዚሁም ምቹ መደላድልን ለመፍጠር እንዲቻል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዲስ አበባ ውስጥ የሰው ዘር አመጣጥ ሙዚየምን (Human Origin Museum) እንደሚገነባ በ2007 ዓ.ም. አስታውቆ ነበር፡፡
አዲሱ ሙዚየም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በሁለተኛው የዕድገትና ውላጤ (ትራንስፎርሜሽን) ዕቅድ ለመገንባት የታቀደ ፕሮጀክት ነው፡፡ ለፕሮጀክቱ ከአውሮፓ ኅብረት የሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ዲዛይኑ እንደሚሠራና ግንባታውም በመንግሥት በጀትና ከዓለም አቀፍ ለጋሾች በሚገኝ ገንዘብ እንደሚሠራ መገለጹም በወቅቱ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቦ ነበር፡፡
አዲሱ ሙዚየም ከብሔራዊ ሙዚየም ፊት ለፊት አስፋልቱን ተሻግሮ ከሚገኘው ቦታ ላይ መገንባት የተፈለገውም ሁለቱንም ሙዚየሞች በድልድይ በማገናኘት ጎብኚዎች በተመሳሳይ ጊዜ ለመጎብኘት እንዲችሉ ነው፡፡
አምስት ኪሎ ከሚገኘው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም” ፊት ለፊት በሚገኘው ስፍራ ይገነባል ተብሎ የነበረው አዲሱ ሙዚየም በ4500 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የሚያርፍ ባለ10 ፎቅ ሕንፃ መሆኑ በወቅቱ ባለሥልጣኑ ገልጾ ነበር፡፡
በ260 ሚሊዮን ብር ወጪ ሙዚየሙን ለመገንባት መታቀዱ፣ ከዚያ ቦታ ለሚነሱት ካሣ ለመክፈል ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር በሒደት ላይ ያለና ለተነሺዎችም ምትክ ቦታ እየተሰጠ ነው መባሉም ያኔ ተውስቷል፡፡ ይሁን እንጂ ላለፉት አራት ዓመታት የታየ እንቅስቃሴ የለም፡፡
ይህንኑ አስመልክቶ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ኤፍሬም እንዳስረዱት፣ የሂዩማን ኦሪጅን ሙዚየም ጉዳይ የጀመረው በ2005 ዓ.ም. ነው፡፡ መሀል ላይ ቢቋረጥም ዳግም ተንቀሳቅሷል፡፡ እስካሁን በቦታው ቤት ላላቸው ሰዎች 10.5 ሚሊዮን ብር ካሳ መከፈሉን፣ ለሌሎች ደግሞ ኮንዶሚኒየም መሰጠቱን፣ ይሁን እንጂ አሁንም በቦታው ሃያ ስምንት ነዋሪዎች መኖራቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ሆኖም ከአራዳ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር መሬቱን ለመረከብ እየጠበቅን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡