ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ እ.ኤ.አ. ለ2019 በዓለም ወካይ ቅርስነት በታጩ 42 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ላይ የበይነ መንግሥታዊ ኮሚቴ በኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ ከኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ቀን ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባው በቅርስነት ከመዘገባቸው አንዱ የኢትዮጵያ የጥምቀት
ክብረ በዓል ነው፡፡ ሞሮኮ የናዋ ሙዚቃዋ (Gnawa music) ናይጄሪያ ዋቅህ የቴአትር ክዋኔዋ (Kwaqh-Hir theatrical performance) በሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት መመዝገቡን በድረ ገጹ ይፋ አድርጓል። የናዋ ሙዚቃ በሞሮኮና በሌሎች የሰሜን አፍሪካ ኢስላማዊ መንፈሳዊ ሃይማኖታዊ ዝማሬና ሥርዓት (ሪትም) አካል ነው።
በጥሩ ሁኔታ የተጠበቀው ቅርሱ የምዕት ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረ ቃላዊ ግጥምን ከባህላዊ ሙዚቃና ዳንስ ጋር ያቆራኘ ነው። የናይጄሪያ ተመዝጋቢው ቴአትራዊ ቅርስ የተለያዩ ባህላዊ መገለጫዎችን ከታሪክ ነገራ ጋር ያያያዘ ነው። ቆጵሮስና ግሪክ የቢዛንታይን የሥርዓተ ማሕሌት ዜማ፣ ስዊዘርላንድ የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰሙነ ሕማማት፣ አርመን በኪነ ቅርፅ መስክ የተደራጀው የፊደል ገበታዋ፣ የጣሊያን የይቅርታ ሥነ በዓል ከተመዘገቡት የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል ይገኙበታል፡፡ ፎቶዎቹ እነሱኑ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
- ፎቶ፡ ዩኔስኮ