በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር መሠረት 2019 ተጠናቋል፡፡ ዓመቱ በተለይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዓለም አደባባይ የነገሡበት፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ የተውለበለበበትና ትኩረት ያገኘበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት 2012 ዓ.ም. የመጀመርያው ወር መስከረም 30 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለዓለም አቀፍ ትብብር ባደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ፣ የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በታላቅ ሥነ ሥርዓት በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ተገኝተው ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ለ20 ዓመታት በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር አስታራቂዎች ተሞክሮ ሊፈታ ያልቻለውን፣ የኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ግጭት ወደ ሥልጣን በመጡ ጥቂት ቀናት ውስጥ መፍታት መቻላቸው ለሽልማት ከታጩባቸው እንቅስቃሴዎቻቸው ዋናውን ይዟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ራሳቸው በሚመሯት አገር የጀመሩትን ሰላም የማውረድ እንቅስቃሴ ወደ ጎረቤት አገሮች በማሻገር በኤርትራና ጂቡቲ፣ በኬንያና ሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንና በሱዳን የተፈጠሩ የሰላም መደፍረሶችን ወደ ሰላም መመለሳቸውም የዓለም ለኖቤል ተሸላሚነት ያበቃቸው ሥራቸው ነው፡፡ ምንም እንኳን በአገራቸው ያለው የውስጥ ሽኩቻ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለ ቢሆንም፣ ሥልጣን በያዙ በአጭር ጊዜ መቶኛውን የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ትልቅ ድል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በጎርጎርዮሳዊው 2019 ዓመት በሠሩት ድንቅ ሥራ ዓለምን በማስደመም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ በዓለም አደባባይ እንዲውለበለብ ያደረጉ፣ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆችም አሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ከአፍሪካ ለዘንድሮ ብቸኛዋና በዓለም ካሉ መቶ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መሀል አንዷ ሆነው መመረጣቸው ፎርብስ መጋዚን ይፋ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያዊው ፓሊዮንቶሎጂስት ዮሐንስ ኃይለ ሥላሴ (ዶ/ር) ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2019 በሳይንስ ልዕልና ካገኙ አሥር ሳይንቲስቶች አንዱ ሆነዋል፡፡ የኦሃዮ ክሊቭላንድ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም የፊዚካል አንትሮፖሎጂ ኪዩሬተሩ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ለዘንድሮው ታላቅ ክብር ያበቃቸው የቅድመ ሰው ዘርና ሌሎች ግኝቶች ይፋ የሚደረግበት ኔቸር ጆርናል ነው፡፡ ለዚህ የላቀ ክብር ያበቃቸውም በነሐሴ 2011 ዓ.ም. ይፋ የተደረገውና ለሦስት ዓመት ጥልቅ ጥናት የተደረገበት በአፋር ክልል 3.8 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረ የራስ ቅል በማግኘታቸው ነው፡፡ ይህ ግኝት አውስትራሎፒቴክስ አናመንሲስ በሚባል የቅድመ ሰው ዝርያ ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ስለዝርያው ያልታወቁ፣ የፊትና የጭንቅላት ቅርፅ ለመጀመርያ ጊዜ ያሳየ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የዓመቱን የአቪዬሽን ሽልማትን በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ላይ በፈጠሩት ተፅዕኖ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ካደረጉ አትሌቶች አንዷ የሆነችው ደራርቱ ቱሉ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ባደረገችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የዓመቱ ምርጥ ሴት በወርልድ አትሌቲክስ ተሸልማለች፡፡
ከአንድ ጊዜ በላይ የሴቶች የወር አበባ ንጽህናን መጠበቅ የሚያስችል የፈጠራ ሥራ በመሥራት ‹‹የዓመቱ ጀግና›› በማለት ሲኤንኤን ፍሬወይኒ መብርሃቱን ሲሸልማት፣ መስፍን ወልደ ማርያም (ፕሮፌሰር) ደግሞ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ባደረጉት አስተዋጽኦ የ”ዲፌንድ ዲፌንደርስ” የ2019 የሰብዓዊ መብት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በአሜሪካ የኬሚስትሪ ማኅበረሰብ ሐረገ ወይን አሰፋን (ዶ/ር) የኬሚስትሪ ጀግና ሲሆኑ፣ እንዲሁም ይሁኔ ድሌ (ዶ/ር) የዓመቱን የምግብ ሰብል ልማት ቦርድ ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ አረጋይ ግርማይ (ዶ/ር) የሰሜን ካሮሊና የዓመቱ ምርጥ ሐኪም ሲባሉ፣ ዘቢብ የኑስ (ዶ/ር) ደግሞ ብቸኛዋ የአፍሪካ ተመራማሪ በመሆን ተሸልመዋል፡፡