ሀበሻ ማን ነው?
ሀበሻ ኢትዮጵያዊ ከሚለው ቃል ይልቅ በአጠቃቀም በህብረተሰቡ ዘንድ ስር የሰደደ ነው። በርካታ ሀገራዊ (ቁሳዊና ሀሳባዊ) ባህሎች በዚህ ቃል ቅፅልነት ሲገለፁ ይስተዋላል። ለዚህ አስረጅ፣ የሀበሻ ዶሮ፣ የሀበሻ ጎመን፣ የሀበሻ መድሀኒት፣ የሀበሻ ኩራት፣ የሀበሻ ተንኮል፣ የሀበሻ ምቀኝነት፣ ወዘተ. የሚሉትን አጠቃቀሞች መጥቀስ ይቻላል። ሀበሻ የሚለው ቃል ከህንድ እስከ አውሮፓ መላው አለም ኢትዮጵያን ለመግለፅ ሲጠቀሙበትም ቆይቷል። በህንድ፣ በፓኪስታን እና በአጎራባች ሀገሮች ሀበሺ የሚባሉ በጀግንነታቸው የተመሰገኑ ከአካባቢያችን የሄዱ ህዝቦችም አሉ (ለመነሻ ግንዛቤ ፓንክረስት 2003ን እና ባሱ 2003ን ይመልከቱ)። ባሁኑ ወቅት በውጭው ሀገር ኢትዮጵያዊው እና ኤርትራዊው መሰሉን ሲያይ “ሀበሻ ነህ?” የሚል ጥያቄ ያቀርባል። ይህን ቃል ኢትዮጵያዊ የመሰለውን ሰው ለመተዋወቅ ከአጎራባች ሀገሮች በተለይ ከሶማሊያ የመጡም ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ይሁን እንጂ ሀበሻ የሚለው ቃል የተለየ ፖለቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶም ይገኛል።
ተክለፃዲቅ መኩሪያ (1951) የኢትዮጵያ ታሪክ ኑብያ–አክሱም ዛጉዬ እስከ ዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመን መንግሥት መፅሀፋቸው ላይ ማርስል ኮሆን “እናንተ ኢትዮጵያውያን ሀበሾች ሲሏችሁ ቅር ይላችኋል ማለትን ሰምቻለሁ። ነገር ግን እውነተኛ ስማችሁ ሀበሻ መሆኑ አይጠረጠርም” (ገፅ 16) እንዳሉዋቸው ይገልፃሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሀበሻ የሚመለከተው የሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ብቻ ነው የሚል በተለያዩ ስራዎች ይገኛል። የዚህ አስተሳሰብ መነሻ ወደኋላ እስከ ሉዶልፍ (1682) ቢደርስም፣ በተለይ ከ1960ዎቹ ወዲህ በምርምር/በትምህርት አለም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ይሁን እንጂ፣ አሁንም ሀበሻን ከሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር ማያያዝ ይታያል። ለምሳሌ በሀበሻ ህዝብ መጣጥፍ “ባሁኑ ግዜ የሀበሻ ህዝብ የሚባሉት አማርኛ፣ ትግርኛ፣ እና ትግረ ተናጋሪውን፣ ጉራጌን፣ እና ሀረሪን ያካትታል” የሚል ይገኛል። በዚሁ መጣጥፍ ሌላ ቦታ “ቃሉ ክርስትያን የአማርኛና የትግርኛ ተናጋሪዎችን ለማመልከት ለሚውለው አቢሲኒያ መሰረት ነው” ይላል። አቢሲኒያ የውጭ ሀገር ፀሀፊዎች ኢትዮጵያን ለመጥራት እስከቅርብ ግዜ ድረስ ይጠቀሙበት የነበረ ቃል ነው። የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት (እንደማንኛውም ጥንታዊ ሀገራት) በየግዜው ሲሰፋ ሲጠብ ቢኖርም በማናቸውም ግዜ ቢሆን አቢሲኒያ ክርስትያን ትግርኛና አማርኛ ተናጋሪን ብቻ ያመለከተበት አጋጣሚ በታሪክ የለም። የዚህ አይነቱ አስተያየት እንዴት ሊመጣ ቻለ በሚል የፖለቲካ ትንታኔ ለመስጠት አንሞክርም። ይልቁንም፣ ለመሆኑ ሀበሻ ማነው? እና የቃሉስ ምንጭ ምንድነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንሞክራለን።

በእነዚህ ጥያቄዎች ዙርያ ጥቂት የማይባሉ ጥናቶች በተለያዩ ወቅቶች ተካሂደዋል። በዚህ ስራ እነዚህ ስራዎችን አሁን ካለው ግንዛቤ አንፃር እንቃኛለን። እስካሁን በቀደምት ስራዎች ውስጥ ያለው ሀበሻ የሚለው በታሪክ ያለውን አጠቃቀም ለማየት የሞከረ እንጂ በሀገራችን ቋንቋዎች ምን አይነት አጠቃቀም እንዳለው የተመለከተ ስራ አላጋጠመንም። በዚህ ስራ ሀበሻ የሚለውን ቃል ስንመረምር አሁን ቃሉ በአማርኛና በትግርኛ ያለውንም አጠቃቀም/አገባብ ከግንዛቤ በማስገባት ነው።
[ማሳሰቢያ፡ ይህ ስራ ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ማንነት እና ቅድመታሪክ ከሚለው መፅሀፍ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎበት የተቀዳ ነው።]
2. ሀበሻና ሴም
ከላይ በመግቢያችን እንደገለፅንው ሀበሻ የሚለውን ቃል ከሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር የማገናኘት ሁኔታ፣ ታሪካዊ መረጃ እንደሌለው ቢገለፅም፣ ባሁኑ ግዜ በተለይ በሀገራችን ተደጋግሞ ሲሰማ ይስተዋላል። በእግረመንገድ ይህን ቃል የሚያነሱ ስራዎችም ይህንኑ ሲደግሙት ይስተዋላል። ለምሳሌ ሚረን የቀይባህር ዜጎች በሚለው መፅሀፉ ሀበሻ የሚለውን ቃል በሙዳየቃላት የበየነው በኢትዮጵያና በኤርትራ ደጋማ ቦታዎች የሰፈሩ ሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦችን የሚመለከት እንደሆነ ነው (ሚረን 2009: 282)።
ሀበሻና ሴምን የማገናኘት ጉዳይ በህብረተሰቡ ዘንድ በስፋት እንዲሰራጭ ያስቻለው በየትምህርት ቤቱ ሲሰጥ የነበረ ታሪክ ይመስላል። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሲሰጥ የነበረው በጣም የተለመደው መላምት ሴማዊ ህዝቦች ከደቡብ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው መጡ የሚል ነው። በዚህ ጉዳይ ከቀደምት ስራዎች ውስጥ እዮብ ሉዶልፍ (1682:8) ሊጠቀስ ይችላል። የመጡበትም ግዜ ባብዛኛው ከ1000 እስከ 500 ቅጋአ (ቅድመ የጋራ አቆጣጠር) ተደርጎ ይወሰዳል። ለዚህ መላምት ስር መስደድ በግንባር ቀደምትነት ከሉዶልፍ በማስከተል ከሚጠቀሱት ውስጥ አንደኛው ኮንቲ ሮስኒ (1906 እና 1928) ናቸው። እነተክለፃዲቅ መኩርያ በዚሁ በወቅቱ አሳማኝ መስሎ በታየው መላምት ላይ ተመርኩዘው የማስተማሪያ መፅሀፍ በማዘጋጀት፣ ሀሳቡን ወደ ትምህርት ቤት አወረዱት። ታደሰ ታምራትም (1972) ታላቅ ናቸው ብሎ ያሰባቸውን እነኮንቲ ሮሲኒን ሀሳብ እንዳለ ተቀብሎ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ታሪክ የሴማዊ ህዝቦች መስፋፋት አድርጎ ማቅረቡ ለአመለካከቱ ስር መስደድ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ማለት ይቻላል። እንደእነዚህ ፀሀፊዎች እምነት ወደኢትዮጵያ መጡ ከሚባሉት የሴም ነገዶች ውስጥ ዋናዋናዎቹ ነገደ ሐበሸት እና ነገደ አግዓዚ የተሰኙ ናቸው። ነገደ ሐበሸት ስሙን ለህዝቡ መጠሪያ ሲያሳልፍ ነገደ አግዓዚ ደግሞ ቋንቋውን ተወልን (ለምሳሌ፣ ትሪሚንግሀም 1952/1965:32፣ ኡለንዶርፍ 1955:7ን ይመልከቱ)። በዚህ ስር በሰደደ መላምት ሀበሻ ከሐበሸት፣ ግዕዝ ደግሞ ከአግዓዚ ከሚሉት ቃላት የመጡ ናቸው። ግዕዝም ከሳባ በቀጥታ የመጣ ነው የሚለውን የግምት አነጋገር የኛዎቹ እንዳለ ተቀብለውት በትምህርት ቤት ማስተማሪያዎች ውስጥ ይሰጥ ነበር፤ “ይህ ግዕዝኛ አነጋገር የመጣ ከክርስትና በኋላ ነው እንጂ የፊተኛው አነጋገርና ፅሑፍ ቀድሞ በደቡብ ዓረብ ሳሉ የሚፅፉበትና የሚነጋገሩበት የሳባ ቋንቋ ነው። ይኸም የሳባ ፊደልና ቋንቋ ለግዕዝ እንደ አባት የሚቆጠር ነው” (ተክለ ፃዲቅ መኩርያ 1951:17)። የዚህ መላምት ቅርሻ እስካሁን ላለው በህብረተሰቡ ዘንድ ለተስፋፋው የተሳሳተ አስተያየት መሰረት የሆነ ይመስላል።
በርግጥ በአንዳንድ ታሪክ ፀሀፊዎች እንደተባለው ሐበሸትና አግዓዚ የሚባሉ ሴማዊ ነገዶች ወደሀገራችን ገብተው አሁን (በሀገሪቱ) ያሉትን ሴማዊ ተናጋሪ ህዝቦች አስገኝተው ከሆነና የጥንታዊ ኢትዮጵያን ስልጣኔና አስተዳደር እነዚህ መጤ ህዝቦች መስርተውት ከሆነ የቀድሞው አስተሳሰብ እውነትነት አለው። ሁኔታው ግን ይህ አይመስልም። የእነኮንቲ ሮሲኒ ስራዎች ከወጡ በኋላ የተደረጉ ምርምሮች የሚያሳዩን ከዚህ የተለየ ነው።
በትምህርት አለም ባንድ ወቅት የተፃፈ የምርምር ስራ (ታሪክን ጨምሮ) ያለቀለት ነው ተብሎ አይወሰደም። ያ ስራ ለሌላው መሰረት ነው የሚሆነው። በዚያ ስራ የተገለፁ ነገሮች እንደገና ይመረመራሉ። ትክክል የሆኑት ሲወሰዱ፣ ትክክል ሳይሆኑ የተገኙት የሚስተካከሉበት መንገድ ይጠቆማል። አዳዲስ ፅንሰሀሳቦችና መረጃዎች በተገኙ ቁጥር የድሮዎቹ መላምቶች ይታደሳሉ። ይህ ማቆምያ የለውም። በወቅቱ ሐበሸትና አግዓዚያን የተሰኙ ነገዶች ወደ ኢትዮጵያ ገቡ የሚለው መላምት እውነት መስሎ ቢታይም ይህ ለሁሌ እውነት ነው ማለት አይደለም። ባሁኑ ግዜ ያለን መረጃ የድሮውን መላምት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ ተገኝቷል። ነጥቦቹን እስቲ በዝርዝር እንመልከት።
የሴም ህዝቦች ወደኢትዮጵያ ባህር ተሻግረው መጡ የሚል ሀሳብ ሉዶልፍ (1682:8-9) ሲሰነዝር ምክንያቱ የሚከተሉት ነበሩ፤
- ኢትዮጵያውያን መልካቸውና የሰውነት ቅርፃቸው ከጥቁር አፍሪካኖች ይልቅ ለአረቦች ይቀርባል፤
- ግዕዝ ከአረብኛ ጋር ይመሳሰላል፤
- በርካታ ባህላዊ እሴቶች (ለምሳሌ እንደግርዛት አይነት) ኢትዮጵያውያኖች ከአረቦች የሚጋሯቸው አላቸው፤
- በመፅሀፍ ቅዱስ የተጠቀሰችውን ንግስተ ሳባ ሁለቱም ሀገሮች (ደቡብ አረቢያና እና ኢትዮጵያ) የኛ ናት ይላሉ፤
- የስድስተኛው ክፍለዘመን እስጢፋኖስ የተባለው ጂኦግራፈር አባሴኖኢ (Αβασηνοι) የሚባል ግዛት በደቡብ አረቢያ መኖሩን ገልጿል፤ እና፣
- ንጉሥ ሲቨረስ በጦርነት ከተሸነፉት የአረቢያ ህዝቦች መሀከል ሀበሾችን በሳንቲሙ ላይ እንዲፃፉ አድርጓል።
ሉዶልፍ (1682) በወቅቱ ኢትዮጵያም ሆነ በደቡብ አረቢያ ውስጥ በሳብኛ የተፃፉ የድንጋይ ላይ ፅሁፎች መኖራቸውን አያውቅም ነበር። በወቅቱ ስለነዚህ ፅሁፎች የሚታወቅ ነገር አልነበረምና፣ ሉዶልፍ ግዕዝን ያመሳሰለውም ከአረብኛ እንጂ ከሳብኛ አልነበረም። ስለዚህም በኢትዮጵያም ሆነ በደቡብ አረቢያ በድንጋይ ላይ በሳብኛ ከተፃፉት “ሀበሻ” ከሚለው ቃል ጋር ግኙነት ያላቸው ተመሳሳይ ቃላት መኖራቸውን ሉዶልፍ አያውቅም ነበር። እነዚህ ፅሁፎች በኢትዮጵያም በደቡብ አረቢያም ከተገኙ በኋላ የሉዶልፍን ሀሳብ በማጠናከር እንዲሁም ማስተካከያና ተጨማሪ ማብራሪያ በማቅረብ ሀሳቡ እንዲስፋፋ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ዋንኛው ኮንቲ ሮሲኒ (1906) ናቸው።
በኮንቲ ሮሲኒ እና በሌሎች ተመሳሳይ ሀሳብ በሚያራምዱ ፀሀፍት (ሐበሸት የተሰኙ) ሴማዊ ነገዶች ከደቡብ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ገቡ የተባሉበት ዋናዋናዎቹ ምክንያቶች፣ አንድ፣ በሁለቱም ግዛቶች በሳብኛ የተፃፉ የድንጋይ ላይ ፅሁፎች መገኘታቸው፤ ሁለት፣ በኢትዮጵያ የሚነገሩት እነግዕዝ፣ አርጎብኛ፣ ስልጢ ወዘተ. ቋንቋዎች በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ከሚነገሩት ቋንቋዎች በዘር አንድ መሆናቸው፤ ሶስት፣ በደቡብ አረቢያ በድንጋይ ላይ ፅሁፍ ሐበሸት/አሕቡሻን የሚል ሀገርን/ነገድን የሚጠቅስ መገኘቱ (የሚከተለውን ክፍል ይመልከቱ)፤ እና አራት፣ አንዳንድ ባህላዊና የቁሳቁስ መመሳሰሎች በሁለቱም ግዛቶች መገኘታቸው ናቸው።
በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች ከላይ የቀረቡትን ነጥቦች የሚደግፉ ሆነው አልተገኙም። አንድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሴም ቋንቋዎች ከሳብኛም ሆነ ከየትኛውም የደቡብ አረቢያ፣ ሴማዊ ቋንቋ የመጡ/የተወለዱ አይደሉም (ከቀደምት ስራዎች ሀድሰን 1977ን፣ 1978ን እና ሙርቶነን 1967ን፣ 1969ን ይመልከቱ)። በፊት የሚታሰበው ሳባዊ ቋንቋ 500 ቅጋአ አካባቢ ወደኢትዮጵያ ገብቶ በሂደት ግዕዝን አስገኘ ነው። ግዕዝ በበኩሉ በሂደት ሌሎቹን ኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋዎች (እነትግርኛ፣ ክስታንኛ፣ ሀረሪ ወዘተ.ን) አስገኘ ነው። በኢትዮጵያ የሚገኙት የሴማዊ ቋንቋዎች ብዛትና ልዩነታቸው ቢያንስ የአምስት ሺህ አመት ግዜን ይጠይቃል። በተጨማሪም፣ በኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋዎች እና በሳብኛ (እና በሌሎቹ የደቡብ አረቢያ ሴማዊ ቋንቋዎች) መሀከል ያለው ዝምድና በሩቅ ርቀት ነው። የኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋዎች ለነሳባና ለሌሎቹ ጥንታዊ የደቡብ አረቢያ ቋንቋዎች፣ በምሳሌ እንናገርና፣ ልጆች ሳይሆኑ ቅም አያቶቻቸው ናቸው። ሁለት፣ በድንጋይ ላይ ተፅፈው በሁለቱም ወገን (ደቡብ አረቢያና ኢትዮጵያ) በተገኙት ፅሁፎች “ሀበሻ” በሚለው ቃል የተጠቀሱት የኢትዮጵያ ነገዶች ናቸው (በዚህ ስራ የሚከተለውን ክፍል ይመልከቱ)። በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ ምድር የሚገኙ ህዝቦችን ሀበሻ በሚል መጥቀስ ሐበሸት እና አግዓዚ የሚባሉ መጡ ከተባለበት 500 ቅጋአ በፊትም የነበረ ነው (ግላሰር 1895:8)። ሶስት፣ በደቡብ አረቢያ የነበረው ስልጣኔ ኢትዮጵያ ከነበረው በጣም ያነሰ ከመሆኑም በላይ በሁለቱ ስልጣኔዎች/ባህሎች መሀከል ያለው መመሳሰል በጣም ትንሽ ነው። በርግጥ በሁለቱ ህዝቦች መሀከል የባህል ንክኪ/መለዋወጥ ነበር። ሆኖም፣ የአክሱም ስልጣኔ በማያጠያይቅ መልኩ አፍሪካ በቀል፣ የውስጥ እድገት ያስገኘው ስልጣኔ ነው (ስርግው 1972፣ ሙንሮ-ሀይ 1991፣ ፊሊፕሰን 2012)።
3. የሀበሻ ቃል ምንጭ
ሀበሻ ለሚለው ቃል ምንጭ ናቸው ተብለው ከሚገለፁት ሶስት ዋና ዋና መላምቶች ውስጥ አንዱ ከአረብኛው ሐበሽ የመጣ ነው የሚል ነው። ሁለተኛው ከደቡብ አረቢያው ከሳብኛ ሐበሸት ከሚለው ቃል ጋር የተያያዘ ነው። ሶስተኛው በጥንታዊ ግብፅ በፑንት ስለነበሩ ኀበሸተየ ስለተሰኙ ህዝቦች ከሚገልፀው ቃል ጋር ማያያዝ ነው። የአንዱ ትክክል መሆን የሌላው ስህተት መሆን ነው ማለት አይደለም። የአረብኛው፣ ከደቡብ አረቢያው፣ እነዚህ ሁለቱ ደግሞ ከግብፁ ሊገናኙ አይችሉም ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ፣ ከእያንዳንዳቸው ጋር በተያያዘ በየወቅቱ የቀረበ መላምት አለ። በዚህ ክፍል ይህን ሁኔታ በቅደም ተከተል አንድ ባንድ እንመረምራለን።
3.1 አረብኛ
ሀበሻ ከአረብኛ ነው የመጣው የሚለው እሳቤ ከቀደምት ስራዎች ውስጥ በሉዶልፍ (1682) ተጠቅሶ ይገኛል። እንደ ሉዶልፍ እምነት ሀበሻ የሚለው ስያሜ ለኢትዮጵያውያኖች ያወጡላቸው አረቦች ሲሆኑ ትርጉሙም “ዝብርቅርቅ ወይም የህዝብ ቅልቅል” ማለት ነው (ሉዶልፍ 1682:7)። ሀበሻ የሚለው ቃል ግን አረቦችና አረብኛ ከመታወቁ በፊት በጥንታዊ የድንጋይ ላይ ፅህፎችም ስለሚገኝ መነሻው አረብኛ ነው የሚለው ሚዛን የሚደፋ አይደለም። በርግጥ ይህን ሀሳብ ባሁኑ ግዜ የሚያራምድ በምሁራዊ ስራ ውስጥ ማግኘት ይከብዳል። የአረብኛው ቃል አንድም በሂደት ከጥንታዊ ስያሜው ጋር ተቀላቅሎ ወይም አረቦች ቃሉን ከሌሎች (ምናልባትም በተገላቢጦሹ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች) ወርሰውት ሊሆን ይችላል። ትንሽ እናብራራው።
ሙዩለር (2005:948) ሐበሸት በሚለው መጣጥፉ ላይ ከላይ ከቀረበው ጋር የተመሳሰለ አስተያየት አስፍሯል። ይህ ሰው የአረብኛው አል-ሐበሻ ከግዕዙ ሐበሣ ነው የመጣው ይላል። ሆኖም፣ በአረብኛ ይህ ቃል ከስምነት በተጨማሪ በግስነትም ይገኛል። ለዚህ ሁለት መላምት መሰንዘር ይቻላል። አንድም፣ ቃሉ ወደአረብኛ ከገባ በኋላ ከስምነት በተጨማሪ በግስነትም እየገባ ትርጉሙን እና አጠቃቀሙን አስፍቶ ሊሆን ይችላል። አሊያም፣ በአረብኛ በድምፅ ተመሳሳይ ነባር ቃል ኖሮ፣ የህዝብ ስያሜ የሆነው ሐበሸ በውሰት (ወደቋንቋው) ሲገባ፣ ነባሩ ቃል በውሰት ከገባው የህዝብ ስም ጋር በመጋጠም የትርጉም ውህደት በሂደት ፈጥሮ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጉዳይ ላይ ፎግት (2005)ን ይመልከቱ። ሉዶልፍ (1682)፣ ምንም እንኳ የባዛንታይኑ እስጢፋኖስ ስራ ላይ ስላለው አባሴኖኢ ቢያውቅም፣ ሀበሻ ከአረብኛ ነው የመጣው ሲል በወቅቱ ስለጥንታዊ የደቡብ አረቢያ ቋንቋዎች እና ከዚህ ቃል ጋር የሚዛመዱ የሳብኛ የድንጋይ ላይ ፅሁፎች ስለመኖራቸው አያውቅም ነበር።
3.2 ደቡብ አረቢያ
ሀበሻ የሚለው ቃል ከደቡብ አረቢያ ነው የመጣው ለሚለው አስተሳሰብ መነሻ ከዚሁ ቃል የሚመሳሰሉ ቃላት በተለያዩ ፅሁፎች መገኘታቸው ነው። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ከላይ ያነሳነው እዮብ ሉዶልፍ (1682) የጠቀሰው የስድስተኛው ክፍለዘመን የባዛንታይኑ እስጢፋኖስ የገለፀው አባሴኖኢ የሚለው ቃል ነው። በስድስተኛው ክፍለዘመን (ጋአ) የነበረው የባዛንታይኑ እስጢፋኖስ አሁን ጨርሶ ከጠፋው የኡራኒዮስ አረቢካ ከተባለው ፅሁፍ አባሴኖኢ ስለተባለ በደቡብ አረቢያ ከሳብያውያን ጎረቤት ስለሚገኝ ሀገር/ህዝብ ጠቅሷል።
ከላይ እንደገለፅንው ሉዶልፍ (1682:8) አባሴኖኢ ሀበሻ ከሚለው ጋር ግንኙነት እንዳለውና አባሴኖኢዎችም የኢትዮጵያውያኖች/የሀበሾች አባቶች እንደሆኑ ግምቱን ሰጥቷል። ቫልተር ቬ ሙዩለርም (2005:949) ተመሳሳይ ሀሳብ ሰንዝሯል። ሙዩለር ወደኢትዮጵያ የፈለሱ ሀበሻ የሚባሉ ዘሮች የሚገልፅ ነገር አለመኖሩን ቢናገርም፣ ሀበሾች አባሴኖኢ ከሚባለው ቦታ የመጡ ናቸው ይላል። ለዚህ አስተያየቱ ግን ያቀረበው አንዳችም አሳማኝ ማስረጃ የለም። ይህን አስተሳሰብ ሀበሾች ከደቡብ አረቢያ መጡ የሚሉትም እነኮንቲ ሮሲኒ አይቀበሉትም። ኮንቲ ሮስኒ (1906:54) ምንም እንኳ ሀበሾች ከደቡብ አረቢያ የመጡ ህዝቦች ናቸው የሚለውን ሀሳብ ቢያራምድም አባሴኖኢ ከሀበሻ ጋር ይገናኛል እንኳ ከተባለ፣ አባሴኖኢ ከኢትዮጵያ ቅኝ ለመግዛት ከሄዱ ወታደሮች የተመሰረተ ህብረተሰብ ይሆናል ይላል። ኤርቪን (1965:196) ከኮንቲ ሮሲኒ ጋር በመስማማት አባሴኖኢ ከኢትዮጵያ የሄዱ ቅኝ ገዥዎች እዚያው በመስፈር የፈጠሩት ህብረተሰብ ይሆናል የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል። የሐበሻ ህዝብ መጣጥፍም ይህንኑ ሀሳብ ይደግመዋል። እንደዚህ መጣጥፍ ከሆነ አባሴኖኢ የሚለው ስያሜ ከአክሱማይት በንጉስ ካሌብ ግዜ የሄዱ ህዝቦችን የሚመለከት ነው። ንጉስ ካሌብ ደቡብ አረቢያ በ525 ጋአ ዘምቶ ካስገበረ በኋላ አብራሀም የተባለው የጦር አዛዡን እዚያው እንዲያስተዳድር ከበርካታ ጦር ጋር ትቶት ነበር። አብራሀምም በዚያ የሕምያር ንጉስ ሆኖ ከ527 እስከ 565 ጋአ እንደገዛ በታሪክ ይታወቃል (ከብዙ በጥቂቱ ስርግው 1972ን፣ ጆርጅ ሀትኬ 2012ን፣ ባወርሳክ 2013ን ይመልከቱ)።
ይሁን እንጂ አባሴኖኢ ከኢትዮጵያ ከሄዱ ቅኝ ገዢዎች እዚያው የቀሩ ህዝቦች ሊሆኑ ቢችሉም በንጉሥ ካሌብ ግዜ ከሄዱት ሊሆን ይችላል የሚለው የሀበሻ ህዝብ መጣጥፍ መላምት ብዙም አሳማኝ አይደለም። የባዛንታይኑ እስጢፋኖስ በስድስተኛው ክፍለዘመን ቢፅፈውም ለፅሁፉ ምንጭ የሆነው፣ ከላይ እንደገለፅንው፣ አሁን የጠፋው የኡራኒዮስ አረቢካ የተባለው ፅሁፍ ነው። የኡራኒዮስ አረቢካ መቼ እንደተፃፈ እርግጡን መናገር ቢያስቸግርም ያለው ግምት ከስድስተኛው ክፍለዘመን በጣም ቀደም ብሎ ንጉስ ካሌብ ከመነሳቱ በፊት እንደሆነ ይገመታል። ስለዚህም አባሴኖኢ ከኢትዮጵያ የሄዱ ህዝቦች ከሆኑ ይህ ሊሆን የሚችለው ከንጉስ ካሌብ ቀደም ብሎ በተደረገ ዘመቻ መሆን አለበት። በርግጥ ከአንደኛው ክፍለዘመን ጋራ አቆጣጠር (ጋአ) ጀምሮ አክሱማውያን ባህር ተሻግረው ደቡብ አረቢያኖችን ያስገብሩ እንደነበር ይነገራል። ለዚህ የስድስተኛው ክፍለዘመን ኮስማስ የተባለው የግብፁ መነኵሴ አዱሊስ ላይ ያገኘው ሞኑመንተም አዱሊስ በሚል እስካሁን የሚታወቀው በዕምነበረድ ላይ በግሪክ የተቀረፀ ፅሁፍን መጥቀስ ይቻላል (ማክሪንድል 1897)። ይህ ፅሁፍ አሁን ቢጠፋም ኮስማስ ክርስትያን ቶፖግራፊ የሚለው ስራው ላይ ገልብጦ ይዘቱን ለታሪክ አቆይቶልናል። ኮስማስ ሞኑመንተም አዱሊስ ላይ ያገኘውን እንደአሰፈረው፤ የዚህ ፅሁፍ የአክሱም ንጉስ በመጀመሪያ በአካባቢው ያሉትን ግዛቶች (እነአጋሜን)፣ ከዚያም በሁሉ አቅጣጫ በመዝመት ያሁኒቱ ኢትዮጵያን አብዛኛ ግዛቶች፣ ሱዳንን እና ሱማሊያን አስገበረ። ከዚያም፣ ባህር በመሻገር በደቡብ አረቢያ እነሳባን እና በባህር ጠረፎች አካባቢ ያሉ ሌሎች ግዛቶችን ማስገበሩን ይገልፃል (ማክሪንድል 1897:55 እና ቀጣይ ገፆች)። ይህ የአክሱም ንጉስ፣ በአንዳንድ ስራዎች የተለያየ ግዜ ቢሰጠውም፣ አሁን ተቀባይነት ያለው በመጀመሪያው ክፍለዘመን (ጋአ) የነበረ መሆኑን ነው። ሌላው፣ ከሶስተኛው ክፍለዘመን መነሻ አካባቢ ጀምሮ ኢትዮጵያውያኖቹ በደቡብ አረቢያ እንቅስቃሴ ያደርጉ እንደነበር በግልፅ ይታወቃል (ከብዙ በጥቂቱ ስርግው 1972ን፣ ሙንሮ-ሀይ 1991ን፣ እና ባወርሳክ 2013ን ይመልከቱ)። ለዚህ አስረጂ፣ ከታች እንደምንመለከተው፣ ስለንጉስ ገደረት (200-230 ጋአ) እና ንጉስ አጽብሀ (230-250 ጋአ) በድንጋይ ላይ በደቡብ አረቢያ የተፃፉ ፅሁፎችን መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህ ለምሳሌ ስለንጉስ ገደረት ከተፃፉት CIH 318ን እና Ja 631ን፣ እንዲሁም ስለንጉስ አጽብሀ Ja 576ን ይመልከቱ።
እስጢፋኖስ ከጠቀሰው አባሴኖኢ በተጨማሪ በደቡብ አረቢያ እና በኢትዮጵያ በድንጋይ ላይ (አናባቢ በሌለው ፅሁፍ) ከሀበሻ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሐበሸተ ወይም ተመሳሳይ የሆኑ ቃላት ከላይ ከገለፅናቸው ሌላ ተገኝተዋል። ከሀበሻ ጋር ዝምድና ያለውን ቃል የያዘ በኢትዮጵያ የተገኘው ቀደምቱ የድንጋይ ላይ ፅሁፍ በኢዛና ግዜ የተፃፈው ነው። የኢዛና የድንጋይ ላይ ፅሁፍ ድል ያደረገበትንና የሚያስተዳድራቸውን ግዛቶች ሲዘረዝር፣ በግሪክ ኢትዮጵያ ያለውን (DAE 5/2-3)—አናባቢ በሌለው ፅሁፍ— በግዕዙ ሐበሠተ (ħbśt) (DAE 6/1) እና በሳብኛ ደግሞ ሐበሸተመ (ħbštm) (DAE 7/1) ብሎታል።
በድንጋይ ላይ በተፃፉ ፅሁፎች ሀበሻ ከሚለው ጋር ግንኙነት ያላቸውን ቃላት በብዛት የምናገኘው በደቡብ አረቢያ በሚገኙት ላይ ነው። እነዚህ ቃላት አናባቢ በሌለው ፅሁፍ ሐበሸተ (ħbšt) እና አሐበሸነ (ʔħbšn) የሚሉ ናቸው። ኤርቪን የነዚህን ቃላት አገባብ ከበርካታ የድንጋይ ላይ ፅሁፎች ከመረመረ በኋላ፣ በሚከተለው ክፍል እንደምንመለከተው፣ በደቡብ አረቢያ ሐበሸተ የሚለው ቃል ባብዛኛው የሚያመለክተው ቦታን/ሀገርን ሲሆን፣ ህዝብን የሚያመለክተው ደግሞ፣ አሐበሸነ የሚል እንደሆነ ይገልፃል (ኤርቪን 1965፡192)። ሐበሸተ እና አሐበሸነ በብዛት ከሚገኙባቸው የሳብያን የድንጋይ ላይ ፅሁፎች ውስጥ CIH 308፣ Ja 631፣ Ja 574፣ Ja 575፣ Ja 576፣ እና Ja 577 ዋናዋናዎቹ ናቸው።
(ምስል 1፡ CIH 308)
ኤርቪን (1965፡190) እንዳስተዋለው ሐበሸተ ስለተባለው ቦታ በቀደምት ስራዎች ያለው መረጃ አጥጋቢ ስላልነበረ በየስራዎቹ የቀረበው ትንታኔ የተለያየ ነበር። ኤርቪን ለዚህ አስረጅ በግላሰር (1895)፣ ሊትማን (1913)፣ እና ኮንቲ ሮሲኒ (1906) የተሰጡትን መላምቶች ይጠቅሳል። ግላሰር (1895) ሁሉም ጥንታዊ ፅሁፎች የሚያመለክቱት ደቡብ አረቢያን ነው ሲል፣ ሊትማን (1913) ግን ሁሉም የሚያመለክቱት ኢትዮጵያን እንደሆነ ይገልፃል። ኮንቲ ሮሲኒ እና ከሱ በኋላ የመጡ ፀሀፊዎች አንዳንዱ ኢትዮጵያን አንዳንዱ ደግሞ ደቡብ አረቢያን ነው የሚያመለክቱት የሚል የተወዛገበ ነገር ነው ያቀርቡ የነበረው (ኤርቪን 1965:190)። ኤርቪን ከነኮንቲ ሮሲኒ ስራዎች በኋላ የተገኙትን የድንጋይ ላይ ፅሁፎችን ከገመገመ በኋላ ሐበሸተ የሚለው ቃል (ሀገርን በማያጠራጥር የሚያመለክት አገባብ ባለው ቦታ ሁሉ) የሚያመለክተው ኢትዮጵያን ሲሆን፣ እንደዚሁ አሐበሸነ ደግሞ የሚያመለክተው በሐበሸተ የሚኖሩ ህዝቦችን እንደሆነ ይገልፃል (ኤርቪን 1965:192)። ይህን አስመልክቶ እዚህ ሰፋ አድርጎ ኤርቪንን መጥቀሱ አስፈላጊ ይመስለናል፤
There is little or no reason to suppose that any case of ħbšt or ‘ħbšn refers to a South Arabian tribe or district. Even with the occasional case where there might be some doubt, it would be very difficult to argue for setting it off and positing a South Arabian locale for it alone. The several alliances or attempts at such between Aksum and Saba’ or Himyar show that the Abyssinian presence in Arabia was largely in the capacity of allies and the varying locations in which they were active at different times is best explained in this light. One might also propose that the prominence suddenly accorded to them in the texts reflects their impact as foreign invaders on the local peoples. The equation of ħbšt with Abyssinia is moreover the most natural one. The onus of proof really lies with those who maintain otherwise and there is little doubt that the earlier views of Glaser and Conti Rossini were largely founded on a priori assumptions, if not wishful thinking. The fact that early Abyssinian culture almost certainly was transmitted to the country from Arabia does not warrant the assumption that the people who took it over had the same name, or came from a district with the same name as Abyssinia itself (Irvine 1965:194-5).
የኤርቪንን ጥናት የሚያፈርስ አዲስ የተገኘ የድንጋይ ላይ ፅሁፍም ሆነ ሌላ መረጃ እስካሁን ድረስ ስለመኖሩ የምናውቀው የለምና እዚህ የኤርቪንን ግምገማ መድገሙ አግባብ አይመስለንም። ስለዚህም፣ የተወሰኑ ነጥቦችን ብቻ ጠቅሰን እናልፋለን።
ስለሀበሻ የሚገልፁ የድንጋይ ላይ ፅሁፎች በደቡብ አረቢያ መታየት የጀመሩት ከ3ኛው ክፍለዘመን ጋአ ጀምሮ ነው። የመጀመሪዎቹ ስለንጉስ ገደረት/ገደረ (200-230 ጋአ) እና ሀበሻ የሚገልጹ ይገኝባቸዋል። ለምሳሌ Ja 631/13: gdrt/mlk/ħbšt/wʔksmn/ ‘ገደረት፡ የሐበሻ እና የአክሱም ንጉሥ’፣ Ja 631/12-13: ʔrd/ħbšt/ ‘የሐበሸት ሀገር/ምድር’፣ Ja 574/5: ʔħzb/ħbšt/ ‘የሐበሸት ጦር’ የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል። ንጉስ ገደረት በደቡብ አረቢያ ጦር ልኮ መዋጋቱን ብቻ ሳይሆን እዚያው ጦር ማስፈሩም ይታወቃል። ስለዚህ ንጉስ CIH 308ን ይመልከቱ። አንድ የሕምያሪቴ ሹም ከገደረት በማስከተል ለነገሰው የአክሱሙ ንጉስ አፅብሐ (ʔs’bh) (230-250 ጋአ)[1] ሳባዎችን ለመውጋት ትብብር እንዲያደርግለት የጠየቀበት ፅሁፍ ይገኛል (Ja 576ን ይመልከቱ)። በወቅቱ ሀበሾች ከሳቢያኖች ጋር ጎን ለጎን ቀይባህርን ተሻግረው ይኖሩ ነበር። የአራተኛው ክፍለዘመን ታላቁ ኢዛና ግዛቶቼ ብሎ ከዘረዘራቸው ዘጠኙ ሀገሮች/ክፍለሀገሮቹ ውስጥ የደቡብ አረቢያው ሕምያር፣ ሳባና፣ ራይዳን ይገኙበታል (DAE 5/6/7)። የመጨረሻው በደቡብ አረቢያ በሳባዊ የድንጋይ ላይ ፅሁፍ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያኖችን የሚገልፀው በ540 ጋአ በንጉስ ካሌብ ጀነራል በነበረው አብራሀ የተፃፈው ይመስላል። የካሌብ ጀነራል የነበረው አብራሀም በኋላ ላይ እራሱን በደቡብ አረቢያ የሕምያር ንጉስ (527 – 565 ጋአ) አድርጎ ሾሞ ነበር። ይህ ንጉስ የመረብን ግድብ ለመጠገንና በዚያ አካባቢ የተነሱበትን ተቃዋሚዎች ለመምታት ከሐበሸት እና ከሕምያር ጦር ማሰባሰቡን በCIH 541 የድንጋይ ላይ ፅሁፍ ገልጿል። ስለዚህ ንጉስ ከሚጠቅሱ ሌሎች የድንጋይ ላይ ፅሁፎች ውስጥ Ry 506 እና Ja 546 ይገኙበታል።
በደቡብ አረቢያ ላይ ከተገኙ የድንጋይ ላይ ፅሁፎች ማረጋገጥም እንደሚቻለው ኢትዮጵያውያኖች ደቡብ አረቢያን ቢያንስ ከሶስተኛው ክፍለዘመን ጀምሮ በተደጋጋሚ በመውረር ከነሳባውያን እና ከሕምያርቲዎች ጋር መዋጋት ብቻ ሳይሆን ጦራቸውንም እዚያው በማስፈር የራሳቸውን ማህበረሰብ እስከመፍጠር ደርሰው ነበር። እነዚህ ህዝቦችን አሐበሸነ፣ የሚገኙበትን/ የሚኖሩበትን ቦታ ደግሞ ሐበሸተ በማለት ሲጠቅሱ ይስተዋላል። ባጠቃላይ በድንጋይ ላይ በኢትዮጵያና በደቡብ አረቢያ ተፅፈው በተገኙት ፅሁፎች ሐበሸተ ወይም ከዚህ ስር የወጡ ቃላት ሁሉም የሚያመለክቱት ኢትዮጵያውያንን/አክሱማውያንን ወይም ከኢትዮጵያ የሄዱ ህዝቦችን ነው (ኤርቪን 1965:186)። አንድም የድንጋይ ላይ ፅሁፍ ሀበሻ በደቡብ አረቢያ የሚገኝ ነገድ ሆኖ ከዚያ ወደኢትዮጵያ የተሰደደ ስለመሆኑ ማረጋገጥ አልቻለም። በተለይ ከኤርቪን ስራ በኋላ ሀበሻ ከደቡብ አረቢያ የመጣ ነገድ ነው የሚለው በትምህርታዊ/ምርምር ስራዎች የሚያራምድ ማግኘት በጣም ይከብዳል።
3.3 ግብፅ
በዚህ ክፍል መግቢያ ላይ እንደገለፅንው ሀበሻ ከሚለው ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው ሶስተኛው በግብፅ የተገኘው ኀበሰተየ (ḫbstῗ) የተሰኘው ቃል ነው። በዚህ ደረጃ በጣም የሚታወቀው፣ የግብጿ ንግስት ሀትሼፐሰት ‘Queen Hatshepsut’ (1508-1458 ቅጋአ) በፑንት ሀገር ሀበሻ ስለሚባሉ ህዝቦች መጥቀሷ ነው። ፑንት የሚባለው ሀገር የአሁኗን ኤርትራን፣ ኢትዮጵያን፣ ጅቡቲን፣ እና ሱማሊያን በብዙ ስራዎች እንደሚጨምር ይገለፃል። አንዳንዶች ከቀይባህር ማዶ ያለውንም በተለይ የደቡብ አረቢያን የባህር ጠረፍ አካባቢ ሁሉ ሀገራትን ያካትታል የሚሉ አሉ። እንደፊሊፕሰ (1997) ከሆነ ግን ፑንት የአሁኒቱን ኤርትራ እና ኢትዮጵያን እንጂ ሱማሊያንም ሆነ ባህር ማዶ ያሉትን የአረቢያ ሀገሮችን አይጨምርም። ጥንታዊ ግብፆች ከኢትዮጵያ ጋር በታሪክ ከሚታወቀው የንጉስነት ግዛት ከመመስረቻው ጀምሮ ግንኙነት እንደነበራቸው ይገመታል። የዚህ አንደኛው ምክንያት ጥንታዊ ግብፆች ይጠቀሙባቸው ከነበሩት ውስጥ አንዳንዶቹ የአሁኒቷ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ቦታዎች የሄዱ ምርቶች መሆናቸው ነው። ለምሳሌ፣ ለአንዳንድ መስታወት ስራና ለጌጣጌጥ የሚጠቀሙበት ባልጩት ኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ሆኖ ተገኝቷል። ሌላው ከርቤ አንድም ከኢትዮጵያ ወይም ከአጎራባች ሀገሮች የሄደ መሆኑን መናገር ይቻላል። ስለፑንት የሚገልፁ ከ2500 ቅጋአ እስከ 600 ቅጋአ ድረስ በግብፅ የተለያዩ መረጃዎች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ወደ እዚህ ፑንት ወይም የእግዚአብሔር ሀገር ብለው ወደሚጠሩት ስላደረጉት ጉዞ በስፋት ተመዝግቦ የምናገኘው በንግስት ሀትሼፐሸት (1508-1458 ቅጋአ) ግዜ ነው። በዚች ንግስት መቃብር የተገኘው ፅሁፍ ይህን ከመግለፁም በላይ በምስል ሲሄዱና ሲመለሱ የነበረውን ጉዞ ያሳያል (ከብዙ በጥቂቱ ፊሊፕስ 1997ን እና በዚያ የተጠቀሱ ስራዎችን፣ ፓንክረስት 1997ን፣ ስርግው 1972ን፣ እና ሙንሮ-ሀይ 1991ን፣ እንዲሁም በአማርኛ ከተፃፉ ስራዎች ደግሞ ተክለፃዲቅ መኩሪያን 1951ን፣ እና አባ ጋስፕሪን ይመልከቱ)።
ንግስት ሀትሼፐሸት መቃብር ላይ በተገኘው ፅሁፍ ኀበሰተየ (ḫbstῗ) የሚል ቃል ነበር። ይህ ቃል፣ በግብፅ ደቡብ የሚገኙ ከርቤና እጣን የሚመርትበት “የፑንት ሀገር ህዝቦችን” የሚገልጽ ነው (ሙዩለር 1893)። ሙዩለር ይህን ቃል በብዙ ቦታዎች ገብቶ እንዳገኘው ይገልፃል። ከነዚህም መሀከል የሚከተሉትን ሀረጎችን መጥቀስ ይቻላል፤ የሀበሻ ሀገር ህዝቦች ‘die Leute der Gegende von Ḫbst’፣ የ(ግብጽ) ሰዎችን የማያውቁት ፑንቶች (በፑንት ያሉት)፣ የእግዚአብሄር ሀገር ሀበሾች ‘die puntῗ, die nichit die Menschen (d. h. Ägypter) kannten, die […] ḫbstῗ des Gotteslandes’ (ሙዩለር 1893:116)። የሙዩለር (1893) ግኝትን ተመርኩዞ ሰፊ ትንታኔ ያቀረበው ግላሰር (1895) ነው። ግላሰር ሀበሾች በአረቢያና በአፍሪካ ‘Die Abessinier in Arabien und Afrika’ በሚለው መፅሀፉ በግብፅ የተገኘው ኀበሰተየ፣ ሀበሻ ከሚለው ጋር ግንኙነት እንዳለው ለማሳየት ሞከረ። እንደግላሰር ከሆነ ጥንት ሀበሻ (ወይም የዚህ ቃል ዝርያ) ለበርካታ ህዝቦች መጠሪያነት ይውል ነበር። ይህ ቃል በኢትዮጵያ ላሉ ብቻ ሳይሆን በሱማሊያ፣ እንዲሁም በደቡብ አረቢያ ላሉ የጠረፍ ህዝቦች መጠሪያ ነበር። ይህ እምነቱ፣ (1) ፑንት የሚለው የምስራቅ አፍሪካን ጠረፍ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ደቡብ አረቢያንም ያካትታል ከሚል፣ (2) ከላይ የገለፅንው በንግስት ሀትሼፕሸት የተገለፀው ኀበሰተየ የሚለው ቃል እና በደቡብ አረቢያ የተገኘው ሐበሸተ/አሐበሸን ከአማርኛው ሀበሻ (እና ከግዕዙ ሐበሣ) ጋር ይገናኛል ከሚል እና (3) በደቡብ አረቢያና በኢትዮጵያ መሀከል ያለው የቋንቋ ዝምድናን መሰረት በማድረግ ነው። የዘመናችን ሙዩለር (2005:948) ደግሞ የጥንታዊውን በግብፅ የተገለፀውን ከአሁኑ ሀበሻ ጋር ማገናኘት ከባድ ነው ይላል። ለዚህ ምክንያቱ የግብፁ ፅሁፍ በጣም የቆየ ስለሆነ ነው። ይህ የሙዩለር አስተያየት ግን ከተራ ጥርጣሬ በላይ የሚቆጠር አይደለም። የግብፁ ፅሁፍ በ1460 ቅጋአ አካባቢ እንደተፃፈ ይገመታል። ሀበሻ የሚለው ቃል በድንጋይ ላይ በሳባና በግዕዝ ከተፃፈው ከቀደምቱ ያለው ልዩነት ወደ 1500 አመት ገደማ ነው። ይኸው ቃል ከድንጋይ ላይ በሳብኛ እና በግዕዝ ከተፃፈው ነው የመጣው እንኳ ብንል ከዚያን ግዜ ጀምሮ ያለው ግዜ ከ1700 አመት በላይ ነው። የዘመን ርቀት ቃሉን ማጥፋት ቢችል ኖሮ አሁን ይህ ቃል ባልነበረ ማለት ነው።
በደቡብ አረቢያ የድንጋይ ላይ ፅሁፎች የተገኘው ሐበሸተ (የሱ ዝርያ አሐበሸነ) የሚያመለክተው ኢትዮጵያኖችን እስከሆነ ድረስ እና የግብፁም ቃል ኀበሰተየ የሚያመለክተው ያንንው ህዝብና ሀገር እስከሆነ ድረስ በዘመን ርቀት ፅሁፎቹ ስለተራራቁ ተብሎ (ቃላቱ በግልፅ በድምፅ መመሳሰላቸው እየታወቀ) አንድ አይደሉም ማለቱ ብዙም አሳማኝ አይደለም።
ሀበሻ የሚለው ቃል መነሻው ጥንታዊ ከሆነ (የፑንት ህዝቦች ሲገለፁበት የኖረ ከሆነ) ለምን በፑንት ውስጥ ለመኖራቸው የማያጠራጥሩ ሱማሌዎች እና ሌሎች በቀይባህር ጠረፍ የሚገኙ ህዝቦች እራሳቸውን ሀበሾች ሲሉ ባሁኑ ወቅት እምብዛም አይታይም የሚል ጥያቄ እዚህ ሊነሳ ይችላል። ለዚህ ጥያቄ አፍ ሞልቶ ትክክለኛው መልሱ ይህ ነው ማለት ባይቻልም ልንገምት የምንችለው ግን አለ። አንደኛው ቃሉ ከመሰረቱ ምናልባት በጠረፍ ያሉትን ህዝቦች ሳይሆን ገባ ብለው የሚገኙትን የሚያመለክት ይሆናል። ሁለተኛው ግን ቃሉ የጠረፉ ህዝብ ሲጠቀምበት ኖሮ የእስልምና መስፋፋት ሲጀምር ቀስ በቀስ ስርጭቱ እየቀነሰ መጥቶ ሊሆን ይችላል።
3.4 ግዕዝ
ሀበሻ የሚለውን ቃል አማርኛና ትግርኛ በቀጥታ ከግዕዝ የወረሱት ነው የሚል በተለያዩ ስራዎች እናገኛለን (ለምሳሌ ሙዩለር 2005:948ን ይመልከቱ)። በግዕዝ ይህ ቃል ሐበሣ(ተ) ነው። የግዕዝ ሠ /ś/ በድምፅ ረገድ ለአማርኛው ሸ /š/ ይቀርባል። ይሁን እንጂ አማርኛ ከግዕዝ ሠ ያላቸው ቃላትን ሲወርስ በሙሉ ሰ /s/ እንጂ ሸ /š/ አድርጎ አንዴም አያውቅም። ለምሳሌ ቀደምት ከግዕዝ ወደ አማርኛ ከተወረሱ ቃላት ውስጥ የማንጠራጠረው ንጉስ ነው። ይህ ቃል ወደአማርኛ የገባው ግዕዝ የንግግር ቋንቋ እያለ ነው ብለን ለመገመት የሚያስችል በርካታ ምክንያት አለን። ይህ ቃል በግዕዝ ንጉሥ /nɨguś/ ነው። አማርኛ በቀጥታ የራሱ የሆኑ ቃላትን፣ ማለት ከማንም ያልወረሳቸውን፣ ብንመለከት በግዕዝ ሠ /ś/ ያለባቸው በአማርኛ ሰ /s/ ሆነው እናገኛለን። ለምሳሌ ስምን መጥቀስ ይቻላል። በግዕዝ ይህ ቃል ሥም /śɨm/ ነው። የትግርኛው ሽም /šɨm/ ለግዕዙ ይቀርባል። የግዕዙ ሠ /ś/ በትግርኛ ሸ /š/ የሚሆንበት አጋጣሚ ቢኖርም ሁሌም ይህ አይሆንም። የዚህ አንድምታው ግልፅ ይመስለናል። ሀበሻ የሚለውን ቃል አማርኛ ከግዕዝ አልወረሰም ነው። ይህ እውነታ ቃሉ በአማርኛ ካለው አጠቃቀም ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። በሚከተለው ክፍል እንደምንመለከተው፣ አማርኛ ሀበሻን የሚጠቀመው (1) ህዝብን ለማመልከት እና (2) ሀገር በቀል የሆኑ ነገሮችን ለመግለፅ ነው። የአማርኛ ተናጋሪ ይህን ቃል ሲጠቀም እራሱን ሁሌም አባል አድርጎ ነው። አማርኛ ሀበሻ የሚለውን ቃል ከግዕዝ ወርሶ ቢሆን ኖሮ የዚህ አይነቱ አጠቃቀም የሚኖርበት አጋጣሚም በጣም ትንሽ ነበር።
4. የሀበሻ ቃል አገባብ/አጠቃቀም
ሀበሻ የሚለው ቃል በአማርኛ እና በትግርኛ ተናጋሪው ዘንድ ያለው አጠቃቀም አንደኛው በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ያለን ህዝብ የሚያመለክት ነው። ለአማርኛ ተናጋሪውም ሆነ ለትግርኛው ተናጋሪ ሀበሻ ማለት ኢትዮጵያዊ/ኤርትራዊ ማለት ነው። አንድን ከተሜ ቀመስ ያልሆነ አማርኛ ወይም ትግርኛ ተናጋሪን አንድ ኢትዮጵያዊ ሀበሻ አይደለሁም ቢለው ወዲያው የሚያስከትለው ጥያቄ “እና ፈረንጅ ነኝ ልትል ነው?” የሚል ነው። ሁለተኛው አጠቃቀም ሀገር-በቀል የሆነውን ነገር ከውጭ ከሆነው ለመለየት ነው። ለዚህ ምሳሌ የሀበሻ ልብስ፣ የሀበሻ ላም፣ የሀበሻ ዶሮ፣ የሀበሻ ምግብ፣ የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል። በትግርኛም ናይ ሀበሻ ዶርሆ ‘የሀበሻ ዶሮ’፣ ናይ ሀበሻ ክዳን ‘የሀበሻ ልብስ’፣ ናይ ሀበሻ ምግቢ ‘የሀበሻ ምግብ’ ወዘተ. ልክ እንደአማርኛው ይባላል።
በግዕዝ ለዚህ ቃል በመዝገበ ቃላት የተሰጠውን ፍቺ ወደጎን በመተው ወደኋላ ሄደን አስቀድመን የጠቀስነውን የኢዛናን የድንጋይ ላይ ፅሁፍ ብንመለከት፣ ሐበሠተ (DAE 6/1) የሚለው በግሪኩ ኢትዮጵያ (Αιθιοπων) (DAE 5/2-3) ነው። በዚህ አገባቡ የሀገር ስም ሆኖ ይመስላል። በኪዳነወልድ ክፍሌ (1948)ም ሆነ በሌስላው (1991) የግዕዝ መዛግብተቃላት የዚህን ቃል ፍቺ ለማግኘት አልቻልንም። ግዕዝ ሐበሣን በሁሉ አገባቡ ቦታ/ሀገርን ብቻ ለማመልከት ከአማርኛ እና ከትግርኛ በተቃራኒ ነው የሚያውለው ለማለት የሚያስችለን ተጨማሪ መረጃ ለግዜው የለንም።
ሀበሻ ወይም ከዚህ ቃል የወጡ በውጭ ቋንቋዎች ለሁለት ነገሮች ሲውሉ ይስተዋላል— አንድ፣ ለቦታ ስያሜ እና ሁለት፣ ለህዝቦች መጠሪያ። ምንም እንኳ ኢትዮጵያውያኖች ሀገራቸውን ኢትዮጵያ ማለት ቢመርጡም፣ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ፣ ባብዛኛው የአለም ክፍል ኢትዮጵያን አቢሲኒያ በሚል ነበር የሚያውቃት። አቢሲኒያ የሚለው መጠሪያ ከዚሁ ከሀበሻ የመጣ ነው። ቱርኮች መላ ሀገሪቱን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት በየጊዜው በጦርነት እየተሸነፉ ባይሳካላቸውም በሰሜኑ ክፍል ብዙ ግዜ ማጥቃት ብቻ ሳይሆን በተለይ በምፅዋ አካባቢ ሰፍረው እንደነበር ይታወቃል። ይህ በነሱ ቁጥጥር ለተወሰነ ወቅት የነበረው ቦታ ሀቤሽ በሚል ይታወቅ ነበር።
ሌላው ሉዶልፍ ሀበሾች ከደቡብ አረቢያ ነው የመጡት ለሚለው ያቀረበው በስድስተኛው ክፍለዘመን ፀሀፊ የተጠቀሰው አባሴኖኢ የተባለው በደቡብ አረቢያ የነበረው ቃል ነው። የሀበሻ ህዝብ መጣጥፍ አባሴኖኢ የቦታን/የሀገርን ስም እንደሚያመለክት ሀርማን ፎን ቪስማንን በመጥቀስ ያቀርበዋል፤ “ሀርማን ፎን ቪስማን አባሴኖኢ ጃባል ሁቢያሽ በሚባለው አውራጃ/ክፍለሀገር ዝናብ በሚበዛበት ተራራማ አካባቢ ካሁኑ ኢብብ በሰሜን-ምዕራብ በኩል እንደሆነ ገልጿል”። የሀበሻ ህዝብ መጣጥፍ ሐበሸ /ħbš/ ከሚለው ስር የወጡ ስያሜዎችን የያዙ ሌሎች በምዕራብና በደቡብ-ምዕራብ የመን የሚገኙ የቦታ ስያሜዎችም እንዳሉ ይገልፃል። “ከነዚህ ውስጥ ጃባል ሐባሺ የተባለው በሑገሪያ ምዕራብ ክፍል ያለው ወረዳ ይገኛል። ይህ ክፍል በአሁኑ ደቡብ-ምዕራብ ታዒዝ ይገኛል” (ምንጭ፡ የሐበሻ ህዝብ)። በዚሁ መጣጥፍ አባሶሴኖኢ የህዝብ ስም እንደሆነ አድርጎ አቅርቦትም እናገኛለን፤ “በስድስተኛው ክፍለዘመን (ጋአ) የነበረው የባዛንታይኑ እስጢፋኖስ ከሳብያውያን ጎን ከሀድራሚውያን ጋር በደቡብ አረቢያ የሚኖሩ አባሴኖኢ የሚባሉ ህዝቦች እንዳሉ ጠቅሷል። አባሴኖኢ ያሉበት ቦታ ከርቤ፣ እጣን፣ እና ጥጥ ያመርታል። […] ይህ ሀገር በባህር ጠረፉ ከሚገኘው ሜዳ፣ ከዘቢድ ተነስቶ ወደ ሕምያሪት መናገሻ ወደነበረችው ዛፋር በሚወሰደው መንገድ ላይ ይገኛል”። የዚህ አይነቱ ለአንድ ቃል የተለያየ ፍቺ መስጠት በብዙ ስራዎች ይታያል።
ኤርቪን (1965:186-7) እንዳስተዋለው የሀበሻ ቃል አገባብ በቀድምት ስራዎች ሁሉ ግልፅ ነበር ማለት አይቻልም። አንዳንዶቹ የቦታ ስም ሲያደርጉት አንዳንዶቹ ደግሞ የህዝብ ስም አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። “ለምሳሌ ግላሰር ሁለቱንም ሳይለይ ሲጠቀምበት፣ ኮንቲ ሮሲኒ የህዝብ ስያሜ ብቻ በማድረግ አውሎታል” (ኤርቪን 1965:186)። በአንዳንድ ስራዎች መቀላቀል ቢኖርም፣ እንደኤርቪን ከሆነ በአረብኛ እና በሳብኛ ህዝቡን እና ሀገርን ለማመልከት የሚጠቀሙት አንድ ቃል አልነበረም። በጥንታዊ አረብኛ (Classical Arabic) አንዱን ከአንዱ መቀላቀል ቢኖርም አል-ሐበሽ ህዝቡን በተመለከተ፣ አል-ሐበሻ ደግሞ ሀገሩን ለማመልከት ይውል ነበር። በደቡብ አረቢያ ፅሁፎችም ሐበሸተ ሀገርን/ቦታን ባብዛኛው የሚያመለክት ሲሆን ህዝብን ደግሞ የሚያመለከትው አሐበሸነ ነው።
በኢዛና የድንጋይ ላይ ፅሁፍ የተጠቀሰውን አከራካሪ ነገር ወደጎን በመተው ሌላውን ብንመለከት፣ በክፍል ሁለት እንደገለፅንው፣ አንዳንድ ፀሀፊዎች ሀበሻ የሴማዊ ህዝብን ብቻ የሚመለከት ነው ሲሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ደጋማውን የክርስትያን ህዝቦችን የሚመለክት ነው የሚል አስተያየት ያቀርባሉ። ሆኖም ከላይ ከገለፅንው በአማርኛና በትግርኛ ካለው አጠቃቀም በተጨማሪ፣ ከሀገራችን ውጭም ሀበሻ ወይም የዚህ ቃል ዝርያቃላት ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ለማመልከት በታሪክ ውለው እናገኛለን። ለምሳሌ ወደ ጀርመን ሄዶ የነበረው የኦሮሞው ተወላጅ አማን ካርል ሀበሽ የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር። የትውልድ ስሙ አማን ጎንዳ ነበር (ፊርላ 2005:949)። በእስልምና የመጀመሪያ የፀሎት ጥሪ አድራጊ ነበሩ የሚባሉት ቢላል ኢብን ራባህ፣ ቢላል አልሐበሺ በመባልም ይታወቁ ነበር። አረቦች ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ (እስላሙን ሆነ ክርስትያኑን) አል-ሐበሺ ማለት ይቀናቸዋል። በህንድ፣ በፓኪስታን እና በዚያ አካባቢ ቃሉ የሚመለክተው ከኢትዮጵያም አልፎ ባጠቃላይ ከምስራቅ አፍሪቃ የሄደውን ህዝብ ሁሉ ነው (ፓንክረስት 2003)። በደቡብ አረቢያ/በየመን በርግጥ ከሀበሻ ጋር በተገናኘ ቃል የሚጠሩ ህዝቦች እስካሁን አሉ። እነዚህ ህዝቦች ባሁኑ የመን ታዓዚ በተባለው ሀገር እንደሚገኙ የሀበሻ መጣጥፍ ይገልፃል፤ “የዚህ አካባቢ ነዋሪዎች እስካሁን አል-አሕቡሽ ይባላሉ። አል-አሕቡሽ የሐባሽ ብዙ ቁጥር ቅርፅ ነው” (ምንጭ፡ የሐበሻ ህዝብ)። እነዚህ ህዝቦች ባለፈው ክፍል እንደገለፅንው ከኢትዮጵያ በአክሱማውያን ግዜ ከሄዱ ወታደሮችና ቤተሰቦቻቸው እዚያው የቀሩ እንደሆነ ይገመታል።
የሀበሻ አጠቃቀም/አገባብ በማናቸውም ግዜ አንድን ነገድ ብቻ ነጥሎ ለማመልከት የዋለበት ግዜ በታሪክ ማግኘት ይከብዳል። ይሁን እንጂ ቃሉ በሁሉም ዘንድ አንድ አይነት አጠቃቀም አለው ማለት አይቻልም። ምንም እንኳ በህንድ እና አጎራባች ሀገሮች ቃሉ ከመላው ምስራቅ አፍሪካ በተለያዩ ወቅት ሄደው እዚያው የሰፈሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማመልከት ቢውልም በምስራቅ አፍሪካ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ውጭ በዚህ ቃል ራሱን የሚገልፅ ነገድ የለም። ለምሳሌ፣ ሱማሌዎች ሀበሻ የሚሉት የደጋማውን ክፍል ክርስትያን ህብረተሰብን ብቻ ነው።
ሀበሻ የሚለው ቃል በሁሉ ቦታ መግባቱና የተለያየው የአለማችን ህዝብ ከጥንት ጀምሮ በዚህ ቃል ኢትዮጵያውያንን መጥራቱ የሚያሳየን ቃሉ ጥንታዊ፣ ሀገር በቀል መሆኑን ነው። ይህ ቃል ሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪውን ብቻ የሚመለከት ነው የሚለው የጥንቱ አስተሳሰብ አሳማኝ ታሪካዊ መረጃ የለውም። ይህ አጠቃቀም የሰሜኑን ክፍል ብቻ እንኳ የሚመለከት ነበር ቢባል በሰሜን ከሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪዎች በተጨማሪ ኩሻዊና አባይሰሀራዊ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከጥንት ጀምሮ አብረው ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ስለዚህም እነሱንም የሚመለከት ይሆናል። ሌላው ነጥብ በቀዳሚው ክፍል ካቀረብንው ማስተዋል እንደሚቻለው ኢዛና ከዘረዘራቸው ዘጠኝ ሀገራት ውስጥ በግሪኩ ኢትዮጵያ በግዕዙ ሐበሠ(ተ) እና በሳብያን ሐበሸተ ነው። በጥንታዊ ግሪክ አብዛኞቹ ፅሁፎች ኢትዮጵያ የሚለው ክፍል ከግብጽ ደቡብ ያለውን ሁሉ ህዝብ የሚያካትት ነው። በኢዛና ፅሁፍ ግን በግልፅ የሱዳንን ግዛት አያካትትም። ይህ ግዛት (በአሁኒቷ ኢትዮጵያ) የደጋማውን ክፍል ብቻ የሚመለከት ነው። ምንም እንኳ ሀበሻ አክሱሞችንም ለማካተት በብዙ ቦታ ቢገለፅም አክሱሞችና ሀበሻዎች ምናልባት በዚያን ወቅት የተለያዩ ህዝቦች ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም ሀበሾች አክሱሞችንም ጨምሮ አጠቃላይ የሚጠሩበት ስም ይሆናል። በኢዛና አክሱምና ሀበሻ እራሳቸውን ችለው ለየብቻ ነው የተዘረዘሩት።
5. መደምደሚያ
በደቡብ አረቢያ በድንጋይ ላይ የተፃፉ ፅሁፎች ላይ የተገኘውን ሐበሸተ/አሐበሸነ ከኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች ጋር ለማዛመድ ከሞከሩት ውስጥ ዋንኛው ካርሎ ኮንቲ ሮሲኒ (1906) ናቸው። እንደእኝህ ሰው እምነት ሐበሸት የሚባሉ ህዝቦች ወደኢትዮጵያ ሰሜን ክፍል የፈለሱት ከደቡብ አረቢያ ነው። የመጀመሪያ ቦታቸውም በደቡብ አረቢያ፣ በአሁኒቷ የመን በደቡብ-ምዕራብ አካባቢ ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦችን ሀበሻ ማለት የመጣው ከነዚህ ከደቡብ አረቢያ ከመጡ ህዝቦች በመነሳት ነው (ኮንቲ ሮስኒ 1906)። ይህ ቃል ቀደምት በድንጋይ ላይ ተፅፎ የተገኘው ከ3ኛው ክፍለዘመን (ጋአ) ሊዘል አልቻለም። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ደቡብ አረቢያን ማስተዳደር ከጀመሩበት ግዜ በኋላ ስለሆነ ቃሉ የሚያመለክተው በደቡብ አረቢያ የሚኖሩ ህዝቦችን ለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለም። ከካርሎ ኮንቲ ሮስኒ ስራዎች በኋላ የተገኙ የድንጋይ ላይ ፅሁፎች በጥንቃቄ ሲመረመሩ ሐበሸተ /ħbšt/ (ወይም የዚህ ዝርያቃል የሆነው አሐበሸነ /ʔħbšn/) የሚያመለክትው ግልፅ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ነው።
በውጭ ሰዎችም ሆኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሀበሻ የሚለው ቃል አንድ የተለየ ብሄረሰብን ብቻ ለማመልከት በታሪክ ውሎ የሚያውቅበት አጠቃቀም አላጋጠመንም። ሀበሻ አንድን ነገድ ብቻ ለማመልከት የዋለበት አጋጣሚም የለም። በደቡብ አረቢያ እና በኢትዮጵያ የተገኙት ጥንታዊ የድንጋይ ላይ ፅሁፎች ሐበሸተ/አሐበሸነ (ሳብኛ)፣ ሐበሠ(ተ) (ግዕዝ) የሚሉትን ቃላት የሚጠቀሙባቸው አንድን ብሄረሰብ ለማመልከት ሳይሆን የህዝብ ስብስብን ነው። በማናቸውም ግዜ ቢሆን “ሀበሻ” (ወይም የዚህ ቃል ዝርያ) የአረቡን ክፍል እና/ወይም በዚያ የሚገኙ ህዝቦችን ለመግለፅ የዋለበት ማግኘት ይከብዳል (ኤርቪን 1967)።
ኢትዮጵያውያኖች ከጥንት ጀምሮ አገራቸውን ኢትዮጵያ ብለው መጥራት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በዚሁ እንዲጠሯቸው ይፈልጉ እንደነበር በተለያየ ወቅት የተሰሩ ስራዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ፣ ሉዶልፍ አዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ በሚለው መጽሀፉ ላይ እንዲህ ይላል፤ ኢትዮጵያውያን “መንግስታቸውን መንግስተ ኢትዮጵያ እራሳቸውን ኢትዮጵያውያን መባልን/ማለትን ይመርጣሉ” (ሉዶልፍ 1682:8)። በመግቢያችን ላይ ያነሳንው፣ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ማርስል ኮኸን “ሀበሻ መባልን አትፈልጉም” አለኝ ያሉት ኢትዮጵያውያን አቢሲኒያ/ሀበሻ የሚል ስም ለሀገራቸው ሰተው ስለማያውቁ ይህን ተቃውሞ ሲያሰሙ ሰምቶ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጭ በሀበሻ ቃል ተጠቃሚ ኢትዮጵያዊው ዘንድ ያለው ሁኔታ፣ በክፍል አራት እንደተመለከትንው፣ ሌላ ነው። የሀበሻ ቃል ጥንታዊነትና ህዝቡ ስለራሱ ያለው አመለካከት በተጨማሪ የሚያሳየን ሀበሻ የሚል ነገድ ከደቡብ አረቢያም ሆነ ከየትም ሌላ ሀገር አለመምጣቱን ነው።
በግርማ አውግቸውና በአህመድ ዘካሪያ