ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ ቀጣዩን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ መንግሥትን ጨምሮ የተወሰኑ የፖለቲካ ተዋንያን እስከ ቀጣዩ ምርጫ የሽግግር መንግሥት መመሥረት ሳያስፈልግ ኢሕአዴግ አገር ሊመራ ይገባል የሚል አቋም ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው እስከ ቀጣዩ ምርጫ ኢትዮጵያን የሚመራ የሽግግር መንግሥት ሊመሠረት ይገባል የሚሉ የፖለቲካ ተዋንያን ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ እነዚህ ሁለት ሐሳቦች በሕዝቡም ውስጥ የሚጉላሉ መሆናቸውን ለመገንዘብ ጥናት ማድረግ አይጠይቅም፡፡ ለምርጫው የቀሩት ወራት በጣት የሚቆጠሩ ከመሆናቸው አንጻር እስከ ምርጫው ድረስ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ሐሳቡ ተግባራዊ ጠቀሜታው ደካማ ነው፡፡ የእናት አገር ኢትዮጵያ ወቅታዊው የፖለቲካ፣ የጸጥታ ሁኔታ እና ለምርጫው ጊዜ የቀሩት ጥቂት ወራት ከግምት ሲገቡ “ምርጫው ይደረግ ወይስ አይደረግ@” የሚለው የሐሳብ ሙግት ከምንጊዜውም የፈጠነ ምላሽ የሚሻው አገራዊ አጀንዳ እንደሆነ ያስገነዝቡናል፡፡
መንግሥትም ሆነ ሌሎች ምርጫው በሕግ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል የሚሉ አካላት “ምርጫው እንዳይከናወን የሚያስገድድ ምክንያት የለም” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ በዚሁ ጎራ ከሚነሱ መከራከሪያዎች ሌላው “ምርጫ ካልተካሄደ ኢሕአዴግ በቀጣይ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር የሚያስችል ሕጋዊ ሥልጣን አይኖረውም” የሚል ነው፡፡ ምርጫው ሊካሔድ አይገባም የሚሉ ወገኖች ከሚያነሷቸው መከራከሪያዎች ዋነኛው “የአገሪቱ የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ ምርጫ ለማከናወን ቀርቶ በሰላም ውሎ ለማደር አስጊ ሆኗል” የሚለው ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም “ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን የሚያስችል አቅም አላዳበረም” የሚል መከራከሪያን ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር የምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማስፈጸም ይረዱት ዘንድ ሊያወጣቸው የሚገባ መመሪያዎች ተጠናቀው አለመውጣታቸው፣ ከቀረው ጊዜ አንጻር የምርጫ ሒደቱ ዋነኛ መገለጫ የሆኑት የፖለቲካ ማኅበራት የምርጫ ቅስቀሳና ውይይት እስከ አሁን አለመጀመሩ፣ አንዳንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ማኅበራት ደኅንነታቸው ተጠብቆ በመላ አገሪቷ ተዘዋውረው የምርጫ ቅስቅሳ ማድረግ ሊያስቡት የማይችሉት ጉዳይ መሆኑን እየገለጹ መሆኑ፤ እንዲሁም እዛና እዚ የሚከሰቱ የጸጥታና ደኅነነት ሥጋቶች ከግምት ሲታዩ ጠቅላላ ምርጫው ሊካሄድ የማይችልበት አዝማሚያ የሚያመዝን ይመስላል፡፡ ምርጫው መካሄድ ቢጀምርም በመላ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ እንዳይደረግ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥጋቶች መኖራቸውን ማሰብ ምክንያታዊ ነው፡፡
የ2012 ጠቅላላ ምርጫ በሰላም ከተደረገ ቀጣዮቹ የውይይት ነጥቦች የምርጫውን ሔደት፣ ውጤትና ቀጣይ የመንግሥት ምሥረታ የሚመለከቱ ይሆናሉ፡፡ ጠቅላላ ምርጫው ተከናውኖ በሰላም መጠናቀቁ ታላቅ እፎይታን የሚሰጠን በመሆኑ ጤናማ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚመኙት ጉዳይ ነው፡፡ “የጠሉት ይወርሳል የፈሩት ይደርሳል” ሆኖ ምርጫውን ማካሄድ ካልተቻለ ግን “የ2012 ጠቅላላ ምርጫ ካልተደረገ ኢትዮጵያን ማን ይመራታል@” እና “ምርጫውንስ በምን አግባብ ማራዘም ይቻላል?” የሚሉት ዓበይት ጥያቄዎች ሕጋዊ ምላሽ ይሻሉ፡፡
እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የተለያዩ አስተያየቶች፣ መላ ምቶችና ሙያዊ ማብራሪያዎች ከተለያየ አቅጣጫ እየተደመጡ ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ማገድ፣ አዲስ ሕገ መንግሥት መቅረጽ፣ እስከዛው የሽግግር መንግሥት ማቋቋም … የሚሉ ሐሳቦች በተደጋጋሚ እየተሠነዘሩ ነው፡፡ በእነዚህ ነጥቦች ላይ ምልከታዬን በሌላ ጊዜ አካፍላችኋለሁ፡፡ ለዛሬ ግን ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ የማያስችሉ ጉዳዮች ቢከሰቱ አሁን በሥራ ላይ ያሉ ሕግጋት የሚያስቀምጡት መፍትሔ መኖር አለመኖሩን ፈትሼ ምልከታዬን አስቃኛችኋለሁ፡፡
በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት መሠረት የሪፐብሊኩ ሥርዓተ መንግሥት ፓርላሜንታዊ ነው፡፡ ይህም ማለት ወደ መንግሥታዊ ሥልጣን የሚመጣው ለፌዴራልና ለክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ ለማግኘት በሚደረግ ምርጫ አሸናፊነት ነው፡፡ የፌዴራሉ መንግሥትና ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነና የምክር ቤቱ አባላት ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በምስጢር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ እንደሚመረጡ ሕግ መንግሥቱ ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የሚያዝበትን መንገድ በተመለከተ የፌዴራል መንግሥትን የሕግ አስፈጻሚ አካል የሚያደራጀው/ጁት እና የሚመራው/ሩት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች እንደሆኑ ይደነግጋል፡፡ (የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 45፣ 50 (1) እና 54 (1) እና (2)፣ 56 እና 9 (3)’ን እንደቅደም ተከተላቸው ይመለከቷል፡፡)
የሥልጣን ዘመንን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩም የሥራ ዘመን ልክ እንደ ምክር ቤቱ አምስት ዓመት መሆኑንና በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ አንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተደርጎ መጠናቀቅ አለበት፡፡ ወደ ሥልጣን የሚመጣበትን መንገድ በዚህ መልኩ የደነገገው ሕገ መንግሥት “በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው” በማለት ወደ ሥልጣን መውጫው ብቸኛ መንገድ በምርጫ አሸናፊ መሆን እንደሆነ ይገልጻል፡፡ (የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 72 (3)፣ 58 (3) እና 9 (3)’ን እንደቅደም ተከተላቸው ይመለከቷል፡፡)
የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት አምስተኛ የሥልጣን ዘመን በያዝነው 2012 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ በመሆኑ በዚህ ዓመት ምርጫ ተካሂዶ መጠናቀቅ አለበት፡፡ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት እስካለው አንድ ወር ጠቅላላ ምርጫ መካሄድ ባይችል የመንግሥታቸው ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል@ የምርጫ ጊዜን ለማራዘም የሚቻልበት የሕግ ማዕቀፍ አለ ወይ@ እናት አገር ኢትዮጵያን በቀጣይነት የሚመራውስ ማን ነው@ ይህንን ጉዳይ በተመለከተስ ሕገ መንግሥቱ ምን ይላል@ የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ በመነሻዬ ያነሳኋቸውን ክርክሮች ለመፍታት አግባብነት አላቸው፡፡
ሕገ መንግሥቱ እነዚህንና ሌሎች የመንግሥት ሥልጣን የሚገኝባቸውን መንገዶች ከመደንገጉ በቀር ምርጫ ለማድረግ የማይስችል ችግር ከገጠመ ምን መደረግ እንዳለበት አንዳች ነገር አይደነግግም፡፡ በሌላ አገላለጽ ሕገ መንግሥቱ ምርጫ ላይደረግ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል ብሎ ታሳቢ አላደረግም፡፡ ከሥልጣን ክፍተት ጋር ታያይዞ የሕግ መንግሥቱ ጉድለቶች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ሕገ መንግሥቱ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖሩበት ጊዜ (ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩን) ተክቶ ይሠራል” ቢልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ቢሞቱ የመንግሥትን ሥልጣን ማን እንደሚረከብ በግልጽ የሚለው ነገር የለም፡፡ “በማይኖሩበት ጊዜ” የሚለው ሐረግ አሻሚ በመሆኑ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ነፍስ ኄር መለስ ዜናዊ ባረፉበት ጊዜ ሕገ መንግሥቱ በተግባር ተፈትኖ ነበር፡፡ “በማይኖሩበት ጊዜ” የሚለው ሐረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል በሥራ ላይ በሌሉ ጊዜ ለማለት እንጂ በሞቱ ጊዜ ለማለት አስቦ አይደለም የሚል ጠንካራ ክርክር በማንሳት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን የሥልጣን ዘመን ሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ጥቂቶች አልነበሩም፡፡
ለንጽጽር ይረዳ ዘንድ በተመሳሳይ ጉዳይ የአሜሪካና የጣሊያንን ሕገ መንግሥታት እንመልከት፡፡ የአሜሪካ ምክር ቤት በ89ኛ ስብሰባው እ.ኤ.አ. የካቲት 10 ቀን 1967 ያጸደቀው 22ኛው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ፕሬዝዳንቱ ቢሞት፣ ሥራውን ቢለቅ ወይም ከሥልጣኑ ቢነሳ ወይም በሕመም ወይም በተለያዩ ምክንያቶች የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት የማከናወን ችሎታውን ካጣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሙሉ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን እንደሚኖረው በመደንገግ የነበረውን ሕግ መንግሥታዊ ድንጋጌ አሻሚነት አስቀርቶታል፡፡ የጣልያን ሕገ መንግሥትም ፕሬዝዳንቱ ቢሞት ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ሥራውን ለማከናወን ችሎታ ካጣ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ (አፈ ጉባዔ) ሥልጣኑን ይይዝና በአሥራ አምስት ቀን ውስጥ አዲስ ፕሬዚዳንት እንዲመረጥ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
ወደ መነሻ ጉዳያችን ልመለስና ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት ተፈጥሯዊ ወይም ሰው ሠራሽ ክስተት ቢፈጠር ምን መደረግ እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ የሚለው ነገር የለም፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥትም በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ያስቀመጠው ግልጽ መፍትሔ የለም፡፡ ምዕራባውያን አገሮች ለዘመናት የዳበረና የማይዋዥቅ የዲሞክራሲ ሥርዓት የገነቡና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታቸው ተቋማዊ ቅርጽ የያዘ በመሆኑ ምርጫ ላይደረግ የሚችልበት ምክንያት በአዕምሯቸው ሽው ባይል የሚደንቅ ነገር አይደለም፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የምርጫ ጊዜ ማራዘምን የተመለከተ ድንገጌ ባይኖረውም የፌዴራሉ ምክር ቤት የምርጫ ጊዜን የመወሰን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ስለተሰጠው፣ ክልሎችም በሥልጣናቸው ሥር ባወጧቸው ሕግጋት መሠረት በምርጫ ወቅት ያልታሰቡ ሠው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ቢፈጠሩ ምርጫውን በከፊልም ሆነ በጠቅላላው የማራዘም ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳም እ.ኤ.አ. መስከረም 11 ቀን 2001 በነበረው የሽብር ጥቃት መነሻነት የጥቃቱ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ በነበረችው ኒውዮርክ ይካሄድ የነበረው ምርጫ በመላ ክልሉ ተራዝሞ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 (ከዚህ በኋላ የምርጫ ሕግ እያልኩ እጠቅሰዋለሁ) በአንቀጽ 7 (1) እና (2) ሥር “ጠቅላላ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ” እንደሚካሄድ ይደነግግና “ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው እና ጉዳዩ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በተለያየ ጊዜ” ሊካሄድ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ይህ አንቀጽ ጠቅላላ ምርጫ የሚከናወን ከሆነ ምርጫው በአንድ ቀን መከናወን ያለበት ስለመሆኑ የሚደነግግና በአንድ ቀን ማድረግ ካልተቻለ በተለያየ ጊዜ ሊደረግ የሚችለበትን ሁኔታ መኖሩን የሚገልጽ ነው፡፡ የምርጫ ሕጉ በተለያዩ ሁኔታዎች የምርጫ ሒደቱ አካል የሆኑ ሁነቶች ሊራዘሙ የሚችልባቸው ሁኔታዎችን ከመደንገጉ በቀር በአንድ ቀንም ሆነ በተለያየ ቀን ጠቅላላ ምርጫ ማከናወን ካልተቻለ ውጤቱ ምን እንደሚሆን በግልጽ የሚደነግግ አንቀጽ አላካተተም፡፡ አንቀጽ 7 (2) ቦርዱ የምርጫ ጊዜን እንዲያራዝም ይፈቅድለታል የሚል መደምደሚያ ላይ ብንደርስ እንኳን ቦርዱ ምርጫውን ለማራዘም አስፈላጊ ሆኖ የሚያገኘው ምን ሁኔታዎች ሲከሰቱ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡
የአሜሪካን ልምድ በመውሰድ የምርጫ ሕጉን በማሻሻል ምርጫውን ማከናወን የማይቻልበት ምክንያት ከተገኘ የምርጫ ቦርድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ይሁንታ በማግኘት ርዝማኔው በግልጽ ለተቀመጠ ጊዜ ምርጫውን ለማራዘም እንዲቻል ማድረግን ሌላው አማራጭ አድርጎ ማየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የተራዘመው ምርጫ እስኪከናወን ድረስ የመንግሥት ሥልጣንን በማን እጅ ይሆናል የሚለው ጥያቄ አሁንም መልስ አልባ ከመሆን የማምለጥ ዕድል የለውም፡፡ ምክንያቱም መንግሥታዊ ሥልጣንን ማን እንደሚይዝ መወሰን የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት ተግባር እንጂ የበታች ሕግ የሆነው የምርጫ አዋጅ ሊሆን አይችልም፡፡
ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት ምክንያት ቢፈጠር የምርጫ ጊዜ የሚራዘምበት ግልጽ ድንጋጌ ካለመኖሩ ባሻገር ይራዘም ቢባል ለምን ያህል ጊዜ እንደሚራዘምና ምርጫው እስኪካሄድ አገርን በመንግሥትነት የሚመራው ማን እንደሚሆን የሚደነግግ ድንጋጌ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በምርጫ ሕጉ ላይ አልሰፈረም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በ2012 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ ማከናወን ካልተቻለ ምርጫውን ለማራዘምም ሆነ የተራዘመው ምርጫ እስኪከናወን ድረስ እናት አገር ኢትዮጵያን የሚመራው ማን እንደሆነ የተቀመጠ ግልጽ ወይም ለትርጉም ቅርብ የሆነ የሕግ ድንጋጌ የለም ማለት ነው፡፡ ግልጽ ድንጋጌ ከሌለ ደግሞ የሥልጣን ክፍተት ይኖራል ማለት ነው፡፡ የሕግ ክፍተቱ በምን ይሞላ ወይም ይተርጐም@
ሕገ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመናቸው ከማለቁ በፊት ምክር ቤቱን በማስፈቀድ አዲስ ምርጫ ለማካሄድ ምክር ቤቱ እንዲበተን የማድረግ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ በጣልያን እና በእስራኤል መንግሥታት በተደጋጋሚ ይከሰታል፡፡ የእኛም ሕገ መንግሥት በጣምራ የመንግሥት ሥልጣን የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራነታቸው ፈረሶ በምክር ቤቱ የነበራቸው አብላጫነት ያጡ እንደሆነ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተበትኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌላ ጣምራ መንግሥት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመመሥረት እንዲቻል ፕሬዚዳንቱ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንደሚጋብዝና የፖለቲካ ድርጅቶቹ አዲስ መንግሥት ለመፍጠር ወይም የነበረውን ጣምራነት ለመቀጠል ካልቻለ ምክር ቤቱ ተበትኖ፣ ምክር ቤቱ በተበተነ ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አዲስ ምርጫ መደረግ እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል፡፡ በዚህ ጊዜ የሥልጣን ክፍተት እንዳይኖር ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ አገሪቱን የሚመራው ሥልጣን ይዞ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራ ነው፡፡ ይህ ነባር መንግሥት የዕለት ተዕለት የመንግሥት ሥራ ከማከናወንና ምርጫ ከማካሄድ በስተቀር አዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችንና ድንጋጌዎችን ማውጣት አይችልም፡፡ (የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 60 ይመለከቷል)
አንቀጽ 60 (1) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤቱን ለመበተን ፈቃድ የሚጠይቁት “የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት” ከማለት በቀር የሥልጣን ዘመናቸው ምን ያህል ጊዜ ሲቀረው እንደሆነ ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡ ከዚህ ባለፈም ምክር ቤቱ ራሱን ለመበተን ፈቃደኛ የሚሆነው በየትኞቹ ምክንያቶች እንደሆነ ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡ አንቀጽ 60 (5) የሥልጣን ክፍተት እንዳይኖር የነበረው መንግሥት በተገደበ ሥልጣን በመንግሥትነት እንዲቆይ ታሳቢ ያደረገው ምክር ቤቱ ከተበተነ እንጂ ምርጫ ማድረግ ካልተቻለ አይደለም፡፡ በመሆኑም ምርጫ ማድረግ ካልተቻለ፣ ምርጫ ባለመደረጉ የሚኖረውን የሕጋዊ ሥልጣን ክፍተት ለመሙላት አንዱ አማራጭ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት ምክር ቤቱ ተበትኖ አዲስ ምርጫ ለማድረግ ምክር ቤቱን ማስፈቀድ ነው፡፡ ይህ ከተሳካ ምክር ቤቱ የሥራ ዘመኑ በሰኔ ወር ላይ ከመጠናቀቁ በፊት ከተበተነ፣ ከተበተነበት ጊዜ ጀምሮ ስድስት ወር ላልበለጠ ጊዜ እናት አገር ኢትዮጵያን ለመምራት ሕጋዊ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ምክር ቤቱ ጥያቄውን ከተቀበለ ብቻ ነው፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ ይህ ኃላፊነት ለአገር መከላከያ ሊሰጥ ይገባል ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ለክርክራቸው በምክንያትነት የሚያቀርቡትም የአገር መከላከያ ሕገ መንግሥቱን የመጠበቅ ተልዕኮ ያለው በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ሕጋዊ ሥልጣን የሌለው አካል የፖለቲካ ሥልጣን ላይ እንዳይቆይ በገለልተኝነት የመንግሥትነት ሥልጣኑን ከተሰናባቹ መንግሥት ተረክቦ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ አገሪቱን ማስተዳደር አለበት የሚል ሐሳብ ነው፡፡ መከላከያ ሕገ መንግሥቱን የመጠበቅ ተልዕኮ ቢኖረውም የማንኛውም መንግሥታዊ ተቋም ሥልጣን የሚመነጨው ከሕግ በመሆኑ የአገር መከላከያ ሚኒስትር የሥልጣን ክፍተትን እንዲሞላና ምርጫ እስኪከናወን አገሪቱን እንዲመራ ሥልጣን የሚሰጠው ግልጽ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የለም፡፡ ይህ ሥልጣን አለው ወይም ሊኖረው ይገባል ተብሎ ቢተረጐም እንኳን የአገር መከላከያን የሚመራው የኢፌዲሪ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ ደግሞ በመከላከያ ሚኒስትሩ የሚመራ ነው፡፡ ሚኒስትሩ ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል በመሆኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን በአምስተኛው ዓመት ላይ ሲያከትም የሚኒስትሩም ሕጋዊ ሥልጣን ያከትማል፡፡ በመሆኑም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሊኖር የሚችለውን የሥልጣን ክፍተት ሊሞላ የሚችልበት ሕጋዊ ሥልጣን አይኖረውም፡፡
ሌላው ሕጋዊ አማራጭ ጠቅላላ ምርጫ ለማድረግ የማያስችሉ ተፈጥሯዊ ወይም ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ከተከሰቱ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ አገር የሚመራው ማን እንደሚሆን በግልጽ በመደንገግ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ የማሻሻያ ሐሳቡን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2/3ኛ ድምፅ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ2/3ኛ ድምፅ ወይም ፌዴሬሽኑን ከመሠረቱት ዘጠኝ ክልሎች ውስጥ የሦስቱ ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ ከደገፉት ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ሕዝብና የሕገ መንግሥቱ መሻሻል ለሚመለከታቸው ክፍሎች መቅረብ ይገባዋል፡፡ ማሻሻያ ለማድረግ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምፅ፣ ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች ውስጥ የስድስቱ ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሊያጸድቁት ይገባል፡፡ ይህ ሊሳካ የሚችለው ግን የሕገ መንግሥቱን ቅቡልነት አስመልክቶ የሚነሳው ክርክር እንዳለ ሆኖ ሕገ መንግሥትን ማሻሻል ምርጫ ከማከናወን የሚቀል ሆኖ ከተገኘ ነው፡፡
አንዳንዶች ሕገ መንግሥቱን ማገድን ወይም ከሥራ ውጪ ማድረግን እንደአማራጭ ሲያነሱት ቢሰሙም ይህንን ማድረግ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በብቸኝነት በሥልጣን ላይ ለማቆየት የሚያስችል ሕጋዊና ቅቡሉነት ያለው ምክንያት አይሆንም፡፡ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ማገድ ሊፈጥር የሚችለው የፖለቲካ ቀውስ እንዳለ ሆኖ ሕገ መንግሥቱን አግዶ አዲስ ሕገ መንግሥት ማውጣትም ሕገ መንግሥቱን ከማሻሻል የበለጠ ጊዜ የሚወስድና ውስብስብ ጉዳይ በመሆኑ ውጤታማ የመሆን ዕድሉ የመነመነ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሚመሩት መንግሥት ጠቅላላ ምርጫ መደረግ እንዳለበት አበክሮ የሚያወሳ በመሆኑ፣ የምርጫ ጊዜውን ማራዘምም ሆነ ሕግጋቱን የማሻሻል አዝማሚያ ያለው የማይመስል መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ አቋሙ የሚጸና ከሆነ የተሳካ ምርጫ ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ቅድመ ዝግጅቶች ከወዲሁ በማከናወን እና ምርጫው እንዳይከናወን ሊያደርጉ የሚችሉ የደኅንነትና የፀጥታ ሥጋቶችን ቀድሞ በመተንተንና በማስቀረት ከተከሰተም መቆጣጠር የሚስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ምርጫውን ከማራዘም ጋር ተያይዘው የሚነሱ ሥጋቶችን እና የሕግ ክፍተቶችን ከወዲሁ ማድረቅ ይቻላል፡፡ ምርጫው የሚራዘም መሆኑን ከወዲሁ መገመትና ማረጋገጥ ከተቻለ ግን ሕገ መንግሥቱ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን ምክር ቤትም ሆነ አስፈጻሚ አካል የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የሚቻልበትን ዕድል በግልጽ የማይሰጠው በመሆኑና እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚው ሥልጣን አዲስ ሕግ በማውጣት ለማራዘም የሚቻልበት ዕድልም ስለማይኖር ምርጫው የሚራዘምበትን እና ምርጫው እስኪደረግ የመንግሥት ሥልጣን በሕግ አግባብ የሚያዝበትን የሕግ ማዕቀፍ ከወዲሁ ማበጀት ፋይዳው የላቀ ነው፡፡
አንድ ሕግ ሲወጣ ድንጋጌው ሊገዛቸው ባሰባቸው ነገሮች ዙሪያ፣ ገባ ያሉ ነገሮችን ቀድሞ መተንበይና መፍትሔ ማበጀት የሚጠበቅበት በመሆኑም ይህም ሆነ መሰል የሕግ ክፍተቶች በቀጣይ በሚደረጉ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎች ወይም ለውጦች ታሳቢ ሊደረጉ ይገባል፡፡ ይህ ሳይከናወን ቀርቶ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት የ2012 ጠቅላላ ምርጫ ካልተደረገ “ኢትዮጵያን ማን ይመራታል@” የሚለው ጥያቄ አወዛጋቢ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ በዚህ ጽሑፌ የዳሰስኩት የሕግ ክፍተት በተግባር ፈታኝ ሆኖ ይከሰት እንደሆነ፣ ከተከሰተም ሕጋዊ መፍትሔ ያገኝ እንደሆነ መጪዎቹ ጥቂት ወራት ተግባራዊ ምላሽ ይሰጡናል፡፡
የዛሬ ምልከታዬን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ የምንደማመጥ፣ ሐሳብን በሐሳብ ብቻ የምንሞግት፣ ካለፈው ይልቅ በመጪው ላይ የምናተኩርና ምንጊዜም ለእናት አገር ኢትዮጵያችን ቅድሚያ የምንሰጥ የአንድ አገር ሕዝቦች እንሁን! ብሩሃን ቀናት ከፊታችን ይቅደሙ! ሰላም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው (LL.B, LL.M, MSW) ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሲሆኑ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡
በዳንኤል አረጋዊ ኃይሉ