የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የግል ንግድ ባንኮችን የሚያስደነግጥ መመርያ አውጥቶ ነበር። በወቅቱ ሁሉም የግል ባንኮች ‹‹መመርያው ከሥራ ውጪ ሊያደርገን ነው›› በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል። ብሔራዊ ባንክ ግን ባንኮቹ ባቀረቡት ተቃውሞ ላይ ምንም ዓይነት ማስተካከያም ሆነ ተጨማሪ ነገር ሳያደርግ በአቋሙ ፀና። መመርያው የግል ንግድ ባንኮች ከሚሰጡት ብድር ላይ 27 በመቶውን ለቦንድ ግዢ እንዲያውሉ የሚል አስገዳጅ መመርያ ነበር።
ባንኮቹ ያቀረቡትን ተቃውሞ በሚመለከት በወቅቱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ የነበሩት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ ‹‹ባንኮቹ ከዚህም በላይ የቦንድ ግዢ እንዲገዙ ቢደረግ አትራፊዎች ናቸው›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። ባንኮቹም በወቅቱ ተቃውሞ ቢያሰሙም መመርያውን ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ምናልባትም ያገኙት የነበረው ዓመታዊ ትርፍ ከፍ ያደርግላቸው እንደነበር እንጂ፣ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥም አትራፊ ሆነው ከርመዋል።
ባንኮቹ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሲያቀርቡት የነበረው ተቃውሞ የተረሳ ቢሆንም፣ ሰሞኑን ግን ባላሰቡበትና ባልተጠበቀ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመመርያ እንዲተገብሩት አውጥቶት የነበረውን አስገዳጅ የ27 በመቶ የቦንድ ግዢ መመርያ አንስቶላቸዋል። ባንኮቹም ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል። ለምን መመርያው እንደተነሳ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፕሬዚዳንት ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ መመርያው በመነሳቱ የግል ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሳይገጥማቸው ብድር እንደ ልብ ማቅረብ ይችላሉ። በቅርቡም በቋሚነት ለሚጀመረው የመጀመርያ ደረጃ የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ ላይ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል።
የግል ባንኮቹም መመርያው በመነሳቱ፣ በብድር ወለድ ላይ የሚጥሉትን ምጣኔ ለመቀነስ መዘጋጀታቸውን (የቀነሱም አሉ) በደስታ ተናግረዋል።
በግል ባንኮች ላይ የተጣለው የ27 በመቶ የቦንድ ግዢ መመርያ ሲነሳ ነጋዴውንም ሆነ ማኅበረሰቡን ያስደነገጠው ሌላ ነገር ደግሞ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ ነው። ቀድሞ የነበረውን ኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ቁጥር 305/95 ለማሻሻል ተብሎ በገንዘብ ሚኒስቴር እንደረቀቀ የተነገረው አዲሱ ማሻሻያ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ፣ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል። ረቂቅ አዋጁ ገመድ አልባ የሞባይል ኢንተርኔት ላይ ከሚጥለው አምስት በመቶ ኤክሳይስ ታክስ እስከ ትልቁ በተሽከርካሪ ላይ የጣለው 500 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ አስደንጋጭ ሆኗል። በመሆኑም መንግሥትና የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው በዝርዝር እንዲመረምሩት ሕዝቡ እያሳሰበ ነው። አዋጁ እንዳለ ከፀደቀና ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ፣ አዋጁን ተላልፎ የሚገኝ ነጋዴ ከ50 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር ቅጣትና ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት የእስር ቅጣት ይጠብቀዋል። ለማንኛውም ረቂቅ አዋጁ ውይይት ተደርጎበት እስከሚፀድቅ ድረስ፣ ነጋዴዎች የሚያስገቡት ማንኛውም ዓይነት የንግድ ዕቃ በነባሩ አዋጅ የሚስተናገድ መሆኑንና በመስገብገብ ቀደም ባለው አዋጅ መሠረት ገዝቶ በማቆየት ለመሸጥ መሞከር የሚያስቀጣ መሆኑም ተጠቁሟል።