ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የመሬት ምልከታ ሳተላይትን ወደ ህዋ ላከች። ኢትዮጵያን ሪሞት ሴንሲንግ ሳተላይት-01 (Ethiopian Remote Sensing Satellite- 01) በምሕፃሩ ኢትረስ-01 (ETRSS-01) የተሰኘችው ሳተላይት፣ ከመሬት 700 ኪሎ ሜትር ርቃ የተወነጨፈችው ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቻይና ታሉያን የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ነው።
በቻይና የተገነባችውና 70 ኪሎ ግራም የምትመዝነዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይቷ በእርሻ፣ በሥነ አካባቢና በአየር ንብረት ጥበቃ፣ በመልክዓ ምድርና ማዕድን ዙሪያ መረጃ የምትሰጥ ከመሆኑ ባሻገር፣ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ለሳተላይት ኪራይ በዓመት ትከፍል የነበረውን ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለማስቀረት ያስችላል።
ከኢትዮጵያ የሕዋ ሳይንስ ተቋም የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ውስጥ ሲገነባ የቆየው የሳተላይት መቆጣጠሪያና መረጃ መቀበያ ጣቢያም የተጠናቀቀ ሲሆን፣ መረጃዎችን መሰብሰቡ ሙሉ በሙሉ የሚከናወነው በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች ነው።
ኢትዮጵያ ሳተላይት ለማልማትና ለማምጠቅ በ2009 ዓ.ም. ከቻይና መንግሥት ጋር ከስምምነት መድረሷ ይታወቃል።