ምርጫ 2012 ዓ.ም. ‹‹መካሄድ አለበት›› እና ‹‹መካሄድ የለበትም›› የሚሉ ወገኖች ጎራ ለይተው እየተናገሩ ነው። ከ70 በላይ የሚሆኑ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፤ አገር በትርምስ ውስጥ ሆና ባለችበት በዚህ ወቅት ምርጫ ይደረጋል ማለት እንዳለፉት አምስት አገራዊ ምርጫዎች ‹‹የይስሙላ›› እንደሚሆን እየተናገሩ ነው። ምርጫ የሚደረገው የአገሪቱ ሕዝቦች በሰላም ውስጥ ሆነው ‹‹ይመራኛል፣ አገርንም ማስተዳደር ይችላል›› የሚሉትን የፖለቲካ ድርጅት ያለምንም መሳቀቅና ፍርኃት፣ ነፃና ገለልተኛ በሆነ ምርጫ መምረጥ ነው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ይህንን ማድረግ ስለማይቻል፤ ‹‹ምርጫው መራዘም አለበት›› እያሉ ነው። ሰሞኑን መዋሃዱንና መጠሪያውም ብልጽግና ፓርቲ መሆኑን ይፋ ያደረገው ኢሕአዴግና የተወሰኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደግሞ ምርጫው ወቅቱን ጠብቆ መካሄድ አለበት እያሉ ነው። በአገሪቱ እየታየ ያለውን አለመረጋጋት ሁሉም ተባብሮ ከሠራ ለውጥ ስለሚመጣ፣ ሁሉም በአንድነትና በሰላም ላይ መሥራት እንዳለበት እየተናገሩ ነው። እንደ ብልጽግና ፓርቲ(ኢሕአዴግ)፤ምርጫው በሕገ መንግሥቱም ተደንግጎ ስለሚገኝ መካሄዱ ግዴታ መሆኑንና ምርጫው አለመካሄዱም ያለውን አለመረጋጋት የሚያባብሰው እንጂ ሰላም የሚያወርድ ባለመሆኑ፤ ምርጫው መካሄድ አለበት እያሉ ነው። ምርጫው መካሄድ አለበት ከሚሉት ወገኖች ስለምርጫውና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የኦዴፓ(ብልጽግና) ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ(ኢህአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ፈቃዱ ተሰማን ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል።
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በአብዛኛው አካባቢ ሊባል በሚችል ሁኔታ በሚነሱ ግጭቶች የሰው ሕይወት እየጠፋና ንብረትም እየወደመ ቢሆንም፣ ምንም ይሁን ምንም አገር አቀፍ ምርጫ እንደሚካሄድ ብልጽግና ፓረቲ አስታውቋል። ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ስለምርጫውና በምርጫው ዙሪያ ብልጽግና እንደ ተወዳዳሪ ፓርቲ ምን እየሠራ ነው?
አቶ ፈቃዱ፡- እንደ በልጽግና ከዚህ ቀደምም አቋማችንን ግልጽ አድርገናል። በ2012 ዓ.ም. አገር አቀፍ ምርጫ እንደሚካሄድ እንደ ብልጽግና አቋም ተይዟል። ብልጽግና በዋናነት አቋም የያዘው፣ በየአምስት ዓመቱ በሚካሄድ ምርጫ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ አካል (ፓርቲ) አገርን ይመራል የሚል እምነት ስላለው ነው። ከዚህ በመነሳት በየአምስት ዓመቱ ኮንትራቱን ማደስ አለበት። በየዓምስት ዓመቱ አገር አቀፍ ምርጫ መካሄድ እንዳለበትም በሕገ መንግሥቱም በግልጽ ተቀምጧል። የሕገ መንግሥቱ አስተሳሰብና አቋም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ አቋም ወይም የቃል ኪዳን ሰነድ ነው ተብሎ ስለሚወሰድ፤ በዚሁ አግባብ ብልጽግና እንደ ፓርቲ ምርጫው ይካሄዳል ብሎ አቋም ይዟል። አቋሙ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ ‹‹ ብልጽግና ፓርቲ ብቻውን ይወስናል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በምርጫ ጉዳይ ትልቅ ድርሻ ያላቸው የዴሞክራሲ ተቋማት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት፤ ‹‹ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ላይ ነን ወይስ አይደለንም?›› የሚለው የነሱ አቋምና ግምገማ ይሆናል። በዚህ ላይ ተመሥርቶ ብልጽግና ምርጫው በወቅቱ እንዲካሄድ ይፈልጋል። አቋሙም ይኼው ነው። ይኼንን አቋም የያዘበት ምክንያት፤ አንደኛው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ነው። ሁለተኛው ሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን፣ ምርጫ አራዝማለሁ ወይም ምርጫ አላካሂድም ማለት የራሱ የሆነ ተቀባይነት የሌለው (ኔጌቲቭ) አንድምታ ይኖረዋል። ሳትመረጥ ሕዝብ ይሁንታ ሳይሰጥህ፣ ከሕዝብ ይሁንታ ውጪ መምራት ሕገ መንግሥታዊም አይደለም። ምርጫ ሊራዘምባቸው የሚችሉ ሕገ መንግሥታዊ አካሄዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ብልጽግና ግን ያ ጥሩ ነው ብሎ አያስብም። ምርጫው መካሄድ አለበት የሚል አቋም አለው። ሦስተኛው ምክንያት ከሕዝቡ ሲነሳ የነበረው፣ ‹‹የዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት አለበት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃ መሆን አለባቸው፣ የሚካሄደውም ምርጫ ነፃ፣ ተዓማኒ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት›› ብሎ በተለያየ ጊዜ በተደጋጋሚ ሲያነሳው ስለነበረ፤ መብቱም ስለሆነና በዚህም እምነት ስላደረባቸው ምርጫው መካሄድ አለበት። በተጨማሪም ወደ አገር የተመለሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በዚሁ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ናቸው። ስለዚህ የሕዝቡን ግምትና የሚጠብቀውን የሚመጥን ምርጫ መካሄድ አለበት ብሎ ውሁዱ ፓርቲም(ብልጽግና ፓርቲ) አምኗል። ዋናው ነገር በምርጫው ‹‹ማን አሸነፈ? ወይም ማን ተሸነፈ? ወይም መንግሥት ሆኖ መቀጠል ወይም አለመቀጠል ሳይሆን፣ ዋናው ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነፃ፤ ተዓማኒና ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ ችለዋል ወይ?›› የሚለውን ማረጋገጥም የመንግስትም ፍላጎት ነው። ይኼ ምርጫ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ያላቸው ትልቅ ዕድልም ነው። ይኼንን ትልቅ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ካልቻልን፣ የአገሪቱም ህልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ከዚህ አኳያ በተለይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን ከስሜት በመውጣት፣ ከቂምና ከጥላቻ በመላቀቅ፣ የፓርቲያቸውን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታንም ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ኃላፊነት በተመላበትና በሰከነ መልኩ ምርጫው ለአገሪቱ ምን አንድምታ እንዳለው ከግምት ውስጥ በማስገባት ከተንቀሳቀሱ፤ ኢትዮጵያውያን ነፃ፣ ተዓማኒና ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ ይችላሉ።በሦስቱ መነሻ ምክንያት ነፃ፣ ተዓማኒና ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሕዝቡ ፍላጎት ነው። የሕዝቡን ፍላጎት ማሟላት ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ምርጫን ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ማራዘም ቢቻልም፣ ሊያስከትል የሚችለውን የፖለቲካ ቀውስና ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች ፤ምርጫው መካሄድ እንዳለበት ብልጽግና ያምናል። አቋምም ይዟል። ይኼ አቋሙ የመጨረሻ ውሳኔ የሚያገኘው ግን ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ምርጫውን ለማካሄድ ያላቸው ሁለንተናዊ ቁመና ብቁ ሆኖ ሲገኝ ነው። ነገር ግን አብዛኛው ቁመና ወይም አቋም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በአብላጫ ድምፅ የሚወሰኑትን የሚከተል ይሆናል።
ሪፖርተር፡- እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ አምስት አገር አቀፍ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በእኒዚህ ምርጫዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀደም ብሎ በሚያወጣው የማስታወቂያ ሰሌዳ መሠረት፤ ከጥቅምት ወር ጀምሮ የሚተገበሩ የምርጫ ሒደት ክንውኖች ነበሩ ። በዚህ ዓመት ግን ምንም የተደረገ ነገር የለም። ቦርዱም በተለያዩ ሥራዎች ከመጠመድ ባለፈ ያወጣው ፕሮግራም የለም። ኢሕአዴግ(ብልጽግና ፓርቲ) የተሻለ ልምድ ያለው ፓርቲ ከመሆኑ አንፃር በምርጫው ዙሪያ ምን እያደረገ ነው?
አቶ ፈቃዱ፡- ብልጽግና ‹‹ተዋህጄ ወደ ምርጫ መግባት አለብኝ›› ብሎ ሲሰራ ቆይቱአል። በ11ኛ የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በተወሰነውና በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የውህደት ሥራውን አጠናቆ ሌሎች ስራዎችን እከናወነ ነው ። ጥናቱ አልቆ የተለያዩ ውይይቶች ተደርገዋል። ከውይይቶቹ በመነሳት ግንባሩ ኢህአዴግ ፈርሶ ዘጠኙንም ክልሎች ያካተተ ውሁድ የብላጽግና ፓርቲ ተመስርታል። ውህዱ ፓርቲም በአገሪቱ ያሉን ተጨባጭ ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመከተል መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች አርሞ በአዲስ መንፈስ ይሰራል። ይህ ራሱ የአንድ ምርጫ ዝግጅት ነው።
ሪፖርተር፡- ውህዱ ፓርቲ ወደ ምርጫ ለመግባት ተዘጋጅታል እያሉኝ ነው?
አቶ ፈቃዱ፡- አዎ። እየተዘጋጀ ነው።ብልጽግና ፓርቲ ወደ ምርጫ በሚያደርሱት ነገሮች ላይ ሁሉ እየሰራ ነው። በመቀጠል የለውጡ ፍኖተ ካርታ የሚመራበት የ‹‹መደመር›› እሳቤ ላይ በየደረጃው ውይይትና ሥልጠና ተደርጎ በተለያዩ አካላት ሐሳብ ተሰጥቶበታል።
ሪፖርተር፡- መደመር የውህዱ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ነው?
አቶ ፈቃዱ፡- መደመር የውህዱ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም አይደለም። የለውጡ ፍኖተ ካርታ የሚመራበት እሳቤ ነው። ርዕዮተ ዓለሙና ሌላው በፕሮግራሙ የሚመለስ ይሆናል። የአዲሱ ውህድ ፓርቲ መሥራች ጉባዔ በሚያፀድቀው መሠረት ርዕዮተ ዓለሙ ይታወቃል።
ሪፖርተር፡- የውህዱ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ መቼ ነው የሚካሄደው?
አቶ ፈቃዱ፡- በአጭር ጊዜ ይካሄዳል። ከምርጫው በፊት ይካሄዳል። እንደ መሪ ፓርቲ ወይም መንግሥት ለምርጫ ቦርድ አስፈላጊ የሆነውን መሥፈርት ለማሟላት ማለትም ፍትሐዊ፣ ነፃና ተዓማኒ የሆነ ምርጫ እንዲካሄድ የተሄደበት ርቀት ለሁሉም ግልጽ ነው። በጀት መመደብ፣ ከላይ እስከ ታች ራሱን እንዲያደራጅ የሚያስፈልገውን ነገር የማሟላት ሁኔታም እየተፈጸመ ይገኛል። ከምርጫ ዝግጅት አኳያ ይህ አንዱ የምርጫ ዝግጅት አካል ነው።
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ይሁንታቸውን ከሰጡ ብቻ ምርጫ ሊደረግ እንደሚችል ተናግረዋል። ቦርዱ የምርጫ ሕግ ማስፈጸሚ መመርያዎችን እስካሁን ባለማውጣቱ፣ የምርጫ ማድረጊያ ሒደቶች ወቅታቸውን ጠብቀው ካለመፈጸማቸውና ጊዜው እያጠረ ከመምጣቱ አንፃር፣ ‹‹ምርጫው በዚህ ዓመት መደረግ የለበትም ወይም መራዘም አለበት›› ቢል፤ ምርጫ አይደረግም ማለት ነው?
አቶ ፈቃዱ፡- ይኼ የምርጫ ቦርድ ጉዳይ ይሆናል። እስካሁን ‹‹ይኼ ምርጫ ቢደረግ አያደናቅፈኝም። ወይም በዚህ በዚህ ምክንያት ምርጫ ማድረግ አይቻልም፣ የሚል ግምገማ በምርጫ ቦርድ በኩል እስካሁን የለም። ምርጫ ዝም ብሎ አይካሄድም። የሚራዘመው በሕገ መንግሥት ድንጋጌ ብቻ ነው። ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ማድረግ የማይቻልበትን ምክንያት በሚገልጽበት ጊዜ የሚወሰን ነው። ነገር ግን በዋናነት መያዝ ያለበት ወይም በኢሕአዴግ አቋም ከላይ እንደጠቃቀስኩት፣ በሦስቱ መሠረታዊ ምክንያቶች ምርጫው መካሄድ አለበት። በቃ! ምርጫው በታለመበት ጊዜ መካሄድ እንዳለበትም አቋም ወስዶበታል።
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ግትር (Rigid) ሕገ መንግሥት ነው። እንደሌሎች አገሮች አማራጭ ያለው (Flexible) አይደለም። በመሆኑም በአንቀጽ 54 (1) መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመቱ በትክክለኛ ምርጫ በሚመረጡ አባለት ይተካሉ። በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርቲ መንግሥት መሥርቶ አገርንና ሕዝብን ይመራል። ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ በመሆኑ ካልተሻሻለ በስተቀር በድንጋጌው መሠረት መፈጸም የግድ ይላል። በመሆኑም ምርጫው መካሄዱ ግድ ይሆናል ማለት ነው። ባለድርሻ አካላት ምርጫው መራዘም አለበት ቢሉ እንዴት ይሆናል?
አቶ ፈቃዱ፡- ያው አቋማችን አንድ ነው። የብልጽግና ፓርቲም አቋም በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት ምርጫው መካሄድ አለበት ነው። ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ ላይ አስገዳጅ ሁኔታ ቢቀመጥም ፓርላማው የሚያራዝምበት ሌሎች አዋጆች አሉ። ሕገ መንግሥት እንዳለ አይተረጎምም። የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ምን ማለት እንደሆነ ማስፈጸሚያ ዝርዝር የሕግ (አዋጆች) ድንጋጌዎች አሉ። ነገር ግን ብልጽግና ፓርቲም የሚያስበው ምርጫው በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት መካሄድ እንዳለበት ነው። ሌሎች ምሁራንና የተለያዩ ሰዎች የፈለጉትን ቢሉ፣ እሱ የእነሱ አመለካከት እንጂ የብልጽግና ፓርቲ አይደለም። ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት እንዲደረግ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ መሪ መንግሥት መሥራት ነው…። እንደ መንግሥት ምርጫ ቦርድ እንዲጠናከር ማድረግ ነው። ሌላው የፀጥታ አካላትና ሌሎች ከምርጫው ሒደት ጋር ሊኖራቸው የሚገባ ሚና ምን መሆን እንዳለበት፣ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ምን መሆን እንዳለበት፣ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ምርጫ ቦርድ የሚያወጣውን የሥነ ምግባር መመርያ መከታተልና ተግባራዊ የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
ሪፖርተር፡- ከ70 በላይ የሚሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ‹‹ምርጫው መካሄድ የለበትም እያሉ ነው። ምክንያታቸው ደግሞ ቅድሚያ አገር ሰላም መሆን አለበት ነው። ሰው እየሞተ፣ እየተፈናቀለና ሁከትና ብጥብጥ ሠፍኖ አገር መቀጠል አለመቀጠሏ ጥርጣሬ ላይ ሆና እያለ ስለምርጫ ማሰብ ተገቢ አይደለም። ምርጫ እንዲካሄድ ቢስማሙ እንኳን በምርጫ ሕጉ የተደነገገውን ለማሟላት መንቀሳቀስ በማይችሉበት ሁኔታ ‹‹እንዴት መወዳደር ይቻላል›› እያሉ ነው። የተፎካካሪ ፓርቲዎችን የሰላም ጥያቄ ቀርፎ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል?
አቶ ፈቃዱ፡- መታየት ያለበት በሚዛኑ ነው። ‹‹አገር ዳር እስከ ዳር ተተራምሷል። መንቀሳቀስ አይቻልም›› የሚለው መታየት አለበት። በአጠቃላይ ከክልሎች ብናይ፣ አንዱ ክልል ላይ ችግር ይፈጠራል፣ ይረጋጋል፣ ሌላው ክልል ላይ ግጭት ይፈጠራል፣ ይረጋጋል፣ ነገር ግን አጠቃላይ ክልሉን የሚሸፍን አይደለም። አንዳንድ ቦታ ስሜት ቀስቃሽ (Sensational) የሆኑ ነገሮችን በሚሠሩ ማኅበራዊ ድረገጾችና ሥነ ምግባር በጎደላቸው ሰዎች በሚደረጉ ቅስቀሳዎች ችግር እየፈጠሩ መሆኑ ይታወቃል። በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በሥራ ላይ በሚውለው የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ አዋጅ መቆጣጠር ስለሚቻል ሕዝቡ ሰላም ይሆናል ማለት ነው። ቀደም ካሉ ጊዜያት ጋር በማነፃፀር ብንመለከት እያደር እየተሻሻለና ወደ ቀልቡ እየተመለሰ ነው። እስካሁንም ችግሮች ሊከሰቱ የቻሉት ላለፉት 27 ዓመታት ሚዲያውም፣ የሕዝቡም እንቅስቃሴ ታፍኖ ቆይቶ ስለነበረና ነፃ ሲሆን፣ የዴሞክራሲ ባህል ባልዳበረበት አገር ችግሮች ይከሰታሉ። ይህንን በሙሉ በማሰር ወይም በመግደል ወይም በማፈን ሕግና ሥርዓት ማሻሻል አይቻልም። ሕግን ተከትሎ አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ነው። ሌሎቹ ደግሞ ከሕዝቡ ጋር በመወያየትና አንድ በመሆን ሰላምና መረጋጋት የሚመጣበት ሁኔታ እየተሠራ ነው። ነገር ግን አጠቃላይ አገሪቱ ውስጥ ሰላም እንደሌለ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። በየትኛውም አገር እዚያና እዚህ የሚፈጠሩ ግጭቶች ይኖራሉ። የብሔር ብሔረሰብ ወይም የሃይማኖት ብዝኃነት ብቻ ሳይሆን፣ የአስተሳሰብ ብዝኃነት የዴሞክራሲው ባህል ባላደገበትና በለውጥ ጎዳና ላይ ባለ አገር ግጭት ሊያጋጥም ይችላል። ይኼ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዓለማትም የሚያጋጥም ነው። ነገር ግን፣ ‹‹ይኼ መቼ ነው የሚቆመው?›› የሚል ጥያቄ ቢነሳ በእርግጠኝነት ‹‹በዚህ ቀን›› ብሎ የሚናገር አይኖርም። ‹‹ምርጫው ‹ባይካሄድ› መፍትሔ ይሆናል? ወይስ ግጭቱን ሊያባብሰው ይችላል?›› የሚለውም መታየት አለበት። ጭራሽ ግጭቱን ሊያባብስ የሚችል ሁኔታም ሊፈጠር ስለሚችል መፍትሔ የሚሆነው አሁን ያለውን የመረጋጋት ሁኔታ አጠናክሮ መቀጠል ነው። በጣም ችግር የነበረበትን የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መመልከት ቢቻል፣ በአሁኑ ጊዜ ከማንኛውም ክልልና አካባቢ በፀጥታ በኩል የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል። በመቀጠል ከሲዳማ የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በሐዋሳና ዙሪያው ግጭቶች ተፈጥረው የነበረ ቢሆንም አሁን ተረጋግቷል። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና አፋርም የነበረው ጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው። በኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ ሁኔታውን ስንመለከት፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸሻለ ነው። ተጨማሪ ሥራዎች ከተሠሩ፣ ሕዝቡ ሰላም ወዳድ በመሆኑ በአጭር ጊዜ የሚፈለገው ሰላም ይመጣል። መንግሥት ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በሰላም ዙሪያ ልዩነታቸውን ትተው ተባብረው ከሠሩ፣ የግል መገናኛ ብዙኃን፣ ማኅበራዊ ድረ ገጾችና ሁሉም ዜጋ በአጠቃላይ ስለሰላም ከሠራ፣ ሰላም የማይፈጠርበት ምክንያት የለም። ስህተትን በስህተት ማረም አይቻልም። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰው ያለፈውን ድርጊት እንደ ታሪክ ወስደን እንዳይደገም በማድረግ፣ በመቻቻልና በመፈቃቀር፣ ዕጣ ፈንታቸው የተሳሰረና የተጋመደ በመሆኑ፣ ይዘው እንዲቀጥሉ ማስተማር አለባቸው።
ሪፖርተር፡- ክልሎች ላይ ማለትም ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ደቡብ ክልል ላይ የሰላሙ ሁኔታ እየተሻሻለ መሆኑ ይታያል። ነገር ግን በተለይ ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት የ87 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። በዚህ ምክንያት በተለይ ከሌላ ክልሎች የሄዱ ነዋሪዎች ከፍተኛ ሥጋት ላይ መሆናቸው ይታወቃል። ይህንን እንዴት ማስተካከል ይቻላል?
አቶ ፈቃዱ፡- በዚህ ላይ በስፋት እየተሠራ ነው። ሁላችንም እየተሳተፍንበት ነው። ሰው ወደ ቀልቡ ተመልሶና ተረጋግቶ እንዲኖር ከፖለቲካና የፀጥታ አካሉ ጋር ተቀናጅቶ እየተሠራ ስለሆነ ይስተካከላል። የማናልፈውና የማንሻገረው ችግር የለም። እዚያም እዚህም በሚታዩ ነገሮች ምክንያት ግን ትልቅ ሥጋት እንዳለ በመቁጠርና ምንም ዓይነት ሰላም እንደሌለ በማሰብ ምርጫው አይካሄድም ብንል ጭራሽ ያባብሰዋል እንጂ ግጭቱን አያስቆመውም። መፍትሔ የሚሆነው ምርጫውን አካሂዶ፣ ነፃና ታማኝነት ያለው የመንግሥት ሥርዓት መዘርጋት ብቻ ነው። ምንም ይሁን ምንም ምርጫው ይካሄዳል የሚለው የውህዱ ፓርቲም አቋም ነው።
ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ ከስሞ ውሁዱ ብልጽግና ፓርቲ መቋቋሙን ገልጸውልናል። ኢሕአዴግ የአራት ድርጅቶች ግንባር መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን ሕወሓት በ11ኛ የኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ የተደረሰበት ስምምነት መርሁን የሳተ እንደሆነ በመግለጽ ውህደቱን ተቃውማል። ይኼ በሆነበት ሁኔታ ውህደት መፍጠሩ ተገቢነው ይላሉ?

አቶ ፈቃዱ፡- ውህዱ ፓርቲ የራሱ አሠራር አለው። በሐዋሳ ጉባዔ ውሳኔ ተካሂዷል። ሁሉም ድርጅቶች፣ አጋር ድርጅቶችንም ጨምሮ ውይይት አድርገው ተስማምተዋል። ውህዱ ፓርቲ ሊኖረው የሚችለውን ጠቀሜታ በሚመለከት ሦስቱ ፓርቲዎችና አምስቱ አገር ድርጅቶች ተወያይተው ስምምነት ላይ ደርሰዋል። እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ከማረጋገጥ አንፃርና አገራዊ አንድነትን ከማረጋገጥ አኳያ ሚዛናዊና ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖር፣ እንዲሁም ሁሉንም በአገር ጉዳይ አካታች በሆነ ሁኔታ በምሁራን ተጠንቶ በቀረበው የውይይት ሰነድ ላይ ውይይት ተደርጓል። ስለዚህ የኢሕአዴግ ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች የውህዱ ፓርቲ አባል ናቸው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በውህዱ ፓርቲ ውስጥ መሳተፍ የሚፈልግ ፓርቲ ካለ እንጂ የግድ ‹‹መደራጀት አለበት›› ተብሎ አይገደድም። ‹‹ገብቶኛል፣ ይጠቅመኛል›› ብሎ ካሰበ የውህዱ ፓርቲ አባል መሆን ይችላል። አልፈልግም ካለም አይገደድም። በራሱ ክልል መንቀሳቀስ ይችላል። ሕወሓት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ ያን ያህል ችግር የለውም። ሕወሓትም ቢሆን በአንዳንድ አመራሮች ከሚሰጥ መግለጫ ባለፈ እንደ ሕወሓት ‹‹አቋሜ ይኼ ነው›› በሚል እስካሁን ያሳወቀው ነገር የለም። ‹‹ውህደቱን አንፈልግም›› ብሎ እንደ ድርጅት ያቀረበው ነገር የለም። ከመገናኛ ብዙኃን ከሚሰማው ባለፈ በትክክለኛ አሠራር ያለው ነገር የለም።
ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ በውስጡ የሚፈጥሩ ማንቸውንም ዓይነት አለመግባባቶች በውስጥ ከመፍታትና ከእነ ችግሮቹም ቢሆን ለሕዝብ ሰላማዊ መስሎ ከመታየት ባለፈ በጽሑፍም ሆነ በቃላት ንግግሮችን የመለዋወጥ ሁኔታዎች አልነበሩም። አሁን አሁን ግን በጽሑፍና በቃላት መነጋገር ከጀመረ ጊዜያትን አስቆጥሯል። ይኼ አካሄድ እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው?
አቶ ፈቃዱ፡- ትክክል ነው። ይህ በተደጋጋሚ ታይቷል። ከድርጅቱ ባህል አኳያ ትክክል አይደለም። ለዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት ሲባል በኅብረተሰቡና አጠቃላይ በአገር ደረጃ የመጣ ከመሆኑ አንፃር፤ በድርጀትም ውስጥ መፈጠሩ አይቀርም። ከዚህ በፊት ኮሚኒስታዊ ዓይነት የሚመስል ‹‹የዴሞክራሲ ሴንትራሊዝም›› ነበር። ማንም ውልፍት አይልም ነበር። ያ አካሄድ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ አይሄድም። ነገር ግን አንዱ እህት ድርጅት በሌላኛው ላይ አላስፈላጊ የቃላት ውርወራና እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት የለበትም። ይኼ አይንተ አሰራር በውህዱ ብልጽግና ፓረቲ ይታረማል። አይጥልም። ወጥ ፓርቲ ሲሆን የተበታተነ አስተሰሰብም ይከስማል። እስካሁን ግንባር ስለነበሩና የየራሳቸው ነፃነት ስላላቸውና የመጠራጠር ሁኔታም ስለነበር የገለጽካቸው ችግሮች መስተዋላቸው አውነት ነው።
ሪፖርተር፡- በደቡብ ክልል ውስጥ ተጠቃሎ የነበረው ሲዳማ ዞን ‹‹ክልል መሆን አለብኝ› ብሎ ባካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ክልልም የመሆን ይሁንታንም አግኝቷል። ሌሎችም ዞኖች ለምሳሌ ወላይታን ጨምሮ በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው። ሁሉንም በዚሁ ሁኔታ እያስተናገዱ መቀጠል ነው? ወይስ ውህዱ ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻልና አሠራሩን ለመቀየር ያሰበው ነገር አለ?
አቶ ፈቃዱ፡- በዚህ ጉዳይ የሕዝብ ጥያቄ ካለ ምንጊዜም ማስተናገድ ነው። ‹‹ክልል መሥርቼ በማንነቴ መኖር እፈልጋለሁ›› ካለ፣ ሕገ መንግሥታዊ እስከሆነ ድረስ ይስተናገዳል። ይኼ ይስማማኛል፣ ይጠቅመኛል ብሎ ካሰበ ይኼንን ነገር በጥናት መመለስ አለበት። ውህዱ ፓርቲ የማንነትን ጥያቄ የሚያስቀር አይደለም። በአግባቡ ለማስተናገድና ከማስቻል በስተቀር የብሔረሰቦች ማንነትንና ብሔራዊ አንድነትን ጠብቆ ማስኬድ ነው። አሃዳዊ መንግሥት እንደሆነ ተደርጎ የሚወራው የተሳሳተ ትርክት ነው። ሕገ መንግሥት ማሻሻልን በተመለከተ ሕዝቡ እስከጠየቀ ድረስ፤ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ አግባብ፣ መክሮና ዘክሮ ‹‹እነዚህ እነዚህ አንቀጾች መሻሻል አለባቸው›› ካለ፣ ፓርቲ ቢዋሃድም ባይዋሃድም ከመሻሻል የሚያስቀረው ነገር የለም።