በኢትዮጵያ ሥራና ሠራተኞች አለመገናኘታቸው ብዙ ጭንቅ አለበት። ሥራው ሲኖር ሠራተኛው፣ የሠራተኛው ጉልበት ሲበዛም ሥራው እየታጣ፤ በርካታ ወጣቶች ሲቦዝኑ እንደሚታየው ሁሉ፣ ሥራውና ሠራተኛውም ሲገናኙ ችግር አያጣቸውም።
በቀን ውስጥ በሕግ የተፈቀደው መደበኛ የሥራ ሰዓት ስምንት ሰዓት ቢሆንም፣ በአገልግሎት፣ በግብርናውና በኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚታየው የሥራ ክንውን ግን አጠያያቂ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ሥራ በተገቢው ጥራትና ብቃት አከናውነው ውጤታማ የሚሆኑ፣ የተሰጣቸውንና የተሰፈረላቸውን የሥራ መጠን ብቻም ሳይሆን፣ ከዚያም አልፈው በመፈጸም ራሳቸውንና ተቋማቸውን የሚያስመሰግኑ ጥቂቶች ናቸው። በተቀረው ግን፤ በዓለም ደረጃ ኢትዮጵያን በዝቅተኛ አምራችነትና ምርታማነት የሚያስፈርጃት፤ የዜጎቿ ሥራ ወዳድነትና ሥራን አክብሮ፣ በጥራትና በብቃት፣ በተቀመጠለትና በሚፈለግበት ወቅት አከናውኖ ውጤታማ መሆን አለመቻል ኢትዮጵያዊ ችግር ይመስላል።
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የታዩ እንደሆነ፤ ቀደም ባለው ጊዜ ‹‹ኃላፊው የሉም፤ ቢሮ አልገቡም፤›› የሚሉ የሥራ ሳንካዎችና የባለጉዳይ እሮሮዎች ይታወሳሉ። አሁን ደግሞ በቴክኖሎጂ ደካማ ጎን እየተሳበበ የሚባክነው የሥራ ጊዜና ሰዓት አይጣል ነው። ‹‹ሲስተም የለምና ኔትወርክ የለም›› የሥራም የደንበኛም ማባረሪያ ስልት ከሆነ ውሎ አድሯል።
በየምድብ ሥራ ቦታቸው ላይ ተሰይመው፣ ደንበኛ በማስተናገጃ ሰዓት የኮምፒውተር ጨዋታ የሚቀናቸው የመንግሥት ሠራተኞችን ማየት የተለመደ ነው። ሥራቸው ከደመወዝና ከምንዳ በቀር ትርጉም የማይሰጣቸው፣ ላልሠሩበትና ላላመረቱበት ጊዜ የርከንና የሌሎች ጥቅማጥቅሞች ጥያቄ በማቅረብ የተጠመዱ፣ ይህ ጥያቄያቸው ምላሽ ላገኘም፣ ሥራቸውን የጥያቄያቸው እሥረኛ የሚያደርጉ፣ የለገሙ ሠራተኞች ሥፍር ቁጥር የላቸውም። እንዲሠሩ የመደቡት ሥራ ገበታቸው ላይ እያላገጡ፣ በአንጻሩ ሥራ ፍለጋ የሚኳትኑ፣ ተምረውም ሳይማሩም ሥራ አጥ የሆኑ ሚሊዮኖች በኢትዮጵያ መሳ ለመሳ ወጥተው ይገባሉ።
እንዲህ ያሉ ሰበብ አስባቦች የኢትዮጵያ ደካማ የሥራ ባህል ማሳያዎች ሊሆኑ ይችሉ እንደሆን እንጂ፣ ከዚህም የከፉ በርካታ የአቅም፣ የዕውቀትና ክፍሎት፣ የሥነ ምግባርና ሌሎችም ችግሮች የኢትዮጵያን ሠራተኞች ምርታማነትና ውጤታማነት ሲጫኑት እየታየ ነው። በቅርቡ ደግሞ በጥናትም እንደተረጋገጠው፣ የአገሪቱ ሠራተኞች ምርትና ምርታማነት ደረጃ ዝቅተኛ ከሚባሉ አገሮችም ዝቅ ያለ ሆኖ ተገኝቷል።
በኢትዮጵያና በጃፓን ባለሙያዎች ትብብር የተደረገው ጥናት ከጥቂት ሳምንታት፤ ምናልባትም በጥር ወር መጀመሪያ ሳምንት ይፋ እንደሚወጣ ይጠበቃል። ይህ ጥናት የኢትዮጵያን የምርትና ምርታማነት ደረጃ ለክቷል። መለካት ብቻም አይደለም። አብዛኞቹ የአገሪቱ ሠራተኞች ከሚሠሩት ሥራ አኳያ የሚከፈላቸው ክፍያ ይበዛባቸዋል በማለት ይሞግታል።
በጃፓን ብሔራዊ የድኅረ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ባልደረባ በሆኑትና በታዋቂው ምሁር ኬኒቺ ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ባልደረባና መሪ ተመራማሪ በሆኑት በኪዳነማርያም በርኸ (ዶ/ር) የተሰናዳው፤ የኢትዮጵያ ምርታማነት ጥናታዊ ሪፖርት ይፋ ከሚያደርጋቸው ዕውነታዎች መካከል አንኳር በሆኑ ግኙቶች ላይ እናተኩራለን።
በምሁራኑ የተካሄደው ጥናት በአብዛኛው ትኩረቱ በአገሪቱ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ የምርትና ምርታማነት ጥናት ትኩረቱም በዚሁ መስክ ላይ ያተኮረ ይመስላል። በጥናት ሪፖርቱ ይፋ እንደሚወጣ የሚጠበቀው አንደኛው ነጥብ፣ ባለፉት 16 ዓመታት ውስጥ ማለትም እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ፤ የሠራኞች ምርታማነት ማደግ የቻለው በ4.9 በመቶ ብቻ ነው። ይህ የሠራተኞች የምርታማነት ዕድገት የሚያጣጥሉት ዓይነት ባይሆንም፣ ከኢትዮጵያ ጋር በተቀራራቢ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ከሚገኙ አገሮች አኳያ ዝቅተኛ የሚባል ሆኖ መገኘቱ ግን አንደኛው እውነታ ነው።
እንደ ኦህኖ (ፕሮፌሰር) ማብራሪያ፣ የ4.9 በመቶ ዕድገት የሚጣጣል ዓይነት ባይሆንም፣ ለኢትዮጵያ ግን አነስተኛና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው። ከሁለት ወራት በፊት ከተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት፤ በአዲስ አበባ የተገኙት ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፣ ስለዚሁ ጥናት ውጤት በጥቂቱ ለሪፖርተር አብራርተው ነበር።
የአንድን ውጤታማ የምርት ሒደት ወይም ሥርዓተ ምርት የሚለካውና በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ዘንድ ‹‹ቶታል ፋክተር ፕሮዳክቲቪቲ›› እየተባለ የሚጠራው መለኪያ፣ በሥርዓተ ምርት ሒደት ውስጥ በግብዓትነት የሚውሉ አላባውያን፤ እንዴት ባለ ውጤታማነትና ብቃት ባለው አመራረት፤ ተፈላጊውን ምርት እንዳስገኙ የሚለካ ዘዴ ነው። የምርት ሒደት ውስጥ ከሚካተቱ አራት ተለምዷዊ መሠረታውያን ማለትም ከካፒታል፣ ከመሬት፣ ከሰው ኃይል ወይም ጉልበት እንዲሁም ከፈጠራ ሥራ ወይም ከኢንትረፕረነርሺፕ መካከል፤ በሰው ኃይል ዘንድ የሚታየው የኢትዮጵያ ሁኔታ ለምርት ዕድገትም ሆነ ውጤታማ አመራረት ሒደት ላይ ችግሮች የሚታዩበት ሆኖ ይገኛል።
በመሆኑም ባለፉት 16 ወይም 17 ዓመታት ውስጥ ከታየው አኳያ፤ አብዛኛውን የኢትዮጵያን የሰው ኃይል ምርታማነት ያመጣው የሠራተኛው ታታሪነት፣ የክህሎትና የዕውቀት፤ ብቃት፤ የሥራ ፍቅርና ለሥራ ያለው አመለካከት እንዳልሆነ በጥናቱ ታይቷል። ይልቁንም በመንግሥት ሲካሄድ የቆየው መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንት የፈጠረው የኢኮኖሚ ዕድገት ተመዘገበ እንጂ፣ እያንዳንዱ ሰው እንደተሰጠው የሥራ ድርሻ፤ እንደሚጠበቅበት መጠን በብቃት አምርቶ፣ በሥራው ውጤታማነት የተገኘ ዕድገት ነው ለማለት እንዳማያስደፍር ጥናቱ አመላክቷል።
እንዲህ ስላለው ጉዳይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የኢኮኖሚ ባለሚያውና ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚስት ቪው›› የተሰኘ ጦማር ከፍተው ኢኮኖሚያዊ እሳቤዎችን ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር እያዛመዱ የሚያብራሩት አቶ ዋስይሁን በላይ አንዱ ናቸው።
እንደ አቶ ዋስይሁን ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያን የሠራተኛ ምርትና ምርታማነት ደረጃ ይህ ነው ብሎ ለመናገር ጥናት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ በየዘርፉ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ መስክ የሚጠቀሰው የጨርቃጨርቅ ዘርፍ፣ በአገልግሎት መስክና በግብርናው አካባቢ የሚታየው የሠራተኛው ዝቅተኛ ምርትማነት እንደሚታይ፣ በኢትዮጵያ ፋብሪካዎች አንድ ሸሚዝ ለማምረት የሚወስደው ጊዜና እንደ ባንግላዴሽ ባሉ የእስያ አገሮች ውስጥ 200 ሸሚዝ ለማምረት የሚጠይቀው የጊዜ በዋቢነት ይጠቀሳል። አሁን አሁን እየተሻሻለ መጣ እንጂ ከእስያውያን ጋር ተመሳሳይ የማምረቻ መሣሪያዎችን በመጠቀም በኢትዮጵያ አንድ ሸሚዝ ለማምረት ቀናት የሚፈጅባቸው ወቅቶች ነበሩ።
በግብርናውም መስክ ለዘመናት ይህ ነው የሚባል የምርታማነት ዕድገት ባለመታየቱ፣ ገበሬው ለዓመታት ሲያመርተው የኖረውን መጠን ብዙም ሳያሻሽል፣ ምርታማነቱ እንደሚጠበቀው ሳያድግ ዘመናት ተቆጥረዋል ያሉት አቶ ዋስይሁን፣ ምርታማነት፤ የግልሰብ ጥረት ከፈጠራ ክህሎትና ከሌሎችም የምርት ግብዓቶች ጋር ተዳምሮ የሚያስገኘው የሥራ ውጤት ወይም ምርት ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ከምርት ግብዓቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የካፒታል ምንነትና ይዘቱ እስከምን ድረስ ነው የሚለው እንደሚያነጋግር፣ ይህ ነው የሚባል ትርጓሜና ይዘት መስጠትም አስቸጋሪ እንደሆነ አብራርተዋል።
የካፒታል መገለጫው ፈርጀ ብዙና ውስብስብ በመሆኑ፣ አንድ ተራ ማጭድና አካፋ፣ ከፋብሪካ፣ ከመጋዘን፣ ከአንድ የማምረቻ ቦታ ጣሪያና ግድግዳ ወዘተ. ሳይቀር በካፒታልነት ይመዘገባል ያሉት አቶ ዋስይሁን፣ ገንዘብና ሌሎችም የሥራ ማስኬጃዎች፤ ካፒታል ውስጥ ስለሚካተቱ፤ ካፒታል እንዲህ ወይም ይህ ነው ብሎ ማስቀመጥ፣ በካፒታል ጽንሰ ሐሳብ ላይ ተመራምረውና የኖቤል ሽልማትን የተቀዳጁ ስመ ጥር ምሁርም፤ ካፒታል ምንድን ነው የሚለውን ፈርጆ ማስቀመጥ እንደሚቸግራቸው መናገራቸውን አስታውሰውዋል። ምርትና ምርታማነት በእንዲህ ያሉት ይዘቶችም ስለሚቃኝ፣ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ምርትማነት የሚያሳዩ ጥናቶች መካሄዳቸው ጠቃሚ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት 17 ዓመታት ገደማ የታየው የሠራተኞች የምርታማነት ዕድገት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ፈጣን ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ ይገባል ያሉት ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፣ ይሁን እንጂ የ4.9 በመቶ ዕድገቱም ቢሆን በሠራተኛው ላብና ድካም፣ በጉልበቱ አስተዋጽኦ ከተገኘው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይልቅ በአብዛኛው በመንግሥት በሚካሄዱ መጠነ ሰፊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች አማካይነት የተገኘ መሆኑን አብራርተዋል። መንግሥት በርካታ የመሠረተልማት አውታሮችን ሲገነባ ኖሯል። አሁንም እንደዚያው። በየከተማው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕንጻዎች ተገንብተዋል። የዚህ ሁሉ ኢንቨስትመንት ውጤት ኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ተንጸባርቋል። ይሁን እንጂ የነጠረ የሠራተኛው ምርታማነት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ያበረከተው ድርሻ ደካማ ነው።
የሠራተኞች ምርታማነትና ለሠሩበት የሚከፈላቸው መጠን አይገኛኝም ያሉት ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፣ ከሚገኘው የሥራ ውጤት ወይም የምርት መጠን ይልቅ ቶሎ ቶሎ የሚጨምረው የሠራተኛው ደመወዝ ሆኖ መገኘቱንም ይጠቅሳሉ። ለዚህ አባባላቸው አጋዥ አላጡም። በኢኮኖሚያዊ ትችቶቻቸው የሚታወቁት የሪፖርተር ጋዜጣ አምደኛ አቶ ጌታቸው አስፋውም ይህንኑ ይጋራሉ። ‹‹ሰው ከሠራው በላይ እየተከፈለው ነው። ይህ አግባብ አይደለም፤›› በማለት ይሞግታሉ። አቶ ጌታቸው እንደሚከራከሩት፣ ሠራተኞች ለሚከፈላቸው ደመወዝና ሌላው ጥቅማጥቅም የሠሩት ሥራ ሚዛን ላይ ሊቀርብ ይገባል። የሥራ ውጤታቸውና የምርት ድርሻቸው እየታየና እየተመዘነ በዚያው አግባብ ሊከፈል ሲገባ፣ ኢኮኖሚ ላይ ጫና በሚያሳድር ደረጃ ሰው ላልሠራበት ሥራ ክፍያ ማግኘት የለበትም በማለት ይኮንናሉ።
ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ሠራተኞች በተለይ የቴክኒክ ክህሎቶችን በቶሎ ይላመዳሉ ቢባሉም፣ ለሥራ ያላቸው አመለካከትና ሥነ ሥርዓታቸው ሲተች ቆይቷል። ፕሮፌሰሩም ይህንኑ ጉዳይ ከጥናቱ ውጤቶች አንዱ ስለመሆኑ አጣቅሰዋል። ‹‹አብዛኞቹ የፋብሪካ ሠራተኞች ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ለመማር በጣም ንቁና ፈጣን ናቸው። ነገር ግን ሰዓት አክብሮ ሥራ ቦታ ላይ መገኘት፣ ሥራ ሳይጨርሱ ከሥራ ቦታ መውጣት፣ ሳያስፈቅዱ ከሥራ መቅረት፣ መሠረታዊ የሥራ ላይ ደህንነት ቁሳቁሶችን በአግባቡ አለመጠቀምና ሌሎችም የሠራተኞች ችግሮቸ ናቸው፤›› በማለት ከሥነ ምግባርና ከአስተሳሰብ ጉድለት የሚመነጩ በማለት ያስቀምጧቸዋል።
እንዲህ ያሉ ጉዳዮች በሠራተኞች ላይ ይሰንዘሩ እንጂ፣ በተለይ የፋብሪካ ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ እንኳንና ለኑሯቸው፣ ለዕለት ጉርሳቸውም የማይሞላ በመሆኑ በርካቶች ከየፋብሪካዎቹ እየፈለሱ እንደሚወጡ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚወጡ መረጃዎች የቅርብ ጊዜ ትውስታ ናቸው። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የሠራተኞች ፍልሰት እንዳስቸገራቸው በየመድረኩ ሲገልጹ ተደምጠዋል። በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ይከሰቱ የነበሩ የሠራተኞች አድማዎችም ሲዘገቡ ቆይተዋል።
ከመንፈቅ ዓመት በፊት ይፋ የተደረገው ጥናት፣ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን በወር ከ26 ዶላር ወይም ከ780 ብር ያልበለጠ ደመወዝ እንደሚከፈላቸው ይፋ አድርጎ ነበር። የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ሜድ ኢን ኢትዮጵያ፡ ቻሌንጅስ ኢን ዘ ጋርመንት ኢንደስትሪስ ኒው ፍሮንቲዬር›› በተሰኘው ጥናቱ፣ ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪው መስክ ከግርጌ የተቀመጠችበትን የ26 ዶላር ወርኃዊ ክፍያ ትከፍላለች ብሏል። ማንይናማርና ባንግላዴሽ በወር 95 ዶላር ለጨርቃጨርቅ ሠራተኞች ሲከፍሉ፣ ላኦስ 128 ዶላር፣ ደቡብ አፍሪካ 244 ዶላር፣ ሌሴቶ 146 ዶላር በመክፈል በአፍሪካ በትልቁ ከሚጠቀሱ አገሮች ተርታ ናቸው። ቻይና 326 ዶላር ስትከፍል፣ ቬትናም 180 ዶላር ትከፍላለች። ምንም እንኳ የኢትዮጵያን የአምራች ኢንዱስትሪ በውጭ ባለሀብቶች ዘንድ ተመራጭ ከሚያደርጉት መስፈርቶች መካከል ዝቅተኛ የሠራተኞች ደወመዝ ክፍያ መኖሩ ዋናው ምክንያት ቢሆንም፣ የሠራተኞች ምርታማነት ደካማ መሆኑ፣ ለኢንዱስትሪ ያላቸው ተሞክሮና ክህሎት አናሳ መሆኑ ሳያንስ፤ የኢንዱስትሪ ሥራ ባህልን አለማወቃቸው ኢትዮጵያውያንን ሲያስተች ቆይቷል።
ይህም ይባል እንጂ በአትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ርከን የሚወሰንበት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ትግበራው እየተጠበቀ ነው። ይህ የመደወዝ ርከን መምጣቱ በሠራተኞች ላይ የምርታማነት ጥያቄና በሠሩት ልክና መጠን ክፍያ ሊያገኙ እንደሚችሉ ከወዲሁ የሚያሳስቡ ምልክቶች እየታዩ ነው። አብዛኞቹ የውጭ ኩባንያዎች በሠራተኞች ጥቅማጥቅምና ክፍያ ላይ በሚመሠረት የፍርድ ቤት ክርክር ጊዜ ማጥፋታቸውን በመግለጽ፤ የሕግ ማሻሻያ እንዲደረግ ሲጠይቁ ቆይተዋል። ይህንን ሊያሻሽል የሚችል የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ እየተጠበቀ ነው።
የሠራተኞች ምርታማነት ዋናው ማጠንጠኛ ሆኖ፤ ከኢኮኖሚው ዕድገት ውስጥ የሠራተኞች ምርታማነት አስተዋጽኦ በ4.9 በመቶ መገደቡ ፈታኝ እንደሆነ የገለጹት ኦህኖ(ፕሮፌሰር)፣ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጋር በተመጣጣኝ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች የምርታማነት ዕድገታቸው ከሰባት እስከ አሥር በመቶና ከዚያም በላይ እንደሚያስመዝግቡ አስታውሰዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም በዜጎች የምርታማነት አስተዋጽኦ ላይ መመሥረት እንደሚገባው፣ መንግሥትም ከሚቀጥራቸው አብዛኞቹ ሠራተኞቹ የሚገባውን ያህል ምርታማነትና ውጤታማነትን በመለካት፤ ውጤትን መሠረት ያደረግ የደመወዝና ጥቅማጥቅም ክፍያዎችን መተግበር እንደሚገባው መክረዋል። የሠራተኞችን የምርታማነት ደረጃ የሚለካው የምሁራኑ ጥናት ዝርዝር መረጃዎችን በማውጣት፣ በየትኞቹ የኢኮኖሚው ዘርፎች የተሠማሩ ሠራተኞች፤ ምን ያህል ውጤታማ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ እንደሚያሳይ ተስፋ ተጥሎበታል። እስካሁን ባለው ሁኔታም የኢትዮጵያ አምራቾች የምርትና ምርታማነት ደረጃ ይህ ነው ተብሎ በጠቅላላው የተቀመጠበት የጥናት ውጤት ባለመኖሩ፣ የእነ ኦህኖ (ፕሮፌሰር) ጥናት ይፋ እስኪወጣ እየተጠበቀ ነው።