የሙዚቃ ስልቱ እንዲማረክ ያደረገው አብሮነታቸውና ብዙ በመሆናቸው ነው። በአፋቸው ከያዙት ቀርከሃ መሰል ነገር የሚወጣው ድምፅ የተለያየ ነው። በቁጥር 20 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ክብ ሠርተው በአፋቸው የያዙት የትንፋሽ መሣሪያ በተጨማሪ የሰውነታቸውና እጅግ የሚያምረው የእግራቸው እንቅስቃሴ ቀልብ ይስባል። ለእነርሱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው በመሆኑ በመካከላቸው አንዱም ቅደም ተከተሉን የሚስት የለም። የትንፋሽ መሣሪያውን የእግራቸው እንቅስቃሴ ሲጨመርበት ልዩ ድባብ ይፈጥራል። የትንፋሽ መሣሪያው ፊላ ይባላል። ፊላ የትንፋሽ መሣሪያ ብቻ አይደለም፣ የውዝዋዜውም መጠሪያ ጭምር እንጂ። በደቡብ ክልል በሚገኘው የጋርዱላ ኅብረተሰብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው የሙዚቃ መሣሪያ ዳንስ (ውዝዋዜ) ፊላ ነው። ፊላን የሚጫወቱት የደራሼ፣ የኩስዬ፣ የሞሴዬና የማሾሌ ብሔረሰቦች ናቸው። የሙዚቃ መሣሪያቸው የሚሠራው ከቀርከሃና ከሸንበቆ ሲሆን፣ በአማካይ ከአንድ ሜትር እስከ አምስት ሳንቲ ሜትር የሚደርስ ቁመት፣ በአንድ በኩል ክፍት፣ በሌላኛው ደግሞ ድፍን የሆነ የሙዚቃ መሣሪያ ነው። የሙዚቃ መሣሪያው ብዛቱ አነስተኛ የሚባለው 24 ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ስምንት ተመሳሳይን በመጨመር 48 የሚደርስበት ጊዜ አለ። 24ቱም ለፊላ ለሙዚቃ የተሰናዱት የሙዚቃ መሣሪያዎቹ ሁሉም የተለያዩ ድምፅ ያወጣሉ። ይህንኑ የሙዚቃ መሣርያ ማዕከል ያደረገ የባህል ፌስቲቫል በርዕሰ ከተማዋ ጊዶሌ በጥር አጋማሽ ተካሂዷል። ፎቶዎቹ የፌስቲቫሉ ነፀብራቆች ናቸው።