ለአፍሪካ እግር ኳስ ልማት አንድ ቢሊዮን ዶላር መድቧል
ከስድስት አሠርታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (አፍኮን) በየአራት ዓመቱ እንዲካሄድ የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ፊፋ) ምክረ ሐሳብ አቀረበ፡፡

በአፍሪካ እግር ኳስ መሠረተ ልማትና ውድድሮች ላይ ትኩረቱን ባደረገውና በሞሮኮ ራባት ጥር 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው የካፍ ሴሚናር ላይ የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ባሰሙት ዲስኩር፣ “በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው አፍሪካ ዋንጫ አውሮፓውያኑ ከሚያስገኙት ገቢ ሲነፃፀር በሃያ እጥፍ ያነሰ ነው። በዚህ አካሄድ በየሁለት ዓመቱ ማካሄዱ አዋጪ ነው? እስቲ በየአራት ዓመቱ ማካሄድን ከግምት ውስጥ እናስገባው” ማለታቸውን ቢቢሲ በድረ ገጹ ዘግቧል።
ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ እንደቀድሞው በጥር 2013 ዓ.ም. በካሜሩን አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን ዓምና ቀድሞ ከሚካሄድበት ወቅት በተለየ መልኩ በሰኔ ወር ግብፅ በ24 ቡድኖች መካከል መካሄዱ ይታወሳል፡፡
ኢንፋንቲኖ የአፍሪካን እግር ኳስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ካለ ቦታ ለማድረስ ያለመውን ፕሮጀክታቸውን በሦስት ዓበይት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የፊፋ/ካፍ የጋራ ስትራቴጂን አብራርተዋል፡፡
“ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎችን ማበልፀግ አለብን፡፡ ለዚህም ሦስት ቁልፍ ጉዳዮችን ማለትም በዳኝነት፣ በመሠረተ ልማትና በውድድሮች የሚታዩት ችግሮች ለመፍታት መነሳት አለብን፡፡
“ስለ አፍሪካ እግር ኳስ ልማት ለበርካታ ዓመታት ስናወራ ኖረናል፡፡ ፔሌ በአንድ ወቅት የአፍሪካ ቡድን የፊፋን የዓለም ዋንጫ እንደሚያሸንፍ ተንብዮ የነበረ ቢሆንም ዕውን አልሆነም፡፡ ይህም ዕድገት እያሳየን እንዳልሆነ ያመለክታልና ቆም ብለን ማሰብ ይገባናል፡፡ ለአፍሪካ እግር ኳስ ልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመር አለብን፡፡ አንድም የአፍሪካ አገር የዓለም ዋንጫን አላነሳም፡፡ አፍሪካ ወደ ኋላ መቅረቷን ያሰማል፤” ሲሉ ኢንፋንቲኖ አክለዋል፡፡
ፊፋ አዳዲስ የውድድር መርሐ ግብሮች እንደሚጀምርም ያስታወቀ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ሊግ እና የፓን አፍሪካን ክለቦች አዲስ ውድድር ይገኙበታል፡፡
በፊፋ ፕሬዚዳንት የቀረበው አዲሱ የፓን አፍሪካን ክለቦች ውድድር ትልም 20 ቋሚ ክለቦች በአባልነት የሚያዙበትና ተጨማሪ ክለቦች ከዞን ውድድሮች የሚያልፉበት ይሆናል፡፡
ፊፋ በተጨማሪም ከካፍ ጋር በመሆን የፕሮፌሽናል ዳኞች ስብስብ በመፍጠር በፋይናንስና በሥልጠና ለመደገፍና ለማደራጀትም አስቧል፡፡
“20 የአፍሪካን ምርጥ የፊፋ ዳኞችን በመውሰድ ፕሮፌሽናል የማድረግና በቋሚነት የመያዝ ዕድ አለን፤” ብለዋል ኢንፋንቲኖ፡፡
በኢንቨስትመንት መስክም የፊፋ ፕሬዚዳንት ቢጋር እንደሚያመለክተው ዘላቂ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት በአፍሪካ ዕውን ይሆናል፡፡
“አንድ ቢሊየን ዶላር በመመደብ ለፊፋና ካፍ 54 አባል ፌዴሬሽኖች በየአገሮቻቸው አንድ ምርጥ ስታዲየም ለመገንባት እቅድ ይዘናል፤” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በጣም ጥሩ ስታዲየም ባለባቸው አገሮች ግን ኢንቨስትመንቱ በሌላ መሠረተ ልማት ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ በ1949 ዓ.ም. በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም መመሥረታቸው ይታወሳል፡፡ በመሥራች ጉባዔው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ወክለው የተገኙት አቶ ይድነቃቸው ተሰማና ሻለቃ ገበየሁ ዱቤ (በኋላ ሌተና ኮሎኔል) እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
አቶ ይድነቃቸው በምሥረታው ጊዜ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ተመርጠው ለ15 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ዜና ዕረፍታቸው እስከተሰማበት ድረስም ለአራት ተከታታይ ዙሮች ለ15 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡
ኢትዮጵያና የአፍሪካ ዋንጫ
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 1949 ዓ.ም. ከመሠረቱት አራት አገሮች ግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው የመጀመርያዎቹን ሦስት አሠርት በበላይነት የመራችው ኢትዮጵያ ናት፡፡ በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በፕሬዚዳንትነት 30 ዓመት የመሩት የኮንፌዴሬሽኑ መሐንዲስ የነበሩት ነፍስ ኄር ይድነቃቸው ተሰማ ይጠቀሳሉ፡፡ በእርሳቸው ዘመን ኢትዮጵያ ያገኘችው ከፍተኛው ውጤት በ1954 ዓ.ም. በመዲናዋ ያዘጋጀችው ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በነመንግሥቱ ወርቁ አማካይነት መቀዳጀቷ ነው፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ የተካሄደው በካርቱም ሲሆን ውድድሩም የተካሄደው በአራት ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ማለትም በኢትዮጵያ፣ በአስተናጋጇ ሱዳን፣ በግብፅና በደቡብ አፍሪካ መካከል ነበር፡፡ ከካፍ መሥራች ጉባዔ በኋላ ውድድሩ በወርኃ የካቲት 1949 ዓ.ም. ሲከናወን በወጣው ዕጣ መሠረት ግብፅ ከሱዳን፣ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ይደርሳቸዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ የምልከው ቡድን ወይ የጥቁር አሊያም የነጭ ቡድን እንጂ ቀላቅዬ አልክም በማለቷና የአፓርታይድ ሥርዓትን ማራመዷ በመታወቁ ከውድድሩ በፎርፌ እንድትሸነፍ፣ እንዲሁም ከመሠረተችው ኮንፌዴሬሽን እንድትባረር ተደርጓል፡፡
እዚህ ላይ ደቡብ አፍሪካን በምትከተለው የአፓርታይድ ሥርዓት ምክንያት ከካፍም ሆነ ከዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች እንድትታገድ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ያደረጉት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ናቸው፡፡
የካፍ ሕገ ደንብ ሲዘጋጅ በዋናነት ካረቀቁት አንዱ የነበሩት ይድነቃቸው የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና ምክትል ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ በደቡብ አፍሪካ በዘር ላይ የተመሠረቱትን የነጭና እንዲሁም የጥቁርና የሌሎች ዘሮች ሁለት ፌዴሬሽኖችን አምርረው ተቃውመዋል፡፡
የካፍ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሱዳናዊው አብደልሃሊም መሐመድ በ1979 ዓ.ም. ለካፍ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ይድነቃቸው በዚህ ጉዳይ የነበራቸውን አቋም እንዲህ ገልፀውታል፡-
“ደቡብ አፍሪካውያን በዘር በተከፋፈለ አሠራራቸው ለአራት ዓመታት ሲጠቀሙ ማንም ተቃውሞውን ያሰማ አካል አልነበረም። ይድነቃቸው የካፍ ሥራ አመራር ከሆነ በኋላ ግን ይህንን ፍፁም እንደማይቀበለው አስታወቀ። በስብሰባዎች ላይም ደቡብ አፍሪካ ነጮችንም ጥቁሮችንም ያካተተ ቡድን ካልመረጠች ከካፍ መታገድ እንደሚኖርባት አጥብቆ ተከራከረ።”
ይህም ጥረታቸው ደቡብ አፍሪካን ከመነሻው ከአፍሪካ ዋንጫ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዓመታት ባደረጉት ግንባር ቀደም ትግል ከዓለም ዋንጫም ሆነ ከኦሊምፒክ እንድትታገድ አስደርገዋል፡፡
በመጀመርያው የአፍሪካ ዋንጫ በተገኘው ውጤትም ግብፅ ሱዳንን 2ለ1 በማሸነፍ፣ ኢትዮጵያም ደቡብ አፍሪካን በፎርፌ 2ለ0 በመርታት ለፍጻሜው በቅተዋል፡፡ የካቲት 9 ቀን 1949 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1957) ኢትዮጵያና ግብፅ ለዋንጫ ባደረጉት ግጥሚያ የግብፅ ብሔራዊ ቡድን 4ለ0 ለዜሮ አሸንፎ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ በ1951 ዓ.ም. የማስተናገድ ተራው የደረሳት ግብፅ ስትሆን፣ ተሳታፊዎቹም በአንደኛው የተካፈሉት ናቸው፡፡ ካይሮ ላይ በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ በግብፅ 4ለ0፣ በሱዳን 1ለ0 በመሸነፍ አጠናቃለች፡፡
ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት ዕድሉን ኢትዮጵያ ያገኘች ሲሆን በመርሐ ግብሩ መሠረት መካሄድ የነበረበት በ1953 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1961) ቢሆንም በኢትዮጵያ በታኅሣሥ 1953 ዓ.ም. በነበረው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሳቢያ ውድድሩ በአንድ ዓመት ተራዝሞ በጥር 1954 ዓ.ም. እንዲካሄድ ሲደረግ ተካፋዮቹ ከአስተናጋጇ ኢትዮጵያ ከመሥራች አባላቱ ግብፅና ሱዳን በተጨማሪ የገባችው ቱኒዝያ ነበረች፡፡
በመርሐ ግብሩ መሠረት ኢትዮጵያ ከቱኒዝያ፣ ግብፅ ከሱዳን የደረሳቸው ሲሆን ጥር 6 ቀን 1954 ዓ.ም. ቱኒዚያን የገጠመችው ኢትዮጵያ 4ለ2 በማሸነፍ ለዋንጫ በማለፍ ከሌላኛው ምድብ ድል የቀናትን ግብፅን ጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም. በመግጠም 4ለ2 ረትታ የሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ አግኝታለች፡፡
በጋና አክራ በ1956 ዓ.ም. በተከናወነው አራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለድሏ ኢትዮጵያ ቱኒዚያን 4ለ2 ስትረታ፣ በጋና 2ለ0 ተሸንፋለች፡፡ ለሦስተኛነት ከግብፅ ብሔራዊ ቡድን ጋር ባደረገችው ግጥሚያ 3ለ0 በመሸነፏ ሻምፒዮናውን በአራተኛነት አጠናቃለች፡፡ በቱኒዝያ በተከናወነው አምስተኛው ዋንጫ ለመካፈል ብትችልም ያለውጤት ተመልሳለች፡፡
ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካን ዋንጫ ለማዘጋጀት ዕድል ያገኘችው በ1960 ዓ.ም. ሲሆን ጨዋታዎቹም የተከናወኑት በአዲስ አበባና በአሥመራ ከተሞች ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት አግኝቶ የነበረው ብሔራዊ ቡድኑ ቢሆንም በለስ አልቀናውም፡፡ በዚህ በውድድሩ ዑጋንዳን፣ አይቮሪኮስትንና አልጄሪያን በማሸነፍ ከምድቡ በመሪነት ለፍጻሜ ግማሽ ቢያልፍም መሻገር አልቻለም፡፡ በፍጻሜ ግማሽ በአሥመራ ምድብ ሁለተኛ ሆኖ በጨረሰው ኮንጎ ኪንሻሳ 3ለ2 ለሁለት በመረታቱ የዋንጫው ጉዞ ቆሟል፡፡ ለደረጃም ያልበቃው ከአይቮሪኮስት ጋር ጥር 12 ቀን 1960 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባደረገው ግጥሚያ 1ለ0 ተረትቶ አራተኛ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያን በፍጻሜ ግማሽ ያሸነፈው ኮንጎ ኪንሻሳ ጋናን 1ለ0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወቅቱ ባሳየው የአጨዋወት ጥበብና ክሂል ‹‹የአፍሪካ ብራዚል›› ተሰኝቶም ነበር፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ በሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፈ በኋላ ተከታታይ ሁለት ዋንጫዎችን ሳያልፍ ቆይቶ የተገናኘው 10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ላይ በ1968 ዓ.ም. ሲስተናገድ ነበር፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው የምድብ ጨዋታዎች ስኬታማ መሆን አልቻለም፡፡ ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላም የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ዙር ተካፋይ ለመሆን የበቃው በ1974 ዓ.ም. ሊቢያ በተዘጋጀው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በመንግሥቱ ወርቁ አሠልጣኝነት ዘመን ነበር፡፡
ከ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ እስከ 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ በተካሄዱ 15 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ብሔራዊ ቡድኑ ሳይሳተፍ ቆይቶ ለስኬት የደረሰው ከ31 ዓመታት በኋላ በ2005 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 29ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው፡፡
“ዋሊዎቹ” የሚል ቅፅል ስም የሚታወቀውን ብሔራዊ ቡድን ለዚህ ያበቁት ዋና አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡
ከሰባት ዓመታት በፊት ከተከናወነው የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ በተከናወኑት ውድድሮች ወደ ፍጻሜው ዙር መዝለቅ ያልቻሉት ዋሊያዎቹ፣ በዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብርሃቱ መሪነት እያካሄዱት ያሉትን የምድብ ማጣሪያ ተሻግረው ከአንድ ዓመት በኋላ በካሜሮን በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ይችሉ ይሆን?