ባለፈው ወር ሪፖርተር መጽሔት ቅጽ 1 ቁጥር 01 እትም ላይ ለፍትህ ስርአቱ መድከም ምክንያት ናቸው ብየ ያመንኩባቸውን ነጥቦች ለመጠቆም ሞክሪያለሁ፡፡ ለፍትሕ ስርአቱ መድከም ተጨማሪ ምክንያቶችንና መፍትሄ ይሆናሉ ያልኳቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው አቅርቢያለሁ፡፡ |
የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አወቃቀር፤ የዳኞች ነፃነትና ገለልተኝነት እንዲሁም የዲስኘሊን ክሶች
የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን የጉባዔው አደረጃጀት የተለያየ ስብጥር ያለው መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሚመለከተው ጉዳይ የዳኞች ምልመለና ሹመት፣ጥቅማጥቅም፣ ጡረታ፣ የዳኞች አመዳደብና የዳኞች የዲስኘሊን ጉዳይ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ መሠረት የሚያደርገው ደግሞ ዳኞች ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሥራቸውን በሕግና በንፁህ ህሊና ማስረጃን መዝነው ውሣኔ እንዲሰጡ ማስቻልን ነው፡፡ ዳኞች በውስጥም ሆነ በውጭ ተጽእኖ ነፃ እንዲሆኑ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጠንክሮ ሊሰራ የሚገባው ዋነኛው ሥራ ከመሆኑ አንፃር፤ በጉባዔው ውስጥ የሚፈጠረው የአባላት ስብጥር ደግሞ አንዱ መሆኑ አይቀርም፡፡
ዳኞች ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ ናቸው ሲባል አንዱ በጀታቸውን ራሳቸው ለተወካዩች ምክር ቤት ማቅረብ የሚችሉበት ስርዓትን መዘርጋት የሚገባ ሲሆን የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በጀቱን ወደ ፖርላማ እንዲያቀርብ አለመደረጉ አንዱ ከበጀት አንፃር ነፃነቱ የተገደበ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት ያ ችግር ተፈትቶ የራሱን በጀት በቀጥታ ማቅረብ ችሉል፡፡የጉባዔው ስብጥርን ስንመለከት በአንድ ወገን ተከራካሪ የሆኑ ወገኖች በሌላ በኩል ደግሞ የጉባዔ አባላት በመሆን ተካተው የሚኙ መሆኑን እናያለን፡፡ነፃነት አንፃራዊ ከመሆኑ አኳያ የዳኞች ጉዳይን የሚመለከቱ አባላት በአሰራር ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ የማይፈጥሩ ቢሆኑ እንኳን ለዳኛው ህሊና ነፃ እንደሆነ የማያስቆጥረው አንዱ ነገር ይሆናል፡፡
በሌሎች ሀገሮች በዚህ ደረጃ የሚመረጡ ሰዎች ከራሳቸው የውስጥ ተጽእኖም ሆነ ሌሎች ተጽእኖ ሊያደርጉባቸው የማይችሉ የሰለጠነ አመለካከት ያላቸው ትልቅ ስብዕና ያላቸው ሰዎች ስለሚሆኑ፤ ሥልጣኔውም የሚረዳቸው እና በጥቃቅን ነገሮች ውስጥ የተዘፈቁ ባለመሆናቸው በጉባዔ አባልነት ቢካተቱ በነፃነቱ ላይ እምብዛም የሚፈጥሩት ነገር እንደማይኖር ይገመታል፡፡ በእኛ አገር ግን የእነዚህን አይነት ስብዕና ያላቸውን ሰዎች ለማፍራት ብዙም ያልተሰራበት ሥልጣኔውም ብዙም ያልገባን ሰዎች ተቋምን ቢወክሉም ነገር ግን ከግል ጥቃቅን ፍላጐቶቻቸው የፀዳ አመለካከት የማይኖራቸው ከመሆኑ አኳያ ወደ ጉባዔ አባልነት መካተታቸው የግድ በውጩ አለም የሚደረገውን ላድርግ ከማለት ውጭ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ በዳኞች ሹመት፣ጥቅማጥቅም፣ እና የዲስኘሊን ጉዳይ ላይ በገለልተኝነት ጉዳዩችን ያያሉ ከራሳቸው እና ከሌሎች ተጽእኖም ይፀዳሉ ብዬ ለማለሰብ ስለምቸገር ተከራካሪ የሆኑ ተቋማትን የሚወክሉ እንዲሁም ጠበቆችን የሚወክሉ መካተታቸው በራሱ ነፃነቱን እና ገለልተኝነቱን ይጐዳዋል ባይ ነኝ፡፡
በረጅም ጊዜ ልምዳችንም ያየነው የዳኞች ምልመላ ላይ በቀጥታ እነዚህ ሰዎች እጃቸውን እንደሚያስገቡ ተሰሚነቱም ስላላቸው በእነሱ ስር ያሉ ተከራካሪዎች የሚፎክሩበት ሁኔታ መኖሩን፣ የዳኞች ጥቅማጥቅም ጉዳይ ሲነሳም ቀንደኛ ተቃዋሚ የሚሆኑ መሆናቸውን የዲስኘሊን ጉዳይን በተመለከተም ተከራካሪ በሆኑበት ጉዳይ ፍርድ እንዲያጋድልላቸው ይህ ካልሆነ ግን የሚከሱ መሆኑን በመግለጽ ማስፈራሪያ የሚያርጉ እና ሌሎች ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን የዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነት የሚጉዱ ነገሮች ሲተገበሩ አስተውለናል፡፡ የዲስኘሊን ክስን አስመልክቶም የሚቀርቡ አቤቱታዎች ለፍ/ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች የሚቀርብ የነበረ እና ወደ ፍርድ ምርመራ የሚመራው አቤቱታውን ያየው ኃላፊ ሆኖ እንደገና በጉባዔ አባልነቱ ደግሞ ያንኑ ቀድሞ በአቤቱታ የሚያውቀው ጉዳይ ክስ ሆኖ ሲቀርብለት በጉዳዩ ላይ አብሮ የሚወስን መሆኑ፣ የፍርድ ምርመራ ክፍሉ ስለ ዳኝነት ስራ በስራው ላይ ያላለፉ ባለሙያዎች ያሉበት በመሆኑ የዳኝነት ሥራ እና የዲስኘሊን ጥፋትን የማይለዩ ከመሆኛቸው የተነሣ ዳኛ በወሰነው ውሣኔ ክስ የሚያቀርቡ መሆኑ፣የሚቀርበው አቤቱታ በቀጥታ ለዳኛው የሚደርሰው እና መልስ የሚሰጥበት ከመሆኑ ውጭ ከቀረበው አቤቱታ ውስጥ የቱ የዲስኘሊን ጥፋት እንደሆነ በመለየት ድርጊቱም በዲስኘሊን የሚያስቀጣ ስለመሆኑ ድንጋጌ ሳይጠቀስ በደፈናው መልስ እንዲሰጥ ከሚደረግ በቀር አንዳንዶቹ በቀረበባቸውን ማስረጃ እንኳን ቀርበው የማስተባበል እድል ሳይሰጣቸው ውሣኔ የሚያገኙ መሆኑና ሌሎችም የተለያዩ ነገሮች መፈፀማቸው የዳኝነት ነፃነቱና ገለልተኝነቱ እንዲሸረሸር ምክንያት ሲሆን ቆይቷል፡፡ በዚህ የጉባዔው አሰራር የተነሳም ዳኞች እየለቀቁ መሄዳቸው፣ እንዳይከሰሱ በማሰብ ታዛዥ መሆናቸው፣ በፍትሀት የተሸበቡ መሆናቸው እንዲሁም መቼ በሰሩት ስራ መቼ እንደሚከሰሱ ያለማወቃቸው እና የክስ የይርጋ ጊዜ አለመኖሩ በራሱ ዳኞች ነፃነታቸውን ተነጥቀው እንዲያገለግሉ ያደረገ ሆኖ ከርሟል፡፡
ሌላው ለፍትህ ስርዓቱ መዳከም ምክንያት ራሱ መንግስት አስተዋጾ አድርጓል፡፡ የዳኝነት ክፍሉ በመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ውስጥ ከሶስቱ አካል አንዱ አካል ሲሆን፣ ዳኞች ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ አንዱና ዋነኛው ያለመከሰስ መብት ሲኖራቸው ነው፡፡
የፖርላማ አባላት፣ የክልል/በተለይም የኦሮሚያ / ዳኞች፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነርና በስሩ የሚኙ ባለሙያዎች ሌሎችም ያለመከሰስ መብት ያላቸው ሲሆን፤ የፌዴራል ዳኞች ግን ያለመከሰስ መብት ተጠቃሚ ባለመሆናቸው በነፃነት በሕግ የተሰጣቸው ተግባር ለመፈፀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ለማሳያ እንዲሆንም አንድ ወቅት ላይ አንድ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኛ በሙስና ተጠርጥሮ ወደ ቢሮው እየገባ እያለ ፍ/ቤት ግቢ ውስጥ ተይዞና በፖሊስ ታጅቦ የተወሰደ ሲሆን ያ ዳኛ ከታሰረ በኋላ ግን ጉዳዩ ተመርምሮ ነፃ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ሌላው ዳኛም እንዲሁ ወደ ሰርቪስ ሊገባ ሲል ከጓደኞቹ መሐከል በፖሊስ ተይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰደ መሆኑንና ዳኛ መሆኑን እንኳን ቢናገር እሱን ፖሊስ ጣቢያ ትናረራለህ ተብሎ የተወሰደና በመጨረሻም የተጠረጠረበት ጉዳይ እሱን የማይመለከት ሆኖ ሊለቀቅ ችሏል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ክስ ደርሶት ክሱን ሳይከላከል መሰናበቱን በሚዲያ የሰማ ዳኛም አይጠፋም፡፡ ይህ የሚያሳየን ዳኞች በሚሰጡት ውሣኔ ላይ ከፍ ያለ ስጋት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ በመሆኑ ማን መቼ እንደሚይዛቸው ለምን እንደሚያዙ ስለማይታወቅ ተሸማቃቂ አድርጓቸው ይገኛል፡፡ እንዲሁም መዝግስት የዳኝነት ክፍሉ እንደ ሶስተኛው የመንግሥት አካል ያለመቁጠርና የሚገባውን ደረጃ እና ቦታ ያለመስጠት በውስጡ ባሉት ዳኞች ላይ በተለያዩ ነገሮች ጫናን ፈጥሯል፡፡ ዳኞች በመንግሥት አይን የሚታዩት ከአስፈፃሚው አካል ባለነሰ መሆኑ፣ በአዋጅ የተቀመጠላቸውን መብት እንኳን የማይጠበቅላቸውና በእንግልት የሚኖሩ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በየትኛውም ተቋም ጉዳይ ኖራቸው ቢሄዱ እንደ አንድ የመንግሥት ከፍተኛ አካል ሳይሆን የሚታዩት በራሱ ዳኛ መሆናቸው ጉዳያቸው እንዳይፈፀምላቸው ጋሬጣ ሆኖባቸው መክረሙ በሁሉም ዳኞችና በፍ/ቤቶች አስተዳደር ኃላፊዎች የሚታወቅ ሃቅ ነው፡፡
ሌላው ለፍትህ ስርአቱ መዳከም ማህበረሰቡ የራሱን አስተዋጽኦ ያደረገ መሆኑም መረሳት የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ በየታክሲው፤ በየመንገዱ፤ በየለቅሶውና በየድግሱ ሁሉ የፍትህ ስርአቱ ሞቷል ዳኞች ፣ዐቃብያነ ሕጐችና ፖሊሶች ጉቦኞች ናቸው አልያም በዘመድ አዝማድ ነው የሚሰሩት እያለ ሲያወራ ይሰማል፡፡
በየትኛውም መንግሥታዊ ተቋም አንድ ዳኛ፤ ዳኛ ነኝ ብሎ መታወቂያውን አሳይቶ ለመገልገል የሚፈራበትና የሚሸማቀቅበት በወሬው መሃከል ገብቶም እስኪ ምን አይታችሁ ነው ማነው የተበደለው ብሎ መጠየቅ የማይችልበት ደፈር ብሎም ከጠየቀ ማስረጃ በሌለው ነገር ሁሉም ተረባርቦ አፉን የሚያዘጋበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ማህበረሰቡ አንዱ ከአንዱ እየተቀባበለ ልክ በህፃንነታችን ጭራቅ መጣ ስንባል ጭራቁን ሳናየው ጭራቅ ጭራቅ እያልን እንደምንሸሽና አንድ ጭራቅ ተነግሮን አስር ጭራቅ ብለን የምናወራበት ሁኔታ አይነት ሌባ ሌባ በማለት የደከመውን የፍትህ ስርአት በደንብ እንዲወድቅ ያደረገ ተግባር ተፈጽሟል፡፡
ማህበረሰቡ የራሱ የሆነውን የፍትህ ስርዓት ችግር ጠጋ ብሎ ምንድን ነው ችግሩ በምን መልኩ መደገፍ እችላለሁ ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ፤ ወሬን እየተቀባበሉ የበለጠ እንዲደክም ማድረግ ተገቢ ካለመሆኑም በላይ አንዳንዱ ወሬውን የሚነዛበት ፍ/ቤት የት እንደሆነ እንኳን የማያውቅ ማን የሚባል ዳኛ ምን እንዳደረገ እንኳን የማያውቅ ዝም ብሎ ሰው ስላወራ ብቻ ተከትሎ የሚያወራ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
አንድ ቀን ከመገናኛ ጦርሃይሎች ታክሲ ውስጥ ተሳፍሬ ስለዳኛ ጐቦኝነት አንዱ ጨዋታ አነሳ፡፡ ሙሉ ታክሲው ዉስጥ ያለው ሰው የዳኞችን ጉቦኝነትና በዘመድ አዝማድ መስራት ጨዋታ አድርገው ሃሜቱ ሲጧጧፍ ስላላስቻለኝ ዋና ጨዋታውን ያነሳውን ሰው ማንነቴን ሳልገልጽ በምን ጉዳይ ፍ/ቤት ሄደው ነው ብዩ ጠየቅሁት፡፡ ጉዳዩን ሊነግረኝ አልቻለም፣ እሺ የትኛው ፍ/ቤት ነው ብዩ ብጠይቀው ፍ/ቤቱንም አያውቀውም እናስ ማን የሚባል ዳኛ ነው ምን አድርግ አለህ ብዩ ስጠይቀው ሊመልስልኝ አልቻለም፡፡ አየህ አንተ የምታወራው ሰው ያወራውን ተከትለህ እንጂ አንተ ፍ/ቤቱንና ጉዳዩን እንኳን ያላወቅህ በመሆንህ ዝም ብሎ ስም ማጥፋት ስለሚሆን ከአንተ አይጠበቅም ትልቅ ሰው ስለሆንክ ብታስተካክለው ስለው ሁሉም በታክሲ ውስጥ ያለው ሰው በራሱ ወሬ አፍሮ ዝም አለ፡፡ ሰውየውም የሚናረገው ውሸት መሆኑን ስለተረዳ ይቅርታ ጠየቀኝና ግን አንቺ ማነሽ ብሎ ሲጠይቀኝ እንማ እንደአንተው በፍ/ቤት የምገለገል ሰው ነኝ እናም አንተ እንዳወራኸው አይነት ነገር ቢገጥመኝ በቀጥታ ሄጄ ለፍ/ቤቱ ኃላፊዎች አመለክታለሁ፡፡ በችሎትም ላይ ለዳኛው ይህንኑ አንስቼ እውነትነቱን አረጋግጣለሁ ስለው እውነት ነው በዚህ መንገድ አልታየኝም ነበር ብሎ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ እናም ማህበረሰቡ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ችግር እንዳለ የሚታወቅ ቢሆንም ነገር ግን ማህበረሰቡ በሚለው ስፋት ግን ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለንም፡፡ በዛም ላይ ወሬውን የሚያወሩ ሰዎች የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል እንዲረዳ በትክክል ማስረጃ እንዲሰጡ ማንነታቸውን እንዲገልፁ ወይም የመዝገብ ቁጥርና የፍ/ቤት ስም የችሎት ስም እንዲገልፁ ቢጠየቁ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ጥሩውን ከመጥፎ መለየት ስላልተቻለ ሕዝቡ በፍትህ ስርዓቱ በአግባቡ እንዳይገለገል አይነተኛ ምክንያት ሆኗል፡፡
ሌላው ፍ/ቤት ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከተ የመጣው ተከሣሾች ዳኞችን መሳደብና ማንጓጠጥ ቁሣቁስ መወርወር እየፈፀሙ ሲሆን በዚህ ተግባራቸው ዳኞች በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን በችሎት መድፈር ቅጣት የሚጥሉ ሲሆን ቀደም ባለው ጊዜ ችሎቱን የደፈሩትን ተከሣሾች ድርጊታቸው በአግባቡ በመዝገብ ተመዝግቦ ቅጣት የሚያርፍባቸው በመሆኑ ይግባኝ ሲባል እንኳን ዳኛው ባለው ሥልጣን ያለአግባብ ቅጣት የጣለባቸው መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ የሚሻርበት ሁኔታ የለም ነበር፡፡ እንግዲህ ችሎቱ ላይ የነበረውን እውነታ በቦታው የነበረው ዳኛና የታደመው ባለጉዳይ የሚያውቁት ቢሆንም ጉዳዩ ይግባኝ ተብሎ ሲሄድ ዳኛ የራሱ ነገረ ፈጅ የሌለው ችሎቱን ወክሎ ይግባኙን የሚቃወምለት አሰራር በሕግም የሌለ በአሰራርም ያልዳበረ በመሆኑ የአንድ ወገን ይግባኝ ቅሬታ ተሰምቶ ብቻ ውሣኔ የሚሰጥበት ነው፡፡ ይህ አሰራር ምናልባትም በሕግ ሳይዘረጋ በአሰራርም ሳይዳብር የቀረው ሕግ አውጭው ይግባኝ የቀረበለት ዳኛ በትክክለኛው መንገድ ጉዳዩን ይመረምራል ያጣራል ከሚል እሳቤ ኃላፊነቱን ለይግባኝ ሰሚው ዳኛ በመተው ይመስለኛል፡፡ አሁን አሁን ግን ችሎት ደፍሮ የተቀጣ ሰው ይግባኝ የማለት ሕገመንግሥታዊ መብት ቢኖረውም በመዝገብ ላይ የፈፀመው ተግባር ቁልጭ ብሎ እየታየ ውሣኔውን መሻርና ቅጣቱን ማገድ የመሳሰሉት ውሣኔዎች ስለሚሰጡ ፍ/ቤቶች የነበራቸውን ክብር እንዲያጡና ማህበረሰቡ የራሱ መገልገያ የሆነው ፍ/ቤት ነፃነቱን እንዲያጣ ዳኞችም በችሎት ውስጥ ለሚፈፀሙ ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት እርምት ከመስጠት ቸል እንዲሉ ያደረገና ስርአት አልበኝነት እንዲጐለብት አድርጐታል፡፡
በችሎት መድፈር የሚጠየቁት ተከሣሾች ብቻ ሳይሆኑ በፍ/ቤቱ ውስጥ የሚገለገሉትን አጠቃላይ የሚመለከት ሲሆን፣ ዐቃብያነ ሕግ ጉዳያችንን ቀደሙ ብሎ ፍ/ቤቱ በሚያስተናግድበት ስርዓት ቆመው ማስረዳት ሲጠበቅባቸው ቆመን አናስረዳም በምን ህግ ነው ቆመን የምናስረዳው በማለት ተከሣሽ ቆሞ እያስረዳ ዐቃቤ ሕግ ቁጭ ብዩ ካልተከራከርኩ ብሎ ከዳኛች ጋር እሰጥ አገባ የሚፈጥርበት፣ ሞባይል ይዘው በመግባት ጌም የሚጫወቱ፤ በችሎት ውስጥ ማስቲካ የሚያኝኩ፤ ይዘው የገቡትን ጉዳይ ዳኛ ጥያቄ ሲጠይቃቸው በአግባቡ ጉዳዩን ከማስረዳት ይልቅ በቃ ማስረዳት አልፈልግም ብለው ቁጭ የሚሉ፣ ካባ ለብሰው የማይገቡና በችሎት ውስጥ ካባ የሚለብሱ ብዙ ብዙ ችግሮች በመፍጠር ፍ/ቤቱ የነበረውን ክብር እንዲያጣ በማድረግ ዳኞች ዋና ስራቸውን ትተው እነሱን ሲገስፁ የሚውሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በሌላ በኩል ችሎቱ ተገቢ የሆነውን ሥራ እንዳይሰራ የሚያውኩ ባለጉዳዩችም ያሉ ሲሆን ሕግና ስርዓትን የሚያስከብሩ የፖሊስ አባላትም እንዲሁ ችሎቱን ስርዓት በማሳጣት የሚያውኩ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በችሎት ለሚቀርቡ ጉዳዩች የፍ/ቤት ሰራተኞች በራሳቸው ችግር የሚፈጥሩበት ፣ በችሎት ተጠርተው ሲታረሙ ፍ/ቤት ስለሚሰሩ ብቻ ለምን ተነካን በሚል ችግር የሚፈጥሩ እየተበራከቱ የመጡበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ በተመለከቱት ዋና ዋና ምክንያቶች የፍትህ ስርዓቱ ቀድሞ ከነበረበት ጥንካሬው መሻሻል ሲገባው እየወረደ እንዲመጣና ህብረተሰቡም በፍትህ ስርአቱ ላይ እምነት እንዳይኖረው ሆኗል፡፡
በፍትህ ስርዓቱ ላይ ሕዝቡ እምነት እንዳይኖረው ካደረጉት አካላት መካከል የአስተዳደር መስሪያቤት ኃላፊዎች፤ የከተማው ፍትህ ቢሮ፤የወረዳ ና የክፍለ ከተማ ፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊዎች የሚጠቀሱ ሲሆኑ፤ በአሰራራቸው መጓደል የተነሳ ተበደልኩ ያለ ግለሰብም ሆነ ድርጅት በፍርድ እንዲወሰንለት ወደ ፍ/ቤት ጉዳዩን አቅርቦ ጉዳዩ እየተመረመረ ባለበት ጊዜ፤ የአስተዳደር መ/ቤቶች ለትክክለኛ ፍትህ ይጠቅም ዘንድ ማስረጃዎችን እንዲሰጡ ሲጠየቁ እኔን አይመለከተኝም በማለት አንዱ ክፍል ወደሌላው ክፍል ሌላው ክፍል ጭራሽ የፍ/ቤትን ትዕዛዝ ተቀብሎ ያለማስተናገድ ፍላጐት በማሳየት በተደጋጋሚ ጊዜ የዜጐች ጉዳይ በበቂ ማስረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዳይወሰን የማድረግ ተግባር እየፈፀሙ መቆየታቸው ትልቅ ችግር ሆኖ ሰንብቷል፡፡
ውሣኔ ካገኘ በኋላም፤ በአስተዳደር ላይ ውሣኔ ከተወሰነ፤ ውሣኔው እንዳይፈፀም መሰናክል በመፍጠር ህዝቡ ውሣኔ በእጁ ይዞ እንዲቀር በማድረግ፣ ክርክሩ ይዞታን አስመልክቶ ከሆነም ከላይ እንደተገለፀው በፍ/ቤት በክርክር ላይ እያለ ይዞታን ካርታን ማምከን፣ ውሣኔ ካገኘ በኋላም ካርታው ስለመከነ አልፈጽምም በማለት ከፍርድ አፈፃፀም ጋር ሙግት መፍጠር የተለመደ ተግባር ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁንም አልተለወጠም ይልቁንም እየባሰበት መጥቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ እንደ ዐቃቤ ሕግ በመሆን አስተዳደሩ በሚከሰስበትም ሆነ በሚከስበት ጊዜ ፍ/ቤት ቆመው የሚከራከሩ ዐቃብያነ ሕጐች ያሉ ሲሆን ዋናው መ/ቤታቸው ያለው በአዲስ አበባ አስተዳደር ሆኖ ነገር ግን በየክፍለ ከተማው ላይ በፍትህ ጽ/ቤት ደረጃ ተደራጅቶ ለክፍለ ከተማውም ሆነ ወረዳዎች በሚከሱበትና በሚከሰሱበት ጊዜ እየቀረቡ የሚከራከሩ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
እነዚህ ዐቃብያነ ሕግ የአስተዳደሩን አደረጃጀት ከማንም በላይ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሆነው ይልቁንም፤ ለምሳሌ ያህል የሠ/መ/ቁ/ 1752ዐ1 በሆነው መዝገብ ክርክር ያደረጉ ዐቃብያነ ሕግ በግለሰብ ደረጃ እንኳን ሳይቀየሩ ወረዳ በተከሰሰበት ጊዜ እስከ ሰበር ተከራክረው ያንኑ ጉዳይ እነዛው ዐቃብያነ ሕግ መልሰው መከሰስ ያለበት ክ/ከተማው ነው በማለት በክፍለ ከተማው ውስጥ ላሉ አደረጃጀቶች ሁሉ ራሳቸው የተከራከሩበትን ጉዳይ መቃወሚያ ያቀርባሉ፡፡
አንድ ቀበሌ ወይም ወረዳ ተከስሶ ክርክር አድርጐ ጉዳዩ ሰበር ደርሶ ከተወሰነ በኋላ፤ ክፍለ ከተማው ቀበሌው ወይም ወረዳው ለተከሰሰበት ጉዳይ ማስረጃ ሲሰጥና በማስረጃም የስራ ኃላፊዎች እየቀረቡ በችሎት እያስረዱ ቆይተው፤ በቀበሌ/ወረዳው ላይ የቀረበውን ክስ ውጤት ጠብቀው ጉዳዩ እኔን የሚመለከት በመሆኑ የተሰጠውን ፍርድ እቃወማለሁ እያሉ፣ የክ/ከተማው ዐቃቤያነ ሕግ ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ሲሆንባቸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ/ዐቃቤ ሕግ / በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ/ 358/418/453 እንዲሁም ውሣኔ ካገኘ በኋላም አዲስ ማስረጃ አግኝቻለሁ እያሉ የፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ/ 6 እየጠቀሱ፤ ህዝቡን ለከፍተኛ እንግልት እየዳረጉት መሆኑ እንዲሁም ፍ/ቤቶችም በአንድ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ጉዳይ እንዲያዩ እየተገደዱ በመሆኑ፤ ሕብረተሰቡ ፍ/ቤት ውሣኔ ቢሰጥም እንኳን የቀበሌ/የወረዳ አልያም የአስተዳደር ኃላፊዎችን ተለማማጭ እንዲሆኑ ፍትህ የማግኘት መብት እንደሌላቸው ሁሉ ተሸማቃቂ እንዲሆኑ አድርገዋቸው ቆይተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ህዝቡ ምን ፍትህ አለ በማለት ሲያማርር እንመለከታለን፡፡
ይዞታን በሚመለከት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ማኔጅመንት ሲከሰስ ክርክር እስኪጨርስ ተጠብቆ የመሬት ይዞታና አስተዳደር ጉዳዩ የሚመለከተው እኔን ነው በማለት የሚመጣበት፣ የይዞታ አስተዳደር ተከራክሮ ሲጨርስ የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ፣መሬት ባንክ እና የመሳሰሉት ወደ ክርክር ልግባና ልከራከር በማለት እየተፈራረቁ ጉዳይ በጊዜ እልባት እንዳያገኝ የሚያደርጉ እራሳቸው በየተራ አንዱ ተከራክሮ ሲያበቃና ፍ/ቤት እግድ ሲያነሳ ሌላኛው እየመጣ እግድ እንዲሰጥ እያደረገ፤ጉዳይን ፍ/ቤት እንደሚያጓትት አድርገው በየሚዲያውና በየመድረኩ የሚያነሱ መሆኑ መታወቅ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡
በሌላ በኩል የቀበሌ ቤቶችን እና ኪራይ ቤቶች የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች አስመልክቶ ለረዥም ጊዜ ከመንግሥት ተከራይተው የሚኖሩ ዜጐች፤በተለይ አቅም የሌላቸውን ተከራዩች የረባ ያረባ ምክንያት በመፈለግ የኪራይ ውላቸውን በማቋረጥ እና ከቤቱ እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ በመስጠት እነሱን ቤት አልባ በማድረግ፤ በአስተዳደር ውስጥ ለሚሰሩ ሲሆን ግን ፍ/ቤት ጉዳዩ ቀርቦ የኪራይ ውሉ እንዲቀጥል ሲወሰን ይህን ተግባራዊ የማያደርጉ፤ ሕዝቡን በአንድም በሌላም መልኩ እያንገላቱ፤ ሕዝብ በፍትህ ስርአቱና በመንግሥት ላይ እንዲያማርር እንደሚያደርጉ የሚታጣ አይደለም፡፡ እንዲሁም የአስተዳደር አካላት የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ የማያከብሩ መሆኑ በራሱ ከፍተኛ የሆኘ የፍትህ መዛባት አስከትሏል፡፡ ለምሳሌ አንድ የሚታወቅ ጉዳይን ብናነሳ፤ ፍ/ቤት አንድ ይዞታ ላይ የተሰራ ቤት እንዳይፈርስ እግድ ሰጥቶ ጉዳዩን አከራክሮ ብይን ይሰጥና እግዱን ሳያነሳ ይቀራል፡፡ በዚህ ጊዜ አስተዳደሩ በፍ/ቤት የተሰጠው እግድ ፀንቶ ባለበት ብይን በተሰጠ በአጭር ጊዜ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ እንዳይፈርስ የታገደውን፤ ጉዳዩም ይግባኝ ተብሎበት በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ታምኖበት አስተዳደሩን ያስቀርባል የተባለና ሌላ እግድ ተሰጥቶ ባለበት፤ ይህን ሁሉ የፍ/ቤት ትዕዛዝ ጥሶ ያፈርሳል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም ጉዳዩን አጣርቶና አስፈፃሚውን ጠርቶ ሲጠይቅ ጉዳዩ እውነት መሆኑን ይደርስበታል፡፡ በዚህ መሠረት ይህን በፈፀሙ አካላት ላይ በወንጀል ምርመራ እንዲጣራና ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ግን በሌሎች ብዙ ተመሳሳይ ጉዳዩች በሰዎች ላይ ክስ አቅርቦ አስቀጥቶ ያስቀጣበት ማስረጃም ተደግፎ ቀርቦለት እያለ፤ እግድ መጣስ ወንጀል አይደለም በሚል ምርመራ መዝገቡ ላይ ክስ አላቀርብም በማለት ትዕዛዝ ሰጥቶበታል፡፡ በዛም ላይ ይህን ድርጊት የፈፀሙ አካላት በፍትሐብሄር ሲከሰሱ አስተዳደሩ ግለሰቦችን ሊወክል የሚችልበት ምንም አይነት በሕግ የተሰጠ ነገር በሌለበት፤ ለግለሰቦች ዐቃቤ ሕግ መድቦ እየተከራከረ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት ሕገወጥ ድርጊት የፈፀሙ ሰዎች በመንግሥት እውቅና እየተሰጣቸው ሥራቸውም ተቀባይነት ያለው መሆኑን ማሳያ ተግባር ነው፡፡ይህ እውነታ ነው፡፡
አንድ ፍርድ ቤት የፍትህ ስርአቱን ለማስከበር የሚጠቀመው በህግ መሠረት ተገቢ ትዕዛዝ በመስጠት እንጂ መሳሪያ ይዞ ራሱ እንዳይደፈር በፈለገው ነገር ላይ ጥበቃ አያሰማራም፡፡ አይጠብቅምም፡፡ ሆኖም በዚህ መልኩ ፍትህ በአስተዳደር አካላቱ እየተዛባ መሆኑ መታወቅ የሚገባው ነው፡፡የአስተዳደር አካላት የፍ/ቤትን ትዕዛዝ ሳይፈጽሙ ሲቀሩ ዳኞች በህግ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ትዕዛዙን ያልፈፀመውን ጉዳዩና ሥልጣኑ የሚመለከተውን የሥራ ኃላፊ ጠርተው ለምን እንዳልፈፀመ ጠይቀው ያልፈፀመው ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ መሆኑን ሲረዱ በግለሰቡ ላይ የእርምት እርምጃ በሚወስዱበት ጊዜ የአስፈፃሚ አካላት ሠራተኛቸው የፈፀመው ተግባር የፍትህን ሥራ ማስተጓጐል መሆኑን እያወቁ የፍ/ቤቱን እርምጃ መደገፍ ሲገባቸው፡ ለፍ/ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች ዳኞች ያልተገባ ተግባር እንደፈፀሙ በመንገርና ዳኛው ላይ ግፊት እንዲፈጠር በማድረግ የፍትህ ሥራ ወደ አልተፈለገ መንገድ እንዲሄድ እያደረጉ የነበሩ መኖራቸው በሥራ አጋጣሚ በተደጋጋሚ ሲያጋጥም የኖረ እውነታ ነው፡፡ የአስፈፃሚው ሥራ ኃላፊዎች በአገሪቱ ላይ ፍትህ እንዲሰፍን የበኩላቸውን እገዛ ማድረግ እንጂ በሥራቸው ተሸጉጦ ፍትህ እንዲዛባ የሚሰራን ሰራተኛ መደገፍ፤ፍ/ቤቶች ያልተገባ ተግባር እንደፈፀሙ በማስመሰል በየመድረኩ ማናገርና መኮነን ካልተማረ ሰው የማይጠበቅ ለአገርም ጠንቅ እንጂ የሚጠቅም አይደለም፡፡
ሌላው የፍትህ ስርአቱ ለመድከሙና በሕዝብ አመኔታ እንዲያጣ ካደረጉት አንዱ በፍ/ቤት ዋነኛ ተገልጋይ የሆኑት ጠበቶች ናቸው፡፡ ጠበቆች አንዳንዶቹ በስነ ምግባራቸውና በችሎታቸው የሚመሰገኑ፣ለፍ/ቤቶች፣ለዳኞች፤በፍትህ አካላት ውስጥ ለሚያገለግሎ ባለሙያዎች፡ ሰራተኞች እንዲሁም በጥብቅና ለቆሙላቸውም ሆነ ለተከራካሪዎች መልካም የሆኑ የፍትህ ስርአቱ ተአማኒ እንዲሆን በእጅጉ የሚታትሩ፤ የሚረዱ በሕግና በሕግ ብቻ የሚሰሩ ምስጉኖች እንዳሉ የሚታወቅ ነው፡፡በሌላ በኩል ደግሞ እነሱም አንዳንድ ጊዜ አንዳንዶቹ ከእውቀት ማነስ፣ የሰዎችን ጉዳይ በአግባቡ ካለመያዝ፤ ቸልተኛ ከመሆን ተገቢ የሆነ ክርክርና ማስረጃ እንደየጉዳዩ አይነት አስተካክለው እና ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ማቅረብና መከራከር ሲገባቸው ይህን ሳያደርጉ ቀርተው ፍ/ቤት ውሣኔ በሚሰጥበት ጊዜ፤ ዳኛው ነው የበደለህ፤ እኔ ተከራክሬልህ ነበር በሚል ተገልጋዩ በፍ/ቤትና በዳኞች ላይ እምነት እንዳይኖራቸው የሚያደርጉ መኖራቸው እሙን ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደሚወራው ጉዳይ ያለው ሰው የሚፈልገው ፍ/ቤት ዳኛን የሚያውቅ ጠበቃ ነው የሚባለውን አስተሳሰብ በደንብ በማህበረሰቡ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያደርግ በአንዳንድ ጠበቆች የሚተገበር በመሆኑ፣ እኔ እከሌን አውቃለሁ እያሉ ጉዳዩችን ከጠበቃ ላይ የሚነጥቁ መኖራቸው ይነገራል፡፡
አንዳንዶቹ ጠበቆ ደግሞ ከፍ/ቤት ድጋፍ ሰጪ ሰራተኛ ጋር እየተመሳጠሩ ዳኛውን እንደጠየቁና እንደሚፈጽምላቸው እያስመሰሉ ገንዘብ ከባለጉዳዩ የሚቀበሉና ከጥብቅና ስነ ምግባር ውጭ እየፈፀሙ ፍ/ቤቱና ዳኞች በተገልጋዩ ማህበረሰብ እንዳይታመን የሚያደርጉ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እንዲሁም አንድ ዳኛ ከስነ ምግባር ውጭ ከፈፀመ ለማረም ከመዘጋጀት ይልቅ ወሬውን በማራገብ ንፁሃኑንና ሁሌም የሚደክሙ ዳኞች አንገታቸውን እንዲደፉ የሚያደርጉበት ተገቢ ያልሆነ ሥራ የሚሰሩ በመሆናቸው፤ የነሱም አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ በየፍትህ ተቋማቱ ሥራቸው እንዲቀላጠፍላቸው ለማድረግ ሠራተኞችን በእጅ እያሉ ሌላው በእጅ ማለት የማይፈልገውና የሌለውም ጭምር በአግባቡ እንዳይስተናገድ የሚደርጉ መኖራቸው ማህበረሰቡ የሚነሳው ነገር ነው፡፡ ችሎቱ ቀጠሮ አሳጥሮ ሲሰጥ እንዲረዝምላቸው ያለምክንያት የሚጠይቁ፣ ለባለጉዳዩ ግን ፍ/ቤቱ ቀጠሮውን አሽቀነጠረው ብለው የሚናገሩ፣ ሐሰተኛ ሰነድ የሚያቀርቡ፤ ለሙያቸው ያልቆሙና አንዳንድ ስነ ምግባር የጐደላቸው ጠበቆች በመኖራቸው ማህበረሰቡ እነሱን ሳይሆን ፍ/ቤት ላይ አይኑን እንዲጥል የሚያደርጐ አይታጡም፡፡
በፍትህ ዙሪያ ለሕዝብ የሚቀርቡ ዘገባዎችን የሚያትሙና የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሃን በፍ/ቤት ቀርበው የሚጠይቁትና ለህዝቡ ማቅረብ የሚፈልጉት፤በክርክር ላይ ያሉ ወይም ውሣኔ ያገኙ ባለጉዳዩችን ታርጌት ያደረገ ሲሆን፤ ፍ/ቤቶች በግራ ቀኝ ተከራካሪ የሆኑትን በአንድ ጊዜ ማስደሰት እንደማይችሉ እየታወቀ፤ የአንዱን ወገን ቅሬታ ብቻ በመስማት ሌላኛውን ወገን ሳይጠይቁ ወይንም የጠየቁትንም ሰው /ተገልጋይ/ እንኳን ቢሆን ዳኞች ገለልተኛ አይደሉም ብሎ የሚነግራቸውን ከሰሙ በኋላ፤ በየትኛው ፍ/ቤት ዳኞች ተግባር እንዳልተደሰተ፤ ገለልተኛ አይደሉም ሲል በምን መገለጫና ሚዛን እንኳን መሆኑን፤ በየትኛው መዝገብ ተከራክሮ ምን አይነት ማስረጃ አቅርቦ እንደተወሰነበት እንኳን ሳያረጋግጡ፤ እውነታውን ሳያጣሩ በደፈናው ዳኞች ገለልተኛ አይደሉም፤ የፍትህ ስርአቱ ችግር ያለበት ነው፤ በማለት የሚዘግቡት ዘገባ ያለ መሆኑን መመልከት ተችሏል፡፡
ይህ ከሆነ ደግሞ በፍ/ቤት የሚቀርቡ ጉዳዩች በሃሰት የሚቀርቡ፣ ጉዳዩች እውነት ሆነው ህግ በሚፈቅደው መልኩ ማስረጃ ያልቀረበባቸው፣ ሕግ በማይፈቅደው መልኩ በጊዜ ገደቡ ውስጥ ያልቀረቡ፤ለምሳሌ በይርጋ የሚታገድ ሆኖ ቅር ለተሰኘው ወገን ያልተፈረደለት ሊሆን ስለሚችል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሱ የተፈረደለትም ሆኖ ሙሉ በሙሉ የጠየቀው የመብት ጥያቄ ያልተወሰነለትና በከፊል የተወሰነለት በሚሆን ጊዜ ለምን ከጠየኩት ተቀነሰብኝ የሚል ወገንም ልክ በዳኝነት ስርአቱ እንደተጐዳ ቅሬታ የሚያሰማ በመሆኑ፤ በእርግጠኝነት በፍ/ቤት የሚቀርቡ ጉዳዩች 75 በመቶ የሚሆነውን ተገልጋይ የማያስደስት ሊሆን ስለሚችል፤ ፍ/ቤቶችና ዳኞች ገለልተኛ አይደሉም የሚያሰኝ ታርጋ እንዲለጠፍባቸው የሚያደርግ በመሆኑ፤ ጋዜጠኞች በዚህ ዙሪያ የሚያቀርቡትን ጥያቄ በጥንቃቄ መመርመር አለባቸው፡፡ከዛም አልፈው ስለጉዳዩ ከተናጋሪው በዘለለ መዝገቦችን መመልከትና ራሳቸው ትክክል ነው አይደለም የሚለው መደምደሚያ ላይ መድረስ እውነታን ማፈላለግ ሲችሉ፤ ይህን ወደ ጐን በመተው ገለልተኛ አይደሉም የፍትህ ስርአቱ ችግር አለበት በሚል ዘገባ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ይህ ማለት ግን በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆኖ የፍትህ ስርዓቱ ምንም አልሰራም ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ፍትህ ስርዓት ውስጥ የሰው መብቶችና ነፃነቶች ተጓድዋል ቢባልም፤ በሌላ ጐኑ ደግሞ በዚህ ጫና ውስጥ ሆነውም ቢሆን አጥጋቢ ባይባልም የተረጋገጡ መብቶች እና ነፃነቶች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ያለበለዚያ ሙሉ ለሙሉ የፍትህ ስርዓቱ ወድቆ ነበር የምንል ከሆነ፤ በዚህ ስርዓት ውስጥ መብታቸው በሕግ የተረጋገጠላቸው ነፃነታቸው በሕግ መሠረት የተከበረላቸው ዜጐች የዚህ የፍትህ ስርዓት ተጠቃሚዎች አይደሉም ማለት ይሆናል፡፡
የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ፣የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማት የፍትህ ሥርአቱ በተገቢው መስመር ላይ እንዲገኝ ያላቸው ድርሻ የአንበሳውን የሚወስድ ሲሆን፣ በተግባር ግን የፍትህ ተቋማትን የመቆጣጠርና ሥራቸውን የመፈተሽ ነገሩ ላይ ግን ምንም የሰሩት ፋይዳ ያለው ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ከየተቋማቱ የሚቀርቡለትን ሪፖርት ከመስማት በዘለለ እስረኞች እንዴት ይያዛሉ፣ ያለባቸው ቅሬታስ ምንድን ነው፣ እስረኞች በአስፈፃሚው አካላት ተንገላተናል፤ በፍ/ቤትም ተገቢ ፍትህ አጥተናል ብለው ሲያማርሩ በሪፖርት ከማዳመጥ በዘለለ የተቋማቱን አሰራር በአካል ወርዶ በመፈተሽና በማስተካከል እረገድ፤ እጥረት የሚታይበት ተቋም ሲሆን፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም ቢሆን ሰብአዊ አብትን ከማስጠበቅ አኳያ፤ በፍትህ ተቋማት ውስጥ ምን እየተሰራ እንደሆነ በመፈተሽ፣ እስረኞችን በመጐብኘት፣ ጥፍር ይነቀልበታል፣ አካል ይጐድልበታል እየተባለ የሚታማውን የምርመራ ክፍል ጭምር በአግባቡ በመመልከት፣ በሰብአዊ መብት አጠባበቅ ረገድ በእስረኞች እና በተከሰሱ ሰዎች ላይ በፍትህ ተቋማት የሚፈጠሩ ችግሮችን መርምሮ በማጋለጥ እርምት እንዲወሰድ ማድረግ እየተገባው በዚህ መልኩ ሲንቀሳቀስ ግን አይታይም፡፡እንዲሁም የእንባ ጠባቂ ተቋምም ቢሆን የዜጐችን እንባ የማበስ ተግባሩን የመወጣት ተግባሩን በአግባቡ እየተወጣ ካለመሆኑም በላይ በተለይ በአስተዳደር መ/ቤቶች በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት የሚንገላቱ እና ሮሮ የሚያሰሙ ዜጐችን መሠረታዊ ችግር ምንድን ነው በማለት በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሄ የመስጠት ዋና ተግባሩ ሆኖ እያለ፤ ዜጐች አቤቱታ ሲያቀርቡ ብቻ ትንሽና አንዳንዴም የዜጐችን እንባ ከማበስ ይልቅ ሌላኛው የመልካም አስተዳደር ችግር ያለበት ተቋም ሆኖ የከረመ መሆኑ የሚያነጋግር አይደለም፡፡
የመፍትሄ ሀሳቦች
የፍትህ ስርዓቱን ተአማኒ፤ ተገማች፤ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን ለማድረግ ምን እርምጃ መወሰድ አለበት?“..ፈራጅም አዋራጅም ያድርግልን!!! ዳኛው ሽበት ስለማይወዱ ጸጉራቸውን ጥቁር ቀለም ይቀባሉ፡፡ባህሪያቸው ጥሩ ስላልሆነ…(የቀረውንሙሉት) ከሳሽ ሲናገር ይቀጥሉ፣ያብራሩት እያሉ ሰፊ እድል ይሰጣሉ፡፡ተከሳሽ ተራው ደርሶት መናገር ሲጀምር፤ ዝምበል መልስ አቅርበህ ሞተሃል፡፡ደግሞስ ተናገር ብትባል ይህን ሁሉ የከሳሽን ንግግርና ማስረጃ ምንብለህ ልታስተባብል ነው እያሉ አፉን ያስይዙታል፡፡በዳኛው ንግግር የተበሳጨው ተከሳሽ ቀለም እንደሚቀቡ ያውቅ ስለነበር እንግዲህ የተቀባው ያውቃል ብሎ ክርክሩን ቋጨ ፡፡ መቀባት አንድም ቀለም አንድም መሾም/ መመረጥ ነው፡፡ ደኝነት ተመርጠው ሲቀቡት ለሰው መድኃኒት ነው ፡፡ ፈራጅ መሆን ሥጦታና የተከበረ ሙያ ባለቤት መሆን ነው ፡፡ ዳኝነትን ተመርጠው ተቀብተው እንዳገኙት መርሳት ወይም ሳይቀቡ መሾም በፈራጅ ካባ አራጅ ሆኖ ብቅ ማለት ነው ፡፡ እንዲህ አይነት ዳኛ ተቀብቷል እጂ አልተቀባም ፡፡ ይህ ደግሞ የአርሰናልን ማሊያ ለብሶ ለማንችስተር መጫወት ነው ፡፡
ፈራጅን አስገድደው አራጅ የሚያደርጉ በርካታ ምክኒያቶች ባሉበት ሐገር ዳኛ መሆን ዕድልም ፈተናም ነው ፡፡ አራጅ ከመሆን ግን አስገድደው አራጅ የሚያድርጉትን ምክኒያቶች ሰው መሆንን ባለመርሳት፣ ጊዜ እውነተኛ ዳኛ መሆኑን ሁልጊዜ በማስታወስ፣ ለዳኛ የተሰጡትን ሕጋዊ ጥበቃዎችና ቆራጥነትን ከጨዋነት አስተባብሮ በመያዝ አራጅ ምክኒያቶችን ድባቅ በመምታት ክፉዎችን በማዋረድ ፈራጅም አዋራጅም መሆን ይቻላል ፡፡ ዳኛ ለውነተኛው ሲፈርድ ሐሰተኛውን እያዋረደው ነው ፡፡ ሙያውን ሲያከብር ባለሙያ የሆኑትንና እውነት ያለቸውን ያከብራል ያሰከብራል፤ ሐሰተኞችን አለቆቹን፣አስፈጻሚውን…… ያዋርዳል፡፡
ፈራጅ መሆን ቀላል ነው ፡፡ ፈራጅም አዋራጅም መሆን ከባድና አንድ ዳኛ ሊታገልለት የሚገባው የሚጠበቅበት ተግባርነው ፡፡ ዳኛ ዳኛ የሚባለው ፈራጅ ሲሆን ብቻ ሳይሆን ሕግን መሰረት አድርጎ በአመክኒዮና በማስረጃ ተደግፎ ፈራጅም አዋራጅም ሲሆን ነው ፡፡ ኢትዮጲያ የሚፈርዱ ሳይሆን የምየሚያዋርድም ዳኛ ትፈልጋለች ፡፡ ጊዜው ደግሞ ለዚህ ምቹ ነው ፡፡ ዳኞቻችንን ፈራጅም አዋራጅም ያድርግልን!! ፈራጅና አራጅ ዳኞችን ከማየት ይሰውረን !!! “
ከችሎት ስለመነሳት
በሕንድ ሃገር በአንዱ ክልል የመንግስትን አሰራር የሚፈትን ክስ ቀረበ ፡፡ ዳኛው መዝገቡን አይተው ለመፍረድ ሲቃረቡ የያዙት አቋም ለመንግስት ስላላስደሰተ ከችሎቱ ተነሱ ፡፡ የሕንድ የፍትህ ሥርዓት የሕዝብ ፍላጎትን የሚጻረር ጉዳይ ያለበትን ጉዳይ ማንኛውም ጠበቃ መብትና ጥቅም አለኝ ብሎ ክስ እንዲያቀርብ ስለሚፈቅድ ጠበቆች ከመንግስትና ከፍርድቤቱ አስተዳደር ጋር ሙግት ያዙ፡፡ “ ፍትህ የሕዝብ ፍላጎትና መብት ነው ፡፡ መንግስት ይህን መብት ማክበር፣ ማስከበር፣ ማሟላትና መጠበቅ አለበት ፡፡ ዳኛው ከችሎት ከተነሱ ሌላ ዳኛ መጥቶ መዝገቡ እስኪገባው ድረስ ፍትህ ይዘገያል ፡፡ የፍርድቤቱ አስተዳደር ስለፈለገ ብቻ ዳኛው ከችሎት መነሳት የለባቸውም :: ” የሚልክስ ፡፡ ጠበቆቹ አሸነፉ ፡፡ ዳኛው መከራቸውን በልተው የሰሩትን መዝገብ ሊቋጩ ይገባል ተብሎ ከችሎት የመነሳታቸው ነገርቀረ ፡፡ ይህ ሕንድ ነው ፡፡
ብዙ ሳንርቅ ፓኪስታን ግን ስንት ጊዜ ዳኞች መንግስትን እንዲያስደስቱ ተብሎ ከችሎት ተነስተው ቀርተዋል ፡፡ አንዳንድ የፓኪስታን ጠበቆች የፍርድቤቱ ፕሬዝዳንት በፈለገ ጊዜ ዳኞችን ከችሎት የሚያነሳ ከሆነ ፍትህ መዘግየቱ አይቀርም ፡፡ እባካችሁን ማስረጃ የመረመረ፣ ምስክር የሰማና የከሳሽና የተከሳሽን ክርክር የሰማ ዳኛ በሕግ ለመወሰን እስከተቀመጠ ድረስ አታንሱት ብለው ቢሞግቱም ፡፡ የፓኪስታን ፍርድቤት አስተዳደር ይህቺ ሕንድ ካሽሚር ላይ የምትፈጥረው የባህል መዳቀል ሳያንሳት ለጠበቆቻችን እንዲህ ዓይነት አጓጉል ነገር ማስተማር ጀመረች ቆይብቻ እያሉ ነው ፡፡ በቅርብ ያለ ጸበል ልጥ ያርሱበታል፤ ከሩቅ ያሉ መጥተው ይፈወሱበታል፤ ይሉሃል እንዲህ ነው ፡፡
የሲሪላንካ ፍርድቤት ፕሬዝዳንቶችስ ቢሆኑ የሲሪላንካ ቴሌቪዥን የሚዘግበው ነገር መጠንከሩን እያዩ እንዲህ በፍርድቤቶች ላይ አምባገነን መሆን አለባቸው ፡፡ እንኳን የሲሪላንካ ሃገር ጠበቃ አልሆንኩ ይወሰንልኛል ብዬ ስሄድ ዳኛ ከችሎት ተነስቶ የሚጠብቀኝ ሃገር ፡፡ አይ ኢትዮጲያዬ አንቺ እኮ ከሁሉም ትሻያለሽ ዕውቀት ያላቸውን ዳኛ ማንሳት ብቻ ሳይሆን ከዳኝነት እንዲወጡ ትመክሪያለሽ ፡፡ ይሄው ነው !!! “የተከበረው ፍርድቤት ! “
የተከበረው ፍርድቤት የምትለው ቃል ከአፌም ከልቤም እንድትሆን አጥብቄ እሻለሁ ፡፡ የሚከበር ፍርድቤት ለሁላችንም ዋስትና ነው ፡፡ የፍርድቤትን ክብር የሚቀንሱ ተግባራት እንዲወገዱ የሚያስፈልገው ትንሽ ሥራ ነው ፡፡ ተባብረን የፍርድቤቶቻችንን ክብር ካላስጠበቅንና ዳኞቻችን በሕግና በሕግ ብቻ እንዲሰሩ ካላደረግን እንዲሁም ሕግን በመተርጎም ሥራቸው አልፎአልፎ የሚደርስባቸው እንግልት – “የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው ከሚለው የአባይ ልጅ ውሃ አያውቅም ወደሚለው ፈሊጥ” እንዳያድግ ሕጋዊ መስመርን የተከተለ ሙግትና ንቃት እንደሚያስፈልግ ለማመን ጠበቃ ከመሆን በላይ ምንም አያስፈልገኝም ፡፡ በተዋረደ ፍርድቤት የተከበረው እያልን በሽንገላ ወደ ሽምግልና ማምራታችን ነው እኮ ጎበዝ!!! ፍርድቤቶችን ለማሻሻል በጠቅላይ ዓቃቤሕግ በኩል የተጀመረ ጥረት እንዳለ ሰምቻለሁ ይበል ያሰኛል ፡፡ በአስፈጻሚው በኩል በፍርድቤቶች፣ ለፍርድቤቶችና ለዜጎች የሚመጣውን ለውጥ ግን በጥርጣሬ ከማየት አልታቀብም ፡፡ እንደ ዜጋና ለውጥን እንደሚናፍቅ የሕግባለሙያ ክብሩ ከፍያለ፣ ሕግ በጥልቀት የሚተረጎምበት፣ ሕግ ተርጓሚው ቀናብሎ የሚሄድበት ፍርድቤት ይናፍቀኛል፡፡ ጸሎቴ፣ጥረቴና ቋንቋዬም ደስ እያለኝ የተከበረው ፍርድቤት የምልበትን ዘመን ቀርቦ ማየት ነው፡፡ ለፍርድቤቱ ክብር ሳልሰራና ምንም አስተዋጽኦ ሳላበረክት በጥብቅና ሳሸንፍም ስሸነፍም የሚከፈለኝ ንገንዘብ እየወሰዱ መኖር ኢ-ኃላፊነት ሆኖ ተሰምቶኛል፡፡ እንጀራ በንጹህ ገበታ ሲቀርብ የምግብ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ለውጥ እያመጡልኝ ሳይሆን በፍርድቤቶቻችን በጎ የሆነ ለውጥ እንዲመጣና ፍርድቤቶች ፍርድቤት ብቻ እንዲሆኑ መሥራት እንዳለብኝ አምኛለሁ፡፡ እናንተስ አጋሮቼ?”
ከላይ ለማሳያነት እንደተጠቀምኩበት የአንድ ወዳጄ ፌስቡክ ላይ የተፃፈው ጽሁፍ ፍ/ቤቱ ምን እንደሚመስል በአጭሩ የሚያሳየን ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ለፍ/ቤቱ ብቻ ሣይሆን በፍ/ቤት ለሚገለገሉ ሁሉ ማድረግና መሆን ያለባቸውን የሚያሳይ በመሆኑ ስለወደድኩት ይጠቅማል ብዩ ነው፡፡
የፍትህ ስርዓቱን በተለይም ፍ/ቤቶችን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ፤ ነፃና ገለልተኛ በማድረግ ህዝቡ በነፃና በገለልተኛ ፍ/ቤት የመዳኘት መብቱን እንዲጠቀም ማድረግ ተገቢ ሲሆን፤ ይህን የማድረግ ኃላፊነት ደግሞ የሁሉም ዜጋ በተለይም በፍ/ቤቱ የሚለገሉ ባለድርሻ አካላትና ጠበቆችን ጨምሮ ሁሉም እጅ ለእጅ በመያያዝ በዳኞች ላይ ከየአቅጣጫው የሚመጡ ጫናዎች እንዲወገዱ፤ ዳኛው ነፃ ሆኖ በሕግ የተሰጠውን ተግባር መተግበር ያስችለው ዘንድ ያለመከሰስ መብቱ እንዲጠበቅለት ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡
ሕግን እና ማስረጃን ከንፁህ ህሊና ጋር በማገናዘብ ብቻ ፍትሐዊ ዳኝነት እንዲሰጡ ማድረግ፣ ዐቃብያነ ሕጐችና የፖሊስ ክፍሉ እንዲሁም ጠበቆች እና በፍ/ቤቱ የሚገለገለው ማህበረሰብ በአጠቃላይ ለፍ/ቤቱ ተገቢ የሆነውን ክብር በመስጠት ዳኞች በገለልተኝነት የቀረበላቸውን ጉዳይ ከሌላ ተጽእኖ ነፃ ሆነው በራሳቸው በመተማመን እንዲወስኑ ማድረግ፣ ዳኞች በማናቸውም ተጽእኖ ውስጥ እንዳይወድቁ እያንዳንዱ ማህበረሰብ ዳኞችን የመጠበቅና ከሚገጥማቸው ነገር የመከላከል ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ዳኞች ደግሞ ነፃ ናቸው ሲባል ነፃነታቸው ለሕዝብ ከሚሰጡት ፍትህ አንፃር ብቻ እየተመዘነ ተጠያቂነት ያለባቸው በመሆኑ፤ ለሚሰሩት ሥራ በሕግ አግባብ የማይሰሩና በሙስና፤ በአድሎና በዘመድ አዝማድ የሚሰሩ ከሆነም በቁርጠኝነት ማጋለጥና የሚገባቸውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡በአገሪቱ ውስጥ አንዱ ከአንዱ በመቀባበል የሚወራ ወሬን ማምከንና ማስረጃን መሠረት ያደረገ ነገሮችን በማንሳትና ማስረጃንም በማቅረብ ከስነ ምግባር ውጭ የሆኑ ዳኞችን መጋፈጥና እርምት እንዲወስዱ ማድረግ፣ የፍ/ቤቱ አመራሮችም ዳኞች በነፃነት ሥራቸውን እንዳያከናውኑ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መጠበቅና ራሳቸውም በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ስለ አንድ ጉዳይ ዳኛው በሚሰራው ጉዳይ ላይ ተጽእኖ ያለማድረግና መቆጠብ ይገባቸዋል፡፡እንዲሁም ዳኞች ከሚሰሩት ሥራ አንፃር ነፃና ገለልተኛ ሆነው መሥራት የሚችሎት ከስጋት ነፃ ሲሆኑ በመሆኑ፤ በሕግ አግባብ ያለመከሰስ መብት እንዲኖራቸው ማድረግ፤ በህግ የተከበረላቸውን መብትና ጥቅማጥቅም እንዲያገኙና ሶስተኛው የመንግሥት አካል ፍ/ቤት መሆኑን ማንኛውም አካል ጠንቅቆ እንዲያውቅና እንዲተገብር ማድረግ የፖርላማው ዋና ተግባር ከመሆኑም ሌላ፤ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤም ይህንን ለመንግሥት አቅርቦ የማስወሰን ኃላፊነት አለበት፡፡
የፍ/ቤት ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችም የፍ/ቤቱንና የዳኞችን ስም ከሚያጐድፍ ስራ መቆጠብ፤ ራሳቸውን በሥራ ገበታቸው ላይ በማድረግ በሚከፈላቸው ደመወዝ ብቻ ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ፤ በስነ ምግባር እንዲታነፁ ማድረግ አማራጭ አይኖረውም፡፡
ዐቃብያነ ሕግ በቅድሚያ በማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ አባል እንዳይሆኑ መደረግ የሚገባው ሲሆን፣ ከዳኛ በፊት ያሉ ዳኞች መሆናቸውን ተረድተው ሙያቸውን አክብረው በሚደርሷቸው መዛግብት ላይ ሙያዊ አስተያየት በመስጠት በአግባቡ ምርመራ እንዲመራ በማድረግ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ክስ ማቅረብ አለባቸው፡፡ በሚያዩት ጉዳይ ላይ የግለኝነት አስተሳሰብን በማስወገድ ጉዳዩ ለተጠረጠረው ሰው ዋስትና የሚያሰጠው ከሆነ፤ ዋስትና እንዲፈቀድለት ለፍ/ቤት አስተያየት በመስጠት የተጠረጠሩ /የተከሰሱ ሰዎች / በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ አለባቸው፡፡ ዋስትና በማያስፈቅድ የሕግ ድንጋጌ የሚሸሹ ሰዎችን ደግሞ ሕግን መሠረት በማድረግ ዋስትና እንዳይፈቀድ ሆኖም ጉዳያቸው ቶሎ ታይቶ ውሣኔ እንዲያገኙ ማድረግ፣ ሐሰተኛ ምስክሮችን ከእውነተኞቹ ክስ ከመመስረታቸው በፊት መለየት፣ ሐሰተኛ ሰነድን ከእውነተኛው ሰነድ መለየትና ለጉዳዩ በሕግ የተደነገገውን ትክክለኛ የህግ አንቀጽ በመጥቀስ ያጠፋ ሳይቀጣ እንዳያመልጥ፤ ንፁሁ ደግሞ ያለአግባብ እንዳይቀጣ እንዳይንገላታ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ እንዲሁም ለምርመራ በእስር የሚቆዩ ተጠርጣሪዎችን አያያዝ መከታተል፤ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተከስተው ሲገኙ ተጠያቂ ማድረግ፣ የተፈረደባቸው ሰዎች ፍርዳቸውን በአግባቡ ሰብአዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲጨርሱ ማድረግ፣ ይቅርታ ለሚገባቸው ይቅርታ፣ ምህረት ለሚገባቸው ደግሞ ምህረት እንዲደረግላቸው በአግባቡ ሲጠየቅ በገለልተኝነት ጉዳዩን በመመርመር ለተገቢው ወሳኝ ክፍል ማቅረብ አለባቸው፡፡
የፖሊስ ጣቢያዎችንና ማረሚያ ቤቶችን በመጐብኘት ለእስረኛ አያያዝ የማያመቹ ሰብአዊ መብትን የሚገፍ አያያዝን የሚያመላክቱ ነገሮች ሲገኙ፤ ፈጥኖ እርምት እንዲደረግ መስተካከል ያለባቸው እንዲስተካከሉ ምክር መስጠት፤ ከምክር የሚያልፍም ከሆነ እርምጃ በመውሰድ በሕግ የተፈቀደው በአገሪቱ ውስጥ በፍትህ ስርዓቱ የሚያልፉ ማህበረሰቦችን እምነት በሚጥሉበት ሁኔታ እንዲታረሙ ማድረና ዋና ሥራው ሊሆን ይገባል፡፡
የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ታራሚዎችንና የቀጠሮ እስረኞች አያያዝን በማዘመን ታርመው የሚወጡበት እንጂ በቀልተኛ ሆነው የሚለቀቁበት ሆኖ እንዳይቀጥል ማድረግ፣ የታሰሩ ሰዎች ሕግ በሚፈቅደው መልኩ ሰብአዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲቆዩ በማድረግ፤ እንደ ስያሜው ማረሚያ ቤት እንጂ ጉልበተኛንና ሞራል የለሽ እስረኛን እንዳያፈራ መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ እስረኞች በቂ የሆኑ መፃህፍትን አግኝተው እንዲያነቡ፣ በእስር በሚቆዩበት ጊዜ ሁሉ ስነ ምግባርንና እውቀትን ቀስመው እንዲወጡ የማድረግ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል፡፡
“የብራዚል እስረኞች አንድ መፅሐፍ አንብበው ሲጨርሱ ሪፖርት ያቀርባሉ አራት ቀንም ከእስር ዘመናቸው ይቀነስላቸዋል። ይህ አሰራር ወደ እኛ ሀገር ቢመጣስ ብዬ ተመኘሁ ለምን ቢሉ፤ ብዙ እስር ቤቶችና ብዙ እስረኞች ስላሉንና ማንበብ ሙሉ ሰው ስለሚያደርግ፡፡
የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋማትም በየበኩላቸው በአገሪቱ ባለው የፍትህ ተቋማት፤ ዜጐች በአግባቡ እንዲገለገሉ የማድረግ፣ ሰብአዊ መብት እንዲከበር፤ የአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ እንዲጠበቅ የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለባቸው ከመሆኑ አኳያ የአስተዳደር አካላትም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን ማረጋገጥ ዋነኛ ተግባራቸው ሊያደርጉት ይገባል፡፡ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
በተለይ የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በየትኛውም የአስተዳደር አካልና የፍትህ ተቋማት የሚቀርቡለትን ሪፖርት እውነተኛነት፤ ሪፖርቱ ከመቅረቡ በፊት ወደ ማህበረሰቡ በመውረድና አስተያየቶችን በመሰብሰብ ጭምር ሪፖርቱ ሲቀርብ የተቋማት ኃላፊዎች እንዲያረጋግጡ ማድረግ፣ በአካል በየቦታው በመገኘትም ተቋማት ሕግን መሠረት አድርገው ማህበረሰቡን እያገለገሉ መሆን አለመሆኑን በመመልከት፣ እስር ቤቶችንና ታራሚዎችን በመጐብኘትና በማነጋገርም ጭምር የዜጐች ሰብአዊ መብት በተግባር እየተረጋገጠ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማት የቆሙለትን አላማ ለማሳካት ሰዎች ተገርፈውና ተንገላተው በራሳቸው ላይ እንዲመሰክሩ እየተደረገ ያለው፤ የምርመራ ሥራን በቀጥታ በመቃወም የተጠረጠሩ ሰዎች በመርማሪዎች የመመርመር ብቃት ላይ የተመሰረተና በተጠረጠሩ ሰዎች እውነተኛ የተጠርጣሪነት ቃል የመስጠት ፍላጐት ላይ የተመሰረተ ጥበብ የተሞላበት የምርመራ ሂደት እንዲከናወን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ዓለም እንዳይፈፀም በተስማማበት የማስገደድ ቃል አቀባበል ዘዴ ቃል በመቀበል ማስረጃ በማድረግ ሰዎችን የማስቀጣት አሰራር እንዲወገድ ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል፡፡
የአስተዳደር መ/ቤት የስራ ኃላፊዎች ዜጐች ማስረጃ ፍለጋ በየመ/ቤቱ ሲመጡ በራሳቸው በኃላፊዎችም ሆነ በሥራቸው በተዘረጉ አደረጃጀቶች ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች፤ ዜጐች ማስረጃ የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን በመረዳት፤ ትክክለኛ ማስረጃ እንዲያገኙ በማድረግ፣ በፍ/ቤቶችና በፍትህ ተቋማት እንዲረጋገጡ የሚሰጡ ትዕዛዞችን በአግባቡ አጣርቶ ምላሽ በመስጠት፣ ለዜጐች መፍትሄ እንጂ ችግር ፈጣሪ ባለመሆንና የፍ/ቤት ውሣኔዎችና ትዕዛዞችን በመፈፀም የኃላፊነት ግዴታቸውን በመወጣት የፍትህ ስርአቱ ወደ ልዕልና እንዲመጣ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሚዲያዎችም የፍትህ ተቋማት የሚፈጽሙትን ተግባራት ትክክለኛ ተግባራት ማህበረሰቡ እንዲያውቅ፤ እውነተኛ መረጃ በማስተላለፍ፣ ተገቢ ያልሆነ ተግባራት ሲፈጽሙም እርምት እንዲወሰድ ሚዛናዊ የሆነ ዘገባን ለሕዝብ በማሳወቅ፤ የአስተዳደር አካላትም የፍትህ ሥራ እንዳይሰናከል አጋዠ እንዲሆኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ በመወጣትና የተዛባ መረጃን ለህዝብ ከማድረስ ተቆጥቦ፣ ጉዳዩ ገና በመታየት ላይ ያለን ጉዳይ ዘገባ ከመሥራት በመቆጠብ፤ የተከሰሱ ሰዎችም ነፃ ሆነው የመገመት መብታቸው በተከበረ መልኩ ጉዳያቸውን ፍ/ቤት እንዲያይ፤ ተገቢ ውሣኔ እንዲሰጥ በማድረና ጭምር የፍትህ ስርአቱ በተገቢው መስመር እንዲመራ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡
ማህበረሰቡም እውነቱን እውነት፤ ሃሰቱን ሃሰት በማለት ትክክለኛ አስተያየቱን በመስጠትና የፍትህ ተቋማቱ እኔ የምገለገልባቸው የራሴ ናቸው ብሎ በማሰብ፤ የታመኑ የተከበሩና እምነት የሚጣልበት የፍትህ ተቋማት አገሪቱ እንዲኖራት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግና የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት ቢወጣ እና እኔ ምን አገባኝ አይመለከተኝም የሚለውን አመለካከት ከውስጡ አስወጥቶ፤ ይመለከተኛል የሚል አስተሳሰብን በማንገብ ቢሰራና ቢደክም፤ አገራችን የተሻለ የፍትህ ሥርአት እንዲኖራት የማድረግ እምቅ አቅም አለ፡፡