‹‹አንዳንዶቹ ሕዝቦች ግን ሐሳባቸው ከሚኖሩበት አገር ወይም አውራጃ ሳይወጣ ቀኑ ይመሻል፡፡ ስለዚህ በሐሳብ የተቀደሙ በመሆናቸው ብቻ ወደ ኋላ ቀርተው ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ ሕዝቦች አንዱ እኛ [ኢትዮጵያውያን] ነን፡፡››
ከበደ ሚካኤል – ‘ጃፓን እንደምን ሠለጠነች?’ ገጽ 100
ይኼንን ጽሑፍ የጻፍኩት ከሦስት ዓመታት በፊት የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር፡፡ በዓድዋ ድል በዓል መባቻ የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች፣ በተለያዩ ጎራዎች ተቧድነው ዳግማዊ አፄ ምኒልክን ማዕከል ያደረጉ ምክንያታዊነትና ስሜት የሚላተሙባቸው የታሪክ ክርክሮች፣ ፉክክሮች፣ ሽሚያዎች፣ ዘለፋዎችና ስድቦች ሲሰነዛዘሩ መታዘቤ ጽሑፉን ለመጻፍ መነሻ ምክንያቴ ነበር፡፡ ጽሑፉን ያኔ ብጽፈውም ሐሳቡ ግን በውስጤ ሲብላላ የኖረ በመሆኑም ይህንን ሐሳብ ይዤ ሳልብሰከሰክ የቀረሁበት ቀን ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ በተለይ በእነዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ ያለፈ ታሪካችንን አስመልክቶ ከታክሲ ላይ የሐሳብ ልውውጦች እስከ አደባባይ ክርክሮች እየተሰሙ ያሉ ዕሳቤዎች ይህንን ሐሳብ ደጋግሜ እንድዘክር እያደረጉኝ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ጽሑፉን የተወሰነ አርትዖት አድርጌበት ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡
ቁርጡ ባይታወቅም የኢትዮጵያውያን ሕዝብ ቁጥር ከ100 ሚሊዮን እንዳለፈ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው፡፡ የተተኪው ቁጥር እንዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ቢሄድም የዚህ ዘመን ትውልድን ተከትሎት የሚመጣ አዲስ ትውልድ እንዳለ የሚያውቅ፣ ቢያውቅም ስለቀጣዩ ትውልድ ዕጣ ፈንታ ግድ የሚለው አይመስልም፡፡ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በ1954 ዓ.ም ባሳተሙት ‹‹ሕዝብና አስተዳደር – ሞራል›› በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 140 ላይ ‹‹የጊዜ ሕግ ሰው ከአባቶች የተበደረውን ለተከታዮቹ እንዲከፍል ያዛል›› ይላሉ፡፡ እኛ ያለፈውን ታሪክ የምናስተናግድበት መንገድና ለመጪው ትውልድ እያስተላለፍነው ያለው የታሪክ ይዘት ስለቀጣዩ ትውልድ ደንታ ቢስ መሆናችንን ለዓለም እየመሰከረ ነው፡፡
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ እ.ኤ.አ. በ1912 በጻፉት ‹‹አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› በሚል መጽሐፋቸው የገለጹት ሐሳብ እንደ አብዛኛዎቹ ቀደምት ጸሐፍት ስለዛሬያችን የሚያወጉን ነው የሚመስሉት፡፡ ነጋድራስ በገጽ 19 ላይ ‹‹(ኢትዮጵያውያን) ካለመስማማታችን የተነሳ ግን ሌሎች ሕዝቦች በአዕምሮና በጥበብ እየበረቱ ሲሄዱ እኛ ወደ ኋላ ቀረን፡፡ … እርስ በርሳችን መጠራጠርንም አልተውነውም፣ …›› ይላሉ፡፡ እንዳንተማመን ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ ሕዝቡን ለመዘወር ጥቅም ላይ ሲውል የምናየው ያለፈ ታሪካችን ነው፡፡ የከፋው ነገር ደግሞ ያጨቃጭቁን የነበሩ ያለፈ ታሪክ ትርክቶች በቁጥርም በይዘትም እየሰፉ መምጣታቻው ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አገራቸው አሜሪካ በኩባ ላይ ለዘመናት ጥላው የቆየችውን የንግድ ማዕቀብ እንድታነሳ ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤታቸው ጥሪ ሲያቀርቡ ባሰሙት ንግግር “I know history but I refuse to be trapped by it.” ‹‹ታሪክን አውቃለሁ፡፡ ታሪክ ወጥመድ ሆኖ እንዲይዘኝ ግን አልፈቅድም!!!›› ብለው ነበር፡፡ እኛ አትዮጵያውያን/ት፣ ታሪካችን ወጥመድ ሆኖ እንዲይዘን የፈቀድን ሕዝቦች ነን እንዴ?
ቀደምት እናቶቻችንና አባቶቻችን (‹‹እነአባቶቻችን›› የሚል አዲስ ቃል ሰጥቸዋለው) ከምንም ተነስተው ለእኛ ያበረከቱት ዕልፍ በረከት እያለ ያኖሩልንን ታሪክ ለመፀየፍ ይዳዳናል፡፡ በእኛው ዘመን ተምሳሌታዊ ታሪክ ሠርተን ለመጪው ትውልድ ማቆየት ስንችል፣ ከምንሆነው ያለፈ ታሪካችን የባሰ አሳፋሪ ታሪክ በዘመናችን ተግተን እየከተብን ነው፡፡ ያለፈውም ሆነ አሁን ያለው የፖለቲካ ታሪካችን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እንዳሉት፣ ‹‹እንዘጭ እንቦጭ›› መሆኑን ሳስተውል በጽሑፌ ርዕስ ያስቀመጥኩትን ጥያቄ እንደተጠየቀው ሰው፣ ‹‹ተግባብተን ለማንኖርበት አገር ስለምን መስዋዕትነት ከፈልን?›› ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ላለፈ ታሪካችን የምንሰጠውን ቦታ በተመለከተ በእኔ ዕድሜ እንኳን ያስተዋልኩትን ላውሳችሁ፡፡
1990 ዓ.ም ሁለተኛ መንፈቅ ዓመት
ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፡፡ የ12ኛ ክፍል የታሪክ መምህራችን የዓመቱን ትምህርት እየከለሱልን ሳለ አንድ ተማሪ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ ጥያቄው፣ ‹‹አንድን ጉዳይ ታሪክ ነው የምንለው ጉዳዩ ከተከሰተ ምን ያህል ጊዜ ሲያልፈው ነው?›› የሚል ነበር፡፡ መምህራችን ምላሽ መስጠት ጀመሩ። ‹‹አንድ ክስተት ታሪክ የሚባለው ይኼን ያህል ጊዜ ካለፈው ነው ተብሎ የተቀመጠ ቁርጥ ያለ ጊዜ የለም። ነገር ግን ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደምናየው አንድ ክስተት ጥቂት አሠርት ዓመታት ካለፈው በሚስጥርነት የተያዙ መንግሥታዊ ጉዳዮች ጭምር ይፋ እየወጡ በየታሪክ ድርሳናቱ ይጻፋሉ። ይህንን ለማድረግ ያስችላቸው ዘንድ ክስተቱን ወደዱትም ጠሉትም ‘ይህ ያለፍንበት ታሪክ ነው!’ ብለው ይቀበሉታል። እነሱ ጋር ሁለት ፕሬዚዳንቶች ከተቀየሩ ከሁለተኛው ፕሬዚዳንት በፊት ያለው ዘመን ታሪክ ሲሆን ይታያል። እኛ ጋርስ? እንኳን ሁለት መሪዎች የሚለወጡባቸው አሠርት ዓመታት ይቅርና አፄ ዮሐንስ፣ አፄ ቴዎድሮስና ዳግማዊ አፄ ምኒልክን እንኳን ታሪክ የመሆን ዕድል አልሰጠናቸውም። ምኒልክ ዛሬም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማዕከል ናቸው፤›› አሉን።
የእኚህ መምህራችን ንግግር 22 ዓመት ሊሞላው ወራት ቢቀሩትም ጥሬ ሀቅነቱ እስከ ዛሬ ዘልቆ በዕዝነ ልቦናዬ ይሰማኛል። ዳግማዊ ምኒልክ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማዕከል መሆናቸው ብሶበት ቀጥሏል፡፡ ንትርካችንም አፄ ዮሐንስ ¢ኛን፣ አህመድ ኢቢን ኢብራሂም ልጋዚ (አህመድ ግራኝን)፣ የነገሥታቱንና የጦር ጀግኖቻችንን ብሔር፣ ወዘተ ማካተት ጀምሯል፡፡ በዚህ መሀል በጎ ታሪኮቻችን ጥላ ያጠላባቸዋል። የጥላቻ፣ የመናናቅ፣ የእኔ እበልጥ፣ … ክፉ ጥላ። ይህ ጥላ ዛሬና ነጋችንን ያደበዝዘው ወይም ያጨልመው እንደሆነ እንጂ የታላላቅ ድሎቻችንንና የደማቅ ታሪኮቻችንን ወርቃማነት አይለውጠውም።
1996 ዓ.ም የማላስታውሰው ወር
የአንድ ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በአንድ ስብሰባ ላይ የሚከተለውን ገጠመኙን አጫወተን፡፡ የሕክምና ትምህርቱን ለመከታተል ባህር ማዶ በነበረበት ወቅት አንድ ካፌ ውስጥ ከተዋወቀው የውጭ አገር ዜጋ ጋር ወግ ጀመሩ። ‹‹ከየት ነህ?›› አለው። ከኢትዮጵያ መሆኑን ገለጸለት፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከአፉ ከመውጣቱ ቀልጠፍ ያለ ጥያቄ አቀረበለት፡፡ ‹‹ኢትዬጵያውያን በነፃነት የኖራችሁና በዚህም የምትኮሩ ናችሁ። ለመሆኑ ያንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈላችሁት ለምንድን ነው?›› አለው። የነፃነት ጥቅም ያልገባው ፈረንጅ ያገኘ መስሎት ስለነፃነት ትርጉም ይደሰኩርለት ጀመር።
ዲስኩሩን አቋረጠና፣ ‹‹የእኔ ነጥብ ይኼ አይደለም! የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ኖሬያለሁኝ። በተለይ ኬኒያና ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ኖሬያለሁ። ኢትዮጵያውያን የአገራችሁን ድንበር ለማስከበር ብዙ ዋጋ ከፍላችኋል። ኬንያ ግን በቅኝ ገዥ ተገዝታ ኖራለች። ኬንያውያንና ኢትዮጵያን የአገር ፍቅርን የምትተረጉሙበት መንገድ ሁሌም ያስገርመኛል። አንድ ኬንያዊ ትንሽ ገንዘብ ብትሰጠው አገሩን አሳልፎ ይሰጥልሃል። አንድ ኬንያዊ ሌላውን ኬንያዊ አሳልፎ እንዲሰጥህ ገንዘብ ብታቀርብለት ግን ዞር ብሎ አያይህም። ኢትዮጵያውያን ደግሞ በተቃራኒው ናችሁ። ለዘመናት እርስ በእርሳችሁ መግባባት አልቻላችሁም። አገራችሁን ጠላት እንዳይነካት ስትሉ ግን በአንድነት ትቆማላችሁ። ተግባብታችሁ ለማትኖሩባት አገር ስለምን መስዋዕትነት ትከፍላላችሁ? አገር ያለ ሕዝብ ይታሰባል ወይ? . . . ›› የሚሉ ጥያቄዎችን አከታትሎ ይጠይቀው ገባ።
ኬንያውያን ይኼ የውጭ ዜጋ እንደገለጻቸው ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አልችልም። ይኼ የውጭ ዜጋ የጠየቃቸው ጥያቄዎች ለእያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን/ት ሊቀርቡ የሚገባቸው ጥያቄዎች ስለመሆናቸው ግን እርግጠኛ ነኝ። ለመሆኑስ ታላላቅ ድሎቻችንን፣ ባህሎቻችንን፣ ቅርሶቻችንን፣ ነገሥታቶቻችንና ጀግኖቻችንን የምንዘክረው ለምንድን ነው? የአንዱን የበላይነት አጉልተን ሌላውን ለማንኳሰስ? ታሪክን ለመሻማት? ያኔ ለነፃነት የከፈልነው ዋጋ ለዛሬይቷ የኢትዮጵያ ልጆችም ቤዛና አርዓያ መሆኑን ለማስታወስ? ወይስ ልማድ ነው? ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፍ ገጽ 188 ላይ ‹‹የአድልኦና የሽሚያ ፖለቲካ የሚከተል ሕዝብ በሌሎች ዘንድ ሞገሥ ያጣል›› እንዳሉት ሌሎች ቁልቁል እንዲያዩን የሚያደርጉ ገጽታዎቻችንን ለማረም የሽሚያ ፖለቲካና ጉንጭ አልፋ ንትርካችንን ትተን አቅማችንንና ጊዜያችን ለነገው ትውልድ መልካም ፍሬ በምናፈራበት ነገር ላይ ብናውለው እንደ ሕዝብ አብረን እንከብራለን፣ እንከበራለን፡፡
1998 ዓ.ም ሁለተኛ መንፈቅ ዓመት
ከምርጦቹ የሕግ ትምህርት ቤት መምህሮቼ አንዱ የነበሩት ከቅርብ ወራት በፊት ያረፉት ነፍስ ኄር አቶ ስለሺ ዘዮሐንስ (ጋሽ ስሌ) ባልና ሚስት በፍቺ ወቅት ንብረታቸውን በዓይነት ስለሚካፈሉበት መንገድ ገለጻ እያደረጉልን ነበር። ‹‹ባልና ሚስት በፍቺ ክርክር ወቅት ንብረታቸው ሙሉ ለሙሉ ተሸጦ የሽያጩን ገንዘብ ከመካፈል ይልቅ የፈለጉትን ንብረት መርጠው በዓይነት ለመከፋፈል ከተስማሙ ከጋራ ንብረቶቻቸው መሀል እያንዳንዳቸው ለራሳቸው የተለየ ትርጉም (Sentimental Value) የሚሰጣቸውን ንብረት እንዲወስዱ ማድረግ ይገባናል›› የሚል ይዘት ያለው አስተያየት ሰነዘሩ። ምሳሌ አስከተሉ፣ ‹‹ለምሳሌ እኔ ከሚስቴ ብፋታ መጽሐፎቼን ብወስድ እመርጣለሁ። እሷንም ብትጠይቋት እንደ እኔ ልዩ ቦታ የምትሰጠው ንብረት ይኖራታል …›› አሉ፡፡ አንድ ተማሪ አቋርጧቸው፣ ‹‹ይህንን ማድረግ አያስቸግርም?›› አላቸው። ቀጠሉና፣ ‹‹ለእኔ ቁም ነገሩ ዋጋ የሚሰጡትን ነገር እንዲለዩ ማገዙ ላይ ነው። በእርግጥ ዋጋ የምንሰጠው ነገር እንደየሰው ይለያያል፤›› ብለው እንደወትሮ የማይረሳና ተያያዥነት ያለው ምሳሌ አስከተሉ።
‹‹ሁለት ፊታውራሪዎች ከጦርነት ድል መልስ ቤተ መንግሥት ተገኝተው ድሉን ለንጉሡ አበሰሩ። ንጉሡ ደስ ብሏቸው የጦር ሜዳ ውሏቸውን ምን ይመስል እንደነበር ጠየቋቸው። አንደኛው ፊታውራሪ ቀልጠፍ ብለው፣ ‹‹በውድቅት ሌሊት የጠላት ጦር ከመሸገበት ቦታ ስንገሰግስ አደርንና ጀንበር ስትወጣ ከጠላት ምሽግ ደረስን፡፡ በዚህ ጊዜ እነ ፊታውራሪ እከሌ ከእኛ ጋር ነበሩ፤›› አሉ ወደ ሁለተኛው ፊታውራሪ እየጠቆሙ። ሁለተኛው ፊታውራሪ ከአፋቸው ነጥቀው፣ ‹‹የለ የለ የለ እኔ ከእነ ፊታውራሪ እገሌ ጋር አልነበርኩም። እነሱ ነበር ከእኔ ጋር የነበሩት፤›› አሉ ወደ መጀመርያው ፊታውራሪ በቁጣ እየተመለከቱ። እነዚህ ፊታውራሪዎች ድል ወደተቀዳጁበት ጦር ግንባር ማን ቀድሞ እንደደረሰና ማን እንደተከተለ ለንጉሡ ለማስረዳት ሙግት ገጥመው አረፈዱ። አያችሁ ልጆቼ (ጋሽ ስሌ ተማሪዎቻቸውን ልጆቼ ነበር የሚሉን)፣ በእነዚህ ፊታውራሪዎች ዘንድ ታላቅ ዋጋ ያለው ድሉ ሳይሆን ለድሉ መገኘት እነሱ የነበራቸውን ሚና ንጉሡ እንዲያውቁ ማድረጉ ነበር፤›› አሉን፡፡
በዚህ ዘመንም ጋሽ ስሌ በምሳሌያቸው እንደገለጿቸው ሁለት ፊታውራሪዎች ‹‹ገዥ መሬት ይዘን››፣ ‹‹ታላላቅ ታሪኮቻችንን ወደ ጎን ትተን›› ከዘመናት በፊት በተከሰቱ ወይም ተከስተዋል በተባሉ የፍሬ ነገር ወይም የትርክት ልዩነቶቻችን ሰበብ የዛሬ ትኩሳታችንን እያስታመመን ነው። ለመሆኑ ለእኛ ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር የዘመናት የታሪክ ትሩፋቶቻችን ናቸው ወይስ ያለፉ ነገሥታት ማንነት? ወይስ የታሪክ ሥፍራዎቻችን ላይ የሠፈሩ ሕዝቦች የነበራቸው ሥፍራ?
ሰኔ 2006 ዓ.ም
ቤቴ ጋደም ብዬ በቢቢሲ የሚተላለፍ የቀጥታ የቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት እያየሁ ነበረ። በዚህ ቀን የአንደኛ ዓለም ጦርነት 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ አውሮፓ ከተሞች እየተከበረ ነበር። ቤልጂየም ውስጥ ‹‹ሞን›› ከተባለ ቦታ ወጣ ብሎ በሚገኝ ‹‹ሴይንት ሴንፎሪየም›› በተባለ የመቃብር ሥፍራ የተደረገው ክብረ በዓል ከ3:00 ሰዓት በላይ የፈጀ ነበረ። ቢቢሲም የቀጥታ ሽፋን ሰጥቶት ነበር። ቦታው በወቅቱ በሁለት ጎራ ሆነው ይዋጉ የነበሩ የጀርመንና የቤልጂየም ብዙህ ሺሕ ወታደሮች አስከሬን ያረፈበት የመቃብር ሥፍራ ነው። ሙሉ ሥርጭቱን ተመልክቼ የታሪክ አመዘጋገባቸው ረቂቅነት አስደመመኝ።
በዚህ ክብረ በዓል ላይ በወቅቱ ጠላት ተባብለው የተዋጉት ኃይሎች አሸናፊም፣ ተሸናፊም፣ በአንድነት ቆመው ያለፈውን ሕመም ዘክረውታል። ዓለም አቀፍ ሽፋን በነበረው በዚህ ዝክረ ጦርነት ላይ የተገኙት የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት ባደረጉት ንግግር የያኔው ጦርነት ያለምንም ፍትሐዊ ምክንያት አገራቸው ጀርመን የለኮሰችው ኢፍትሐዊ ጦርነት እንደነበረና በዚህ ታሪካቸው እንደሚያፍሩና እንደሚቆጩ ገልጸዋል፡፡ ይህም ከእኛ በተቃራኒ አገራቸው ባለፈ ታሪኳ የነበረውን መራራ ሀቅ ያለማቅማማት እንደተቀበለችው ምስክር ነው። በዚሁ መርሐ ግብር ላይ ታዳሚ የነበሩት የታላቋ ብሪታኒያ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ካሜሮን ባደረጉት ንግግር ጦርነቱንና የጦር ሜዳ ጀግኖቻቸውን በተመለከተ፣ ‹‹መቼም አንረሳውም። ሁሌም እናስታውሳቸዋለን፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህንን ሲሉ ግን ተጠቃን የሚል ቅንጣት ስሜት በፊታቸው ላይ አልተነበበም፡፡ ምክንያቱም ለእነሱ ይህ ታሪክ እንጂ ፖለቲካ አይደለም፡፡ የዝግጅቱ አንድ ኩነት የነበረው በጦርነቱ የወደቁትን ሰዎች ለማሰብ በመላ አውሮፓ በተመሳሳይ ሰዓትና ደቂቃ መብራት ማጥፋት ስለነበረ አውሮፓ በድቅድቅ ጨለማ ተውጣ ታሪኳን ዘክራዋለች፡፡ ቁጭትና ሕመም ግን አልዋጣትም።
እኛ ኢትዮጵያውያን/ትም ያለፈ ታሪካችንን ወደድነውም ጠላነውም ዋጥ አድረግን ልንቀበለው የግድ ይለናል፡፡ ያለፈ ታሪክ ጠባሳ በስድብ አይታረምም። የተዛባ የታሪክ ዘገባን ጥናትና ምርምር እንጂ የአንድ ሰሞን የፌስቡክ እንካ ሰላምታ ወይም የመገናኛ ብዙኃን የቃላት እሩምታ አያርመውም። በዚህ ዘመን እናት አገራችን ኢትዮጵያን አንገት የሚያስደፋት ያለፈ ታሪኳ እድፍ ሳይሆን እኛ የዚህ ዘመን ትውልዶች ስሟንና ዘመኗን በሚመጥን ገጽታና ልዕልና ላይ ማስቀመጥ አለመቻላችን ነው፡፡ በመሆኑም ፀባችንንና ሽኩቻችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገታ አድርገን ለእናት አገራችንና ለቀጣይ ትውልዱ ልዕልና ብለን በአንድነት ልንቆምና ትኩረታችን በሙሉ በጎ ተፅዕኖ ልንፈጥርባቸው በሚገባ ችግሮቻችን ላይ ሊሆን ይገባል፡፡ ህሊናም፣ ታሪክም ይህንን ኃላፊነት ጥሎብናልና፡፡
ዛሬ በየቋንቋችን የመሰዳደቡን ‹ዕድል› ያገኘነው እንደ ዓድዋ ባሉ የጦር ዓውዶች ላይ በወደቁት የነፃነት ጀግኖች ክቡር የደም ዋጋ መነሻነት ነው። የዛሬ መጎሻሸማችን ያለፈ ታሪካችንን ወርቃማነት አይለውጠውም። ስህተቱንም አያርመውም፡፡ የቀደምት አባትና እናቶቻችንን በጎ አስተዋጽዖ ዋጋና ክብር አይቀንሰውም። ዛሬ ጎራ ለይተን ያለፈ ታሪካችን በሚመለከት ጉንጭ አልፋ ንትርክ ላይ መጠመዳችን ከድህነት ነፃ አያወጣንም፡፡ እንደ ዓድዋ ድል መላው ዓለም ያወቀውን ታላቅነታችንንም ሆነ የቀደምት መሪዎቻችንን ክብር ቅንጣት አይቀንሰውም፡፡ የታሪካችን ክፍል የሆኑት ቀደምት ድሎቻችን የኢትዮጵያውያን/ት ድል ናቸው። የቀደምት እናቶቻችንና አባቶቻችን (‹‹እናባቶቻችን››) አንድነት፣ ኩራትና ነፃነት ሁላችንም ኢትዮጵያውያን/ት በኩራት የምንዘክረው የጋራ እሴታችን ነው፡፡ ባለፈ ታሪካችን የነበረው ስህተት ልንደግመው የማይገባ፣ ልንክደውም የማይጠበቅብን የታሪካችን አንዱ ክፍል ነው፡፡ ወደኋላ ሄደን የማረምም ሆነ ጨርሶ የማጥፋት ቅንጣት ሥልጣንም አቅምም የለንምና፡፡
እናት አገር ኢትዮጵያ ካሳለፈችው የጨለማ ዘመን ይልቅ ብሩሃን ዘመኖቿ በቁጥርም በበረከትም ይልቃሉ። በቅንነት፣ ባለማወቅ፣ በክፉ ልቦና ወይም በአፍቅሮተ ተድላና ክብር ከበደሏት፣ ካዋረዷት፣ ሕዝባቸውን ካሳዘኑና ከበደሉ ስብዕናዎች በቁጥር የላቁ የተድላዋ፣ የገናናነቷ፣ የታላቅነቷና የክብሯ መሐንዲሶች፣ ባለሟሎች፣ ምሰሶና ማገሮች ነበሯት፣ አሏትም። ይህ እውነታ አሁን ላለንበት ዘመንም ይሠራል። እንደማንኛውም ሕዝብና አገር የከፍታም የቁልቁለትም ታሪክ አለን። የከፍታውም የዝቅታውም ታሪክ ዋነኛ ጸሐፊዎች፣ አዘጋጆች፣ አቅራቢዎችና ተዋናዮች ቀደምት እናቶቻችንና አባቶቻችን (‹‹እነ አባቶቻችን››) ናቸው።
እኚህ ቀድምት እናቶቻችን እና አባቶቻችን (‹‹እነአባቶቻችን››) ጊዜው፣ ዕውቀታቸውና የነበሩበት ዓውድ በፈቀደላቸው ልክ ለሠሩት ሥራና ላኖሩልን ታሪክ ኃላፊ ናቸው። ሰው ነበሩና እንደ እኛ ተሳስተው፣ እንደ እኛ አጥፍተው አልፈዋል። ከእነሱ ታሪክ ተነስተን ዛሬን ማበጀት ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ነው። ከተዉልን መርገምት ይልቅ የተዉልን በረከትና ፀጋ በእጅጉ ይልቃል። ከምናፍርባቸው ይልቅ የምንኮራባቸውን ዕልፍ ገጸ በረከቶችን አውርሰውናል። ያለፈው ታሪክ ቀስፎ ይዞን በምንከትበው የዛሬ ተግባራችን የነገ ተረካቢዎቻችንን አገር እያነወርን ነው። ስለዚህ ያለፈ ታሪካችን ታሪክ መሆኑን መረዳት፣ ማረጋገጥና መቀበል ይገባናል፡፡ ያለፈ ታሪካችንን ገንቢና ወደፊት የምናማትርበት ኃይል ብቻ ልናደርገው ይገባል።
ታሪክ የትምህርት ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን ጥናቱና ክርክሩ ሙያዊ እንጂ ፖለቲካዊ ሊሆን አይገባም። የኋላ ታሪካችን ቀስፎ ሊይዘን ስለማይገባ ራሳችንን አስታርቀን ከኋልዮሽ ጉዞ ነፃ ልንወጣ ይገባል። የኋላ ታሪካችን ጎዶሎዎች የዛሬይቱ እናት አገር ኢትዮጵያ አጀንዳ መሆናቸው የሚቋጭበት ድምድማት ያስፈልገናል። ትናንት የሆነውን ለመቀየር ቅንጣት አቅም የለንም። ዛሬ የሚሆነውን የማበጀት ሙሉ አቅምና ሥልጣን አለን። ነገን ብሩህ የማድረግ ታላቅ ኃላፊነት በእጃችን አለና ያለፈ ታሪካችን ታሪክ ብቻ ይሆን ዘንድ ድምድማቱን አበጅተን ወደፊት ልንጓዝ ግድ ይለናል። ድምድማቱን ለማበጀት ጊዜው አሁን ነው!!!
የዛሬ ምልከታዬን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ በቀጣይ ሳምንት ‹‹መሪዎቻችን ሰነፎች መሆናችንን በድፍረት የሚነግሩን መቼ ነው?›› በሚል ርዕስ እጠብቃችኋለው፡፡ የምንደማመጥ፣ ሐሳብን በሐሳብ ብቻ የምንሞግት፣ ካለፈው ይበልጥ በመጪው ላይ የምናተኩርና ምንጊዜም ለእናት አገር ኢትዮጵያችን ቅድሚያ የምንሰጥ የአንድ አገር ሕዝቦች እንሁን!!! ብሩሃን ቀናት ከፊታችን ይቅደሙ!!! ሰላም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው (LL.B, LL.M, MSW) ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ፡፡