Ethiopian Reporter Magazine
Wednesday, March 29, 2023
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት
Ethiopian Reporter Magazine
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
Ethiopian Reporter Magazine
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ

ለቅዱስ ያሬድ ሐውልት ማቆም ያለበት ማን ነው?

በ ሔኖክ ያሬድ
February 2020
ለቅዱስ ያሬድ ሐውልት ማቆም ያለበት ማን ነው?

በመስቀል ፍላወር አካባቢ በቅዱስ ያሬድ ስም የታነፀው አደባባይ

0
ያጋሩ
1.2k
ዕይታዎች
Share on FacebookShare on Twitter

“ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ እርሱን የመሰለ አልተገኘም!”  የሚል ብሂል በግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ የሠፈረለት የስድስተኛው ምዕት ዓመት የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ደራሲ፣ የዜማ ቀማሪ፣ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ግዕዙ “አልቦ እምቅድሜሁ ወአልቦ እምድኅሬሁ” ይለዋል፡፡

በብዙኃኑ ጎልቶ ከሚነገረው ከዜማው በተጨማሪ ሊወሱ ከሚገባቸው የቅዱስ ያሬድ ትሩፋቶች አንዱ ከሥነ ጽሑፍ ጋር የተያያዘው ነው፡፡ ከድንጊያ ላይ ጽሑፍ ወደ ብራና ላይ ጽሑፍ ሽግግር በተደረገበት ዘመነ አክሱም የሥነ ጽሑፍ መነሻው የቅዱሳት መጻሕፍት ከግሪክና ዕብራይስጥ፣ ከሱርስጥና ከዓረቢ ከሌሎችም ወደ ግዕዝ መተርጐማቸው ነበር፡፡

የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የልደት ዘመን (በብራና) ከትርጉም ጋር ቢያያዝም፣ ቅዱስ ያሬድ በስድስተኛው ምዕት ዓመት ከተነሣ በኋላ ያዘጋጃቸውና የደረሳቸው አንቀጸ ብርሃንን ጨምሮ ስድስቱ ዐበይት መጻሕፍት (ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ መዋሥዕት፣ ዝማሬ፣ ምዕራፍ) የመጀመሪያ አገራዊ ሥራዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ፕሮፌሰሩ ጌታቸው ኃይሌ ‹‹ቀሲስ ያሬድን ብቸኛ የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ መሥራች አድርጎ ለማየት በቂ ምክንያት አለን›› በማለት ብቻ ሳይወሰኑ ‹‹እንዲያውም የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ መሥራች ከማለት ይልቅ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ መሥራች ልንለው ይገባል፤›› ብለው አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ‹‹በድንጋይ ላይ ተጽፈው ከተገኙት ጽሑፎች በቀር የቅዱስ ያሬድን ድርሰቶች የሚቀድም በግዕዝ ቋንቋ የተደረሰ ድርሰት እስካሁን አልተገኘም፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፎች

አርበኞች ሽለላና ፉከራ ሲያሰሙ

May 2021
ደም የተከፈለበት ባርነት፤ የኤርትራ አብዮት ህልሞችና ውድቀት።

እውነትና ንጋት… (የመጽሐፍ ቅኝት)

August 2020

“ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም” ዓውደ ጥናት ሊካሄድ ነው

June 2020

ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

May 2020

ዓባይ የህልውና ዋስትና የሕይወት ኅብስተ መና

April 2020

ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

April 2020

 በአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት (515-529) ዘመን የኖረው ቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልቱ በሦስት መሠረታዊ መደቦች ግዕዝ፣ ዕዝልና አራራይ የተመደቡ ናቸው፡፡ ከደራሲነቱ ባሻገር ለዝማሬ እንዲመች ምልክት (ኖታ) አበጅቶላቸዋል፡፡ በኋላ ዘመን በዘመነ ጎንደር በ17ኛው ምዕት ዓመት ታካይና ተጨማሪ ምልክቶች ሊቃውንቱ አዘጋጅተውለታል፡፡ አሥሩ ምልክቶች ይዘት፣ ደረት፣ ርክርክ፣ ድፋት፣ ጭረት፣ ቅናት፣ ሂደት፣ ቁርጥ፣ ድርስ፣ አንብር ሲሆኑ የዜማ መሣሪያዎቹም መቋሚያ፣ ጸናጽልና ከበሮ ናቸው፡፡

ይህ ሥርዓተ ሙዚቃ ከኢትዮጵያ በመሻገር በመቋሚያ አማካይነት ሙዚቃን መምራት (ኮንደክቲንግ) በቅዱስ ያሬድ አማካይነት ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ትሩፋት መሆኑን የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ፈጣሪው ሙላቱ አስታጥቄ በምርምራቸው አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሥርዓተ ማሕሌት በምትጠቀመው መቋሚያ ላይም በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ስር ያካሄዱት ምርምር “ሙዚቃን መምራት ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው አስተዋፅኦ ነው” (ኮንደክቲንግ ኢዝ ኢትዮፕያን ኮንትሪዩብሽን ቱ ዘ ወርልድ) በሚል ርዕስ ነው፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በመቋሚያ ሙዚቃን መምራት  መምራት ማስተማሯን የሚያሳይ ኦፔራ አቅርበዋል፡፡ ይህም የጎላ ቅዱስ ሚካኤል ካህናት መዘምራንና የአውሮፓ ታዋቂ ኮንዳክተርን አቀናጅተው ያቀረቡት ሥራ በባህር ማዶ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥም በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የቅዱስ ያሬድ ቀን ሲከበር ጭምር ቀርቧል፡፡

ለቅዱስ ያሬድ መታሰቢያ ምን ተሠራ?

ለአሥራ አምስት ምዕት ዓመታት ሳይቋረጥ የኖረው ድርሰቱና ዜማው፣ ህያው መታሰቢያዎች ቢሆኑም፣ የእርሱን ታላቅነት የሚያመለክቱ ውርስና ክብሩን የሚገልፁ ቁሳዊ ነገሮች ምን ተሠርተውለታል? በአክሱም በስሙ የሚጠራ የአብነት ትምህርት ቤት፣ እንዲሁም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (1923-1967) በስሙ የቆመና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኝ ‹‹ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት›› አለ፡፡ ግን የትኛው ያሬድ?  መለያው ‹‹ቅዱስ ያሬድ›› ለምን ይዘነጋል? 

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መካከል ያለው አውራ ጎዳናም ‹‹ያሬድ መንገድ›› ተብሎ ተሰይሞለታል፡፡ ሰሌዳም ነበረው (ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰሌዳው በቦታው የለም)፡፡ ሐውልት ግን የለውም፡፡ ለምን?

የቀድሞው የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር መራሔ መዘምራን (ኮንዳክተር) አማኒ ኢብራሂም በ1970ዎቹ አጋማሽ በየካቲት መጽሔት ስለ ትምህርት ቤቱ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ስለ ቅዱስ ያሬድ ታላቅነት አውስተው ‹‹ሐውልት ቢቆምለት በወደድኩ›› ብለው ነበር፡፡ ያኔም ሆነ አሁን መንግሥታዊም ሆነ ያልሆነ ተቋም አዳምጦ ወደ ተግባር ለመሻገር ስለ መሞከሩ አልተሰማም፡፡

ይሁን እንጂ በቅርቡ በስሙ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ አስተዳደር፣ በመስቀል ፍላወር አካባቢ የሚገኘውን አደባባይ ለማልማት ከአራት ዓመታት በፊት ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ባገኘው ፈቃድ መሠረት፣ በ3.2 ሚሊዮን ብር ወጪ ያሠራውንና በቅዱስ ያሬድ ስም የሰየመውን አደባባይ ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊቃነ ጳጳሳትና የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ኃላፊዎች በተገኙበት አስመርቋል፡፡  

የሰበካ ጉባዔው ርዕይ በአደባባይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን እስከ ሐውልት መትከል ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ በአደባባዩ ምረቃ ወቅት እንደተገለጸው፣ የሐውልቱ ዲዛይን መዘጋጀቱንና ሐውልቱን ለመገንባት ፈቃድ የሚሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሆኑ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሐውልቱን ለማቆም ቅዱስ ያሬድ ከቤተ ክርስቲያን ጉያ እንደመውጣቱ ቤተ ክርስቲያን  ተነሳሽነቱን ብትወስድም፣ ከአገራዊ ባለውለታነት ከዘርፈ ብዙ የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ወጣኒነቱ አንፃር መንግሥት በተለይም የባህልና ቱሪዝም፣ የትምህርት ሚኒስቴሮች ድምፅ ማሰማት አይገባቸውም ወይ የሚሉ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡ ለባሕር ማዶ ታላላቅ ሰዎች ለነካርል ማርክስ፣ አሌክሳንደር ፑሽኪን፣ ካርል ሄንዝ ሐውልት በመዲናዪቱ ለማቆም የተጉ ተቋማትስ ለፋና ወጊው ቅዱስ ያሬድ ላለማቆም ምን ገታቸው?

የቅዱስ ያሬድ ሰብእና

የታሪክ ምሁሩ ሥርግው ሀብለ ሥላሴ (ዶ/ር) “Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270” በተሰኘው መጽሐፋቸው ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ባህል ዕድገት ውስጥ ያለውን ሁለገብ አስተዋጽኦ ከትምህርት፣ ከሥነ ጽሑፍ፣ ከሙዚቃና ከመሣሪያዎች አኳያ ይዘረዝራሉ፡፡ እርሱን የቅኔ ጀማሪና የባህላዊ ትምህርት መሥራች ይሉታል፡፡ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ የተጀመረው በቅኔ መልክ ሆኖ በይቀጥላልም ወደ ዝርው መሻገሩ ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ ማሳያ የያሬድን ድጓ የቅኔና የዝርው ስብጥር መሆኑ ይገለጻል፡፡

በሥነ ጽሑፍ ረገድ ከአክሱም ዘመን ጀምሮ ልዩ ቦታ እንዳለው የሚያሳየው አንዱ ድጓው የኤፒክ ቅርፅ ያለው መሆኑ ያም በመላእክት፣ ቅዱሳንና ሰማዕታት ትግልና ገድል አጉልቶ በቅኔያዊ ቋንቋው ያሳያል፤ ይገልጻል፡፡

እንደ ሥርግው አገላለጽ፣ በድጓ ውስጥ የፍልስፍና መነሻዎች ወይም ኖኅያት (ኢሌመንትስ) እናገኛለን፡፡ ሰው ማወቅ፣ መርመር እንደሚገባው የሚያስገነዝብበት መልክ አለው፡፡ ትክክለኛውን የሕይወት መንገድ መከተል መጻሕፍትን መመርመር አስፈላጊነቱን ይጠቁማል፡፡ ያሬድ ለጥበብ ልዩ ቦታ ይሰጣታል፡፡ ጥበብ በዋጋ የማትተመን የሰው ልጅ ስጦታ መሆኗን ለዚህች ዓለም ከጥበብ ጋር የማይወዳደር አንዳች ነገር አለመኖሯን ያመለክታል፡፡ ሀብትን ከመሰብሰብ ይልቅ ጥበብን መጠየቅ እንደሚሻል፤ ከወርቅ፣ ብር፣ ዕንቁ ወይም ማንኛውም የከበረ ድንጊያ ከጥበብ ጋራ ሊተካከሉ፣ ዕሪና ሊሆኑ እንደማይችሉ ያመሠጥራል፡፡

ያሬድ ማኅሌታይ በድርሰቶቹ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የሥነ ምኅዳር (ኢኮሎጂ) ፍሬ ጉዳዮችን አካትቶ ይዟል፡፡ በዘመናችን በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ የነገረ ሃይማኖት ተቋማት ‹‹ኢኮቴኦሎጂ›› የተሰኘ ሥነ ምኅዳር ከነገረ መለኮት ጋር ያያያዘ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ ሥነ ምኅዳርን ሥነ ፍጥረትን በተለይም ከዕፀዋትና አዝርዕት ጋር አዛምዶ የኢኮሎጂንና ቴዎሎጂን ጽንሰ ሐሳብ በድጓው ያስቀመጠ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ይህን ጽንሰ ሐሳብ ያስተዋወቀ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኢኮቴኦሎጂ የበላይ ጠባቂ (ዘፓትረን ኦፍ ኢትዮፒያን ኢኮቴኦሎጂ) ተብሎ መጥራት ይገባል፡፡

ሸዋ እና ጎጃምን በሚያዋስነው የዓባይ ወንዝ ላይ የተሠራውና በሁለተኛው ሺ መዝጊያ በሦስተኛው ሺ ዋዜማ (2000 ዓ.ም.) የተመረቀው አዲሱ ድልድይ ‹‹ህዳሴ›› መሰኘቱ ተምሳሌነቱ በወቅቱ እንደተገለጸው ወደ ቁሳዊ ዕመርታ ለማምራት የተተለመ የመሆኑን ያህል፣ ቅዱስ ያሬድም የኪነ ጥበብም ሆነ የመንፈሳዊ፣ የሰብአዊ (ሒዩማኒትስ) ጉዳይ የህዳሴው ድልድይ እንዲሆን ምልክት ሊቆምለት፣ በአርአያነት ሊጠቀስ እንደሚገባ በወቅቱ ያመለክቱ ነበሩ፡፡

ለዚህም ዋቢ ያደረጉት “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” የሚባለውን የእጓለ ገብረ ዮሐንስ (ዶ/ር) መጽሐፍ ነበር፡፡ በመጽሐፉ አንደኛው ክፍል ያሬድና የኢትዮጵያ ሥልጣኔ በሚል የሠፈረውን ሐተታቸውን ማጠየቂያ አድርገውታል፡፡

 ‹‹በአፍሪካ ምሥራቃዊ ዳርቻ የታወቀውን ሥልጣኔ ለማስገኘት ብዙ ሊቃውንት ጥረዋል፡፡ ሰማዩ ወይም ጠፈሩ ልሙጥ ነበር፡፡ የነዚህ ሰዎች ጥረት የሚያበሩ ከዋክብት በዚህ ጠፈር ላይ አስገኝቶአል፡፡ ምን ይሆናል ብዙ ደመና ሸፍኖቸአዋል፡፡ እነሱን ለመረዳት ክንፍ፣ ብርቱ የሕሊና ክንፍ ያሻል፡፡ ከማኅበረ ሊቃውንት አብነት ወይም ምስለኔነት ያለውን እንመርጣለን፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዘመናት መካከል ለነበሩት ሁሉ የአገራችን ሊቃውንት እንደራሴነት ያለው ትልቅ መንፈስ ነው ብለን እናምናለን፡፡››

ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ገጽ ነው፡፡ የእርሱን ምሳሌ መሠረት አድርገን ስለ ሀገራችን ሥልጣኔ ለመናገር እንፈልጋለን የሚሉት እጓለ፣ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ቴኦሴንትሪክ (theocentric) ብሎ መጥራት የሚቻለው የማናቸውም ነገር ማዕከል የሰብአዊ ጥረት ሁሉ ምክንያት እግዚአብሔር ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡ ፕላቶ እና ያሬድንም ያነፃፅራሉ፡፡

በፈላስፋው ፕላቶ (አፍላጦን) ሪፐብሊክ  እና በቅዱስ ያሬድ ድጓ  ውስጥ የሚገኙ ሐሳቦችን እጓለ ገብረ ዮሐንስ (ዶ/ር) እንዲህ ፈክረውታል፡-

ሪፐብሊክ ‹‹የሕግጋት ውሳኔ ምክንያት ማነው ወዳጄ እግዜር ነው ወዳጄ እግዜር ነው›› ሲል፣ የዘመነ ጽጌ ድጓ ደግሞ እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ያደረገውን እነሆ ተመልከቱ፤ በጽድቅ ለጽድቅ ነገሡ፡፡ የጽድቅን የብረት ልብስ ለበሱ፤ የጽድቅን ብርሃን ተጎናጸፉ፡፡ የደኅንነትን ሽልማት ደስ እያላቸው አጌጡ፡፡

እንደ እጓለ አገላለጽ፣ ቅዱስ ያሬድ የዘመነ ጽጌን ድጓ ስመ ጥሩዎቹን ነገሥታት አብርሃና አጽብሓን በማሞገስ ነው የሚጀምረው፡፡ የሊህ ነገሥታት ምርጫቸው እግዜር ነው፡፡ ሐሳባቸው ሥራቸው መለኮታዊ ዋስትና ያለው ጽድቅ ትክክለኛ ፍርድ ነው፡፡ በዚህ አንገርጋሪ በሚባለው መዝሙር ውስጥ ቅዱስ ያሬድ አንዱን ቃል ሦስት ጊዜ ደጋግሞታል፡፡ ይህም ቃል ጽድቅ የሚለው ነው፡፡ እውነት፣ ትክክል ፍርድ ማለት ነው፡፡

ፕላቶን በሪፐብሊክ ድርሰት ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚመላልሰው ቃል ይኸው ጽድቅ (ዲኪዮሲኒ) የሚለው ነው፡፡ እንደሚለው የመንግሥት መሠረቱ ጽድቅ ትክክለኛ ፍርድ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም የአብርሃንና የአጽብሐን ንግሥ ከጽድቅ ከትክክለኛ ፍርድ ጋር አፃምሮታል፡፡

ቅዱስ ያሬድ በሠዓሊ ዳንኤል ጧፌ

ነገረ አእምሮ በቅዱስ ያሬድ

ሃቻምና አክሱም ዩኒቨርሲቲ በቅዱስ ያሬድ ቀን ባዘጋጀው ዓውደ ምርምር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ‹‹ነገረ አእምሮ፡- ምን፣ እንዴት እንወቅ?›› በማለት በመጽሐፈ ድጓ ላይ የተመሠረተውን ጥናታቸውን አቅርበው ነበር፡፡

መንደርደሪያው፣ ‹‹አንተስ፣ አንተ ግን፣ አንተንኳ፣ አንተንማ ለማወቅ ብትሻ የምድርን (አፈር÷ ጠፊ የኾነውን) ሐሳብ ተው፡፡ ከዋክብትን ተሻገራቸው፡፡ የሕብረታቸውን – የአኳኋናቸውን ውበት ተመልከት፡፡ ከዚኽ ኹሉ እይታኽ ተነስተኽ በልቡናኽ የማይጨፈለቅ ሥሉስን ዐስብ›› የሚል ነው፡፡

አንድ ከባድ፣ የሚቻል የማይመስል ኃላፊነት ነው ሊቁ የጣለብኽ፡፡ ‹‹ከዋክብትን ተሻገራቸው፣ ዙራቸው፣ አገላብጠኽ እያቸው›› ነው ቃል በቃል ያለኽ፡፡ ይኽ እንዴት ነው እሚቻል? ሌላም ሥራ ጥሎብኻል፡ ‹‹ከዚኽ ተነስተኽ ዐስብ››፡፡ ኹለት ታላላቅ የነገረ አእምሮ ሐሳቦች ናቸው በዚኽች የድጓ ንባብ የተነገሩ፡፡

ሰው አንድን ነገር ከማወቅ ተነስቶ ሌላን ነገር ሊያውቅ ይችላል፡፡ የአእምሮ – የዕውቀት ተሸጋጋሪነትን ነው ይኽ የሚያስረዳን፡፡ ‹‹የከዋክብትን ሥን፣ ስንኝ፣ ሕብረት ተመልክተኽ ዐስብ›› ይላል፡፡ ማየት፣ መመልከት ለሐሳብ መነሻነት እንዲውል እንጂ ቆሞ እንዳይቀር ዐደራ ሰጠ፡፡

በዚኽች ድጓ የተነገረ ሌላው ቊም ነገር ‹‹አንተ ግን ለማወቅ ብትሻ›› በምትለው ሐረግ የተሰጠው ሐሳብ ነው፡፡ የትሕትና ውጤት ነው፡፡ በጥበብ፣ በከፍተኛ ሐሳቦች የታሸ ሊቅ ደረቅ ትእዛዛትን ከማውረድ ይልቅ ማስፈቀድ፣ ማስወደድ ይቀናዋል፡፡ ውስጡ ‹‹እባክኽ ማወቅን ውደድ›› የሚል አባታዊ ምክር አለ፡፡ እርሱን ተከትሎም የአስተዋወቅን ስልት የተለመው ‹‹በልቡናኽ ዐስብ፤ ከዋከብትን አልፈኽ ዙር፤ ይኸንም ለማድረግ ተራ ዐሳብን ተው›› የሚለው ትምህርት ተሰጠን፡፡

ሥነ ፍጥረትን ማወቅ እንዲቻል ከያሬድ በላይ የሰበከልን፣ ያሳየን ወገን የለንም፡፡ ከዝናብ ኮቴ እስከ ዕፀዋት ዝማሬ በያሬድ የተብራራ ሥነ ፍጥረት ነው፡፡

የጥናት ደወል

‹‹የያሬድ ስም ገናና የሆነው በዝማሬው ብቻ አይደለም፡፡ የቃላቱ ጣዕም፣ የቅኔዎቹ ረቂቅነትና የሐሳቡ ምጥቀት እኩያም የለው፤ እንዲያው ቀረብ ብለን ብናጠናው ለመላ የባህል ታሪካችን ዋና ምንጭ መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ግን ሊቃውንቶቻችን በጸሎትነት ሲዘምሩት፣ በተመስጦ ሲደጋግሙትና በረቀቀ ውዝዋዜ ሲያሸበሽቡት ነው የኖሩት እንጂ፣ ታሪካዊ ይዘቱንና ማኅበራዊ መልእክቱን ተንትነው በጽሑፍ አላቆዩንም፡፡ አሁን እኛ ይህንን ለማድረግ መጀመር አለብን፡፡››

የጥናት ደወሉ በተስተጋባ ከአርባ ዓመታት በኋላ ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ ከዓመት በፊት ስለ ቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ጥልቅ ትንተና ያለበትን ግዙፍ መጽሐፋቸውን ኆኅተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቅጽ ፩ አደባባይ ላይ አውለውታል፡፡

ሊቀ ጉባኤ በመጽሐፋቸው፣ ቅዱስ ያሬድ ዜማን ቅርጽ በማስያዝ ሳይጠፋ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ያደረገ ለሌሎች የዜማ ሊቃውንት ፈር የቀደደ ሊቅ ነው ብቻ በማለት አልተወሰኑም፡፡ ዘርፈ ብዙ መምህርና ተመራማሪ መሆኑን ያጠይቃሉ፡፡ ከመረመሩት ሥራዎቹ በመነሳትም በምሳሌዎች በማስደገፍ እርሱ ሳይኮሎጂስት፣ ሶሺዮሎጂስት፣ አንትሮፖሎጂስት፣ ፈላስፋ፣ ቦታኒስት፣ አስትሮኖመር፣ ጋዜጠኛ፣ ወዘተ… ይሉታል፡፡  ያየውንና የሰማውን አደላድሎ ሚዛናዊ ዘገባ ዘግቦ ይገኛል፤ ለፈጣሪ፣ ለነፍስና ለሥጋ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ ይገኛል፡፡ ከክርስቶስ በስተቀኝ የተሰቀለው ሽፍታንም በምናብ ቃለ ምልልስ ያደርግለታል፡፡ ከሥነ ልቦና አንፃርም በምሳሌነት የቀረበውም እነሆ፡- “ዕውቀት ለደኃራዊው ሕይወትህ ለቀሪው ህልውናህ እንደጣፋጭ ወይን ነው፡፡ ተስፋህም አይጠፋም፡፡ አሟሟትህም ያማረ የሠመረ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ተማር ሌባ የማይነጥቅህን የጥበብ መዝገብ ሰብስብ፡፡”

አንዱ የመልክዕ ደራሲ ቅዱስ ያሬድን የገለጸበት ግዕዛዊ ድርሰት ጌታቸው ኃይሌ በአማርኛ እንዲህ አስተጋብተውታል፡፡

‹‹ሰላም ለመላስህ አርያምን ለገለጸ፣

በጽዮን ቤተ መዳረሻ፡፡

ዓለምን የቀደስክ ቀሲስ ያሬድ፡፡

ቀደም ብሎ ያለፈ እንዳንተ ያለ የለም፣

እንዳንተ ያለ የሚመጣም የለም፡፡››

 

ShareTweetShare

ተዛማጅ Posts

አርበኞች ሽለላና ፉከራ ሲያሰሙ
ታሪክ

በ ሔኖክ ያሬድ
May 2021
0

ኢትዮጵያ በወራሪው የፋሺስት ጣሊያን ሠራዊት ላይ ድል የተቀዳጀችበት ሰማንያኛ ዓመት ረቡዕ ሚያዝያ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. አክብራለች፡፡ በተለይ በዓሉ በአዲስ አበባ ከተማ በአራት ኪሎው የሚያዝያ 27 አደባባይ፣ የጥንት አርበኞችና...

ተጨማሪ ያንብቡ
ደም የተከፈለበት ባርነት፤ የኤርትራ አብዮት ህልሞችና ውድቀት።

እውነትና ንጋት… (የመጽሐፍ ቅኝት)

August 2020
“ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም” ዓውደ ጥናት ሊካሄድ ነው

“ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም” ዓውደ ጥናት ሊካሄድ ነው

June 2020
ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

May 2020
ከህዳሴው ግድብ ድርድር በስተጀርባ

ዓባይ የህልውና ዋስትና የሕይወት ኅብስተ መና

April 2020
ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

April 2020
ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

February 2020

በብዛት በመነበብ ላይ ያሉ መጣጥፎች

ዶ/ር ቅድስት

“አንድ ሰው ምልክቱ ስላልታየበት በኮሮና ቫይረስ አልተጠቃም ብሎ መደምደም አይቻልም”

May 2020
C:\Users\IT\Documents\A01\pics

የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውኃ ሙሌትና መቆሚያ ያጣው የግብፅ ሩጫ

July 2020
የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ

የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ

May 2020
ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

May 2020
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ

ከጦር ጀግኖች ባሻገር . . .

May 2020

Follow us on Facebook

  • ዶ/ር ቅድስት

    “አንድ ሰው ምልክቱ ስላልታየበት በኮሮና ቫይረስ አልተጠቃም ብሎ መደምደም አይቻልም”

    384 shares
    Share 384 Tweet 0
  • የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውኃ ሙሌትና መቆሚያ ያጣው የግብፅ ሩጫ

    21 shares
    Share 21 Tweet 0
  • የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ

    0 shares
    Share 0 Tweet 0
  • ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

    44 shares
    Share 44 Tweet 0
  • ከጦር ጀግኖች ባሻገር . . .

    169 shares
    Share 169 Tweet 0
Ethiopian Reporter Magazine

ሪፖርተር ሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተር

(+251) 116 61 61 81

(+251) 116 61 61 85

[email protected]

የኢትዮጵያ ሪፖርተር መጽሔት

የኢትዮጵያ ሪፖርተር መጽሔት በሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተር እየታተመ የሚወጣ ወርኃዊ መጽሔት ሲሆን፣ የሚያተኩረውም በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር መጽሔት በ ኢሜይል ለማግኘት

  • Ethiopian Reporter
  • The Reporter Ethiopia
  • Reporter Tenders
  • Ethiopian Reporter Jobs

© 2020 Ethiopian Reporter Magazine - By Media And Communications Center.

ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
  • የፊት ገጽ
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት

© 2020 Ethiopian Reporter Magazine - By Media And Communications Center.

Login to your account below

Forgotten Password?

Fill the forms bellow to register

All fields are required. Log In

Retrieve your password

Please enter your username or email address to reset your password.

Log In