ክፍል ፩

የኩሽና የኩሸቲክ ጉዳይ የፖለቲካ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነበተ። እውነታውን መርምሮ ከማወቅ ይልቅ እዚህም እዚያም ለጊዜያዊ ፍጆታ በሚመስል የታሪክ መሠረት የሌለው ትርክት በዘፈቀደ ሲሰጥ ይስተዋላል። ይህን ጉዳይ ፈረንጆች ሳይቀሩ ታዝበውታል፣ “ዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የኩሸቲክ ሕዝብ ከሴሜቲክ ሕዝብ በላይ የአገሪቱ ባለመብት እንደሆኑ አጥብቀው ያሰምሩበታል” (ብሬየር 2007:460)። ለዚህ ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች ማቅረብ ይቻላል። አንደኛ፣ የዘመናችን የኩሸቲክ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ከጥንታዊ የኩሽ ሕዝቦች ጋር አለቦታቸው ማዛመድ፤ የቋንቋና የሕዝብ ግንኙነትን በውል አለመለየትና ስለቋንቋዎቹ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች የደረሱበትን በአግባቡ አለመረዳት ችግር ነው። ሁለተኛው፣ በቀደምት ጸሐፊዎች የቀረቡ ግልፅ ያልሆኑ፣ በተወሰነ ደረጃም የሚያምታቱና አሳማኝ ታሪካዊ መረጃ የሌላቸው፣ እንዲሁም ታሪክና እምነት አለመንገዳቸው እየተደባልቁ የቀረቡባቸው ትርክቶች መቅረባቸውም ጭምር ሊሆን ይችላል። ሦስተኛው፣ ስለኩሽ ስርወ መንግሥትና ስለኩሸቲክ ቋንቋዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዙም አለመታወቁ ነበር። ስለኩሸቲክ ቋንቋዎች የእርስ በርስ ግንኙነትና አጠቃላይ የዘር ምደባ በበቂ ሁኔታ አይታወቅም ነበር። አሁንም በአርኪ ሁኔታ ታውቋል ማለት አይቻልም። ለዚህ የተለያዩ ድምዳሜ ላይ የደረሱ የቅርብ ጊዜ ጥናቶችን ማየቱ ብቻ በቂ ነው። ስለጥንታዊው የኩሽ ስርወ መንግሥትም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። የግብፅ ታሪክ ጥላ የሆነበት ይመስላል። ስለዚህ ስርወ መንግሥት አሁንም ብዙ ታውቋል ማለት አይቻልም። ለዚህ በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንደኛው፣ ጽሑፍ በኩሽ ስርወ መንግሥት የጀመረው ዘግይቶ መሆኑና እሱም ቢሆን ይዘቱ አለመታወቁ ነው። ሁለተኛው ዘረኝነት ነው። የኩሽ መንግሥት በማያጠያይቅ የጥቁር ሕዝብ ታሪክ በመሆኑ ይህን ለማጥናት በቀደሙት ጊዜያት ብዙም ተነሳሽነት አለማሳየት ነበር። በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ጥናቶች እየቀረቡ ይገኛል።
ታሪክ ተረት አይደለምና ታዳሚን ለመሳብ እያጣፈጡ፣ ሲያሻም እየለወጡ ወይም እያዛቡ ለማቅረብ የሚያስችል መድረክ የለውም። በታሪክ ስም የቀረቡ ሥራዎች ሁሉ ታሪክ ሊሆኑ አይችሉም። ሰነድና ማስረጃ የሌለው ሥራ ጎራው ከታሪክ አይደለም። በሰነድና በማስረጃ የቀረቡ የታሪክ ሥራዎች እንኳ ተጨማሪ ሰነድና ማስረጃ ሲገኝ፣ ውስጣቸው እየተመዘነ የሚሻሻለው ተሻሽሎ፣ የሚለወጠው ተለወጦ ይጻፋል። የተረት ዋንኛ መመዘኛው ውበቱ ሲሆን፣ የታሪክ ግን እውነታ ነው። በቋንቋዎች መካከል ያለ ዝምድናም ከስያሜ መመሳሰል ብቻ ተነስቶ የሚፈረጅ ሳይሆን፣ ራሱን በቻለ ሳይንሳዊ መንገድ ተጠንቶ የሚወሰን ነው። ልክ እንደ ታሪኩ ሥራ ተጨማሪ ማስረጃ ሲገኝ በአንድ ወቅት የነበረ አስተሳሰብ/ምደባ በሌላ ወቅት የማይሻሻልበት ወይም ሙሉ በሙሉ የማይሰረዝበት ምክንያት የለም። በዚህ መጣጥፍ ወደ ፖለቲካው ዝርዝር ሳንገባ፣ ከሥነ ልሳንና ከታሪክ አንፃር በኩሽና ኩሸቲክ ላይ ጠቅለል ያለ ትንታኔ ለማቅረብ እንሞክራለን። ሰፊ ቦታ የለንምና የኩሽን አጠቃቀም ከጥንት እስከ ዛሬ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ስንሞክር በጣም ባጠረ መልክ ነው። ዋናው ዓላማችን ኩሽ ወይም የዚህ ዝርያ ቃል በሆኑት ስያሜዎች ስለሚጠቀሱት ሕዝቦችና ቋንቋዎች እንዲሁም ስለጥንታዊ የኩሽ ስርወ መንግሥት ጠቅለል ያለ ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው።
ኩሽ
ኩሽ ጥንታዊ ቃል ነው። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም በጥንታዊ ግብፆች ሥራዎችም ተጠቅሶ ይገኛል። እስካሁን ባለን መረጃ፣ በግብፅ ኩሽ የሚል ቃል (ወይም የዚህ ተመሳሳይ ቅርፅ) ተጽፎ ከተገኘው ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው በመካከለኛው ስርወ መንግሥት ዘመን በ2100 ቅድመ ጋራ አቆጣጠር (ቅጋአ) ነበር። የኩሽ ሀገረ-ግዛት በየወቅቱ መስፋትና መጥበብ ቢያሳይም በዋናነት የሚያመለክተው ከግብፅ ደቡብ ነጭ ዓባይ፣ ጥቁር ዓባይና አትባራ ወንዞች የሚገናኝበትን ግዛት ባሁኑ ጊዜ ሱዳን የሚባለውን የጎረቤታችንን ሀገር ነው። በሰሜን በኤለፋንቴ የመጀመሪያው ካታራክት የጥንታዊ ግብፅ እና የኩሽ ስርወ መንግሥታት ጥንታዊ ወሰን ተደርጎ ይቆጠራል። ደቡብ ሱዳን በዚህ መንግሥት ግዛት ስር አይካተትም። ኢትዮጵያን ቀርቶ ከኢትዮጵያ ግዛት በኩሽ ስር የነበረ በታሪክ አይታወቅም። ኩሽ ግዛቱን ወደሜሮኤ ባዞረበት ወቅት ኢትዮጵያ የተጠናከረ የራሷ አስተዳደር ነበራት። እንደውም ለኩሽ ማዕከላዊ መንግሥት መጥፋት ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያው የአክሱም ስርወ መንግሥት እንደሆነ ይታመናል።
የኩሽ ስርወ መንግሥት የኢትዮጵያ ስርወ መንግሥት እንዲሁም የኑብያ ስርወ መንግሥት በመባልም ይታወቃል። እነዚህ የኋለኞቹ አጠቃቀሞች አሁንም በተለዋዋጭነት በምሁራን ሥራዎች ይገኛሉ። በእርግጥ ኑብያ የሚለውን ስያሜ በስፋት የሚጠቀሙበት የታሪክ ባለሙያዎች ናቸው። የኩሽ ስርወ መንግሥት ራሱን ኑብያ በሚል ስያሜ ጠርቶ አያውቅም። የኩሽ ስርወ መንግሥት የራስ ስያሜ ምናልባት ካሽ ሊሆን ይችላል። ከመካከለኛው የግብፅ ስርወ መንግሥት ጀምሮ በግብፃውያን ዘንድ በአብዛኛው ተመዝግቦ የሚገኘው ካሽ በሚል ነው።
የኩሽ ስርወ መንግሥት የ25ኛው ስርወ መንግሥት ባለቤቶች ናቸው። በዚህ ስርወ መንግሥት በርካታ ታላላቅ የሥልጣኔ ተግባራት ተከናውነዋል። ግብፅም ታላቅ የቆዳ ስፋት የነበራት በዚሁ በኩሽ አገዛዝ ስር በነበረችበት ወቅት ነው።
ኩሽ በጥንታዊ አጠቃቀሙ ሕዝብን/ነገድን ለማመልከት ሲውልም ይስተዋላል። በሁሉም ቦታዎች በዚህ ቃል የተገለፁት ነገዶችም ሆኑ ቦታዎች ሁሌም አንድ ናቸው ማለት ግን አይቻልም። በአንዳንድ ሥራዎች የቃሉ አጠቃቀም ግልፅ ያልሆነበት ሁኔታም አለ። በዚህ ክፍል በጥንታዊ ሥራዎች የዚህን ቃል አገባብ፣ እንዲሁም የኩሽ ግዛትን እንመረመራለን።
የኩሽ/የቃሉ ምንጭ
ኩሽ እንደቃልነት ከጥንት እስካሁን በሁሉ ቋንቋ አንድ ዓይነት ንበት አልነበረውም። በእርግጥ ይህ እንዲሆን መጠበቁም የዋህነት ነው። ከተለያዩ ታሪካዊ አጋጣሚዎች በተጨማሪ እያንዳንዱ ቋንቋ የራሱ የሆነ የሰዋስው ሥርዓት አለውና አንድ ዓይነት ንበት በሁሉ ቋንቋ የግድ መኖር የለበትም። ይህ ቃል በግዕዝ ካሱ ነው። ለዚህ ከቀዳሚ ሥራዎች ውስጥ የኢዛናን የድንጋይ ላይ ጽሑፎች መጥቀስ ይቻላል። በኢዛናው ጽሑፍ (DAE 5,6,7) ላይ በግሪኩ ኢትዮጵያ የሚለው በግዕዝና በሳብያን ቅጂው ሐበሠተ ‘ሀበሻ’ የሚለውን ወክሎ ነው።
ብሬየር በግብፅ በተለያዩ ወቅት እንዲሁም በተለያዩ ቋንቋዎች ቃሉ ምን እንደሚመስል በዝርዝር ተመክልቷል። እንደብሬየር ከሆነ፣ በጥንታዊ ፋርስ ኩሳ፣ በእብራይስጥ ኩሺ፣ በሜሮቲክ ቄስ /qes/፣ (በመካከለኛው) ባቢሎንያን ካሺ /Ka-ši/፣ በቅብጥ (Coptic) ኤክዮሽ /ekjōš/ የሚል እናገኛለን (ብሬየር 2007:458)። ብሬየር የቅብጡ ኤክዮሽ ከኢካሽ እንደመጣ ግምቱን ሰጥቷል። ለዚህ ምክንያቱም፣ በ25ኛው የግብፁ ስርወመንግሥት ወቅት በተፃፈ ፅሁፍ ላይ እና በዲሞቲክ የዚህ ቃል ቅርፅ ኢክሽ /ikš/ ስለሆነ ነው። ብሬየር ኢክሽ በበኩሉ ከካሺ/ክሺ//kši/ የመጣ ይመስላል ይላል። በመካከለኛው የግብፅ መንግሥት፣ ካ/ክሺ /K š(i)/ ሲሆን፣ ሁለተኛው አማካይ ዘመን በሚባለው ክሺ /Kš(i)/ ነው። በአዲሱ ስርወመንግሥት ደግሞ ክሽ /Kš/ ነው። በጥንታዊ የግብፅ ቋንቋ ከ /k/ ስርጭቱ በጣም አናሳ ነው። ይህ ድምፅ ብዙውን ግዜ የሚገኘው በተወሰኑ ቃላት ውስጥ በመሆኑ የውሰት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ። ይህም ማለት ከ ያላቸው ቃላት በጥንታዊ ግብፅ የምናገኛቸው ከሌሎች ቋንቋዎች የተወሰዱ/የተወረሱ ሳይሆኑ አይቀርም ነው። የዚህ አንድምታው ደግሞ ጥንታዊ ግብፅ ካሽ (ወይም የዚህ ቃል የተለያየ ቅርፅ) ከሜሮቲክ ጋር ተዛማጅ ከሆነ ጥንታዊ አባት ቋንቋ ተውሶ ይሆናል የሚል ነው (ብሬየር)። የሜሮቲክ አባት ቋንቋ ሜሮቲክ ይገኝበት የነበረው አካባቢ፣ የአሁኒቱ ሱዳን የነበረ ነው ተብሎ ይታሰባል።
ጥንታዊ ሀገረ ኩሽ
የዛሬ ዘጠኝ ሺሕ ዓመት ገደማ ከኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች ጀምሮ የዓባይ ሸለቆን ይዞ እስከታች ግብፅ ድረስ ተመሳሳይ የባህል ሥልጣኔ አብቦ እንደነበር ይገመታል። የስንቁፋሮ/አርኪዮሎጂ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በዚህ አካባቢ የነበሩ ሕዝቦች እስከ 3000 ቅጋአ ድረስ ተመሳሳይ ባህልና የዕድገት ደረጃ ላይ ነበሩ። የቀብር ሥርዓታቸው ተመሳሳይ፣ ካልሆነም አንድ ዓይነት ነበር። የሸክላ ሥራዎቻቸው፣ ከድንጋይና ወደኋላ ላይ ደግሞ ከብረት የተሠሩ መሳሪያዎቻቸው አንድ ናቸው። እነዚህ መሳሪያዎች በደቡብ እስከ ካርቱም፣ በሰሜን ደግሞ እስከ አስዩት ድረስ በቁፋሮ ተገኝተዋል። እንደ አዳም ከሆነ መሳሪያዎቹ በርካታ አካባቢዎች የአኗኗር ዘይቤያቸው፣ እምነታቸው፣ የቀብር ሥርዓታቸው፣ እንዲሁም አጠቃላይ ሕይወታቸው/የየቀን ኑሯቸው፣ አደን፣ አሳ ማስገርና የከብት እርባታ እንዲሁም በጣም ቀላል የሆነ የእርሻ ተግባር ጅማሮ ተመሳሳይ ነው።
በግብፅና ከመጀመሪያው ካታራክት በስተደቡብ ባለው ሕዝብ መካከል የሥልጣኔ ልዩነት በዋነኛነት መታየት የጀመረው ከጽሑፍ ጋር በተያያዘ ባህል እንደሆነ ይገመታል። ጽሑፉ በግብፅ 3200 ቅጋአ አካባባቢ መታየት ጀመረ። ከመጀመሪያው ካታራክት በታች ባለው ሕዝብ ግን ይህ ሁኔታ አልታየም። የኩሽ ግዛት የጽሕፈት ባህልን ያስተዋወቀው በኋላ ላይ ዘግይቶ በሜሮኤ ዘመን ነው። በርግጥ ኩሾች ግብፅን ጠቅልለው በገዙበት ወቅት የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ ባህል በመውሰድ በጽሑፍ መገልገላቸው አልቀረም።
በአሁኒቷ ሱዳን የዛሬ ስድስት ሺሕ ዓመት (ቅጋአ) ገደማ በከርማ አካባቢ መታየት የጀመረው ሥልጣኔ እያደገ ሄዶ ምናልባትም በከርማ ራሱን የቻለ መንግሥት በ2600 ቅጋአ አካባቢ የተመሠረተ ይመስላል (ለምሳሌ ቦኔትን 1983ን ይመልከቱ)። የከርማ ስረወ መንግሥት ወይም የከርማ ባህል በአሁኑ ማዕከላዊና ሰሜን ሱዳን ተነስቶ በጊዜ ሒደት እየተስፋፋ ከ2500 እስከ 1500 ባለው ጊዜ ውስጥ የጥንታዊ ግብፅ ደቡብ ጠረፍ እንደደረሰ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉ። የኩሽ ስርወ መንግሥት መነሻ ይህ የከርማ ስርወ መንግሥት ነው። ስለከርማ በርግጠኝነት ብዙ ማለት አይቻልም። በዚች ከተማ እስካሁን የተገኘ ምንም የጽሑፍ ማስረጃ የለም። ከተማዋም በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅድመ ጋራ አቆጣጠር (ቅጋአ) በግብፆች እንዳልነበረች ሆኗ ወድማለች። ስለዚች ከተማና ባጠቃላይ በወቅቱ ስለነበረው የኩሽ/የከርማ ስርወ መንግሥት መረጃ የምናገኘው ከውድመት ከተረፈው ከከተማዋ ፍርሥራሽ እና ከግብፅ ምንጮች ነው።
የመካከለኛው ስርወ መንግሥት መሥራች የሚባለው የ21ኛው መቶ ቅጋአ ዳግማዊ ሜንቱሆተፕ የተከፋፈሉትና የደከሙትን የግብፅ ግዛቶች አንድ በማድረግ ወደጠነከረ ማዕከላዊ ስረወ መንግሥት ማምጣት ብቻ ሳይሆን፣ ከግዛቱ አልፎ በኩሽ ስርወ መንግሥት/በከርማ ስርወ መንግሥት ላይ በሃያ ዘጠነኛውና በሰላሳ አንደኛው የንግሥና ዘመኑ ዘመተ። የግብፅና የኩሽ ስርወ መንግሥታት ግጭት በዳግማዊ ሜንቱሆተፕ አላበቃም። ከዳግማዊ ሜንቱሆተፕ ከአምስት መቶ ዓመት በኋላ የተነሳው ቀዳማዊ ቶተሚስ ተደጋጋሚ ዘመቻ በኩሽ ላይ በማድረግ ወደኋላ ላይ ተሳክቶለት በ1504 ቅጋአ አካባቢ ኩሽን በራሱ ግዛት ስር አደረገ። የኩሽ ስርወ መንግሥት በግብፅ ስር ከመውደቁ በፊት ከ1700 ጀምሮ በጣም እየተጠናከረ መጥቶ ነበር። በ1700 እስከ 1500 ባለው ጊዜ ውስጥ በአካባቢው የነበሩትን ትንንሽ ስርወ መንግሥታት አስገብሮ ድንበር ለማስፋትም ችሎ ነበር።
ኩሽ በ15ኛው መቶ ቅጋአ አካባቢ በግብፅ ስር ብትወድቅም፣ ከሁለት መቶ ዓመት በላይ በዘለቀ ሕዝቡ በግብፅ አገዛዝ ላይ ያምፅ ነበር። ይህ አመፅ ገፍቶ የግብፅ አዲሱ ስረወ መንግሥት በተከፋፈለበትና በደከመበት በ11ኛው መቶ ቅጋአ አካባቢ ኩሽ ራሷን ችላ ነፃ ወጣች (ከብዙ በጥቂቱ አርኬል 1955ን ይመልከቱ)።
ኩሽ ከግብፅ በነበራት ጥንታዊ ንክኪ በተጨማሪ ለአራት መቶ ዓመት ያህል እንደ አንድ የግብፅ አካል ሆና መቆየቷ ከፍተኛ የባህል ተፅዕኖ አሳድሮባታል። በተለይ ናፓታ ከፍተኛ የሥልጣኔና የሃይማኖት ማዕከል ሆና እንድትወጣ አስችሏታል። ናፓታ በሃይማኖት ማዕከልነቷ የግብፅ እምብርት ከመሆንም አልፋ የኩሽ ስረወ መንግሥት መቀመጫም/ዋና ከተማም በ8ኛው መቶ ቅጋአ ለመሆን በቃች። ኩሽ ነፃነቷን ካስመለሰች በኋላ ከ11ኛው መቶ ቅጋአ እስከ 8ኛው ቅጋአ ድረስ ዋና ከተማዋ ከርማ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ ይገመታል። በዚህ ላይ ያለው መረጃ ስስ ነው።
በናፓታ የኩሽ ስረወ መንግሥት የመጀመሪያው ንጉሥ አላራ ነው። በግብፅ ላይ ወረራ በማካሄድ ግብፅን ሊቆጣጠር የሞከረው ንጉሥ ካሻታ የአላራ ወራሽ ነው። ንጉሥ ካሻታ ምንም እንኳ በአንዳንዶች የ25ኛው የግብፅ ስርወ መንግሥት መሥራች ተደርጎ ቢቆጠርም ሙሉ በሙሉ ተሳክቶለት ግብፅ በተራዋ በኩሽ ግዛት ስር እንድትወድቅ ያደረገው ፕዬ ነው። ከዚህ ዘመን ጀምሮ ያለውን የኩሽ ስረወ መንግሥት በሁለት ከፍሎ መመልከቱ የተለመደ ነው። እነዚህም የናፓታን ዘመንና የሜሮኤ ዘመን በመባል ይታወቃሉ። ስያሜያቸው የወጣው የኩሽ ስርወ መንግሥት መቀመጫ ከነበሩት ዋና ከተሞች በመነሳት ነው። የናፓታን ዘመን ከከርማ ማግስት በግልፅ ከሚታወቀው የኩሽ ታሪካዊ ስርወ መንግሥት ምስረታ አንስቶ መቀመጫው ከናፓታን ወደ ሜሮኤ ከተሸጋገረበት 591 ቅጋአ አካባቢ ወይም አንዳንዶች እንደሚሉት 4ኛው መቶ ቅጋአ አካባቢ ያለውን ሲያመለክት የሜሮኤው ደግሞ ከዚህ ዘመን ቀጥሎ የኩሽ ስርወ መንግሥትን ወደ የመጨረሻ መቃብር ከተተው ከሚባለው ከኢዛና ጊዜ፣ አራተኛው ጋአ ድረስ ያለውን ይይዛል። የናፓታ ዘመንን በራሱ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው ኩሽ ገናና ሆኖ መላው ግብፅን ተቆጣጥሮ ከራሱ ግዛት ጋር ደምሮ ያስተዳደረበትን እስከ 654 ቅጋአ አካባቢ ዘመን የሚያካትት ሲሆን፣ ሁለተኛው ከግብፅ ተባሮ የበላይነቱ አክትሞ በጥንቱ ግዛቱ ብቻ የተወሰነበትንና ከዚያም የአስተዳደር ከተማውን ወደሜሮኤ ያዛወረበትን እንደዲክሰን (1964: 123) ከሆነ ከ654 እስከ 591 ቅጋአ ያለውን ጊዜ ያካትታል።
ኩሾች ናፓታ ላይ ሆነው ግብፅን ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን ከግብፅ ግዛት ከተባረሩም በኋላ ዋና ከተማቸውን ወደ ሜሮኤ እስኪዛወሩ ድረስ እዚያው ነበሩ። ኩሾች ግብፅን ተቆጣጥረው የ25ኛው ስርወ መንግሥት በመመሥረት የቆዩበት ዘመን 744 እስከ 656 ቅጋአ አካባቢ ድረስ ነው። ናፓታ ዋና ከተማቸው አድርገው የቆዩበት ዘመን ደግሞ እስከ 538 ቅጋ አካባቢ ይደርሳል። የሜሮኤ ዘመን ከዚህ፣ ማለት 538 ቅጋአ ጀምሮ እስከ 350 ጋአ አካባቢ ያለው ነው። 350 ጋአ ሜሮኤ ሙሉ በሙሉ በኢዛና የወደመችበት ዓመት መሆኑን ልብ ይሏል።
የኩሽ ስርወ መንግሥት ለኢትዮጵያ ድንበር ወደሚቀርበው ወደሜሮኤ ዋና ከተማውን ያዞረው በኢትዮጵያ የዳኣማት ስርወ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ ነው ማለት ነው። በዚህን ወቅት በአሁኒቷ ኢትዮጵያ-ኤርትራም ሆነ በጥንቱ የአክሱምና የዳአማት ስርወ መንግሥታት በሚያካልለው ግዛት የኩሽ ስረወ መንግሥት አልፎ ስለመግዛቱ እስካሁን የሚታወቅ ምንም ማረጋገጫ የለም። በእርግጥ ስለኩሽ ሀገር ስፋት እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። አንድም በየወቅቱ የመጥበብና የመስፋት ሁኔታ ከላይ እንደገለፅንው ስለሚያሳይ ነው። ይሁን እንጂ ኩሽ በተለይ በደቡብና በምዕራብ ያሉትን ጠረፎች ካሳደረባቸው የባህል ተፅዕኖ በመነሳት ግምት መስጠት ይቻላል። በሜሮኤና በአክሱም የነበሩት ስርወ መንግሥታት ስሪት የተለያየ ነው። የኩሹ ሙሉ ዝምድናው/ባህላዊ ተፅዕኖው የግብፁ ሲሆን፣ የኢትዮጵያው ግን ባህር ተሻግሮ ከደቡብ ዓረቢያ ነው። ይህን በተመለከተ ከብዙ በጥቂቱ ሙንሮ ሄይ (1991)ን፣ ባጅ (1928) እና ስርግው ኃብለ ሥላሴ (1972)ን ይመልከቱ። ለተጨማሪ፣ ሌክላንት በዚህ ጉዳይ ላይ የዘረዘረውን ይመልከቱ (ሌክላንት 1981: 283-285)።
ኩሽ ኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ዘልቃ ስለማስተዳደሯ ሳይሆን፣ ይልቁንም ወደኋላ ላይ ሜሮኤ ራሷ በአክሱም አገዛዝ ስር ሳትወድቅ አልቀረችም። ኢዛና በሜሮኤ የነበረውን የኩሽ መንግሥት እንደደመሰሰ ትቶልን ካለፈው የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ይታወቃል። ምናልባትም ኢዛና ወደሜሮኤ ዘምቶ ሊያጠፋት ያስቻለው፣ ግብር አልከፍልም በማለት እያስቸገረች ሊሆን ይችላል።
የኩሽ ነገድና ቋንቋ በጥንታዊው የኩሽ መንግሥት
ኑቢያ የጥንቱን የኩሽ ሀገርና ሥልጣኔ ለማመልከት በስፋት በተለይ በምሁራን ሥራ ላይ ይዘወተራል። ይሁን እንጂ፣ ኑቢያ የሚለው ቃል የመጣው ኖባ ከሚባሉ በሦስተኛው መቶ ጋአ (ጋራ አቆጣጠር) አካባቢ የላይኛው ኑቢያን/ኩሽን ወረው ከነበሩ (በወቅቱ) ዘላን ሕዝቦች ነው። እነዚህ ሕዝቦች ሮማኖች ኖባቲያ ይሏቸው ነበር። ኑቢያ ከኖባቲያ በሒደት የተገኘ ነው። ቃሉ መጀመሪያ ተጠቅሶ የሚገኘው ኖባዎች ኩሽን ከወረሩበት ከ600 አመት በፊት ጀምሮ ነው። ኖባቲያ በፕሊኒ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ሥራ ተጠቅሶ ይገኛል። ፕሊኒ የጠቀስውን ሥራ ከያዝን 3ኛው መቶ ቅጋአ ይሄዳል (ለእንግሊዝኛ ትርጉም ራክሃም 1942፡480ን እና ኤዲ እና ሌሎች 1996፡548ን ይመልከቱ)።
ኑቢያኖች በኩሽ ስርወ መንግሥት ስር ቢኖሩም የኩሽ ስርወ መንግሥት በተለዋጭ የኑብያ ስርወ መንግሥት እየተባለ ቢጠራም፣ እነዚህ ሕዝቦች ግን ከኩሾች የተለዩ ናቸው። የኖባ/ኑብ ሕዝቦች በዚሁ ስያሜ እየተጠሩ አሁንም በግብፅና በሱዳን አሉ። በሱዳን እነዚህ ሕዝቦች 15 በመቶ እንደሆኑ ይነገራል። ቋንቋቸውም የአባይሰሀራዊ ወገን ነው። ጥንታዊ የሥልጣኔው ባለቤት ኩሾች ግን በአሁኑ ጊዜ ራሱን በቻለ ብሔረሰብ አይታወቁም። የኑቢያን ሕዝቦች ቋንቋ ከኩሾች ቋንቋ ጋር ግን የተለየ ነው። የኩሾች ቋንቋ በሜሮኤ የተገኘው ነው ተብሎ ይታሰባል። በናፓታና ሜሮኤ ከተሞች የነበሩት ሕዝቦች የተለያዩ ተደርገው አይወሰዱም። እነዚህ ሕዝቦች ኩሾች ናቸው።
የሜሮቲክ ቋንቋ እስካሁን ሁሉም የተስማማበት የዘር ምደባ የለውም። በተወሰኑ ሥራዎች የአፍሮኤስያዊ ቋንቋ አካል ተደርጎ ሲቆጠር፣ በአንዳንድ ሥራዎች ደግሞ በኒሎሰሃራን ታላቅ የቋንቋ ቤተሰብ ስር የምሥራቅ ሱዳኒክ ቋንቋ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለ። የኋለኛውን በተለይ ራይሊ (2004) አጥብቆ ይገፋበታል። ይሁን እንጂ፣ የሜሮቲክ ቋንቋ ወገኑ ከዚህ ነው ለማለት የሚያስችል በቂ መረጃ እስካሁን አልተገኘም።
ስለኩሽ ሕዝቦች ማንነት የተለያየ፣ አንዳንዴም ተቃራኒ አስተያየት ይገኛል። በጥንታዊ ግብፆች ዕይታ ኑቢያኖች/ኖባዎች በመልክ ከእነሱ ጠቆር ቢሉም በተክለ ሰውነታቸው ግን አንድ ናቸው። እንደአዳም ከሆነ ኩሾች ግን በመልክ ብቻ ሳይሆን በሰውነት ቅርፅም ከኑቢያኖችና ከግብፆች የተለዩ ናቸው (አዳም 1981፡231)። የኩሾች ተክለ ሰውነት የማዕከላዊና ምዕራብ አፍሪካን ይመስላል።
ኩሾች ከኑቢያኖችና ከግብፆች በተለይ የምዕራብ አፍሪካን ሰዎች ይመስላሉ የሚለውን የአዳምን ትንታኔ ለመቀበል አስቸጋሪ ነው። አንደኛ፣ የምዕራብ አፍሪካን ተክለ ሰውነት የሚመስሉ ስዕሎችና ቅርፆች መገኘታቸው እውነት ቢሆንም፣ ይህ የኩሽን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ለመግለፅ አይበቃም። በግብፅም የምዕራብ አፍሪካ ሰዎችን የመሰሉ የጥንታዊ ግብፃውያን ምስሎች አሉ። እንደዚህ ዓይነቱን ብቻ በመያዝ ጥንታዊ ግብፆች የምዕራብ አፍሪካን ይመስላሉ ማለቱ አሳማኝ አይደለም። ምክንያቱም በርካታዎቹ ቅርፃ ቅርፆችና ስዕሎች የሚያሳዩት ከዚህ የተለየ ነውና። በኩሾችም ያለው ሁኔታ ይኸው ነው። ጥንታዊ ግብፆችም ሆኑ ኩሾች በትክለ ሰውነት ደረጃ በበርካታ ቅርፆች እንደሚታየው ልዩነት የላቸውም። በሰርቪስ (1998) እና ሌሎች በርካታ ሥራዎች ላይ የቀረበውም ይህንኑ የሚያስረግጥ ከአዳም የተለየ ሐሳብ ነው። ለምሳሌ የኩሽ ሕዝቦች የአሁኒቷን ሰሜን ሱዳን ሕዝቦች እንደሚመስሉ፣ ከተዉልን የግርግዳ ላይ ስዕሎችና ቅርፃ ቅርፆች/ሐውልቶች እንዲሁም ከጥንታዊ ኩሾች ቅሪተ አካል የሥነሰብ ጥናት እንዳረጋገጠው የሰሜን ሱዳን ሕዝቦች ጋር አንድ ናቸው (ሰርቪስ 1998: 56)። በእርግጥ ኩሾች ከጥንታዊ ግብፆች ምናልባት ትንሽ ጠቆር ያሉ ሊሆን ይችላል። ብሬየር ቪችልን በመጥቀስ የሚከተለውን ይላል፣ ‹‹ዓረብኛ ተናጋሪ የሆኑ በግብፅ የሚገኙ የቤጃ ሰዎች/ቡድን አሁንም ጠቆር ያለ ቆዳ ያለውን ሕዝብ ኪሻብ ይላሉ (ብ በኪሻብ ላይ ያለችው ተባእታይ ተሳቢ አመልካች ነች)” (ብሬየር 2007:459)። በ1820 ቅጋአ በማለፊያ/መግቢያ መፅሀፍ ‘ቡክ ኦፍ ጌትስ’ የነገዶች ምስል ላይ ኩሽ የቀረበው ከሌሎቹ ጥቁር ሆኖ ነው።
ኩሽን ከጥቁረት ጋር ማያያዝ የመጣውም እንዲያም ራሳቸው ኩሾች ከግብፆች በተለይ ጠቆር ስለሚሉ ወይም በሚያስተዳድሩዋቸው ሕዝቦች መካከል ሌሎች ጠቆር የሚሉ ኖረው ሊሆን ይችላል። ግሪኮች ኩሾችን ለመግለፅ ኢትዮጵያ የሚለውን የተጠቀሙበት ለዚህ ሊሆን ይችላል። በቀጣዩ ክፍል እንደምንመለከተው ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ኩሽ የሚለው ስም በአብዛኛው በግሪክ ኢትዮጵያ በሚል ተተክቶ ይገኛል።
ምናልባት ከሦስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የኑቢያኖች/ኖባዎች የበላይነት እያገኙ መምጣት፣ ከዚያም የእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት የተለየ የዓረብ ማንነትን እያላበሰ የኩሽ ማንነት ሊጠፋ እንደቻለ መገመት ይቻላል። “በአሁኑ ጊዜ 70 በመቶ ያህሉ የሱዳን ሕዝብ ዓረብ ነኝ ወይም የዓረብ ዝርያ አለኝ ይላል። ከእነዚህ ጃአልዪን፣ ሻይጊያ እና ማናሴር ይገኙበታል። በእነዚህ 70 በመቶ ዓረብ ነን በሚሉ ሱዳኖችና በኑቢያኖች መካከል ያለው ዋና ልዩነት ቋንቋ ነው። ኑቢያኖች የጥንቱን ኑቢያን የሚባለውን ቋንቋ ሲናገሩ፣ ሌሎቹ ዓረብኛን ይናገራሉ።
ኑቢያኖችም አሁንም ማንነታቸውን ሳያጠፉ በመኖራቸው፣ የዓረብ ማንነት የወሰዱት ኩሾች ናቸው ብሎ መገመት ይቻላል። ይህ ግን ኑቢያን ማንነትን የወሰዱ ኩሾች ሊኖሩ አይችሉም ማለት አይደለም። ሕዝቡ ከነበረው ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት የተነሳ የተቀላቀሉ እንዳሉ መገመት ስህተት ሊሆን አይችልም። በአሁኑ ጊዜ ዓረብ ነኝ በሚለውና በኑብያኖች መካከል በመልክም ሆነ በአጠቃላይ በሰውነት/በአካል መለየት አይቻልም። ስለዚህ ዓረብ ነን የሚለው ሱዳናዊ ከቋንቋ የዘለለ የደም ትስስር ከዓረቦች ጋር እንደሌለው መገመት ይቻላል። ከዚህ በፊት የወጡ ሥራዎችም በእርግጥ ይህንኑ አስረግጠው ብለውታል። የኩሾች ጉዳይ ከአግዐዝያን/ግዕዝ ተናጋሪዎች ጋር ተመሳሳይ ነው። ዛሬ የጥንታዊ አክሱም መሥራች የሚባሉት ግዕዝ ተናጋሪ የነበሩት በሌላው ተውጠው የተለየ የነገድ ማንነት የላቸውም።
ከአዘጋጁ፡- ግርማ አውግቸው ደመቀ፣ የሥነልሳን እና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ባለሙያ ናቸው። የምርምር ትኩረታቸው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ታሪክና ሥነመዋቅር ላይ ነው። በቅርቡ በእንግሊዝኛ ካሳተሟቸው መጽሐፎች መካከል የአማርኛ ጥንተ አመጣጥ—ሁለተኛ እትም (2013)፣ ሰዋስዋዊ ለውጥ በሴሜቲክ—የአማርኛ ሰዋስው በዘመን ሒደት (2014)፣ እና የአርጎባ ንግግር ዓይነቶች/ቋንቋዎች (2015) ይገኙባቸዋል።