መንግሥታትና መሪዎች አገርን ለመገንባት ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል ረቂቅ ወይም ተምሳሌታዊ (ሲምቦሊክ) ጉዳዮች ውስጥ አገራዊ ትርክቶችና የጋራ ትውስታዎች ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ ውስጥ ደግሞ ታሪክ አለ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ማኅበራዊ ቅራኔዎችንና የታሪክ ጠባሳዎች እየተለቀሙ አቃቃሪና ግጭት ጠሪ ትረካዎች (በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጭምር) በቆስቋሾች እየተደረቱና እየተወረወሩ ለቁርሾ ማወራረጃና ለሥልጣን ሸኩቻ መሣሪያ እየተደረገ በመሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክ ለአገረ መንግሥት ግንባታ ያለው ተፅዕኖ አነጋጋሪነቱ እየጐላ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያለው ክርክር& እስጥ አገባና እንዲያም ሲል መማማርና መደማመጥ በራቀው ድባብ በልሂቃን መካከል ሳይቀር ወዝግቡ ቀጥሏል፡፡ በታሪካችን ላይ ልዩነት እየሰፋና አንዳንዴም እየተካረረ በመሄዱና ታሪክ በተለይ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉልህ ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል ችግሮቹና መፍትሔዎቹ ላይ ባተኮረ መልኩ የሚከተሉትን ጉዳዮች ለመግለፅ ወድጃለሁ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ታሪክ ያለፉትን ተከታታይ ትውልዶች ከዛሬውና ከወደፊት ትውልዶች ጋር የሚያገናኝ& የሚያስተዋወቅና የሚያስተሳስር ሰንሰለት ነው፡፡ ታሪክ የታሪክ ጠባሳዎች መደገም እንደሌለባቸው የሚያስገነዝበንና ትምህርት የምንቀስምበት& በምንኖርበት ዘመን ላይ ያሉንን ጥያቄዎችንና ችግሮቻችንን መፍቻ ቁልፍ ዋቢ መረጃችን ነው፡፡ ያለፈውን በማብራራት ለወደፊቱም የአገርና የዜጐች ዕጣ ፈንታ ፋና የሚሆን ዕውቀት የሚሰጥበት ዘርፍ ነው፡፡
የታሪክ ባለሙያ ከግራ ከቀኝ ያገኘውን ማስረጃ መዝኖ አመሳክሮ ፍርድ የሚሰጥ ባለአደራ ነው፡፡ የሚሰጠው ፍርድ ግን ከማስረጃዎቹ የሚመነጭና ሚዛናዊ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሲሆን የጐደለው ይሟላል& የተዛነፈው ይቃናል& የተጣረሰው እየተነቀሰ ይታረማል& ድክመቶችም ይመላከታሉ& ጥንካሬዎች ይዘረዘራሉ& ልዩነትና ተመሳሳይነትም ይመዘገባሉ& በየጊዜው የተከሰቱ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ይገለፃሉ& መስተጋብሮች ይተነተናሉ& ተወራራሽነትም ይንፀባረቃል& የጋራ እሴቶች ይጎላሉ& የትምህርት ገበታነቱ ይደምቃል& ስር መሠረትንም ያጠናክራል& ከታሪክ መታረቅንና ብሔራዊ ተመልካችነትን ያዳብራል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝቦችና ብሔሮች የጋራ ወደፊትን ያስተሳስራል& ያስተባብራል፡፡
በማስረጃ ላይ በመመሥረት የታሪክ ጠባሳዎችንም ሆነ ዘመን ተሻጋሪ የጋራ ትውስታዎችን (Shared memories) መተረክ ይቻላል፡፡ የታሪክ ጠባሳዎች ትርክትን አስመልክቶ የሁነቶች ጠባሳ ያልታተመበት አንድም ኅብረተሰብ የለም የሚለው እውነታ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ታሪካችንን በዚህ መንፈስ ብንመለከተው ከኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ውስጥ ሺሕ የታሪክ ጠባሳዎችን መደርደር ይቻላል፡፡ የታሪክ ጠባሳዎችንና በደሎችን የማቅረብ ዓላማ የለኝም፡፡ መዘርዘሩም ተገቢ አይመስለኝም፡፡ መታወቅ ያለበት ግን አሉ የሚባሉ የታሪክ ጠባሳዎች በተገቢ የሚያዙ የጋራ ታሪካችን ትውስታዎችና ልንማርባቸው የሚገቡ እንጂ ደም አቃቢ መሆን የለባቸውም፡፡ የታሪክ ጠባሳዎች ቆጠራ ላይ በማትኮር የአባት ዕዳ ለልጅ በሚል በእገሌና እገሌ ዘመን ደረስ የሚባሉ የታሪክ ጠባሳዎች እየተለቀሙ ለፖለቲካ ግብ መቀስቀሻና ማነሳሻ እንዲሆኑ በማድረግ የዛሬ መናቆሪያዎችና የግጭት መነሻዎች መሆን የለባቸውም፡፡
በአንፃሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ያስተሳሰሩና የጋራ ምንነታችንን ማንነታችንን በረዥሙ የታሪካችን ዘመን የጋራ ትውስታዎች ዐበይት ክንዋኔዎች ላይ ትኩረት ቢደረግ አገረ መንግሥት ግንባታችን ፈርጥሞ የጋራ የወደፊት ማገር ጠንክሮ ይቆማል፡፡ ኢትዮጵያዊነትም ያብባል፡፡ በዚህ ረገድ በሺሕ ዘመናት የታሪክ መስተጋብሮች የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ማንነት ካበጁት ሺሕ የጋራ ትውስታዎች መካከል የኢትዮጵያ ታሪክ በከፍተኛ የሕዝቦች መደበላላቅ ላይ እንደተመሠረተ በርካታ ባህሎች ተቀራርበውና ተወራርሰው እንደኖሩ& ሁሉ አቀፍ ማኅበራዊ& ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች እንደነበሩ& የኢትዮጵያ ሁሉም ሕዝቦች ገደብ የለሽ መስዋዕትነት ለአገራቸው ነፃነት ስለመክፈላቸው እንዲሁም በውጭ ፖሊሲም ለፓን አፍሪካኒዝምና ለአፍሪካ ኅብረት መመሥረት የተደረጉ ሁሉ የጋራ ዘመን ተሻጋሪ ክንዋኔዎችና ሕዝቦች ሁሉ አሻራቸውን ያሳረፋበት ተከታታይ& ተያያዥና የለውጥ የጋራ ታሪክ ክንዋኔዎችን መሆናቸውንና ቀጣይ የአገራችን ዕድሏም መልካም ዕድላችን አድርገን ወደፊት ለመመልከት እንችል ዘንድ የሚያጠነጥን ታሪክ ቢጻፍ& ቢነገር ለትምህርት ቢውል ተመራጭ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ልሂቃንና የታሪክ ምሁራንም ከፖለቲካ ማኅበራዊ ቅራኔዎችና ከታሪክ ጠባሳ ሁነቶች ትረካ ይልቅ የትናንቱ መልካም ሁነት የዛሬው& በነገው ላይ ያሳረፈውንና የሚያሳረፈውን የዘመናት የታሪክ ማህተም አበጥሮ አውጥቶ የመጻፍና የማስተማር ግዴታቸውን መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃርም የታሪካችንን ክንዋኔ& ሒደት& ተከታታይነትና ተያያዥነትን በሚያሳይ የሁሉንም ድርሻና አሻራ በሚያጐላ መንገድ ሊቀርብ ይገባል፡፡ በሌላ አገላለጽ ለማወደስ ብሎ ማወደስ ለመውቀስ ብሎ መወቀስ አይደለም የነገውን ሁኔታ ለማነፅ፣ ወይም ለመቅረፅ አስተሳሰብ መጐልበት አለበት፡፡ የኢትዮጽያ ፖለቲካ ማኅበራዊ ዓብይ ቅራኔዎች ቅሪቶችና የታሪክ ጠባሳዎች በዛሬው ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ መፍጠራቸው የማይቀር ሆኖ ማለት ነው፡፡
በአገራችን የታሪክ ይዘት ላይ የተራራቀ አቋም መያዝስ ችግሮቹ ምንድን ናቸው? የኢትዮጵያ የታሪክ ሒደት ከሌላው ዓለም ምን የመረረ ጐልዳፋ ነገር አለው? የሚሉትን ጥያቄዎችን ስመለከታቸው መልስ ሊሆን የሚችሉት አንደኛ እውነታን በመሻት ታሪክን በምሁራዊ ሀቀኝነትና በትክክል አጥንቶ የማቅረብ ጉድለት ሊሆን ይችላል፡፡ እርግጥ ይህ ችግር በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም በሰፊው ይስተዋላል፡፡
ሁለተኛው ታሪክ በባህሪው ለሁሉም ክፍት በመሆኑ በተገኘው አጋጣሚ እጅ በፈታና አፍ ባፈተተ የዘርÕን ዲስÝሊን ሳይጠበቅ በመጻፉና በመነገሩ የተነሳ የታሪክ እውነታዎች እየተጣመሙ፣ በስክነትና ሆደ ሰፊነት ይልቅ ስሜታዊነት ባጠላበት መልኩ በመተረካቸው የተነሳ የተፈጠረ መደናገር ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ሁኔታ እየቀጠለ በመምጣቱ ምክንያትም የሚቀርቡት መጻሕፍትና መጣጥፎችም በሚያተኩሩበት ጉዳይ ላይ የተሟላና በቂ የማስረጃ ድጋፍ ሳይኖራቸው ትርጉም የሚሰጡበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ የሚሰጡትም ትርጉም ከአስተማማኝ የታሪክ ሰነዶችና ተዋናዮች ሳይሆን አካዴሚያዊ ደረጃቸውን ካልጠበቁ ምንጮች ላይ በመመርኮዝ ታሪክን የፖለቲካ ወይም ለሌላ የግል ተዛማጅ ዓላማ ማስፈጸሚያ ለማድረግ በዘፈቀደ ታሪክን የመተርጐም አካሄድ እየታየ መጥቷል፡፡ የዚህ ውጤትም ታሪክ በተከናወነበት ዘመንና ይዞታ አውጥቶ አዲስ የታሪክ ትርጉም በመስጠት ለፖለቲካ መሣሪያ ወይም የግል አጀንዳ ማጠንጠኛ የማድረግ ሁኔታ ይከስታል፡፡ እንደሚታወቀው ታሪክ በመሠረቱ የፖለቲካ ባህሪ አለው፡፡ የዛሬ ፖለቲካ የነገ ታሪክ ነው፣ ያለፈ ታሪክም ቢሆን ለአሁን ፖለቲካ እንደ ምርኩዝነት ማገልገሉ አይቀርም፡፡ ቁምነገሩ ታሪክ ከፖለቲካ ተነጥሎ የማይታይ ቢሆንም ቅሉ ፖለቲካ ውስጥ በመወሸቁ ምክንያት ሀቅን በጠበቀ መልኩ ለአገረ መንግሥት ግንባታ ለዜጐች ማስተማሪያ ሳይሆን ቀርቶ የተፈጠረ መደነጋገር እንደ ችግር ሊታይ ይችላል፡፡
Sስተኛው ችግር እ.ኤ.አ ከ1980ዎቹ ዓመታት ወዲህ ተጠናክሮ የመጣው የድህረ ዘመናዊነት (Post Modernist) አመለካከት ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ዋናው ማጠንጠኛ ታሪክን በጥርጣሬ ማዕቀፍ አብዝቶ በማየት በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ዓብይ ሚና ማሳነስ ነው፡፡ የዚህ ልዩነት የጣለው ጥላ በሀቀኛ ምሁራን ጥናትና በልበ ወለድ መካከል ያለውን ልዩነት እስከ መጋረድ ደርሷል፡፡ ስለዚህ በእኔ ግምት ታሪክን የማዳከም አዝማሚያ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ በአገራችንም በዩኒቨርሲቲ እንደ አንድ የሙያ መስክ እንጂ ለማንኛውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በጋራ ትምህርትነት (ኮመን ኮርስነት) እንዳይሰጥ የማድረግ ሁኔታም ታሪክን ከማዳከም አዝማሚያ ጋር ሊያያዘ ይችላል፡፡ እርግጥ ይህ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ታርሟል፡፡ ከአንደኛ ዓመት የጋራ ኮርሶች ውስጥ አንዱ የታሪክ ትምህርት ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክና ትርክትን ለአገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ለማዋል የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት መወሰድ ካለባቸው መፍትሔዎች ውስጥ የአሜሪካን ሁኔታ መጥቀስ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአሜሪካ የታሪክ ማኅበር (American Historical Association) የመተዳደሪያ ቻርተር በማርቀቅ ለመሥራች አባሎቹ የአሜሪካን ታሪክ በጥንቃቄ እንዲይዙና በታሪክ ላይ የሚሠራውን ስህተትና ተፋልሶ እንዲመረምሩ ሥልጣን ሰጣቸው፡፡ ይህ ማኅበር ይህንን ተግባሩን እስከ አሁንም በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ የምንማረው ዋናው ቁም ነገር በኢትዮጵያም ውስጥ ቢሆን በታሪክ ላይ እየተስተዋለ ያለውን መጣረስ እያጣራና እየተፈተሸ የሚሄድ ሥርዓት መዘርጋት፣ አደረጃጀትም መፍጠር (የኢትዮጵያን የታሪክ ማኅበር ማዋቀር) ያስፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያ የታሪክ ማኅበር ተቋቋሞ የታሪክ ተፋልሶ ያዘሉና በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ግርታን የሚረጩ ሐሳቦችን በያዙ መጻሕፍት ላይ ማኅበሩ ወዲያውኑ ትምህርታዊ ዕርምትና ማስተካከያ በመስጠት የዓቃቤ ታሪክነት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ የታሪክ ትምህርት ለአገረ መንግሥት ግንባታ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑም ወጣት ተማሪዎች የተሟላና ጥራት ያለው የታሪክ ትምህርት ሊቀርብላቸው ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃርም አንጋፋዎቹ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ& ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ዲላ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ዝግጅት ልዩ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የታሪክ ክበባት እንዲቋቋሙ ቢደረግና ክበባቱም በየወቅቱ ከሚነሱ የፖለቲካ ትኩሳቶች ነፃ ሆነው አገራዊ የታሪክ ውይይቶችና የመረጃ ልውውጦች የሚከናወኑበት መድረክ ቢሆኑ& በዘርፉ ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆኑ አስተማማኘ መጻሕፍት በአማርኛም ከተቻለም በሌላ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ቢቀርቡ& ከልሂቃን ብቻ ሳይሆን መንግሥት& ዜጐችና የተለያዩ ተቋማት ሳይቀሩ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ቢችሉ ስኬት ይኖረዋል፡፡ በመጨረሻም ታሪክን ለቅንጦት በፈለጋቸው መንገድ የሚያብራሩ ልሂቃንና ታሪክን በፈለጉት መንገድ የሚጠመዝዙት ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የሚያንፀባርቁት የታሪክ ህፀፆች በባለሙያ እንዲመረመሩና እንዲታይዩ ቢደርጉ መልካም ነው፡፡ እነዚህ ከላይ የተገለጹት የመፍትሔ ሐሳቦችን ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ ታሪክ አገረ መንግሥትን ያደረጃል ያፀናል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በውጭ ፖሊሲና ዲÝሎማሲ ሁለተኛ ዲግሪ በተጨማሪም በመልቲ ካልቸራሊዝም ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡ መጣጥፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡