ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች የተፈጠረው ሕዝባዊ አመፅና አለመረጋጋትን ተከትሎ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር በአንዳንድ እንግዳ ንግግሮች፣ አቋሞችና አመለካከቶች የተሞላ መሆኑን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን የያዙ ሰሞን ቃል የገቧቸው ነገሮች ለብዙዎች ተስፋ ያሰነቁ ቢሆንም፣ ተስፋው ሙሉ በሙሉ ሊፈጸም አልቻለም ፡፡ በሌላ በኩል በርካታ ተፃራሪ ቡድኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል ሊፈጽሙ አለመቻላቸውንና ሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያቶች መነሻ በማድረግ ባደረጉት እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሆነ የድጋፍ መሠረት በማግኘት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነበራቸው ቅቡልነት ላይ የራሱን ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡
በተለይ የገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አባል የነበሩት አራት ፓርቲዎች፤ በተለያየ የፖለቲካ አቅጣጫ መጓዝና በመሀላቸው የነበረው መለያየት መጠኑ እየሰፋ መምጣቱ፤ በአጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ላይ አዳዲስ አመለካከቶች እንዲታዩ መንገድ ከፍቷል፡፡
የኢሕአዴግ መክሰምና የብልፅግና ፓርቲ መመሥረት ደግሞ በሕወሓትና በሌሎች የድርጅቱ አባል ፓርቲዎች መሀል ሊታረቅ የማይችል ልዩነት መፍጡሩን መታዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር ሕወሓት የፌዴራል ሥርዓቱንና ሕገ መንግሥቱን ከአደጋ መታደግን ያለመ አገር አቀፍ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ኮንፈረንስ ያዘጋጀ ሲሆን፣ በእነዚህ መድረኮችም አራት ኪሎ ያለው ኃይል አገር ሊያፈርስ እንደሆነና አሃዳዊ ሥርዓትን ሊያቆም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመገግለጽ ትችት ሰንዝሯል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የሕወሓትን ስሞታ የሚቃወሙ በርካቶች ሲሆኑ፣ አጋር ድርጅቶችን አንድ ላይ መሰብሰብና ኢሕአዴግን አንድ አገራዊ ፓርቲ ማድረግ ችግሩ ምኑ ላይ ነው? የአሃዳዊ ሥርዓት መገለጫ የሚሆነው ምኑ ነው? በማለት የሚሞግቱ ሲሆን፣ የሥጋቱ ምንጭ ሥልጣንን የመቆጣጠር አባዜ ካልሆነ በስተቀር የአሃዳዊ ሥርዓት መገለጫዎች የሚያሳይ አንድም ነገር እንደሌለ በመግለጽ ስሞታውን ያጣጥሉታል፡፡
በሌላ በኩል የተለያዩ ኮንፈረንሶችን በመቐለ እያደረገ የሚገኘው ሕወሓትን፤በርካቶች የፌዴራሊስት ኃይል እያሉ የሚጠሩት በርካቶች ናቸው፡፡ ሕወሓት እየተከተለው ያለው ስርዓት የፌዴራሊዝም ሳይሆን የኮንፌዴራሊዝም ስርዓት ነው በማለትም ይተቹታል፡፡ ለዚህም እንደ መከራከሪያ የሚያነሱት ፓርቲው በተለያዩ አጋጣሚዎች ራሱን የማስተዳደር መብትም ሥልጣንም እንዳለው እየገለጸ መሆኑንና የፌዴራል ሥርዓቱን ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል የሚል ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፣ ‹‹እውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት እንገነባለን፣ የፌዴራሊስት ኃይሎች›› ወዘተ የሚሉ ቃላት በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየተሰነዘሩ ነው፡፡ሆኖም በዋነኛነት የፌዴራሊስት ኃይሎች ነን የሚሉት የፖለቲካ ድርጅቶች መሠረታዊ የፌዴራሊዝም ምሰሶ የሆነውን፤ “በልዩነት ውስጥ ያለንን አንድነት ለመተግበርና ለማስፈጸም ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?” የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ አልተገኘም፡፡
ፖለቲከኞቹም ሆኑ የአገሪቱ ልሂቃን በተካረረው የብሔር ፖለቲካ አማካይነት የሚያቀርቡት ትንታኔም ሆነ የሚይዙት አቋም ቅድሚያ ‹‹የእኔን›› የሚል እንጂ፤ “በጋራ ሆነን ‹‹የእኛን›› ማንነት ባስጠበቀ መልኩ እንዴት የጋራ አገር የመገንባት ሒደቱን እናፋጥን?” የሚለውን ጥሬ ሀቅ ወደ ጎን ለማድረግ በብሔር ፖለቲካ መጠላለፍ ውስጥ ለመዳከር ምክንያት ሆኗል፡፡
የፌደራሊዝም ስርዓት ምንም እንኳን ለአገራችን የፖለቲካ ባህል ሩቅ ቢሆንም፣ በአሜሪካ የፌዴራሊስቶች ንቅናቄና ህቡዕ እንቅስቃሴ አገሪቱ አሁን ላለችበት ደረጃ እንዳደረሳት የተለያዩ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡በተለይ የፌዴራሊዝም ሥርዓት መከተልና ተከትሎ በክልሎች (States) መሀል ያለውን ግንኙነት ምን መምሰል አለበት?፤ የሕዝቦች ውክልና እንዴት ይሆናል?፣ ብሔራዊ የሀብት ክፍፍሉ እንዴት ያለ ይሁን? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው የአገሪቱን አቅጣጫ የጠቆመ ሲሆን፣ አሁን ድረስ የተገነባው ሥርዓት ምሳሌ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
አልጋ በአልጋ ያልነበረው የሥርዓቱ ግንባታ ላይ በተለይ፣ ‹‹The Federalist Papers›› በሚል የብዕር ስም ሲጽፉ ከነበሩ አሜሪካውያን መካከል በተለይ አሌክሳንደር ሀሚልተንና ጓደኞቹ፤ የአገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት ምን መምሰል እንደሚኖርበትና የሁሉም የሆነች አሜሪካንን እንዴት መገንባት እንደሚገባ በመጻፍ፤ አካሄዱን ቅርፅ በማስያዝ ታሪክም፤ አሜሪካውያንም የማይረሷቸው ባለውለታ ሆነው ዘልቀዋል፡፡እነዚህ ቡድኖች የፌዴራሊስት ኃይል ተብለው የሚጠሩ የነበሩ ሲሆን፣ ዓላማቸውም እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት እንዲገነባ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው፡፡
በዚህ ማንፀባረቂያነት ስንመለከተው በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ የሚገኙት ‹‹የፌዴራሊስት ኃይሎች›› ወጥ የሆነ፤ሁሉንም በእኩልነት የሚመለከትና የሚያስተናግድ የፌዴራል ሥርዓት መገንባት ወይስ በሕዝቦች ስም ሥልጣንን መቆናጠጥ የሚለው ጥያቄ ሁነኛ ምላሽ የሚሻ አጀንዳ ቢሆንም በሃገሪቱ እውቅና ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች፤ሰላምና ዴሞክራሲ ፈላጊው ሕዝብ የሚፈልገውን ሳይሆን የየራሳቸውን የፖለቲካ ፍልስፍና ወይም ትንተና እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ሕወሀትና በኦሮሚያ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት ኦፌኮ የፖለቲካ ድርጅቶች “የምናራምደው የፌደራል ስርዓት ነው” ቢሉም፤ ሌሎች የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮች ደግሞ “አይደለም፤ እያራመዱት ያለው ስርዓት የኮንፌደሬሽን ስርዓት ነው እያሉ ነው”፡፡ ስለሁለቱም የፖለቲካ ስርዓቶችና ትክክለኛ መካሄጃው ቀን ስላልተቆረጠለት ሀገራአቀፍ ምርጫ የኦፌኮና መድረክ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና(ፕሮፌሰር) አነደሚናገሩት፤ ስለፌዴራሊስቶች፤ ኮንፌዴራሊስቶችና የምርጫ ተግዳሮት ብዙ ነገሮች ይወራሉ፡፡ በተግባርም የታዩ ነገሮች አሉ፡፡ የፌዴራል የፀጥታ አስከባሪዎችን፣ የክልሎች የፀጥታ አስከባሪዎች ድንበር አልፈው እንዳይሠሩ የሚከለክሉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፣ ኢንቨስተሮችም እየተቸገሩ ነው፡፡ ተማሪዎች በተመደቡበት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መማር አልቻሉም፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ተጠያቂው መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም የሚፈጸሙ እኩይ ተግባራትን መቆጣጠር ሲገባው፣ እያስተባበለ ነው፡፡ ነገር ግን በዩኒቨርሲቲዎች ቅጥር ግቢ የስለት መሣሪያ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን፣ ከመንገድ ላይ ጠልፎ የሚወስደውን በቁጥጥር ሥር አውሎ የማንን ዓላማ እያስፈጸመ እንደሆነና ማን እንደላከው በግልጽ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መንገርና ችግሩን በትብብር መቅረፍ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰውን በስለት መሣሪያ ወግቶ መግደል ‹‹ሱስ›› ሳይሆን ‹‹ተልዕኮ›› ስለሚሆን፣ ተልዕኮው ከየት እንደመጣና ማን እየደገፈው እንደሆነ (በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ኃይል) ለማወቅ መንግሥት መረጃ የለውም ብሎ ባይገመትም፣ አጉል በሆነ የፖለቲካ ጨዋታ እየተፈራሩና ማን ‹‹ቡዳ›› እንደሆነም እየታወቀ ማለፉ ወደማይወጡት ማጥ ውስጥ መግባትን ሊያስከትል ስለሚችል ቆም ብሎ በማሰብ ማስተካከሉ አማራጭ እንዳለው አክለዋል፡፡ ሕወሓትም ቢሆን ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አድርጎ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲፈጠር መግፋት እንጂ፣ አንድ ቦታ ላይ መሽጎ የሚያደርጋቸው ነገሮች ራሱንም ሆነ ኢትዮጵያን የሚጠቅም አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ትግራይም ሆነ የትኛውም ክልል ‹ደሴት› መሆን አይችልም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ፣ ‹‹እንደ አገር አብሮ የሚያሻግር ወይም አብሮ የሚያሰምጥ›› መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በጎ በጎውን በማሰብና ተባብሮ በመሥራት አብሮ መሻገሩ መልካም ነው፡፡ በኦሮሚያ አካባቢ ተፎካካሪ ፓርቲዎች (መድረክ) ብዙ ነገር መሥራት ቢችሉም፣ ገዥው ፓርቲ ግን ብቻውን ብዙ ነገር ለመሥራት ስለሚሞክር፣ በክልሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው የሚባሉ ኃይሎች፣ ሕዝቡ ሊሰማቸው የሚችሉና ወጣቱ በቀላሉ የሚታዘዝላቸው ቢኖሩም ያንን ማድረግ አልቻሉም፡፡ ይኼ ትልቅ ክፍተት ነው፡፡ መንግሥት ከላይ እየወሰነ ወደ ታች ለማስተላለፍ የሚሞክራቸው ነገሮች በሥራ ላይ እንዲውሉ የሚፈልግ አይመስልም፡፡ በብዙ ቦታዎች ሕዝቡ፣ ‹‹ለውጡ እዚህ አልደረሰም፤›› እያለ ነው፡፡ አንዱ ክልል ሌባ የነበረውን ወደ ሌላ ክልል፣ አንዱ ወረዳ ሌባ የነበረውን ወደ ሌላ ወረዳ፣ ወዘተ አዘዋውሮ መሾም ሳይሆን፣ ሁሉም የየድርሻውን በአግባቡና በመናበብ ቢሠራ ሕዝቡ ማን ምን እንደሆነ በቀላሉ መለየት እንደሚችልና መሪውን ያለ ምንም ጥርጣሬ ሊመርጥ እንደሚችልም አክለዋል፡፡ አለበለዚያ ችግሮች እየጨመሩና እየተስፋፉ ስለሚሄዱ አንዱ ፌዴራሊስት፣ ሌላው ኮንፌዴራሊስት፣ ሌላው ደግሞ የዜጎች ፖለቲካ፣ ወዘተ እያሉ መያዣ መጨበጫ ወደ ሌለው ቀውስ ውስጥ መግባትን ያስከትላል፡፡ የሁሉም መንገድ የመንግሥተ ሰማያት ማስገቢያ መንገድ ስላልሆነ፣ ተቀራርቦና ተስማምቶ መሥራት ለሁሉም እንደሚበጅ መረራ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡ ኮንፌዴራል ኃይሎች የሚል ነገር በመገናኛ ብዙኃን የሚራገብ ቢሆንም፣ ‹‹ያልታሰበ ነገር ማሳሰብ›› ስለሚሆን፣ እሱን ተወት አድርጎ በሚሆኑና ለኢትዮጵያ የሚጠቅመውን መሥራት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኦነግ የመገንጠልን ነገር ‹‹በኤርትራ›› ላይ ጥሎ መጥቷል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ ኦሮሚያን ለመገንጠል ሌላ ጨዋታ ካልሆነ በስተቀር የማይሆን ነገር መሆኑን አክለዋል፡፡ በግልጽ ቋንቋ “ሀቀኛ የፌዴራል ሥርዓት ነው የሚያራምደው” ብለዋል፡፡
ሕወሀትም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ሕገመንግስቱ ይከበር” ይላሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን ‹‹የኮንፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት ነው›› የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓ) ብሄራዊ ምክርቤት አባል አቶ ልደቱ አያሌው ናቸው፡፡ እንደሳቸው አባባል ሕገመንግስቱን ኮንፌደራል የሚያስብሉት ሁሉም ድንጋጌዎች (አንቀጾች) ሳይሆኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ አብዛኛው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉት ድንጋጌዎች ከዓለም አቀፍ ሁኔታ የተቀዱ ናቸው፡፡ ማንም መንግሥት ቢመጣ ይዟቸው የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ የሳቸው ፓርቲ መንግሥት ቢሆን 75 በመቶ የሚሆነውን ድንጋጌ ይዞ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በጣም መሠረታዊ የሆኑ፣ የኢትዮጵያን አገራዊ ህልውና አደጋ ውስጥ ያስገቡና ዘላቂ የኢኮኖሚ ብልፅግናን ችግር ውስጥ የሚከቱ አንቀጾች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ እነዚያ አንቀጾች ናቸው ችግር እየፈጠሩ ያሉት፡፡ ከመቅድሙ (Preamble) ጀምሮ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ የኮንፌዴራሊስት ኃይሎች የሚባሉት የብተና ኃይሎች ናቸው፡፡ “እኛ ሕዝቡ የማያውቀውን እንዲያውቅ የኮንፌዴራሊስት ኃይሎች ብለን እነማን እንደሆኑ አሳወቅን እንጂ እነሱ፣ የፌዴራሊስት ኃይሎች ነን ቢሉም በውስጣቸው ግን ኮንፌዴራሊስት መሆናቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ሁልጊዜ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው የሚመሠረተው በአንድነታችንና አብሮነታችን ላይ ሳይሆን በልዩነታችን ላይ ነው፡፡ ጠንካራ የሆነ የፌዴራል መንግሥት እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ በጣም ደካማ የሆነ፣ በሚፈልጉት ጊዜ የሚሠሩትና የሚበትኑት የፌዴራል መንግሥት እንዲኖር ነው የሚፈልጉት፡፡ ሲመቻቸው አብረው መኖር፣ ካልተመቻቸው ደግሞ መነጠል የሚፈልጉ ናቸው ፡፡ ለአንቀጽ 39 የሚከራከሩት ለዚህ ነው፡፡ እነዚህ የብተና ኃይሎች የ27 ዓመታቱ የብተና ሥርዓት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፤” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት አደባባይ ወጥቶ ደረቱን ለጥይት የሰጠው የ27 ዓመታቱ ሥርዓት እንዲቀጥል ነው? 27 ዓመታት የነበረው ሥርዓት መገለጫው ሕጉና መዋቅሩ ነው፡፡ ይኼ አይቀየርም ከተባለ፣ ታዲያ ምኑ ነው የሚቀየረው? ለውጡ ምንድነው? እነዚህ ኃይሎች ካለፈው ውድቀታቸው ያልተማሩ ናቸው፡፡ የተማሩ ቢሆን ኖሮ ቆም ብለው የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላትና ስህተቶችን በማረም ‹‹አንድነታችንን የሚያጠናክር ሥራ እንሥራ›› ብለው ይቀጥሉ ነበር እንጂ፣ ለ27 ዓመታት የነበረው መዋቅር ይቀጥል ማለት፣ ሕዝቡ ያመጣውን ለውጥ ወይም ትግል መካድ ነው፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ችግር የለበትም፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀርም ችግር የለበትም፡፡ ችግሩ ያለው አፈጻጸም ላይ ነው፤›› በማለት፣ ችግሮችን ከአፈጻጸም ጋር ሊያያይዙ እንደሚሞክሩም አቶ ልደቱ ተናግረዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ትንሽም ቢሆን የፖሊሲ ፍንጭ እንደሌላቸው ነው፡፡ የአንድ ፖሊሲ ችግር በዋናነት ፈጥጦ የሚወጣውና የሚታወቀው መፈጸም ሳይችል ሲቀር ነው፡፡ ወይም ሲፈጸም ችግር ሲፈጥር ነው እንጂ በወረቀት ላይ ያለውን ፖሊሲ ዓይቶ መስማማት ወይም አለመስማማት ይቻላል፡፡ ድክመቱንና ጥንካሬውን የምትለየው መሬት ላይ አውርደህ ስትተገብረው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት ትመራበት የነበረው ሥርዓት መሬት ላይ ወርዶ ተፈትኖ ወድቋል፡፡ መልሶ ያንን ሥርዓት ለማስቀጠል መፍጨርጨር ለአቶ ልደቱ ከጥፋት የማያድን ግብዝነት ነው፡፡የፌደራል ስርዓቱን ከለላ በማድረግና “ሕገመንግስቱ ይከበር” በሚል ሽፋን የኮንፌደሬሽን ስርዓት እያራመዱ መሆኑንም አቶ ልደቱ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዋጋ ከፍለው ያስወገዱትን አሀዳዊ ስርዓት መልሶ ለመተግበርና የዜጎችን እኩልነት ያረጋገጠውን ሕገመንግስቱንና የፌደራል ስርዓት በኃይል ለማስወገድ የሚደረገው ማንኛውም ሀወገወጥ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እነደሌለው ደጋግመው የሚናገሩት ደግሞ የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ሕወሀት) ምክትል ፕሬዝዳንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል(ዶ/ር) ናቸው፡፡ ሕወሀት “የፌደራሊስት ኃይሎች” በማለት በመቐለ ባደረገው ሁለት ስብሰባዎች ላይ ፕሬዝዳንቱ ሲናገሩ እንደተሰማው የስብሰባው ዋና ዓላማ የፌደራል ስርዓቱን ማጠናከር ነው፡፡ በመሆኑም ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ሕወሀት የፌደራል ስርዓቱን ሽፋን በማድረግ እያራመደ ያለው የኮንፌደራሊሰት ስርዓት እንደሆነ የሚገልፁትን ሀሳብ አጣጥለውታል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ላይ ላዩ ሲታይ ገራገር የሚመስል ነገር አለው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የመደብ ጭቆና ነበር ሲሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ የነበረው የብሔር ጭቆና ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ያለ ገደብ መከበር አለበት በማለት የእነ ‹‹እስታሊንና ሌኒንን መጻሕፍት›› ያነበቡ ሰዎች፣ ቀጥታ ገልብጠው ወደ ኢትዮጵያ ይዘውት መምጣታቸውን የሚናግሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ኃይሎች ንቅናቄ (ኢኅን) ሊቀመንበር ይልቃል (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ በተግባር ግን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሚያሳየው፤ የሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎች ዓላማ እነሱ እንዳሉት የብሔር ጭቆና አለበት የሚሉትን የብሔር ብሔረሰብ መብት ማስከበር ሳይሆን፤ ኢትዮጵያን እንደገና ማዋቀር፣ መከፋፈልና በጠነከረ የፓርቲ ማዕከላዊነት በማቋቋም ከፋፍሎ መግዛት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ አንድ ክልል ‹‹ባለቤት›› እና ‹‹መጤ›› አለው ማለት ነው፡፡ የክልሎቹ ሕገ መንግሥት ‹‹የክልሉ ነዋሪዎች የክልሉ ባለቤቶች ናቸው›› ይላል፡፡ ከዚያ ውጪ የሚኖሩ ሌሎች ኢትዮጵያውን በክልሉ ላይ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት መሆን አይችልም፡፡ በትንሹ የሐረሪን ክልል ማየት በቂ ነው፡፡ ይኼ የብሔር ብሔረሰብን መብት ከማክበር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ እንዲያውም የብሔር ብሔረሰብ ጭቆና መኖሩን ቁልጭ አድርጎ የሚሳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ (አማራ) የሚለውን ለማፍረስ፣ ኢሕአዴግ አገሪቱ የተሠራችበትን ድርና ማግ በመበጣጠስ፣ በመበታተንና በማዳከም ጠንካራ ፓርቲ በማቋቋም በኃይል ሲገዛ ነበር ፡፡ አሁን ያ ፈርሷል፡፡ ማዕከላዊነቱ ቀርቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ሕገ መንግሥቱ የኮንፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት መሆኑ በግልጽ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ አንቀጽ 39 ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል የሚለውና በአስቸኳይ የጊዜ አዋጅ እንኳን የማይገደብ መሆኑን ብቻ እንኳን የኮንፌዴራል አስተሳሰብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ግን ‹‹እንለያይ›› ቢባል እንኳን የማይቻል ነው፡፡ የተጋመደ ሕዝብ በመሆኑ ወደ ድብድብና ጦርነት ከማስገባት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ የአንዱ ድንበር የቱ ጋ ነው? ታሪካዊ ዳራው ማነው? ማነው ባለቤት? ማነው መጤ? ከላይ ከላይ የተሠራ እንጂ በጥያቄ ደረጃ፤ ኢትዮጵያ ሁሉም በፈለገበት ቦታ ሄዶ መጠየቅ የሚችልባት ታሪክ ያላት አገር መሆኗን በጦርነቱም፣ በኢኮኖሚውም፣ በንግዱም በሁሉም ነገር ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ ሲዘዋወርና ሲዋሃድ የነበረ ሕዝብ አገር ነች፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚለያይ በመሆኑ፣ አመራሮቹ (ኤሊቶቹ) ይኼንን ተጠቅመው ራሳቸውን ችለውና ማንም የማይደርስበት፣ በጦር ኃይልና አስተዳደርም የራሳቸውን ክልል የመገንባቱ ነገር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይኼ የሚያሳዝነው ‹‹ወክለነዋል›› ለሚሉት ሕዝብ እንኳን የማይጠቅምና አደጋ ላይ የሚጥለው መሆኑን ሊቀመንበሩ አብራርተዋል፡፡ በአጠቃላይ ‹‹ሕገ መንግሥቱ አይነካብን››፣ ‹‹የክልሎችን ሉዓላዊነት ያከበረ ሕገ መንግሥት ነው›› በማለት የኮንፌዴራሊስት አስተሳሰብ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሕወሓትና በኦሮሚያ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ኃይሎች መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ‹‹አንድ ኢትዮጵያዊ ወይም ውጭ ዜጋ በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ተዘዋውሮ የመሥራት፣ ሀብት የማፍራት፣ ቤት ሠርቶ የመኖር መብት አለው፤›› ሲል፣ አንድ ኢትዮጵያዊና ውጭ አገር ዜጋ በኢትዮጵያ ውስጥ ተዘዋውሮ የመሥራት መብቱ እኩል ነው ማለቱ ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየው አዲስ አበባ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ጋምቤላ ሲሄድ፣ ለአንድ ኬንያዊ ወይም ከሌላ አገር ዜጋ ጋር ያለው መብት እኩል ነው ማለት ነው፡፡ ይኼ ማለት ክልሎች የተለያዩ (ባዕድ) ናቸው ማለት ነው፡፡ ይኼንን የሚለው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ሲጀምር ራሱ ‹‹እኛ ብሔር ብሔረሰቦች የራሳችን ማንነት ያለን፣ ወደንና ፈቅደን፣ የራሳችንን ተወካዮች ልከን . . . ›› ሲል በሌላ አነጋገር፣ ‹‹አገር የነበረን ነን› ወደ ማለት ነው:: ይኼ ደግሞ ኢትዮጵያን የነበሩ አገሮች እንደገና የፈጠሯት (Coming Together) አገር የሚያደርግ ሕገ መንግሥት መሆኑን የሚያሳይ መሆኑንና የኮንፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ክልሎች የሌላ ብሔር ተወላጆችን እያፈናቀሉና እያባረሩ ያሉ የራሳቸውን አገር ለመገንባት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የኮንፌዴሬሽን ሥርዓት መገለጫም ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም፣ የሃይማኖት ተቋማት (ኦርቶዶክስ) ላይም እየታየ ያለው ነገር የእሱ ውጤት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ አምስት የኦሮሚያ የኮንፌዴራል ኃይሎች በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ ለኦሮሚያ የፊንፊኔን ጉዳይ በሚመለከት፤ ለኦሮሞ ሕዝብ በአገር ባለቤትነት ጉዳይ ከኦሮሚያ ተለይቶ አይታይም ማለታቸው፣ ኦሮሚያ የሚባል አገር መኖሩን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡ በቋንቋ ላይ መብት የሰጠውን ሕገ መንግሥት መንካት፣ ‹‹በህልውናችን ላይ እንደመጣ እንቆጥረዋለን፤›› ማለታቸው ደግሞ ሕገ መንግሥት የሚሻሻል፣ የሚለወጥ የሕዝቦች የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ መሆኑን የሚቃወምና አገር ከመመሥረት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይኼ የሚያሳየው ከውጭም ከውስጥም ያሉ የኢትዮጵያን መሰባበር የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን መሆኑንም አክለዋል፡፡
ሕገመንግሥቱና ችግሮቹ
ሕገ መንግሥቱ ችግር አለበት፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተሳተፈበት ውይይት የተሰናዳ ሕገ መንግሥት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥት ሆኖ መሬት ላይ አለ፡፡ በጠብመንጃና አብዮት ካልተወገደ በስተቀር ላለማክበር ምርጫ የለህም፡፡ መድረክም ለሕገ መንግሥቱ ልዩ ፍቅር ስላለው ሳይሆን ሌላ አማራጭ ስለሌለ ነው፡፡ ክፍተቶቹ ግልጽ ናቸው፡፡ በመሬት ላይ ያልተተረጎመ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ የሚያስፈልገው እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት፣ ሀቀኛ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫና ሁሉንም እኩል የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት መሆኑን የመድረክ ሊቀመንበር መረራ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡ መድረክ ለሕገ መንግሥቱ ልዩ ፍቅር ስላለው ሳይሆን የግዴታ መሬት ላይ ያለው እሱ ስለሆነ የማከበር መሆኑንም አክለዋል፡፡ አሁን ያለው የፌዴራል መዋቅር፣ በተለይ በማንነት ላይ የተመሠረተው የመብቶች አጠባበቅ ምንም የሚደረግ (የሚጎድለው) አይደለም፡፡ ወደኋላ ይመለስ ከተባለ ኢትዮጵያን ውድ ዋጋ የሚያስከፍልና ‹‹የእርስ በርስ ጦርነት›› ውስጥ ሊያስገባ ይችላል፡፡ ስም መጥቀስ ባያስፈልግም አንዳንድ ቦታዎች ለጎረቤት አገሮች የሚቀርቡ አሉ፡፡ የሰው ሞኝ ‹‹ይህች ተባይ እስከ መቼ ድረስ ነው የምታስቸግረኝ ብሎ በቤት ላይ እሳት ይለቃል›› እንዳይሆን፣ ጥንቃቄ ማድረጉና መረዳት አስፈላጊ መሆኑንም መክረዋል፡፡ ሰው ያላሰበውን ማሳሰብና ‹‹ሁሉን ተንታኝ ነኝ›› ብሎ የማይሆን ነገር ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ ላለፉት 50 ዓመታት የመብት ትግሎች ሲካሄዱ ነበር፡፡ ሁሉም ግን የኢትዮጵያን አንድነት ፈላጊ ነበር፡፡ ለሁሉም በሚመችና በሚያሳምን መንገድ መቅረፅና ማደስ አስፈላጊ ነው፡፡ ለሁሉም የምትሆን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር የሁሉም ዓላማ መሆን እንዳለበትም መክረዋል፡፡ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ሁሉም መብቶች እኩል መከበር አለባቸው፡፡ ከ50 ዓመታት በፊት ‹‹ኢትዮጵያዊው ማነው?›› የሚለው ጥያቄ ሳይመለስ ቆይቷል፡፡ የዘርና የጎሳ ፖለቲካ እያሉ መንቀሳቀሱ ሌላ ድንጋይ ስለሚያወራውር፣ የተሻለ፣ ሁሉንም የሚያካትትና የሚያጠቃልል አካሄድ የተሻለ መሆኑን አክለዋል፡፡
የምርጫ ዝግጅት
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የሚችለውን ያህል ለ2012 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ እየተዘጋጀ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ከ1997 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ ጀምሮ እየተሳተፈ ነው፡፡ ነገር ግን የተደረጉ ምርጫዎችን ‹‹ምርጫ›› ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ኢሕአዴግ የምርጫ ኮሮጆ በመዝረፍ እስከ መቶ በመቶ ድረስ አሸናፊ የነበረ በመሆኑነው ፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ኦፌኮ ሊሸነፍ እንደማይችልና አሁንም አሸናፊ እንደሚሆን የመድረክና የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ይናገራሉ፡፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚደረግ ከሆነ ኦፌኮ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የምንጮኸውን ያህል እየሠራን ነው፤›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ እየተዘዋወሩ ማስተማር፣ ስለፖለቲካ ፕሮግራማቸውና አጠቃላይ ሁኔታ ከደጋፊዎቻቸው ጋር እየተወያዩና ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምርጫ ዝግጅትና ሒደት እየተባለ የሚንዛዛው ወይም ብዙ ጊዜ የሚሰጠው ዝም ብሎ ነው፡፡ የሚንዛዛውም ሆን ተብሎ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ የሚሠሩ በረዥም ጊዜ የሚሠሩ ነገሮች አሉ፡፡ ወሳኙና ዋናው ቁም ነገር የጊዜ መስፋት ወይም ጥበት አይደለም፡፡ ጨከን ብሎ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ምድር ‹‹ይካሄድ›› ብሎ መወሰንና ሁሉም የየራሱን የቤት ሥራ መሥራት ላይ ነው ፡፡ ለውጥ ከተጀመረ ሁለት ዓመታት ሊሞላው ሁለት ወራት ናቸው የቀሩት፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ የሆኑ የአገሪቱ ፖለቲካ ጥያቄዎች እየተመለሱ አይደለም፡፡ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ቢጨመርም የተሻለ ጊዜ ይመጣል ወይም አይመጣም ለማለት ፕሮፌሰር እርግጠኛ ሆነው መናገር አልቻሉም፡፡ ብዙዎች የምርጫው ጊዜ እንዲተላለፍ ይጠይቃሉ ወይም እየጠየቁ ነው፡፡ ነገር ግን መታወቅ ያለበት አገሪቷን ለዚህ ደረጃ ያደረሳት ኢሕአዴግ ነው፡፡ የመጀመርያው (በአቶ አቶ መለስ ዜናዊ የተመራው)፣ ሁለተኛውም (በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተመራው) እና ሦስተኛውም (በዓብይ አህመድ ዶ/ር እየተመራው ያለው) ያው ኢሕአዴግ ነው፡፡ የተሻለ ነገር ይፈጥራል ብሎ መጠበቅ ‹‹የፖለቲካ የዋህነት ነው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡ ዋናው መሆን ያለበት ነገር ሕዝብን በማደራጀትና በመቀስቀስ ለነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተገቢ ትኩረት በማድረግ መዘጋጀትና ትግሉን መቀጠል ነው የሚያዋጣው፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብዙ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ ዋናው ነገር የምርጫውን ጊዜ ቆርጦ መግባት ነው፡፡ እንኳን ከአምስት ወራት በላይ እያለ፣ በሁለትና ሦስት ወራት ውስጥ ብዙ ነገር መሥራት ይቻላል፡፡ ትልቅ ሥጋት የሚሆነው ብሔራዊ መግባባት ሳይፈጠር ወደዚህ ምርጫ መግባቱ ካልሆነ በስተቀር፣ የጊዜው ጉዳይ ችግር እንደማይሆን መረራ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡
ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ጀምሮ ያለውን ብንመለከት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ተሰባስቦ እኔን የሚያሸንፍ ድርጅት የለም፡፡ ስለዚህ እንከን የለሽ ምርጫ አደርጋለሁ አሉ፡፡ ነገር ግን የተወሰነ ድምፅ ፓርላማ ቢገባ የበለጠ የኢሕአዴግን ስም ከፍ ያደርጋል እንጂ ሥልጣናችንን አደጋ ላይ አይጥልም፤›› ብለው ነበር፡፡ ውጤቱ ግን የተለየ ሆነ፡፡ ያንን ሲያዩ የሚታገሉት አመለካከት ኃይለኛ እንደሆነ፣ ብዙ ሥራ መስራት እንደሚቀራቸውም ተረዱ፡፡ ከዚያ በኋላ ለእስርና እንግልት የሚዳርጉ የሲቪክ፣ የፀረ ሽብርተኝነት፣ የምርጫና የመሬት ሊዝ አዋጆችን አወጡ፡፡ ‹‹ቀልድ የለም፣ አብየታዊ ዴሞክራሲ መንግሥት ነው ብለው አንድ ለአምስት በሚል አደረጃጀት ጥፍንግ አድርገው በ2002 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ 99.6 በመቶ አሸነፉ፡፡ ሥልጣንን ዘለዓለማዊ የማድረግ ዝንባሌ አደረባቸው፡፡ ለ2007 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ አቶ መለስ(ማስተር ማይንዱ ስለሌሉ፣) ችግር እንኳን ቢፈጠር ሁሉንም ነገር ዝግት አደረገና መቶ በመቶ አሸነፈ፡፡ ‹‹አሁንስ በዚህኛው ሀገራዊ መምርጫ ምንድነው የሚሆነው?›› የሚለውን ስናይ ‹‹ዘረኝነት›› ያልገባበት ቦታ ስለሌለ፣ አለመተማመን ጫፍ ላይ በመድረሱ፤ ለውጥ የሚፈልገው ሕዝብ ሜዳ ላይ እያለ እዚያው እንዳይቀር፤ ምርጫው ቀርቶ መጀመርያ ሕዝባዊ መግባባት መፈጠር እንዳለበትና እስከዚያው ድረስ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ሦስተኛ አማራጭ መሆን እንዳለበት ይልቃል (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡
የፓርቲዎች ጥምረትና ምርጫ
ኦፌኮ፤ ኦነግና በብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) ጋር ጥምረት ፈጥረው ለመስራት እየተሞከሩ ቢሆንም ‹‹ያልተፈቱና የተፈቱ፣ ስምምነት የተደረገባቸውና ያልተደረገባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ነገር ግን በመድረክ ደረጃ በአፋር፣ በሲዳማና ሌሎችንም ክልሎች ጨምሮ እየተሠራ ነው፡፡ ተወዳዳሪነትንና አሸናፊነትን በሚመለከት፣ በገዥው ፓርቲ (ኦዴፓ/ብልፅግና ፓርቲ) ጉልበት አለው፡፡ ገንዘብና ሠራዊትም አለው፡፡ በተፎካካሪ ፓርቲዎች አካባቢ ደግሞ ከበቂ በላይ የሕዝብ ድጋፍ አለ፡፡ ዋናው ጉዳይ ሕዝቡ የተመቻቸ ሁኔታ እንዲያገኝና የፈለገውን እንዲመርጥ ማድረግ ነው፡፡ ያዋጣኛል፣ ይጠቅመኛል ያለውን መምረጥ ይቻላል፡፡ ግን በጠመንጃ የሚወሰን የሕዝብ ድምፅ መሆን እንደሌለበትና የጠመንጃ አገዛዝ መቅረት እንዳለበትፕሮፌሰሩ መክረዋል ፡፡ ብልፅግና ፓርቲም ይሁን ወይም ሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ ለመድረክ/ኦፌኮ ጭንቀት አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ በመሬት ላይ ሀቀኛ የሆነ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መካሄድ አለበት፡፡ ዜጎች መሪዎቻቸውን ለመምረጥ መብቶቻቸው ሊከበሩላቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥና እንደ አገር እንድትቀጥል ለማድረግ፣ የተሻለ መልካም አስተዳደር እንዲኖር ከተደረገ ብቻ ወደ ብልፅግና መሄድ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ሁለትና ሦስት ጊዜ ‹‹ተቀይሬያለሁ›› እያለ ስሙን መቀያየር ብቻ ሳይሆን በሀቅ ሠርቶ መሬት ላይ ሕዝቡ መብቱን እንዲጎናፀፍና መሪዎቹን መምረጥ የሚያስችለውን ሁኔታ መፍጠር አለበት፡፡ ይኼንን መፍጠር ከቻለ ሁሉም ነገር በቀላሉ ሊፈጸም ይችላል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ላለፉት 27 ዓመታት ኢሕአዴግ ‹‹እንከን የለሽ ምርጫ›› እያለ ሲቀልድ መኖሩን ማስታወስ በቂ መሆኑን መረራ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያውን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢኀን) ሊቀመንበር ይልቃል(ኢንጂነር) ም፤ ፓርቲያቸው ኢሃን ከኢዴፓና ኅብር ኢትዮጵያ ጋር ጥምረት በመፍጠር በጋራ ለመሥራት ተስማምተው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ በዋናነት የተጣመሩት፣ በዚህ ዓመት ‹‹ይካሄዳል›› እና ‹‹መካሄድ የለበትም›› እየተባለ፣ እርግጠኛው የትኛው እንደሆነ ባልተረጋገጠበት አገራዊ ምርጫ ጋር በተገናኘ ለየት ያለ ሐሳብ ወይም አማራጭ ለማቅረብ ነው፡፡ ጥምረቱ ይዞት የቀረበው ‹‹ምርጫው ይካሄድ›› ወይም ‹‹መራዘም አለበት፤›› ሳይሆን፣ ‹‹አገረ ኢትዮጵያን ለማትረፍ ወይም እንዳትበታተን ለማዳን ከተፈለገ የሽግግር መንግሥት መቋቋም፤›› አለበት የሚል አማራጭ ሐሳብ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ የራሳቸው የሆነ ርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ ፕሮግራም አሠላለፍ ያላቸው ቢሆንም፣ በዋናነት እንዲሰባሰቡ ያደረጋቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያላቸው ግምገማ ተመሳሳይ መሆኑንም ይልቃል (ኢንጂነር) ይናገራሉ፡፡ የችግሩ አሳሳቢነት ከቀን ወደቀን እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲም ወዴት እንደሚወስደንም ግልጽ የሆነ ነገር ጠፍቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወቅታዊ ሁኔታውን በየራሳቸው መንገድና ፍልሚያ ለማስኬድ የተለያዩ ቡድኖች በተለያዩ ቦታዎች እየፈጠሩ መጥተዋል፡፡ አገሪቱም ከምትገኝበት ቀጣና አንፃር ከቅርብም ከሩቅም ጥሩነቷን የማይቀበሉ ኃይሎች እጃቸውን እያስገቡ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየታቸውን፣ በነባራዊው ሁኔታ ደግሞ የሥራ አጥነቱ፤ ጎሰኝነቱና ሃይማኖቱ ሕዝቡን የበለጠ ስሜታዊ የሚያደርጉ ብዙ ሁኔታዎች መኖራቸው፣ የአገሪቱን ሁኔታ እንዲገመግሙ እንዳስቻላቸውና አንድ ነገር ማለት ስለሚገባቸው ጥምረቱን እንደፈጠሩ ይልቃል (ኢንጂነር) ይናገራሉ፡፡
ኃላፊነት ላይ ረዥም ዓመታት (27 ዓመታት) የቆየው ሕወሓት ከሥልጣን እየተገፋ በመምጣቱ ስለተረበሸ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኃይሎችን ትኩረትንም ለማግኘት ወይም ጉልበቱንና ኃይሉን አሳይቶ ትኩረትና እንዲታይ ለማግኘት እንደሚፈልግ የሚናገሩት ይልቃል (ኢንጂነር)፣ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ እዚህም እዚያም የሚያደርጋቸው የሚታዩ ነገሮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
ሕወሓት የራሱን መንግሥት (Defacto State) እስከ መመሥረት እንደሚደርስ ማሳወቁ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹የሕገ መንግሥቱ ችግር የአፈጻጸም በመሆኑ፣ በአግባቡ ይፈጸም አልን እንጂ፣ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አካሄድ እንዳላማራቸው ገልጸው፣ እንደገና ራሳቸውን አጠናክረዋል፡፡ ጫፍና ጫፍ የነበሩ፣ ተራራቁት ሁሉ አንድ ሆነውና ተሰባስበው መምጣት አዝማሚያ እየታየ መሆኑ ይልቃል (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ደግሞ ቅርፀ ቢስ (Amorphous) ሆኖ ወዴት እንደሚሄድ በግልጽ ሳይታወቅ ችግሮቹ እየቀደሙት እያየ፣ ነገሮች በራሳቸው ጊዜ ይፈታሉ በሚል ሁኔታ ነገሮችን ቀላል (Over Simplified) አድርጎ የማየት ሁኔታ አለ፡፡ አለመርካቱን እየገለጸ ከታች የሚመጣ እንዳለ እያየ ዝም ብሏል፡፡ የችግሮቹ መገለጫዎችን ለማየት ያህል፣ ኢኮኖሚው በጣም አደገኛ ሁኔታ ላይ ወድቋል፡፡ ከቱሪዝምና ከውጭ ኢንቨስትመንት (FDI) የሚገኘው ገንዘብ በጣም ቀንሷል፡፡ የኑሮ ውድነቱ፣ ትምህርት በየዩኒቨርሲቲዎች መቋረጥ ብቻ ሳይሆን፣ ተማሪዎች እየተገደሉ በመሆኑና ሌሎችም ችግሮች እንዳሉ ይልቃል (ኢንጂነር) አብራርተዋል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች አንድ ዓይነት መፍትሔ ካልተገለፈ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ እንደ አገር የመቀጠል ሥጋት መኖሩን በመረዳታቸውና የአገሪቱን ህልውና ከማዳን አንፃር ጥምረቱን መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡ መፍትሔው ምን ይሆናል? ለሚለው ደግሞ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት እንደሚያስፈልጋት የጋራ እምነታቸው በመሆኑ፣ በእሱ ላይ ለመሥራት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ምርጫ ካልተደረገ ብሎ ሙጭጭ ማለት ተገቢ አለመሆኑንና ‹‹በምርጫ የተፈጠረ ችግር የለም፡፡ በምርጫ የሚፈታም የለም፡፡ ይደረግ ቢባል እንኳን ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ አለመኖሩን ይልቃል (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ምርጫው መካሄድ አለበት ተብሎ የግድ የሚደረግ ከሆነ እንደሚወዳደሩም ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡበት ጊዜ የሚያነቃቃና ለውጥ የሚመስል ነገር ስለነበረ በተቻለው ሁሉ ለማገዝ ኢዴፓ ዝግጁ የነበረ ቢሆንም፤ የኢሃን ግን የተለየ አስተያየት ነበረው፡፡ ለውጡ በሐሳብ ተመርቶ የመጣ ለውጥ አይደለም፡፡ በነባራዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት የመጣ ለውጥ ነው፡፡ አገሪቱ የወጣት አገር እየሆነች በመሆኗ ሥራ አጥነቱ እያደገ መጥቷል፡፡ ይኼ ነገር ኢሕአዴግን እንዲናጥና ገፊ ምክንያቱ በመብዛቱ (የአቶ መለስ ዜናዊ ሞትን ጨምሮ) ለውጡ መምጣቱንና ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ መሆኑን ሊቀመንበሩ ይገልጻሉ፡፡ የ‹‹ለውጥ ኃይል ነኝ›› የሚለው አካል ‹‹የት ነበርኩ? አሁን የት ነኝ? ወዴትስ እሄዳለሁ?›› ብሎ አስቦ ያመጣው ለውጥ እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ በአጭሩ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የለውጥ ኃይል ካልሆነ፣ ኦዴፓ የለውጥ ኃይል የሚሆንበት ነባራዊ ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ አንድ የሽግግር መንግሥት እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ፡፡ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ የለውጡ ሒደት ግን የኢሕአዴግ መሰባበር (Disintegration) እንጂ ለዴሞክራሲ ሒደት ዕውን የሆነ የፖለቲካ ኃይል አይደለም የሚል አመለካከት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ በሒደት ኢሃን ከመጀመርያው አንስቶ ሲያነሳቸው የነበሩ ነጥቦች ሁሉ እየተተገበሩ በመምጣታቸው ኢዴፓና ኅብር ኢትዮጵያም የአገርና የሕዝብ ጉዳይ እያሳሰባቸው በመምጣቱና የሦስቱም ፓርቲዎች አስተሳሰብ አንድ ሊሆን በመቻሉ ጥምረቱን በመፍጠር አብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይልቃል (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ችግር ላይ ተመሳሳይ አረዳድ ካላቸው ሌሎች ፓርቲዎችም ወደ ጥምረቱ ለመቀላቀል በሒደት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ሥልጣን የሕዝብ ነው፡፡ መልካም ነገር ካለም የሚወደሰው ሕዝብ ነው፡፡ ችግር ከመጣም የመጀመርያው ገፈት ቀማሽ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ሥልጣን የሕዝብ እንዲሆን ካስፈለገ ለሕዝብ መሥራት የግድ ነው፡፡ በመሆኑም ወደ ሕዝብ መቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሽግግር መንግሥት አቋቁሞ ከሕዝብ ጋር በመምከር አማራጭ የሌለው ነገር በመሆኑ፣ ይህንን አማራጭ ለሕዝብ ለማቅረብ ፓርቲዎቹ እየሠሩ መሆኑን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ አሁን እየታየ ያለው ነገር ሁሉ ኃላፊነት የጎደለው ይመስላል፡፡ የብሽሽቅ ሁኔታዎች ስላሉ ባልታወቀ መነሻ ወደ ቀውስ ተገብቶ አገርን ሊያፈርስና ሕዝብን ወዳልተፈለገ መጠፋፋት ውስጥ ሊከት ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ‹‹ነገ እከሌ ይወደኝ ይሆን? ወይም ይጠላኝ ይሆን? ብሎ በፖለቲካ ውስጥ ሆኖ ይሉኝታ አይሠራም፡፡ የአገሪቱ ሁኔታ እንቅልፍ የሚነሳ ጣጣ በመሆኑ ችግሩን በድፍረት መጋፈጥ የግድ ነው፡፡ ቁጭ ብሎ መነጋገር ያልተቻለበት ደረጃ ላይ ተደርሶ እያለ ምርጫ ማድረግ ቀልድ እንደሆነ ይልቃል (ኢንጂነር) ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በድንበር የማይጣላ የለም፡፡ ሁሉም በሚባል ደረጃ ‹‹እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ›› በሚል የየራሳቸውን ጦር የማዘጋጀትና የማስታጠቅ ዝግጀት ላይ ናቸው፡፡ ይኼም አካሄድ ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ አደገኛ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ባልተስተካከሉበት ሁኔታ ምርጫ ይደረግ ማለት ኃላፊነት መጉደል ነው፡፡
የሽግግር መንግሥትና ተግዳሮቶቹ
የአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመጨረሻ ቀኖች ‹‹ለውጥ›› ማለት ሲጀመር፤ መድረክ “ይኼ ለውጥ በሚሆን መንገድ ይመራ፡፡ ኢሕአዴግም ሥልጣኑን ይዞ ይቀጥል፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ የሆኑ የአገሪቱ ችግሮች ዕውቀቱና ልምዱ ያላቸው የአገሪቱ ባለድርሻ አካላት ይግቡበትና ለውጡን ከኢሕአዴግ ጋር ይምሩት” ማለቱን መረራ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡ ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሁኔታ ያጨመላለቀ መንግሥት መምራት የለበትም የሚል አቋም እንደነበረውም አክለዋል፡፡ ለውጥን ለመምራት ከዕውቀትና ከልምድ በተጨማሪ የፖለቲካ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕዝብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን መድረክ ሲገልጽ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን “የሽግግር መንግሥት” ማለት መተካትን (Displacement) ያመጣል፡፡ ይኼ ደግሞ አብዮት ነው፡፡ ይኼ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው የ‹‹ብሔራዊ አንድነት መንግሥት›› ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሚባሉ፣ ዕውቀቱ፣ ልምዱና ችሎታ ባላቸው ኢትዮጵያውያን የሚመራ አንዲሚያስፈልግ መድረክ 17 የድርድር ነጥቦችን ጽፎ መስጠቱንም አስታውሰዋል፡፡ አሁን የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሐሳብ ማቅረብ ውኃ የማይቋጥር ሐሳብ መሆኑንና የፖለቲካ ዕውቀት ካለው አካል የማይጠበቅ መሆኑን ጠቁመው፣ ትንሽ ሰከን ብሎ ኢትዮጵያ ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ ሲያታግል የቆየውንና አሁንም የቀጠለውን የእኩልነት ጥያቄ መፍቻ መንገድ መፈለጉ ብቻ እንደሚያዋጣታ ፕሮፌሰር መረራ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ከተስማማ ግን የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ጽድቅ መሆኑን አክለዋል፡፡ ግን መሻገሩና ማሸጋገሩ ቀላል ጨዋታ እንዳልሆነ መታወቅ እንደሌለበት በመግለጽ እነ አቶ ልደቱና ይልቃል (ኢንጂነር) ሀሳብ የማይሆንና ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ምርጫና ሰላም
በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎችና አካባቢዎች ችግሮች እየተፈጠሩና ዜጎችም እየሞቱ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት፣ ‹‹ችግሮቹን ማነው የሚፈጥራቸው? ተጠያቂውስ ማነው?›› የሚለውን መለየትና ማወቅ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የመንግሥት ኃይላት፣ ተቋማት፣ ፖሊሶችና ልዩ ኃይሎች ወጣቶች በድንጋይ ተደብድበው ሲገደሉ ቆመው ያያሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ‹‹የሕግ የበላይነት አካላት ናቸው?›› ሲሉም መረራ (ፕሮፌሰር) ይጠይቃሉ፡፡ መንግሥት በተለይ፣ ‹‹የፀጥታ መዋቅሩን የሚያንቀሳቅሱትን እየተቆጣጠረ ነው? ሕዝቡ በየዕለቱ የሚያነሳው ጥያቄ ነው፡፡ ‹‹መንግሥት ምን እያደረገ ነው?›› በዋናነት ሰላምን የሚያደፈርሰው፣ የሚያጋጨው፣ በሚፈጠረው ግጭት አተርፋለሁ ብሎ የሚንቀሳቀሰው በአብዛኛው በ27 ዓመታት ውስጥ የመንግሥት አካል የነበረና አሁን ‹‹ጥቅሜ ተነካ›› ወይም ዶሮ እንዳለችው፣ ‹‹ባልበላውም ጭሬ አፈሰዋለሁ›› የሚሉ የመንግሥት አካላት መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ ቁጥር አንድ ኢሕአዴግ በግልጽና ቁጥር ሁለት ኢሕአዴግ ባልታወቀ መንገድ መሆናቸውን አክለዋል፡፡ ወጣቱ ተረጋግቶ እንዳይማርና እንዳይሠራ ከፍተኛ በጀት መድቦ በየዩኒቨርሲቲዎቹና ክልሎች ላይ የሚሠራ አካል ለመኖሩ ምንም አያጠራጥርም፡፡ ይህች አገር እንድትበታተን የሚፈልጉ ኃይሎች እንጂ፣ ሕዝብ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ‹‹ይኼንን ድርጊት የሚፈጽሙት እነ ማን ናቸው? ቡዳው ማነው?›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ አካላት እንደጠፋም መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡ ዝም ብሎ የጊዜ ጨዋታ በማንሳት ‹‹እንደዚህ እየተደረገና ሰው እየሞተ፣ ዝግጅት ሳይኖር እንዴት ወደ ምርጫ እንገባለን?›› የሚባለው ሰበብ ከማብዛት የዘለለ አይደለም፡፡ ራሱ የሕግ የበላይነት ማክበር ያለበት ሕግን እየጣሰ ነው፡፡ በ2006 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ከፍተኛ ተቃውሞ አንስተው ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. ደግሞ አገራዊ ምርጫ ነበር፡፡ ምርጫው ሲደረግ ግን በኦሮሚያ ምድር አንድም ድንጋይ አለመወርወሩንና የሕዝቡ ትኩረት ምርጫ እንደነበር፣ ምክንያቱ ደግሞ በምርጫው ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ ስለነበረው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ግን ለውጥ የሚለውን ነገር ትቶ ‹‹አውራ ፓርቲ›› ለመሆን ፈልጎ፣ ‹‹አውሬ ፓርቲ›› በመሆኑ፣ ‹‹መቶ በመቶ አሸንፌያሁ›› ያለበት የምርጫ ጨዋታ መበላሸቱን ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገውን ነገር ምርጫው ራሱ እንደሚሰጠው ካመነ፣ አሁን የሚታየው አለመረጋጋትና ውዥንብር ወይም የወጣቱ ዕይታ ወደ ምርጫው ሊዞር ስለሚችል፣ ምርጫን ማካሄድ የደፈረሰ የሚመስለውን ሰላም ሊያስተካክል እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በተቻለ አቅም ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ ምርጫ እንዲሆን መሥራት እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡ በጠመንጃ የሕዝብ ድምፅ መስረቅ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ ሠራዊቱ የአገሪቱን ዳር ድንበር መጠበቅ እንጂ ኮሮጆ ገልባጭ አይደለም፤›› እያሉ ማስተማር አለባቸው፡፡ እንደዚህ ከተሠራ የሕዝቡ ቀልብ በሙሉ ወደ ምርጫ ይዞራል፡፡ ስለዚህ ምርጫ ማካሄድ ለተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ሁኔታ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችልም አክለዋል፡፡ መድረክን ጨምሮ ሁሉም ሥጋት ቢኖረውም፣ ነገር ግን መሠረታዊ በሆነ መንገድ ሁሉም የራሱን የቤት ሥራ መሥራት አለበት፡፡
ጃዋርና ኦፌኮ
ጃዋር መሐመድ የኢትዮጵያን አንድነት ‹‹አልፈልግም›› ያለበትን ጊዜ እንደማያስታውሱ መረራ (ፕሮፌሰር) ይናገራሉ፡፡ የዜግነት ጉዳይን በሚመለከት ሁሉም ከኢትዮጵያ ተገዶና ተሰዶ የሄደ ነው፡፡ ጃዋርመም እነደዛው፡፡ ጃዋርን ‹‹ዕውቁ የፖለቲካ ተንታኝ…›› እያሉ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሱት ቪኦኤና ኢሳት ናቸው፡፡ ኦፌኮ ስለኦሮሞ ወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በአሜሪካን አገር በሚካሂዳቸው ስብሰባዎች ላይ ወጣቶችን ሰብስቦ በመገኘት ንግግር ያደርግ ነበር እንጅ የኦፌኮ አባል አልነበረም፡፡ አልጀዚራ ላይ በሚሠራ ጓደኛው አማይነት ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት፣ ስለኦሮሞ ሕዝብ ትግልና ኢትዮጵያ ደጋግሞ ይናገራል፡፡ በዚህ ጊዜ ጋዜጠኛዋ፣ ‹‹ለአንተ አንደኛ ኢትዮጵያ ወይስ ኦሮሞ?›› የሚል ጥያቄ ስትጠይቀው፣ ‹‹ለእኔ አንደኛ ኦሮሞ›› (Oromo First) የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ጃዋር የኢትዮጵያዊነቱን ካባ አውልቆ ጣለ መባሉን ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡ ወቀሳና ውግዘት ሲበዛበትም የራሱን ሚዲያ መፍጠሩን አክለው፣ በዋናነት እዚህ ያደረሱት ግን ቪኦኤና ኢሳት መሆናቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡ ኦፌኮ ውስጥ ተመዝግቦና አባል ሆኖ መሥራት የጀመረው ግን ሰሞኑን ነው፡፡ ኦፌኮ አሜሪካን አገር ባካሄዳቸው ስብሰባዎች ላይ ይሳተፍ የነበረው እንደማንኛውም ሰው እንጂ በአባልነት አይደለም፡፡ ጋዜጣኛ ስለነበርና የራሱ ሚዲያ ስለነበረው በተለያየ ጊዜ ከኦፌኮ አመራሮች ጋር ከመገናኘቱ በስተቀር አባል እንዳልበርና እሳቸውም ከእሱ ሚዲያ ጋር ተነጋግረዋል ተብለው አብረውም ተከሰው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ምንም ይሁን ምን፣ ጃዋር በሜዳ ላይ ሆኖ ከሚያስቸግር መስመር ላይ ቢገባና ቢታገል ይሻላል፡፡ ምርጫ ስለመወዳደሩና ስለዜግነቱ የማጣራት ጉዳይ የኤምግሬሽን ወይም የፖሊስ ሥራ ቢሆንም፤ ልጁ ግን ኢትዮጵያዊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሞ ድርጅቶችን ሲሰበስቡም አብሮ ተሰብስቦ መመልከታቸውን ጠቁመው፤ በዚህ ደረጃ የሚታወቅና የሚንቀሳቀስን ሰው ‹‹ኢትዮጵያዊ ነህ ወይስ አይደለህም?›› ብሎ ኦፌኮ የሚጠይቅበትና የፖሊስ ሥራ የሚሠራበት ምክንያት እንደሌለውም አክለዋል፡፡
በአጠቃላይ በአገሪቱ ዉስጥ የሚታየው የፖለቲካ ሀይሎች አሰላለፈፍና የምርጫ ዝግጅት የተደበላለቀ መሆኑን የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች ከላይ ከሰጡት ትንተና መገንዘብ ይቻላል፡ በመሆኑም ስለሀገርም ሆነ ሕዝብ ሁሉም ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም፤ በተለይ መንግሰትይበልጥ ኃላፊነት ስላለበት ፖለቲካዊ ሂደቶች መስመራቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ማድረግ አለበት፡፡የፖለቲካ ድርጂቶችም ልዩነታቸውን ጠብቀው ለኢትዮጵያ አንድነት፤ ለሰላምና እውነተኛ ዴሞክራሲ መታገል አለባቸው፡፡ምርጫ ዜጎች ይመራኛል የሚሉትን የፖለቲካ ድርጅት ነፃ፤ ተአማኒና ፍትሀዊ በሆነ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሚመርጡበት እንጅ መንግስተ ሰምያት የሚገቡበት ባለመሆኑ ተኩርት ሊሰጠው ይገባል፡፡