Ethiopian Reporter Magazine
Wednesday, March 29, 2023
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት
Ethiopian Reporter Magazine
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
Ethiopian Reporter Magazine
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ

የኢትዮጵያ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት

በ መሐሪ መኰንን (ዶ/ር)
February 2020
የኢትዮጵያ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት
0
ያጋሩ
564
ዕይታዎች
Share on FacebookShare on Twitter

የአንድ ሀገር የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት ማለት የሀገሩ የፋይናንስ ተቋማት እና የፋይናንስ ገበያ በሥራ ጥልቀታቸው (Depth)፣ በተደራሽነታቸው(Access) እና በቅልጥፍናቸው (Efficiency)በዓመታት ያሳዩት ዕድገት ማለት ነው፡፡ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፈርት ተበጅቶለት ይለካል፡፡ የፋይናንስ እንቅስቃሴው ጥልቀት፣ ተደራሽነትና ቅልጥፍና በገበያውም ይሁን በተቋማቱ ላይ ለዕድገቱ መሰረታዊ መስፈርት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

በዚህ መሰረት የተቋማት የሥራ ጥልቀት የሚለካው ተቋማቱ ለግሉ ክፍለ-ኤኮኖሚ የሰጡት ብድር ከዓመታዊ የሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት ጋር በማነጻጸር ይሆናል፡፡ ተደራሽነቱ ደግሞ የቅርንጫፎቹ ብዛት በ100,000 ሰዎች ምጣኔ የሚሰላ ይሆናል፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ቅልጥፍና የሚለካው ደግሞ በተቋማቱ ትርፋማነትና ወጪ ቆጣቢነት ነው፡፡ ገበያውን በሚመለከት ጥልቀቱ፣ ተደራሽነቱ እና ቅልጥፍናው የሚለካው ከአክሲየንና ዕዳ ሰነድ ሽያጭ ገበያ እንቅስቃሴ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም (IMF) የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገትን በመለካት ይታወቃል፡፡ ይህ ተቋም የዕድገት መለኪያ (Index) አዘጋጅቶ የሀገራትን የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት ያነጻጽራል፡፡ ከፍተኛ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት ያላቸው ሀገራት ወደ መቶ የሚጠጋ ስሌት ሲያስመዘግቡ፤ አነስተኛ እድገት ያላቸው ደግሞ ዝቅተኛ ስሌት ያስመዝግባሉ፡፡ እኤአ በ2017 በተደረገው የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት ጥናት ስዊዘርላንድ (93%) ቀደምት ስትሆን፤ አሜሪካ (88%)፣ ጃፓን (88%)፣ አውስትራሊያ (87%) እና ደቡብ ኮሪያ (87%) እንደቅደም ተከተላቸው ይሰለፋሉ፡፡

የሀገራችን አጠቃላይ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት እምብዛም የሚመሰገን አይደለም፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት (እኤአ 2008-2017) በአማካይ ያደገው 13% ብቻ ነው፡፡ እኤአ የ2017 በተደረገው የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት ጥናትም ላይም ያሳየው ዕድገት ያው 13% ብቻ ነው፡፡ በዚህ ዘመን በሀገራችን የፋይናንስ ተቋማት በአማካይ 26% ሲያድጉ፤የፋይናንስ ገበያው ግን ዕድገቱ በአማካይ ከ1% አልዘለለም፡፡ ምናልባት ለምስክር የሚሆነው ወጣ ገባ የሚለው የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ገበያ ካልሆነ በስተቀር በሀገራችን የፋይናንሰ ገበያ አለ ለማለትም አያስደፍርም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፎች

2013 በጀት ዓመት

ለ2013 በጀት ዓመት ከ476.3 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ቀረበ

June 2020
ኮቪድ-19 የፈጠረው ቀውስና የደቀነው የምግብ እጥረት ሥጋት

ኮቪድ-19 የፈጠረው ቀውስና የደቀነው የምግብ እጥረት ሥጋት

May 2020

የመድን ንግድ ሥራ በኢትዮጵያ ከትላንትና አስከ ነገ

April 2020

ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ የሚፈልገው የግንባታ ኢንዱስትሪ

March 2020

በሠራተኛው ጉልበት ከተመዘገበው ይልቅ በመንግሥት ወጪ የተገነባው የኢኮኖሚ ዕድገት

January 2020

በአጠቃላይ ሲታይ የሀገራችን ፋይናንስ ተቋማት ከፋይናንስ ገበያው በተሻለ የዕድገት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ከላይ በተጠቀሰው 10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ቅልጥፍናቸው በአማካይ 75% አድጓል፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት የባንኮች ትርፋማነት ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እኤአ ከ2010-2018 ባለው ጊዜ ውስጥ የባንኮች የአክሲዮን ዲቪደንድ በ14.7% ዕድገት አሳይቷል፡፡  ጥልቀታቸውና ተደራሽነታቸው ግን ያደገው በአማካይ 5% እና 3% ብቻ ነው፡፡

የባንክ ቅርንጫፍ
በ100,000
ህዝብ ምጣኔ
(እኤአ 2007-2019)

የሀገራችን የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት ከምስራቅ አፍሪቃም ሆነ ከጠቅላላ የአፍሪቃ ሀገራት የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት አንጻር ሲታይ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የምስራቅ አፍቃ ሀገራት ኬንያ (20%)፣ ቡሩንዲ (16%)፣ ጂቡቲ (15%) እና አንጎላ (15%) ኢትዮጵያን (13%) በብዙ ይቀድሟታል፡፡ ከአፍሪቃ ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪቃ (63%)፣ ሞሮኮ (42%)፣ ግብጽ (30%)፣ ቦትስዋና (27%) እና ናይጄሪያ (24%) ከፍተኛውን ቦታ ይይዛሉ፡፡

እንደሚታወቀው የፋይናንስ ገበያው አለ የሚባል አይደለም፡፡ ስለሆነም የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት የፋይናንስ ተቋማት ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር በሀገራችን በሰፊው የሚታወቁት የፋይናንስ ተቋማት ባንኮች፣ የመድን ድርጅቶችና የማይክሮ ፋይናነስ ተቋማት ናቸው፡፡ እኤአ በ2019 መጨረሻ የእነዚህ ተቋማት ጠቅላላ ካፒታል ከዓመታዊ የሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት ጋር ሲጻጸር 6.36% ይሸፍናል፡፡

ከዚህ ውስጥ 5.11% (ወይም 80.36%) የባንኮች ድርሻ ነው፡፡ ስለሆነም የባንኮችን የፋይናንስ እንቅስቃሴ መቃኘት የሀገሪቱን የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት በግልጽ ያመላክታል፡፡

የባንክ ፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት

እኤአ በ2019 መጨረሻ በተወሰደ መረጃ በሀገራችን 16 የግልና 2 የመንግስት በድምሩ 18 የንግድ ባንኮች ያሉ ሲሆን  በ5,564 ቅርንጫፎቻቸው የገንዘብ ልውውጥ ያከናውናሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 70% የሚሆኑት ቅርንጫፎች በግል ባንኮች የተያዙ ሲሆን ቀሪው 30% ደግሞ በመንግስት ባንኮች የተያዙ  ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ መሰረት ከግል ባንኮች ውስጥ አዋሽ ባንክ፣ ዳሸን ባንከ፣ ኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ፣ ወጋገን ባንክና አቢሲኒያ ባንክ እንደቅደም ተከተላቸው ከፍተኛ የቅርንጫፍ ብዛት ያላቸው ባንኮች ናቸው፤ እነዚህ ባንኮች 50.45% የሚሆነውን የግል ባንኮች የቅርንጫፍ ብዛት ይይዛሉ፡፡ይሁን እንጂ ከሀገራችን ቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት አንጻር ሲታይ የቅርንጫፎች ስርጭትያልተስተካከለ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት 35% የሚሆኑት ቅርንጫፎች የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡

የቅርንጫፍ ስርጭት አለመመጣጠን ብቻ ሳይሆን የባንኮች ተደራሽነትም እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የዓለም ባንክ በሚለካበት የባንክ ቅርንጫፍ በ100,000 ሰዎች ምጣኔ ሲለካ እጅግ አናሳ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ መሄዱን ከስዕል-1 ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ በስዕሉ እንደሚታየው እኤአ ከ2007 እስከ 2019 ባለው የ13 ዓመታት ጊዜ በ100,000 የሰዎች የቅርንጫፍ  ምጣኔ ከ0.76 ወደ 5.64 አድጓል፡፡ ይህም በአማካይ በዓመት 19% ዕድገት አስመዝግቧል ማለት ነው፡፡ 

ከላይ እንደተጠቀሰው የሀገራችን የባንክ ቅርንጫፎች ብዛትና ስርጭትሀገሪቱ ካላት ኢኮኖሚ፣ የህዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ባጠናቀቅነው የበጀት ዓመት ለ100,000 የሰዎች 5.64 የባንክ ቅርንጫፎች ነበሩን፡፡ በቆዳ ስፋት ሲታይም በ1000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት (በሙያው የተለመደው መለኪያ) ድርሻ 5.04 የባንክ ቅርንጫፎች ብቻ ናቸው፡፡ በተለያዩ ሀገራት ከዚህ የተሻለ የስርጭት ምጣኔ ተመዝግቧል፡፡ እኤአ በ2018 በተወሰደ መረጃ ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ በቅርንጫፍ የህዝብ ምጣኔ በ23ኛ ደረጃ ትገኛለች፡፡ ይሁን እንጂ ከምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት አንጻር ሲታይ ብዙም የተራራቀ አይደለም፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ዓመት በ100,000 የሰዎች የባንክ ቅርንጫፍ ምጣኔ ጅቡቲ (7.28)፣ ሩዋንዳ (5.75)፣ ኬንያ (5.03)፣ እና ቡሩንዲ (3.17) ላይ የገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ ከአፍሪቃ 10 ከፍተኛ የቅርንጫፍ ምጣኔ ያላቸው ሀገሮች የሚከተሉት ናቸው፤ሲሺልስ (50.6)፣ ኬፕ-ቬርዴ (33.01)፣ሞሮኮ (24.87)፣ ቱኒሲያ (22.04)፣ሳኦ-ቶሜ (20.58)፣ ሞሪሸስ (17.13)፣ ናሚቢያ (14.70)፣ ደቡብ አፍሪቃ (10.2)፣ አንጐላ (9.46) እና ጋቦን (9.23)፡፡

 

በሌላ በኩል ደግሞ በ100,000 የሰዎች የባንክ ቅርንጫፍ ምጣኔ ማነስ ወይም መብዛት በአንድ ሀገር ካለው የባንክ ቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር የሚታይ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኤቲኤም አገልገሎት፣ የሞባይል ባንኪንግ፣ የኢንተርኔት ባንኪግ እና የኤጀንት ባንኪንግ መስፋፋት የባንክ ቅርንጫፍ አስፈላጊነትን ቀንሶታል፡፡ ከዚህ አንጻር በባንክ ቴክኖሎጂ የገፉ ሀገራት የባንክ ቅርንጫፍ ምጣኔአቸው እየቀነሰ እንደሚሄድ ይገመታል፡፡

የዓለም ባንክ የኤቲኤም አገልገሎት መስፋፋትን እንደ አንዱ የባንኪንግ የቴክኖሎጂ ዕድገት መለኪያ ይቆጥረዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሀገራት በ100,000 ሰዎች የሚደርሳቸውን የኤቲኤም ማሽን ምጣኔ ብዛት መሰረት በማድረግ ይመደባሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጀ መሰረት እኤአ በ2018 መጨረሻ  4220 የኤቲኤም ማሸኖች አገልግሎት ላይ እንደዋሉ ያስረዳል፡፡ ይህም 3.86 ማሸኖች ለ100,000 ሰዎች ማለት ነው፡፡በቆዳ ስፋት አንጻር ሲከፋፈል 3.82የኤቲኤም ማሸኖች በ1000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ተሰራጭተዋል ማለት ይሆናል፡፡ እነዚህ አሀዞች ሀገራችን በዝቅተኛ የባንክ ቴክኖሎጂ ደረጃ እንዳለች ይጠቁማሉ፡፡ እኤአ በ2018 የዓለም ባንክ ባቀረበው የ146 ሀገሮች የኤቲኤም መረጃ መሰረት ኢትዮጵያን 142ኛ ደረጃ ትመደባለች፡፡ የተሻለ የቴክኖሎጂ አቅም የፈጠሩ 5ቱ የአፍረቃ ሀገራት ደቡብ አፍሪቃ (66.66) 44ኛ፣ ኬፕ-ቨርዴ (50.03) 65ኛ፣ ሞሪሸስ (43.20) 75ኛ፣ ቱኒዚያ (30.67) 100ኛ እና ሞሮኮ (27.77) 105ኛ በዝርዝሩ ይገኙበታል፡፡ በዚህ መረጃ 29 የአፍሪቃ ሀገራት የተወዳደሩ ሲሆን በዚህ ውድድር ኢትዮጵያን ከአፍሪቃ 27ኛ ደረጃ ያስቀምጣታል፡፡ በውድድሩ ከገቡት 6 ከምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት ጋር ሲወዳደር ደግሞ ከአንጎላ(18.85)፣ከግብጽ (18.59)፣ ከኪንያ (9.2)፣ ከሩዋንዳ (5.17) እና ከኡጋንዳ (4.18) ቀጥላ በ6ኛ ደረጃ ኢትዮጵያ (3.86) ተቀምጣለች፡፡

 

ማጠቃለያ

ከላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት እጅግ ዝቅተኘኛ ነው፡፡ ከጉረቤት የአፍሪቃ ሀገራት አንጻርም ሲገመገም የመጨረሻውን ደረጃ ይይዛል፡፡ ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ የመንግስትና የፋይናንስ ተቋማት ትኩረት ማነስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በመጀመሪያ ሊጠቀስ የሚገባው መንግስት ለዘርፉ ላለፉት ዓመታት የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ ነው፡፡ከ1995 ወዲህ የፋይናንስ ሥርዓቱን ገበያ-መር ለማድረግ ቢሞከርም የተደረሰበት የዕድገት ደረጃ ከተጓዝነው ዓመታት ጋር ሲነጻጸር አመርቂ አይደለም፡፡ በመጠኑም ቢሆን የተሻለ ጥረት የተደረገው የፋይናንስ ተቋማት  (ባንክ፣ መድን፣ ብድርና ቁጠባ እና ማይክሮ ፋይናንስ)  በግል ባለሀብቶች እንዲመሰረቱ የተደረገው ጥረት ነው፡፡ በፋይናንስ ገበያው በኩል ምንም አመርቂ ስራ አልተሰራም ለማለት ይቻላል፡፡ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም በተለያየ ጊዜ ቢሞከርም ጠቀሜታውን አሳንሶ በማየት እሳከሁን ሊመሰረት አልቻለም፡፡

ሁለተኛው በዘርፉ ያሉት የፋይናንስ ተቋማት  (ተዋናዮች) ዘርፉን ለማሳደግ ቀናኢ አለመሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ምክንያት የሚከተሉትን ነጥቦች በዝርዝር ማንሳት አስፈላጊ ይሆናል፡፡

  1. ቴክኖሎጂ ላይ በቂ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ ያስፈልጋል፡፡ በስራ ላይ ያሉት የፋይናንስ ተቋማት በተለይም ባንኮች ትርፋማ የመሆናቸውን ያህል በባንክ ቴክኖሎጂ ላይ በበቂ ሁኔታ መዋዕለ-ንዋይ ባለማፍሰሳቸው (ውጤታማ የሆነ ኢንቨስትመንት)፤ ህዝቡም የሚጠብቀውን ያህል ከባንክ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አልሆነም እነሱም ዘመናዊነትን በበቂ ሊላበሱ አልቻሉም፡፡

 

  1. ለባለሙያው ጊዜው የጠየቀውን ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የፋይናንስ ተቋማት በተለይም ባንኮች ለሰራተኞቻቸው ስልጠና የሚሰጡት ተገደው እየሆነ መጥታል፡፡በዚህ ምክንያት ብሔራዊ ባንክ 2% ዓመታዊ ወጫቸውን ለሰራተኛ ስልጠና እንዲያውሉ መመሪያ አስከማውጣት አድርሶታል፡፡ ለዚህ እውነታ መመሪያውን ተግባራዊ ያላደረጉ ሰባት ባንኮች መቀጣታቸውን ፎርቹን እኤአ በኦክቶበር 27 ቀን 2018 ባተመው ዜና አስነብቦናል፡፡ መመሪያውን አክብረው ያሰለጠኑትስ እውን ስልጠናው ፍሬ አፍርቶ ይሆን? መፈተሸ አለበት፡፡ ምክያቱም በየባንኮቹ ስንገለገል የአስራርም ሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ብዙም አይታይም፡፡ እንደ ትላንቱ ዛሬም ባንኮች “አበዳሪ” እንጂ የ”ኢንቨስተርነት” ስሜት ሲሰማቸው አይስተዋልም፡፡

 

  1. የፋይናንስ ተቋማት በተለይም ባንኮች ለተከታታይ ዓመታት ትርፋማ በመሆናቸው “ምቾት-ክልል” (Confort Zone) መግባታቸው ለዕድገት እንቅፋት ሊሆን እደሚችል የተቋማት ባሕርይ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በርግጥም የመንግስት ጥብቃ (ከለላ) የተደረገለት የንግድ መስክ መሆኑ የ“ምቾት-ክልል”ውስጥ እንደሆነ ቢታሰብ አያስገርምም፡፡

 

  1. የገበያ ፍክክሩ በተመሳሳይ ደረጃ ባሉ ባንኮች መካከል በመሆኑ፤ የሰው ኃይሉም ሆነ የአስራር ስርዓቱ ተመሳሳይ (አንድ ዓይነት) በመሆናቸው ደንበኛው የሚያገኘው የተለየ ጥቅም የለም፡፡ በሌላ አገላለጽ አሁን ያሉት የፋይናንስ ተቋማት በስራ አዳዲስ ሀሳብ (አገልግሎት) ማፍለቅ አይታይባቸውም፡፡ አሁን ገበያ ላይ ያሉት ዋናዎቹ አገግሎቶች (በኤሌክተሮኒክስ ከተቀየሩት በስተቀር) በሀገራችን ከ50 ዓመታት በላይ የቆዩ ናቸው፡፡

 

  1. ከአንዱ ተቋም ወደ ሌላ ተመሳሳይ ተቋም ከፍተኛ የሆነ የሰራተኞች ፍልሰት ሌላው የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ በመጠኑም ቢሆን የተረጋጋ ሰራትኛ አለመኖር ለዕድገት አሉታዊ ተጽኖ ያሳድራል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አዲስ የደሞዝ ስኬል አስጠንቶ ወደተገበረ ባንክ የሌሎች ባንክ ሰራተኞች ፍልስት እየተለመደ መጧል፡፡ ይህን ፍልሰት በተሻለ ማበረታቻ ማስቆም ካልተቻለ ሁሌም በለቀቁት ሰራተኞች ቦታ አዲስ ሰራተኛ ማሰልጠን ለእድገት የሚደረገውን ጉዞ ያዘገየዋል፡፡

 

የሀገራችን የቴሌኮምና የመብራት ኃይል መሰረተ ልማቶች ጠንካራ አለመሆን፣ የቅርንጫፍ ባንኮች ኪራይ ዋጋ እየናረ መሄድ … ወዘተ ተጨማሪ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡

አሁን ያለንበትን ዘመን ስንዋጅና የጎረቤቶቻችንን የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት ስንቃኝ፤ የሀገራች ፋይናንስ ተቋማት የፈተና ጊዜ መጀመሪያ ሩቅ እንደማይሆን እንገምታለን፡፡ የሀገራችን የአክሲዮን ገበያ መከፈት፣ የአፍሪቃ የንግድ ቀጠና ስራ መጀመር፣ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አባል መሆን፣ ምናልባትም የውጭ ሀገር ባንኮች በሀገራችን ስራ የሚጀምሩበት ሁኔታ መመቻቸት…ወዘተ አሁን ከለመድነው የ“ምቾት-ክልል” የሚያወጣን ይሆናል፡፡ ያኔ ድግሞ ራስን ፈትሾና አስተካክሎ ገበያው የሚጠይቀውን አሟልቶ ለመጓዝ የዘገየ ይሆናል፡፡በዚህም ምክንያት ፋይናንስ ተቋማት ሳይፈልጉ መዋሀድ፣ ሳይፈልጉ መሸጥ ወይም መገዛት አይቀሬ ይሆናል፡፡

ስለዚህ የሀገራችን የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲያድግ መንግስትና ፋይናንስ ተቋማት ታላላቅ የቤት ስራዎችን መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡

በመንግስት በኩል ሰፊ የማሻሻያ ሥራ እየተስራ ቢሆንም ገና ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ይገመታል፡፡ለምሳሌ የሚከተሉትን ከፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት አንጻር እናንሳ፡-

(1) ግለሰቦች/ኩባንያዎች (ባንክ ያልሆኑ) የተጠቃሚ ፋይናንስ (Consumer Finance) ስራዎችን እንዲሰሩ በሩን መክፈት፣ መመሪያዎችና ደንቦች ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የኤክሳይዝ ታክስ በአዲስ መኪና ላይ ቀንሷል፡፡ አዲስ መኪና ለመግዛት የተጠራቀመ ገንዘብ የሌለው ሰራተኛ፤ ነገር ግን ነገ የመክፈል አቅም ያለው ከመኪና አምራቾች ወይም ከመኪና አከፋፋዮች በረጅም ጊዜ ወለድ ባዘለ-ብድር መኪና እንዲገዛ፤ አንዱን ብድር በሌላ ብድር የመቀያየሩንም አማራጮች ጭምር ልንፈቅድ ይገባል፡፡

(2) በመጪው ዓመታት አክሲዮን ገበያ መከፈቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢንቨስትመንት ባንክ ስራዎችን (ባንክ ያልሆኑ) ለመስራት ለሚፈልግ ግለሰብ/ኩባንያ የፈቃድ በር መክፈትና የምናስተናግድበትን መመሪያ ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

(3) በየሀገሩ ገንዘብ ያላቸው ግለሰቦች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በፋብሪካም ሆነ በእርሻ ስራ መሰማራት አይፈልጉም፡፡ ይሁን እንጂ ገንዘባቸውን ተረክቦ የሚያስተዳድርና ትርፍ የሚያመጣ ተቋም ይፈልጋሉ፡፡ በሌሎች ሀገሮች ፈንድ ማኔጀሮች ይባላሉ፡፡ በእኛ ሀገር ይህንን የንግድ ዓይነት የሚገዛ ሕግና ስርዓት የለም፡፡ዛሬ ልንጀምረው ይገባል፤ የፋይናንስ እንቅስቃሴውን ዕድገት ያፋጥናልና፡፡

(4) እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የፋይናንስ ግብይይት ስራዎች ከደንበኞች ፍላጎትና ከገበያ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የትኛው ደንበኛ የመበደር አቅም አለው፤ የትኛው የለውም፣ የትኛው ተበድሮ ይመልሳል፤ የትኛው ብድሩን ያዘገያል፤ የትኛው አይመልስም … ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ በመረጃ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ስራ የሚያከናውኑና ከፋይናንስ ተቋማት የዕለት-ከዕለት እንቅስቃሴ ጋር የሚጓዙ የተጠቃሚ ፋይናንስ ስጋት ተንታኞች (Credit Rating/Analyst) እንደ አንድ የፋይናንስ ንግድ ድርጅት ሊቋቋሙ ይገባል፡፡

ባንኮች የመጀመሪያ እርምጃቸው በሰው ኃይል ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ አሁን ያለው የኢንዱስትሪው የሰው ኃይል በብዛትም በጥራትም ከምናስበው ዕድገት አንጻር በቂ አይደለም፡፡ ብዙ መሰራት አለበት፡፡ ሌላውና መሰረታዊው በባንክ ቴክኖሎጂ የሚደረገው ግስጋሴ ነው፡፡ ይህ የባንክ ቴክኖሎጂ አስፈላጊነት ባንኮቹን ለማዘመን ብቻ ሳይሆን፤ የህልውናቸው ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ በየዓመቱ ከትርፉ እየተወሰደ በቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ የግድ ይላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፡፡

        መሐሪ መኰንን(ዶ/ር) በፋይናንስና ኢንቨስትመንት ሙያ የሙሉ ጊዜ አማካሪ፤እንዲሁም

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በድኅረ-ምረቃ ፕሮግራሞች በመምሕርነት ያገለግላሉ፡፡በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

ማንበብ ይቀጥሉ
ShareTweetShare

ተዛማጅ Posts

2013 በጀት ዓመት
ምጣኔ ሀብት

ለ2013 በጀት ዓመት ከ476.3 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ቀረበ

በ ታምሩ ጽጌ
June 2020
0

የሚኒስትሮች ምክርቤት ለ2013 በጀት ዓመት 476,012,952,445 ብር ረቂቅ በጀት እንዲያጸድቅለት፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ግንቦት 29 ቀን 2012 ዓ.ም ውሳኔ አሳልፎ ልኳል። ምክር ቤቱ ለፌደራል መንግስት መደበኛ ወጪ...

ተጨማሪ ያንብቡ
ኮቪድ-19 የፈጠረው ቀውስና የደቀነው የምግብ እጥረት ሥጋት

ኮቪድ-19 የፈጠረው ቀውስና የደቀነው የምግብ እጥረት ሥጋት

May 2020
የመድን ንግድ ሥራ በኢትዮጵያ ከትላንትና አስከ ነገ

የመድን ንግድ ሥራ በኢትዮጵያ ከትላንትና አስከ ነገ

April 2020
ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ የሚፈልገው የግንባታ ኢንዱስትሪ

ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ የሚፈልገው የግንባታ ኢንዱስትሪ

March 2020
በሠራተኛው ጉልበት ከተመዘገበው ይልቅ በመንግሥት ወጪ የተገነባው የኢኮኖሚ ዕድገት

በሠራተኛው ጉልበት ከተመዘገበው ይልቅ በመንግሥት ወጪ የተገነባው የኢኮኖሚ ዕድገት

January 2020
Ethiopian Reporter Magazine

ሪፖርተር ሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተር

(+251) 116 61 61 81

(+251) 116 61 61 85

[email protected]

የኢትዮጵያ ሪፖርተር መጽሔት

የኢትዮጵያ ሪፖርተር መጽሔት በሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተር እየታተመ የሚወጣ ወርኃዊ መጽሔት ሲሆን፣ የሚያተኩረውም በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር መጽሔት በ ኢሜይል ለማግኘት

  • Ethiopian Reporter
  • The Reporter Ethiopia
  • Reporter Tenders
  • Ethiopian Reporter Jobs

© 2020 Ethiopian Reporter Magazine - By Media And Communications Center.

ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
  • የፊት ገጽ
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት

© 2020 Ethiopian Reporter Magazine - By Media And Communications Center.

Login to your account below

Forgotten Password?

Fill the forms bellow to register

All fields are required. Log In

Retrieve your password

Please enter your username or email address to reset your password.

Log In