አቶ ልደቱ አያሌው የአዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ላለፉት 27 ዓመታት ገዥውን ፓርቲ በመቃወም የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ታስረዋል፡፡ ተገርፈዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም. በተደረገው አገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ደግሞ ከፍተኛ ዕውቅናን አትርፈው ነበር፡፡ ቅንጅትን በመወከል በምርጫ ከተወዳደሩት የወቅቱ ዕውቅ ፖለቲከኞችም አንዱ ነበሩ፡፡ ምርጫውን በአገር አቀፍ ደረጃ ማሸነፉን ገልጾ፣ መንግሥት መመሥረት እንጂ የፓርላማ አባል መሆን እንደሌለበት፤ ከመረጠው ሕዝብ ጠይቆ የምርጫውን ውጤት፣ ‹‹አልቀበልም›› ያለውን የቅንጅት አመራር በመለየት፤ ፓርላማ በመግባታቸው ውግዘት ደርሶባቸዋል፡፡ ነገር ግን በፖለቲካው መስክ ቀዳሚ በሚባል ሁኔታ ብቃት ያላቸው ፖለቲከኛ መሆናቸውን መካድ አይቻልም፡፡ የነበረባቸውን ወቅታዊ ውግዘት ‹‹ካለመረዳት የመነጨ እንጂ፣ ሕዝብ ገብቶት የሚያደርገው አይደለም፡፡ እውነቱን ሲረዳ የእኔን ማንነት ይረዳል፤›› በማለት፣ ላለፉት 15 ዓመታትም የፖለቲካ ጉዟቸውን ቀጥለው በ2012 ዓ.ም. ይደረጋል በሚባለው አገራዊ የምርጫ ሒደት ላይም ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ የሪፖርተር መጽሔት አደባባይ እንግዳችን የመላው ኢትዮጵያውያን ፓርቲ (ኢዴፓ) ብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ልደቱ አያሌው ናቸው፡፡ በተለይ በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ታምሩ ጽጌ ከአቶ ልደቱ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ እንደሚከተለው አዘጋጅቶታል፡፡ |
ሪፖርተር፡- የተለያየ የፖለቲካ ፍልስፍና፣ ፕሮግራምና ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱ ኢዴፓ፣ ኢሃንና ኅብር ኢትዮጵያ ተጣምረው አብረው ለመሥራት ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ ይኼ እንዴት ሊሆን ቻለ? እንዴትስ ተስማማችሁ?
አቶ ልደቱ፡- ልዩነት ሊኖረን ይችላል፣ አለንም፡፡ አብሮነትን ለመመሥረት ስንስማማ ቁጭ ብለን ገምግመናል፡፡ ከግምገማ በኋላ ያገኘነው ውጤት በመካከላችን ልዩነት እንደሌለ ሚያሳይ ነው፡፡ በግምገማችን ያረጋገጥነው ነገር ቢኖር፣ አሁን የለውጡ ሒደት ክሽፈት ገጥሞታል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ከፍተኛ በሆነ የህልውና ፈተና ውስጥ ትገኛለች፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ ሆኖና የሕግ የበላይነትን ማስፈን ባልተቻበት ሁኔታ፤ ከባድ የፖለቲካ ቀውስ ባለበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ለአገሪቱ ሰላምና ህልውና አደጋ እንዳለው አምነናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓመት ‹‹ምርጫ መካሄድ የለበትም፤›› ብለን አቋም ወስደናል፡፡ ምርጫ መካሄድ አለበት ከተባለ ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ሥልጣኑን አራዝሞ ሊቀጥል አይችልም፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሁለት ዓመታት ዕድል ተሰጥቶታል፡፡ ዕድሉ ተሰጥቶት የነበረው የለውጥ ሒደቱን ውጤታማ እንዲያደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን ውጤታማ ማድረግ አልቻለም፡፡ የተሰጠውን ዕድል ውጤታማ ሳያደርግ ስለምርጫ እያወራ ነው፡፡ ሁሉንም ሊያሳምንና ሊያስማማ በሚችል መልኩ የሽግግር ሒደቱን ውጤታማ አላደረገም፡፡ ወይም የአገሪቱን የሰላምና የሕግ የበላይነት አልፈታም፡፡ ምርጫ ብቻውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ሊፈታ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ችግራችን በምርጫ የመጣ ስላልሆነ በምርጫ የሚፈታም አይደለም፡፡ ከምርጫ ያለፈ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ባደረግነው ግምገማ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ይኼንን የለውጥ ሒደት ውጤታማ የማድረግ ፍላጎትም አቅምም የለውም፡፡ ስለዚህ አንድ ሁሉን አቀፍ የሆነ የዕርቅና የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት፡፡ ቢያንስ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመታት ለሚሆን ጊዜ፣ ‹‹ምን ዓይነት የሽግግር መንግሥት? በማንስ ይመራል? ምን ዓይነት ጉዳዮችንስ ያስፈጽማል? በምን ሁኔታ ይቋቋማል?›› የሚለውን ዝርዝር ሁኔታን ይጠይቃል፡፡ እኛም ዝም ብለን ሐሳቡን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ዝርዝር የውይይት መነሻ የሚሆን ሐሳብ ለማቅረብ እየተዘጋጀን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሦስቱም ፓርቲዎች ምንም ዓይነት ልዩነት የላቸውም፣ ስምምነት ላይም ደርሰናል፡፡
ሪፖርተር፡- በለውጥ ላይ የሚገኘው ወይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጥ ሒደት ከሽፏል ብላችኋል፡፡ ለመክሸፉ የምታቀርቡት ማሳያ፣ ወይም ማረጋገጫ ምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- ጥያቄው፣ ‹‹ምን እንጠብቅ ነበር? ነው፡፡ ጥያቄው አንድ ነገር የሚለካው የተጠበቀው ነገር መሳካት ወይም አለመሳካቱን በማየትና በመፈተሽ ነው፡፡ እኔ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ 27 ዓመታት ቆይቻለሁ፡፡ አባል የሆንኩበት ኢዴፓ እንኳን 20 ዓመታት ዕድሜ አለው፡፡ በእነዚህ የትግል ዓመታት፣ ‹‹ስንጠይቀው የነበረው ምንድነው? እንዲመጣ የምንፈልገውስ ምን ነበር?፣ . . . የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ስንፈልግ የነበረው ከአንድ አምባገነን ሥርዓት ወጥተን ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ነበር፡፡ ነገር ግን ይኼ የለውጥ ሒደት ተጀመረ ሲባል የለውጥ አመራሩ ይሠራቸዋል ብለን የምንጠብቃቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ደጋግመንም ግፊት ስናደርግ ነበር፡፡ ለምሳሌ 27 ዓመታት የችግሩ አካል የነበረውና ችግሩን የፈጠረው አካል የችግሩ ብቸኛ መፍትሔ ሰጪ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም፡፡ ስለዚህ በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ኮሚሽን መቋቋም አለበት ብለን እናምን ነበር፡፡ እንዲቋቋም ስንጠይቅና ግፊት ስናደርግም ነበር፡፡ ይኼ አልተሳካም፡፡ እንዲያውም ገዥው ፓርቲ ራሱ፣ ‹‹እኔ አሸጋግራችኋለሁ›› ብሎ በተለመደው አስተሳሰቡ ቀጠለ፡፡ የጋራ የሆነ የሽግግር ተቋም ከተቋቋመ በኋላ በዚያ ውስጥ የታቀፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራድረው አንድ ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) መውጣት ነበረበት፡፡ የሽግግር ወይም የለውጥ ሒደቱ አስቀድሞ በተዘጋጀና በተጻፈ ኦዲት ሊደረግ በሚችል ፍኖታ ካርታ መመራት ነበረበት፡፡ ይኼንንም ጥያቄ ያቀረብን ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሌላው የፖለቲካ ቅራኔዎቻችን የመነጩት ከመዋቅራዊ ችግር ነው፡፡ ከሕገ መንግሥትና ብሔር ተኮር ከሆነው የፌዴራል አደረጃጀት፡፡ ስለዚህ እነዚህ መዋቅራዊ ችግሮች መዋቅራዊ በሆነ አሠራር ወይም አደረጃጀት መፈታት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ ሕገ መንግሥት የማሻሻያ ሥራ አልተካሄደም፣ ብሔር ተኮር የሆነውን የፌዴራል አደረጃጀቶችንም ለማሻሻል የተሠራ ሥራ የለም፡፡ በዚህ አገር ጤናማ የሆነ የፖለቲካ ሒደት እንዲኖር ከተፈለገ፣ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ የምርጫ ሁኔታ እንዲኖር ከተፈለገ ብሔራዊ ዕርቀ ሰላም መውረድ አለበት፡፡ አንፃራዊ የሆነ የፖለቲካ መግባባትና አገራዊ መግባባት መምጣት ቢኖርበትም አልመጣም፡፡ የሆኑ ኮሚሽኖች እዚህም እዚያም ቢቋቋሙም ምን እየሠሩ እንደሆነ እንኳን ሕዝብ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ተጨባጭ የሆነ የሠሩት ነገር የለም፡፡ ወደ ምርጫ ከመሄዳችን በፊት የፖለቲካ ምኅዳሩ ለሁላችንም እኩል የሚያሳትፍና የሚያሠራ መሆኑን መተማመን አለብን፡፡ ነገር ግን በቂ ዝግጅት አልተደረገም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራድረን መተማመን ላይ አልደረስንም፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሳይካሄዱ ነው ወደ ምርጫ እየሄድን ያለነው፡፡ በምርጫ የሚቋቋመው ቋሚ መንግሥት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የለውጥ ሒደት የሚባል ነገር የለም፡፡ የተመረጠው ፓርቲ ነው የራሱን አጀንዳ ወደ ተግባር የሚቀይረው፡፡ ስለዚህ የለውጡ ኃይል እነዚህን ጉዳዮች መፈጸምና ማሳካት ሲገባው ባለማድረጉ ነው ከሽፏል የምትለው፡፡ እንዲያውም ሕዝብ የሰጠውን አደራ ትቶ በማግሥቱ የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ ገባ፡፡ አይደለም የአገሪቱን ችግር ሊፈታ ቀርቶ፣ ራሱ ወደ መፍረክረክና ወደ ቅራኔ ነው የገባው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቅራኔ ውስጥ በመግባቱ የአገሪቱ የለውጥ ሒደት ሊከሽፍ ችሏል፡፡ ራሱ እየፈረሰ ያለ ድርጅት፣ ራሱ በቅራኔ ውስጥ ያለ ድርጅት ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን፣ ዘላቂ የሆነ መዋቅራዊ የፖለቲካ ሽግግር ሊያመጣ አይችልም፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በአብዛኛው አካባቢ ሊባል በሚችል ሁኔታ ሰላም ደፍርሷል፣ አንድነት ጠፍቷል፡፡ ሰላምና አንድነት ሳይኖር ደግሞ ምርጫ ማድረግ ለይስሙላ በመሆኑ ምርጫው መካሄድ እንደሌለበት ከ70 በላይ የሚሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እየተቃወሙ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲን ጨምሮ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ምርጫው መደረግ አለበት፣ ሕገ መንግሥቱ ይከበር እያሉ ነው፡፡ እናንተ ደግሞ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት እያላችሁ ነው፡፡ እነዚህን የተለያዩ ሐሳቦች እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?
አቶ ልደቱ፡- በትግራይ ክልል ምርጫ ማካሄድ ይቻላል፡፡ በጣም ጠንካራ የሆነና ምርጫን በአፈና ማሸነፍ የሚችል ፓርቲ አላቸው፡፡ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት በትግራይ ውስጥ አለ፡፡ ስለዚህ ትግራይ ውስጥ ምርጫ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ትግራይ ማለት ግን ኢትዮጵያ ማለት አይደለም፡፡ ትግራይ ውስጥ ያለና የአገር ኃላፊነት ይሰማኛል የሚል አንድ ድርጅት፣ ትግራይ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ስለቻለ፤ በመላው ኢትዮጵያ ምርጫ መካሄድ አለበት ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ትክክልም አይደለም፡፡ አጠቃላይ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መገምገም አለበት፡፡ ‹‹ምርጫ ማካሄድ እንችላለን? አንችልም?›› የሚለውን በአራቱም አቅጣጫ መፈተሽ አለበት፡፡ ሕወሓት ግን ለራሱ ቡድን ጥቅም ብቻ ወይም ለትግራይ ብቻ በመቆም፣ ‹‹ምርጫ መካሄድ አለበት፤›› ይላል፡፡ ይኼ አንድ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ 45 ዓመታት የትግል ታሪክ አለኝ የሚልና 27 ዓመታት አገር ያስተዳደረ ፓርቲ ኢትዮጵያ በዚህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ ሆኖ ወደ ምርጫ ትግባ ብሎ አቋም መውሰድ ትክክል አይደለም፡፡ ሕወሓት በአንድ በኩል፣ ‹‹አገሪቱ ዓይተን በማናውቀው ሁኔታ ቀውስ ውስጥ ናት፤›› ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ‹‹ምርጫ ውስጥ መግባት አለብን፤›› ይላል፡፡ ምርጫ ሰላማዊ መረጋጋት ይፈልጋል፡፡ የአዕምሮ ነፃነትና ሰላም ይጠይቃል፡፡ በአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ አንድ አገር አይደለም ቀውስ ውስጥ ሆኖ አንፃራዊ ሰላም ሆኖ እንኳ ወደ ምርጫ ሲሄድ ግጭት የመምጣቱ ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ለምሳሌ ኬንያና ኡጋንዳ ላይ ከእኛ የተሻለ ሰላም አላቸው፡፡ ነገር ግን ምርጫ ሲመጣ ግጭት ይከሰታል፡፡ ምክንያቱም ምርጫው ለሥልጣን ፉክክር የሚደረግበት መድረክ ነው፡፡ ሕወሓት ብቻ ሳይሆን አንዳንድ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምርጫ መደረግ አለበት እያሉ ነው፡፡ በጣም የሚገርመው በአሁኑ ጊዜ ላንጋኖ፣ ሶደሬና ሌሎች መዝናኛ ቦታዎች እንኳን ሰው ተዝናንቶ የሚመጣበት ሁኔታ የለም፡፡ በአዳማ፣ ቢሾፍቱና ሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች ሰዎች በአደባባይና በጠራራ ፀሐይ ከተገደሉ እኮ ሁለት ወራት አልሞላቸውም፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው? ምርጫ የአዕምሮ ዝግጅትና ሰላም ይፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ምርጫ ሲገቡ ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ለመሸነፍም ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ አሁን ባለው የብሔርተኝነትና የጽንፈኝነት ክረትና ጡዘት ግን ዝግጁ የሆነ ፓርቲ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥት ሕግና ሥርዓትን የማስከበር አቅም እንደሌለውም ማወቅ አለብን፡፡ እያስከበረም አይደለም፡፡ በየአካባቢው ያለ የጎበዝ አለቃ የፈለገውን ማድረግ የሚችልበት አገር ውስጥ ነን፡፡ ከታች ያሉት የመንግሥት መዋቅሮች በዞንም ሆነ በቀበሌ የፈረሱበትና እንዳሉ የማይቆጠርበት ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡ ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን እንዴት ነው ምርጫ የምናካሂደው? አይደለም ምርጫ ሕዝብና ቤትን እንኳን መቁጠር አልቻልንም፡፡ ሕዝብና ቤት ቆጠራ የቀረው፣ ‹‹ብጥብጥ ይፈጠራል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለራሳቸው ጥቅም ያውሉታል፣ ፖለቲካ ይዘት እንዲኖረው ያደርጉታል፤›› ተብሎ አይደል እንዴ? ታዲያ ሕዝብና ቤት መቁጠር ካልተቻለ፣ እንዴት ለሥልጣን የሚያበቃውን ምርጫ ማካሄድ ይቻላል? እንደ ፖለቲካ ድርጅት ከቡድን ስሜትና ፍላጎት አንፃር ሳይሆን ማየት ያለብን ከአገር ህልውና አንፃር ነው፡፡ የሚታዩት ምልክቶች አሳሳቢ በሆኑበት ሁኔታ እንደ ቀልድ ምርጫ ውስጥ መግባት በእሳት መጫወት ነው፡፡ ትልቅ የሆነ የፖለቲካም እብደት ነው፡፡ ይኼንን የምንለው እኛ ብቻ አይደለንም፡፡ International Crises Group (ICG) በዓለም ውስጥ ምርጫ ከሚደረግባቸው አሥር አገሮች ውስጥ፣ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ከፍተኛ ግጭት ውስጥ እንደሚገቡና ኢትዮጵያም አንዷ መሆኗን ባደረገው ቅድሚያ ጥናት አረጋግጧል፡፡ ከአፍጋኒስታንና የመን ቀጥሎ በሦስተኛነት አስቀምጧታል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ውስጥ አስተያየት የማይሰጡት ቻይናዎች ሳይቀሩ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡ ይኼ ጉዳይ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡ ከውጭ ያሉት ይኼንን ያህል ከተገነዘቡ እኛ ውስጡ ሆነን ይህንን መገንዘብ እንዴት ያቅተናል? አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ ባለቤት በሆኑበት ሁኔታ ምርጫ ውስጥ ዝም ብሎ ገብቶ ማበድ ሩዋንዳን መርሳት ነው፡፡ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ተፅዕኖ በሚፈጥሩበት ወቅት ላይ ሆነን፣ የምርጫ ቅስቀሳ ቢጀመር ይህ ሁሉ ጽንፈኛ ኃይል፣ ‹‹የምረጡኝ›› ቅስቀሳ ሲያደርግ ሚዲያውን መቆጣጠር እንችላለን? እንደ አገርም፣ እንደ መንግሥትም፣ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲም ሆነ እንደ ሕዝብ አልተዘጋጀንም፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ እንደ ምርጫ ቦርድም አልተዘጋጀንም፡፡ ምርጫ ቦርድ ካለፉት ምርጫዎች የተሻለና የተለየ ምርጫ ማድረግ ካለበት ምርጫ አስፈጻሚዎች መልምሎና አሥልጥኖ ማሰማራት ነበረበት፡፡ ይኼንን አላደረገም፡፡ታዛቢዎች በሕዝብ ተመርጠውና ሠልጥነው መዘጋጀት ነበረባቸው፡፡ አልተደረገም፡፡ ምርጫ ቦርድ አይደለም በዚህ ደረጃ የክልል የቢሮ ኃላፊዎችን ቀጥሮ አልጨረሰም፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ይችን ትልቅ አገርና መሠረተ ልማት እንደ ልብ በሌለበት ሁኔታ ምርጫ ማድረግ የሚቻለው? አዋጁን ተከትሎ 20 መመርያዎች መውጣት አለባቸው፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቁጭ ብለው ተነጋግረው መተማመን ያለባቸው ብዙ አጀንዳዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ አልተሠሩም፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ብንወስድ ሰርተፊኬት ያላገኙ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ትልቁ ፓርቲ የሚባለው ብልፅግና ፓርቲ እንኳን ከተቋቋመ ሁለት ወራት አልሞላውም፡፡ የፖለቲካ ፕሮግራሙን ለሕዝብ አይደለም ለራሱ አባሎች ማወያየት የጀመረው አሁን ነው፡፡ እንደ ፓርቲ እንኳን ሳይቆም እንዴት ነው ምርጫን የምናስበው? ወይስ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ ዓለም ባንክን፣ አሜሪካንንና አውሮፓ ኅብረትን ለማስደሰት በአገርና ሕዝብ መቀለድ አለብን? ይኼ ሊሆን አይችልም፡፡
ሪፖርተር፡- ‹‹ምርጫ መደረግ አለበት›› በሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚነሳ የሕግ ጉዳይ አለ፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመቱ በምርጫ መቀየር አለባቸው ስለሚል ምርጫው በሕግ አስገዳጅነት መካሄድ አለበት፡፡ በሌላ በኩል ምርጫው ተካሄደም አልተካሄደ አሁን ያለው ሁኔታ ወደ ትርምስና ግጭት የሚያመራበት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ በመሆኑ የሕዝቡንም አዕምሮ ወደ ምርጫ ማዞርና ትኩረቱን ማስቀየር ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ የእርስዎ አመክንዮ ምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- ሁለቱም ውኃ የማይቋጥሩ ክርክሮች ናቸው፡፡ ስለሕገ መንግሥቱ የተነሳው ጉዳይ ነገሩ ላልገባው ትርጉም የሚሰጥ መከራከሪያ ይመስላል፡፡ ግን ትልቅ ስህተት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ ‹‹ምርጫ መካሄድ ያለበት ለአምስት ዓመት ብቻም ሳይሆን፣ አንድ መንግሥት ከምርጫ ውጪ በሌላ የኃይል አማራጭ ከሥልጣን ሊወርድ አይችልምም፤›› ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአገሪቱ የሚሠራ ቢሆንና ይኼ መንግሥት ያለው ቅቡልነት (Legtmecy) የተመሠረተው በአምስት ዓመታት ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት ሦስት፣ አራት ዓመታት አመፅ ማመፅ አልነበረበትም፡፡ ወይም አመፁ የአገር ክህደት (Treason) ነበር የሚሆነው፡፡ እሱ ደግሞ ወንጀል ስለሆነ 25 ዓመታት በእስር ያስቀጣል፡፡ ይኼ መንግሥት መንግሥት የሆነው በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አይደለም፡፡ በአፈና ነው፡፡ አሁን ያለው የለውጥ ኃይል ቅቡልነት (Legtimacy) የተመሠረተው ባለፈው አምስት ዓመታት በተደረገው ምርጫ አይደለም፡፡ ቅቡልነቱ የተመሠረተው ይቅርታ ስለጠየቀ፣ ከልቡ መፀፀቱን ስለገለጸ፣ ‹‹ተለውጫለሁ፤›› እና ‹‹በጥልቀት ለመታደስ ተዘጋጅቻለሁ›› ስላለ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ቃል ስለገባ ሕዝቡ የሰጠው ሁለተኛ ዕድል ነው፡፡ ስለዚህ መመዘን ያለባቸው ለሕዝቡ ከገቡት ቃል አንፃር ቃል የገቡትን የለውጥ ሒደት ተግባራዊ አድርገውታል ወይስ አላደረጉትም በሚለው ነው፡፡ እኛ እያልን ያለነው፤ ቃል የገቡትን የለውጥ ሒደት ተግባራዊ ስላላደረጉት፣ ምርጫ ከመደረጉ በፊት የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ነው፡፡ ይኼ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት ወደ ቅድመ 2007 ዓ.ም. ምርጫ መመለስ ነው የሚሆነው፡፡ መቶ በመቶ በምርጫ ድል ያደረገ መንግሥት ተመልሶ ወደ አመፅና ተቃውሞ ሲገባ ወራትን እንኳን አላስቆጠረም፡፡ ይኼ የሚያሳው የኢትዮጵያ ችግር የመጣው በምርጫ አለመሆኑንና መፍትሔም የሚያገኘው በምርጫ አለመሆኑን ነው፡፡ ከምርጫ በፊት አገሪቷ ላይ በሚታዩ ሁሉም ዓይነት ጉዳዮች ላይ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍትሔ ማምጣት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ ከሕግ ጋር አያይዞ የአምስት ዓመታት ኮንትራት ሊያልቅ ስለሆነና ከዚያ በኋላ ሕጋዊ መንግሥት ሊኖር አይችልም የሚሉ ሰዎች ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በተዘዋዋሪ እያሉን ያሉት፣ አሁን ያለው መንግሥት ሕጋዊ ነው እያሉን ነው፡፡ ለእኔ ይኼ የለውጥ ሒደቱን መካድ ነው፡፡ ሕዝቡ መስዋዕትነት ከፍሎና ኢሕአዴግን አሸንፎ ያመጣውን የለውጥ ሒደት መካድ ነው፡፡ ሕግ ቢኖርማ ኖሮ አመፅ ሳያስፈልግ በአምስት ዓመታት ውስጥ መንግሥት በምርጫ ይለወጥ ነበር፡፡ ያ አልሆነም፡፡ ኢሕአዴግ ከጫካ በ1983 ዓ.ም. ደርግን አሸንፎ ሲገባ፣ የደርግ ሕገ መንግሥት ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ቀዳዶ ጥሎ የራሱን ሕገ መንግሥት ነው ያፀደቀው፡፡ ‹‹የደርግ ሕገ መንግሥት ሕግ ነውና ማክበር አለባችሁ፣ መሻር አትችሉም›› አልተባለም፡፡ የለውጥ ሒደት ሁል ጊዜ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ይህም የለውጥ ሒደት ሕዝቡ አሸንፎና እነሱ ተሸንፈው የመጣ ለውጥ ነው፡፡ ለውጡ ከመጣ በኋላ ሕጋዊ ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ ሕጋዊ ቢሆን ኖሮማ እንደዚህ ያለ ሕዝባዊ አመፅ አይነሳም ነበር፡፡ መጀመርያ ማመን ያለበት ሕጋዊ አለመሆኑን ነው፡፡ በምርጫ እንዳልመጣ (የለውጥ ሒደቱ) ማመንና ሕዝቡ የከፈለውን ዋጋ ማክበር አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ ክልሎች የራሳቸውን የፀጥታ አስከባሪ ኃይል (ልዩ ኃይል እያሉ) በማጠናከር፣ ጉልበታቸውን በማፈርጠምና ራሳቸውን እንደ ሉዓላዊ አገር በማየት ለፌዴራል መንግሥቱ አለመታዘዝ ደረጃ ላይ የደረሱበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ይህ የሚያሳው የአገሪቱ ፖለቲካዊ መዋቅር ፌዴራላዊ ሳይሆን ኮንፌዴራል መሆኑን ወይም መቀየሩን ማሳያ እንደሆነ እናንተን ጨምሮ የተለያዩ ምሁራን እየተናገሩ ነው፡፡ ይኼንን ጉዳይ እስኪ ያብራሩልኝ?
አቶ ልደቱ፡- ችግሩ የክልሎች አይደለም፡፡ የሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው ሕገ መንግሥት የፌዴሬሽን ሳይሆን የኮንፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት በመሆኑ ነው፡፡ ያኔ የሆነው አንድ ጡንቻ ያለው ገዥ ፓርቲ፣ በፓርቲ ማዕከላዊነት ሥልጣኑን ሁሉ በብቸኝነት ይዞ አሻንጉሊት ክልሎችን የሚያስተዳድርበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡ ይኼ የኮንፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት በተግባር የሚተረጎምበት ዕድል አልነበረም፡፡ ያ ጠንካራ ይባል የነበረው አምባገነን መንግሥት ሲፈርስ ሕገ መንግሥቱ በተግባር የሚተረጎምበት ዕድል አገኘ፡፡ የኮንፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት መሆኑ ይፋ ወጣ፡፡ ደካማና የተበተነ ማዕከላዊ መንግሥት በመፈጠሩ፣ ጉልበተኛና ጡንቻ ያላቸው ክልሎች መታየት ጀመሩ፡፡ ይኼ የክልሎች ሳይሆን የሕገ መንግሥቱ ውጤት ነው፡፡ ‹‹27 ዓመታት ሙሉ በዚህ ሕገ መንግሥት ሄደን፣ ሄደን እንፈርሳለን እንጂ አገራዊ አንድነታችን አይጠናከርም፤›› እያልን ስንከራከር የኖርነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ መጀመርያውኑ ሲፀድቅ ታቅዶ የኮንፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት ተደርጓል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በተግባር በሥራ ላይ መዋል ሲጀምር የአገርን ህልውና አደጋ ላይ እንደሚጥል እርግጠኞች ነበርን፡፡
ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱን ‹‹የኮንፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት ነው›› የሚያስብሉት ሁሉም ድንጋጌዎ ናቸው?
አቶ ልደቱ፡- ሁሉም ድንጋጌዎች (አንቀጾች) አይደሉም፣ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ አብዛኛው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያለው ድንጋጌ እኮ ከዓለም አቀፍ ሁኔታ የተቀዳ ነው፡፡ ማንም መንግሥት ቢመጣ ይዟቸው የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ እኛ መንግሥት ብንሆን 75 በመቶ የሚሆነውን ድንጋጌ ይዘን ነው የምንቀጥለው፡፡ በጣም መሠረታዊ የሆኑ፣ የኢትዮጵያን አገራዊ ህልውና አደጋ ውስጥ ያስገቡና ዘላቂ የኢኮኖሚ ብልፅግናን ችግር ውስጥ የሚከቱ አንቀጾች አሉ፡፡ እነዚያ አንቀጾች ናቸው ችግር እየፈጠሩ ያሉት፡፡ ከመቅድሙ (Preample) ጀምሮ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ የኮንፌዴራሊስት ኃይሎች የሚባሉት የብተና ኃይሎች ናቸው፡፡ እኛ ሕዝቡ የማያውቀውን እንዲያውቅ ‹‹የኮንፌዴራሊስት ኃይሎች›› ብለን እነማን እንደሆኑ አሳወቅን እንጂ እነሱ፣ ‹‹የፌዴራሊስት ኃይሎች ነን›› ቢሉም በውስጣቸው ግን ኮንፌዴራሊስት መሆናቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ሁልጊዜ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው የሚመሠረተው ‹‹በአንድነታችንና አብሮነታችን›› ላይ ሳይሆን በልዩነታችን ላይ ነው፡፡ ጠንካራ የሆነ የፌዴራል መንግሥት እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ በጣም ደካማ የሆነ፣ በሚፈልጉት ጊዜ የሚሠሩትና የሚበትኑት የፌዴራል መንግሥት እንዲኖር ነው የሚፈልጉት፡፡ ሲመቻቸው አብረው መኖር፣ ካልተመቻቸው ደግሞ መነጠል የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ለአንቀጽ 39 የሚከራከሩት ለዚህ ነው፡፡ እነዚህ የብተና ኃይሎች የ27 ዓመታቱ የብተና ሥርዓት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት አደባባይ ወጥቶ ደረቱን ለጥይት የሰጠው የ27 ዓመታቱ ሥርዓት እንዲቀጥል ነው? 27 ዓመታት የነበረው ሥርዓት መገለጫው ሕጉና መዋቅሩ ነው፡፡ ይኼ አይቀየርም ከተባለ፣ ታዲያ ምኑ ነው የሚቀየረው? ለውጡ ምንድነው? እነዚህ ኃይሎች ካለፈው ውድቀታቸው ያልተማሩ ናቸው፡፡ የተማሩ ቢሆን ኖሮ ቆም ብለው የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላትና ስህተቶችን በማረም ‹‹አንድነታችንን የሚያጠናክር ሥራ እንሥራ›› ብለው ይቀጥሉ ነበር እንጂ፣ ለ27 ዓመታት የነበረው መዋቅር ይቀጥል ማለት፣ ሕዝቡ ያመጣውን ለውጥ ወይም ትግል መካድ ነው፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ችግር የለበትም፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀርም ችግር የለበትም፡፡ ችግሩ ያለው አፈጻጸም ላይ ነው፤›› በማለት፣ ችግሮችን ከአፈጻጸም ጋር ሊያያይዙ ይሞክራሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ትንሽም ቢሆን የፖሊሲ ፍንጭ (Clue) እንደሌላቸው ነው፡፡ የአንድ ፖሊሲ ችግር በዋናነት ፈጥጦ የሚወጣውና የሚታወቀው መፈጸም ሳይችል ሲቀር ነው፡፡ ወይም ሲፈጸም ችግር ሲፈጥር ነው እንጂ በወረቀት ላይ ያለውን ፖሊሲ ዓይቶ መስማማት ወይም አለመስማማት ይቻላል ድክመቱንና ጥንካሬውን የምትለየው መሬት ላይ አውርደህ ስትተገብረው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት ትመራበት የነበረው ሥርዓት መሬት ላይ ወርዶ ተፈትኖ ወድቋል፡፡ መልሶ ያንን ሥርዓት ለማስቀጠል መፍጨርጨር ለእኔ ከጥፋት የማያድን ግብዝነት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሕወሓት የ‹‹ፌዴራሊስት ኃይሎች››› በሚል ስብሰባዎችን በመቐለ በማካሄድ የፌዴራል ሥርዓቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና መንግሥት ኢሕአዴግን በሕገወጥ መንገድ እንዲፈርስ አድርጓል እያለ ነው፡፡ ኢሕአዴግን በሕገወጥ መንገድ ማፍረስ ደግሞ ሁሉም የመንግሥት ተመራጮች ከሥልጣን ውጪ ስለሚሆኑ አገሪቱ መሪ አልባ ትሆናለች እያለም ነው፡፡ እናንተ ደግሞ ለማስመሰል እንጂ እያካሄዱት ያሉት የኮንፌዴራሊስት ተግባራትን ነው እያላችሁ ነው፡፡ ይኼንን ያስባላችሁ ምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- የፌዴራል ሥርዓትን የጀመረችውና የተገበረችው አሜሪካ ነች፡፡ በአሜሪካ፣ ‹‹እኔ ፌዴራሊስት ነኝ›› ካልክ ‹‹የአንድነት ኃይል ነኝ›› ማለትህ ነው፡፡ ‹‹ጠንካራ የሆነ የፌዴራል መንግሥት እንዲኖር እፈልጋለሁ፡፡ ነፃነት ያላቸው ክልሎች እንዲኖሩ እፈልጋለሁ፤›› ማለት ነው፡፡ ደካማ የሆነ የፌዴራል ኃይል እንዲኖር የሚፈልግ ‹‹ፀረ ፌዴራሊስት›› ነው የሚባለው፡፡ ይኼንን የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ ወይም ‹የተኛን . . . › እንዲሉ ነው፡፡ የሚነሱት ከጠባብ አመለካከት እንጂ አገራዊ መፍትሔ ለማምጣት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ችግር የአንድን ችግር ነጥሎ በማየትና ለዚያ ብቻ መፍትሔ በማግኘት አይፈታም፡፡ የእያንዳንዱ ክልል ችግር የሚፈታው ችግሩን በአገር ደረጃ መፍታት ስንችል ብቻ ነው፡፡ የእነሱ ችግር ሁሉን ነገር የሚያዩት ከራሳቸው ጠባብ ፍላጎትና አካባቢያዊ ሁኔታ አንፃር ነው የሚያዩት፡፡ አዕምሯቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ የተቀረፀው እንደዚያ ነው፡፡ በትግራይ ውስጥ ችግር እንዳለ አምናለሁ፡፡ ያ ችግር ግን የኢትዮጵያም ችግር ነው፡፡ መፍትሔም መስጠት የሚቻለው እንደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱንም የኮንፌዴሬሽን ሕገ መንግሥት አድርገው የቀረፁትም በኢትዮጵያዊነት የመተማመን ችግር ስለነበረባቸው ነው፡፡ ተቀባይነትን አግኝተውና ገዥ ሆነው መኖር ከቻሉ፤ በኢትዮጵያዊነት አንድነት ሥር ሊኖሩ፣ በሌላ ኃይል በሰላማዊ ምርጫም ሆነ በጉልበት ከተሸነፉ ግን ለመገንጠል የሚያስችላቸውን ሕገ መንግሥት ነው የቀረፁት፡፡ ይኼ ከኮንፌዴሬሽን ኃይልነት በላይ የመበተን ኃይል ነው፡፡ እኔ የትግራይን ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡ ሕወሓት እስከመራው ድረስ ራሱን ከጥቃት መከላከል ይችል እንደሆነ እንጂ፣ ዴሞክራሲን ግን ሊያመጣ አይችልም፡፡ አገራዊ አንድነትን ሊያመጣ አይችልም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር በተያያዘ ለዚያ ኢትዮጵያዊነቱ የሚመጥን አመራር ያስፈልገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያዉያን በተለያዩ ነገሮች እርስ በርሳቸው የተጋመዱና የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በጊዜያዊ ዘራዊ ሽኩቻ የተጠላላ ቢመስልም ሊለያዩ አይችልም፡፡ በትግራይም ሆነ በኦሮሚያ የኮንፌዴራሊስት ኃይሎች የሚያደርጉ እንቅስቃሴ ከጊዜያዊ ሩጫና ዕለታዊ ግጭቶችን ከማባባስ ያለፈ ሊሆን አይችልም የሚሉ አሉ፡፡ የእርስዎን አስተያየት ምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- እኔም ያለኝ አረዳድ ኢትዮጵያውያን ህልውናችን እርስ በርሱ የተሳሰረ ነው፡፡ አንዳንዳችን ለሌላችን እናስፈልጋለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተነጥለህና ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና አግኝተህ የምትኖርበት ዕድል የለም፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ኤርትራ ነች፡፡ በጣም ብዙ ወጣቶችን ገብራ ነፃነቷን ብትቀዳጅም፣ ዛሬ ሕዝቧ ያለበትን ሁኔታ ማየት በቂ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳንንም መመልከት እንችላለን፡፡ እኔ የሚገርመኝ ከጓሯችን መማር አለመቻላችን ነው፡፡ በመነጣጠል የሚገኝ ጥሩነት የለም፡፡ በእኩልነትና አንድነት መኖር ነው ጥሩ ውጤት ያለው፡፡ በግለሰብና በቡድን ደረጃ ያለው መብት መከበር አለበት፡፡ ብሔር ተሻጋሪ የሆነን ነገር ሠርተን ለልጆቻችን ጥሩ ነገር ትተን ማለፍ እንጂ፣ ያንን እየበጣጠሱ መለያየት ላይ ማተኮር ማንንም ተጠቃሚ አያደርግም፡፡ በዚህ ዓይነት ሒደት ውስጥ ማንም አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ አይችልም፡፡ ሁላችንም ተሸናፊ እንሆናለን፡፡
ሪፖርተር፡- ፌዴራሊስትና ኮንፌዴራሊስት እያሉ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሌላ ሦስተኛና ሁነኛ አማራጭ አለ የምትሉት አካሄድ አለ?
አቶ ልደቱ፡- የእኔን አመለካከት ብነግረህ እዚህ አገር ትልቅ እንቅፋት እየሆነ ያለውና የለውጥ ሒደቱም እንዲከሽፍ እያደረገው ያለው፣ የፖለቲካ ጽንፈኝነትና ብሔርተኝነት ነው፡፡ ከዚህ ካልወጣን የትም ልንደርስ አንችልም፡፡ በድርድርና ሰጥቶ በመቀበል ፖለቲካ ማመን መቻል አለብን፡፡ ሁልጊዜ ልዩነት ላይ የሚያተኩር አካሄድ ከ1960ዎቹ ትውልዶች ጀምሮ እስካሁን ሲካሄድ የኖረ ችግር ነው፡፡ ይኼንን የጽንፍና የፖለቲካ አካሄድ ካላስወገድን በኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላምና ብልፅግና ሊኖር አይችልም፡፡ እያወራሁት ያለው ስለንዑስ ብሔርተኝነት ሳይሆን ስለኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ነው፡፡ ሁልጊዜ ‹‹የእኔ›› ለሚሉት ብሔሮች ብቻ መቆርቆርና ለሌሎቹ ቦታ ያለመስጠት አስተሳሰብ መራቅ ያስፈልጋል፡፡ ብሔርንና አገርን መውደድ በምክንያት መሆን አለበት፡፡ ለብሔርና ለአገር ተገቢ የሆነ ትኩረት መስጠት እንጂ፣ ጭልጥ ብሎ ብሔርተኛ በመሆን በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለውን ብዝኃነት መርሳትና መካድ ትክክል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የልዩነት አገር ብቻ ሳትሆን፣ የብዙ መስተጋብር አንድነት አገር በመሆኗ፣ ይኼ አንድነት ምሉዕ ሆኖ መቀጠል አለበት፡፡ እነዚህን ሁለት ጽንፍን ያሉ ልዩነቶች የሚያቻችል የፖለቲካ አስተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ ያንን አስተሳሰብ እኛ ‹‹‹ሦስተኛ አማራጭ›› ብለን እንወስደዋለን፡፡
ሪፖርተር፡- እናንተ፣ ‹‹የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት፤›› ያላችሁት ሐሳብ ተቀባይነት ቢያገኝ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጀርባ በተሰጣጡበት ሁኔታ እንዴት አንድ ሆኖ ሐሳብን ማራመድ ይቻላል?
አቶ ልደቱ፡- ያንን ማድረግ አለመቻል አማራጭ አይደለም፡፡ ግዴታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ብቃት አለን የምንል ከሆነ፣ ከራሳችን የግል ስሜትና የቡድን ፍላጎት የአገርን ጥቅም እናስቀድማለን ካልን፣ በዚህ አጀንዳ ላይ ወደድንም ጠላንም ውጤታማ መሆን አለብን፡፡ አለበለዚያ የትም አንደርስም፡፡ በሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጥያቄ ካልተስማማህ፣ ምርጫ በመሸነፍና ለማሸነፍ ልትስማማ አትችልም፡፡፡ የሚጮኽና ስሜታዊ የሚያደርግ የምርጫ ቅስቀሳ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ለአንድ ሁለት ዓመታት በአንድ ሸንጎ ዙሪያ ቁጭ ብለን የአገራችንን ችግር መፍታት አለብን፡፡ በዚህ ካልተስማማን በምርጫ ውጤት ልንስማማ አንችልም፡፡ ይኼንን ጥያቄ ማቅረባችን የተለጠጠ ሊሆን የማይችል እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፡፡ ሱዳንን እንደ ምሳሌ እናንሳ፡፡ አመፅ የተነሳው ከእኛ በኋላ በቅርቡ በዳቦ ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ ቀውስ ውስጥ ከገቡ በኋላ መፍትሔ ሆኖ የቀረበው የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ነው፡፡ ያንን ሐሳብ ተቀብለው የሽግግር መንግሥት ማቋቋም በመቻላቸው ከእኛ የተሻለ አንፃራዊ ሰላም ውስጥ ናቸው፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ ይኼንን ሐሳብ ያቀረቡት ‹‹የእኛ መሪዎች›› ናቸው፡፡ ለሱዳን የሠራው መፍትሔ ለምንድነው ለአገራቸው የማይሠራው? ወይም የማይፈልጉት? ውስብስብና የማይሳካ አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው? ተሳክቶ እያየን ነዋ! በዓረብ ስፕሪንግ ውስጥ ከነበሩት ውስጥ ቱኒዝያን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር መታየት አለበት፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላም ከመጨነቃችን የመነጨ ሐሳብ እንጂ ባንጨነቅ ኖሮ ‹‹ይለይልን›› ብለን መጨረሻውን እናይ ነበር፡፡ ስለዚህ፣ ‹‹የሽግግር መንግሥት ይቋቋም፣ምርጫ መካሄድ የለበትም፤›› ስንል ምርጫችን ሰላም ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ቀውስ የሚያመጣ ከሆነ፣ ያለምንም ጥያቄ ጦርነትና ቀውስ የሚያመጣብን ምርጫ መካሄዱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ምርጫ መደረግ አለበት፤›› የሚሉት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋምና ምርጫ እንዲራዘም እየጠየቁ ያሉት በምርጫው ለመሳተፍ ብቁ ስላልሆኑና ስላልተዘጋጁ ነው ይላሉ፡፡ እውነት ነው?
አቶ ልደቱ፡- ኢዴፓ፣ ኢሃንና ኅብር ኢትዮጵያ፣ ‹‹አብሮነት›› ን ስናቋቁም ሦስት ነገሮችን ታሳቢ አድርገን ነው፡፡ የመጀመርያው አገራችን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው እውነተኛ የፌዴራሊስት ኃይሎች ጎራ የመፍጠር ጉዳይ ሲሆን፣ ሦስተኛው ይኼ መንግሥት ‹‹አሻፈረኝ›› ብሎ ወደ ምርጫ የሚገባ ከሆነ ለማሸነፍ የሚያስችል አንድ ጠንካራ ጎራ ለመፍጠር ነው፡፡ ከዝግጀት አንፃር የሚያዩት ከሆነ በሚቀጥሉት ወራት ከማንም ያላነሰ ዝግጅት በማድረግ ከማንም ያላነሰ እንዲያውም በበለጠ ሁኔታ አሸናፊ እንደምንሆን እናሳያቸዋለን፡፡ ምርጫው አይደረግ፣ ይራዘምና የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የምንለው ከዝግጅት ማነስ አይደለም፡፡ ከአጠቃላይ አገራዊ ሁኔታ የሕግና የሰላም አንፃር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የዚህች አገር ትልቁ ችግር የ1960ዎቹ ትውልድ ነው ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ይኼንን ያስባለዎት ምን እንደሆነ እስኪ ያብራሩት?
አቶ ልደቱ፡- የአገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ የጀመረው በ1960ዎቹ ነው፡፡ ከዋለልኝ ቁንፅል የሆነ የብሔር ጭቆና ትንተና ጀምሮ እስካሁን ድረስ የአገሪቱን ፖለቲካ ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› ነው ተቆጣጥሮት የሚገኘው፡፡ የብሔር ፖለቲካ ትልቁ የአገሪቱ አጀንዳ እንዲሆን ያደረገው የ1960ዎቹ ትውልድ ነው፡፡ በእውነት የብሔር ጥያቄ ከሌሎቹ መሠረታዊ ጥያቄዎች የበለጠ ሆኖ አይደለም፡፡ ከእሱ የገዘፉና የበለጡ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ የብሔር ጥያቄ ነጥሎ ገዥ ጥያቄ እንዲሆን ያደረገው የ1960ዎቹ ትውልድ ነው፡፡ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ተከታይ የነበሩ ናቸው፡፡ ከአገሪቱ ተጫባጭ ሁኔታ ጋር የማይሄድ የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ተቀበለ፡፡ ሶሻሊዝምን ለመቀበል ግን ‹‹ወዝ አደር›› የሚባል መደብ መኖር ነበረበት፡፡ ይኼንን የባዕድ አገር ርዕዮተ ዓለም ሲወርሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ወዝ አደር›› የሚባል መደብ አልነበረም፡፡ ለትግል ለማነሳሳት ሌላ አጀንዳ መፈለግ ስለነበረባቸው ተፈልጎ የተገኘው የብሔር ጥያቄ ነው፡፡ ይኼም የብሔር ጥያቄ የተገኘው ከኢትዮጵያ ሳይሆን ከእስታሊንና ሌኒን መዝገበ ቃላት ነው፡፡ ለብሔር ጥያቄ ማነሳሳት የሚሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የተዛቡ የብሔር ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ከባህል፣ ከቋንቋና ኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ እነዚህን ከአግባብ በላይ በመለጠጥ በማጋነን፣ የተዛባ ትርክት በመስጠት የብሔር ጥያቄ ከሁሉም ጥያቄዎች በላይ ገዥ እንዲሆን አደረጉት፡፡ ትልቁ ስህተት ይኼ ነው፡፡ ስህተቱን የፈጸመው ደግሞ ያ ትውልድ ነው፡፡ ያ ትውልድ ያንን አጀንዳ እስካሁንም ይዞት ቀጥሏል፡፡ የአስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ይኼ የተንፀባረቀውም የአገሪቱ አከላለል ብሔር ተኮር መሆኑ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ብሔርተኛ ድርጅት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች ብሔርተኞች ናቸው፡፡ በዚህ ደረጃ ብሔርተኝነት ሁላችንንም ተቆጣጥሮን እያለ፣ አሁንም ትልቅ ጥያቄ ሆኖ እየቀረበ ያለው የብሔርተኝነት ጥያቄ ነው፡፡ ይኼ እየሆነ ያለው የብሔርተኝነት ጥያቄ ተፈትቷል ወይም አልተፈታም ሳይሆን፣ ይኼ ጥያቄ ሲቆም ከባህር የወጣ ዓሳ ይሆናሉ፣ ይሞታሉ፡፡ ስለዚህ ይዘውት ቀጠሉ፡፡ እስካሁን ድረስ ትልቁ ችግር የሆነብን ይኼ ነው፡፡ ያ ትውልድ ያመጣብን ብሔርተኝነትና የጽንፍ ፖለቲካ ወይ ከእኔ ወይ ከእነሱ ብቻ የሚል አማራጭ እንጂ፣ ሦስተኛ አማራጭን የማይቀበል አስተሳሰብ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ወሳኝ የመንግሥት ሰዎች የፖለቲካ ሒደቱን በዋናነት እየመሩ የሚገኙትም እነሱው ናቸው፡፡ ስለዚህ ተጠያቂዎቹ እነሱው ናቸው፡፡ ለአዲሱ ትውልድ ብሔርተኝነትንና ጽንፈኝነትን ያወረሱት እነሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይኼንን ስንል ያ ትውልድ ጠንካራ ጎን የለውም ማለት አይደለም፡፡ በጣም የሚያስቀና የአገር ፍቅር ነበረው፡፡ ላመነበት ነገር ከእኛ የተሻለ ለመሞት ቁርጠኛም ነበር፡፡ እሱን ዕውቅና መስጠት እንፈልጋለን፡፡ በፖለቲካው ያሰፈነውን ችግር ደግሞ መቀበል አለበት፡፡ መቀበል ሲችል ነው ማረም የሚቻለው፡፡ እስካሁን ግን ማረም አልተቻለም፡፡ እስካሁን የኢትዮጵያ ገዥ አስተሳሰብ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ እነሱ ግን ሁልጊዜ ለኢትዮጵያ ጉዳይ የመፍትሔ ሐሳብ አመንጪ እንደሆነ ሲናገሩና ሲኩራሩ አያለሁ፡፡ ያ ትክክል አይደለም፡፡ ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን፣ ጥፋታቸውንና ልማታቸውን አግባብ ያለው ሚዛን ላይ አስቀምጠው ራሳቸውን ማየት መጀመር አለባቸው፡፡ መፀፀትም አለባቸው፡፡ ማመን አለባቸው፡፡ በድፍረት ማመንና መወያየት ስንጀምር ነው መፍትሔ የምናመጣው፡፡
ሪፖርተር፡- ‹‹ለዚህች አገር ችግር ውስጥ መግባት ዋናው ምክንያትና ተጠያቂም መሆን ያለበት ኢሕአዴግ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ቢፈርስና ቢጠፋ የመጀመርያው ተደሳች እኔ ነኝ፤›› ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ አሁን ላይ ኢሕአዴግ መክኖ በአዲስ ፓርቲ ተተክቷል፡፡ አሁን ደስተኛ ሆነዋል?
አቶ ልደቱ፡-ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ተቃዋሚ ነኝ፡፡ ኢሕአዴግን ነው የምቃወመው፡፡ ኢሕአዴግ ቢዳከምና ቢፈርስ ሊከፋኝ አይችልም፡፡ ግን ኢሕአዴግ የሚባለው ድርጅት፤ ድርጅትንና የአገር ህልውናን፣ መንግሥትንና ፓርቲን መለየት በማይቻልበት ደረጃ ነበር ሲያስተዳደር የኖረው፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ የሚፈጠረው ችግር ለአገር የሚተርፍበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ይኼ እንዳይሆን ስለማንፈልግና ከኢሕአዴግ ነጥቆ ሥልጣን ለመያዝ የሚችል የተደራጀ ኃይል አለመኖሩንና ክፍተቱን በመረዳት፣ ኢሕአዴግ ቢያንስ ይኼ የለውጥ ሒደት እስከሚሳካ ድረስ ፍትሐዊ አንድነቱንና ጥንካሬውን ጠብቆ እንዲቀጥል እፈልግ ነበር፡፡ የአገር ህልውና ችግር ውስጥ ባለበት ሁኔታ ኢሕአዴግ መፈረካከስ ነበረበት ብዬ አላምንም፡፡ ጉዳት ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ እያመጣም እያየንም ነው፡፡ የለውጡ ኃይል ውጤታማ እስኪሆንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መግባት የሚችልበት ሁኔታ እስከሚፈጠር ድረስ የኢሕአዴግ ውስጣዊ አንድነት ጠብቆ እንዲቀጥል እፈልግ ነበር፡፡ ያ ባለመሆኑ አዝናለሁ፡፡ የሕዝቡን አደራ መወጣት ባለመቻላቸው የለውጥ ኃይሉ በመጣ ማግሥት ሽኩቻ ውስጥ ገቡ፡፡ ለውጡን ውጤታማ አድርገው ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ማሸጋገር ነበረባቸው፡፡ በውስጥ ሽኩቻ ምክንያት ፓርቲ መፍረሱ አያስደስተኝም፡፡ ይኼንን የምለው ለአገር ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው ብዬ ስለማምን እንጂ ሲያስረኝ፣ ሲገርፈኝ የነበረ ሥርዓት በመሆኑ በኖ ቢጠፋ አይከፋኝም፡፡
ሪፖርተር፡- በ1997 ዓ.ም. ከተደረገው ምርጫ ጋር በተያያዘ በእርስዎ ላይ ትችቶች ሲሰነዘሩና የማውገዝ ደረጃ ላይ የደረሱም ነበሩ፡፡ ‹‹ተንሸራታች፣ ቃሉን የበላና ከሃዲ›› እና ሌሎችም ወቀሳዎችና ዘለፋዎች ሲሰነዘርብዎት ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ በተለይ እርስዎንና ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) በሚመለከት የሚሰነዘሩ ትችቶች አሉ፡፡ ሥልጣን ፈላጊዎች እንደሆናችሁና አሁን የምታደርጉት እንቅስቃሴም የሕዝብ ቀልብ ለመሳብ እንደሆነ አስተያየታቸውን ለሚሰጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምላሽዎ ምንድነው?
አቶ ልደቱ፡- ይኼ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት ተወቅጦ ተወቅጦ የተሸነፈ የአሉባልታ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከተጨባጭ መረጃ የሚነሳ አይደለም፡፡ ልደቱ ሥልጣን ይወዳል? አይወድም? የሚለውን በፓርቲዬ ውስጥ ያሳለፍኩትን ታሪክ ማወቅ ይበቃል፡፡ አሁን ከአንተ ጋር ሳወራ እንኳን የኢዴፓ ሥራ አስፈጻሚ አይደለሁም፡፡ ካሉት 25 የብሔራዊ ምክር ቤት አባል አንዱ ነኝ፡፡ ምንም ሥልጣን የለኝም፡፡ የሚመርጠኝ አጥቼ ሳይሆን ፍላጎቱ ስለሌለኝ ነው፡፡ አሁንም የምታገለው ለሥልጣን አይደለም፡፡ ለሥልጣን ቢሆን ኖሮ አቋራጭ መንገድ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ አባል ከሆንክና ጥሩ አፍ ካለህ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ባለሥልጣን መሆን ይቻላል፡፡ ለአገሬ አስተዋጽኦ ለማድረግ እንጂ አቋራጩን መንገድ በደንብ አውቀው ነበር፡፡ ግን እንደዚያ ብለው የሚያወሩ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ጥያቄውን ማንሳት ስላለብህ አነሳኸው እንጂ፣ የተዘጋ ምዕራፍ ነው፡፡ ሕዝቡ ገብቶትና ተረድቶት የተወው ነገር ነው፡፡ እንደነገርኩህ የ1960ዎቹ ትውልዶች ፊት ለፊት ሐሳባቸውን መግለጽ ስለማይችሉ ከኋላ ሆነው እንደዚህ ያለ አሉባልታ ያስወሩብሃል፡፡ በአንድ ወቅት ሕዝቡ በደንብ ስላልተረዳው ትንሽ የአስተሳሰብ መፋለም ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን በደንብ ተረድቶታል፡፡ ያለ ቀና የተዘረጋ ምዕራፍ ነው፡፡ የወጣትነት ዕድሜዬን የፈጀሁትን የፖለቲካ ትግል ዝም ብዬ አንድ ሜዳ ላይ ልበትነው አልችልም፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ እጅግ ያሳስበኛል፡፡ ቤቴ ቁጭ ብዬ ልመለከት ስለማልችል እንጂ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት የሥልጣን ፍላጎት አይደለም፡፡ የምታምንበትን ጉዳይ ለመፈጸም ዕድል ስለሚሰጥህ ሥልጣን ብታስብም መጥፎ አይደለም፡፡