በአሜሪካ አደራዳሪነት እየተካሄደ ያለው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር፣ በግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ሥርዓት ላይ መሠረታዊ መግባባት ላይ መደረሱ ቢገለጽም፣ ተጨማሪ ድርድር የሚፈልጉ ጉዳዮች መኖራቸው ተነግሯል።
የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ ውኃ ሚኒስትሮች፣ የውኃ ዘርፍና የሕግ ባለሙያዎች ጭምር በድርድሩ ላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ በዋናነት ሲነጋገሩበት በነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ሥርዓትን በሚመለከት መሠረታዊ መግባባት ላይ መድረሳቸውን፣ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ተናግረዋል። በድርቅ፣ ለዓመታት በተራዘመ ድርቅና ለዓመታት የተራዘመ አነስተኛ የወንዝ ፍሰት በሚኖረው የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ መሠረታዊ መግባባት ላይ የደረሱ ቢሆንም ተጨማሪ ውይይት የሚፈልጉ ጉዳዮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የሚደረገው ድርድር በግድቡ ላይ ብቻ የተወሰነ መሆኑን፣ ነባርና ወደፊት በዓባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብትን በሙሉ የሚያስከብር ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት የማይናወጥ አቋም መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ስለሚደረገው ድርድር ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ ኢትዮጵያን በሚገልጽ መልኩ የሚወስን መንግሥት አይኖርም። ኢትዮጵያም ብትሆን ጎረቤት አገሮችን የሚጎዳ ተግባር አታደርግም።
ዓለም አቀፍ የውኃ አጠቃቀም ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ድርድሩ እንደሚቀጥልና በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።