በቻይናዋ ዉሀን ከተማ የተነሳው ኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ፤ በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበና የሟቾችም ቁጥር እየጨመረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ ለዓለም አገሮ ጭምር ስጋት መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አውጇል።የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴደሮስ አድሀኖም እንዳስታወቁት፤ ኮሮና ቫይረስ በቻይና ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገሮች በፍትነት እየተስፋፋ ነው። የአለም ጤና ድርጅት ቫይረሱ በተለይ በታዳጊ አገሮች ላይ ከተከሰተ አደጋው የሚከፋ መሆኑን አውጆ እያለ፤ የኢትዮጵያ ቸልተኝነት በተለይ የሕክምና ባለሙያዎችን አሳስቧል።
በርካታ ሀገሮ ወደ ቻይና ያደርጉት የነበረሙን በረራ ለጊዜው ማቋረጣቸውን እየገለጹ ባለበት በዚህ ወቅት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ “በረራዬን አላቋረጥኩም፤ በረራውን የማደርገው በጥንቃቄ ነው” ማለቱ ከማስገረምም አልፎ ጥያቄ አጭሯል። እንደ ቻይና ላለች በማንኛውም ሁኔታ ብትመዘን አቅም ላላት አገር የከበደ መድሃኒት ያልተገኘለት በሽታ ወደ አገር እንዲገባ በር ከፍቶ መጠበቅ “ሞትን ና ግባ ብሎ መጋበዝ ነው” ይላሉ የሕክምና ባለሙያዎች። ኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚገቡ ተጓዦችን ሙቀት መጠን ለክቶ እንደሚያሳልፍ ቢገልጽም፤ ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ለመራባት የሁለት ሳምንት ጊዜ ስለሚወስድ በዚህ ጊዜ ውስጥ ወደ አገር ቤት የሚገባ ተጓዥ በቀላሉ ሊያልፍ እንደሚችልም ተናግረዋል። ከሁለት ሳምንት በኋላ ግን ቫይረሱን ማስተላለፍ እንደሚችልም አክለዋል። በመሆኑም ሌሎች አገሮች እንዳደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድም ለጊዜው በረራውን ማቆም እንዳለበት መክረዋል። ቫይረሱ በተለይ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሽታው ቢከሰት በኢትዮጵያ ካለው የህክምና መሣሪያዎች እጥረትና የሕብረተሰቡም አኗኗር ሁኔታ ለበሽታው መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግና ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ እንደሚሆን ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። በመሆኑም ለጊዜው በረራውን አቋርጦ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረጉ አማራጭ የሌለው ውሳኔ መሆኑንም መከርዋል። ቫይረሱ አደገኛ የሳንባ ምች የሚያመጣና የመተንፈሻ አካልን የሚጐዳ ሲሆን፤ በደም ውስጥ የሚሰራጭ ኢንፌክሽን በማምጣት ኩላሊት እንዳይሰራ በማድግ የሚገድል በሽታ መሆኑንም ባለሙያዋች እየገለጹ ይገኛሉ። በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማከም የጽኑ ህሙማን ክፍሎች፣ መተንፈሻ ማሽኖችና ሌሎች የህክምና መሳሪያዎች በብዛት የሚያስፈለጉ መሆናቸውንም ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው። በመሆኑም ያደጉ አገሮች ሳይቀሩ ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ እያቋረጡ ባሉበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ድፍረት የተሞላበት እንቅስቃሴ ተገቢ ባለመሆኑ ቆም ብሎ ማስብ እንደሚያስፈልግ እየተገለጸ ነው።