ከታገቱ ሁለት ወራት ያለፋቸው የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ወላጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዩጵያውያንን ማስጨነቁ ቀጥሏል። የተወሰኑ ታጋች ተማሪዎች ወላጆች ወደ አዲስ አበባ ጥሪ ተደርጒላቸው መምጣታቸው ሲሰማ፤ የተለያየ ግምት ተሰጥቶ ነበር። ስለተማሪዎቹ መታገት በተለያዩ ድረ-ገጾች አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ መረጃ ይተላለፍ ስለነበር፤ቤተሰቦቻቸው በመንግስት ደረጃ መጠራታቸው ሲሰማ፤ በድረገጾች የተላለፈው አስደንጋጭ መረጃ ትክክለኛነትም እስከማረጋግጥ የተደረሰ ቢሆንም ውጤቱ ግን ሌላ ሆኗል። የታገቱ የተወሰኑ ተማሪዎች ቤተሰቦች አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ የተገናኙት ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ጋር ነው። ወላጆቹ ከልጆቻቸው መገናጀት ካቋረጡበት ጊዜ አንስትው በጭንቀት ላይ መሆናቸውን ተናግረው፤ መንግስት የልጆቻቸውን ሕይወት እንዲታገድላቸው ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች እነዲሁም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የተማሪዎቹ የትውልድ ቦታ ተወካዮች ከታገቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወላጆች ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል።ወላጆች የልጆቻቸው አድራሻ እስከጠፋበት ዕለት ድረስ የነበራቸው የስልክ ልውውጥ ምን እንደሚመስልም ጉዳዩን በሚመለከት ለተቋቋመውና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለሚመራው ግብረ-ሃይልን መናገራቸውም ተነግሯል።
ግብረ-ሃይሉን የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስት የታገቱ ተማሪዎችን ለማስፈታት እያከናወነው ያለውን ተግባር ለወላጆቹ እንዳብራሩላቸው፤ በተማሪዎቹ ላይ ጉዳት እንደደረሰ የሚያሳይ የተረጋገጠ መረጃም ሆነ ማስረጃ አለመኖሩንና ከወላጆቹ ጋ ለቀጣይ ስራ የሚሆን መረጃ መገኘቱንም ገልጸዋል ተብሏል።
መንግስት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ ሲባል በጥንቃቄና አስተውሎት እየሰራ መሆኑንና ችግሩን ለመፍታት ወላጆች በምን መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ጭምር ምክክር መደረጉተጠቁሟል። የጸጥታ መዋቅሩና የፖለቲካ አመራሩ፤ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ ያለምንም እረፍት እየሰራ መሆኑም አንደተገለጸ ታውቋል።
ሁሉም የታገቱት ተማሪዎች 17 እንደሆኑና ሁሉም የአራማ ክልል ተማሪዎች መሆናቸው ሲነገር የቆየና ዘርን መሠረት ያደረገ እገታ እንደሆነ ቢገለጽም መንግስት ግን አስተባብሏል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬትሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ቀደም ብለው በሰጡት መግለጫ፤ የታገቱት ተማሪዎች 17 ሳይሆኑ ከዛበላይ መሆናቸውን ጠቁመው 21 ተማሪዎችን በድርድር ማስመለስ መቻሉንና ስድስት ተማሪዎች ብቻ እንደቀሩ መግለጻቸው ይታወሳል። አቶ ንጉሱ መግለጫውን ከሰጡ በኋላ ተለቀዋል የተባሉት ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር አልተገናኙም።ወይም ወደ ዩኒቨርሲቲው መመለስ ባለመቻላቸው “ተማሪዎቹ የታሉ? ተማሪዎቻችንን መልሱ፤ አስመልሱና መንግስት ግልጽ መረጃ ይስጥ” የሚሉ ተቃውሞዎች በድረ ገጾችና በሰላማዊ ስልፎች ጭምር ሲቀርቡ ከርመዋል። ስለታገቱ ተማሪዎች ጥያቄውና ተቃዉሞው እስከ ሰላማዊ ሰልፍ ደርሷል። ሰላማዊ ሰልፉም በአማራ ክልል በባህር ዳር፤ ጎንደር፣ደብረብርሀን፤ በደብረ ማርቆስና በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ መንግስት ስለታገቱት ተማሪዎች ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ ተጠይቋል። ሰላማዊ ሰልፉ እንደተደረገ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰውና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል። ኃላፊዎቹ “እገታው የብሄር መልክ የለውም” ካሉ በኋላ፤ ቀደም ብሎ የተነገረውን የታገቱ የዩኒቨርሲ የተማሪዎች ቁጥር 14 መሆኑንና አምስት የአካባቢውነዋሪዎች በድምሩ 19 መሆናቸውን በመግለጽ ሁሉንም ግር ያሰኘ መረጃ ሰጥተዋል። ከሶስት ሳምንታት በፊት 21 ተማሪዎች ስመለቀቃቸውና ስድስት ተማሪዎች ስለመቅረታቸው የተነገረው መረጃ ተትቶ 14 ተማሪዎች እንደታገቱና አምስት ደግሞ ሌሎች ሰዎች መሆናቸውን በመገለጹ፤ የሁሉም ጭንቀትና ጥርጣሬው ቀጥሏል።
የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ ቡድን አቋቁሞ ክትትል እያደረገ መሆኑን፤ የታገቱት ተማሪዎች የደረሰበቸው ጉዳት ስለመኖሩ መረጃ እንደሌለውና በአጠቃላይ በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የፀጥታ ኃይሎች ተባብረው እየሰሩ መሆኑን ኃላፊዎቹ ገልፀዋል። የመንግስት ኃላፊዎች መግለጫውን ከሰጡ በኋላ ስለተማሪዎቹ እገታ ያለው ጭንቀት ጨምሯል። መንግስት ያለውን አስቸጋሪም ይሁን ጥሩ ነገር ሳያቅማማ በግልጽ ሊናገር ይገባል የሚል ተቃውሞም መሰማቱ ቀጥሏል።