ውድ አንባቢዎቼ ዛሬ “መሪዎቻችን ሰነፎች መሆናችንን በድፍረት የሚነግሩን መቼ ነው?” በሚል ርዕስ ምልከታዬን ላካፍላችሁ ቀጠሮ አስይዣችሁ ነበር፡፡ ሆኖም በክልል መንግሥታት መካከል እየተስተዋሉ ያሉ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ የቃላት ልውውጦች ደርዝ እየሳቱ መምጣታቸው ቢያሳስበኝ፤ ርዕሰ ጉዳዬን ቀይሬ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ግንኙነትን ገጽታ ለመፈተሸ ወደድኩ፡፡ በመሆም ዛሬ ላቀርብላችሁ አቅጄ የነበረውን ጽሑፍ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡ በቃሌ ላለመገኘቴ ታላቅ ይቅርታን እጠይቃለሁ፡፡ የዛሬውን ሐሳቤን አነሆ፡፡
የዛሬው ሀሳቤ ወይም መጣጥፌ የሚያተኩረው የፌዴራልና የክልል መንግሥታትን ግንኙነት ምን እንደሚመስል ለማሳይት መሞከር ነው፡፡የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ውሎ የፌዴራል ሥርዓቱ በይፋ ከተመሠረተበት ከነሐሴ 1987 ዓ.ም ጀምሮ አስከ ዛሬ ድረስ በፌዴራል መንግሥቱ እና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት እስከአሁን ሥልጣን ላይ ባለው ኢህአዴግ (ብልጽግና የፖለቲካ ፓርቲ እና ህውሃት) እና አጋር የፖለቲካ ድርጅቶች ባላቸው የፓለቲካ ግንኙነት ልክ የተከረከመ እና የተሰፋ ነበር፡፡ በመሆኑም የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታትን ግንኙነት የሚቃኘው በእነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶችና በባለሥልጣኖቻቸው በሚሰጠው ውሳኔ ነበር፡፡ በሌላ አገላለጽ የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታት ግንኙነት በሕግና በሥርዓት ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ የማይጓዝ ግለሰቦችና የፖለቲካ ማኅበራቱ እንዳሻቸው የሚቀይዱት ነበር፡፡
በሕገ መንግሥቱ አቀራረጽ መሠረት የፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ ክልሎች ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው አካላት ናቸው፡፡ መንግሥታቱን በምርጫ ያሸነፈ አካል ተረክቦ ይመራቸዋል፡፡ አሸንፎ ሥልጣን የሚረከበው አካል እና መንግሥታቱ የተነጣጠለ ኀልዎት ያላቸው ናቸው፡፡ አንዱ በምርጫ ሕጉ አግባብ ተመዝግቦ የሕግ ሰውነት ያገኘ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የየራሳቸው እና የጋራ ሥልጣን ባለቤት ሆነው የተቋቋሙ መሆናቸው ነው፡፡ ሁለቱን የሚያገናኛቸው ድልድይ በምርጫ አሸናፊ ሆኖ የፌዴራሉንም ሆነ የክልል መንግሥታትን ሥልጣን መረከብ ነው፡፡ በሌላ ምሳሌ አንድ የግል ባንክን ብንመለከት ባንኩ የሚቋቋመው በሥራ ላይ ባሉ ሕግጋት እና በብሄራዊ ባንክ ዕውቅና ነው፡፡ የባንኩ አስተዳዳሪዎች ደግሞ በሕግጋት፤በባንኩ መመሥረቻ እና መተዳደሪያ ድንብ አግባብ የሚመረጡ ወይም የሚሾሞ ናቸው፡፡ ባንኩና የባንኩ አስተዳዳሪዎች የተለያየ ኀልዎት አላቸው፡፡ መሪዎቹ ማለት ባንኩ ማለት አይደሉም፡፡ ባንኩ ማለትም መሪዎቹ ማለት አይደሉም፡፡ አስተዳዳሪዎቹ የባንኩን አስተዳደር በሕግ እና በአስተዳደር ጥበብ አንጻር ይመሩት እንደሆነ እንጂ፤ ባንኩን አይፈጥሩትም፡፡ ባንኩ በሕግ አግባብ ካልከሰመ በቀር ባንኩ ያለ መሪዎቹ መኖር ይችላል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ መንግሥታት ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ሕግና ሥርዓት ከተበጀ ማንኛውም የፖለቲካ ማኅበር የፌዴራልንም ሆነ የክልል መንግሥትን ሥልጣን ቢይዝ፤ በሕግ አግባብ ማስተዳደር ስለሚችል ላፉት አሠርት ዓመታት በሥልጣን ላይ የነበሩት የፖለቲካ ማኅበራት ባይኖሩም የመንግሥታቱ ኀልዎት ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ማኅበሮቹ ማለት ክልል ማለት እይደሉም፡፡ ክልሎቹ ማለትም የፖለቲካ ድርጅቶቹ ማለትም አይደለም፡፡
መንግሥት እና የፖለቲካ ማኅበር የተለያዩ መሆን ቢገባቸውም እውነታው ግን ይህ ባለመሆኑ እስከ አሁን በነበረን ጉዞ የክልል መንግሥታት ማለት ኢህአዴግ እና “አጋር” የፖለቲካ ድርጅቶቹ ማለት ነበሩ፡፡ ኢህአዴግ እና “አጋር” የፖለቲካ ድርጅቶቹ ማለት የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ማለት ሆነው ቆይቷል፡፡ አሁንም ከዚህ አዙሪት የመውጣት ምጣችን እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህን ስል ግን በምርጫ አሸንፈው የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሥት የሚመሠርቱ የፖለቲካ ማኅበራት በሚመሠርቱት አሥተዳደር ላይ ተፅዕኖ ሊኖራቸው አይባም ማለቴ አይደለም፡፡ እያልኩ ያለሁት የመንግሥት አሥተዳደር የሚፈጸምበት እና የክልል እና የፌዴራል መንግሥታት ግንኙነታቸውን የሚመሩበት ሥርዓት በመሪዎች ፍላጎትና ፈቃድ ብቻ የሚቃኝ ሳይሆን፤ መሪዎቹ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ሥርዓት እና ደንብ ቀድሞ የተበጀ ሊሆን ይገባል ነው፡፡ ይህ ሲሆን መሪዎች በተሰጣቸው የግንኙነት ሥርዓት ማዕቀፍ ሳያፈነግጡ የመሪነት ሚናቸውን ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ይህ መሆኑም የመንግሥታቱ ግንኙነት በመሪዎቹ ፈቃድ ሥር አነዳይወድቅ እና በመንግሥታቱና በመሪ የፖለቲካ ድርጅቶቹ መካከል ያለውን የተነጣጠለ ኀልዎት ሳይደበላለቅ አሥጠብቆ እንዲቆይ ያስችለዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ሕግና ሥርዓት የሚዘውራት አገር እንጂ ግለሰቦች በተቀያየሩ ቁጥር እንዳሻቸው የሚፈነጩባት አገር መሆኗ ደርዝ እየያዘ እንዲመጣ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡
ቀጣዩ የመንግስታት የግንኙነት ሥርዓት ምን ይመስላል?
መንግሥት በአሁን ሠዓት የክልል እና የፌዴራል መንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ያልተበጀለት በመሆኑ ሥርዓት ለማበጀት ይረዳል ያለውን ሕግ ለማውጣት በሒደት ላይ ነው፡፡ ይህም እሰዬው የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ በረቂቅ ደረጃ ያለው ይህ ሕግ “በኢፌዲሪ የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓትን ለመወሰነ ታስቦ የወጣ አዋጅ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቷታል፡፡ የዛሬ ምልከታዬም ይህንን ረቂቅ አዋጅ በወፍ በረር የሚቃኝ ይሆናል፡፡ በረቂቅ አዋጁ መግቢያ ላይ አዋጁ የወጣባቸው ዓላማዎች ተዘርዝረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም አዋጁ የሚወጣው “… አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብን ለመገንባት ይቻል ዘንድ ከተናጠል ጥረቶች ይልቅ የየእርከኑን አካላት አቅሞች በተገቢው መንገድ አቀናጅቶና አዋህዶ ዘርፈ-ብዙ የልማትም ሆነ የመልካም አስተዳደር ተገባራትን ለማከናወን የሚያስችሉ መደበኛ የመንግሥታት ግንኙነቶችን በግልጽ መደንገግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤” የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት “… በተናጠል በየተመደቡላቸው ሥልጣንና ተግባራት ተቀራርርቦ፤ እርስ በእርስ ተናቦ መሥራትና ተገቢ ሆኖ ሲገኝ የጋራ ፖሊሲዎችንና እስትራቴጂዎችን ነድፎ በውጤታማነት ለመንቀሳቀስ የሚያግዝ ትብብራዊ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልጋቸው መታመኑን፣ “ፌዴራላዊ ሥርዓቱንም ሆነ የሀገሪቱን ዲሞክራሲያዊ አንድነት ለማጠናከር ብሎም በየእርከኑ መንግሥታትና አቻ ተቋማቱ መካከል በመርኅ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የትብብር ሥርዓት መፍጠር፤ ለፌዴራላዊ ሥርዓቱ ጤናማነትና ቀጣይት ጉልህ ድርሻ ያለው በመሆኑ …” እንደሆነ ይገልጻል፡፡
አንድ አዋጅ ሲወጣ መጀመሪያ ከግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባው “አዋጁን የማውጣት ሥልጣን የማን ነው?” የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በረቂቁ አዋጁ መግቢያው ላይ በግልጽ ባይካተትም በረቂቁ መደምደሚያ ላይ በኢፌዲሪ ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፊርማ እንዲወጣ የታቀደ መሆኑን ሰለተመለከተ፤ ሕጉን የሚያወጣው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55 (1) መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት በተሰጠው የሥልጣን ክልል ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር ደግሞ አንቀጽ 51 ሥር ተዘርዝሯል፡፡ በዚህ አንቀጽ ሥር የፌዴራል መንግሥቱ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት እንዲሁም የክልል መንግሥታትን የእርስ በእርስ ግንኙነት የመምራትና የመወስን ግልጽ ሥልጣን የሚሰጠው ዝርዝርም ሆነ ጠቅላላ ድንጋጌ የለም፡፡
የክልል መንግሥታት በውስጣቸው በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የተቀመጡ መብቶች ባለቤቶች የሆኑ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የያዙ የፌዴሬሽኑ አባል እንደመሆናቸው፤ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የክልል መንግሥታት በሕግ የተሰጧቸውን ተግባራት ሲያከናውኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የክልል መንግሥታቱንና የኢትዮጵያውያን/ትን ጥቅም የሚመለከቱ ውሳኔዎችን መወሰናቸውና የቀጥታና የጎንዮሽ የሥራ ግንኙነት ማድረጋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በመግቢያው ሥር፤ ሕገ መንግሥቱ ሊያሳካቸው ከሚሻቸው ነገሮች፤ እንደ ሕገ መንግሥቱ አገላለጽ “ … (የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች) ጥቅማችንን፣ መብታችንና ነጻነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ …” መገንባት ነው፡፡ ይህንን ግብ ለማሳካት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነታቸውን በሕግ አግባብ መምራታቸው ሊነቀፍ የማይገባ ተግባር በመሆኑ፤ ረቂቅ አዋጁን ወይም ሕጉን የማውጣት ሥልጣን ምክር ቤቱ ያገኘበትን አግባብ በቀጥጣ ድንጋጌም ሆነ በትርጓሜ ቢያካትተው፤ ቅቡልነቱን እና ሊነሱ የሚችሉ ክርክሮችን ከወዲሁ ያስቀረዋል፡፡
የሚጋጩና የማይናበቡ የፌዴራልና የክልል ሕግጋት መኖር
ረቂቅ አዋጁ ከሚያስገኛቸው በጎ ነገሮች አንዱ በክልል እና በፌዴራል መንግሥታት መካከል ወይም በክልል መንግሥታት መካከል የሚኖሩ ጉራማይሌ አሠራሮችን ፈር ለማስያዝ እና እርስ በእርስ የሚኖር የአሠራር ሥርዓቶች ግጭትን ለማስወገድ ወይም ለመቀነስ መንድ የፈጠረ መሆኑ ነው፡፡ በክልሎች የሚወጡ ሕግጋት በፌዴራል መንግሥት ከሚወጡ ሕግጋት ጋር ቢጋጩ አልያም በአንዱ ክልል የወጣ ሕግ በሌላው ክልል ከወጣ ሕግ ጋር ቢጋጭ የሚደንቅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የፌዴራላዊ መንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ባኅርይ ነውና፡፡ ነገር ግን መጣጣምና መናበብ ሲገባቸው ወይም ቢጣጣሙ መልካም ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ ሕግጋትና አሠራሮች የተለያዩና የማይጣጣሙ መሆናቸው፤ ያሉትን ችግሮች የሚያባብሱ ያደርጋቸዋል፡፡
ለአብነት ያህል የሞተር ሳይክል ወይም የተሸከርካሪ ሰሌዳ አሠጣጥን ብንመለከት፤ አዲስ አበባ አስተዳደር የከለከለውን ሰሌዳ ተገልጋዮች ከተለያዩ የክልል የትራንሰፖርት ቢሮዎች አውጥተው ተሽከርካሪያቸውን በመዲናዋ በማሽከርከራቸው በክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንሰፖርት መሥሪያ ቤቶች መካከል ጣት መቀሣሣር ይስተዋል ነበር፡፡ የመሬት ወረራንም እንዲሁ ብንመለከት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን መካከል ውዝግብና ጣት መቀሣሠር ይታይ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የደን አዋጅ እና የፌዴራ መንግሥቱ የደን አዋጅ ልዩ ባህርያታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አዋጆቹን በጣሱ ሰዎች ላይ የሚጥሉት የወንጀል ቅጣት የተለያየ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ ከመሆኑ አንጻር ደኖቿ የሚገኙት ከኦሮሚያ ጋር በምትዋሰንባቸው ቦታዎች በመሆኑ፤ የደን አዋጁን ጥሰት ተከትሎ በሚደረጉ የሕግ ክርክሮች የቅጣት ልዩነታቸው አከራካሪ ሆኖ ሲነሳ ይስተዋላል፡፡ ለሁሉም አስተዳደር አካላት የተሠጠ ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ መንግሥታት ወጥ ወይም ተቀራራቢ ሕግጋት ወይም የአሠራር ሥርዓት ሊዘረጉ በሚችሉባቸው ነገሮች ላይ በምክክር ቢሠሩ መልካም ውጤት ማስገኘቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ረቂቅ አዋጁ ወጥ ወይም ተቀራራቢ አሠራሮች ለመዘርጋት፤ ሥርዓት ለማበጀት መነሳቱ ሊደገፍ የሚገባ ተነሳሽነት ነው፡፡
ረቂቅ አዋጁ ከዳኝነት ነጻነት አንጻር
ፍርድ ቤቶች የመንግሥት አንዱ አካል በመሆናቸው ከሌሎች የመንግሥት አካላት ጋር ግንኙነት ቢኖራቸው የሚደንቅ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱም ሦስቱ አካላት አንዱ ሌላኛውን እንዲቆጣጠርና ሚዛናዊነታቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ ይሻል፡፡ ይህንን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት የሚስችላቸውን ሥልጣንና ተግባርም ሰጥቷቸዋል፡፡ በሕግ ሥርዓታቸው በበለጸጉ አገራትም፤ ፍርድ ቤቶች ከአስፈጻሚው አካልም ሆነ ከሕግ አውጪው ጋር በትብብርና በቅንጅት ይሠራሉ፡፡ ሆኖም ይህ የትብብር እና ቅንጅት ሥራ የፍርድ ቤቶችን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ነጻነት የሚንድ ወይም የሚሠረሥር ሆነ አይታይም፡፡ የትብብር ሥርዓቱም ልክ የተበጀለትና የሦሥቱንም መንግሥታዊ ተቋማት ነጻነት እና ሥልጣን የሚያጎለብት እንጂ፤ አንዱ በሌላው ሥልጣን ገብቶ እንዳሻው የሚያዳውርበት አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በመከናወንም ላይ ናቸው፡፡ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (Business Process reengineering – BPR) በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ሲሆን፤ በፌዴራል ደረጃ የፍትሕ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ሊኖር ይገባል በሚል መነሻ ዋነኞቹ የፍትህ አካላት ማለትም የፌዴራል ፖሊስ፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በተለያዩ ደረጃዎች ኮሜቴዎችን አዋቅረው ሥራዎቻቸውን በጋራ “ሲገመግሙ” እና የተለያዩ መድረኮች ሲያዘጋጁ ቆይተዋል፡፡ የፍትሕ አካላቱ ቅንጅት የፍትሕ አካላቱን ሥራ ከማዘመን እና በሕግና ሥርዓት የሚመራ ለማድረግ ካስመዘገባቸው ስኬቶች ይልቅ፤ በስመ ቅንጅት አንዱ በሌላው ሥራ ውስጥ ገብቶ አዛዥና ተናዛዥ ሲኮንበት የቆየ በጽኑ የታመመ ሕብረት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህ የተነሳም በተለይም የዓቃቢያነ ሕግ እና የፍርድ ቤቶች ሥልጣንና የሙያ ነጻነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱም በቀላሉ ልናስወግደው ስንችል በነበረው ጉዳት ክፉኛ ተመትቷል፡፡
አልአግባብ ተለጥጦ በተተረጎመ እና በተተገበረ አጉል “ቅንጅታዊ አሠራር” የተነሳ ለደረሰው ጉዳት ዋነኛ ተጠያቂዎች፤ኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት በመበልጸጉ ዜጎችም ከሚያኙት ጥቅምና ትርፍ ይልቅ ፖለቲካዊ ወገንተኝነትና ግላዊ ትርፍ የበለጠባቸው በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የፍትሕ አካላት “አንዳንድ መሪዎች” ነበሩ፡፡ እነኚህ “አንዳንድ መሪዎች” ተግባራዊ የነበረው “ቅንጅታዊ አሠራር” የፍትህ አካላቱን ሙያዊ ነጻነት የሚያኮስስ በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባ በማስገንዘብ፤ የተለያዩ ባለሙያዎች የሠነዘሯቸውን ሐሳቦች “ጸረ ለውጥ ሐሳቦች!” በማድረግ የሐሳቦቹን አፍላቂዎች ክፉኛ በመደቆስና በማሸማቀቅ፤ ውጥንቅጡ የወጣ የፍትሕ ሥርዓት እንዲሰፍን አድርገዋል፡፡ መንግሥትንና ሕዝብንም የከፋ ጭንቀትና ነውጥ ውስጥ አስምጠውት ቆይተዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ከዚህ ሕመሙ ለመዳን ዛሬም ሕክምና ላይ ነው፡፡ ሕመሙ አለመሻሩን የሚያሳዩ የሕመሙ ምልክቶችም በተደጋጋሚ ሲታዩ ተስተውሏል፡፡
በዚህ ነጥብ ሥር ይህንን ሁሉ ሃሳብ ማስቀደሜ ረቂቅ አዋጁ ባካተታቸው ሐሳቦችና እንዲዘረጉ በወጠናቸው የአሠራር ሥርዓቶች ውስጥ፤ የትናንት ሥህተት እንዳይደገምና መልሰን ወደውጥነቅጥ እንዳናመራ ለማስገንዘብ፤ እንዲሁም በመንግሥት አሥተዳደር የሚሣተፉ የመጪው ትውልድ አባላት፤ ለሚመጣው መንግሥት ታማኝ በመሆን ከሚገኘው ግለሰባዊ “ጥቅም” በላይ ለሕግና ለሕሊና መገዛት ለአገር የሚበጅ የግለሠብን ክብርና ጥቅምም ከፍ የሚያደርግ መሆኑን የሚገነዘቡበት፤ ሥርዓት መዘርጋቱን ማረጋገጥ የሁላችንም ግዴታ በመሆኑ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግ ለመጠቆም ነው፡፡
ረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 11 ሥር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች እና መድረኩ አስፈላጊ ናቸው ብሎ ካመነባቸው የፌዴራልም ሆነ የክልል ዳኝነት አካላት ወይም ሌሎች ተቋማት ባልደረቦች እንደተገቢነቱ በአባልነት ወይም በአሥረጂነት እንዲሳተፉበት፤ የሚጋበዙበት አገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች የግንኙነት መድረክ እንደሚቋቋም ይገልጻል፡፡ በአንቀጽ 12 ሥር “ … ቀደም ሲል ተቋቁመው በመሥራት ላይ ያሉት ፍትህና ዳኝነት-ነክ የምክክር አካላት ባሉበት ሁኔታ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን በዚህ አዋጅ የተደራጀው መድረክ የሚከተሉት ዝርዝር ተግባርና ኃላፊነቶች ይኖሩታል …” የሚል ድንጋጌ ተካቶበታል፡፡
በዚህ አንቀጽ ሥር “… ቀደም ሲል ተቋቁመው በመሥራት ላይ ያሉት ፍትህና ዳኝነት-ነክ የምክክር አካላት፤ ባሉበት ሁኔታ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን …” የሚለው ሐረግ ረቂቅ አዋጁ ቀድመው በአዋጅ የተቋቋሙ የክልል እና የፌዴራል የዳኝነት አካላት መድረክ መኖሩን እንደሚያውቅ ያሥረዳል፡፡ በፌደፌራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 31 ሥር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች አባላት የሆኑበትን እና አግባብነት ካላቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ማኅበራት፣ ድርጅቶች፣ በሕግ ፋኩሊቲዎች እና የሳይንስ ተቋሞች የሚወከሉ ሰዎች ወይም ሌሎች ተጋባዦች የሚሳተፉበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ እንዳለው ይደነግጋል፡፡ በዚህ ሕግ አግባብ የተቋቋመው ጉባዔም ሆነ ሌሎች ኢ-መደበኛ የፍርድ ቤቶች መድረኮች በየጊዜው እየተገኛኙ በጋራ ጉዳዮች ላይ ሲመከሩ ቆይተዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 12 የሚያቋቁመው መድረክ ከእነዚህ መድረኮች ተጨማሪ መሆኑን ድንጋጌው በግልጽ ያሥረዳል፡፡ ጉባዔው እና ይህ መድረክ በአባላታቸው ጥንቅር፣ በተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር እንዲሁም የሥልጣን ወሰን መጠነኛ ልዩነት ያላቸው ቢሆንም ተደጋጋሚ ሥራዎችን በሁለት የተለያዩ አካላት እንዳይሠራ ረቂቅ አዋጁ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ በተለይም አሁን እየረቀቀ ካለው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ አንጻር መቃኘትና መጣጣም ይገባዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም “… ቀደም ሲል ተቋቁመው በመሥራት ላይ ያሉት ፍትህና ዳኝነት-ነክ የምክክር አካላት ባሉበት ሁኔታ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን …” የሚለው ሐረግ፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔን አመላካች ቢመስልም “ፍትህና ዳኝነት-ነክ የምክክር አካላት” የሚለው ሐረግ ከላይ የገለጽኩትን “የፍትሕ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር” በሚል መጠሪያ ሢሠራበት የነበረውን ግልጽ የሕግ ማእቀፍ የሌለው እና ደርዝና ሥርዓት ያልተበጀለት መድረክ፤ ሕጋዊ ዕውቅና እየሠጠ አለመሆኑን በግልጽ ለይቶ ማሳየት አለበት፡፡
የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 12 (3) “የፌዴራል ሕጎች በክልል ደረጃ የተቀረራበ አተረጓጎም እንዲኖራቸው ምክክር ያደርጋል፣ የመፍትሄ እርምጃዎችን ይወስዳል” ይላል፡፡ ንዑስ አንቀጹ መዳሰስ የፈለገው የፌዴራል ሕጎች የክልል ፍርድ ቤቶችን ሲተረጎሙ የሚኖረው የአተረጓጎም ልዩነት መሆኑን ከአቀራረጹ መረዳት ይቻላል፡፡ ሕግን በተግር የሚተረጉሙት ፍርድ ቤቶች እንደመሆናቸው እና የትርጉም ሥራው የሚከናወነው በዳኞች መሆናቸው ዕሙን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር “… የመፍትሄ እርምጃዎችን ይወስዳል …” የሚለው ሐረግ፤ ለትርጉምና ተገቢ ላልሆነ አጠቃቀም ላይ እንዳይውል ሊታሰበብትና መድረኩ ተቀራራቢ ትርጉሞች እንዲኖሩ ሊወስዳቸው የሚችሉትን “… የመፍትሄ እርምጃዎች …” አመላካች ቃላት ሊታከሉበት አልያም የበለጠ ግልጽ ሊደረግ ይገባል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 21 የመንግሥታት ግንኙነት አደረጃትቶችና ተግባራት ተቀናጅተው የሚመሩትን የአሠራር ሥርዓት ይደነግጋል፡፡ በንዑስ አንቀጽ (1) ሥር “ሀገር-አቀፍ የሕግ አስፈጻሚው እና የሕግ ተርጓሚው አካላት መድረኮች አፈጻጸማቸውን፣ ያጋጠሟቸውን ችግሮችና ሕግ እንዲወጣላቸው የሚፈልጓቸውን ጉዳዮች በሚመለከት ለሕግ አውጪው የግንኙነት መድረክ ያቀርባሉ” ይላል፡፡ በንዑስ አንቀጽ (2) ሥር ደግሞ የአስፈጻሚዎችም ግንኙነት መድረክም፤ በተመሳሳይ መልኩ ለሕግ አውጪዎች መድረክ ያስተላፋል፡፡ በንዑስ አንቀጽ (3) ሥር “ሀገር-አቀፍ የሕግ አውቺዎች ግንኙት መድረኩ በበኩሉ ከሀገር-አቀፍ የአስፈጻሚዎች ግንኙነት መድረክ የተላለፈለት ሪፖርት የዳኝት ሥርዓቱን የሚመለከት ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ለሀገር-አቀፍ የሕግ ተርጓሚ አካላት ግንኙነት መድረክ እንዲደርስ ያደርጋል” ይላል፡፡
በመነሻዬ እንደገለጽኩት በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አካላት ተነጥለው ብቻቸውን የሚኖሩ ደሴቶች ባለመሆናቸው፤ ሥራቸውን በአግባቡ ለመወጣት እና ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ይረዳቸው ዘንድ የእርስ በእርስ ግንኙነት ቢያደርጉ የሚያስወቅሳቸው አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ግንኙነታቸው በሕግና መርኅ የሚመራና ተቋማዊ ነጻነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የማይከት ትብብር መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም በአንቀጽ 21 ሥር የተቀመጠው የግንኙነት ሠንሠለት የፍርድ ቤቶችን ነጻነት ጥያቄ ውስጥ የማይከት ቀድሞ ይደረግ እንደነበረው የአስፈጻሚ አካላት አመራሮች፤ በእጅ አዙር ፍርድ ቤቶች የሚጠመዘዙበት እንዳይሆን የፍርድ ቤቶችን ተቋማዊ ነጻነት፤ ከጥያቄ ውስጥ የማይከት መሆኑን የሚያደነግግ ግልጽ አንቀጽ ሊኖረው ይገባል፡፡ የሌሎቹ ተቋማት ነጻነትም እንዲሁ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ነገር አንዱ ለሌላው ሪፖርት የማድረግ ግዴታ የተጠሪነት መዋቅር ስለሚመስል፤ ግልጽነት ሊኖረውና በሕገ መንግሥቱና ሌሎች ሕጎች የተቀመጡ የተቋማት የሥልጣን ተዋረድ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ሊደረግ ይገባል፡፡
መደምደሚያ
በዚህ አጭር ጽሑፍ ረቂቅ አዋጁን መቃኘትም ሆነ ጠንካራ እና መሻሻል ያለባቸውን ነጥቦች ዘርዝሮ መተንተን የሚታሰብ ባለመሆኑ ምልከታዬን በዚህ ላይ እገታለሁ፡፡ ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸውም ሆነ ሌሎች መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ ድንጋጌዎች፤ ረቂቅ አዋጁ በሚያልፍባቸው ቀሪ የሕግ ማውጣት ሒደቶች እንደሚቃኙና ጤናማና ዘላቂ ሥር እንደሚያበቅሉ ዕምነት አለኝ፡፡ ረቂቅ አዋጁ በዘፈቀደ እና በልማድ የዳበሩ አሠራሮችን ፈር በማስያዝ፤ የመንግሥታቱ ግንኙነት በሕግና በሥርዓት እንዲመራ ማድረግን ዓላማው አድርጎ መነሳቱ ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባው ነገር ነው፡፡ የየራሳቸው ሉዓላዊ ሥልጣን ያላቸውን መንግሥታት ግንኙነት አዋጅ በማውጣት ብቻ መፍታት ለክርክር በር ከፋች ነውና ወደፊት በሚኖሩና ሊኖሩን በሚገቡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የቀጥታና የጎንዮሽ ግንኙነቶች በተመለከተ፤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጡ ጥቅል ሥልጣኖችን ማብራራትን ጨምሮ በፖሊሲና በዝርዝር ሕግጋት የሚመሩበት የሕግ ማዕቀፍ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡
የዛሬ ምልከታዬን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ የምንደማመጥ፣ ሐሳብን በሐሳብ ብቻ የምንሞግት፣ ካለፈው ይበልጥ በመጪው ላይ የምናተኩርና ምንጊዜም ለእናት አገር ኢትዮጵያችን ቅድሚያ የምንሰጥ የአንድ አገር ሕዝቦች እንሁን!!! ብሩሐን ቀናት ከፊታችን ይቅደሙ!!! ሰላም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው (LL.B, LL.M, MSW) ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሲሆኑ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ፀሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ፡፡