በብስራት ተክሉ
የኢትዮጵያ መንግስት በመንግስት ቁጥጥ ስር ያሉ ትላልቅ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር የሆኑ የንግድ ተቋማቱን ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዞር በእንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንኑ ለማስፈጸም ዋነኛ መንገድ አድርጎ የወሰደው የነዚህን ግዙፍ ድርጅቶች ከፊል ድርሻ ለውጭ ባለሃብቶች አሳልፎ መሸጥን ነው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከሌብነት በጸዳ መልኩ የሃገሪቱን ጥቅም በሚያስጠብቅ መንገድ ድርጅቶቹን ወደ ግሉ ዘርፍ ማዘዋወር ትችላለች ወይ የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ሆኖም ግን ለዛሬ ይህንን ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያ መንግስት ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ እና ሎጀስቲክስ አ.ማ››ን /ከዚህ በኋላ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ›› ተብሎ ይጠራል/ ለውጭ ባለሃብቶች ሊሸጥ ይገባልን የሚለውን ይዳስሳል፡፡
መንግስት ለሽያጭ አቀርባቸዋለሁ ካላቸውዋና ዋና ድርጅቶች ውስጥ ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ይገኙበታል፡፡ እንደፀሐፊው እይታ የእያንዳንዱ የመንግስት የልማት ድርጅት ወደ ግል በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ መሸጋገር ከድርጅቱ ወቅታዊ አቋም፣ ታሪካዊ ዳራ እንዲሁም የወደፊት ስጋቶች ጋር ተሰናስሎ ሊገመገም ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ ሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ችግር እና አንዳንድ የማክሮ-ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች በጥቅሉ ምክንያት በማድረግ ሁሉንም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ልሽጥ ብሎ መነሳት ተገቢነት የጎደለው ተግባር ነው፡፡
የዚህ ጽሁፍ አላማየኢትዮጵያ ንግድ መርከብን ድርሻ ለውጭ ባለሃብቶች ሊሸጥ ይገባልን የሚለውን ይዳስሳል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በከፊል ወደ ውጭ ባለሀብቶች ይተላለፍ? ወይስ አይተላለፍ? የሚለው እስከአሁን ቁርጥ ያለ ውሳኔ ላይ አልተደረሰበትም፡፡ በመስከረም ወር 2011ዓ/ም የታተመው የኢ.ሬ.ዲ.ሪ መንግስት ብሔራዊ የሎጀስቲክስ ስትራቴጂ በገጽ 52 ላይ በመጀመሪያው ምእራፍ ማለትም ስትራቴጂው በፀደቀ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የንግድ መርከቡን የተወሰነ ድርሻ ለከፍተኛ አስመጪዎች እና ላኪዎች እንደሚሸጥ ይደነግጋል፡፡ ከፖሊሲው ለመረዳት እንደሚቻለው እነዚህ ባለሃብቶች የውጭ ሃገር ዜጎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም በሁለተኛው ምእራፍ ማለትም ከላይ ተቀመጠው የመጀመሪያው ምእራፍ ከተገባደደ በኋላ ባለው ሁለት ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በፓርትነርሺፕ/partenership/ የሚሰራበትን አሰራር ይዘረጋል ይላል፡፡ ሆኖም ስትራቴጂው ፓርትነርሽፑ በምን መንገድ ይቋቋማል እንዲሁም ደግሞ ምን አይነት ቁመና ይኖረዋል የሚለውን ግልጽ አላደረገውም፡፡ በአጠቃላይ ከስራቴጂውም ሆነ በመንግስት ተቋማት ውስጥ ካሉ ሰሰዎች እንደሚነገረው ከሆነ የንግድ መርከቡ የተወሰነ የአክስዮን ድርሻ ለውጭ ሃገር ኩባንያዎች ሊሸጥ እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥ መንግስት ስትራቴጂውን አሳትሞ ካወጣው አንድ አመት ከ5 ወር ያለፈ ቢሆንም እስካሁን መንግስ የመጀመሪያውን ምእራፍ እንኳ አልተሸገረም፡፡ ይህ የሆነው በመንግስት ውስጥ ያለ የአፈጻጸም ደካማነት እንዳለ ሆኖ ንግድ መርከቡ ለውጭ ሃገር ዜጎች ሊሸጥ አይገባም የሚል ሙግትበዘርፉ ላይ ካሉ ባለሞያዎች በመንግስት ላይ በስፋት በመነሳቱ ጭምር ነው፡፡
በዚህ ጽሁፍ የንግድ መርከቡ ሽያጭ ሊኖረው የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ እና ደህንነት ተኮር አንድምታዎች በአምስት ርእሶች ከፍዬ በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አ.ማ በገቢ ንግድ አጓዥነት የበላይ መሆን፡ መንደርደሪያ
ወደ ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ እቃዎችበአብዛኛው የሚገቡት በባህር ተጓጉዘው ነው፡፡ 90% የሚሆነው የሃገሪቱ እቃ ከውጭ የሚገባው በባህር ተጓጉዞ ነው፡፡ ከዚህም ኢትዮጵያ ዙሪያውያን ካሉ የጎረቤት ሃገራት ወደቦች አብዛኛው የሚገባው በጅቡቲ ወደብ በኩል ነው፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከውጭ ተጓጉዞ የሚገባ እቃ በመርህ ደረጃ እንዲገባ የሚደረገው በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክስዮን ማህበር በኩል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ይህንን ሚና በዋነኝነት እንዲጫወት የተደረገው በግንቦት 15 ቀን 1992ዓ/ም የወጣውን የጠቅላይ ሚኒስር ጽ/ቤትመመሪያተከትሎ ነው፡፡ ይህ መመሪያ በተለምዶ ‹‹የካሱ ዳይሬክቲቭ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ይህንን ስያሜውን ያገኘው በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ማእረግ የኢኮኖሚ ዘርፍኃላፊ በነበሩት ዶ/ር ካሱ ይላላ ተፈርሞ ወጪ የተደረገ መመሪያ በመሆኑ ነው፡፡
በመመሪያው መሰረት ማናቸውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የመንግስት ተቋምም ሆነ የግል አስመጪ ከሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በሚገኝ ገንዘብ የሚገዛቸውና የሚያስጭናቸው ገቢ እቃቆች በሙሉ በኤፍ.ኦ.ቢ (FOB) እንዲገዙና በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ መርከቦች እንዲጓጓዙ ያስገድዳል፡፡ ይኸውም ሃገሪቷ በምታገኘው ብድር እና እርዳታ የምትገዛቸውን እና የምታጓጉዛቸውን ንብረቶች አጓጉዛ ወደ ሃገር ውስጥ የምታስገባበትን ሂደት ይጨምራል፡፡
በሌላ በኩልአንድ አስመጪ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በኩል እቃውን አጓጉዞ እንዲያመጣ የማይገደድባቸው ሁኔታዎች በዚሁ መመሪያ ላይ በግልጽ ሰፍረዋል፡፡ ይኸውም በብድር ወይም በእርዳታ የሚገኘው ገንዘብ እና በዚሁ የሚጓጓዘው እቃ በገንዘብ አቅራቢዎቹ በቀረበ ጥያቄ በሌላ መንገድ እንዲጓጓዝ የሚያስገድድ ስምምነት ሲደረግ ነው፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አገልግሎት የማይሰጥባቸው ወደቦች ላይ የሚገኙ እቃዎችን ወይም ንግድ መርከብ አገልግሎቱን ቢሰጥ አዋጭ አይሆንልኝም ከሚላቸው ወደቦች በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በሚሰጥ ፍቃድ በሌላ መርከብ አስጭኖ እቃን ወደ ኢትዮጵያ ማስመጣትን መመሪያው ይፈቅዳል፡፡ይህ ፍቃድ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ማርኬተንግ ዲፓርትመንት በኩል ነው፡፡
ከላይ ከቀረበው ሃተታ በቀላሉ ለመረዳት እንደሚቻለው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በባህር ተጓጉዞ የሚገባውን የገቢ እቃ ማጓጓዝ ንግድበኤፍ.ኦ.ቢ ዳይሬክቲቩ መሰረት በብቸኝነት እና በበላይነት እየመራ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ የሃገር ውስጥ ፍጆታን የሚያጓጉዝባቸው መንገዶች
የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ያሉት መርኮች አስራ አንድ ብቻ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ዘጠኙ የተለያየ የጭነት አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ የሚችሉ መርከቦች ናቸው፡፡ በሌላ ቋንቋ ብትን ካርጎ (bulk cargo)፣ ኮንቴነር እንዲሁም ሌሎች አይነት ጭነቶችን ሊጭኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ መርከቦች አንድ የተለየ የእቃ አይነትን ብቻ እንዲያጓጉዙ ተደርገው የተሰሩ አይደሉም (The ships are conventional. They are not specialized)፡፡ በሌላ በኩል የተቀሩት የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ያሉት ሁለት መርከቦች ለተለየ አገልግሎት የተሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህ መርከቦች ለፈሳሽጭነት ማመላለሻነት እንዲያገለግሉ ተለይተው የተሰሩ ናቸው፡፡ ሁለቱ መርከቦች የተገዙበት አላማ በዋናነት ሃገሪቱ የሚያስፈልጋትን ነዳጅ ከውጭ ሃገራት ጭኖ በማምጣት አቅራቢያ ወደቦች ላይ ማራገፍ ነው፡፡
ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ባለበት የአቅም ውስንነት እና የገበያው የአሰራር ልማድ ባሳደረበት ተጽእኖ በወደብ በኩል ወደ ሃገር ውስጥ ከሚገቡ እቃዎች ውስጥ በራሱ መርከቦች ጭኖ ወደ ሃገር ውስጥ የሚያስገባው እቃ በባህር ተጓጉዞ ከሚመጣው 10% የሚሆነውን ብቻ ነው፡፡ ቀሪው 90%እቃ በባህር ተጓጉዞ አቅራቢያ ወደቦች ላይ የሚራገፈው በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በርከቦች ሳይሆን የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ የመጫኛ ቦታ በተከራያቸው የውጭ ሃገር የመርከብ ድርጅቶች አማካኝነት ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ 90%ሚሆነው በባህር ተጉዞ ወደብ ድረስ የሚመጣ እቃ ላይ የኢትዮጵያ ንግድመርከብ ትርፍ የሚያገኘው በውጭ መርከብ በሚያስጭንበት ሂሳብ እና በሃገር ውስጥ የሚገኘውን ነጋዴ በሚያስከፍለው ገንዘብ መካከል የሚገኘውን ትርፍ መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ይኸውም በተወሰነ መልኩ በአስመጪዎች የማስጫኛ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲኖር አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ
ባለበት የአቅም ውስንነት እና
የገበያው የአሰራር ልማድ
ባሳደረበት ተጽእኖ በወደብ
በኩል ወደ ሃገር ውስጥ
ከሚገቡ እቃዎች ውስጥ
በራሱ መርከቦች ጭኖ ወደ
ሃገር ውስጥ የሚያስገባው እቃ
በባህር ተጓጉዞ ከሚመጣው
10% የሚሆነውን ብቻ ነው::
- የገቢ እቃን በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በኩል ማድረግ፡ ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎች
መንግስት ማናቸውም በባህር ተጓጉዘው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ እቃዎች በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በኩል እንዲሆን ማድረጉ የራሱ የሆነ ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎች አሉት፡፡ እነዚህ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎች በመልካም እና በአሉታዊ ጎኖቻቸው ተለይተው ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ከነዚህም መካከል የሚከተሉት በዋናነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡-
የንግድ መርከብ የበላይነት አዎንታዊ ተጽእኖዎች
- የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ የገቢ እቃዎችን ሙሉ በሙሉ እንዲጭን የሚዘው መመሪያ በወጣበት ወቅት ቀላል የማይባል የውጭ ምንዛሪን ከዝርፊያ አድኗል፡፡ መመሪያው የወጣው በ1992 ዓ/ም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት መንግስት ገጥሞት ከነበረው ችግር ውስጥ አንደኛው የውጭ ምንዛሪን ከሃገሪቱ ካዝና ማሸሽ አንዱ ነበር፡፡ በወቅት በርካታ ኤርትራውያን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ሌሎች በርካታ ኤርትራውያንም ቢሆኑ ኢትዮጵያን ለቆ የመውጣት እቅድ የነበራቸው ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ በርካታ ባለሃብቶች ነበሩ፡፡ ይህንን ተከትሎ ታድያ በውጭ ያሉ ኤርትራውያን እና በሃገር ውስጥ ያሉት በሰፊው ገንዘብ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ማውጣት ይፈልጉ ነበር፡፡ በዚህም ዋነኛ የውጭ ምንዛሪን ማውጫ መንገድ ያደረጉት እቃ ከውጭ ማስመጣትን እንደሰበብ በመጠቀም ገንዘብ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ማድረግን ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ሲሉም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የአስመጪነት ፍቃድ ያለው ሰው ከሌላ አገር እቃ እንዲመጣለት በባንክ በኩል የውጭ ምንዛሪ ፍቃድ እንዲያገኝ ያደርጋሉ፡፡ ቀጥሎም በሲ.አይ.ኤፍ (CIF) እቃውን ውጭ ከሚገኘው ድርጅት ግዢ እንደፈጸመ አድርጎ በባንክ በኩል ይኸው ክፍያ በኤልሲ እንዲከፈል ያደርጋል፡፡ ሆኖም ግን ለባንክ በተሰጠው የማስጫኛ ሰነድ መሰረት መጣ የሚባለው ኮንቴነር የተባለውን እቃ ያልያዘ ሆኖ ይገኛል፡፡ ወይም ቅራቅንቦ ለሃገሪቷ ይላካል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እቃ ይመጣበታል ተብሎ ከሃገሪቱ ካዝና ወጪ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ ሳይመለስ ይቀራል፡፡ በዚህም ከሃገሪቱ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እንዲሸሽ ይደረጋል፡፡ ውጭ አለ የተባለው ላኪ ድርጅት ከገዢው እና ገንዘቡ ከኢትዮጵያ እንዲወጣለት ከሚፈልገው ግለሰብ ጋር በመመሳጠር ገንዘቡን ያሸሻል፡፡ ይህ በሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ላይ ቀላል የማይባል ተጽእኖቸ,ን አሳድሮ ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎ መንግስት ሌላው ቢቀር ለእቃ መጓጓዣ እና ለኢንሹራንስ የሚወጣውን ክፍያ በሃገር ውስጥ ለማስቀረት በሚል እሳቤ የኤፍ.ኦ..ቢ መመሪያውን አውጥቷል፡፡
- የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ አይ.ኤም.ኤፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በሚል ይሰጠው የነበረውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ እንዲያቋርጥ ሆኖ ነበር፡፡ አይ.ኤም.ኤፍ ይህንን እርዳታ ለኢትዮጵያ መስጠት ያቆመው ሃገሪቱ የሚሰጣትን ገንዘብ ለኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዋል ሲገባት ለጦር መሳሪያ ግዢ እያዋለችው ነው በማለት ነው፡፡ ይኸውም በሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ ይህንን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተወሰነ መልኩ ለማቃለል ሲል መንግስት በወቅቱ ገቢ እቃ በንግድ መርከብ በኩል እንዲሆን ማድረግን እና ኢንሹራንስ ሃገር ውስጥ ከሚገኝ መድን ሰጪ ድርጅት በብር እንዲገዛ ማድረግን እንደ መፍትሄ ወስዷል፡፡ በእውነትም እርምጃው ስኬታማ ነበር፡፡
- አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና ፖለቲካዊ ትኩሳት ተከትሎ በርካታ ባለሀብቶች እና ፖለቲከኞች ገንዘባቸውን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከሃገር ለማውጣት ይፈልጋሉ፡፡ አሁን ባለው አካሄድ መንግስት የኦፍ.ኤ.ቢ መመሪያውን ቢያነሳ በ1990 ዎቹ አጋጥሞ የነበረው የገንዘብ ማሸሽ መደገሙ የማይቀር ይመስላል፡፡
የንግድ መርከብ የበላይነት አሉታዊ ተጽእኖዎች
- ከላይ ለመጥቀስ እደሞከርኩት የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በራሱ መርከቦች አስጭኖ ወደ ሃገር ውስጥ የሚያስገባው አሥር በመቶ የሚሆነውን ገቢ እቃ ብቻ ነው፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው ገቢ እቃ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ የመጫኛ ቦታ በተከራያቸው የውጭ ሃገር የመርከብ ድርጅቶች አማካኝነት ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ 90 በመቶ የሚሆነው እቃ ላይ የኢትዮጵያ ንግድመርከብ ትርፍ የሚያገኘው በውጭ መርከብ በሚያስጭንበት ሂሳብ እና በሃገር ውስጥ የሚገኘውን ነጋዴ በሚያስከፍለው ገንዘብ መካከል የሚገኘውን ትርፍ መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ይኸውም በተወሰነ መልኩ በአስመጪዎች የማስጫኛ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲኖር አድርጓል፡፡
- በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ውስጥ የሚታየው አስተዳደራዊ መዋቅር ለንግድ አመቺ አይደለም፡፡ በተቋሙ ስር ያሉ ኃላፊዎች ለንግድ ስራ ሳይሆን ለመንግስታዊ አስተዳደር ስራ የተመቹ ናቸው፡፡ በዚህ የአስተሳሰብ ችግር የተነሳ በርካታ በዋጋ ረገድ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ እርምጃዎች እንዳይወሰዱ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም በተቋሙ ውስጥ ለንግድ አስፈላጊ የሆነው ፈጣን ውሳኔ አይወሰንም፡፡ ይኸው በቢሮክራሲያዊ አስተሳሰብ የናወዘ አቋም ተቋሙ የተሻለ የሎጅስቲክስ አገልግሎት ለገቢ እቃዎች እንዳይሰጥ አድርጎታል፡፡ በዚህ ብቻም ሳይወሰን ይህ ተቋም እራሱን ከመንግስት ባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት ነጻ ሊያደርግ አልቻለም፡፡ ይህ ባልሆነበት እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠትና ለማደግ እንዳይችል አድርጎታል፡፡
ከላይ በተነሱት ምክንያቶች በገቢ ንግዱ ላይ አላስፈላጊ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዲያሳድር ሆኗል፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛውን ጊዜ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሃገር የሚሄድ የወጪ ንግድ ጭነቶች በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት በኩል የማይሆነው፡፡
የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና የሃገር ደህንነት
የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ተከትሎ በተለያዩ ጉዜያት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በአውሮፓ ህብረት የጦር መሳሪያ ግዢ እና ማጓጓዝ ላይ የጦርነቱ ተካፋይ በነበሩት በሁለቱ ሃገራት ላይ ማእቀብ ጥለው ነበር፡፡ የማእቀቦቹን የኋሊት ታሪክ ለማየት ያህል አስቀድሞ በሃገራቱ ላይ የጦር መሳሪያ ግብይት ማእቀብ የተጣለው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ነው፡፡ ይኸውም የሆነውበየካቲት 03 ቀን 1991ዓ/ም በዩ.ኤን ሪዞሉሽን ቁ 1227 ሲሆነ በይዘቱም አስገዳጅ አልነበረም፡፡ ይህ የመሳርያ ሽያጭ ማእቀብ ሃገራት ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤረርትራ የጦር መሳርያ እንዳይሸጡ ምክረ ሃሳብ የሚሰጥ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የዚህን ሪዞሉሽን መኖር ወደ ጎን በመተው የተለያዩ ሃገራት ለሁለቱም ሃገራት የጦር መሳሪያ ማቅረብ ቀጥለዋል፡፡ ይህንን የተመለከተው የአውሮፓ ህብረት በመገጋቢት 06 ቀን 1991ዓ/ም አስገዳጅ የሆነ የጦር መሳሪያ ግብይት ማእቀብ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ጥሏል፡፡ ይህ ማእቀብ ሃገራት ለኢትዮጵያ ማናቸውንም የጦር መሳርያ፣ መለዋወጫ፣ ጥገና እንዲሁም ቴክኒካዊ እገዛ እንዳይሰጡ የከለከለ ነው፡፡ በዚህ ብቻም ሳይወሰን ማእቀቡ ከተጣለ በኋላ ግዢ የተፈጸመባቸውን የጦር መሳርያዎች ማናቸውም አጓጓዦች ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የጦር መሳርያ ጭነት (የማጓጓዝ) አገልግሎት እንዳይሰጡ ከልክሏል፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ በግዢ ብታገኝ እንኳን የሚያጓጉዝላት እንዳታገኝ አድርጓል፡፡ ይባስ ብሎ በግንቦት 09 ቀን 1992ዓ/ም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ አስገዳጅ የሆነ የጦር መሳሪያ ግብይት ማእቀብ ጥሏል፡፡ ይህ ማእቀብ ሃገራት ለኢትዮጵያ ማናቸውንም የጦር መሳርያ፣ መለዋወጫ፣ ጥገናና እንዲሁም ቴክኒካዊ እገዛ እንዳይሰጡ የከለከለ ነው፡፡ በተጨማሪ ማእቀቡ የመርከብ እና የሌላ ማጓጓዣ ባለሃብቶች ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የጦር መሳርያ ጭነት (የማጓጓዝ) አገልግሎት እንዳይሰጡ ማእቀቡ ከልክሏል፡፡በዚህ የተነሳ የኢትዮጵያ መንግስት በጦር መሳርያ አቅርቦት እጥረት እንዲያጋጥመው አድርጓል፡፡
ይህንን ችግር ለመጋፈጥ ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በካሱ ኢላላ የተፈረመውን መመሪያ ለማውጣት ተገዷል፡፡ መመሪያው የወጣበትን ቀን ስንመለከትም የተባበሩት መንግስታትን ማእቀብ ለመቋቋም የወጣ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማእቀቡን የጣለው በግንቦት 09 ቀን 1992ዓ/ም ሲሆን መመሪያው ደግሞ የወጣው በግንቦት 15 ቀን 1992ዓ/ም ነው፡፡ የቀኑ ቅርበት በራሱ የሚናገረው ነገር አለ፡፡ መመሪያው የተተገበረበትን አካሄድ የሚያውቁ የመረጃ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ወደኢትዮጵያ የሚገባ ማናቸውም እቃ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በሁኩል ይጓጓዝ የሚለው መደምደሚያ ላይ ከተደረሰ በኋላ ማናቸውም እቃዎች በተቻለ መጠን በነዚሁ መርከቦች እንዲጫን ተደርጓል፡፡ የገቢ እቃዎችን ከመጫን ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ለማጓጓዝ ከምትፈልጋቸው ወደቦች ከሌሎች እቃዎች ጋር ቀላቅላ በመጫን ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገባ አድርጋለች፡፡ ይህንን ስራ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ከመንግስት እጅ ውጭ በሆኑ ባለኃብቶች እጅ የሚገኝ ቢሆን ኖር የግዳጁን ሚስጥራዊነት እና ተግባራዊነት አጠራጣሪ ሊያደርግ እንደሚችል በዘርፉ ላይ ያሉ ባለሞያዎች ይስማማሉ፡፡
- ባህር ትራንስፖረትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ሽያጭ ውጤት እና ስጋት
ከላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት ንግድ መርከብን መሸጥ የራሱ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እና የደህንነት መለኪያዎች ይኖሩታል፡፡
የንግድ መርከብን ድርሻ በተወሰነ መልኩ ለግለሰብ ነጋዴዎች መሸጥ፤ ሁሉም ገቢ እቃ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ብቻ ይጫን የሚለው መመሪያ እንዲነሳ ምክንያት ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ነጋዴዎችን የትርፍ ህዳግ ለማሳደግ ሲባል መመሪያ የበላይነት ኖሮት እንዲቀጥል የሚደረግበት አግባብ የለምና፡፡ ግለሰቦች በተቋሙ ውስጥ ድርሻ ገዝተው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ አስመጪው የነዚህን የተመረጡ ነጋዴዎች ኪስ ጎን ለጎን እንዲያደልብ የሚደረግበት አግባብ የለም፡፡
ለኢትዮጵያ ንግድ መርከብ የበላይነትን የሰጠው ይኸው መመሪያ የሚነሳ ከሆነ ንግድ መርከብን በመሸጥ የሚገኝ እዚህ ግባ የሚባል ትርፍ አይኖርም፡፡ አንድ ንግድ በዋናነት የሚሸጠው መልካም ዝናው (Good will) ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ቆሞ እየሄደ ያለው በመመሪያ ባገኘው የበላይነት /ሞኖፖሊ/ ነው፡፡ ይህ የበላይነትን የሚሰጥ መመሪያ ቢነሳ ንግድ መርከብ ገበያውን ተቋቁሞ መቀጠሉ አጠያያቂ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነም ያገለገሉ መርከቦችን በዋጋቸው ከመሸጥ በዘለለ ለኃገሪቱ የሚያመጣው አንዳች ትርፍ የለም፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ መርከብን መሸጥ የደህንነት ስጋቶች አይኖሩትም ወይ የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ በእርግጥ ይህ ጥያቄ በተለያዩ ደረጃዎች ባሉ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ሳይነሳ አልቀረም፡፡ ሆኖም ግን ጸሃፊው ባለው መረጃ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የንግድ መርከብ መሸጥ በኢትዮጵያ ላይ የደህንነት ስጋትን ሊፈጥር አይችልም የሚል አቋም ይዟል፡፡ በጸሃፊው እምነት እንደዚህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የአስፈጻሚው አካል አቋም በአግባቡ ሊፈተሽ የሚገባው ነው፡፡ ከኋላ ታሪካችን ለማየት እንደምንችለው ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች በመሳሪያ እጦት ለተጠቂነት ተጋላጭ ሆናለች፡፡ በትንሹ ሁለት ጊዜ በጣልያን የተቃጣባትን ወረራ፣ የሱማልያን ወረራ እንዲሁም የኢትዬ-ኤርትራን ወረራ ማውሳት ይቻላል፡፡ በሁሉም ጦርነቶች ላይ ኢትዮጵያ በጦር መሳሪያ ሎጅስቲክስ አቅርቦት ችግር የተነሳ ተጎድታለች፡፡ የኋላ ኋላ በዜጎቿ ወኔ ታፍራና ተከብራ ትቁም እንጂ በአብዛኛዎቹ ጦርነቶች በመሪዎቿ ቸልተኝነት በጦር መሳርያ እና በጦር ሰራዊት ሎጀስቲክስ ችግር አገር ቆስላለች፡፡ ይህ ከዚህ በኋላ ሊደገም አይገባውም፡፡ ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን ለማስጠበቅ እና ከውጭ አጥቂዎች ራሷን ለመጠበቅ ስትል ድርጅቱን በመንግስት አልያም በዜጎቿ እጅ እንድታቆየው ሊደረግ ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ሃገሪቱ የወጪ እና ገቢ ንግድ ስርአቱ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያለስጋት የዜጎቿን ፍላጎት ሊያረካ የሚያስችል አቅም እንዲኖራት ያደርጋል፡፡ ከዚህ አልፎም በተለያዩ ምክንያቶች የሃገሪቱን ደህንነት መጠበቅ አስፈላጊ ሲሆን ንግድ መርከቡ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሃገሪቱን ሊታደጋት ይችል ይሆናል፡፡
ከላይ በቀረቡት ትንታኔዎች መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ መርከብን ስለመሸጥ ብቻ ከማሰብ ሌሎች አማራጮችን መመልከቱም መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ የንግድ መርከብን ድርሻ ለግል ባለሃብቶች ከመሸጥ ይልቅ ንግድ መርከብ በመንግስት እጅ እንዲቆይ ማድረጉ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም ምንአልባት ንግድ መርከብ የመንግስት እቃን እንዲያጓጉዝ በማድረግ ውጪ ባለው ጉዳይ የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ ላይ እንዲሰማሩ ሊፈቀድ ይችል ይሆናል፡፡ ይህም ቢሆን ሰፊ ጥናትን ይፈልጋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ጠበቃ፤ የሕግ አማካሪና የዩኒቨርስቲ መምህር ሲሆኑ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ፀሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡