ክፍል ፪
የኩሽ ነገድ በመፅሀፍ ቅዱስ እሳቤ
በመፅሀፍ ቅዱስ ያለውን የኩሽ አገባብ በርካታ ስራዎች ሲመረምሩት ቆይተዋል። በሀገራችን እንኳ ሩቅ ሳንሄድ ኪዳነወልድ ክፍሌን (1948) እና ተክለፃዲቅ መኩሪያን መጥቀስ ይቻላል። የኤፍሬም ይስሐቅ (1980) ኩሽ፣ ጁዳይዝም እና ስሌቨሪ ‘ኩሽ፣ ይሁዲነት እና ባርነት’ የሚለው መጣጥፍ የኩሽን አገባብ በስፋት በመፅሀፍ ቅዱስና በድኅረ-መፅሀፍ ቅዱስ የአይሁድ እምነት ስራዎች ውስጥ የሚመረምር ነው።
ኩሽ (እና ከዚህ ስር የወጡ ቃላት) በተለያዩ ቋንቋዎች ባሉት መፅሀፍ ቅዱስ ተመሳሳይ አይደለም። በአንድ ቋንቋ በተለያየ ወቅት በሚገኙ መፅሀፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ እራሱ ልዩነት አለ። በእብራይስጥ ኩሽ የሚለውን በሶስተኛው መቶ ቅጋአ (ቅድመ ጋራ አቆጣጠር) ወደግሪክ የተተረጎመው ብሉይ ኪዳንና ሌሎች የእብራይስጥ ፅሁፎች ላይ በወጥነት ኢትዮጵያ በማለት ቀርቧል። እንደዚሁም፣ ቨልጌት የሚባለው የአራተኛው ክፍለዘመን የላቲን መፅሀፍ ቅዱስ ትርጉምም ኢትዮጵያ በሚል ያቀርበዋል። በእንግሊዝኛው ኪንግ ጀምስ ቅጂ ኢትዮጵያ የሚለውን ከኩሽ ከሚለው ጋር እናገኛለን። ለምሳሌ፣ የካም ልጆችን ሲዘረዝር (ዘፍ 10፡6, 1መዋ 1፡8፣ 1መዋ 1፡9፣ 1መዋ 1፡ 10) ኩሽ ሲል፣ በሌሎች በርካታ ቦታዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ይላል። በአማርኛው መፅሀፍ ቅዱስ ያለው ሁኔታም እንደዚሁ ነው። ለምሳሌ፣ በ1962 በወጣው መፅሀፍ ቅዱስ ላይ ኩሽ (ዘፍጥረት 10:6፣ 7 እና 8)፣ ኢትዮጵያ (ዘፍ 2፡13፣ 2መሳ 19፡9፣ አስ 1፡1፣ አስ 8፡9፣ ወዘተ)፣ እንዲሁም ኵሲ (2ሳሙ 18:21፣ 2ሳሙ 18:22፣ 2ሳሙ 18:23፣ 2ሳሙ 18:31፣2ሳሙ 18:32፣ ኢር 36፡14፣ ሶፎ 1፡1) እና ኩዝ (መዝ 7፡መግቢያ [7፡1]) እናገኛለን። ከእብራይስጡ ለመስማማት በእንግሊዝኛው ቅጂ ከግሪኩ ኢትዮጵያ የሚለውን በመተው ኩሽ የሚለውን ብቻ በመውሰድ የቀረቡ የቅርብ ግዜ ቅጂዎች አሉ። የዚህን ቃል አገባብ በመፅሀፍ ቅዱስ ስንመረምር ለሁለት ነገሮች ውሎ እናገኛለን። አንድም፣ ህዝብን (ማ. ነገድን ወይም ግለሰብን)፣ እና ሁለትም ሀገርን ሲገልፅ ይታያል። ሀገርን የሚገልፀው በእንግሊዝኛው ኪንግ ጀምስ ቅጂም ሆነ በአማርኛው በ1962 ህትመት ላይ ብዙውን ግዜ ኢትዮጵያ በሚል ይገኛል።
ኩሽ የሚለው ወይም ከዚህ ቃል የወጡ በመፅሀፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን በድኅረ-መፅሀፍ ቅዱስ ባሉ የአይሁድ ስራዎች ህዝብን እና ሀገርን ለማመልከት ሲውል እንደሚገኝ በመስኩ ጥናት ያደረጉ በርካታ ባለሙያዎች ሲገልፁ ኖረዋል።
በመፅሀፍ ቅዱስ ያለው ኩሽ የወከለው ከግብጽ በስተደቡብ ያለውን በቀዳሚዎቹ የተመለከትንውን ሀገርና ነገድ ብቻ አይደለም። ከላይ እንደገለፅንው ኩሽ የካም የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን፣ ሚዝራም (ግብፅ)፣ ከነዓን (የከነዓን ምድር)፣ እና ፑት ወንድሞቹ ናቸው። ኩሽ በዘፍጥረት 10፡6 እና መዋዕለ ቀዳማዊ 1:8 የኒምሮይድ አባት ነው። ኒምሮይድ እንደአይሁዶች ዘልማድ የመጀመሪያውን መንግስት በባቢሎን የመሰረተ ታላቅና ኃይለኛ ንጉስ ነበር። በኦሪት ዘኁልቆ 12፡1 የሙሴ ሚስት ኢትዮጵያዊ/ኩሽ ይላታል። ይሁን እንጂ የሙሴ ሚስት ዚፎራ/ሲፎራ ከሚዲያን እንደሆነች በተለያዩ ቦታ ተገልፆ ይገኛል። ሚዲያን ደግሞ ትክክለኛው ቦታ የት እንደሆነ የተለያየ አስተያየት ቢኖርም፣ በመካከለኛው ምስራቅ የነበረ ሀገርን እንደሚያመለክት ሁሉም ማለት ይቻላል የታሪክ ባለሙያ የሚስማሙበት ነው። ሌላኛው በእብራይስጥ መፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ኩሽ ስለተባለው ሰው በመዝሙር 7 ላይ የተገለፀው የብንያማዊው ሰው ነው። ይህ ሰው የሳኦል ተከታይ እንደነበር ይገመታል።
አንዳንድ ቀደምት ስራዎች የሁሉም ምንጭ መፅሀፍ ቅዱስ አድርግው ከማሰብ ኩሽ የሚለው ቃል ከግብፅ ደቡብ ለሚኖረው ህዝብና ሀገር መዋል የጀመረው ከመፅሀፍ ቅዱስ በመውሰድ ነው ቢሉም፣ እብራይስጥ እራሱ ቃሉን የወሰደው በተገላቢጦሹ ከሀገሩ ስያሜ መሆኑን መገመት አዳጋች አይደለም። ባለፈው ክፍል እንደተመለከትንው ኩሽ አዲስም ሆነ ብሉይ ኪዳን የሚባል ሳይፃፍ የነበረ ስያሜ ነው። ይህ ቃል ዳዊት ነገሠ ከተባለበት ከሺህ ዓመት በፊት የነበረ ቃል ነው። ለመጀመሪያ በግብፅ ስራዎች በተጠቀሰበት በ11ኛው ስርወመንግሥት በ2100 ቅጋአ ራሱን የቻለ እብራይስጥ የተባለ ቋንቋም ሆነ የአይሁድ ህዝብ አይታወቅም። የእብራይስጥ ምሁር የሆነው ዴቪድ ጎልደንበርግ (ገፅ 18)ም የእብራይስጡ ኩሽ በግብፅ ስራዎች ከእነሱ ደቡብ ለሚኖሩት መጠሪያነት ካዋሉት ካሽ ከሚባለው ቃል ነው የመጣው ይላል። የእብራይስጥ መፅሀፍ ቅዱስ በተፃፈበት ወቅት የኩሽ/ኑቢያ መንግስት ዋና መቀመጫው ሜሮኤ ነበር። በመፅሀፍ ቅዱስ ይህን ቦታ በተለይ የሚመለከት ተደርጎ የተጠቀሰበትም አለ። ለምሳሌ፣ ሕዝቅኤል 29፡10ን፣ ናሆም 3:9ን ይመልከቱ።
ኩሽ፣ ኢትዮጵያና ጥቁረት
የኩሽ መንግስትንም ሆነ በመፅሀፍ ቅዱስ የሚገኘውን ኩሽ የተሰኘውን ነገድ በጥንታዊ ግሪክ ኢትዮጵያ ይለዋል። ግሪኮች ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ተጠቅመው የምናገኘው ከሆሜር እና ሄሮዱተስ ጀምሮ ነው። ቃሉንም የተጠቀሙበት ወጥ በሆነ መልኩ አይደለም። አንዳንዴ መላው አፍሪካን ለማመልከት ነው። ከላይ እንደገለፅንው በግሪክ ኢትዮጵያ ማለት በፀሀይ የተቃጠለ ፊት ያለው ህዝብ ማለት ነው። ይህን የኛ ሀገር ቀደምት የታሪክ ፀሀፊዎችም ተገንዝበውታል። ለምሳሌ ተክለፃዲቅ (1951፡12)ን ይመልከቱ። በጥንታዊ ግሪክ ፀሀፊዎች ስለዚህ ሀገርና ህዝብ ያለውን አጠቃቀም፣ በአንደኛው ክፍለዘመን የነበረው ስትራቦ ጂኦግራፊያ በሚለው መፅሀፉ በምዕራፍ አንድ በዝርዝር የቃኘበትን ክፍል መመልከት ጠቃሚ ነው።
የኦሪት ዘፍጥረትን ወደግሪክ በአራተኛው መቶ ቅጋአ ሲመልሱ ኩሽ የሚለውን ኢትዮጵያ ብለውታል። ይህ የግሪኩ ስራ ሴፑጊነት በመባል የሚታወቀው ነው። በዚህ ስራ በእብራይስጡ ኩሽ የሚለውን የተረጎመው ኢትዮጵያ እያለ ነው ። ኢትዮጵያ ማለት የተቃጠለ ፊት ማለት ነው። በሀገር ስምነትም ጥቁር ህዝብ የሚኖርበትን አፍሪካንና የተወሰነ የኤስያን ክፍልም ያመለክት ነበር። የዚህ ቃል ፍቺ መለጠጥ ኩሽ ወይም ኢትዮጵያ አፍሪካን ባጠቃላይ አንዳንዴ ሲያመለክት በመጥበብ ደግሞ የጥንቱን ኩሽ ግዛት ያመለክታል። ይህን ጉዳይ፣ የኛ ፀሀፊዎች ሳይቀሩ የተገነዘቡት ጉዳይ ነው። ለምሳሌ፣ ኪዳነወልድ ክፍሌን (1948)፣ ኅሩይ ወልደስላሴ (1999) እንዲሁም ተክለፃዲቅ መኩሪያን ከብዙ በጥቂቱ ይመልከቱ።
የቃሉ በሀገር ስምነትም ሆነ በህዝብ ስምነት የነበረው ውክልና በታሪክ ሁልግዜ አንድ አልነበረም። ከላይ በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ እንደተመለከትንው በታሪክ ፀሀፊዎችም ያለው አጠቃቀም እንደታሪክ ፀሀፊው የጂኦግራፊ እውቀት ይወሰን ነበር። ከክርስትና በፊት በግሪኮች ስላለው አጠቃቀም ዳሰሳ የአንደኛው መቶ ክፍለዘመን የነበረውን ስትራቦን መመልከት ጠቃሚ ነው። ስትራቦ እራሱ ኢትዮጵያ ሲል መላው አፍሪካን የሚያካትት ነው። እዚህ ላይ ጃክሰን (1939:4-5) ስታሮቦ እና ከሱ በፊት የነበሩት ስለቃሉ ያላቸውን አጠቃቀም የገለፀውንም ይመልከቱ። በግሪኮችና በሮማኖች ቃሉ ስለነበረው አጠቃቀምና ስለአጠቃላይ ጥቁር ህዝቦች ስኖውደንን (1970) መመልከቱ ጠቃሚ ነው።
ኢትዮጵያ በታሪክ ለአሁኒቷ ሀገር መጠሪያ እራሱ ተወላጁ አውሎት የምናገኛው ወደ አራተኛው ክፍለዘመን አካባቢ ነው። በቀዳሜ ክፍሎች እንደገለፅንው ኢዛና ግዛቶቼ ባላቸው ስር በግሪኩ ኢትዮጵያ ብሎ የጠቀሰው በሳቢያን እና ግዕዝ ‘ሀበሻ’ የሚለውን የሚመለከት ነው። ይህ ግዛት ከሰሜን ኢትዮጵያ ይዞ በአክሱማውያን ይተዳደር የነበረውን ቢያንስ እስከ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ያለውን የሚያካታት ነው። ኢዛና ግዛቴ ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ ጽያሞ በምዕራብ ኢትዮጵያ ጋምቤላን የሚመለከት ነው (ስርግው 1972፡94ን ይመለከቱ)። የሚገርመው አንዳንድ የኩሽ ሰዎችም ሀገራቸውን ኢትዮጵያ ያሉበት መረጃዎች አሉ። ለዚህ ዋናው ተጠቃሹ የስድስተኛው ክፍለዘመን ጋአ የሲልኮ ፅሁፍ ነው (በጅ 1928፡114ን ይመልከቱ)።
***
ታሪካዊው የኩሽ/ኑብያ ስርወመንግሥት በአፍሪካ የነበረ የጥቁሮች መንግሥት መሆኑ ጥያቄ የለውም። ይህ መንግስትን ግሪኮች ኢትዮጵያ ይሉት ነበር። ኩሽም ሆነ ኢትዮጵያ ከጥቁረት ጋር እየተያያዘ ለመላው አፍሪካና ሌሎች ጠቆር ላሉ ህዝቦችና እነዚህ ህዝቦች ለሚገኙባቸው ሀገሮች ሲውል ቆይቷል። የአብረሀም እምነት፣ ስለፍጥረት ትንታኔ ሲሰጥ አንድም ከዚህ ጋር እያዛመደ፣ አንዳንዴም ከዚህ እየዘለለ ማቅረቡን አይተናል። ኩሽ በመፅሀፍ ቅዱስ ያለው እሳቤ ሙሉ በሙሉ ከታሪካዊው ኩሽም ሆነ ከህብረተሰቡ የዘርም ሆነ የቋንቋ ግንኙነት/ዝምድና አንድ ነው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ፣ ከነኣን የኩሽ ወንድም የሀም ልጅ ተደርጎ ሲቀርብ፣ እስራኤሎች ደግሞ ከሀም ወንድም ከሴም የተወለዱ ተደርገው ቀርበዋል። ከነአን ይናገሩት የነበረው ቋንቋ፣ ከእብራይስጥ ጋር በጣም የሚቀራረብ የዘዬ ያህል ሊታይ የሚችል የንግግር አይነት ነው። እነዚህ ህዝቦች የሚኖሩትም አንድ ቦታ ወይም ጎን ለጎን ከእስራኤሎች ጋር ነበር። ለእስራኤሎች ከእነዚህ ህዝብ በላይ በዝምድና የሚቀርባቸው አልነበረም። እስራኤሎች በኦሪት ያለውን ታሪክ ሲያቀናብሩ ከከነአኖች ጋር ደመኛ ስለነበሩ፣ ከነአኖችን ከነሱ በዝምድና ማራቅ ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሄርም እርግማን እንዳለባቸው በማድረግ ለማቅረብ ሞክረዋል የሚል ግምት አለ። ከነአን የኩሽ ወንድም ሊያስብላቸው የቻለውም ምክንያቱ ይህ ሊሆን ይችላል። ኑምሮእድ የባቢሎን/የአካድያን መስራች ተደርጎ የተወሰደው ካየን አካዶች ሴሚቲክ እንጂ የኩሸቲክ ቋንቋ ወገን ተናጋሪ አይደሉም። ስለዚህም በእብራይስጥ ቋንቋ እራሱ ኩሽን ከጥቁረት ጋር ማያያዝ የተጀመረው ጎልደንበርግ እና ሌሎችም በርካታዎች እንዳሉት የግሪኩን ትርጉም በመመልከት ወደኋላ ላይ የመጣ ነው።
ኩሸቲክ
ኩሸቲክ በአፍሮኤስያዊ ስር ለሚመደቡ ቋንቋዎች (እና እነዚህን ቋንቋዎች ለሚናገሩ ህዝቦች) መጠሪያ የሚውል የቤተሰብ ስም ነው። በዚህ ቤተሰብ ስር ባሁኑ ወቅት የሚመደቡት፤ (1) ማእከላዊ ኩሸቲክ፣ (2) ሰሜን ኩሸቲክ፣ (3) ደቡብ ኩሸቲክ፣ እና (4) ምስራቅ ኩሸቲክ ናቸው። ኦሞቲክ በቀደምት ስራዎች፣ ምዕራብ ኩሸቲክ በሚል በዚሁ የቋንቋ ቤተሰብ ስር ይመደብ ነበር። ፍለሚንግ በተለያዩ ስራዎች ይህ የቋንቋ ቤተሰብ እራሱን ችሎ (በአፍሮኤስያዊ ስር) አንድ የቋንቋ ቤተሰብ እንደሆነ ካሳየ በኋላ በኩሸቲክ ስር የመመደቡ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ቀርቷል። ባሁኑ ወቅት በዚህ ጉዳይ ብዙም የሚያከራክር አይደለምና የኦሞቲክን ጉዳይ እዚህ አናየውም። ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ ቅፅ ሁለትን ይመልከቱ። ለተለየ አመለካከት ግን ዛቦርስኪ (1986)ን ይመልከቱ።
ኩሽ የሚለውን ቃል ለቋንቋ ቤተሰብ እና ያንን ቋንቋ ለሚናገሩ ህብረተሰብ ማዋል የተጀመረው ሴም የሚለውን ቃል ለዚሁ ተግባር መዋሉን በማስተዋል ነው። በኩሸቲክ እና በሴሜቲክ ቋንቋዎች መሀከል መመሳሰል መኖሩን ማስተዋል የተጀመረው ወደኋላ እስከ 17ኛው ክፍለዘመን ይሄዳል (ላምበርቲ 1991፡52)። ሴማዊ ያልሆኑ ግን ከሴም ቋንቋዎች ጋር የሚመሳሰሉ ቋንቋዎች ሲገኙ በ19ኛው ክፍለዘመን እነዚህ ቋንቋዎች ሀሜቲክ የሚል ስያሜ ተሰጣቸው። አሁን አፍሮኤስያዊ የሚባለው ግዙፍ የቋንቋ ቤተሰብ በመነሻው የሚታወቀው ሀሚቶ-ሴሚቲክ በመባል ነበር። በወቅቱም ጥናቶቹ የሚያተኩሩት ሀሜቲክ የተባሉትን ከሴሜቲክ ቋንቋዎች አንፃር መተንተን ላይ ነበር። ሀሜቲክ የተባሉት ቋንቋዎች ግን በውስጣቸው የሴምቲክ የቋንቋ ቤተሰብ ያህል የሚታዩ በርካታ ቡድኖች የሚመሰርቱ መሆናቸው ሲታወቅ ይህን ስያሜ በመተው እራሳቸውን ችለው በተለያዩ ስያሜዎች መጠራት ተጀመረ። የቋንቋው የቤተሰብ ስያሜም ተለውጦ አፍሮኤስያዊ ተባለ። እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን በአፍሮኤስያዊ ደረጃ የሚታዩ በአፍሪካ ደረጃ ብቻ ቢያንስ ሌሎች ሶስት የቋንቋ ግዙፍ ቤተሰቦች መኖራቸው ነው። በመፅሀፍ ቅዱስ እሳቤ ከሄድን እነዚህ ብቻ ሳይሆን በአለማችን ያሉ ሁሉ የቋንቋ ግዙፍ ቤተሰቦች አንድ ብቻ በሆኑ ነበር። የቀረው ያፌት ነውና። ሀሜቲክ፣ ሴሜቲክ የሚሉት ቃላት ከመፅሀፍ ቅዱስ ካለው ቢወሰዱም በቋንቋ ቤተሰብ ስያሜነታቸው ፈፅሞ የመፅሀፍ ቅዱስን የዘር ግንድ እሳቤ መሰረት ያደረጉ አይደለም። ይህ ባለመሆኑም ነው አሁን ይህ ቃል ታላቅ የቋንቋ ቤተሰብ አፍሮኤስያዊ የሚባለው። ይህንንም ትቶ ሌላ ማለት ይቻላል። በርግጥም ሌሎችም ስያሜዎች አሉ። ለዝርዝሩ ሆጅ (1976:43)ን ይመልከቱ።
የኩሽ ቋንቋዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና ምደባ
ኩሸቲክ ተዘውትረው ከሚጠሩት ስድስት የአፍሮኤሽያዊ ታላቅ ቤተሰብ ቅርንጫፎች ውስጥ አንደኛው ቤተሰብ ተደርጎ ቢወሰደም፣ ይህ ምደባ ያልለቀለት አይደለም። ኩሸቲክ እንደተቀሩት ቤተሰቦች በእኩል ደረጃ የሚታይ አንድ ቤተሰብ ተደርጎ መወሰድ አይገባውም የሚሉ ትንሽ የማይባሉ ጥናቶች አሉ። ቀረብ ብለን ስንመረምርም የምናገኘው እውነታ ከእነዚህ ጥናቶች ጋር ተመሳሳይ ነው፤ በኩሸቲክ ቋንቋዎች ውስጥ ያለው ግንኙነትም ጥብቅ አይደለም። በእያንዳንዳቸው ንኡሳን የቋንቋ ቤተሰቦች ውስጥ ያለው ክፍፍል በየወቅቱ እየታደሰ ያለ ከመሆኑም በላይ፣ በየክፍሎቹ መሀከል ያለው ግንኙነት እንኳ ገና መፍትሄ አላገኘም። ለዚህ አንደኛው ምክንያት በየቋንቋዎቹ ላይ አጥጋቢ ጥናት አለመደረጉ ነው። ትንሽ የማይባሉት ቋንቋዎች ገና መሰረታዊ የሰዋስው ጥናት እንኳ ያልተደረገባቸው ናቸው። በማናቸውም የሀገራችን ቋንቋዎች ላይም ቢሆን አጥጋቢ ጥናት ተደርጓል የሚያስብለን ደረጃ ላይ አይደለንም። ትንሽ ጥናት በተደረገባቸው ቋንቋዎች ላይ እንኳ ያለው ሁኔታ በታች ደረጃ በአንዳንዶቹ ለምሳሌ ኮንሶና ኦሮምኛ፣ ሱማልኛና ሬንድባሬ፣ የአገው ቋንቋዎች፣ የደጋማው ኩሸቲክ ቋንቋዎች መሀከል እርስ በርስ ግልፅ የሆነ ዝምድና ቢኖርም ወደላይ በሄድን ቁጥር (ማ. ከፍ ባለ የቤተሰብ ደረጃ ሲደርስ)፣ ግንኙነቱ በጣም ደካማ/ስስ ነው። ይህም ዝምድና አብዛኛው የተወሰኑ ምእላዶችን ከመያዝ ላይ የመጣ እንጂ በመሰረታዊ የቃላት ደረጃ ግንኙነቱ በጣም አናሳ ነው። በምዕላድ ደረጃም ቢሆን በኩሸቲክ ስር የተመደቡት ከሌሎቹ በበለጠ ይቀራረባሉ ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ ቤንደር (1997ሀ&2003) በኩሸቲክ ስር ያሉትን ንዑስ ቤተሰቦች ያስቀመጣቸው በእኩል ደረጃ ከበርበር እና ሴሜቲክ ጋር ነው። በአፍሮኤስያዊ ስር የራሳቸውን ክፍል ይዛመዳሉ ብሎ ማክሮ-ኩሸቲክ በሚል ስያሜ ስር የመደባቸው በእኩል ደረጃ የሚታዩ ቡድኖች ከበርበርና እና ሴሜቲክ ተርታ፣ ማዕከላዊ ኩሸቲክ/አገው፣ ቤጃ፣ ደጋማው ምስራቅ ኩሸቲክ፣ እና ቆላማው ምስራቅ ኩሸቲክ (ደቡብ ኩሸቲክን ጨምሮ) ናቸው (ቤንደር 2003: 29)። ኦሬልና ስቶልቦቫ (1995) በኩሸቲክ ስር ባሉት ንኡሳን ቤተሰቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት ከቤንደር ጋር ተመሳሳይ አከፋፈል ሰንዝረዋል። እንደነዚህ ሰዎች ከሆነ፣ በኩሸቲክ ንዑሳን ቤተሰቦች ስር የሚታየው መመሳሰል አይነታዊ ነው።
የኩሽ ቡድኖች ዳሰሳ
ኩሸቲክ ቤተሰብን ሰሜን ኩሸቲክ (ቤጃ)፣ ማእከላዊ ኩሸቲክ/አገው፣ ምስራቅ ኩሸቲክ፣ እና ደቡብ ኩሸቲክ በሚል የሚታየው የተለመደ ክፍፍል ከቀድሞው የነበረ ወይም በሁሉ ስምምነት ያለበት አይደለም። የዚህ ምደባ በተለይ በግሪንበርግ (1963) የቀረበ ነው። ግሪንበርግ ኩሸቲክን የከፋፈለው ሰሜን ኩሸቲክ፣ ደቡብ ኩሸቲክ፣ ማእከላዊ ኩሸቲክ፣ ምስራቅ ኩሸቲክ፣ እና ምእራብ ኩሸቲክ በሚል ነው። ከላይ እንደገለፅንው፣ የኋለኛው በአሁኑ ግዜ ለብቻው ተገንጥሎ የወጣውን ኦሞኦቲክን የሚመለከት ነው። የተቀሩት አራቱ ምድቦችም አከፋፈል ቢሆን በሁሉ ተቀባይነት ያለው አይደለም። የኩሸቲክ ውስጥ ምደባ ከስራ ስራ አብዛኛውን ግዜ ይለያያል። በአንዳንድ ስራዎች ደቡብ ኩሸቲክ የሚባለው እንዳለ ቀርቶ በምስራቅ ኩሸቲክ ተጠቃሎ ይገኛል። እንደዚሁም ማእከላዊ ኩሸቲክ በምስራቅ ኩሸቲክ ውስጥ ተመድቦ የምናገኝበትም አጋጣሚ አለ። በዚህ ክፍል ስለእነዚህ ቡድኖች መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን። ይህን ዳሰሳችንን የምናደርገው ከላይ በጠቀስናቸው አራት ምድቦች፣ ማለትም ሰሜን ኩሸቲክ፣ ማእከላዊ ኩሸቲክ፣ ደቡብ ኩሸቲክ እና ምስራቅ ኩሸቲክ በሚሉ ምድቦች ስር ነው። ይህን ያደረግንው ምደባው የተዘወተረ ከመሆኑ የተነሳ እንጂ ትክክል ነው ከማለት አይደለም።
ማእከላዊ ኩሸቲክ
ማእከላዊ ኩሸቲክ የአገው ቋንቋዎች በመባልም የሚታወቁት ናቸው። እነዚህ ቋንቋዎች ኻምጣንጋ፣ ቅማንትነይ፣ አዊ፣ እና ቢለን ናቸው። አሁን የጠፋው ከይላ በዚህ የቋንቋ ቤተሰብ ስር የሚመደብ ነው።
ኻምጣንጋ በማእከላዊ ወሎ የሚነገር ቋንቋ ነው። ህብረተሰቡ ኽምጣ ይባላል። ቅማንትነይ የቅማንት ብሄረሰብ የሚናገረው በጎንደር ያለ ቋንቋ ነው። ይህ ቋንቋ በመጥፋት ላይ እንዳለ ይታወቃል (ዘለዓለም ልየው 2003ን ይመልከቱ)። አዊ በአዊ ዞን በጎጃም ክፍለሀገር የሚገኝ ነው። ቋንቋው በርካታ ዘዬዎች በውስጡ እንዳሉት ይገመታል። ህብረተሰቡ አዊ ይባላል (ተሾመ 2015 እና በዚያ ላይ የተጠቀሱ ስራዎችን ይመልከቱ)። ቢለን በኤርትራ የሚገኝ ነው። እነዚህ አራቱም ባንድ ወቅት ምናልባትም ወጥ የሆነ ሀገር ይዘው እንደነበር ይገመታል። ልክ ሰሜን አርጎብኛ ከአማርኛና ከደቡብ አርጎብኛ ቋንቋዎች ይልቅ የአባት ማእከላዊ ደቡብ ኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋን ጥንታዊ ቅርፅ የሚያንፀባርቅ ነው ተብሎ እንደሚወሰድ ሁሉ፣[1] አውንጊም ከሁሉም የማእከላዊ ኩሸቲክ ቋንቋዎች ጥንታዊ ቅርፅ የያዘ ነው ተብሎ ይገመታል (ዛቦርስኪ 1984ን ይመልከቱ)።
የአገው ቋንቋዎች ምንም እንኳ ኩሸቲክ ቢባሉም ከሌሎች ኩሸቲክ ከሚባሉት የቋንቋ ቤተሰቦች ጋር ያላቸው ግንኙነት ግልፅ ነው ማለት አይደለም። ሄትዝሮን (1980) እና ዛቦርስኪ (2001) ማእከላዊ ኩሸቲክ እራሱን የቻለ የኩሽ ክፍል ሳይሆን በምስራቅ ኩሸቲክ ክፍል እንዲካተት ሀሳብ አቅርበዋል። ሄትዝሮን በተለይ ከደጋማው ምስራቅ ኩሸቲክ ጋር አንድ ግንባር አድርጎታል። ሄትዝሮንና ዛቦርስኪ የማእከላዊ ኩሸቲክን ራሱን የቻለ ቅርንጫፍነት የሞገቱት አንዳንድ የስነምዕላድ ባህርያትን በመያዝ ነው። ለምሳሌ፣ ዛቦርስኪ ቅድመቅጥያ የሚወስዱ ግሶችን መሰረት በማድረግ ነው። በሌላ በኩል በመሰረታዊ ቃላት ደረጃ የአገው ቋንቋዎች ከሌሎቹ ኩሸቲክ ቋንቋዎች ያላቸው ዝምድና ለሴሜቲክ ቋንቋዎች ካላቸው የተለየ አይደለም። በዚህ ምክንያት አንዳንድ ጥናቶች፣ ለምሳሌ፣ ቤንደር (1997 & 2003)ን ይመልከቱ፣ የሴም ቋንቋዎችን ከሌሎቹ የኩሽ ቋንቋ ቤተሰቦች በእኩል ደረጃ መመደብ እንደሚገባቸው ይገልፃሉ። አፕልያርድም (2011:39) በእያንዳንዱ ኩሸቲክ የቋንቋ ክፍለ ቤተሰብ ውስጥ ያለው ልዩነት ባጠቃላይ ሴሜቲክ ውስጥ ካለው አይተናነስም ይላል። መረጃዎችና ሰፊ ጥናቶች ሲገኙ አሁን ኩሽ የተባሉት ልክ ኦሞቲክ ኩሽ አይደለም እንደተባለው ሌላ ስያሜ ወጥቶላቸው ለብቻቸው ሊቀመጡ ወይም ባንድ ሊጣመሩ ይችላሉ። የሌሎቹ የኩሽ ቋንቋዎች ቤተሰቦችም የእርስ በእርስ ግንኙነት ይህን ያህል የጠበቀ አይደለም። እስቲ በዝርዝር ሌሎቹንም እንመልከታቸው።
ሰሜን ኩሸቲክ
ሰሜን ኩሸቲክ ባሁኑ ግዜ ውክልናው በቤጃ ነው። ይህ ቋንቋ አንዳንዶች ከኩሽ በመጀመሪያ ላይ የተገነጠለ ነው ሲሉ፣ የተወሰኑ ደግሞ ለምሳሌ ሮበርት ሄትዝሮን (1977/1980) ፈፅሞ በኩሽ ቤተሰብ መመደብ የለበትም ይላሉ። እንደኋለኞቹ አባባል ቤጃ ራሱን ችሎ በቀጥታ ከአፍሮኤስያዊው ልዕለ ቋንቋ/ታላቅ ቤተሰብ የወረደ ተደርጎ መቆጠር ይገባዋል። ቤጃ በኩሸቲክ ስር ሊመደብ የሚያስችለው አንዳንድ ከሌሎች ኩሸቲክ የሚጋራቸው ድህረቅጥያዎች አሉት የሚልም ይገኝበታል (ዛቦርስኪ 1984:128ን ይመልከቱ)። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፣ ቤጃ በኩሸቲክ ስር መመደብ አለበት የሚባል ከሆነ፣ ከዚህ ቤተሰብ በመጀመሪያ የተገነጠለ ተደርጎ መወሰድ ይገባዋል ነው። ማውሮ ቶስኮም የኩሸቲክ እና ኦሞቲክ ቅኝት በሚለው መጣጥፉ የተለያዩ ባለሙያዎችን ስራዎች በቃኘበት ስራ ውስጥ ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ደርሷል (ቶስኮ 2003:87)።
ቤጃዎች ጥንት የኩሽ ግዛት በተዳከመች ግዜ በ1ኛው ቅጋአ ሜሮኤን ተቆጣጥረው ዳግም እንዲያንሰራራ ጥረው ነበር። እራሳቸው ግን በቀጥታ ጥንታዊ የኩሽ ግዛትን የመሰረቱ ተደርገው አይወሰዱም። አብዛኛው አሰፋፈራቸውም በባህር ጠረፉ ነው። ቤጃ በግዕዝ በኢዛና ፅሁፍ (DAE 11) ላይ ብጋ በሚል የተገለፀው ነው። እነዚህ ህዝቦች በኢዛና ስር ነበሩ።
ደቡብ ኩሸቲክ
ደቡብ ኩሸቲክ ከኢትዮጵያ ውጭ በታንዛንኛ፣ በኡጋንዳ፣ እና በኬንያ የሚነገሩ ቋንቋዎችን የሚመለከት ነው። ይህ የቋንቋ ቤተሰብ በጣም አከራካሪ ነው። በዚህ ቋንቋ ቤተሰብ ስር የተመደቡ ቋንቋዎች ካንድ ወላጅ ደቡብ ኩሸቲክ መምጣታቸው በጣም አጠያያቂ ነው። እራሱ ደቡብ ኩሸቲክ የሚለው ምደባ በጣም አጠያያቂ እንደሆነ የዛቦርስኪን (1984) ጥናት መመልከቱ ይበቃል። እንደዛቦርስኪ ከሆነ በዚህ ስር የተመደቡት አንዳንዶቹ ቋንቋዎች በምስራቅ ኩሸቲክ ስር ሊመደቡ ይችላሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ከብዙ በጥቂቱ ዛቦርስኪ (1984)ን እና በዚያ የተጠቀሱ ስራዎችን ይመልከቱ።
ምስራቅ ኩሸቲክ
ምስራቅ ኩሸቲክ በሁለት ይከፈላል። አንደኛው ደጋማው ምስራቅ ኩሸቲክ የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቆላማው ምስራቅ ኩሸቲክ የሚል ነው። የመጀመሪያው ሲዳማን፣ ከምባታን፣ ሀዲያን፣ ጌዲኦን፣ እና ቡርጂን ይይዛል። ቡርጂ ከሁሉም ይልቅ ጥንታዊ ተደርጎ ይቆጠራል (ዛቦርስኪ 1984: 133)። ቆላማው ምስራቅ ኩሸቲክ ሶማሌን፣ ኦሮሞን፣ ኮንሶን፣ አፋርን እና ሌሎች በርካታ በቁጥር አናሳ ተናጋሪ ያላቸውን ቋንቋዎች ይይዛል። ይህ የቋንቋ ቡድን ከሌሎቹ የኩሸቲክ ቤተሰቦች ይልቅ በርካታ ቋንቋዎችን የሚይዝ ነው። ከነዚህ ውስጥ ኦሮምኛና ሶማልኛን መጥቀስ ይቻላል።
ለኦሮምኛ በጣም ቅርብ የሆነው ቋንቋ ኮንሶኛ ነው። እነዚህ ሁለቱ ኮንሶይድ ወይም ኦሮሞይድ በሚል በአንድ ቡድን ይመደባሉ። የኮንሶ ህዝብና የኦሮሞ ህዝብ በባህልና በትክለ ሰውነት/መልክ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ስለሚለያዩ፣ በቋንቋ ቢዛመዱም ሁለቱ ህዝቦች ጥንተ አመጣጥ አንድ ላይሆን ይችላል ከሚል የተለያየ መላምት አለ። ለምሳሌ ፓውል ብላክ (1975)ን ይመልከቱ።
ማጠቃለያ
ኩሽ የሚለው ቃል በመፅሀፍ ቅዱስ እንዲሁም በጥንታዊ ግብፆች ስራ ውስጥ ይገኛል። ጥንታዊ ግብፆች ኩሽ የሚለውን (ወይም የዚህን ዝርያቃል) የሚጠቀሙበት ከነሱ ግዛት በስተደቡብ በአሁኑ ግዜ በሱዳን ከዛሬ አራትና አምስት ሺህ ዓመት ገደማ ጀምሮ የነበረውን የከርማን ስርወመንግሥትና ከዚያም በማስከተል በእዚሁ በሱዳን እስከ አራተኛው ክፍለዘመን ድረስ የነበሩትን ስልጣኔዎችና መንግስታት ለማመልከት ነው። በመፅሀፍ ቅዱስ ደግሞ ኩሽ በዋነኛነት ነገድን ያመለክታል። በቋንቋ ቤተሰብ ስያሜነቱ፣ ኩሸቲክ ይባላል።
በክፍል ሶስት በቋንቋዎች መሀል ስላለው ግንኙነት ያነሳንው ኩሸቲክ የሚለው ስያሜ ከጥንት ጀምሮ ኩሽ በመባል የሚታወቁ ህዝቦች የሚናገሩትን ቋንቋዎቹ ምንም አጠያያቂ ባልሆነ መንገድ እርስ በርስ የሚዛመዱ ታሪካዊ መሰረት ያላቸው መሆኑን የሚያመለክት አለመሆኑን ለማመልከት ነው። በርግጥ፣ የተወሰኑ ፊደል የቆጠሩ ሰዎች ካልሆኑ በቀር ባሁኑ ወቀት የትኛውም የኩሸቲክ ቋንቋ ተናጋሪ ኩሽ ነኝ ሲል አይሰማም። ኩሽ ስለመባሉም የሚያውቀው ነገር የለም። በህዝቡ ዘንድ ያለው የተለየ ነው። ለምሳሌ ቤተ እስራኤል በሚል ወደ እስራኤል የሄዱት የአገው ወገን የነበሩ ህዝቦች ናቸው። እንዚህ ህዝቦች ከጥንትም አይሁዶች ሆነው በግዜ ሂደት ግን አገው ሆነው ሊሆን ይችላል። ሱማሌዎችንም ብንወስድ የአረብ ሊግ መሆናቸውን እንኳ ከፖለቲካ/ሀይማኖት ጋር ብናያይዘው እንደ ኢሳ፣ ዳሮድ የሚባሉት ጎሳዎች የሴም ዘሮች ነን የሚሉ ናቸው። በርግጥ የጎሳቸው መስራች ተደርገው የሚቆጠሩት ከአረብ ሀገር መጥተው ሊሆን ይችላል (ሌዊስ 1998፡18ff.)። በሲዳማ ህዝቡ ከእስራኤል እንደመጣ የሚገልፅ አፈታሪክ አለ። ለህብረተሰቡ የትመጣ አፈታሪክ የሀይማኖት ተፅዕኖ ትልቅ ቦታ ቢኖረውም፣ በሁሉም ቦታ የጥንቱን ማንነት ያስተዋል ማለት አይቻልም። በየትኛውም ወቅት ኩሽ አሁን በዚህ ስም የሚጠሩ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ነጥሎ ለማመልከት የዋለበት ግዜ የለም።
በሀገራችን ኢትዮጵያ የኩሽ ምድር መባሉ ዋናው መሰረት የአለማችንን ህዝብ በመፅሀፍ ቅዱስ እሳቤ አለምን ከመተርጎም የመጣ ነው። በአይሁዶች በወቅቱ በነበራቸው ግንዛቤ ለራሳቸው ህብረተሰብ የፃፉትን ይዘው የአለምን ህዝብ መግለፁ ሳይሆን፣ ያንን እውነት ነው ብሎ አለማዊው ፖለቲከኛ መጠቀሙ ይመስላል ትልቁን ስህተት ያመጣው።
ከአዘጋጁ፡- ግርማ አውግቸው ደመቀ የስነልሳን እና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ባለሙያ ናቸው። የምርምር ትኩረታቸው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ታሪክና ስነመዋቅር ላይ ነው። በቅርቡ በእንግሊዝኛ ካሳተሟቸው መፅሀፎች መሀከል የአማርኛ ጥንተ አመጣጥ—ሁለተኛ እትም (2013)፣ ሰዋስዋዊ ለውጥ በሴሜቲክ—የአማርኛ ሰዋስው በዘመን ሂደት (2014)፣ እና የአርጎባ ንግግር አይነቶች/ቋንቋዎች (2015) ይገኙባቸዋል።