በሀገራችን አደገች፤ ተመነደገች፤ ሰለጠነችና የብዙ ጉዶች ተሸካሚ ከተማ ተብላ የምትታሰበው ከተማ፤ አዲስ አበባ ከተማ ናት፡፡ ህገወጥ ተግባራትን ለመፈፀም ከማስፈራት ይልቅ የምታበረታታ እየሆነች የመጣች ከተማም ነች ለማለት ይቻላል፡፡እኛም ነዋሪዎቿ በእለት ከእለት ኑሮአችን በራስ ህሊና ልንቆጣጠራቸው የምንችላቸውን ተግባራት በደፋርነት ከልለን የምግባር ህመምተኞች እየሆንን ነው፡፡ ሥነምግባር ሠዎችን ያለምንም ክፍያ ሥርዐትን እንዲያወሩት ሳይሆን እንዲኖሩት የሚያስችል የህሊና አለቃ ነው፡፡ ነገር ግን እንደከተማዋ ህንፃዎች አብሮ ለማደግ የሚጥረው የነዋሪዋ የዘመነኛነት ዝንባሌ መስመሩ ተዘበራርቆበት አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሰለጠንኩ ባዩ ድፍረት እያመጣ ስርዐትን እያጣ በመምጣቱ ነው፡፡ ሠዎች በሠለጠኑ መጠን ሥርዐትን ያለዕረኛ በራሳቸው ህሊና መሪነት ሊኖሩት በተገባ ነበር፡፡ አሁን አሁን ሥርዐት የባለሀብቱና የባለገንዘቡ ጉዳይ የሚመስልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡የከተማዋ የአኗኗር ዘይቤ ድፍረትን ብቻ የሚጠይቅ መምሰሉ ብዙ አላዋቂዎችን አዋቂ አስመስሎ፣ ሥርዐት ጠባቂዎችን ተጎጂ እንዲሆኑ ሲያደርግ ይታያል፡፡
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ጉዳይ ሠሞኑን የቤት ኪራይ ያማረረው አንድ ወዳጄ ከዲስ አበባ ዳርቻ በአንዱ እየተጓዝን አንዱን የጠራ ሜዳ ሲያይ “ድፍረት አጣሁ እንጂ እዚች ሜዳላይ አንድ አስር ቆርቆሮ ጭቃቤት ነገር ብሠራ …ከዛ ቀስ እያልኩ … በቃ ከኪራይ ተገላገልኩ ማለት ነበር” አለኝ፡፡ ለዚህ ምን ምላሽ እሰጣለሁ ህግ ባለበት ሀገር መንግስት መፍራትም ቀረ እንዴ እያልኩ እራሴን ጠየኩኝ፡፡ አዎ አልለው ነገር ሆኖብኝ ምላሼ ዝምታ ሆነ፡፡ የቤት ችግሩ ሁላችንንም የሚለበልበን ወላፈን ቢሆንም መፍትሔያችን ለየቅል ነው፡፡ ሠሞንኛ የቤት አሠራር ጉዳይን ተከትሎ ወዳጄ ያነሳው ሀሳብ ግን ብዙ ጥያቄን ፈጠረብኝ፡፡ ድፍረት ካለ በዚህች ከተማ ምን የማይደረግ ነገር አለ! ከተሜነታችን ባመጣብን ውስብስብ አኗኗር ላይ ድፍረት ሲጨመርበት ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖብናል፡፡ ከተማ ነዋሪነት ወይም ከአውሮጳውያኑ የቀዳነው የስልጣኔ መስመር እያጠፋን ይሁን እያለማን ግራ ግብት የሚል ሆኗል፡፡ እንዳው ልማድ ሆኖ እንጂ ግራ መጋባት በራሱ ምን እንደሆነ ግራ ይገባኛል፡፡ የሆነ ሆኖ በዚህች ሁላችንም ከሩቅ ስናስባት እንደእንቁ በምናያት፤ ነገርግን ውስጧ ስንገባ ግን ውጥንቅጧ የወጣ፤ ማህበራዊና እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዋ ከእለት ወደእለት እየናረ የመጣች ከተማና ለመኖር ድፍረት ብቻ በቂ የሆነባት ከተማ እየመሰለች መጥታለች፡፡ይኸንን እውነታ ለማረጋገጥ መቼም የሳይንስ ጥናት አያስፈልግም፡፡ በአንዱ ጎዳና መርጦ መጓዝ ነው፡፡ ከዛም ባለማወቅ ከሚጠፋው ጥፋት አውቆ እና በማናለብኝነት የሚፈፀሙ ድርጊቶችን ማየት ቀላል ይሆናል፡፡ የሚያስተዛዝበንም ይኸው ደፋርነታችን ነው፡፡ ሥርዐትን ከቤት፣ ከትምህርት ቤት፣ ከማህበረሰብ ተምረን አድገናል፡፡ ሠዎችን ማክበር፣ ቅንነት እና የመሳሰሉትን ስንማር ለይስሙላ ጆሮ እንዲቀላ ሳይሆን እንድንኖረው ነበር፡፡ ነገር በዚህች የአፍሪካ መዲና በምትባል ከተማ የምናያቸው የሠዎች ድርጊቶች የግዴለሽነት እና የድፍረት እየሆነ መጥቷል፡፡ ለሥርዐት መከበር ልክ እንደ ተማሪ አለቃ አያስፈልገውም፡፡ ፖሊስ ቆሞም ሊያስጠብቀው አይችልም፡፡ ሥርዐት የህሊና መርህ ነው፡፡ ነገር ግን ደፋርነትን ካስቀደምን ማመዛዘን ይቀርና ስሜት ጎልቶ ስለራስ ብቻ አያሰቡ ለሌሎች መሰናክል መሆን ይቀጥላል፡፡ አንድ እና ሁለት ግለሠቦች ሲፈፅሟቸው የቆዩ ድርጊቶች ተፅዕኖ መፍጠር በመቻላቸው የብዙሀን እየሆነ ነው፡፡በከተማዋ ጎዳና እየተጓዝንና አለፍ አለፍ እያልን ቆም ስንል ብዙ የሚያስተዛዝበን ነገር እናያለን፡፡ ስለማን ነው የሚወራው ብትሉ አቤት የሚሉ እራሳቸውን ያውቃሉ፡፡ “እኛ ነን ያላችሁ እስቲ እንያችሁ!!” እንዲሉ፡፡
ከባለስልጣናት ቡጨቃ እና ከገንቢዎች (ኮንትራክተሮች) ሽወዳ ተርፎ በተሰራው አስፋልት መንገድ የሚንከባለለውን ጎማ መሪ የጨበጡት አንዳንድ ሠዎች የሚያሳዩን ትርኢት ገራሚ ነው፡፡ ትንሽ በዛ ያለ ተሽከርካሪ ባለበት መንገድ ወይም መስቀለኛ መንገድ ላይ መብራት ወይም ነጭ ለባሽ ከሌለ ትርምሱ የከብት እንጂ የሠው አይመስልም፡፡ በቃ ሁሉም መሀል መንገድ ላይ ይገባና መተላለፊያ ይጠፋል፡፡ ሁሉም እኔ ልቅደም ባይ ይሆናል፡፡ የጡርንባው ጩኸት ጆሮዋችንን ለመታከም የሚጋብዝ ነው፡፡ የአንዱ አሽከርካሪ መስኮት ዝቅ ይልና ከጎኑ ካለው አሽከርካሪ ጋር መሰዳደብ ይጀመራል፡፡ አልፎ አልፎ ከመኪና ወርዶ ቡጢ መሰናዘርም አይቀርም፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ ልቅደም ባይ በመብዛቱ እንጂ ደቂቃ ለማይሞላ ጊዜ መታገስ ቢኖር ኖሮ ሁሉም ተከባብሮ ባለፈ ነበር፡፡ በዚህ መሀከል ግጭት ከተፈጠረማ አለቀልን፡፡ የገጪው ንዴት ከተገጨው በልጦ በሙቀት ይሁን በነፋስ መለኪያ የሚለካው ባይታወቅም ጦርሜዳ ያስመስሉታል፡፡ ምን ይደረግ ጥፋትን በሌሎች ማላከክ ለምደናላ!፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ይህች ሀገር ከጦርነት መራቋ የጎዳቸው እየመሰለኝ ነው፡፡ ዘራፍ የሚሉበት ቢያጡ መንገዱን የጦር አውድማ ያስመስሉታል፡፡ በዚህ ላይ አላፊ አግዳሚው ዳኛ ይሆንና ለመፍረድ ይረባረባል፡፡ መቼም የአሽከርካሪ ስነባህሪ የሚለውን ትምህርት ሁሉም ዘንግቶት መፅሀፉ ላይ ብቻ የቀረ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ አሁን አሁን እንደ ምግብ እቤት ቁጭ ብሎ በማዘዝ መንጃ ፈቃድ ማውጣት በሚቻልበት ዘመን ደርሰን ለምን ትምህርት ቤት ምናምን ብሎ መቸገር አስፈለገ?! ምንበወጣቸው ያውቁታል? መንዳቱንም ቢሆን ዋናው ድፍረት ነው ብለው መሪ ጨብጠዋል፡፡ በመኪናቸው ውበትና ዘመናዊነት፣ በአለባበሳቸው ማማር፣ በድንቅ ጌጣቸው ያደነቅናቸው ሠዎች፤ ልክ የመኪና መሪ ሲጨብጡ አብሮ ሥርዓት አልበኛ ለመሆን መብት እንደተጣቸው እርግጠኛ በሆነ ስሜት ሥርዐት ሲጥሱ፣ ሌሎችን ሲሳደቡ ለተመለከተ፤ገንዘብ ነውር እንደማይሸፍን ማን በነገራቸው ያስብላል፡፡
በግል ትምህርት ቤት ደጃፎች ስንደርስ የምናየው ውጥንቅጥ ደግሞ ማሳያው ምን እንደሆነ ግራ እስኪገባን ድረስ ሆኗል፡፡ እኔ ምለው ዘንድሮ ልጆቹ በሙሉ መኪና ካልያዛችሁ እንዳትመጡ መባል ተጀመረ እንዴ? በየመንደሩ እንደአሸን የፈሉት የግል ትምህርት ቤቶች የመግቢያ እና የመውጫ ሠዐት የምናየው የመንገድ መዘጋት ችግር ምን ጉድ ነው? የሚያስብል ነው፡፡ ጠዋት መንገድ ሞልተው ሦስተኛ ዙር ድረስ ደርበው የሚቆሙት ተሽከርካሪዎች ከልጃቸው ጋር ተሰነባብተው፣ የቤት ሥራ ከረሳም እዛው ሠርተው እስኪጨርሱ ከኋላ አልፎ ሒያጅ ተሽከርካሪ መንገደኛን ከቁብ የማይቆጥሩ በርክተውልናል፡፡ የሚከፈቱት ትምህርት ቤቶችም ቢሆኑ በአብዛኛው የመኪና ማቆሚያ ጉዳያቸው አድርገው እንዳልወሰዱት ያስታውቃል፡፡ ትምህርት ቤቶች ከመጀመራቸው በፊት ዋነኛ ችግራቸውን አብሮ ለማስተካከል ካልጣሩ ልጅ ትምህርት ቤት በማድረሱም ሆነ ለትምህርት ቤቱ ንግድ ምንም የማይመለከተው የህብረተሰብ አካል ለምን በመንገድ መዘጋት ይሠቃያል? ከዚህም ያልፍና በመውጫና በመግቢያ ሠዐታቸው እኛን ማስጨነቃቸው ሳያንስ እርስ በእርስ በሚያደርጉት ፉክክር መከባበር በማጣት ምክንያት መንገዱን እራሳቸው ላይም ይቆልፉታል፡፡ ከዛም መስኮት ወረድ ወረድ ይደረግና ይሔን ስድብ ከሀገር ውስጥም ከውጭ ቋንቋም እየቀላቀሉ መቀባበል ነው፡፡ እኛም በጉዞዋችን የሀገር ውስጥና የውጭውን ሃገር ቋንቋ ስድብ ቆመን እንድናዳምጥ ተፈረደብን ይመስላል፡፡ አሳዛኙ ነገር ይንፁህ አእምሮ ባለቤት የሆኑት ከኋላ የሚቀመጡ ልጆች የሚማሩትን አስቡት፡፡ መቼም እሰይ አባቴ ጥሩ ተሳዳቢ ነው እሰይ እናቴ ጥሩ ጥሩ ስድብ ታውቃለች ሳድግ እንደነሱ ነው መሆን እፈልጋለሁ ብሎ የሚያድግ ትውልድ ማፍራት የምንፈልግ አይመስለኝም፡፡ ዋናው ድፍረት እንጂ ሀይ ባይማ የለም፡፡ ትራፊኩም እንዲህ ያለውን ለመናገር አፍ የለው፡፡ ባለሀብቶች ናቸዋ! አúረ እንደውም በሠፈሩም ዝር አይሉም፡፡ ትምህርት ቢሮው ፈቃድ ሠጥቶ ሥራውን ጨርሷል ምን ይመለከተኛል ብሎ ያስባል፡፡ ደፋር ከሆኑ በዚህች ከተማ የፈለጉትን መሆን እንደሚቻል እያስተማሩን ነው፡፡
ደፋር አሽከርካሪዎችን ለማለፍና ከመንገዱ መሀል ወደ መንገዱ ዳር ወጣ ብለን ጉዟችንን ነዳነቀጥል ምን መሔጃ አለ? ኮብል ተነጥፎ የነበረ መንገድ አለ አይደል እንዴ? እንዳትሉኝ፡፡ እነ እንቶኔ ግቢያቸውን ለማንጠፍ ፈነቃቅለውታል፡፡ ተስተካክሎ ቴራዞ ተነጥፎ የነበረው አሸዋና ድንጋይ ተዘርግፎበታል፡፡ አለፍ ሲባልም ባለሱቁ ሸራውን ወጥሮ ከሠሉን፣ ለስላሳውን፣ አትክልቱን ደርድሮበታል፡፡ ባለቡቲኩ ጫማና አሻንጉሊቱን፣ ባለካፌው ወንበርና ጠረጴዛውን ይዘረጋበታል፣ ፀጉር ቤቱ ፎጣ አጥቦ አስጥቶበታል፡፡ ታዲያ በዚህ ማለፍ ስለማይቻል በአስፋልቱ ላይ እኛ በሁለት እግራችን ከአራት ጎማ ጋር እየተጋፋን መሔድ ነው፡፡ ሠሌዳ ቀረን እንጂ እኛም ያው ሆነናል፡፡ ደፋር ከሆኑ አነስተኛ ሱቅ መንገድ ዳር ይከራዩና ከእግረኛ መንገዱ ሠፋ ያለ ኪራይ የማይከፈልበት ቦታ ይመረቅሎታል፡፡ ደንቦች ቢመጡ የተለመደውን ሸጎጥ ነው፡፡ ማን ተቆጪ አለ፡፡ አይንና ዱላ ብቻ እንድንፈራ ሆነን ኖረን ህሊናችን እኛን መግራት አቃተው ፡፡ ምክንያቱም ትክክል የሆነና ያልሆነውን የመለየት ችሎታ ከመንግስት፣ ከተፃፈ ህግ ወይም ከደንብ አስከባሪ ሳይሆን ቅድሚያ የሚመነጨው ከእያንዳንዳችን ህሊና ነው፡፡ ሥርዐት ማለት ከውስጣችን የሚፈልቅ ትዕዛዝ እንጂ በዱላና በተቆጣጣሪ የምናዳብረው የኑሮ መስመር አይደለም፡፡ ለነገሩ ምን ይደረግ በዕጅ ያለ ቆሻሻን እንኳ በተገቢው ቦታ ስንጥል ምነው አካበድክ የምንባልበት ከተማ እየኖርን ንፁህ እና አረንጓዴ አካባቢ ብለን እናወራለን፡፡ ካማረ ተሽከርካሪዎቻቸው ውስጥ የነሱ እንዳይቆሽሽባቸው በመስኮታቸው ፊታችን ላይ የሚያሽቀነጥሩት ባለ ጎማዎችን ህሊናቸው ካልገራቸው ማን ይቆጣቸው?
የንፅህና ነገር ከተነሳ አዲስ በአበባ መንገዶች ላይ ስትጓዙ አይናችሁን የሚያጭበረብር ስሜት አይፈጥርባችሁም? ምኑ አትሉኝም፡፡ በየመንገዱ ዳር በተገኙት ነገሮች ላይ ሁሉ የሚለጠፉት ማስታወቁያዎች፡፡ አሁን አሁንማ ታክሲ ለመጠበቅ ረዘም ላለ ሠዐት መቆምም አሳሳቢ ሆኗል፡፡ማስታወቂያ አለጣጠፋችን እንዴት ነው?ዋናው ደፋር መሆን ነው፡፡ መብራት ኃይል ፖል ይትከል እንጂ፣ አዲስ አጥር ይገኝ እንጂ ምንም ችግር የለም፡፡ ከልካይ በሌለበት ከተማ እየኖርን የምን የከተማ ውበት ምናምን ብሎ ማሰብ? እሱን የሚያስብላት ያስብላት፡፡ አዲስ አበባን ከላይ ሆነን ብንመለከታት ከተሰጣ በርበሬ መልኳ ባለፈ የብጭቅጫቂ ወረቀቶች ክምር የበዛባትና የቆሻሻ መጣያ ከተማ ሆናለች ማለት ይቻላል፡፡ እድሜ ለማስታወቂያ ለጣፊዎች አንዱ የለጠፈው ላይ ሌላ ሲደረብ ፖሎቹ እና አጥሮቹ ውፍረታቸው የተመቻቸው ይመስለኛል፡፡ ማስታወቂያውን ለማንበብ ጠጋ ስንል እንኳ በአንዱ ማስታወቂያ ላይ የተጀመረውን ስልክ ቁጥር ከሥር ከሌላኛው ማስታወቂያ ስልክ ቁጥር ጋር አዳቅለን መውሰዳችን አይቀርም፡፡
አስቡት የአዲስ አበባን የማስታወቂያ ቆሻሻ ለማፅዳት እንነሳ ቢባል መቼም እንደ ችግኝ ተከላው ሥራ ተዘግቶ ሁሉም ህብረተሰብ ወጥቶ እንዲፈገፍግ ካልተፈረደበት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ባይሆን ከፅዳት መልስ እንደተለመደው የድራፍቱንና የቁርጡን ነገር ቀድሞ ማዘጋጀት ነው፡፡ ለሥነምግባር እና ለህሊና ተገዢ ሆኖ መኖር ከዘመነኛነት ያወጣናል በሚል እሳቤ በድፍረት እየኖርን ነው፡፡ የአንድ ሠሞን ህግ አክባሪ የመሆን ዝንባሌያችን ለህገወጦች የልብ ልብ እየሰጠ ማን አለብኝነት እንዲዳብር እያደረገ ነው፡፡ እንዲሁ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየተጓዙ በሚታዘቡት ነገር ሳይንሳዊ ትርጉሙን ትተው ከተማ ማለት ምን ማለት ነው ብትባሉ ምን ትላላችሁ? እኔ ቆሻሻማ፣ ደፋርነት አራዳነት፣ ስርዐት መጣስ የገባው የሚያስብልበት የአኗኗር ዘይቤ ያለው ሥፍራ ብዬ በአጭሩ ልናገር እችላለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ለማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ በአሁኑ ዘመን ከተሜነት ብለን የምንጠራውን አኗኗርን የጀመረችው እንግሊዝ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት ስታፋፍም በርካታ ማህበረሰብ ከገጠር ወደ ከተማ ምለሱን ተከትሎ ነው፡፡ ልክ የአሁኗ አዲስ አበባ ማለት ነው፡፡ በዘመኑ የተጀመሩት አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች በርካታ የሠው ኃይል የሚቀበሉ በመሆናቸው ሥራ አጥነት የኛን ያህል አላሳሰባቸውም ነበር፡፡ነገር ግን የከተማ መቆሸሽ እና በውስን ስፍራ በርካታ ሠው በጋራ እንዲኖር ተገዶ ነበር፡፡ በዚህም እንደ መፀዳጃ እና ውሃ ያሉ መሠረታዊ ነገሮች አጠቃቀም እውቀት ስላልነበረው በርካታ የከተማው ነዋሪ በተስቦ በሽታ እንዲጠቃ ሆኗል፡፡ ታዲያ እንግሊዞች እንደኛ ችግሩን አልተላመዱትም፡፡ ይልቁንም አብዮቱ ካመጣው የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ጋር አብረው የሚሔዱ የመኖሪያ ቤት ዲዛይኖችን፣ የውሃ መስመሮችን፣ የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀምን፣ የቆሻሻ አወጋገድን እና መሠል ችግሮችን ለመፍታት በመሞከራቸው ዘመናዊነትን ኖሩት፡፡ እኛስ? እኛማ የመጀመሪያ መፍትሔያችን ችግርን መላመድ ነው፡፡ ሀገሪቷን በተለያየ ዘመን የመሩ መሪዎችም በዚህ የሕዝቡ ዘዬ የተማረኩ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በአንድ ሠሞን ሞቅ ሞቅ አድርገው ስለሥርዐት ስለሕግ ያወሩንና ከረም ሲሉ መተው ልማድ ሆኖባቸዋል፡፡ የእንግሊዝ የዘመናዊነት አብዮት ሶስት መቶ አመታትን ሲሻገር እነሱ የደረሱበት ለመድረስ እየጣርን ነው፡፡ ጥረታችን ግን ድብልቅልቅ ሆነና ግራ ገባን፡፡ ደፋሮች ወደ ፊት፤ ስርዐት አክባሪው ፈሪ፣ ያልገባው፣ ፋራ በሚባልበት መንገድ ሆነ፡፡ ማህበረሰብ የዑደት እንጂ የአንድ ጀንበር ለውጥ ውጤት አይሆንም፡፡ ነገር ግን ለምን አንማርም? እኛ ኋላ ቀር ነን ነገር ግን ኋላ የመሆን ጥቅሙ ከቀደሙት ለመማር ነው፡፡ እውነት ነው እንግሊዝ ስትከትም በቆሻሻ ተሞልታ ስለነበር እኛም እንቆሽሽ፣ እንግዚዞች በተስቦ አልቀው ስለነበር እኛም አተት ይጨርሰን እና እናድጋለን የምንል ከሆነ፤ እውነትም ከኃላ ቀርም በላይ ስያሜ ያስፈልገናል፡፡ የዘመኑት አውሮጳዎች ከሥር ከመሠረት ስለጀመሩት ችግሩ ሲፈጠርባቸው መፍትሔ እያበጁ ሔደዋል፡፡ እኛ የራሳችንን አዲስ የዘመናዊነት መስመር አልጀመርንም፡፡ የውጪዎቹን እየቀዳን እያስመሰልን ለመኖር ጥረት እያደረግን ነው፡፡ የወደፊቱን አርቆ ለማሰብ ችግሮቻቸውን ቀድመን ለመዘጋጀት መፍትሔያቸውን ፅፈው አስቀምጠዋቸዋል፡፡ እናስ ስለምን መማር አቃተን?
ደፋር መሆንን ብቻ በሚገፋፋ መስተጋብር ውስጥ ከቀጠልን ሥርዐት አልበኝነት እየገዘፈ ትላንት ስናሾፍባቸው የነበሩ ጎረቤት ሀገሮች ዛሬ በእኛ ላይ መሳቅ እንዳይጀምሩ ያሰጋኛል፡፡ ህገ-ወጥነት የሚያስከብርባት ደፋር መሆን አራዳ የሚያስብልባት ደንብን መጣስ የገባው ተብሎ ሙገሳ የሚያሰጥባት ከተማ እየሆነች ነው፡፡ እንደ ከተማ የራሷ የአኗኗር ስልት አላት እንዳይባል የመዘበራረቁ ብዛት ይህ ነው ተብሎ ሊጠራ የሚችል አኗኗር መንገድ የላትም፡፡ ነገር ግን ከተሜነትን ተላበስን ለማለት ደንብ እና ስርዐትን መጣስ ከሆነ ሳንዘምን ብንቀር ይመረጣል፡፡ ድፍረት የህሊና ማመዛዘኛን ዘግቶ እንደ ጋሪ ፈረስ ፊታችንን ብቻ እያየን እንድንጓዝ የሚያደርገን ስሜት ነው፡፡ በእድሜ የማይወሰን በትምህርት ደረጃ የማይገደብ በሀብት ብዛት የማይሸፈን እውር ፈረስ መጋለብ ነው፡፡ ይህንን አላማ ብለን ይዘን የምንኖር ሠዎች ምንም አይነት የራስ ኃላፊነት አለብን ብለን አናምንም፡፡ መታረምም አይቻልም፡፡ መልካም ባህርያት የትወና ገፀባህሪያት እና የድርሰት ማድመቂያ ሆነው እንዳይቀሩ ያሰጋኛል፡፡
ለነገሩ “ደፋርና ጪስ መውጫ አያጣም፣ ከራስ በላይ ንፋስ፣ እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል አለች አህያ” በሚሉ አባባሎች ስንማርና ስንፈተን አድገን ወዴት እናምራ? ከተነገሩን አባባሎች ጠቃሚ መስሎ የተሰማንን ስለምንይዘው ደፋሮችም እነዚህኞቹ አባባሎች ጠቃሚዎቻችን ናቸው ብለው ይዘዋቸው ይኖሯቸዋል፡፡እንዲሁ ወኔ ብቻ ሆነን ቀረን፡፡ ግብዝነታችንን ረገብ አድርገን ዘመን የደረሰበትን ቁስ መጠቀም ብቻ ዘመነኛ እንደማያስብል ተረድተን ዘመኑ የሚጠይቀንን የአስተሳሰብ ሥርዐት ማክበር እና መከባበር መልመድ የምንጀምረው መቼ ይሆን?
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ የጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡