ዓድዋ – “የአንድነታችን ድርና ማግ”
«ሃያ ሺሕ ያህል ወታደሮች ያሉበት የአውሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋው ያለ ጦርነት የለም፡፡ 25,000 ሰዎች በአንድ ቀን ጀንበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ ሀበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የእኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ ሀበሾች ክርስትናን የተቀበሉ ናቸው፡፡»
ከ124 ዓመታት በፊት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ፣ በአውሮፓዎቹ ቀመር ማርች 1 ቀን 1896 ኢትዮጵያ የነጩን ዓለም ያናወጠ፣ ለጥቁር ሕዝቦች ሞገስ የሆነውን የዓድዋ ጦርነት በጣሊያን ወራሪ ሠራዊት በድል የተወጣችበት ዕለት ነበር፡፡ ይህንን የ19ኛው ምዕት ዓመት ታሪካዊ ገድል ነበር ጆርጅ በርክሌ በመጣጥፉ ያንፀባረቀውና “አጤ ምኒልክ” ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ የሠፈረው፡፡
ከዓድዋ ጦርነት አሥር ዓመታት በፊት 14 የአውሮፓ አገሮች በርሊን ላይ ባደረጉት ስብሰባ አፍሪካን ለመቀራመት ሲወስኑ የጣሊያን ድርሻ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ቅድመ ዓድዋ ከወራሪዎችና ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር ተዋግታ ድል መታለች፡፡ አንዱ በአፄ ዮሐንስ ዘመን በጥር 1879 ዓ.ም. ዶግዓሊ ላይ በራስ አሉላ አዝማችነት በጣሊያን ላይ ለመጀመርያ ጊዜ የተቀዳጀችው ድል ነበር፡፡ ጣሊያን ያዘመተችው 500 ወታደሮች ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፉ የተደመሰሱበት ነበር፡፡
በ19ኛው ምዕት ዓመት ሁለተኛው አጋማሽ ጀምሮ በመቅደላ (እ.ኤ.አ. 1868) ከእንግሊዝ፣ በጉንደትና በአውሳ፣ በጉራዕ (1875 እና 1876) ከግብፅ፣ በመተማ (1889) ከደርቡሽ፣ በኮአቲትና ሰንአፈ (1895) ከጣሊያን ጋር ጦርነት ገጥማ በድል ተወጥታለች፡፡
ጣሊያን የቅኝ ግዛት ሕልሟን እውን ለማድረግ ስትነሳ በ1888 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ለማድረግ ምክንያት የሆነው የውጫሌው ውል ነበር፡፡ ይህም በአንቀጽ 17 በጣሊያንኛ ትርጉሙ ኢትዮጵያ የጣሊያን ጥብቅ ግዛት ነች፡፡ የውጭ ግንኙነቷ በርሷ በኩል ይሆናል የሚለው ሐረግ ነው፡፡
ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑን ሲታወቅ ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሕዝቡንና የየአካባቢውን መኳንንትና ገዢዎች በጣሊያን ላይ እንዲነሱ የአገርን ክብርና ነፃነት እንዲያስጠብቁ የሚከተለውን አዋጅ አስነገሩ፡፡

“አሁንም አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል . . . በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ . . . ያገሬ ሰው . . . ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ፡፡”
ኢትዮጵያውያንም የርስ በርስ ግጭታቸውን፣ ውስጣዊ ችግሮቻቸውንና አለመግባባታቸውን ወደጎን ትተው ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተጠራርተው እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው ወደጦር አውድማው ተመሙ፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ጠቅላይ አዝማችነት 120,000 ተዋጊ ተሰለፈ፡፡
የዓድዋ ድል 100ኛ ዓመት መታሰቢያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታተመ የጥናት መድበል ላይ እንደተጻፈው፣ አዝማቾቹ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ መኰንን፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ ወሌ፣ ራስ ስብሐትና ደጃዝማች ሐጎስ ተፈሪ፣ ራስ አባተ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ደጃዝማች ባልቻ፣ ዋግ ሹም ጓንጉል ናቸው፡፡

የጣሊያን ወታደሮች የሚመሩት በጄኔራል ባራቴሪ ሲሆን አራት ጄኔራሎችም ክፍለ ጄኔራል አልቤርቶኒ፣ ጄኔራል ኤሌና፣ ጄኔራል አሪሞንዲና ጄኔራል ዳቦርሚዳ ጦሮቻቸውን ይመራሉ፡፡
አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚባለው መጽሐፋቸው እንደተረኩት፣ የጣሊያንንም ወታደር ከበው እየተፏከሩ በጥይትና በጎራዴ ሲደበድቡት የኢጣሊያ ጦር አራት ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሽሽት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እየተከታተሉ ሲወጉት፣ አዝማቹ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተቀምጦበት የነበረው በቅሎ ተመቶ ወደቀ፡፡ ወዲያው ተነሥቼ አመልጣለሁ ብሎ ለመነሣት ሲጥር ከቅምጡ ሳይነሳ እየተሽቀዳደሙ የሚሮጡት ኢትዮጵያውያን ደርሰው ጄኔራሉን ማረኩት፡፡ የ1ኛው ክፍለ ጦር አዛዡ ተማርኮ፣ ሠራዊቱ በጭራሽ ከጠፋ በኋላ ሁለተኛው ክፍል የጦር ሠራዊት ራአዮ ከሚባለው ስፍራ ላይ ሆኖ፣ ካራት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ የሦስተኛውን ክፍል የጄኔራል ኤሌናን ጦር ጨምሮ ተዋግቶ በመጨረሻ የጦር አዛዡ ጄኔራል አሪሞንዲ እዚያው እጦርነቱ ላይ ሞቶ ተገኘ፡፡
ከዚህም በኋላ በመጨረሻ ያለው የጣሊያን ጦር በተለይ ማርያም ሸዊቶ ከሚባለው ስፍራ ላይ ተጋጥሞ ከቀድሞው የበለጠ ጦርነት ተደረገ፡፡ ይልቁንም የመጨረሻው ድል የሚፈጸምበት በመሆኑ የሁለቱም የጦር ሠራዊት ተደባልቆ በጨበጣ በሚዋጉበት ጊዜ፣ በጨበጣ በሚደረገው ዘመቻ ከኢጣሊያኖች ይልቅ ኢትዮጵያውያን በጎራዴ አነዛዘር የቀለጠፉ ነበሩ፡፡
ይሁን እንጂ ጣሊያኖች ተስፋ በቆረጠ ኃይል እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ በጉብዝና ሲዋጉ በመጨረሻ አዛዣቸው ጄኔራል ዳቦርሚዳ በጥይት ደረቱን ተመቶ ወድቆ ባንዲት ጠብታ ውሃ ማነው አፌን የሚያርሰኝ እያለ እንደ ተኮነነው ነዌ ሲጮኽ ጥቂት ቆይቶ ሞተ፡፡
ታሪክ እንደመዘገበው በዓድዋ ጦርነት በስለላው የጣሊያንን የጦር እቅድ በማሳከር አኩሪ ተግባር የፈጸመው ባሻዬ አውአሎም ሐረጎት ነው፡፡ የባዕዳኑ አገልጋይ የነበረው አውዓሎም በቁጭት በመነሳሳትና በብላታ ገብረእግዚአብሔር ጊላ አማካይነት ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር ይገናኛል፡፡
ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ታሪኩን በመጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ራስ መንገሻም ከአፄ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ይገናኙና የጦርነቱ ጊዜ ሲቃረብ የተሳከረውን እቅድ ለጄኔራል ባራቲየሪ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. አውዓሎምና ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ከጣሊያናውያን ተለይተው ወደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ገብተው ጦርነቱ ሲፋፋም ከጣሊያን መኰንኖች አንዱ «አውዓሎም አውዓሎም» እያለ ሲጣራ አውዓሎም ሰምቶ፣ «ዝወኣልካዮ ኣያውዕለኒ» (ከዋልክበት አያውለኝ) ብሎ አፌዘበት ይባላል፡፡
የዓይን ምስክር
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም በዓድዋው የጦር ግንባር በመሰለፍ ያዩትን በሕይወት ታሪካቸው ጽፈውታል፡፡
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ባሉት ሳምንታት የአካባቢው እረኞች ሲጫወቱ ደበሎ እየሰቀሉ አዋጅ ይናገሩ እንደነበር አዋጁንም በመጥቀስ አኑረውታል፡፡

«እሽ ስማ ብለውሃል መስማሚያ አይንሳህ
«ያድባርን ያውጋርን ጠላት…
«ሐማሴንን ለራስ አሉላ፣ አጋሜን ተምቤንን ለራስ ስብሐት፣ እንደርታን ዋጀራትን ለደጃዝማች ሐጎስ፣ እንዳመኾኒ ሰለሞንን ለፊታውራሪ ተክሌ፣
«ዋድላን ደላንታን ለፊታውራሪ ገበየሁ፣ ሰጥቻለሁ ብለውሃል! ይበጅ ያድርግ፤
«በየካቲት ጣጣችን ክትት
«በመጋቢት እቤታችን ግብት
«በሚያዛሳ ያገግም የከሳ
«ይበጅ ያድርግ…» እያሉ ይተነባሉ፡፡
ስለ ጦርነቱ ውሎም እንዲህ ተርከውታል፡፡
“የሰው ብዛት እንደ ጎርፍ ሆነ፡፡ እግረኞችም በቅሎኞችም ተደባልቀን እንርመሰመሳለን፡፡ ፈረሰኞች በጎን እያለፉን ይቀድማሉ፡፡ ይሮጣሉ! እንደተቻለን እንሽቀዳደማለን፡፡
ጠመንጃ ሲንጣጣ ሰማን፣ መድፍ ወዲያው ያጓራ ጀመር፡፡ ተኩሱ እያደር እየባሰበት ተቃረበን፣ አረሮቹ ማፏጨት ጀመሩ፡፡ የቆሰሉ ሰዎች ተቀምጠው አገኘን፡፡ አያ ታደግ እጁን ተመትቶ ከመንገዱ ዳር ከዛፍ ሥር ተቀምጧል፡፡ ገና በሩቁ አይቶን ተጣራ፣ ቁስሉን በመቀነቱ አሰርንለት፡፡ ጥለነው እንዳንሄድ ለመነን፣ ፈይሣ ጠመንጃ የለውም፤ የቁስለኛውን ጠመንጃ ተሸከመና እዚያው ቀረ፡፡ እኔ ዝም ብዬ ወደ ግምባር አለፍኩ፡፡ የማውቀውን ሰው አንድም አላጋጠመኝም፡፡ ተኩስ ስለበዛ መሮጥ የማይቻል ሆነ፡፡ የሰውም ብዛት እንደልብ አያስኬድም፡፡
ደጃዝማች ማናዬ እና ልጅ አስፋው (ልጃቸው) ሁለቱም ቆስለው ድንጋይ ተንተርሰው ተጋድመው አገኘኋቸው፡፡ ልጅ አስፋው (በኋላ ፊታውራሪ አስፋው) አወቀኝና ጠቀሰኝ፡፡ ዝም ብዬው እንዳላየ ሰው ወደ ግምባር ሮጥኩ፡፡ ጦራችን ተደባልቋል፡፡ ሰውና ሰው አይተዋወቅም፡፡ ሴቶች ገምቦ ውሃ እያዘሉ፣ በበቅሎቻቸው እንደተቀመጡ፣ ለቁስለኞች ውሃ ያቀርባሉ፡፡ ሲነጋገሩ ሰማኋቸው፡፡ «ኧረ በጣይቱ ሞት» ይላሉ፡፡ እቴጌ የላኳቸው ይሆናሉ እያልኩ አሰብኩ፡፡
ነጋሪቱ ከግምባርም፣ ከጀርባም፣ ከቀኝም ከግራም ይጎሸማል፡፡ የተማረኩ ጣልያኖችን አየሁ፡፡ ወዲያው ምርኮኞቹ በዙ፣ አንዳንዶቹ ወታደሮች፣ ይበልጡን ጣልያኖችን እየነዱ መጡ፡፡ በኋላ የምርኮኞች ብዛት ለዐይን የሚያሰለች ሆነ፤ ድል ማድረጋችንን አወቅሁ፡፡ ጣልያኖች መዋጋታቸውን ትተው ማርኩን እያሉ ይለምናሉ፡፡ እንደዚህ የዓድዋ ጦርነት ዕለት አንድ ጥይት እንኳ ሳልተኩስ ጦርነቱ አለቀ፡፡
የተክለ ሐዋርያት ምልከታ የበርክሌን አገላለጽ እንዲህ የሚያስታውስ ነው፡፡ በጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” ላይ እንደሚከተለው ተጽፏል፡፡ “የተተከለው ድንኳን ሲታይ ከብዛቱ የተነሳ አፍሪካ አውሮፓን ለመጠራረግ የተነሳች ይመስላል፡፡ የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፣ ጠመንጃና ጦር ይዘው፣ ጎራዴ ታጥቀው፣ የነብርና የአንበሳ ቆዳ ለብሰው፣ አዝማሪዎቹ እየዘፈኑ ቄሶች፣ ልጆች፣ ሴቶች ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የጣሊያንን ጦር አሸበሩት፡፡”
የሴቶች ተሳትፎ
በዓድዋው ዘመቻ የሴቶች ተሳትፎ በወሳኝነት ይታወቃል፡፡ እቴጌ ጣይቱ ከአፄ ምኒልክ ጦር ጋር የራሳቸውን ፈረሰኛ ጦርና እግረኛ ሠራዊት እየመሩ ከመዝመታቸውም በተጨማሪ ለቁስለኞች የሚያስፈልገውን ዝግጅት፣ ለስንቅ የሚያስፈልገውን ምግብም አሰናድተዋል፡፡ በቤተ መንግሥት ያካበቱት ዕውቀት በጦር ሜዳም አገልግሏቸው ኖሮ፣ እንዳ ኢየሱስ ላይ ጣሊያን የመሸገበትን ለማስለቀቅ በኃይል ሳይሆን በብልሃት ብለው በነደፉት እቅድ መሠረት የእቴጌ ጣይቱ ጦር ጠላትን ማርኳል፡፡
ከእቴጌ ጣይቱ አንስቶ እስከ ታች ድረስ የነበሩት አገልግሎታቸው ለድሉ ስኬት ያስጠቅሳቸዋል፡፡ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት በነበሩበት ዐውደ ግንባር የታዘቡትን እንዲህ ጽፈውታል፡፡
“ሴት አገልጋይ የተባለችው (የቤት ውልድ ነች ወለተ አማኔል የእንኮዬ ወለተ ማርያም ልጅ ከኛው ጋር ያደገች ነች) ከዘመቻው ላይ በጣም አገለገለች፤ ከቶ እሷ ባትኖር እንዴት እሆን ኖሯል፡፡ እያልኩ ዘወትር ሳስበው ያስደንቀኛል፡፡ እቃ ተሸክማ ስትሄድ ትውላለች፡፡ ከሰፈርን በኋላ ውሃ ቀድታ፣ እንጨት ለቅማ፣ ቂጣ ጋግራ፣ ወጥ ሰርታ ታበላናለች፡፡ ወዲያው እንደዚሁ ለማታ ታሰናዳለች፡፡ እንደዚህ የወለተ አማኔልን አገልግሎት እያሰብኩ ስደነቅ ደግሞ፣ በየሰፈሩ እንደዚህ እንደርሷ ስንት ሴቶች እንደሚያገለግሉ ይታሰበኛል፡፡
የሴቶቹን አገልግሎት ስገምት፣ ደግሞ የበቅሎቹ አገልግሎት ይታወሰኛል፡፡ በመጨረሻው ድምሩን ስገምተው፣ የዓድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና በበቅሎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል፡፡ ሁሉንም አያይዤ በደምሳሳነት ስመለከተው፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ነፃነቱን ጠብቀው እዚህ አሁን አለንበት ኑሮ ላይ ያደረሱት፣ እነዚህ የዘመቻ ኃይሎች መሆናቸውን አልስተውም፡፡
የጥበብ ማዕድ
የዓድዋ ድልን አስመልክቶ በተለያዩ የጥበብ ሰዎች የተሠሩ ኪነጥበብ ተኮር ሥራዎች በፊልም፣ በተውኔት፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ግጥም፣ በቅኔ ወዘተ. የቀረቡት በርካታ ናቸው፡፡
ከሩብ ዘመን በፊት ታዋቂው የፊልም ዳይሬክተር ኃይሌ ገሪማ (ኘሮፌሰር) “ዓድዋ በሚል መጠሪያ የደረሰው ፊልም በበርካታ ታሪካዊ ፎቶግራፎች የታጀበ ነበር፡፡ በተውኔት ዘርፍ ጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን «ዓድዋ» ከተሰኘውና በ1964 ዓ.ም. ከደረሰው ግጥም ሌላ አሜሪካ ውስጥ ለእይታ የበቃው «ምኒልክ» ተውኔት ዓድዋን ያጎላበት ነበር፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ 100ኛ ዓመት ታዋቂው የቴአትር ዳይሬክተር አባተ መኩሪያ በአጋጣሚው የዓድዋውን ዘመቻ ክተት የሚያሳይ ትርኢት ‹‹ክተት ወደ ዓድዋ ዘመቻ›› በሚል ርዕስ ያሳየው ዘመን ተሸጋሪ ሥራ ይጠቀሳል፡፡ የደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ካለፉ በኋላ የታተመው «ዓድዋ» ተውኔታቸውም ይጠቀሳል፡፡ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ጥቁር ሰው ዓድዋ ተኮር ቅንቀናውም የቅርብ ዘመን ሥራ ነው፡፡ ሌሎችም እንዲሁ፡፡
ሥነ ሥዕልን በተመለከተ ድሉን የሚያሳዩ በተለያዩ ሠዓልያን የተሣሉ ባህላዊና ዘመናዊ ሥዕሎች የመኖራቸውን ያህል ጣሊያናውያንም የምኒልክን ታላቅነትና ድል አድራጊነት፣ የክሪስፒን ተሸናፊነትና ውድቀት የሚያሳይ የካርቱን ሥዕል አሰራጭተዋል፡፡ ሥዕሉ በ«ለ ፐቲት ጆርናል» የታተመ ሲሆን፣ ምኒልክ ክርስፒን ሲጎሽሙትና ሲጥሉት ያሳያል፡፡
የዓድዋ ጦርነት ድልን በሥዕል በመግለጽ በኩል የቤተ ክርስቲያን ሠዓሊዎች ዓይነተኛ ሚና እንደነበራቸው ይገለጻል፡፡ አቶ ግርማ ፍሥሐ፣ “Ethiopian Paintings on Adwa” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት ትውፊታዊ ሠዓሊያኑ የዓድዋውን ድል በሥዕላቸው የዘከሩበት መንገድ ለኢትዮጵያ ባህላዊ አሣሣል ዕድገት አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሥዕሎች የአፄ ምኒልክ አማካሪ በነበሩት አልፍሬድ ኢልግ ስብስብ ውስጥ በስዊዘርላንድ ሲገኙ፣ የሆልትዝ ስብስብ በበርሊንና የሆፍማን ስብስብ በዋሽንግተን ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1905 አካባቢ የተሣሉት ከነዚህ ሥዕሎች መካከል የአለቃ ኤሊያስ፣ የአለቃ ኅሩይና የፍሬ ሕይወት ይገኙበታል፡፡
በሥዕሉ ጐልተው ከሚታዩት ከጠቅላይ አዝማቹ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በተጨማሪ አዝማቾች፣ መካከል ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ አባተ፣ ደጃዝማች ባልቻ ይጠቀሳሉ፡፡ ከአዝማሪዎች መካከልም አዝማሪ ፃዲቄ እየሸለለችና እየፎከረች ስታዋጋ የሚያሳይ ሥዕልም አለበት፡፡
የዓድዋ ጦርነት የተካሄደበት ዕለት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት ትውፊት መሠረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀን ነው፡፡ ከቀደመው ጊዜ አንስቶ እስካሁን «ጠባቂ ቅዱስ» (ዘ ፓትረን ሴንት) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ዘመን የተሻገረው ዝማሬም፣

«የዓድዋ አርበኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከምኒልክ ጋር አብሮ ሲቀድስ፤
ምኒልክ በጦሩ ጊዮርጊስ በፈረሱ
ጣሊያንን ድል አደረጉ ደም እያፈሰሱ» የሚለው ነው፡፡
አቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ «ዐፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት» በተሰኘው መጽሐፋቸው የጐጃሙ ሊቅ መምህር ወልደ ሥላሴ እንደመልክ አድርገው ለአፄ ምኒልክ በግዕዝ ደርሰው ያበረከቱት የደራሲውን ሊቅነት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካውንም የጦርነቱንም ታሪክ በትክክል የተከታተሉት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
“ሰላም ለአፉከ ለፈጣሪ ዘየአኵቶ
ኢይትናገር ስላቀ ወኢይነብብ ከንቶ
ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለኢትዮጵያ ማኅቶቶ
ኃልቀ ማንጀር [ማዦር] ወስዕነ ፍኖቶ
ዤኔራል ባራቲዬሪ ሶበ ገብዓ ደንገፀ ኡምቤርቶ፡፡”
ሰላም ፈጣሪን ለሚያመሰግነው አፍህ ስላቅ ለማይናገረው፣ ከንቱ ነገር ለማያወጋው አፍህ ሰላም ይሁን፡፡ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለኢትዮጵያ ብርሃኗ ማዦር ማለፊያ መንገድ አጥቶ አለቀ
ዤኔራል ባራቲዬሪ ወደርሱ በተመለሰ ጊዜ ኡምቤርቶ ደነገጠ፡፡
በድል ማግስት
የዓድዋ ድል ብስራት በዓለም በተለይም በጥቁሩ ዓለም ሲናኝ ኢትዮጵያን የነፃነት ተምሳሌት አድርጎ ያዛት፡፡ ባሕሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደጻፉት፣ “የዓድዋ አብነት በተለይም የነጮች የበላይነት ከአስከፊ የዘር አድልዖ ፖሊሲ ጋር ከተቆራኘባቸው አካባቢዎች (ለምሳሌ በደቡባዊ አፍሪካና በአሜሪካ) የላቀ ነበር፡፡ በእነዚህ አገሮች ለሚገኙ ጥቁሮች የዓድዋ ባለድል የሆነችው ኢትዮጵያ የነፃነትና የክብር ፋና ሆነች፡፡
“ቀድሞውንም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የምትወሳው ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያኒዝም” እየተባለ ለሚጠራ ከነጮች ተጽዕኖ ነፃ የሆነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ መንሥኤ ሆና ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በዓድዋ ድል አማካይነት ቀድሞ በረቂቅ ትታወቅ የነበረችው ኢትዮጵያ ሥጋና ደም ተላብሳ ታየች፡፡”