የአሜሪካ መንግስት እና የዓለም ባንክ የታዛቢነት ሚና ይዘው ያመቻቹትን የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቅ ድርድር ከውስጥ ሆነው ሲከታተሉ የነበሩ እና ለፊርማ ሊቀርብ የነበረውን ረቂቅ የስምምነት ሰነድ የተመለከቱ አንድ ከፍተኛ ኃላፊ፤ መንግስት በ11ኛው ሰዓት ላይ ስምምነቱን በተያዘው ፕሮግራም ላለመፈረም ያሳለፈውን ውሳኔ ሲሰሙ እረፍት እንደተሰማቸው ይናገራሉ፡፡ ቢሆንም መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር ውሳኔ አሳልፎ እስኪመለከቱ ድረስ ከስጋታቸው ሙሉ በሙሉ ነፃ እንደማይሆኑ ይገልጻሉ፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ በማሳሰብ ለሪፖርተር በላኩት የጽሑፍ መልእክትም እ.ኤ.አ. ከ29 ኖቬምበር 2019 ጀምሮ በአዲስ መልክ ሲካሔድ የነበረውን ድርድር ገጽታ እንዲሁም የነበረባቸውን ስጋት በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ‹‹በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሲካሄድ የነበረው ድርድረ ከተሰጠው መርሕ እና ዓላማ አፈንግጦ ኢትዮጵያን በመርገጥ በአባይ ውኃ ላይ ያላትን በሉዓላዊነት የመጠቀም መብት አሳልፋ እንድትሰጥ ወደ ሚያስገድድ መድረክነት ተቀይሯል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንን ኢፍትሐዊ መድረክ እንዳይቃወም እና የሀገሩን ብሔራዊ ጥቅም ከነጣቂዎች እንዳይከላከል መረጃ ከመነፈጉም ባለፈ፤ ድርድሩ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር እንደሆነ ተደጋጋሚ መግለጫ መሰጠቱ አሳሳቦኝ ነበር›› ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ይተርካሉ፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ የታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት የሆኑት ግብፅ እና ሱዳን የተፈጠረባቸውን ስጋት ለመቅረፍ እና ኢትዮጵያ በአባይ ላይ የኃል ማመንጫ ግድቡን የጀመረችው፤ በታችኞቹ ሀገራት ላይ ተገቢ ያልሆነ ጉዳት ለማድረስ አለመሆኑን ለማስረዳት፤ መንግስት ባሳለፈው ፖለቲካዊ ውሳኔ ሁለቱ ሀገራት የግድቡ ግንባታ ጥራት እና ደህንነት ደረጃ እንዲሁም ግድቡ የውሃ ለመያዝ የሚያስችል ደረጃ ላይ ሲደርስ የሙሌት ሂደቱን እና የውኃ አስተዳደሩን ሁለቱን ሀገራት ባሳተፈ መንገድ ለመቅረጽ በራሱ አነሳሽነት ፈቅዷል፡፡ይህንን ተከትሎ ከሦስቱ ሀገራት ዕኩል የተወከሉበት የጋራ የቴክኒክ ባለሙያዎች በማቋቋም ላለፉት ከሰባት ዓመታት በላይ ከላይ በተገለጹት ጉዳዮች ላይ ድርድር ሲያደርጉ ነበር፡፡ ባለፉት ዓመታት በነበረው የድርድር ሂደት የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን በዋናነት በግብፅ ወገን የሚነሱ የድርድር ሀሳቦችን በጥንቃቄ እና በእርጋታ መክሮ ምላሽ ሲሰጥባቸው እንደቆየ ይታወሳል፡፡በእያንዳንዱ ድርድር ከግብፅ ወገን ለሚቀርቡ አዳዲስ ሐሳቦች፤ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ብቻውን ምላሽ ከመስጠት በመቆጠብ ከተደራዳሪ ቡድኑ ውጪ ሆኖ ወደ ተቋቋመው ብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን ይዞ በመቅረብ በግብፅ ወገን የሚቀርቡ አዳዲስ ሀሳቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲመረመሩ እና አቋም እንዲያዝባቸው ያደርግ ነበር፡፡ይህ በመሆኑም ግብፅ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ቡድን አጭበርብረው ፍላጎታቸውን መፈጸም እንደይችሉ ብቻ ሳይሆን፤ ሳይንሳዊ በሆነ መሰረት ላይ ቆመው ኢትዮጵያን ማሸነፍ እንደማይችሉ እንዲረዱ ማስቻሉን እኝሁ ምንጫችን አስረግጠው ይናገራሉ፡፡
የግድቡ ግንባታ በተጀመረበት ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ፕሮጀክቱ ላይ ጥናት እንዲያደርግ የተደረገው ገለልተኛ ዓለም ዓቀፍ የባለሙያዎች ቡድን፤ ጥናቱን አጠናቆ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ሦስቱ ሀገራ በጋራ ቢያከናውኗቸው ለመተማመን ይረዳል ብሎ ያቀረባቸውን ሁለት ምክረ ሐሳቦች ማትም የግድቡ ውሃ አሞላል፤ አለቃቅ እና ግድቡ ሊያስከትለው የሚችለው አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ተጽዕኖን ለማጥናት ሁለት ገለልተኛ ከባንያዎች ተቀጥረው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ነገርግን ከእነዚህ ኩባንያዎች ጥናት ሊገኝ የሚችለው ሳይንሳዊ ውጤት በመሆኑ የግብፅ ወገን ለኩባንዎቹ የተሰጠው ኃላፊነት እንዲስተጓጎል ማድረጉን በመግለፅ፤ ፤ የግብፅ ወገን በሳይንሳዊ መንገድ ለሚገኝ መፍትሔ ዝግጁ እንዳልነበር ይህ ከበቂ በላይ ማስረጃ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ግብፆች ለዓመታት ሲካሄድ በነበረው ቴክኒካዊ ድርድር ውጤት እንደማያመጡ በማመን በተደጋጋሚ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ ሲያደርጉት የነበረው ሙከራ ዘንድሮ እንደተሳካላቸው የሚናገሩ ትምንጫችን ፤መንግስት ይህንን በማድረጉ ትልቅ ስህተት ፈጽሟል ብለው ያምናሉ፡፡ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ባቀረበችው ተቃውሞ ሚናቸው ከአደራዳሪነት ወደታዛቢነት እንዲወርድ ተደርጎ ለዓመታት ድርድር ሲደረግበት የነበረው የቴክኒክ ጉዳይ በልዩ መድረክ ስር እንዲካሔድ ሆኗል፡፡
ከሞላጎደል ስምንት ዓመታት ፈጅቶ ስምምነት ያልተደረሰበትን ድርድር በአራት ስብሰባዎች ለመጨረስ የጊዜ ማዕቀፍ ተቀምጦ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ፋታ እንዲያጡ እና ሀገርቤት ካለው ብሔራዊ የባለሙያዎች መማክርት እንዳይገናኙ ሆነው ማሳለፋቸውን የሚገልጹት እኝሁ ምንጫችን
‹‹ የነበረው የድርድር ሂደት ፍትህ የተጓደለበት እና የኢትዮጵያን ጥቅም ሙሉበሙሉ ለመንጠቅ በስልት የተቀነባበበረ ነበር››
ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ሐሳብ ተቀባይነት እንዳይኖረው ከመደረጉ ባለፈ ‹‹ ስምምነት ደርሳችሁ ባትፈራረሙ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት ይመጣል›› የሚሉ ማስፈራሪያዎች ጭምር እንደገጠማቸው ገልጸዋል፡፡
የታዛቢነት ሚና ብቻ እንዲኖራቸው ስምምነት ተድርጎ ድርድሩን ይከታተሉ የነበሩት አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ተወካዮች ፤ወደስምምነት የሚያቀርቡ ሐሳቦች እያሉ ድርድሩ ግብፅን በሚጠቅም አቅጣጫ እንዲጓዝ ይዘውሩ እንደነበረም ገልጸዋል፡፡ስምምነት እንዲደረግበት የተረቀቀው ሰነድ ላይ ባደረጉት ምልከታም የህዳሴ ግድቡ ዝቅተኛ ኃይል የማመንጨት አገልግሎቱን ለማከናወን የሚያስችለው (Minimum Operation Level) የውኃ ሙሌት በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲከናወን የሚደነግግ አንቀጽ ከመቀመጡ ውጪ ፤ቀሪው ዋና የውኃ ሙሌት በምንያህል ዓመት እንደሚከናወን የሚገልጽ አንቀጽ በረቂቁ አለመካተቱን ገላጸዋል፡፡
ግብፅ በድርድሩ ወቅት ካነሳቻቸው ነጥቦች አንዱ እና አከራካሪ የነበረው በዋናው የውኃ ሙሌት ወቅት ወደታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የሚፈሰው ተፈጥሯዊ የውኃ መጠን መቀነስ የለበትም የሚለው ሐሳብ እንደሚገኝበት ያስታወሱት ምንጫችን፤ በተመለከቱት ረቂቅ ስምምነት ሰነድ ውስጥ የግድቡ ዋና ሙሌት በምን ያህል ዓመት ውስጥ ይከናወናል የሚል አንቀጽ ሳይካተት እንደታለፈ እና ይህም ሆንተብሎ ኢትዮጵያን በቃላት ትርጓሜ ለመጠምዘዝና የግብፅ እና ሱዳንን የውኃ ፍላጎት ለማስጠበቅ የተቀመጠ ሴራ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ወደዚህ ድምዳሜ ሊያደርሱ የሚችሉ ሌሎች ተያያዥ አንቀጾች መኖራቸውንም ይገልጻሉ፡፡ለዓብነትም በመደመኛ የዝናብ ወቅት የግድቡ ውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ እንዴት እንደሚሆን ወይም በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በዓመት የምትለቀው ውኃ ምን ያህል እንደሆነ አልመገለጹን ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን በድርቅ ወቅት ፤ በተራዘመ የድርቅ ወቅት እና በተራዘመ ዝናብ ወቅት ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በግድቡ ሙሌት ሆነ ሙሌቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚለቀቅላቸው ዓመታዊየ ውኃ መጠን በሰነዱ መመላከቱን ገልጸዋል፡፡ ይህ አንቀጽ ለዘመናት የቆየውን ኢፍተሐዊ አጠቃቀም የሚያስቀጥል እንደሆነ የሚገልጹት ባለሙያው ፤ በዚህ አንቀጽ ኢትዮጵያ መልቀቅ የሚጠበቅባትን የውኃ መጠን ይገልጻል እንጂ ድርቅ፤ የተራዘመ ድርቅ ማለት ምን እንደሆነ አለመተርጎሙንም ጠቁመዋል፡፡
ለነዚህ ወቅቶች ሳይንሳዊ ትርጓሜ ሊሰጥ ሲገባ ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 37 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከሆነ እንደድርቅ የሚቆጠር መሆኑ በሰነዱ መመላከቱን ያስረዳሉ፡፡
ይኸው ፍሰት መጠን ለተከታታይ ዓመታት ከቀጠለ ደግሞ ተከታታይ ድርቅ የሚል ትርጓሜ እንደሚይዝ እና ሁኔታው ለአምስት ዓመታት ከቀጠለ ኢትዮጵያ ለታችኞቹ ሀገራት 40 ቢሊዮን ሜተር ኩብ ውኃ በዓመት እንድትለቅ የሚያስገድድ አንቀጽ መስፈሩን ይገልጻሉ፡፡
በመሆኑም የተባለውን የውኃ መጠን በነዚህ ወቅቶች ለማሟላት ግድቡ ከያዘው ውኃ መልቀቅ እንደሚኖርባት እና ይህንን ሳታደርግ ብትቀር ዓመት የምትለቀው የውኃ መጠን እንደተጠበቀ ሆኖ ግድቡ ዝቅተኛ ኃይል የማመንጨት አገልግሎቱን ለማከናወን ከሚያስችለው 18 ቢሊዮንሜትር ኩብ ውኃ በላይ ያለው የተጠራቀመ የውኃ ወደ 25 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እስኪደርስ ድረስ በዓመታት ተከፋፍሎ ከግድቡ እንዲወጣ ማድረግን ሰነዱ በቅጣት መልክ አስቀምጦታል፡፡‹‹ወደግድቡ የሚደርሰው የአባይ ዓመታዊ ፍሰት 37 ቢሊዮን ሜትር ኩብ የሆነው በዝናብ እጥረት ይሁን፤ ወይም ኢትዮጵያ በላይኛው የአባይተፋሰስ ላይ ሌሎች መሰረተልማቶችን በማልማቷ፤ አልያም ያልተለመደ ከፍተኛ ሙቀት ተከስቶ የውሃ መጠኑ በትነት ቀንሶ እንደሆነ ሰነዱ ከግምት ለማስገባት አልፈለገም፡፡ ስለዚህም እጅግ ኢፍትሐዊ ከመሆንአልፎ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጭምር የሚጨፈልቅ ድንጋጌነው›› ሲሉይገልጹታል፡፡
‹‹የአባይ ውኃ አማካኝ ዓመታዊ መጠን 49.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ መሆኑ በሳንይንስ የተረጋጠ ሆኖ ሳለ ወደ ግድቡ የሚመጣው ዓመታዊ የውኃ መጠን 37 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከሆነ የድረቅ ወቅት ነው ማለት ፤ ኢትዮጵያ የግድቡን የኃይል ማመንጨት ተግባር ለማስቀጠል እና በላይኛው የአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ሌሎች ልማቶችን ለማከናወን የምትችለው በሁለቱ አህዞች መካከል ያለውን 12 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ስምምነትመቀበል ማለት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲደፈር ማድረግ እና በቀጣዩ ትውልድ ፍላጎቶች ላይ መወሰን ነው›› ሲሉ ተያይዞ ሊመጣ የሚችለውን አጣብቂኝ አብራርተዋል፡፡የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ድርድሩ ወደታችኞቹ ሀገራት በዓመት የሚለቀቅ የውሃ መጠንን በማረጋገጥ ላይ መሰረት አድርጎ የተካሄደ በመሆኑ ወደታችኞቹ ሀገራት የሚወርደው የውሃ መጠን ስሌት በዓመት ወደግድቡ ከሚመጣው የአባይ ውሃ መጠን ላይ ሊሆን ሲገባው በረቂቅ ሰነዱ ላይ ግን የተመለከተው ከህዳሴ ግድቡ ተብሎ መሆኑ ሌላው በረቂቁ ያስተዋሉት ሸፍጥ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን የተገለጹት ስህተቶች እንዲታረሙ በአሜሪካ በተካሄደው የመጨረሻ ድርድር ወቅት አንስቶ የነበረ ቢሆንም በረቂቅ ሰነዱ ውስጥ ግን አለመካተታቸው ተረጋጧል፡፡ ‹‹ይህንን ስምምነት ሰነድ ተቀብሎ መፈረም ኢትዮጵያ በትውልዶች መካከል የግብፅ ውኃ ባለዕዳ እንድትሆን ያደርጋታል ፤ የህዳሴ ግድቡም ለኢትዮጵያውያን ኩራት እና የሰነደቅ ዓላማ ፕሮጀክት መሆኑ ቀርቶ አንጡራ ሀብቷን አፍስሳ ለግብፅ እና ሱዳን የገነባችው የውኃ ቋት ይሆናል›› ሲሉ ምንጫችን ገልጸውታል፡፡
ኢትዮጵያ የተሳሳተችው የቱጋርነው?
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የህግ መምህር እና በዓለምአቀፍ ህግ በዋናነትም ድንበር ተሸጋሪ ወንዞችን በተመለከተ ተመራማሪ የሆኑት (ዶ/ር) የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በሚደረገው ድርድር ውስጥ ሦስተኛ ወገን እንዲገባ ኢትዮጵያ የፈቀደች ቀን ስህተቱ እንደተፈጸመ ያስረዳሉ፡፡
አ.ኤ.አ. ማርች 2015 ላይ በኢትዮጵያ ፤ በግብፅ እና ሱዳን መካከል ህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ የተፈራረሙት የትብብር መርህ መግለጫ ስምምነት (Declaration of Principles) ለኢትዮጵያ የጉዳት መንገድ እንደሆነ እና መንግስት አሁን የሚገኝበት አጣብቂኝም የዚሁ ውጤት መሆኑን ይከራከራሉ፡፡ኢትዮጵያ ግድቡን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻ እንደምትጠቀምበት ፤የግድቡ አሞላል እና የረጅም ጊዜ አስተዳደርን የተመለከተ ቀመር ከታችኞቹ ሀገራት ጋር በስምምነት ለመቅረጽ ፤ እንዲሁም በነዚህ ጉዳዮች ላይ ስምምነት መድረስ የማይቻል ከሆነ አሸማጋይ ለማስገባት ስምምነት መፈራረሟን ያስታወሱት የድንበር ተሸጋሪ ወንዞች ባለሙያው ደረጄ ዘለቀ (ዶ/ር) ፤ በዚህምምክንያትፈቅዳበገባችበትየጉዳትመንገድለመጓዝመገደዷንይገልጻሉ፡፡ መንግስት ይህንን ስምምነት በፈረመበት ወቅት ስምምነቱ ‹‹በአባይ ውኃ ፖለቲካ ላይ ጨዋታ ቀያሪ›› እንደሆነ በድል ስሜት ሆኖ ለህዝብ ተናግሮ ነበር፡፡ የዚህ ስሜት እና መረጃ ምክንያቱ ግብፅ በስምምነቱ ውስጥ የሰፈረውን ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን የመጠቀም መብት ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀብላ መፈረሟ ነው፡፡
ስለጉዳዩ የተጠየቁት ደረጄ ዘለቀ (ዶ/ር) ግን፤ ግብፅ በኢትዮጵያ የመጠቀም መብት ላይ ተስማማችም አልተስማማችም የተባበሩት መንግስታት ባጸደቀው እና እ.ኤ.አ. በ2014 ወደ ተግባር የገባው የዓለም የውኃ ኮንቬንሽን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት ሳያደርሱ ድንበር ተሸጋሪ ወንዞቻቸውን መጠቀም እንደሚችሉ መደንገጉ ንይገልጻሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ግብፅ በአባይ ውኃ ላይ በያዘችው የበላይነት ጥቅማቸውን ያጡ ሀገራትን ኢትዮጵያ አስተባብራ ግብፅ እና ሱዳንን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት 13 ዓመታትን የፈጀው ድርድር ውጤት የሆነው የአባይ ውኃ የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ ከተካተቱት ድንጋጌዎች መካከል ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት ውኃውን በተገለጸው ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህ መጠቀም እንደሚችሉ እውቅና ማግኘታቸውን ያስረዳሉ፡፡
ይህ ማእቀፍ ከመፈረሙ በፊት በነበረው ድርድርም የአባይን ውኃ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎቹ ሀገራት የመጠቀማቸው ጉዳይ በግብፅ በኩል ተቃውሞ እንዳልቀረበበትም ይገልጻሉ፡፡ ስለሆነም መንግስት ይህንን ጉዳይ እንደ ድል የሚቆጥረው የፈጸመውን ስህተት ለመደበቅ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ በማከልም ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከሱዳንእና ግብፅ ጋር በፈረመችው ስምምነት የአባይ ውኃ ትብብር ማዕቀፍን እንዲፈረም ከጎኗ በነበሩ ሌሎች የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ክህደት ፈጽማለች ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡‹‹አሁን ያለው አማራጭ ጉዳቱን መቀነስ ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ፍላጎት ምንድን ነው ?
የአባይ (የናይል) ወንዝ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በተለይ ደግሞ ከቀዝቃዛው ጦርነት አንስቶ የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ትኩሳት አካል መሆኑን፤ አሩን ኢልሐንስ የተባሉት አሜሪካዊ የውኃ ፖለተካ ተመራማሪ እ.ኤ.አ. በ1999 ለንባብ ባበቁት Hydropolitics in the Third World: Conflict and Cooperation in International River Basin በተሰኘ መጽሐፋቸው በዝርዝር ገልጸዋል፡፡
ግብፅ ሌሎች የአረብ ሀገራትን በመምራት እ.ኤ.አ. በ1949 የመጀመሪያውን የአረብና እስራኤል ጦርነት መክፈቷን ተከትሎ አሜሪካ ፤ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ በግብፅ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የጣሉ ሲሆን በ1950 መጀመሪያ ላይ የወቅቱ የግብፅ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጋማል አብዱል ናስር በአባይ ወንዝ ላይ ይፋ ላደረጉት የታላቁ አስዋን ግድብ ፕሮጀክት የፋይናንስ ድጋፍ የተጠየቁት አሜሪካም ሆነች በአሜሪካ ተጽዕኖ ስር የሚገኘው የዓለምባንክ የግብፅን የፋይናንስ ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ግንባታ መግባት ያልቻለው ‹‹የናስር ፒራሚድ›› በሚል ቅጥያ መጠሪያ የሚታወቀውን ታላቁ አስዋን ግድብ ከፕሮጀክት፤ ከሰነድነት ወደ ዕውነታ መምጣት የቻለው በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በነበረው የመካለኛው ምስራቅን ፖለቲካ ለመቆጣጠር በነበረው የኃያላን አገራት ፉክክርን እንደ እድል በመጠቀም በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ መሆኑን አሩን በመጽሐፋቸው ያስረዳሉ፡፡
የመካከለኛው ምስራቅን ፖለቲካ ለመቆጣጠር ሶቬት ህብረት እና አሜሪካ ያደርጉት የነበረውን ብርቱ ፉክክር ወደ ዕድል የለወጠችው ግብጽ ከሶቬት ህብረ ትባገኘችው ፋይናንስ ድጋፍ እ.ኤ.አ. በ1961 የአስዋን ግድብን ግንባታ አስጀምራለች፡፡
ለዚህ አጠፋዊ ምላሽ ለመስጠትም አሜሪካ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ በማዞር በወቅቱ የነበረው የንጉስ ኃይለስላሴ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ የልማት ፕሮጀክቶችን እንዲያከናውን ማገዝ ጀመረች፡፡ አሁን ህዳሴ ግድብ ተብሎ የሚጠራው ፕሮጅክትም የተቀረጸው በዚሁ ወቅት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡አሜሪካ ከግዛቷ ውጪ ያላትን ጂኦ ፖለተካዊ ፍላጎት ለማስፈጸም የምትጠቀምበት ቢሮ ኦፍሪክላሜሽን የተሰኘው ተቋም ኢትዮጵ በአባይ ወንዝ ላይ ልትገነባቸው የምትችላቸውን አራት የኃይል ማመንጫ ፕሮጅክቶችን አጥንቶ በወቅቱ ለነበረው መንግስት አስረክቧል።
እነዚህ ካራዶቢ (1350 ሜጋዋት) ፣ማቢል ( 1200 ሜጋዋት) ፣መንዲያ ( 1620 ሜጋዋት ) እና ቦርደር ዳም (የድንበር አካባቢ ግድብ) የሚል መጠሪያ የተሰጠው 1400 ሜጋ ዋት እንደሚያመነጭ በጥናቱ የተገመተውና አሁን ላይ ህዳሴ ግድብ የተባለው ኃይል ማመንጫ ይገኝበታል። አሜሪካ ይህንን ጥናት እ.ኤ.አ. በ1964 አስጠንታ ለኢትዮጰያ ካስረከበች በኋላ በወቅቱ አቅም ያልነበረውን የኢትዮጵያ መንግስት ፕሮጀክቶቹን እንዲተገብር ያደረገችው እገዛ አልነበረም። ከዛ ይልቅ በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካን ለመቆጣጠር የጀመረችውን ትግል መቀጠሉን መርጣለች።
የጋማል ናስር ወራሽ በመሆን ግብፅን ለማስተዳደር የተሾሙት ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት እስራኤል እ.ኤ.አ. በ1967 በግብፅ እና በሌሎች የአረብ ሀገራት ላይ የተቀዳጀችውን ድል ለመበቀል እና የተቆጣጠረቻቸውን አካባቢዎች ለማስለቀቅ ከሶሪያ እና “ጆርዳን ጋር በአንድነት ሆነው እ.ኤ.አ. በ1973 በእስራኤል ላይ የከፈቱት ጦርነት ያልተጠበቀ እና አሜሪካ እና ሶቬት ህብረትንም ከእጅ አዙር ውጊያ በቀጥታ ሊያጋጥም የሚችል ክስተት ነበር።የሶቬት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ላይ ተንተርሰው ወደ ውጊያ የገቡት ፕርዝዳንት አንዋር ሳዳት ጦርነቱ ያቀዱትን ያህል ውጤታማ ባለመሆኑ እና ከሶቬት ህብረት ያገኙት ድጋፍም የተሻለ የማጥቃት አቅም እንዳልፈጠረላቸው በመገንዘብ የስትራቴጂ ለውጥ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።በዚህምመሆንምክንያትግብፅከሶቬትህብረትጋርየነበራትንግንኙነትበይፋአቋርጣለች።
በተመሳሳይ ወቅት የኢትዮጵያ አብዮት ተጠናቆ ወታደራዊው መንግስት ስልጣን የጨበጨበት እና የኢትዮጶያ የፖለቲካ አሰላለፍም ቀድሞ ከነበረው የአሜሪካ ወዳጅነት ወደ ሶቬት ህብረት የተሸጋገረ መሆኑ ግብፅ ትኩረቷን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ እንድታተኩር ደርግ አስገድዷታል።

ወደ ስለጣን የመጣው ወታደራዊ መንግስት መገለጫ የሆነው ኢትዮጵያዊ አንድነት እና ቁርጠኝነት የአባይ ውኃን ወደ መንካት ይሸጋገራል የሚል ስጋት የገባው የግብፅ መንግስት ፊቱን ወደ አሜሪካ በማዞር አስደናቂ ወዳጅነትን በአጭር ጊዜ በመመለስ ከእስራኤል ጋር የነበረውን ግጭት እ.ኤ.አ. በ1979 የካምፕዴቪድ ስምምነት ፈትቷል።ይህ ስምምነት የአረብ እና እስራኤል ጦርነቶች ምክንያት የሆውን እና እስካሁንም የቀጠለውን የፍልስጤም ጉዳይ ምላሽ ባይሰጥም፤በእስራኤል ቁጥጥር ስር ወድቀው የነበሩ የግብፅ የሲናይ ግዛት እና ሌሎች ይዞታዎችን አስመልሷል።
ይህንን በአሜሪካ ግዛት አካል በሆነችው ኬምፕዴቪድ የተፈጸመውን የሰላም ስምምነት ያደላደሉት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፤ስምምነቱ ዕውን እንዲሆን በግብፅ በኩል ከቀረቡላቸው ሁለት የጎንዮሽ የድርድር ነጥቦች መካከል አንዱ የግብፅን የአባይ ውኃ ጥቅም እንደራሷ የደህንነት ጉዳይ እንድታስጠብቅ የሚጠይቅ ሲሆን፣ሁለተኛው ደግሞ ግብፅ ከእስራኤል ጋር የምታወርደው ሰላም ከሌሎች የአረብ ሀገራት ተነጥላ በመሆኑ ከነዚህ አገራት ሊደርስ የሚችል ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል የመከላከያ ኃይል የግንባታ ድጋፍ ነው።በዚህ ቅድመ ሁኔታ መሠረት የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የግብፅ መከላከያ ሰራዊት በየዓመቱ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ድጋፍ ከአሜሪካ ያገኛል።
ይህ ከሆነ ከ45 ዓመት በኋላ በስልጣን ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕረዚዳንት ዶናልድትራምፕ 70 ዓመታትን ያስቆጠረውን የእስራኤል እና የፍልስጤም ጉዳይ በሰላም ለመቋጨት እርሳቸው “Deal of the Century” ያሉትን የሠላም ፍኖተካርታ እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2020 ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዞዳንት ትራምፕ ይህንን የሠላም ዕቅድ ለማሳካት የአረብ ሀገራትን ድጋፍ በተለይም በአረብ ሀገራት ላይ ተፅዕኖ ያላትን የግብፅን ድጋፍ የበለጠ የሚሹ ሲሆን ይህንን የምትገነዘበው ግብፅም በታላቁ የኢትየጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ ጠረጴዛዋ ላይ አኑራዋለች።በዚህም የተነሳ የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ እና የአባይ ውኃ በአጠቃላይ የተፋሰሱ ሀገራትን ብቻ የሚመለከት መሆኑ ቀርቶ የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ውስብስብ ውስጥ መውደቅ ግልጽ ሆኗል።
የኢትዮጵያአማራጭምንድንነው ?
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ፖለቲካዊ ጉዳዮች እና የውኃ ፖለቲካ ዙሪያ የሚመራመሩት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ከአሜሪካ መንግስት መፍትሔ ይገኛል ብሎ በአሜሪካ አደራዳሪነት ወይም ታዛቢነት ኢትዮጵያ ድርድር ውስጥ መግባቷ ስህተት ነው ይላሉ።አሜሪካ እንድታደራድራቸው የተማፀኑት የግብፅ ፕሬዚዳንት አልሲሲ መሆናቸውን የሚናነሩት ፕሮፈሰር ተስፌዬ በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያቶች በተለይም ግብፅ ናአ ሜሪካ ከካምፕ ዴቪድ ስምምነት ጊዜ ጀምሮ በፈጠሩት ጠበቅ ያለ ግንኙነት ሁሉንም ሀገራት በዕኩል የሚጠቅም መፍትሔ ሊገኝ እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡
እንደሚታወቀው በዓለም ላይ ከፍተኛ የአሜሪካ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕርዳታ ከሚያገኙት አንደኛ እስራኤል ስትሆን፣ሁለተኛዋ ደግሞ ግብፅናት፡፡በዚህም ምክንያት
የግብፁ አልሲሲ ፤ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ከኢትዮጵያ ጋር እንዲያሸማግሉዋቸው ስለተማፀኑዋችው ነው የገቡበት እንጂ፣ሰውዬው (ዶናልድትራምፕ) ስለ ናይል ብዙ የሚያውቁት ነገርያ ለአ እንደማይመስላቸው ተናግረዋል፡፡
በግብፆች ዕሳቤ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጠቀም ያለ ድጋፍ የምታገኝ ስለሆነች አልያም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች አሜሪካውያንን ሲያዩ ሊፈሩ ይችላሉ ብለው ገምተው ጉዳዩን ወደ አሜሪካ እንደወሰዱት የሚናገሩት ፕሮፌሰር ታፈሰ፤ “ኢትዮጵያ የአሜሪካን ሸምጋይነት በምን ዕሳቤና ለምን እንደተቀበለች ለእኔ ግልጽ አይደለም” ብለዋል።ይህ ዕሳቤያቸው ውጤት እያመጣላቸው እንደሆነ የሚገልጹት ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ ጥቅሟን ማረጋገጥ ከፈለገች ከዚህ ኢፍትሀዊ መንገድ ለመውጣት መወሰን እንዳለባት ይመክራሉ።የአባይ ወንዝ ላይ ያለመግባባት መፍትሔ ማግኘት ያለበት፤ ወንዙ ከሚፈስባቸው አገሮች ከራሳቸው አልያም እነርሱን ከሚወክለው ከአፍሪካ ህብረት እንደሆነ የመከሩት ተመራማሪው ፤ህብረቱም የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊያን መፍትሔ መስጠት (African Solutions to African Problems) የሚል ፕሮግራም የዘረጋ በመሆኑ ይህንን ልዩነቶቹ በሦስቱ አገራት የማይፈታ ከሆነ ይሀንን እድል መጠቀም እንደሚሻል ጠቁመዋል።
ደረጄ ዘለቀ (ዶ/ር) የሰጡት የመፍትሔ ሀሳብም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ኢትዮጵያ በ2015ቱ ስምምነት ስህተት ብትፈጽምም አሜሪካ ጣልቃ እንዳትገባ ግን ጥርሷን ነክሳ መወሰን እንዳለባት ይመክራሉ።አሜሪካ እና ዓለም ባንክ ሊመጣ የሚችለው ተጽዕኖ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የኢኮኖሚ ድጋፍ ማድረቅ ሊሆን እንደሚችል የሚገልጹት ደረጄ ዘለቀ (ዶ/ር)፤ትውልድን ባለእዳ ከማድረግ መንግስት የሚመጣውን የአጭርጊዜ ጉዳት ጠንካራ ሆና ለመወጣት ቢሞክር የተሻለ እንደሚሆን አሳስበዋል።
አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ ደግሞ መንግስት በአሜሪካ ተጽዕኖ ስር ከወደቀው ድርድር ለመውጣት በመወሰን የራሱን የድርድር ሀሳብ በማርቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።እንደምንጫችን ገለጻ የታዛቢነት ሚና የተሰጣቸው አሜሪካ እና ዓለም ባንክ ድርድሩን ወደ ሽምግልና መቀየራቸው እና በመጨረሻም ራሳቸው አርቅቀው ለስምምነት ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ኢትዮጵያ እንደማትደራደርባቸው የገለጸቻቸውን በርካታ ነጥቦች ያላካተተ እና ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ጥቅም በዕጅጉ ያደላ በመሆኑ በኢትዮጵያ ተቀባይነት እንደማይኖረው አቋም መያዙን ገልጸዋል።የቀረበው ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ከህዳሴ ግድቡ አልፎ የአባይ ውኃ ክፍፍልን የሚመለከቱ አንቀጾች የተካተቱበት በመሆኑ ከድርድር አጀንዳው ያፈነገጠ መሆኑን በመንግሰት ተለይቷል ያሉት ምንጫችን፤ በቀጣይ የሚከተለው መንገድ የኢትዮጵያ ሉዐላዊነትን እና ጥቅምን በማስከበር እንደሚሆንም ገልጸዋል።