የዚህ ወር ሪፖርተር መጽሔት የአደባባይ እንግዳችን ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር) ናቸው፡፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሕግና አስተዳደር ዲፓርትመንት ተመራማሪና መምህር ሲሆኑ፤ በዓለም አቀፍ የውሃ፤አየርንብረትና ደርጅቶች ላይ በርካታ ጠናቶችን አድርገዋል፡፡ ስለ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሕጎችጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ዶ/ር ደረጀን፤ኢትዮጵያ፤ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ እያደርጉት ስላለው ድርድርና ተያያዢ ጉዳዮች ላይ ከሪፖርተር መጽሔት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ |
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷ የታችኞቹን የተፋሰስ አገሮችን ጥቅም ባገናዘበ መልኩ ለማረጋገጥ ያደረገችውን፤ የምታደርገውን ጥረትና እየገጠማት ያለውን ፈተና ቢያስረዱን?
ዶ/ር ደረጀ፡- በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ በኢትዮጵያ የተለዋወጡ መንግሥታት አቋም፣ ያልተለዋወጠ አቋም ነው፡፡ ይኼ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጀምሮ፣ በደርግም ሆነ በኋላ በነበረው መንግሥት ያልተለወጠ አቋም ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ የተፈጥሮ ሀብት የነበረው ፍትሐዊ የሆነ የመጠቀም ፖሊሲ ነው ፡፡ የሌሎች አገሮችን ልምድ ብንመለከት፣ በኢንዱስትሪ ውኃ አጠቃቀም አገሮች ለፍሰቱ ባላቸው ተዋጽኦ መሠረት ነው የመጠቀም ጥያቄ የሚያነሱት፡፡ ህንዶች ‹‹90 በመቶ የሚሆነው ውኃ የሚመነጨው ከእኛ ስለሆነ ማንም አያገባውም፤›› የሚል አቋም ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት የነበራት አቋም በመንግሥታት መቀያየር ያልተቀየረ ዘላቂ አቋም ነው፡፡ ከዚህ የተፈጥሮ ሀብት ፍትሐዊ ድርሻን የመጠቀም አቋም ነበራት፡፡ አሁንም ያ አቋም ቀጥሏል፡፡ ይኼ አቋም ሁልጊዜ የሌሎች የተፋሰሱ አገሮች መብትን ዕውቅና የሰጠ አቋም ነው፡፡ ዛሬም ሆነ ወደፊትም የሚደረገው ጥረት ይኼንኑ ፍትሐዊ የተጠቃሚነት መብት የማረጋገጥ ጥረት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ግብፅና ሱዳን የዓባን ወንዝ በብቸኝነት የመጠቀም ሕጋዊ መብት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ እንደ መከራከሪያ የሚያነሱትም በ1929 ዓ.ም. የተፈረመውን የቅኝ ግዛት ስምምነትና በ1959 ዓ.ም. የተፈራረሙትን ስምምነት ነው፡፡ ይኼ ስምምነት ደግሞ 85 በመቶ የሚሆነው የውኃው ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎች የተፋሰሱ አገሮችም አባል ያልሆኑበት ስምምነት ነው፡፡ ይህ ስምምነት በሌሎቹ አገሮች ላይ የመፈጸም ሕጋዊነትን ከዓለም ዓቀፍ ሕጎች አንፃር እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ደረጀ፡- ግብፅና ሱዳን ተፋሰሱን በብቸኝነት የመጠቀም መብት ታሪካዊ ዳራ አለው፡፡ በሁሉም ትልልቅ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ታሪክ ውስጥ ሁልጊዜም የግርጌ አገሮች የቀደመ የመጠቀም መብት አላቸው፡፡ በአብዛኛው ውኃ የሌላቸው በመሆኑ ከዚያ ጋር ተያይዞ ለብዙ ዘመናት በውኃ ላይ የመጠቀም ታሪካዊ እውነታ አለ፡፡ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥርዓት ሲተከል ይህንን የተፈጥሮ ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ በማልማት ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ታሳቢ ያደረገ የኢምፔሪያል ዲዛይን ነበር፡፡ በእነዚህ ሒደቶች የግርጌ አገሮች በተለይም ግብፅና ሱዳን ተጠቃሚነትን ዕውን እንዲያደርጉ ታሪካዊ እውነታዎችን አመቻችተውላቸዋል፡፡ የ1929 ዓ.ም. ስምምነትም ይህንኑ እውነታ ቅርፅ ለማስያዝ የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ በእርግጥ ስምምነቱ ኢትዮጵያን የሚመለከት ምንም ዓይነት ነገር አልነበረውም፡፡ ሌሎቹን የተፋሰስ አገሮች መለከታተል ቢባል እንኳን የፀና የዓለም አቀፍ የሕግ መሠረት የለውም፡፡
ሪፖርተር፡- ግብፆች አሁንም ያላቸው አቋም ይኼንን መብት የማስከበር ነውና እዚህ ላይ በደንብ ቢያብራሩት?
ዶ/ር ደረጀ፡- ግብፆች ለሺሕ ዓመታት ውኃውን በብቸኝነት ሲጠቀሙ የኖሩ በመሆናቸውና በኋላም በ1929 ዓ.ም. በነበረው ውል ብቸኛ ተጠቃሚ አድርጎ ታሳቢ በማድረግ የተሠራ ውል በመሆኑና እነዚህን እየደማመሩ የውኃው ባለመብቶች ነን ይላሉ፡፡ ታሪካዊ ባለመብትነትን ለማስረዳት ልዩ ልዩ ስያሜ ይሰጡታል፡፡ የቀዳሚ ተጠቃሚነት መብት እንዳላቸው ደጋግመውም ይናገራሉ፡፡ እነዚህ የሚያነሷቸው ጽንሰ ሐሳቦች በዓለም አቀፍ ሕግም ሆነ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሕግ ውስጥ ምንም መሠረት የሌላቸው ናቸው፡፡ ምክንያቱም ‹‹የተፈጥሮ ሀብቱ የሚመነጭበት አገር ውኃውን መቼ መጠቀም አለበት?›› የሚለው ጥያቄ ከተጠቃሚነቱ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ለአምስት ሺሕ ዓመታት ተጠቅመነውም፣ ለሚቀጥለው ሁለት ሺሕ ዓመታት አልተጠቀምነውም፣ ያንን በማድረጋችን የምናጣው ነገር የለም፡፡ የተፈጥሯዊ ተጠቃሚነት መብት፣ የሉዓላዊነት መብት ነው፡፡ ስለዚህ በመጠቀም ወይም ባለመጠቀም የሚታጣ መብት አይደለም፡፡ የሀብቱ ምንጭ የሆነው አገር ሉዓላዊ መብት እስከሆነ ድረስ የማይታጣ መብት ነው፡፡ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ላይ ‹‹ታሪካዊ የመጠቀም መብት›› ብሎ ነገር የለም፡፡ በዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ማዕቀፍ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ጽንሰ ሐሳብ የለም፡፡ ተጠቃሚ መብት፣ ታሪካዊ መብትና ሌላም ስም ሊሰጡት ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡
ሪፖርተር፡- የመከራከሪያ ነጥባቸው ቋሚ (Existing) ወይም ዋና (Potential) ተጠቃሚ የሚለው ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል?
ዶ/ር ደረጀ፡- እንደሱ አይደለም፡፡ እነሱ ታሪካዊ ወይም ቀዳሚ የተጠቃሚነት መብት ሲሉ፣ እንደ ሕጋዊ መብት ነው እያነሱ (Claim) ያሉት፡፡ እነዚያን መብቶች የሚያቋቁም የዓለም አቀፍ መርህ የለም፡፡ ለሺሕ ዓመታትና ከዚያም በፊት ከሌሎቹ አገሮች በተለየ ሁኔታ ሲጠቀሙ መኖራቸው ታሪካዊ እውነታ ነው፡፡ ግን ታሪካዊ እውነታ (Historical Fact) ወደ ሕጋዊ መብትነት (Legal Right) ሊተረጎም አይችልም፡፡ ስለዚህ መሠረት የለውም፡፡ የ1929 ዓ.ም. ስምምነት 85 በመቶ የሚሆነው የተፈጥሮ መብት ያላትን ኢትዮጵያ የማይመለከት ስምምነት ነው፡፡ ምናልባት ይመለከታታል ከተባለም ተተኪ መንግሥታትን (Successor States) ነው የሚመለከተው፡፡ ይኼም ቢሆን መሠረት የለውም፡፡ ወደ እነሱ ሊሻገር የሚችልበት አግባብ የለም፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ተተኪዎቹ አገሮች፣ መብቶችና ግዴታዎች በጥቅሉ ይሸከማሉ የሚለው መርህ ተቀባይነት የለውም፡፡ የአገሮች የመተካካት ሕግ ተብሎ ሊተረጎም ይችል ይሆናል፡፡ በሕጉ ሎው ኦፍ ሰክሴሽን (Law of Succession) ይባላል፡፡ አንድ አገር ተለያይቶና ፈርሶ በእሱ እግር ሌሎች ቢመጡ ‹‹የቀደመው መንግሥት ሕጋዊ ግንኙነቶች፣ መብቶችና ግዴታዎች ወደ አዳዲሶቹ አገሮች እንዴት ነው የሚተላለፉት?›› የሚል አንድ ዓለም አቀፍ ሕግ ክፍል ሲሆን፤ ከቅኝ ግዛት የወጡ አገሮች የሚኖራቸውን ሕጋዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች የሚመለከተው መርህ(Clean Slate Theory)፤ እያንዳንዱ አገር ሉዓላዊ ሆኖ ነው ዓለም አቀፍ ግንኙነቱን የሚቀላቀለው፡፡ ስለዚህ የሉዓላዊ አገር መብቶችና ግዴታዎች ለአዲሶቹ ተተኪ አገሮች በቀጥታ (Automatic) ይሸጋገራል በሚለው በዓለም አቀፍ ጽንሰ ሐሳብ (Universal Succession Theory) ተቀባይነት የለውም፡፡ በዚያም እንኳን ቢሆን በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የተፋሰሱ አገሮች የ1929 ዓ.ም. የውኃ ስምምነት በሌሎቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ለመጫን የሚቻልበት ሕጋዊ መሠረት የለም፡፡ ሌላው የሚያነሱት መከራከሪያ ምክንያት በ1959 ዓ.ም. በሱዳንና ግብፅ መካከል ያደረጉትን ስምምነት ነው፡፡ ይኼ ስምምነት በሁለት ነፃ የተፋሰስ አገሮች መካከል ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት ነው፡፡ ስለዚህ በሁለት አገሮች መካከል የተቋረጠ ውል መብትም ይሁን ግዴታ ሊጫን የሚችለው በሁለቱ አገሮች መካከል ነው፡፡ ሌሎቹ የተፋሰስ አገሮች ግን በዚህ ውል ሊጫንባቸው የሚችል ግዴታ የለባቸውም፡፡ የስምምነቱ ዓላማ ቀድሞ የነበረውን የበለጠ መሠረት ለማስያዝና የውኃውን ተጠቃሚነት ሙሉ በሙሉ በሁለቱ አገሮች ብቻ ለማድረግ ነው፡፡ የ1929 ዓ.ም. ስምምነት የተወሰነውንና በጥቅም ላይ ሊውል የሚችለውን የተፋሰሱን 52 ቢሊዮን ኩብ ውሃ ውስጥ 48 ቢሊዮን ኩብ ለግብፅ፣ አራት ቢሊዮን ኩብ ለሱዳን በሚል ስምምነት ተከፋፍለውት የነበረውን በ1952ቱ ስምምነት ደግሞ ተጨማሪ ሥራዎች ለመሥራት የውኃውን ፍሰት በመጨመር ሙሉ በሙሉ (Full Utilization) ለመጠቀም የተደረገ ስምምነት ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል አለ በሚባለው የውኃ አጠቃቀም የሕግ ማዕቀፍ መሠረት፤ ለሌሎች ተፋሰስ አገሮች ጠብታ ውኃ እንኳን አልተረፈም ማለት ነው፡፡ ይኼንን እውነታ ነው ሌሎች አገሮች እንዲቀበሉ ለረዥም ዓመታት ክርክር ሲደረግበት የነበረው፡፡ ይህንኑ ዓላማ በልዩ ልዩ ስም ሕጋዊ መልክ ባላቸው፣ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ሕግ ግን መሠረት የሌላቸው ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፡፡ የረዥም ጊዜ ተጠቃሚነት፣ ታሪካዊ መብት የሚባሉት በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ የውስጥ ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፡፡ አንድ ሰው በንብረቱ ለረዥም ጊዜ ሳይጠቀምበት ከቆየና ሌላ ሰው ሲጠቀምበት ከኖረ፣ ያ ሰው በንብረቱ ላይ የባለቤትነት መብቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነው በግለሰብ ግንኙነት (Private Law Concept) ውስጥ ነው፡፡ በአገሮች ግንኙነት መካከል፣ በተለይም ደግሞ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም በሚመለከት ጉዳይ ይህ መርህ አይሠራም፡፡ በተፈጥሮ ሀብት መጠቀም የሉዓላዊነት መብት (Soverign Right) ነው፡፡ በሉዓላዊነት የመጠቀም መብት እስካለው ድረስ በመብቱ መጠቀም ወይም አለመጠቀም የሚያሳድረው ሕጋዊ ተፅዕኖ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከህዳሴው ግንባታ መጀመር ጋር ተያይዞ ግብፅ የመጠቀም መብቷ እንዳይቀንስ ተከራክራለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀድሞ የነበረ ቅድሚያ የመጠቀም ታሪካዊ መብቷ እንዳይነካ ትከራከራለች፡፡ ሁለቱ የመከራከሪያ ሐሳቦች አይጋጩም?
ዶ/ር ደረጀ፡- ግብፆች ሊከላከሉት የማይችሉትን የዲፕሎማሲ አካሄድ ያንቀሳቀሳሉ፡፡ በማንኛውም ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብት አጠቃቀም አንፃር ኢፍትሐዊነቱ እንደ ዓባይና ናይል ተፋሰስ የገጠጠ ሁኔታ የለም፡፡ ምንጭ የሆኑት አገሮች በሙሉ አንድም ጠብታ ሳይተርፍላቸው፣ ለተፋሰሱ ምንም አስዋጽኦ የሌላቸው ወይም እዚህ ግባ የማይባል አስተዋጽኦ ያላቸው አገሮች ጠቅላላውን ፍሰት ተካፍለው ቁጭ ብለዋል፡፡ ይህ ያገጠጠ ኢፍትሐዊ የውኃ ሀብት አጠቃቀም በሌሎች አገሮች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ውስጥ አይታይም፡፡ ግብፅና ሱዳን ይኼንን ለመከላከል ነው የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ እየጣሩ ያሉት፡፡ አስፈላጊ ሲመስላቸው ሕጋዊ ክርክሮችን ያነሳሉ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የትብብርና የወዳጅነትን ትርክት በመተረክ ጊዜ የመግዛትና ፋይዳ ያለው የውኃ ሀብት አጠቃቀምና ልማት በራስጌ ተፋሰስ አገሮች ውስጥ እንዳይከናወን ሁሉንም ዓይነት ጥረቶች ያደርጋሉ፡፡ ግብፅ በዓባይ አጠቃቀም ላይ በሕግም፣ በፍትሕና ርትዕም ሊደገፍ የማይችል አጠቃቀምን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን እንደምትጠቀም ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በማንኛውም ሁኔታ ግጭት ውስጥ በምትገባበት ጊዜ፣ ግብፅ ሁልጊዜ በሌላኛ ወገን በኩል ትወግናለች፡፡ ምክንያቱም የዚህን የውኃ ሀብት አጠቃቀም ሊገዳደር የሚችልና ትርጉም ያለው ተጠቃሚነት መብትን አንስቶ፣ አሁን ያለውን የአጠቃቀም ሥርዓት በመሠረታዊነት ሊለውጥ የሚችል ሁኔታ ማምጣት የምትችል አገር ኢትዮጵያ መሆኗን ስለምታውቅ ነው፡፡ ምክንያቱም 85 በመቶ በላይ የሚሆነው የውኃው አመንጪ ኢትዮጵያ መሆኗን ስለምታውቅም ነው፡፡ የግብፅን አቋም በዘመን ማዕቀፍ ውስጥ ብንመለከተው መጀመርያ የነበረው ግልጽ የሆነ የጦርትና ማስፈራሪያ ዛቻ ነበር፡፡ ‹‹አንዲት ጠብታ ውኃ ቢነካ እንወራለን፣ እንዋጋለንለ›› የሚል አቋም ነበር፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ግን ዓለም አቀፍ ሕግ እየተሻሻለ፣ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም የሚገዛው ዓለም አቀፍ ሕግ እየዳበረና ሰፊ ተቀባይነትን እያገኘ በመምጣቱ፣ እንዲሁም በአገሮች ግንኙነት መካከል ኃይል መጠቀምና ዛቻ ከተባሩት መንግሥታት ቻርተር ጋር የሚጋጭ በመሆኑ፣ በቀላሉ በማስፈራራትና በዛቻ የሚሆን ነገር እንደ ሌላ እየታወቀ ሄደ፡፡ አገሮች በሰላምና በሕግ አግባብ ልዩነቶቻቸውን የመፍታት ግዴታ አለባቸው፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ወይም ማንኛውም ብሔራዊ ጥቅም በኃይል ማራመድ የሚከለክል የዓለም አቀፍ ሕግ ሥርዓት ውስጥ ነን፡፡ ስለዚህ ግብፅ ቀደም ብላ እንደምታስበው ማድረግ የማትችልበት ጊዜ ውስጥ ነች፡፡ ዛቻና ማስፈራራት የአገልግሎት ዘመኑን ጨርሷል፡፡ እየዳበረና ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው ዓለም አቀፍ ሕግ ጋር በተቃውሞ መቆም ብልጥነት አይደለም፡፡ ግብፆችም ብልጦች በመሆናቸው ዛቻና ማስፈራራቱን ትተው የቋንቋ ለውጥ አደረጉ፡፡ ‹‹መጠቀማቸውን አንከለክልም፡፡ ኢትዮጵያ መጠቀም አለባት፡፡ አጠቃቀሟ ግን እጅግ ቢበዛ ኃይል ከማመንጨት የማይዘልና የውኃውን ፍሰት ፋይዳ ባለው መልኩ የማይቀንስ መሆን አለበት፤›› በማለት፣ ያንን ‹‹ታሪካዊ ድርሻችን ነው›› የሚሉትን ቋንቋ ቀይረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1999 ጀምሮ በነበረው Nile Basin Initiative ውስጥ የተጫወቱት ሚና ይኼው ነው፡፡ ድርድሩ በተካሄደባቸው ዓመታት ሁሉ፣ የወዳጅነት፣ የጋራ ተጠቃሚነት፣ የጋራ ልማት ሐሳብ ተቀብለው ነበር፡፡ ‹‹ፍትሐዊና ዘላቂ በሆነ አጠቃቀም የጋራ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማትን ማሳካት›› የሚለውን ራዕይ ተቀብለው በድርድሩ ሒደት ከአሥር ዓመታት በላይ ስለትብብር እያወሩ ከቆዩ በኋላ፣ ስምምነቱ በሚፈረምበት 11ኛው ሰዓት ላይ ‹‹አንፈርምም›› ብለው ወጥተዋል፡፡ የሚገርመው ነገር ‹‹አንፈርምም›› ብለው ከወጡ በኋላ ወደ ቀድሞ ሐሳባቸው መመለሳቸው ነው፡፡ በውኃ አጠቃቀም ሆነ በሚሊቴሪና ፖለቲካ፣ እንዲሁም በዲፕሎማሲ አቋሟ ግብፅ የተፋሰሱ ኃያል አገር (Hegemony) ልትባል ትችላለች፡፡ ለሌሎች ተገዳዳሪ ኃይሎች የማይመቻቸውን ኢፍትሐዊ እውነታ የሚያስቀጥሉባቸው ብዙ መንገዶች አሏቸው፡፡ መብታቸውን ሊጠይቁ የሚችሉ አገሮችን መብት በድርድርና በልዩ ልዩ ሁኔታዎች አናገኛለን በሚል ተስፋ አስሮ ማቆየት ነው፡፡ ይህ በእርግጥ ጊዜ ይገዛል፡፡ በዚህ መካከል ትልልቅ ፕሮጀክቶቻቸውን ሠርተው ጨርሰዋል፡፡ ለምሳሌ ፒስ ካናል ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው፡፡ ድርድሩ በአንድም በሌላ መንገድ ተጠናቆ መፈረሚያው ጊዜ ሲደርስ ‹‹ከሒደቱ ወጥቻለሁ›› ሲሉ ዝም ብለው አልወጡም፡፡ አጠቃላይ የድርድሩን ሒደት ከፍትሕ ማዕቀፍ ሊያስወጣ የሚችል፣ ወደፊትም በቀላሉ ከስምምነት ለመውጣት የሚያስችል ጽንሰ ሐሳብ እንዲገባ አድርገው ነው የወጡት፡ ይህም ‹‹የውኃ ደኅንነት መርህ›› የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ (Water security) ነው፡፡ በማዕቀፉ ውስጥ በማስገባትና ለዘለቄታው ችግሩ እንዳፈታ የሚያደርግ እንቅፋት ካስገቡ በኋላ ነው ከድርድሩ የወጡት፡፡
ሪፖርተር፡- የውኃ ደኅንነት መርህ እንዴት ነው ችግሩ እንዳይፈታ ሊያደርግ የሚችለው?
ዶ/ር ደረጀ፡- ይህ የውኃ ደኅንነት መርህ የሚባለው ለስምምነቱ መፋረስ ምክንያት የሆነ ነው፡፡ በቂና አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር ነው ጽንሰ ሐሳቡ ወደ በCooperative FrameWork Agreement ውስጥ እንዲገባ የተደረገው፡፡
ሪፖርተር፡- ከተባበሩት መንግሥታት ኮንቬንሽን ጋር ይጣረሳል ማለት ነው?
ዶ/ር ደረጀ፡- በተባበሩት መንግሥታት ኮንቬንሽን ውስጥ የውኃ ደኅንነት መርህ (Water Security Principle) የሚባል ጽንሰ ሐሳብ ኖሮ አያውቅም፤ የለምም፡፡ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሕግ ውስጥም የሚታወቅ ጽንሰ ሐሳብ አይደለም፡፡ ገና እየወጣ ያለ መርህ ነው፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ሴኪዩሪቲ ስተዲስ በሚባለው ዲሲፕሊን ውስጥ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ቀድሞ የነበረውና ለዓመታት የሚታወቀው የአገሮች የደኅንነት ችግርና በአገሮች መካከል የሚነሳ ሪቫይለሪ ሞገደኛነት ነው፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ ግን የራስ ችግር መሆኑ አብቅቶ፣ችግሮቹ ሌሎች ሆነዋል ፡፡ ስለዚህ የደኅንነት ችግር የሚለው ጽንሰ ሐሳብ እየሰፋ መጥቷል፡፡ ስቴት ሴንትሪክ የነበረው የደኅንነት ሥጋት አረዳድ፤ ከችግሮቹ መብዛትና የችግሮቹ ምንጭ ከመቀየሩ የተነሳ መሠረታዊ የደኅንት ችግር ሆኗል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት (Non State Actors) እየተደራጁ፣ ነገር ግን ከፍተኛ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የውኃ ደኅንነት የሚለው ሐሳብ መጥቷል፡፡ በእርግጥ ከውኃ ሀብት አጠቃቀም፣ መሠረታዊ የደኅንነት ጥያቄዎችን መመርመር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ቢኖረውና የአገራችን መብትና ግዴታዎች በሚወስነው ዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም አንፃር ይህ መርህ የሚታወቅ መርህ አይደለም፡፡ ስለዚህ ግብፆች ያስገቡት የውኃ አጠቃቀሙን በምንም ቢሆን በሕግና በፍትሕ እንዲበየን ስለማይፈልጉ ነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም የሕግና የፍትሕ ብያኔ 85 በመቶ የውኃ ሀብቱን የምታመነጭ አገር ከጨዋታ ውጪ አድርጎ በዜሮ ድርሻ ለሁለት አገሮች ብቻ የሚያካፍልበት ሁኔታ የለም፡፡ስለዚህ በግብፅና ሱዳን እውነታ ውስጥ ማንኛውንም የውኃ ሀብት አጠቃቀም በሕግና ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ የማስገባት ሒደት የለም፡፡ ያልተገባ ጥቅም ይዘው እየተጠቀሙ ስለሆነ በማንኛውም ፍትሐዊና እውነተኛ አመለካከት፣ እንደገና የሚደረግ ውኃ ክፍፍል ተጎጂ ያደርገናል ብለው ያስባሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የውኃ ደኅንነት መርህ እንዲገባ ያደረጉት፡፡ ጽንሰ ሐሳቡ የገባበትም መንገድ ቅርፅም ሆነ ይዘት የሌለው፣ ማንኛውም አገር ለፈለገው መንገድ ትርጉም ሊሰጠው በሚችልበት መልኩ ሆኖ የገባ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ የማይገባቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚጠቀሙበት መሣሪያ (Tool) ነው፡፡ ዓላማቸው የሕግና የፍትሕ ጥያቄ እንዳይነሳ አጀንዳዎችን ሚስጥራዊ ማድረግ ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ፍትሐዊና ርዕታዊ የሆነውን የውኃ ሀብት አጠቃቀም፣ የደኅንነት ጥያቄ ለማድረግም ነው፡፡ የፍትሕና የርትዕ መሠረት ያለው የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም ጉዳይ ቀርቶ የደኅንነትና የህልውና ጥያቄ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይህ መርህ ገባ ማለት ደግሞ ማዕቀፉ በዘላቂነት በቀላሉ የማይሻገረው እንቅፋት አለበት ማለት ነው፡፡ ያም ሳይበቃቸው የእኛን የብቸኝነት የባለቤትነት መብት ዕወቁ የሚል ማሻሻ አቅርበው ነው እንዲፈርስ ያደረጉት፡፡ ሌሎቹን የራስጌ ተፋሰስ አገሮን ግዴታ ውስጥ የማስገባትና በሕግ ማሰር ሐሳብ በማቅረባቸው ሒደቱ ተፋልሶ ነው ከሲኤፍኤ (CFA) የወጡት፡፡ በትብብር ማዕቀፉ ላይ ዘላቂ ሳንካ (እንቅፋት) ተክለው ነው የወጡት፡፡
ሪፖርተር፡- በተጀመረው ድርድር ላይ ግፊቶች ሲመጡ ውይይቶችን ለማድረግ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበልዎት የውይይት ግብዣ ላይ አልተገኙም፡፡ ያልተገኙበት ምክንያት ምን ነበር?
ዶ/ር ደረጀ፡- በመጀመርያውና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተደረገው ውይይት ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በጠራው ስብሰባ ላይ ግን በግል ችግር ምክንያት መገኘት አልቻልኩም፡፡
ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ አሁን የተጀመረውን ድርድር እንዴት ይመለከቱታል? ድርድሩ የሚካሄደው ሦስቱ አገሮች በተፈራረሙበት ‹‹ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ›› ውስጥ ሆኖ እየተካሄደ ነው፡፡ እርስዎ ደግሞ በዚህ መርህ ላይ ጥያቄ አለዎት፡፡ ቢያብራሩልን?
ዶ/ር ደረጀ፡- የዓባይ ውኃ አጠቃቀምን ማየት ያለብን በዓውድ ነው፡፡ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ በማይታይ መልኩ ያገጠጠ ኢፍትሐዊነት ያለበት ነው፡፡ በፊት የነበረው የውይይት ሒደት ሁሉም የዓባይ ተፋሰስ አገሮች በፍትሐዊነትና በርትዕ የሚጠቀሙበትን መንገድ ለመፍጠር ነበር፡፡ ውጥረቱ ከ1950 ዓ.ም. ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በወሳኝ መልኩ ይፋ ያደረገው ወይም እንዲታይ የሆነው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነት (Cooperative FrameWork Agreement) ነው፡፡ ይህ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (Cooperative Frame Work Agreement) ሳይፈረም የቆየው ከአሥር ዓመታት በላይ ሲሆን፤ የጸደቀው ከፍተኛ ክርክር ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ የዓባይን ውኃ አጠቃቀም በሚመለከት ለኢትዮጵያ ቀዳሚ ብሔራዊ አጀንዳ የመሆኑን ያህል ለሌሎቹ ተፋሰስ አገሮች ያንን ያህል አንገብጋቢም አይደለም፡፡ ሌሎች አማራጮች አሏቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ሥራ መሥራት ነበረባት፡፡ የተፋሰሱ አገሮች አጀንዳው ወሳኝ መሆኑን አምነውና ተቀብለውት ፍትሐዊ የሆነ አጠቃቀምን የሚወስን የሕግና የውኃ አጠባበቅ ማዕቀፍ እንዲሠራ ማድረግ ትልቅ ጥረት የጠየቀ ሥራም ሠርታለች፡፡ ሒደቱ እንዲሳካም ትልቅ የፋይናንስ ፍሰትም አስገኝቶ ነበር፡፡ ብዙ ለጋሽ አገሮች ተሳትፈውበት በብዙ ጥረት የተካሄደ አጀንዳ ነበር፡፡ ነገር ግን ግብፆች ‹‹የውኃ ደኅንነት ፕሪንሲፕል›› የሚል ጽንሰ ሐሳብ በስምምነቱ ውስጥ እንዲገባ በሚል፣ አጠቃላይ ሒደቱን ለዘለቄታው የሚያሰናክል መርህ አስገቡ፡፡ ያም ቢሆን፣ ‹‹ወደፊት በሒደት እንፈታዋለን፣ የተፋሰሱን ጉዳይ የሚፈታውን ድርጀት አናቋቁም፣ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ሁሉንም የተፋሰሱ አገሮች ጥያቄዎችና ሥጋቶች የምናስተናግድበት አመቺ ሁኔታ (ፕላት ፎርም) እናዘጋጅ፤›› ሲባሉ፤ ግብፅና ሱዳን ከማዕቀፉ ወጡ፡፡ ሳይፈርሙም ቀሩ፡፡ ነገር ግን በነበረው የውይይት አጀንዳ ላይ ድል ማስመዝገብ የተቻለበት፣ በተለይ ግብፅ ከመቼውም በላይ እጅግ በጣም በማይመች ሁኔታ ውስጥ እንድትቆይ ተደረገበት፣ በተደራዳሪነት ስትሳተፍበት የነበረውን የሕግና የውኃ አጠቃቀም መርህ፣ በዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሕግ መርህ ጋር የተጣጣመ ድርድር (መድረክ) ረግጠው ወጥተው፣ ‹‹ሕግን መሠረት ያደረገ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀምን አንቀበልም፤›› ያሉ አመፀኛ አገሮች ሆነው የቆሙበትና ከዲፕሎማቲክ ግንኙነትም አንፃር ራቁታቸውን የቀሩበት ሁኔታ መፈጠሩም ትልቅ ድል ነበር፡፡ በእርግጥ አገሮቹ የግርጌ ተፋሰስ አገሮች እንደመሆናቸው፣ የጂኦግራፊ አቀማመጣቸውም ጉዳት (Geographic DisAdvantage) አለባቸው፡፡ ስለዚህ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ሌሎቹ የተፋሰስ አገሮች ያንን ዶክመንት ወደሚሠራ የሕግ ማዕቀፍ ቀይረውት በጋራ ማልማት፣ በጋራ ፕላን ማድረግ ጀምረው ቢሆን ኖሮ፣ ሳይወዱ በግዳቸው ወደ ሕግ ማዕቀፍ በመግባት ለፍትሐዊና ሁሉን ያማከለ የውኃ አጠቃቀም መርህ መገዛታቸው አይቀርም ነበር፡፡ ግብፅና ሱዳን በእንቢተኝነት ተነጥለው በቀሩበት ሁኔታ፣ የተጀመረውን የማዕቀፍ ሰነድ ወደ ፍፃሜው እንዲደርስ ማድረግ እ.ኤ.አ. በ2015 ‹ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕል› የሚል ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ሌላ የጎንዮሽ ስምምነት ተፈራርሙ፡፡ መዘንጋት የሌለበት ይህ የጎንዮሽ ስምምነት የተፈረመው፣ ከአሥር ዓመታት በላይ የተከደመበትን የሕግ ማዕቀፍ አሻፈረን ብለው ከወጡ አገሮች ጋር ነው፡፡ ለላይኞቹ የተፋሰስ አገሮች፣ በተለይም የውኃው ከፍተኛ አመንጪ ለሆነችው ኢትዮጵያ ጥቂት ውኃ ለመፍቀድ ዝግጁ ካልሆኑ አገሮች ጋር ነው የጎንዮሹ ድርድር የተካሄደው፡፡ የውኃ ትብብር ማዕቀፉ ስምምነት ትልቅ ሥራ የጠየቀ ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ አንገብጋቢ የሆነውን ያህል ለሌሎቹም የተፋሰስ አገሮች ያን ያህል አንገብጋቢ አይደለም፡፡ ለዚያም ነው ከግብፅ ጋር የዲፕሎማሲም ይሁን ሌላ እሰጥ እገባ ውስጥ የሚገቡበት ምክንያት የለም፡፡ ነገር ግን ያንን ሁሉ ድርድር ሲያደርጉና ሲተባበሩ ቆይተው፣ ከዚያም በማለፍ ትብብር ማዕቀፉን ፈርመው የነበረበትን አጀንዳ ትታ ከእንቢተኞቹ ጋር ድርድር ማድረጓ በጣም ትልቅ ስትራቴጂያዊ ስህተት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስህተት የሠራችው በሁለት መልኩ ነው፡፡ አንደኛው ሕግና ሥርዓትን አክብረው ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን፣ ‹‹አንቀበልም፤›› ብለው ከወጡ አመፀኞች ጋር ለድርድር መቀመጧ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሌሎቹ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ያለውን የተለመደና ስታንዳርድ ያለውን አሠራር በሚጥስ መልኩ ከእንቢተኞች ጋር በራሷ ፕሮጀክት መደራደሯ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የተፋሰስ አገሮች ተሞክሮ ብናይ ኮሚሽኖች ይቋቋማሉ፡፡ አብዛኞቹ ኤክስፐርቶች ናቸው፡፡ ፖለቲከኞች በጣም በጥቂት ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው ተሳትፎ የሚኖራቸው፡፡ የተናጠል ፕሮጀክት ድርድር የሚባል ነገር ስለሌለ፤ እያንዳንዱ ጉዳይ (Issue) በኮሚሽኑ እየተጠና ይቀርባል፡፡ ስለዚህ ትክክለኛውንና በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ ምንም ዓይነት የውኃ መብትና የውኃ ሀብት ጥበቃ ጉዳዮች የሚታይበትን መድረክ ትቶ፤ በነጠላ ፕሮጀክት የመደራደርና ውል መቋጠርን አደገኛ መንገድ የከፈተ ነው፡፡ የፍትሐዊ አጠቃቀምን ሕግና መርህን መሠረት ባደረገ ስምምነት አንገዛም ብለው በማመፅና በውጪ ብቻቸውን ከቆሙ ኃይሎች ጋር የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ አደገኛና ዘለቄታዊ ውጤት (Consequence) ያለው ስትራቴጂያዊ ስህተት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ግብፅ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት በሕግ ዕውቅና መስጠቷ በ‹‹Declaration of Principles›› ትልቅ ድል እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ደረጀ፡- ይህ ተራ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ሲጀመር ራዕዩ የነበረው ፍትሐዊ፣ ዘለቄታነት ያለው የውኃ አጠቃቀምን ዕውን በማድረግ የአገሪቱን ኢኮኖሚዊና ማኅበራዊ ብልፅግና ዕውን ማድረግ ነው፡፡ Property Frame work Agreement ብትመለከተው Equitable and Reasonable Utiliization የሚለውን Recognize ያደረገ ነው፡፡ በእሱም አልተጣሉም ነበር፡፡ የውሃ ደኅንነት መርህ የሚለውን ሲያስገቡ ነው ፀብ የመጣው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ያንን ሲሉ አልሰማንም፣ አላየንም ለማለት ነው፤ ወይም ያንን ለማዳን ‹‹Salvage›› ነው፡፡ እኔ በሕጋዊ መብቴ ለመጠቀም የማንም ቡራኬ (Blessing) አያስፈልገኝም፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግ የተረጋገጠ መርህ ነው፡፡ ግብፅ ብታውቀውም ወይም ባታውቀውም ምንም የሚቀንስ ወይም የሚጨምር ነገር የለም፡፡ ዝም ብሎ ኪሳራ እንዳልሆነ ለመናገር የሚደረግ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ነው፡፡ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱም፤ ከፍተኛ ጉዳት አለማድረስ፣ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም የሚሉትን፤ የዓለም አቀፍ ሕጎችና መርሆዎች ያካተተ ነው፡፡ ለመፍረስ ምክንያት የሆነው ግብፆች የውኃ ደኅንነት መርህ የሚል ጽንሰ ሐሳብ በማቅረባቸውና ለዚያ የተሰጠው ትርጉም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከ‹‹ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪነስፕልስ›› ኢትዮጵያ ምንም የምታገኘው ጥቅም የለም እያሉ ነው?
ዶ/ር ደረጀ፡- ጥቅም ማግኘት አለማግኘት ሳይሆን የተከፈተው የአደጋ መንገድ ነው፡፡ በደንብ መመልከት ቢቻል በትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ውስጥ ያሉትን ዓለም አቀፍ መርሆዎች የሚያጣምም ነገር አለው፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዓላማ ኃይል ማመንጨት ነው ይላል፡፡ በውል የተሠራ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ይህ ማለት ግድቡን ከኃይል ማመንጫ ውጪ አንጠቀምም ማለት ነው፡፡በአገር ደረጃ በሚደረግ ፕሮጀክት ላይ ፍትሐዊ በውኃ የመጠቀም መብትን ተቃውሞና አፈንግጦ ከወጣ ፓርቲ ጋር ‹‹ግድቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ብቻ ነው የምጠቀመው፣ የማመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይልም ቅድሚያ የመግዛት መብት አላችሁ፤›› ብሎ ስምምነት ውስጥ መግባት ተገቢ አይደለም፡፡ ከስምምነት ዶክመንቱ ውስጥ ‹‹Diclaration of Principle›› በጎ ነገር ለማውጣት መሞከር ቀልድ ነው፡፡ ሌላ ምክንያት መኖር አለበት እንጂ ይህ በፍፁም ሊሆን የማይችል ስምምነት ነው፡፡ ረዥም ሒደት የተደረገበትን ድርድር የሚያፋልስ፣ ለኢትዮጵያ አንዳች ፋይዳ የሌለው፣ ነገር ግን በርካታ ችግሮችን የፈጠረ ስምምነት ነው፡፡ በቀላሉ ማስቆም ይቻል ነበር፡፡ አሥር ዓመታት የተደከመበት የሕግ ማዕቀፍ አለ፡፡ በዚያ ማዕቀፍ ማንኛውም የተፋሰስ አገሮች ጥያቄና ሥጋት ይስተናገዳል፡፡ መጀመርያ መሆን ያለበት ‹‹ኑ ግቡ›› ነው፡፡ በአመፅ ከዳር ቆሞ ‹‹ኑ እንደራደር›› ማለት አይቻልም፡፡ የ2015 ዓ.ም. ስምምነት ‹‹Diclaration of Principles›› ባይከፈት ኖሮ፣ የግብፅ ስትራቴጂክ ወዳጅ የሆኑት አሜሪካኖች እንድንደራደር ግፊት ማድረግ አይችሉም ነበር፡፡ ወደ ትብብር ማዕቀፉ ግቡና (Any Quations Under The Sun) መደራደር እንችላለን ማለት እንችል ነበር፡፡ ‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል›› እንዲሉ የ2015 ዓ.ም. መንገድ ተቀደደ፡፡ በቀጥታ ወደማይቀረው (Inevitable) ድርድር ገባን፡፡ ስምምነት ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እንደ አቅጣጫ ግን የተደከመበትን፣ ብዙ ዓመታት ያስቆጠረውንና ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር ስምምነት ያለውን ትብብርና የሕግ ማዕቀፍ ‹‹አንቀበልም›› ብለው አፈንግጠው ከወጡ አገሮች ጋር የተደረገ ውል በመሆኑ፣ በየትኛውም የድንበር ተሻጋሪ ወንዝ አጠቃቀም ታሪክ ውስጥ፣ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከሕግ ማዕቀፍ ውጪ የነጠላ ፕሮጀክት ድርድርና ስምምነት አቅጣጫ የከፈተ ድርድር ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ አሥር ፕሮጀክት ቢኖር አሥር ድርድር ሊኖርና አሥር ውል ልንቋጥር ነው ማለት ነው፡፡ ይህ የስህተት መንገድ (Wrong Truck) ነው፡፡ መሠረታዊ የሆነና ስትራቴጂካዊ ስህተት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምንም ይሁን ምንም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር እየተደረገ ያለው ሦስቱ አገሮች በተፈራረሙበት በ2015 ዓ.ም. ስምምነት መርህ (Declaration of Principles) መሠረት ነው፡፡ ምን ዓይነት ውጤት ላይ ይደርሳል ይላሉ?
ዶ/ር ደረጀ፡- ይኼ ይሆናል ወይም አይሆንም ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ አጠቃላይ ሒደቱ ካለበት ዓውድ አኳያ ግን እንጠቀማለን ማለት አይቻልም፡፡ በእኔ እምነት በብሔራዊ ጥቅማችን ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳትን መጠን እንዲቀንስ ማድረግ ነው፡፡ በእኔ ግምገማ ወደዚህ ሒደት መግባታችን የጉዳትን መንገድ እንድንከተል አድርጎናል፡፡ ስትራቴጂክ ስህተት ነው ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡ ጉዳቱን መቀነስ ይቻል እንደሆነ እንጂ መንገዱ የጉዳት መንገድ ነው፡፡ በማያዋጣ መንገድ ላይ ነን፡፡ ጥያቄው ‹‹የሚደርሰውን ጉዳት መያዝ ወይም መቀነስ ይቻላል ወይ?›› የሚለው መሆን አለበት፡፡ ለማንኛውም ብሔራዊ ኩራታችን ይሆናል ያልነው ግድብ የድርድር አጀንዳ ሆኗል፡፡ ግብፆች አንዲት ሳንቲም ሳይከፍሉበት በብሔራዊ ኩራታችን ላይ ይደራደራሉ፡፡ ኢትዮጵያ የመጠቀም መብት እንዳላት እንኳን ለማወቅ ፈቃደኛ ካልሆኑ አገሮች ጋር መደራደራችን በጣም ያሳዝናል፡፡ በራሱ ጉዳትም ነው፡፡ ከእነዚህ ጋር ድርድር ላይ መቀመጣችን አሳፋሪም ነው፡፡ ሌላው በድርድሩ ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው የተደረጉት አሜሪካና ዓለም ባንክ መሆናቸው በግልጽ የሚታይ ችግር ነው፡፡ ከዚህ ሒደት ኢትዮጵያ ትጠቀማለች ብሎ ማውራት ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ያለችው በምትጎዳበት መንገድ ላይ ነው፡፡ መሠረታዊው ጥያቄ ኢትዮጵያ ትጠቀማለች ወይ ብቻ ሳይሆን፣ ምን ያህል ጉዳት መቀነስ እንችላለን? የሚለው ነው፡፡ ባለን ኃይልና ሀብት መረባረብ ያለብን የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከልና ከዚህ ስህተት መንገድ ለመውጣት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን አጠናቆ ለአፍሪካ ኅብረት ለማቅረብ የቀረው የኬንያ ፊርማ ብቻ ነው፡፡ በኬንያ ላይ ግፊት ፈጥሮ ማስፈረም ከተቻለ የ2015 ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልን ቀሪ ማድረግ ይቻላል?
ዶ/ር ደረጀ፡- ከዚህ ስምምነት በሆነ መንገድ መወጣት አለበት፡፡ የተጀመረ ሒደት ነው፡፡ የዓለም ባንክ ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡ አሁን በተጨባጭ ካለንበት የኢኮኖሚ ሁኔታና እነሱም እያቀረቡት ካለው ስጦታ አንፃር በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ እንደ እኔ ግን መቼም ቢሆን ከችግር ወጥተን ስለማናውቅ፣ ለመጀመርያ ጊዜ የገጠመን ችግር ተደርጎ ዘላቂ ጥቅማችንን አሳልፈን መስጠት የለብንም፡፡ ታዳጊ አገር ምንጊዜም የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ውስጥ ናቸው፡፡ ምንም ገንዘብ በማናገኝበትና ለዕለት ጉርስ እንኳን ያጣንበትንና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ላይ የተደገፍንበት ወቅትንም ማለፍ ችለናል፡፡ ጥቅማችንን በዘላቂነት ከሚጎዳን ነገር ተከላክለን ለማለፍ የማይቻልበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናውና ተመራጭ ነገር ከዚህ ከተሳሳተ ጎዳና ፈፅሞ መውጣት ነው፡፡ ከዚህ የጥፋትና የጎን በር ወጥተን በዋናውና በትክክለኛው በርና ሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ መሆን አለብን፡፡ ማንኛውም ጥያቄ መሆን ያለበት በዚያ ውስጥ ነው፡፡ ብሔራዊ ግባችን ይህ መሆን አለበት፡፡ ያ የማይሆን ከሆነ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲቀንስ ማድረግ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ የሚያነሷቸው፤ የህዳሴው ግድብ የረዥም ጊዜ አገልግሎት፣ የዓባይን የተፈጥሮ ፍሰትና ሌሎች መከራከሪያ ነጥቦችን የሚያነሱበት ሁኔታም አለ?
ዶ/ር ደረጀ፡- ዞሮ ዞሮ የግብፆች ዓላማ፣ የውኃውን ብቸኛ ተጠቃሚነት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ማረጋገጥ ነው፡፡ በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ ስንት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሌትር ውኃ እንደሚለቀቅ ጭምር የሒሳብ ሥሌት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ያለፍትሕና ርትዕ ሲጠቀሙ የቆዩትን ውኃ በመያዝ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት እንዳይዘል ማድረግ ነው፡፡ የመጡበት መንገድ ይለይ እንጂ የመጨረሻ ግባቸው (Ultimate Objective) የራሳቸውን ሐሳብና ጥያቄ ማስፈጸም ነው፡፡ የፍሰቱ መጠን “ድርቅ ከሆነ፣ በጣም ድርቅ ከሆነ” በማለት በሁኔታ ውስጥ ለማድረግ የሚፈልጉት ብቸኛ ተጠቃሚነታቸው እንዳይነካባቸው ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ብቸኛ የሆነው ብሔራዊ ፕሮጀክታችን የጋራ አጀንዳ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ይኼን ያህል ይለቀቅ፣ ይኼንን ያህል ይሞላ፤›› ለማለት ምንም ዓይነት መብት የላቸውም፡፡ ሱዳኖችም ሆኑ ግብፆች የራሳቸውን ግድብ በቅርቡ ሲገነቡ ማንንም አላማከሩም፡፡ የእኛ ፕሮጀክት ግን በእነሱ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ መደራደሪያ ሒደት ውስጥ መግባታችን በጣም አሳዛኝ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከድርድሩ ብትወጣ ሊፈጠር የሚችለው ውጤት ምን ሊሆን ይችላል? ወደ ጦርነት መግባት? ወይስ ወደ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት( International Albitration tribunal) መሄድ?
ዶ/ር ደረጀ፡- በ2010 ዓ.ም. ድርድሩ አብቅቶ ለስምምነት ፊርማ ሲከፈትና አገሮች ሲፈርሙ ግብፆችም ሆኑ ሱዳኖች በጣም ፎክረው ነበር፡፡ ግን ምንም ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ያ ሒደት ተገፍቶ ቢሆን ኖሮ የግርጌ ተፋሰስ አገሮች እንደመሆናቸው ምንም ሊፈጥሩ ስለማይችሉ ሳይወዱ በግድ ወደ ሒደቱ መግባታቸው አይቀርም ነበር፡፡ አሁንም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከዚህ ሒደት ወጥተን ወደ ማዕቀፉ እንዲገቡ ብናደርጋቸው ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር የለም፡፡ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ላይ ማድረግ የሚፈልጉትን ሁሉ ያላደረጉት ነገር የለም፡፡ ተፅዕኖ የለውም እያልኩ አይደለም፡፡ አሁን በአደራዳሪነት የገባችው አሜሪካ ከመሆኗ አንፃር ከፍተኛ የሆነ ጫና ማሳደር ይችላሉ፡፡ ካለንበት የኢኮኖሚ ሁኔታ አንፃር የሚሰጡትን ብድሮችንና ስጦታዎች በመያዝ ተፅዕኖ መፍጠር ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ወቅታዊ ችግሮችና ግፊቶች ብለን ዘላቂ የሆነውን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈን መስጠት የለብንም፡፡ ከዚህ በፊትም አስከፊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን ተቋቁመን ስላሳለፍን አሁንም ያለውን ሁኔታ ተቋቁመን ማለፍ አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ሒደት ብትወጣ የግብፅ አቋም ምን ሊሆን ይችላል? ለሚለው ጥያቄ፤ በዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሕግ መሠረት ሁሉም የተፋሰስ አገሮች የሚያነሱትን “ፍትሐዊ የውኃ መጠቀም መብታችን ይረጋገጥልን” የሚል መሠረታዊ፤ ፍትሀዊና ሕጋዊ ጥያቄ ነው ኢትዮጵያም ያነሳችው ጥያቄ፡፡ ስለዚህ ጥያቄው መሆን ያለበት “ጥያቄውን የማይቀበሉበት ምክንያት ምንድነው?” የሚለው ነው እንጂ፤ ተጠያቂ መሆን ያለባት ኢትዮጵያ አይደለችም፡፡ መባል ያለበት፣ ‹‹የትብብር ማዕቀፍ አለ፡፡ ከአሥር ዓመታት በላይ ተደራድራችሁበታል፡፡ መሠረታዊ የሚባሉ ዓለም አቀፍ መርሆዎች ያካተተ ሰነድ ነው፡፡ በዚያ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ግቡና ቁጭ ብላችሁ የፈጀውን ዓመት ያህል ፈጅቶ ይኼንን ውኃ በፍትሐዊነት የምትጠቀሙበትን ፎርሙላ ፈልጉ፤›› ነው መባል ያለበት እንጂ፣ ‹‹የያዝነውን ይዘን ሌሎች በሚያለሙት ውስጥ እጃችንን እያስገባን፣ ‹‹ይኼን ያህል ልቀቅ፣ ይኼንን ያህል ያዝ… ›› የሚሉ አካሎች ሊስተናገዱ አይገባም፡፡ እኔ እንደማስበው ግብፅም ሆነች ሱዳን እንደዚያ ዓይነት ጨዋታ የመጫወት አቅም የላቸውም፡፡ ሱዳን በራሱ ችግር ውስጥ ያለ አገር ነው፡፡ ግብፅም ሺሕ ጊዜ የአሜሪካ ወዳጅና ስትራቴጂካዊ አጋር ብትሆንም፤ ኢትዮጵያን በረዥም እጆችና በውስጥ ችግሮች ከማተራመስ ያለፈ ድንበር ተሻግሮ መጥቶ ይኼንንና ያንን አድርጉ ማለት አትችልም፡፡ የራሷ መሠረታዊ ችግሮች ያነቃት የአምባገነኖች አገር ነች፡፡ በእሱ የሚመጣውን ተፅዕኖ ከፍ አድርጎ ማውራት ተገቢም አይደለም፡፡ ግብፅ በራሱ የውስጥ ችግር የተያዘችና ብዙ ብዙ ችግር ያለባት አገር በመሆኗ ያንን ያህል ከፍ አድርጎና አጋኖ ማቅረብ ከወዲሁ የፖለቲካዊ ኤክስኪዩዝ እንዳይሆን ሥጋት አለኝ፡፡ ችግር የለም እያልኩ ሳይሆን የምንነጋገርበት ጉዳይ ብሔራዊና ዘለቄታዊ የሆነ የአገር ጥቅም በመሆኑ ነው፡፡ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በሚቻለው መንገድ ሁሉ ከዚህ የተሳሳተ አቅጣጫ ወጥቶ ወደ ሕጋዊ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ የሚገባበትን ዕድል እያሰቡ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን አደራዳሪ አሜሪካ መሆኗ ቀላል ባይሆንም፣ በተባለው ጊዜ መስማማት ካልተቻለ ድርድሩ ሊቀር ይችላል፡፡ የድርድሩም ሒደት ያበቃል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት የመሄድ ዕድል የለም ማለት ነው?
ዶ/ር ደረጀ፡- ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ዝም ተብሎ ዘው ተብሎ አይገባም፡፡ አገሮች ጉዳዮቹን በዓለም አቀፍ መድረክ ለመፍታት ፈቃድ መስጠት አለባቸው፡፡ እንድ አገር ውስጥ ፍርድ ቤት ና ሲል መሄድ የለም፡፡ አገሮች መፍቀድ አለባቸው፡፡ ግብፆቹ ግን ለፕሮፓጋንዳ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ይናገራሉ፡፡ ይህ የማይሆንና ዓለም አቀፍ የፍትሕ ሒደቶችን ካለመረዳት ወይም ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ከሚነገር በስተቀር እውነታ የለውም፡፡ በስምምነታቸው ላይ አለመግባባት ከተፈጠረ በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት እንደሚፈቱት ካልተስማሙ በስተቀር፤ ዝም ብሎ ክስ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ማንም ሉዓላዊት አገር ያለ ፈቃዱ ወደ ፍርድ ቤትም ሆነ ሽምግልና አደባባይ መውሰድ አይቻልም፡፡ ይሁን ተብሎ እንኳን በማንኛውም የፍርድ ቤት ሒደት ውስጥ ቢታይ 85 በመቶ የሚሆነውን ውኃ የምታመነጭ አገር አንድ ጠብታ ውኃ ሳትጠቀም፣ ከታች ያሉ የተፋሰሱ አገሮች ውኃውን ለሁለት ተካፍለው የሚጠቀሙበትን ሁኔታ የሚያፀና የፍትሕ መድረክ የለም፡፡ የግልግል ዳኝነትም ይሁን ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚሠሩት በዓለም አቀፍ ሕግ መርህ ነው፡፡ የአይሲጄ (ICJ) ውሳኔ 97 በሀንጋሪና ስሎቫኪያ መካከል የሰጠውን ውሳኔ ብንመለከት፤ በዓለም አቀፍ ሕግ መርህ መሠረት ነው ውሳኔ የሰጠው፡፡ በሌሎችም ተመሳሳይ ነው፡፡ መሄድ ካለብንም ደግሞ የምንሄደው ማንም ጎትቶን ሳይሆን በራሳችን ፍላጎት ነው፡፡ ያገጠጠ ኢፍትሐዊ አጠቃቀም ሁኔታ ሕጋዊ ነው ብሎ ሊበይን የሚችል ፍርድ ቤትም ይሁን ትሪቡናል አይኖርም፡፡ እኛ የያዝነው የሕግና የፍትሕ አቋም ስለሆነ ምንም የሚያስፈራን ነገር የለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ያለ ፈቃዳችንና ስምምነታችን በማንኛውም የፍትሕ አደባባይ እንድንሄድ የሚያስገድደን ሁኔታ የለም፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ድርድሩን አቋርጣ ብትወጣ ግብፆች በህዳሴ ግድቡ ላይ ጥቃት ሊያደርሱ ወይም ጦርነት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚሉ አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ደረጀ፡- ግብፆች ምንም ነገር ከመሞከር አይመለሱም፡፡ ግን ሊሞክሯቸው የሚችሏቸው ነገሮች ያንን ያህል በተግባር የሚታዩ አይሆኑም፡፡ ግድብ የማፍረስና ጦርነት የማንሳት ጉዳይ የማይመስልና የማይሆን ነገር ነው፡፡ መቶ በመቶ አይሆንም ብሎ መዘናጋት ባይቻልም መሠረታዊ የሆኑ ማስፈራሪዎችን መንዛት አንዱ ታክቲክ በመሆኑ፤ ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያን ሰብሮ (Subdue) የግብፅን ጥቅም ማስጠበቅ የማይሞከርና የማይሆን ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ረግጣ ይዛ በኃይል ልታስፈጽም የምትችልበት ዕድል ባዶ ነው፡፡ ሁልጊዜ ሊያስጠቃን የሚችለውና ወደፊትም በብሔራዊ ሀብታችን እንዳንጠቀም የሚያደርገን፤ ውስጣዊ ሰላማችን ሁልጊዜ አደጋ ውስጥ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ መጠቂያዎቻችን በፖለቲካ ሜዳዎቻችን ላይ ያሉ ስንጥቃቶች ናቸው፡፡ እነሱም ሊያደርጉት የሚችሉት ሱዳንን ተሻግረው ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ማንሳት ሳይሆን ውስጣዊ ቁስላችንን በመንካትና እርስ በርስ እንድንነቋቆር በማድረግ ፕሮጀክታችን እንዲዘገይ ማድረግ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በታሰበው ወቅት ተጠናቆ ቢሆን ኖሮ አሁን ያለው ነገር ሁሉ ታሪክ ነበር፡፡ ለዘለቄታው ማሰብ ያለብን ከግብፅ አንፃር በውኃ አጠቃቀም የሚመጣብንን ተፅዕኖ ስናይ ከፍተኛው የተጋላጭነታችን ምንጭ፤ ውስጣዊ ሰላማችንና ፖለቲካዊ አለመረጋጋታችን ነው፡፡ እንደ አገር አብረን መቆም ካልቻልን በቀላሉ ዒላማ ውስጥ እንገባለን፡፡ እንደ አገር በጋራ ልንቆምባቸው የምንችልባቸው ብሔራዊ ጉዳዮች ከሌሉ ነው ትልቁ አደጋ፡፡ ግብፆች በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እያሉ የጀመርነውን የህዳሴ ግድብ፣ እኛም በተመሳሳይ ሁኔታ በፖለቲካ ችግር ውስጥ መሆናችንን ዓይተው ወደ ድርድር እንድንገባ ያደረጉት፤ ያደረግናቸውን መበቀላቸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ እያደረገች ባለው ድርድር ከሕግ፣ ከፖለቲካና ቴክኒክ አንፃር ተደራዳሪዎችን አሠልፋለች፡፡ የተደራዳሪነት አቅማችንን እንዴት ይገመግሙታል?
ዶ/ር ደረጀ፡- የድርድር መድረኩ ለኢትዮጵያ የሚመች መድረክ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በሒደቱ ውስጥ የገቡ አሜሪካና ዓለም ባንክ ሚዛን የሚያሳጡ ናቸው፡፡ ይህንንም ጉዳይ እራሳቸው ተደራዳሪዎቻችን ይህንኑ ግልጽ አድርገዋል፡፡ ሚዛናዊነት ሊኖረው አይችልም፡፡ እንደ እኔ አስተያየት ወደ ማይሆን ስምምነት ውስጥ እንዳንገባ ዋነኛው መከላከያ ነጥብ መሆን ያለበት የውኃ አጠቃቀምን ፍትሐዊነት መልሶ መልሶ ማንሳት ነው፡፡ የ2015ቱ ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪነሲፕልስ ለግብፅና ሱዳን የሕጋዊነት ካባ ስላለበሳቸው፣ ይኼንን ካባ ማውለቅ የሚቻለው ከአሥር ኣመታት በላይ ድርድር አድርገው እንዲፈርሙ ሲጠበቁ እንቢ ብለው ማፈንገጣቸውን በማስረዳት የትብብር ማዕቀፉን ደጋግሞ በማንሳት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የድርድር ስምምነቱ የሚፈረምበት ሰነድ በአሜሪካ እንዲዘጋጅ መደረጉ የሚያመጣው ተፅዕኖ አይኖርም? ከሕግ አንፃርስ ተቀባይነቱ ምን ያህል ነው?
ዶ/ር ደረጀ፡- ትክክል አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሒደት ድርድሩ ብቻ ዓመታትን የሚፈጅበት ሁኔታ አለ፡፡ የ1997 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሕግ፣ ድርድሩ ከ20 ዓመታት በላይ ወስዷል፡፡ ዝም ብሎ ማምጣት አይደለም፡፡ ይህ ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ አደራዳሪ መሆኑ ሚዛናዊ ሊሆን አይችልም ተብሎ የሚገመት አገር፤ መፈራረሚያ ሰነድን ጽፎ እንዲያመጣ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ተዘጋጅቶ በሚመጣው ሰነድን በጥንቃቄ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ አደገኛነቱ ተፅዕኖ ማምጣቱ ብቻ ሳይሆን ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በተቆረጠና አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ ሐደቱ ሊጠናቀቅ የተፈለገበት ሁኔታ አደገኛ ነው፡፡ በዓለም አገሮች ተሞክሮ እንደሚታወቀው፤ ስምምነት የሚያርፍበትን ሰነድ እያንዳንዷ ቃላት፣ ሐረግና ነጥብ የክርክር ሒደት ስለምትሆን፤ ልዩ ትኩረት ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ሙያዊ ዕገዛ ማድረግ አንድ ነገር ቢሆንም፤ አዘጋጅቶ ማቅረብ ግን ፍፁም ጤናማ አካሄድ አይደለም፡፡ እንደዚያም መሆንም የለበትም፡፡