ረቂቁ መዘጋጀቱ ከተሰማ ግዜ ጀምሮ ከፍተኛ ጫጫታና ተቃውሞ ፈጥሮ የነበረው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ አዋጅ፤ ከተቋማት እስከ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረስ ከፍተኛ የሆነ ክርክር ተደርጐበት የነበረ መሆኑ ይታወሳል:: ምክር ቤቱ በረቂቅ ደረጃ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ፤ የአገሪቷን የኢኮኖሚ ሁኔታና የሕዝብ አኗኗር ከግምት ውስጥ ሳያስገባ አስቀምጦት የነበረውን የኤክሳይስ ታክስ ጭማሪ፤ በተወሰነ መልኩ ቅናሽ በማድግ ባለፈው ወር አጽድቆታል:: የፀደቀውን አዋጅ ለማስፈፀም ደንብና መመሪያ ማዘጋጀት ተገቢ በመሆኑ፤ ሰነዶች እስከሚፀድቁና አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እስከሚወጣ ድረስ፤ የመተግበሪያ ጊዜ እንደሚኖር ቢታወቅም፤ ከረቂቁ ጀምሮ የኤክሳይስ ታክሱ እንዳይፀድቅ ሲቃወሙ የነበሩ አምራቾችና አስመጪ ድርጅቶች፤ አዋጁ በፀደቀ ማግስት ታክሱ በተጣለባቸውም ሆነ በማይመለከታቸው መጠቀሚያና መገልገያ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ዋጋ ጨምረዋል:: ምንም እንኳን አምራቾቹ ወይም አስመጪዎቹ የአዋጁ አስፈፃሚ የሆነው የኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር በማሻሻያ አዋጁ ላይ ከጨመረው ተመጣጣኝና ትንሽ ከፍ ያለ ጭማሪ ቢያደርጉም፤ ለሕዝቡ ወይም ለተጠቃሚው የሚያደርሱት (የሚሸጡት) ነጋዴዎች ግን ጭማሪውን ከእጥፍ በላይ በመጨመር ተጠቃሚውን እያማረሩት መሆኑ ታውቋል:: በኤክሳይስ ታክስ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገው የአገር ውስጥ ምርቶችን በማሳደግ፤ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለመደገፍ መሆኑን መንግስት ቢናገርም፤ የአገልግሎት ዘርፉን ችላ እንዳለው ወይም እንተወው የዘርፉ ተዋናዮች እየተናገሩ ነው:: አገልግሎት ሰጪ ከሚባሉት የሆቴል፣ ሬስቶራንትና በችርቻሮ የንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች፤ አምራች ወይም አስመጪ በጅምላ ተቀብለው ለተጠቃሚው የሚያደርሱበት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ፤ ተጠቃሚ እያጡ መሆኑን እየገለፁ ነው:: አንድ 15 ብር የሚሸጥ ቢራ ከ25 ብር በላይ እና አንድ ጃምቦ ድርፍት ከ15 ብር ወደ 25 ብር ከፍ ማለቱን ለምሳሌ ያህል ጠቁመው፤ ሁሉም ነገር በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ በመሆኑ ደንበኛ እያጡ መሆኑን ተናግረዋል:: መንግስት ሁኔታውን አስጠንቶ አፋጣኝ ማሻሻያ ካላደረገ ሠራተኞቻቸውን ከማሰናበት ባለፈ ድርጅታቸውን እስከመዝጋት በሚያደርስ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን እየገለጹ ነው:: የአስፈፃሚው ተቋም የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ግን በነጋዴዎቹ አቤቱታ አይስማሙም:: ይህ ድርጊት በስግብግብ ነጋዴዎች የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው “አዋጁ ወጣ እንጂ መተግበር አልጀመረም” ብለዋል:: የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ ላይ ጭማሪ ተደርጓል በሚል በገበያ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረግም ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል::
በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ብዛት ሥጋት ፈጥሯል
አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ -19) ተጠቂዎች ቁጥር ከመቶ በላይ መድረሱ በተለይ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ አብዛኛዎቹ የቫይረሱ ተጠቂዎች ከአዲስ አበባና ከሶማሌ ክልል...
ተጨማሪ ያንብቡ