በጥር ወር 2ዐ12 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት አካባቢ ከቻይናዋ ውሀን ከተማ የተነሳው ኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ዓለምን እያዳረሰ፤ ስጋቱና ጭንቀቱ በየቀኑ እየጨመረ ነው::
ባለፈው ሳምንት በአሜሪካን ሀገር ዋሽንግተን ሲያትል ከተማ ውስጥ፤ አነድ 5ዐ ዓመት እድሜ ያለው ግለሰብ በቫይረሱ ተጠቅተው መሞታቸው ተረጋግጧል:: የዋሽንግተን አገረ ገዥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጃቸው አብዛኛው የአሜሪካ ሕዝብ ስጋት ውስጥ መግባቱን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል::ዶናልድ ትራምፕ ግን “ምንም እንኳን ቫይረሱ አገራችን ውስጥ ቢገባም የሚያስደነግጥ ነገር የለም” በማለት የሕዝባቸውን ስጋትአቃለውታል:: የኮሮና ቫይረስ እስከ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ (ሪፖርተር መጽሔት ማተሚያ ቤት እስከገባበት ድረስ) በመላው ዓለም የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ87,ዐዐዐ በላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን፤ የሟቾች ቁጥርም ከ3,ዐዐዐ በላይ መድረሱንም መረጃዎች ያሳያሉ::
ግብጽና አልጀሪያን ተከትላ ናይጄሪያ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ሲገኝባት ሶስተኛዋ የአፍሪካ ሀገር ሆናለች:: በናይጄሪያ የተገኘው የቫይረሱ ተጠቂ የጣሊያን ዜጋ ሲሆን በናይጄሪያ የሚሰራ እነደሚሰራ ተነግሯል:: የቫይረሱ ተጠቂ መሆኑ የታወቀውም ከሚላን ከተማ ከመጣ በኋላ መሆኑም ተገልጿል:: ቫይረሱ በአጭር ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየስፋፋባት የምትገኘው አገር ደግሞ ደቡብ ኮሪያ መሆኗም እየተነገረ ነው::
በደቡብ ኮሪያ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 594 ሰዎች የቫይረሱ ተጠቂ መሆናቸውንና እስካለፈው ሳምንት መገባደጃ ድረስ የተጠቂዎች ቁጥር ከ3ዐዐዐ በላይ መድረሱም ተጠቁሟል:: እሰከ አሁን በኢትዮጵያ የለያዩ ሀገር ሰዎች በሙቀት መለኪያ ውስጥ ሲያልፉ የተወሰኑት ጥርጣሬ ውስጥ ወድቀው በመገኘታቸው፤ ለጊዜው በማግለያ ቦታ እንዲቆዩ ተደርገው በተደረገ ምርመራ፤ ከቫይረሱ ነፃ ሆነው በመገኘታቸው ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል:: ምንም እንኳን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደቻይና የሚያደርገውን በረራ ያላቋረጠ ቢሆንም፤ እስካሁን በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የገባና ወደሌላ አገሮች የተላለፈ ቢሆንም በቫይረሱ የተጠቃ ሰው አለመኖሩ ተረጋግጧል::የቫይረሱ በመላው ዓለም ሊባል በሚችል ሁኔታ እየተሰራጨ መገኘቱ ከፍተኛ ሰጋት እንደፈጠረበት፤ በኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የሚመራው የዓለም ጤና ድርጅትም ስጋቱን እየገለፀ ይገኛል:: በጉሮሮ ውስጥ የሚገኘው ሰልፈር የሚባለው ንጥረ ነገር ከደረቀ ቫይረሱ በአሥር ደቂቃ ውስጥ ወደ ሰውነት ይሰራጫል:: በመሆኑም ጉሮሮ እንዳይደርቅ ሞቅ ያለ ውሃ በሎሚ መጠጣት ከመከላከያ ዘዴዎች አንዱ መሆኑም እየተገለፀ ነው::አዋቂዎችም ሆኑ ልጆች ውሃ ይዘው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የሚመከር እንደሆነም ተገልጿል:: የበሽታው ምልክቶች ተደጋጋሚ የሚከሰትን ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት፣ራስ ምታትና ሳል ዋና ዋናዎቹ በመሆናቸው እንዚህ ምልክቶች የታዩበት ሰው እራሱን ፈጥኖ ከሌሎች በማግለል ወደ ህክምና ቦታ መሄድ እንዳለበት የህክምና ባለሙያዎች እየመከሩ ነው::

