“……ሀገሬ ኢትዮጵያ በዓለም ሸንጎ ላይ ፍርድ ተነፍጓት ስታዝን የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡….ኢትዮጵያ ያለፉት ታሪኮቿ በትክክል እንዳስረዱት ለነጻነቷና ለመብቷ በኮሎኒያሊስት ጣሊያን ጋር በየጊዜው ስትዋጋ ያሸነፈችው ብቻዋን ነው፡፡ የተጠቃችውም ብቻዋን ስለሆነ፤ አገሬ መቸውንም ስለሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም፡፡ ዛሬም ሆነ ነገ ነፃነቷን ለመጠበቅ፣ ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ያለባት እሷ ራሱ ብቻ ነች… ” በማለት የተናገሩት አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ ከ63 ዓመታት በፊት ህዳር 21 ቀን 1949 ዓ.ም ነው፡፡ ትክክል ነው፤ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ ከመጡባት የማንንም እርዳታ ወይም እገዛ አትፈልግም፡፡ ከ124 ዓመታት በፊት የሆነውም ይኸው ነው፡፡ ምንም እንኳን ችግሮች የተፈራረቁባት ሀገር ብትሆንና ልጆቿ በውስጣዊ ግንኙነታቸው የማይስሟሙባቸው ልዩነቶች የነበሩና ያሉ ቢሆንም ውበቶቻቸው እንጂ መለያያቸው አይደሉም፡፡ አይሆኑምም፡፡ የእናት ሆድ ዥጉርጉር እንዲሉ የኢትዮጵያም ልጆች የግድ አንድ አይነት አስተሳሰብ፤ አተያይና እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም በልዩነት ውስጥ መኖር ውበት ነውና፡፡ ይህንን ያልተረዱ የውጭ ኃይሎች ጥሩ አጋጣሚ ያገኙ መስሎአቸው በተደጋጋሚ ድንበሯን በማለፍ ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ ለውርደት እንጂ ለድል ሲያበቃቸው አልታዩም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን በሉዓላዊነታቸው ላይ የሚያለያይ ነገር የላቸውም፡፡ አስተማሪና ሌሎችም የዓለም ህዝቦች እንዲማሩት የሚያደርጋቸውን የማያዳግም እርምጃ ኢትዮጵያውያን በ1988 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣልያንን አድዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነውን ድል ያስመዘገቡትና እስከዛሬም ድረስ ትውልድ እየተቀባበለ የሚዘክረውን የነፃነት፣ የኩራትና የሉዓላዊነት ድል ያደረጉት ብቻቸውን ያለማንም እገዛና እርዳታ ነው፡፡ ይህ የጀግንነት ድል አሁንም ይሁን ወደፊት በኢትዮጵያውያን ብቻ ያለማንም ዕርዳታና ተሳትፎ ቀጥሎ ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ አጋጥመዋት በነበሩ የድርቅ ዘመናት ምንም እንኳን የዓለም ህዝብ ድጋፍ ያልተለያት ቢሆንም በዘመናት መካከል እሷም ለተጐጂ አንዳንድ የዓለም ሀገራት ታደርግ እንደነበረው እርዳታ ከመመልከት ባለፈ፤ ብሔራዊ ጥቅሟን ወይም ልዓለዊነቷን አሳልፋ የመስጠት ወይም መደራደሪያ አድርጋ አታውቅም፡፡ ወደፊትም አታደርግም፡፡ የቅኝ ግዛት ሰለባ የነበሩት ጐረቤት ሀገሮች ሱዳንና ግብፅ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ወይም ብሔራዊ ጥቅም መደራደሪያ ለማድረግ እያደረጉ ነው፡፡ “አባይን ያላየ ምንጭ ይመሰግናል” እንዲሉ ሀገራቱ የድርድር አጀንዳ አድርገው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፈታተን ድርጊት ለመፈፀም እየተንቀሳቁሱ የሚገኙት ደግሞ በአባይ ወንዝ ላይ መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት የአባይ ወንዝን ሳትጠቀምበት የኖረች አገር ብትሆንም፤ በአስፈለጋትና በመረጠችው ጊዜ ለመጠቀም ስትፈልግ የማንንም ይሁንታ መጠየቅ አያስፈልጋትም፡፡ የዓለምአቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ህግጋትን ካለማወቅ ወይም “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንዲሉ ሁለቱ የአባይ የታችኛው ተፋሰስ አገራት “አባይን የመጠቀም መብት ያለን እኛ ብቻ ነን” በማለት የ1929 የቅኝ ግዛት እሳቤአቸውንና በኋላም የ1959 የሁለቱ አገራት ስምምነትን ዛሬም ህያው አድርገው ለመቀጠል እየተሯሯጡ ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት የመጠቀም መብት ከ85 በመቶ በላይ ቢሆንም፤ ወንዙ ከሚመለከታቸው አሥራ አንድ ሀገሮች ጋር በጋራ ለመጠቀም (Equitable share) ለዓመታት ስትመካከርና ስትደራደር ኖራለች፡፡በዚህ መካካል ተፈጥሯዊ የመጠቀም መብቷን ዕውን ለማድረግ ማንንም ሳታማክርና የማንንም እርዳታ ሳትሻ፤ በአባይ ላይ የማልማት መብቷን ተጠቅማ በራሷና በልጆቿ ወጭ ለመገነንባት የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ግንባታ ጀምራ ላለፉት ስምንት አመታት በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡እኩይ ድርጊታቸውን የቀጠሉት ግብፅና ሱዳንም ስራ ሳይፈቱ የግድቡን ግንባታ ለማሰናከል ሩጫቸውን ቀጥለዋል፡፡የቻሉትን ሁሉ አድርገው ማጣፊያው ሲያጥራቸው፤በኢኮኖሚም ሆነ በቴክኖሎጂ የአለም ቁነጮ የሆነችውን አሜሪካንንና ዓለም ባንክን በታዛቢነት በተቀመጡበት ስለግድቡ አጠቃላይ ሁኔታ ድርድር ማድረግ እንዲችሉ ጠይቀው ያሉት ከሆነላቸው በኋላ፤ ታዛቢዎቹ ወደ አደራዳሪነት ተቀይረዋል፡፡ ይኸ ሁሉ ሲሆን ኢትዮጵያዉያን ዝምታን መርጠዋል፡፡ አሜሪካና ዓለም ባነክ ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪንት ተቀይረው የድርድሩ ሂደት ከቀጠለ በኋላ፤ግብፅ ጥያቄዋን በመለወጥ ምላሽ ልታገኝ የማትችልበትን ጥያቄ አቅርባለች፡፡ “ጌታዋን የተማመነች….” አንዲሉ ግብፆች ያቀረቡት ጥያቄ ድንበር ዘለል ከመሆኑም በላይ ሉዓላዊነትን የሚዳፈር ሆኖ በመገኘቱ፤መላው ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ ልዩነታቸውን ወደጎን በመተውና አንድ ሆነው በመቆም “እረፉ፤ አይሆንም” እያሉ ይገኛሉ፡፡የተለያዩ የብድርና የስጦታ ማባባያዎችን በማሳየት በማደራደር ላይ የሚገኙትን አሜሪካና የዓለም የገንዘብ ተቋማትንም “ድንበር ዘለል የሆነና ብሔራዊ ጥቅማችንን ከሚነካ ጉዳይ ላይ ላይ እጃችሁን አንሱ” እያለም ይገኛል፡፡የኢትዮጵያውያኑን ምላሽ የሰሙት አደራዳሪዎችም ማን አለብኝነት የተሞላበት መግለጫ እስከማውጣት ደርሰዋል፡፡ የአደራዳሪዎቹን ፍላጎትና እቅድ አስቀድሞም የተረዳው የኢትየፐጵያ ሕዝብ “ኢትዮጵያ ብቻዋን መቆም የምትችል ሀገር በመሆኗ በሉአላዊነቷ ላይ አትደራደርም” በማለት አስጠንቅቋል፡፡