በማይታመን ፍጥነት ዓለምን እያዳረሰ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት በርካታ ስፖርቶች እንዲቋረጡ ተደርጓል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ ከ34,000 በላይ ሰዎችን ለኅልፈት ዳርጓል፡፡ ኮቪድ-19 የሚል ተቀፅላ ያለው በሽታው ከ735,000 በላይ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡
መንግሥታት ወረርሽኙን ለማቆም የተለያዩ ዕርምጃዎች እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ሕዝብ በየቦታው እንዳይሰባሰብ፣ እንዳይጨባበጥ ግዴታም መልዕክትም እያሠራጩ ነው፡፡

ከታላላቅ መግለጫዎች መካከል የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) እና የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንሁ አቤ የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ዘንድሮ ከሐምሌ 17 ቀን ጀምሮ ለማካሄድ የተያዘውን ፕሮግራም በመሰረዝ ለሚቀጥለው ዓመት እንዲካሄድ መስማማታቸው ነው፡፡ አይኦሲ መጋቢት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው የ2020 ኦሊምፒክ ከዓርብ ሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ እሑድ ነሐሴ 2 ቀን እንዲካሄድ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል በሰሜን አሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶኮር፣ ብሔራዊ የቅርጫት ኳስ ማኅበርና ብሔራዊ ሆኪ ሊግ ውድድሮች እንዳይካሄዱ አግደዋል፡፡ በአውሮፓ በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቃችው ጣሊያንም ሁሉንም ስፖርታዊ ኩነቶች ዘግታለች፡፡
እግር ኳስ
በመጪው ሚያዝያ በካሜሩን አዘጋጅነት ሊካሄድ የነበረው የ2020 አፍሪካ ዋንጫ ለቀጣዩ ዓመት እንዲተላለፍ አኅጉራዊው ኮንፌዴሬሽን ወስዷል፡፡ በደቡብ አሜሪካ ፉትቦል ኮንፌዴሬሽን የሚዘጋጀው ኮፓ አሜሪካም እንዲሁ ለቀጣይ ዓመት አስተላልፎታል፡፡ በተመሳሳይም የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የዘንድሮውን የአውሮፓ ዋንጫ ለ2021 አስተላልፏል፡፡
ማራቶን
በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና ያላቸው የለንደንና የቦስተን ማራቶች ውድድር ወደ መስከረም 2013 ዓ.ም. ሲተላለፉ፣ የአምስተርዳም፣ ፓሪሰና ባርሴሎና ማራቶኖችም ተመሳሳይ ዕርምጃ ወስደዋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ለቀጣይ ዓመት ከተላለፉት ውስጥ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ምላሽ
ኮሮና ካሰናከላቸው ስፖርቶች ኢትዮጵያውያኑ የሚታወቁበት አትሌቲክስ ዋነኛው ነው፡፡ የማናጀር ተወካይና አሠልጣኝ እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብሔራዊ አትሌቶች አሠልጣኝ የሆኑት አቶ ሐጂ አዴሎ እንደሚገልጹት፣ ኮሮና አሁን ባለው ሁኔታ አደገኛና ዓለምን ትልቅ ሥጋት ውስጥ ያስገባ ቫይረስ ሆኗል፡፡
አሠልጣኙ ከ100 በላይ ታዋቂና ጀማሪ አትሌቶች በሥራቸው ይገኛሉ፡፡ አትሌቲክስ በባህሪው ለአንድ ውድድር ብቻ አራትና ከዚያም በላይ የዝግጅት ጊዜ የሚጠይቀውን ያህል ከፍተኛ የሆነ ላብ የሚያስወጣ የስፖርት ዓይነት መሆኑን የሚናገሩት አሠልጣኝ ሐጅ፣ ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ከየትኛውም አገር በተለየ ለኢትዮጵያውያን ከባድ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ፣ “የሩጫ ውድድር ውጤት የሚያስገኘው ከብዙ ድካምና ልፋት በኋላ ያውም ዕድለኛ ለሚሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደግሞ ሁሉም እንደሚያውቀው አንዳንዶቹ የቀን ሥራ እየሠሩ ነገን ተስፋ አድርገው የሚሠሩ ምንም ዓይነት ወርኃዊ ገቢ የሌላቸው በመሆኑ ጉዳቱ ሕይወትን ከማሳጣት በተጨማሪ በጥቅማ ጥቅም ደረጃም ነው” በማለት የሚኖረውን ተፅዕኖ ያስረዳሉ፡፡
በሥነ ልቦናው ረገድም ቢሆን አትሌቶች ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዚህ የሚስማሙት አሠልጣኙ፣ ‹‹አትሌቶቻችን የሚያጡት ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ ችግሩ የመላው ዓለም በመሆኑ መቅደም ላለበት የሰው ልጆች ሕይወት ስለሆነ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ነው እየሠራን የምንገኘው፡፡ ቫይረሱ ከተከሰተ ማግሥት ጀምሮ አትሌቶች ጥቅም የሚያገኙባቸው የተለያዩ በርካታ ውድድሮች ተሰርዘዋል፡፡ በግሌ እንደ አሠልጣኝና ማናጀር የሚሰማኝ ይኖራል፣ ይሁን እንጂ አሁን ቅድሚያ መስጠት የሚጠበቅብን ለሰው ልጆች ጤና ነው፣ አትሌቶቹ ይህን ክስተት ማለፍ ከቻሉ ብዙ ነገር ከፊት ለፊታቸው የሚጠብቃቸው እንደመሆኑ ያንን አስበው ሊንቀሳቀሱ ይጋባል፤›› በማለት ይመክራሉ፡፡
ለወትሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ተራራማና ጫካማ ሥፍራዎች ጠዋትና ከሰዓት እጅብ ብለው ልምምድ የሚሠሩ አትሌቶች እነዚያ ሮጠው የማይጠግቡ እግሮቻቸው ተጣጥፈው ከቤት እንዲውሉ አስገድዷቸዋል፡፡
አሠልጣኝ ሐጅ፣ ወረርሽኙ ምንም እንኳ ከሰዎች ወደ ሰዎች የሚተላለፍበት አንዱና ዋናው ንክኪ እንደሆነ ቢታመንም በጥንቃቄ የተናጠል ልምምዶችን መሥራት እንደሚያስፈልግ ያምናሉ፡፡ በእርግጥ ኮሮና መቼና በምን ያህል ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንደሚውል አሁን ከፈጣሪ ውጪ የሚያውቅ እንደሌለ የሚናገሩት አሠልጣኙ፣ ‹‹ቫይረሱ መፍትሔ ቢገኝለት እንኳ ቀደም ሲል ወደነበረው ዓይነት ፕሮግራሙን ለማስተካከል ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም ውድድር አዘጋጅ አገሮችና ስፖንሰር አድራጊ ኩባንያዎችና ድርጅቶች በቫይረሱ ምክንያት ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ የገባባቸው በርካታ ናቸው፡፡ አትሌቲክስ ደግሞ ከሌሎች ስፖርቶች በተለየ በስፖንሰሮች አማካይነት የሚንቀሳቀስ ዘርፍ ነው፡፡ ስፖርቱ ወደ ነበረበት ለመመለስ በተለይ በዚህ ቀውስ ኢኮኖሚያቸው ጉዳት የደረሰበት ኩባንያዎችና ድርጅቶች ጊዜ የሚፈልጉ በመሆኑ በግሌ ለአትሌቲክሱ ትልቁ ጉዳት ይህ ነው የሚመስለኝ፤›› በማለት አትሌቲክሱ በሒደት ስለሚገጥመው ፈተና ሥጋታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
ኮሮና ቫይረስ ባይከሰት ኖሮ አንዳንዶቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይህ ወቅት ዓለም ላይ በወርቅ ደረጃ በሚመደቡ የጎዳና ላይ ውድድሮች ውስጥ እንደ ቦስተንና ለንደን ማራቶኖች እንዲሳተፉ የሚደረገው የመግቢያ ተከፍሏቸው ነው፡፡ አትሌቶቹ ውድድሩን አሸንፈው ከሚያገኙት በላይ ለመግቢያ ብቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮች ማግኘት የሚችሉባቸው እንደሆኑ የሚናገሩት አሠልጣኝ ሐጅ፣ ‹‹ሁለቱም ውድድሮች እንዲተላለፉ ሲወሰን የሚደረጉበት ወቅትም ተቀራራቢ ነው፣ ሥጋቱ አንዱና ዋነኛው እንደዚህ ውድድሮች ሲደራረቡ አትሌቶች የሚያገኟቸውን ጥቅሞች ያጣሉ፡፡ ከአትሌቶች ባሻገር ለዋናው አወዳዳሪ አካል የዓለም አትሌቲክስ ማኅበር ጭምር ትልቅ ራስ ምታት መሆኑ የማይቀር ነው፤›› በማለት የችግሩን ግዝፈት ያስረዳሉ፡፡
የኮሮና ቫይረስ በዚህ መልኩ መከሰት ሌላው ችግር ሲሉ የሚያስረዱት አሠልጣኙ፣ ‹‹እኔን ጨምሮ ብዙዎቹ የዘርፉ ሙያተኞች የተለመደውን የዕለት ዕለት ሥራ እየሠራን ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡ ወጥተን የምንገባው በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ሆነን ነው፡፡ በአትሌቶቹ መካከል ከፍተኛ የሆነ መፈራራትና መጠራጠር ይስተዋላል፣ ማናጀሮችና ውድድር አዘጋጆች እስካሁን ባለው አንዳቸውም በስፖርቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ መናገር አይፈልጉም፣ ሁሉም ቅድሚያ ለአትሌቶቻችን ጤንነት ትኩረት እንድንሰጥ ብቻ ነው፤›› በማለት አሁን ላይ የስፖርቱን የወደፊት ዕጣ በሚመለከት የሚናገሩት አንዳችም እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቅ ታሪክ ካላቸው ቀደምቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በኦሊምፒክና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና ከሁለት አሠርታት በላይ ቆይታው የዓለም አዳዲስ ክብረ ወሰኖች በእጁ ጨብጧል፡፡ ከአዲስ አበባ 175 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የአሰላ ከተማ አቅራቢያ ከምትገኝ የገጠር ቀበሌ ተነስቶ በአሁኑ ወቅት ከባለ ቢሊየነሮች ተርታ የሚመደበው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ኮሮና ቫይረስ ለኢትዮጵያውያን አትሌት የሚኖረውን ተፅዕኖ አስመልክቶ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዓለም እያተራመሰ የሚገኘው ኮሮና ቫይረስ አሁን በያዘው መልኩ የሚቀጥል ከሆነ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እንደተጠበቀ፣ በተለይ ለወጣት አትሌቶች የወደፊት ዕጣ ከባድ እንደሚያደርግባቸው ቅድመ ግምቱን አስቀምጧል፡፡
አትሌቲክስ በተለይም የጎዳና ላይ ውድድሮች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የአትሌቶችን ሕይወት የሚቀይሩ እየሆኑ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ ወጣትና ተተኪ አትሌቶች በዚህ እጅግ አስፈሪ በሆነ ወረርሽኝ ሲበላሽ መመልከት ከባድ ቢሆንም፣ በሕይወት መኖር ካልተቻለ ሁሉም ነገር ስለሚቀር በተለይ ወጣት አትሌቶች ነገሮችን በትዕግሥት ማለፍ እንደሚጠበቅባቸዋል ይመክራል፡፡