ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ከመግባቴ በፊት አንድ የወንጀል ጉዳይ ከተፈጸመ ወይም ተፈጽሟል ተብሎ ከታመነ፤ የሚኖሩትን ሒደቶች በጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ልግለጽ፡፡ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊዎች ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፍረድ ቤት እና ማረሚያ ቤቶች ናቸው፡፡ ፖሊስ የቀረበለትን የወንጀል አቤቱታ ወይም ክስ ተቀብሎ፤ የወንጀል ምርመራ ያደርጋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ምርመራ መዝገቡን ተቀብሎ የወንጀል ክስ ለማቅረብ ወይም ላለማቅረብ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ፍርድ ቤት የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል በማለት ተጠርጥረው በፖሊስ የተያዙ ሰዎችን የዋስትና ጉዳይም ሆነ፤ በዓቃቤ ሕግ የቀረበለትን የወንጀል ክስ አከራክሮ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ የቀጠሮ ማረፊያ እና ማረሚያ ቤቶች ደግሞ በእሥር ላይ ሆነው ጉዳያቸውን የሚከታተሉ ተከሳሾችን የመጠበቅ እና በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆነው የእሥራት ቅጣት የተጣለባቸውን ታራሚዎች፤ የመጠበቅና ተኀድሶ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የእነዚህ አራት ተቋማት ተግባር እና ኃላፊነት በሕግ ተሠፍሮ የተሰጠ እና አንዱ በሌላው ላይ በሚያደርገው ሕጋዊ የቁጥጥር እና ሚዛን የመጠበቅ ሥራ (checks and balance) መሠረት ሕጋዊነቱ የሚፈተሽ ነው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሕግ ከተሠጡት ዋነኛ ተግባራትና ኃላፊነቶች መካከል፤ በሥልጣን ክልሉ ውስጥ የሚከናወኑ የወንጀል ምርመራ መዝገቦች ላይ ክስ ማቅረብ፣ ክሱን በፍርድ ቤት ቀርቦ መከታተልና መከራከር፤ እንዲሁም በወንጀል ምርመራ ላይም ሆነ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ያለ ክስ እንዳይቀጥል ማቋረጥ ነው፡፡ የቀድሞው የፍትሕ ሚኒስቴርም ሆነ የአሁኑ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፤ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይፋ የሆኑ ጉዳዮችን፤ ይፋ ያልሆኑ የተለያዩ የወንጀል የምርመራ መዝገቦችን፤ በፍርድ ቤት በክርክር ላይ የነበሩ የወንጀል ክሶችንም እንዲቋረጡ ውሳኔ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በከባድ የሙስና ወንጀሎች፣ በጸረ ሽብር አዋጁ እና መሰል ክሶች ተከሰው ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት፤ አመራሮች እና ግለሰቦች እንዲሁም ከታክስና ግብር ጋር ተያያዥት ያላቸው ክሶች ቀርበውባቸው የነበሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ክስ እንዲቆረጥ ሲወሰን ቆይቷል፡፡ የዛሬውም መጣጥፌ ቅኝት የሚያተኩረው ይህንን ክስ የማቋረጥ ሥልጣን እየተተገበረበት ያለውን መንገድ ነው፡፡
ሰሞኑን ከየካቲት ወር 2012 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ “ለሕዝብ ጥቅም ሲባልና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት” በሚል፤ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክርክር ሒደት ላይ የነበሩ ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ ወስኗል፡፡ በአማራ፤ በትግራይ፤ በደቡብና ሌሎችም ክልላዊ መንግሥታት በኩልም ተመሳሳይ ውሳኔ መወሰኑ በመገናኛ ብዙኋን ይፋ ተደርጓል፡፡ እነዚህን የወንጀል ምርመራዎችን ወይም ክሶሶችን ማቋረጥ ተከትሎ እንደወትሮው ሁሉ በሕብረተሰባችን ዘንድ ግርታ፣ ሐሜትና ስጋት እየተንጸባረቁ መሆኑን በቀላሉ ማስተዋል ችያለሁ፡፡ የግርታው አንዱ መንስዔ በፖሊስ የተጀመረ የወንጀል ምርመራ ወይም የፍርድ ቤት የወንጀል ክስ ሂደት መቋረጥ የሚችልበት የሕግ አግባብ ግልጽ ካለመሆኑ የመነጨ እንደሆነም እረዳለሁ፡፡ እኔን ጨምሮ የብዙዎች ሐሜትና ስጋት መነሻ እስከዛሬ በይፋ የተቋረጡት የወንጀል ምርመራዎችም ሆኑ ክሶቹ የተቋረጡትበት አግባብ ግልጽነት የጎደለው መሆን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እስከ አሁን የተሰጡትን ውሳኔዎች ንድፍ (pattern) እና ጠቅላላ ሁኔታ በቅርበት መመልከቱ፤ ውሳኔዎቹ የተሰጡት በእርግጥም የሕጉን ዓላማ ለማስፈጸም ይሁን ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት በእርግጠኝነት መናገር ያዳግታል፡፡
የወንጀል ምርመራ ወይም ክስ መቋረጥ ዛሬ የተፈጠረ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ የወንጀል ምርመራ ወይም ክስ መቋረጥ በአገራችን የሕግ ሥርዓት ውስጥ የተካተተው በንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ (የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ) ቁጥር 42 (1) (መ) እንደተደነገገው “የፍርድ ሚኒስትሩ (አሁን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ) በፈረመበት ማዘዣ ለሕዝብ ጥቅም ሲል ክስ እንዳይቀርብ ዓቃቤ ሕጉን ያዘዘው እንደሆነ” የወንጀል ምርመራ የተጀመረ ቢሆንም እንኳን፤ ዓቃቤ ሕጉ ክስ ማቅረብ አይችልም፡፡ በሌላ አገላለጽ የተጀመረው የወንጀል ምርመራ ይቋረጣል፡፡ ከባድ የግፍ አገዳደል ወይም ከባድ የውንብድና ተግባር ካልሆነ በስተቀር ዓቃቤ ሕጉ በተከሳሹ ለይ ያቀረበውን ማንኛውንም ክስ፤ በፍርድ ቤቱ ፈቃድ ከፍርድ በፊት ክሱ በሚሰማበት በማንኛውም ጊዜ ክሱን ለማንሳት እንደሚችል በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ ቁጥር 122 (1) ላይም ተደንግጓል፡፡ በሌላ አገላለጽ የተጀመረውን የወንጀል ክስ በክርክር ሒደቱ በማንኛውም ጊዜ ማቋረጥ ይችላል ማለት ነው፡፡
የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ በደፈናው ለሕዝብ ጥቅም ሲል ከሚል በስተቀር “የሕዝብ ጥቅም” ምን እንደሆነ በግልጽ የሚያስቀምጠው ዝርዝር መሥፈርት የለም፡፡ በዚህ ረገድ በኢፌዲሪ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ከየካቲት 25 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የወንጀል ጉዳዮችና የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ተሣታፊ በሚሆኑት አካላት ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን የጸደቀው የኢፌዲሪ የወንጀል ፖሊሲ የተሻለ ግልጽነት አለው፡፡ ፖሊሲው የወንጀል ምርመራና ክስ ሊቋረጥባቸው የሚገቡ ምክንያቶችን፣ “የሕዝብ ጥቅም” ማለት ምን ምን ነገሮችን ሊያካትት እንደሚገባው፣ ወደ ፊት በሚወጡ ሕግጋት፤ የወንጀል ምርመራንና ክስን ከማቋረጥ ረገድ ሊያካትቱ የሚገቧቸው ፍሬ ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ ይዘረዝራል፡፡
ይኸው ፖሊሲ የወንጀል ምርመራ ሂደት የሚቋረጥባቸውን ሁኔታዎች በተመለከተ የሚወጡ ሕጎች፤ ዓቃቤ ሕግ በመከናወን ላይ የሚገኝ የምርመራ ሂደትን ለማቋረጥ በሕግ ተለይቶ የተደነገገ በቂ ምክንያት መኖሩን ማመን እንዳለበትና “ማንኛውም የወንጀል ምርመራ … ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ትዕዛዝ ከሰጠ” እንደሚቋረጥ ባካተተ መልኩ መቀረጽ እንደሚገባቸው በአንቀጽ 3.9 ሥር ይደነግጋል፡፡ የፖሊሲው አንቀጽ 3.12 “ተጠርጣሪውን ጥፋተኛ ለማድረግ የሚያስችሉ በቂ ማስረጃዎች ቢኖሩም እንኳ የሚመሠረተው ክስ የሕዝብ ጥቅም የማያስከበር መሆኑ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በታመነ ጊዜ፤ ዓቃቤ ሕግ ክስ ላይመሠርት ይችላል፡፡ … ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ የማይመሠረትባቸው ጉዳዮች የሚከተሉትን ዋና ዋና መስፈርቶችን መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህም በመጀመሪያ የተፈፀመው ወንጀል በጣም ቀላል መሆኑን ሕጉ በግልጽ በደነገገ ጊዜ፤ክሱ ቢመሠረት የሚወሰነው ቅጣት ተግሳጽ፣ ማስጠንቀቂያና ወቀሳ መሆኑ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከታመነ ሲሆን፤ሁለተኛ ደግሞ ተጠርጣሪው በዕድሜ መጃጀት ወይም በማይድን በሽታ በመያዙ ምክንያት ጉዳዩን በፍርድ ቤት መከታተል የማይችል የሆነ እንደሆነ፤ ሶስተኛ ወንጀሉ ከባድ ቢሆንም በተጠርጣሪውና በግል ተበዳይ መካከል የተፈጠረው የወንጀል ምክንያት በመደበኛ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ከሚሰጠው ውሣኔ ይልቅ ፤በባሕላዊ ሕጎችና ተቋማት ዘላቂ መፍትሔ ያገኛል ተብሎ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ከታመነ፤አራተኛ ጉዳዩ በክስ ሂደት ውስጥ ቢያልፍ ብሔራዊ ደኅንነትን ወይም የዓለም አቀፍ ግንኙነትን የሚጎዳ ይሆናል ተብሎ ከታመነበት፤አምስተኛ በቀላል እሥራት ወይም በሕጉ መሠረት በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጡ እና በግለሰብ ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ሆነው በተበዳዩና በተጠርጣሪው መካከል እርቅ ተፈፅሞ ከሆነ፤ስድስተኛ ክስ መመሥረቱ ተመጣጣኝና ሚዛናዊ ያልሆነ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ፤ሰባተኛ በማንኛውም ምክንያት ጉዳዩ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በመቆየቱ ወቅታዊነቱን ወይም አስፈሊጊነቱን ሲያጣና የተፈፀመው ድርጊት በጣም ቀላል ወንጀል ከሆነ፤ጉዳቱ አነስተኛ ሆኖ ተጠርጣሪው ያደረገው ድርጊት የወንጀል ባሕርይ እንዳለው፤ ፍፁም ከሆነ ግንዛቤ ማጣት የተነሳ ከሆነና የመሳሰሉት ናቸው” በማለት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ የማይመሠረትባቸው ጉዳዮችን ይዘረዝራል፡፡
አዲስ የሚወጡም ሆነ በሥራ ላይ ያሉ ሕግጋት ከፖሊሲው ጋር ተጣጥመው ከሚተረጎሙና ከሚፈጸሙ በስተቀር ፖሊሲው እንደ ሕግ የሚጠቀስ ሰነድ አይደለም፡፡ “ዓቃቤ ሕግ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ እንዳይቀርብ ለመወሰን የሚችልባቸው ሁኔታዎች በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ እና በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሚወጡ መመሪያዎች ውስጥ በዝርዝር ሊቀመጡ”እንደሚገባና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ የማይመሰርትባቸው መስፈርቶችን ለመወሰን የሚረዱትን የአሠራር መመሪያዎች ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አዘጋጅቶ በሥራ ላይ እንዲውሉ እንደሚያደርግ እንደቅደም ተከተላቸው የፖሊሲው አንቀጽ 3.12 እና 3.10 ይደነግጋሉ፡፡
በአንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ ላይ የወንጀል ምርመራ ወይም ክስ ሊቋረጥ የሚችልበት ሌላው ምክንያት፤ ዓቃቤ ሕጉ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ በአንድ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ መሆኑን የሚጠቁሙ ማሥረጃዎች ስላሉት ተጠርጣሪውን ለመክሰስ ወይም ለማስቀጣት የሚያስችሉ ማስረጃዎች አሉኝ ብሎ ቢያምንም “ምርመራ የሚደረግበት ወንጀል በአፈፃፀም ደረጃው እና በሚያስከትለው የቅጣት መጠን ከባድ ሊባል የሚችልና በተለይም በተደራጁ ቡድኖች፣ የጦር መሣሪያን በመጠቀም ወይም እንደ ሙስና እና ሽብርተኝነት ዓይነት ሆነው በረቀቀ ስሌት የሚፈፀሙ ወንጀሎች ሲሆንና ከወንጀሉ ውስብስብነት የተነሣ በድርጊቱ ተካፋይ የነበረውን ተጠርጣሪ ትብብር ማግኘት ካልተቻለ በስተቀር ጉዳዩን በምርመራ ለማውጣት እና ውጤታማ ክስ ለማቅረብ የማይቻል ወይም አዳጋች ሲሆን” በተጠርጣሪው ላይ የተጀመረውን የወንጀል ምርመራ ወይም ክስ በማቋረጥ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ በሌሎች ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሳሾች ላይ እንዲመሰክርና ማሥረጃ እንዲሰጥ የሚደረግበት የሕግ አግባብ ሊኖር ኤገባም፡፡ “ዓቃቤ ሕግ የተፈለገውን ውጤት ያስገኛል ብሎ ካመነ [በእነዚህ] ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ተጠርጣሪ[ው]ን ከክሱ ነፃ ማድረግ የሚችል መሆኑ በወንጀል እና በሥነ ሥርዓት ሕጎች ውስጥ በግልጽ ሊቀመጥ” እንደሚገባ ፖሊሲው በአንቀጽ 3.17.5 ሥር ይደነግጋል፡፡
እያንዳንዱን ክስ የማቋረጫ ምክንያቶች ዘርዝሮ መጨረስ (Exhaustive listing) አስቸጋሪ በመሆኑ ሕግጋቱ የወንጀል ፖሊሲው እንዳስቀመጠው አመላካች ዝርዝሮችን (Illustrative listing)ይዘው መውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የወጡት ሕግጋትም በተግባር ሲውሉ የሕጉን ዓላማ የሚያሳካ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፉነት የመንግሥት ነው፡፡ የጽሑፉ ዓላማ እስከ አሁን የተቋረጡት የወንጀል ምርመራዎች ወይም የወንጀል ክሶች ለምን ተቋረጡ የሚል ባለመሆኑ፤ እያንዳንዱን ክስ አንስቶ የመተንተን ዓላማ የለውም፡፡ ነገር ግን መሰል ውሳኔዎች የሚሰጡበት ሥርዓት በሕግ የተገደበ እና በባለሥልጣናት ይሁንታ ሥር ያልወደቀ መሆን አለበት፡፡ተገማች ሥርዓት እና ተጠያቂነት የሠፈነበት ሊሆን ይገባል፡፡ አሠራሩም ጉራማይሌ ያልሆነና ለፖለቲካ መጠቀሚያ ሊውል የማይገባ ነው፡፡ከሁሉም በላይ ደግሞ ምንም እንኳን ክስ የማቋረጥ ሥልጣን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሆንም፤ የውሳኔው መሠረት ሕግ እና ሕግ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥትም ሆነ በወንጀል ሕጉ መሠረት ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸውና ከክስ መቋረጡ ውሳኔው ሊጠቀሙ የሚገቡ ሰዎች ሁላ ሊካተቱበት ይገባል፡፡ የክስ ማቋረጥ ውሳኔውን ጉራማይሌነት ለማሳየት አንድ ተግባራዊ ምሳሌ በማሳያነት ላንሳ፡፡
የፌዴራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008ን የተለያዩ ድንጋጌዎችን ተላልፈዋል ተብለው የወንጅል ምርመራ ሲካሄድባቸው የነበሩ እና በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ የነበሩ ብዙህ ሺህ ተከሳሾች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ተጠርጣሪዎችና ተከሳሾች መካከል በተለይም ያለ ደረሰኝ ግብይት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በወንጀል ምርመራና በክስ ላይ የነበሩ ግለሰቦች ክሳቸው እንዲቆረጥላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ጥያቄያቸውን በመቀበል ክሳቸው ቢቋረጥ የሚደግፍ መሆኑን አሳውቆ፤ በቁጥር አአ/ከጸ/01/01/42 ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ይህንን ደብደቤ መነሻ በማድረግ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በቁጥር 01/ደሚ/258/11 በ03/08/2011 ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት በላከው ደብዳቤ “ከግብር ከፋዮቹ ባህሪ፣ ከወንጅሉ ባህሪ እና ከሚያስከትለው ውጤት አንጻር … እጅግ አነስተኛ የገንዘብ መጠን የያዙ ሆነው ያለደረሰኝ … ግብይት የተከናነባቸው … ጥፋቶች በመሆናቸው … ከያዙት የገንዘብ መጠን አነስተኛ መሆን እንዲሁም ከተየዘው የኢኮኖሚና የታክስ ሪፎርም እና ከግልሰቦቹ ኢኮኖሚ አቅም አንጻር፤ በምርመራም ሆነ በፍርድ ቤት ደረጃ ያሉ በሙሉ እንዲቋረጡ ቢደረጉ በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዝቅተኛ በመሆኑ ክሳቸው ተቋርጦ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ቢገቡ ለመንግሥትና ለሕዝብ የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ከፍተኛ በመሆኑ … በማለት ክሳቸው እንዲቋረጥ ወስኗል፡፡”
በዚህ ውሳኔ መሠረትም ተመሳሳይ ክስ የቀረበባቸው በሺዎቸ የሚቆጠሩ ተከሳሾች በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ውሳኔ፤ የክስ ማቋረጥ ውሳኔው እስከተወሰነበት ጊዜ በወንጀል ምርመራ ደረጃ ላይ የነበሩትም ሆነ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የነበሩ ክሶች ተቋርጠው በነጻ ተሰናብተዋል፡፡ ሆኖም የክስ መቋረጡ ከሚመለከታቸው ተመሳሳይ ጉዳይ ያላቸው ተከሳሾች መካከል ከሶስት ሺህ (3000) የሚበልጡ ተከሳሾች ስም ዝርዝር በመረጃ አያያዝ ምክንያት ክሳቸው ከሚቋረጡት ተጠርጣሪዎችና ተከሳሾች ዝርዝር ውስጥ ሳይካተት ቀርቶ ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከልም የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ እና ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምድብ ጽህፈት ቤቶቹ ጋር መረጃ በመለዋወጥ በሁለተኛ ዙር ስማቸው እንዲካተት በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ተከሳሾች ክሳቸው በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ውሳኔ በሒደት ተቋርጧላቸዋል፡፡ ሆኖም ሌሎች ክስ ለማቋረጥ በመሥፈርትነት የተቀመጡትን ከላይ ያሰፈርኳቸውን መለኪያዎች የሚያሟሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተከሳሾች ስም ዝርዝራቸው በድጋሚ ሳይካተት በመቅረቱ ክሳቸው እንዲቋረጥ ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጀምሮ በሚመለከታቸው የፌዴራልና የአዲስ አበባ መስተዳደር ቢሮዎች በጋራና በተናጠል አቤቱታ ቢያቀርቡም አቤቱታቸው እስከ አሁን ሰሚ አላገኘም፡፡ በዚህ የተነሳም ተመሳሳይ ክስ፣ ተመሳሳይ ጊዜ እና ተመሳሳይ ሌሎች የሕግ እና የፍሬ ነገር መለኪያዎችን የሚያሟሉ ተከሳሾች ጉዳያቸው ባለመቋረጡ በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ፍርድ ተጥሎባቸዋል፡፡
እኔን ጨምሮ ሌሎችም የሕግ ባለሙያዎች እስከአሁን በነበሩን የፍርድ ቤት ክርክሮች ላይ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተወሰኑትን ተከሳሾች ክስ አቋርጦ የቀሪዎቹ ሊቋረጥ አይገባም ማለቱ በሕገ መንግሥቱ ጥበቃ የተሰጣቸውን የእኩልነት መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተቃውሞ ያቀረብን ቢሆንም፤ ውሳኔ ያላገኙት ክርክሮች እንዳሉ ሆነው ሌሎቹ ግን ፍሬ አላስገኙልንም፡፡ ይህ መሠረታዊ ፍትሕ የማግኘት መብትን በጽኑ የሚጋፋ እና ክስ የማቋረጥ ሥልጣንን አለአግባብ መጠቀም ነው፡፡
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 (1) ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ መሆኑን እና ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ አሠራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት የሌለው እንደሆነ ደንግጓል፡፡ማንኛውም የመንግሥት አካል እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማሥከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ግዴታ እንዳለባቸው፣ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት እና ማንኛውም የመንግሥት ኣስፈጻሚ አካል በምዕራፍ ሦስት ሥር የተደነገጉትን መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 (2)፣ 12 (1) እና 13 (1) በግልጽ ደንግገዋል፡፡ በምዕራፍ ሦስት ከተቀመጡት ድንጋጌዎች አንዱ በአንቀጽ 25 የተቀመጠው የእኩልነት መብት ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ እደሚደረግላቸው፣ በማናቸውም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግባቸው ሁሉም እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡
እነዚህ በምሳሌነት ያነሳኋቸው ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስና ክሱ እንዲቋረጥ የተወሰነበት ጊዜ እንዲሁም ክሱን ለማቋረጥ የተቀመጡት መሥፈርቶች ተከሳሾቹንም የሚመለከት ቢሆንም ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ተመሳሳይ ክስ ያላቸው ተከሳሾች ክሳቸው ሲቋረጥ የእነሱ ክስ አይቋረጥም መባሉ፤ ክሳቸው በተቋረጠላቸው ሰዎችና በሌሎቹ ተከሳሾች መካከል ጉልህ ልዩነት የሚያደርግ አድሏዊ አሠራር ነው፡፡ በመሆኑም የእኩልነት መብት የሚጥስ ተግባር ነው፡፡
በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 (እንደተሻሻላው) አንቀጽ 5 (1) (2) (3) መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዓላማዎች ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማክበርና ማስከበር እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና የወንጀል ሕግን ማስከበር ናቸው፡፡ በአንቀጽ 6 (3) (ሠ) ሥር ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባራት አንዱ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ማንሳት ነው፡፡ በአንቀጽ 6 (6) መሠረት የፌዴራል መንግሥቱ ሕጎች ተግባራዊ መደረጋቸውን እና አተገባበራቸውም ወጥነት ያለው መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥትም ሆነ የወንጀል ሕግ ተከሳሾች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑ የሚደነግግ ቢሆንም ከሳሽ በሕግ ከተጣለበት ኃላፊነት እና ከቆመበት ዓላማ በተቃራኒ በተከሳሾች መካከል ልዩነት ማድረጉ ሕገ መንግሥቱን ይጥሳል፡፡
በምሳሌነት ይህንን አነሳሁ እንጂ ተመሳሳይ ነገሮች በይፋም በባለሙያዎች ዘንድ በተደጋጋሚ ይገጥማሉ፡፡ ግልጽነት የሚጎድለውና ቁጥጥር የማይደረግበት የክስ ማቋረጥ ሒደት ከተንሠራፋ የሚፈጥረው ተጽዕኖ እጅግ የከፋና ዜጎች በፍትሕ ተቋማቱ ላይ ያላቸውን የመነመነ ዕምነት የባሰ የሚያጠፋ ነው፡፡ በመሆኑም ክስ የሚቋረጥበት ሥርዓት በዝርዝር ሕግጋትና መመሪያዎች ሊደገፍና የበላይ ሕግጋትን ባከበረ መልኩ ሊቀረጽ ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ የትኛውም አካል የመንግሥት ሥልጣን ላይ ቢወጣ ከሕግ ውጪ የማይለውጠው ተመሳሳይ እና ተገማች ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ሌሎች የመንግሥት አካላትም አስፈጻሚው አካል የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ሕግ መንሥቱን የጣሱ እንዳይሆኑ የተሰጣቸውን ሥልጣን በመጠቀም ቁጥጥር ማድረግና ውሳኔዎቹ ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን ሊጠቀሙ ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ዋስትና ሊኖራቸው የሚችለው ሦስቱም የመንሥት ተቀቋማት አንዱ የሌላውን ተግባር ሕገ መንግሥታዊነት በሕግ አግባብ የመቆጣጠር ልማድም ሲዳብር ነውና የቁጥጥር እና ሚዛን የመጠበቅ (checks and balances) ተግባር ከወረቀት አልፎ ወደ መሬት ሊወርድ ይገባል፡፡ በሕግና በሥርዓት የማይመራ የወንጀል ክስ የማቋረጥ ሒደት፤ ሕዝብ ሊያገኝ የሚችለው ጥቅም ሕብረተሰቡ በፍትሕ አካላት ላይ ያለውን አመኔታ ጨርሶ ከማሟጠጥ በስተቀር የሚሰጠው ጠቀሜታ፤ ከስጋትና ከሃሜት የላቀ ሊሆን አይችልም፡፡
የዛሬ ምልከታዬን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ የምንደማመጥ፣ ሐሳብን በሐሳብ ብቻ የምንሞግት፣ ካለፈው ይበልጥ በመጪው ላይ የምናተኩርና ምንጊዜም ለእናት አገር ኢትዮጵያችን ቅድሚያ የምንሰጥ የአንድ አገር ሕዝቦች እንሁን!!! ብሩሐን ቀናት ከፊታችን ይቅደሙ!!! ሰላም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው (LL.B, LL.M, MSW) ያላቸው ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሲሆኑ፤ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን እየገለጽን፤ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ፡፡