መሬት የአንድ ሀገር አንኳር የምጣኔ ሀብት ከሚባሉት ዘርፎች ዉስጥ ግንባር ቀደሙን ድርሻ ይይዛል፡፡ይህ በመሆኑም በአወንታዊም ይሁን አሉታዊ ጎኑ፤ ሃገር አቀፍም ይሁን ዓለም አቀፍ ትኩረትን በማግኘት ረገድም ተወዳዳሪ የለውም፡፡ በኢትዮጲያ ታሪክም ዉስጥ የፖለቲካ ትግሎች ማጠንጠኛ ሆኖ ብቅ ካለበት ጊዜ አንስቶ እስካለንበት ጊዜ ድረስ መሬት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ቆይቷል፡፡እያሳረፈም ነው፡፡
አብዛኛዉ የሀገሪቱ ዜጎች በግብርና ስራ ላይ የሚተዳደሩና መሬት የኑሮኣቸዉ ሁለንተናዊ መሰረት ሆኖ በመቆየቱ፤ በየጊዜዉ የነበሩ መንግስታት የልማት ዕቅዶች መሬትን ማዕከል ያደረጉ በመሆናቸዉ መሬት የሀገሪቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ዋና የስበት ማዕከል ሆኖ ይታያል፡፡ ቀደም ያሉት ነገስታት መሬትን በመቆጣጠርና በመዘወር የስልጣናቸዉ ዋነኛ መጠበቂያ መሳሪያ ያደርጉት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
በኢትዮጲያ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ትልቅ የሚባል አሻራ አሳርፎ ካለፈዉ የ1967ዓ.ምቱ የመሬት ላራሹ አዋጅ በፊት ብዙ ትኩረት ተሰጥቶት የመነጋገሪያ አጀንዳ የነበረዉ የገጠር መሬት ጉዳይ ነበር፡፡
የደርግን በመገርሰስ በ1983 ዓ.ም ወደ ስልጣን የመጣዉ የኢህአዴግ መንግስት፤ ባጸደቀው ህገ መንግስት አንቀጽ 40(3) እንደተደነገገው፤ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነትና መብት፤ የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነዉ፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት መሆኑን ቢገለጽም፤ የሀገሪቱ ትልቅ ሀብት በሆነዉ መሬት ላይ አዛዥ በመሆንና የመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀሩ በመሬት ማግበስበስ ላይ ተሰማርተዉ መጠነ ሰፊ የሆነ የመሬት ሀብት በህገወጥ መልኩ ሲመዘበር ቆይቷል፡፡ ቀጥሏልም፡፡
በተለይ በከተሞች የሚስተዋለዉን የኗሪዎች ቁጥር ማሻቀብ ተከትሎ ትልቅ የሀብት ምንጭ የሆነው የመሬት አቅርቦቱ እያነሰ በመምጣቱ ዋጋዉም እጅግ እየናረ መጥቷል፡፡ ይህም መሬትና የመሬት ነክ ጉዳዮችን በከፍተኛ ሁኔታ ለሙስናና ለብልሹ አሰራሮች እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡
የከተማ መሬት በተለያየ ጊዜ መሬትን ለመስጠት ህጋዊ ስልጣን ከተሰጠው አካል እውቅና ውጪ በህገወጥነት እና በጉልበት (በወረራ) መልክ እየተያዘ ለተለያዩ ተግባራት እየዋለ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያደረሰ ይገኛል፡፡ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጭምር የተሳተፉበት ይህንን የመሬት ዝርፊያ በርካቶች ኢህዴግን አጣብቂኝ ዉስጥ ካስገቡት ሀገራዊ ጥፋቶች እንደ አንዱ አድርገዉ ይቆጥሩታል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ የመሬት ሀብቱን በከፍተኛ ደረጃ ከማመናመኑም በላይ መሬትን ለሚፈለገዉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማዋሉ ቀርቶ የጥቂቶች መክበሪያ እንዲሆን አድርጓል፡፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ወረራ እጅግ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ እየተስፋፋ የመምጣቱ ዜና መሰማት የጀመረዉ በተለይ የ1997 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ መሆኑ ይታወሳል፡፡በተለይ የከተማው ዳርዳር ክፍት ቦታዎችን በመውረርና ጨረቃ ቤት በመስራት ዓመታትን ካስቆጥሩ በኋላ ኢህአዴግ በወረራ የተያዘውን ቦታ ህጋዊ በማድረግን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በመስጠት የመሬት ወራሪዎችን ህጋዊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ውሻ በቀደደው እንዲሉ አልፎ አልፎም ቢሆን ጭለማን ተገን በማድረግና ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት የመሬት ወረራው ተጧጡፎ ቀጥሏል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይቶችን በማካሄድ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ቢሞክርም፤ ወረራዉ ግን ከመቆም ይልቅ ቅርጹን እየቀያየረ ዘመቻ በሚመስል መልኩ በከፍተኛ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ በማስፊፉያ አካባቢ የሚገኘዉ የመሬት ሀብት በሕገወጥ መንገድ በወረራ እየተያዘ ከፕላን ዉጪ ግንባታዎች ሲካሄዱ ይታያል፡፡ ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ የመረጃ አያያዝ ማነስ፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት ችግሮች ከህግ ስርአቶች አለመከበር ጋር ተዳምረው ለመሬት ወረራው መስፋፋት ምክንያት መሆናቸዉ በተደጋጋሚ ቢገለጽም በአሁኑ ሰዓት እየተስተዋለ ያለዉ የመሬት ወረራ ግን የፖለቲካ መልክ ያለዉና ፖለቲካዊ ለዉጡን እንዳጋጣሚ በመቁጠርና ለመጠቀም ከማሰብ የመነጨ እንደሚመስል ብዙዎች ይናገራሉ።
ባለፉት አመታት በሀገሪቱ የታየዉን አስተዳደራዊ ለዉጥ ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተስፋፋ የሄደዉ ሥርዓት አልበኝነት ህግና ስርዓት ማስከበር ላይ ትልቅ እንቅፋት እየፈጠረ በርካታ ጥፋቶች ተፈፅመዋል፡፡ እየተፈፀሙም ይገኛሉ፡፡
በአንድ ሃገር የዴሞክረሲ ስርዓት ለማምጣት ምርጫ የመጀመሪውና ቁልፉ ሂደት ነው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ምርጫ ዜጎች መሪያቸውን ያለምንም ተጽእኖ በነጻነት በካርድና በካርድ ብቻ የሚመርጡበት ሳይሆን የምርጫ በቅት በመጣ ቁጥር ጭንቀት ውስጥ የሚገቡበት እየሆነ መምጣቱ በተለይ ከ1997 ወዲህ የነበሩት የምርጫ ውጤቶች ምስክር ናቸው፡፡ግድያ እስራት፤ መፈናቀል፤ ስደት፤ፍረጃና የመሬት ወረራ መገለጫዎቹ ሆነው መቀጠላቸውም ያደባባይ ሚሰጥር ነው፡፡ምርጫን ተከትሎ በተለይ በከተማ መሬት ላይ የሚደረገው ወረራ ይማይቀርና እንደአንድ የምርጫ ምሟያ መስፈርት የሆነ ይመስል ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ መካሄድ አለመካሄዱ እርግጠኛ ያልተሆነበት ምርጫ 2012ን ተከትሎ በመሬት ዙሪያ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ መመልከት ቢቻል፤በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ችግሮቹን ይበልጥ እንዲባባሱ ያደረገ ይመስላል፡፡ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ፤ የተለየ የግል ጥቅምና ፍላጎት ያላቸዉ አካላት ወቅቱ የፈጠረዉን አለመረጋጋት በመጠቀም የመሬት ወረራ ላይ መሰማራቸዉ እየታየ ነዉ፡፡ በመንግስት አሊያም በግል ይዞታነት ተለይተዉ የተቀመጡ፤ ለአረንጓዴ ስፍራነትና ለተለያዩ የልማት ስራዎች ተብለዉ የተከለሉ መሬቶች በጠራራ ፀሀይ እየተወረሩ ይገኛል፡፡የሚገርመው ነገር መሬቱን የወረሩ ግለስቦች አዲስ የተሰራ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ሆነ የከተማ አስተዳደሩ የከተማ መሬት የሚሰጠው በጨረታ፡በምደባና በልዩ ሁኔታ መሆኑን በመመሪያ ጭምር አሳውቆ እያል፤ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ግን ህጋዊ የሚመስል ሰነድ በሜያዝ ወረራውን ተያይዘውታል፡፡ለምሳሌ ያህል በየካ፤በቦሌ፤በንፋስስልክ ላፍቶ፤በአቃቂ ቃሊቲ ክፍላተ ከተሞች ባሉ አረንጓዴ ቦታዎችና ክፍት ቦታዎች ላይ የተፈጸሙ ወረራዎችን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ በእርግጥ በከተማዋ የሚፈጸሙ የመሬት ወረራዎች መሰረታዊ መነሻቸዉ የተለያዩ ቢሆንም ከአንዳንድ መረጃዎች ለመገንዘብ የሚቻለዉ በድርጊቱ ዉስጥ በተደጋጋሚ እና በዋና ተዋናይነት እየተሳተፉ ያሉት ወረራዉን የኑሯቸዉ መሰረት ያደረጉ ህገወጥ ደላላዎችና በመንግስት ተቋማት ዉስጥ ህገወጥ አሰራሩን በመደገፍ የሚያመቻቹ ህገወጥ አካላት በስፋት በመኖራቸዉ ነዉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ቢሆን በዚህ ሀሳብ ይስማማል የሚል ግምት አለን፡፡ በሳለፍነዉ አመት መገባደጃ ላይ አስተዳደሩ ባወጣው አንድ መግለጫ ላይ፤ በመሬት ወረራዉና በህገወጥ የቤቶች ግንባታ ላይ የመንግስት አሰፈፃሚ አካላት፤ ደላሎች እና የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸዉ ኃይሎች ጭምር እንደሚሳተፉበት መረጃ እንዳለዉና የከተማ አስተዳደሩ ህገወጥ ቤቶችን ከማፍረስ በተጨማሪ እነዚሁ አካላት ህግ እንዲጠየቁ እንደሚያደርግ ገልፆ የችግሩን ስፋት ለማሳየት ሞክሮ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነዉ መጥቷል፡፡ በርካታ የመንግስትና የግል ይዞታዎች በህገወጥ መንገድ እየተወሰዱ መሆኑን በንፋስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ስሜ አይጠቀስ ያሉ ግለሰብ ለሪፖርተር ገልፀዋል፡፡በክፍላተ ከተሞች ተከልለዉ የተያዙና ህገወጥ ናቸዉ የተባሉ መሬቶችን ሪፖርተር በቦታዉ ተገኝቶ የተመለከተ ሲሆን፤ ብዙዎቹ ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ካርታ የሌላቸዉ ሲሆን፤ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ግን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች በህገ ወጥ መንገድ በደላሎች እጅ እየገቡ እየተቸበቡ እንደሆነ ሪፖርተር በተጨባጭ ያገኛቸው ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡በተለይ ከተማ አስተዳደሩ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ቦሌ፣ አቃቂ ቃሊቲና የካ ክፍላተ ከተሞች፤ ሕገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታዎች በስፋት ከተከናወኑባቸው መካከል እንደሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጧል፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ያገኘነዉ መረጃ እንደሚያመለክተዉ ከሆነ፤ በያዝነዉ ዓመት የመጀመሪያዎች አራት ወራት ብቻ ከ2,317 በላይ ይዞታዎች በሕገወጥ መንገድ ተወረው እንደተገኙ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለው የመሬት ወረራ ለከተማው አስተዳደር ፈተና እየሆነ መምጣቱ ተነስቶ ነበር።ወረራዉ የከተሞችን አረንጓዳ ቦታዎች፣ የወንዝ ዲርቻዎች፣ ለመሰረተ ልማት አዉታር ዝርጋታ በፕላን የተከለሉትን ቦታዎች ያካተተ በመሆኑ የጉዳቱን መጠን ከፍተኛ እንዳደረገው ተወስቷል፡፡ ይህንንም ለመከላከል በከተማ አስተዳደሩ የሚገኝ የመሬት ሀብትን በአግባቡ በመቁጠር እና ምዝገባ በማካሄድ፤ እንዲሁም ተገቢዉን ጥበቃ በማከናወን የመንግስት እና የህዝብ ሀብትን ከብክነት እና ከወረራ መከላከል፤ እንዲሁም በመሬት ወረራ የተያዘና የተከናወነ ማንኛዉም ግንባታ ላይ እርምጃ በመዉሰድ፤ ይዞታዎቹን በህጋዊ አግባብ ወደ መሬት ባንክ የማካተት ስራዉን የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል ሲሉ አስተያየት ሰጭዎች ለሪፖርተርመጽሔት ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት ቢሮ በበኩሉ በከተማዋ ህገወጥ የመሬት ወረራ እና ተያያዥ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓቱን የማዘመን ስራ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አቶ ነጋሽ ባጫ የአዲስ አበባ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሀላፊ ለሪፖርተር መፅሄት ተናግረዋል፡፡የመሬት ወረራዉን አስመልክቶ የከተማ አስተዳደሩ የመለየት ስራ ሰርቶ በክፍለ ከተማ ደረጃ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠና እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ገልፀዉ፤ በቀጣይ ግን የመከላከል ስራዉ ላይ ትኩረት በማድረግ ቢሮዉ በሚዘረጋዉ አዲስ አደረጃጀት አማካኝነት ችግሩን ከመከሰቱ አስቀድሞ የመከላከል ስራ ለመስራት እንደተዘጋጀ ገልፀዋል፡፡ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ የከተማዋ መሀል አካባቢዎች በመንገድ ዳርቻዎች፤በመንግስት ይዞታዎች እንዲሁም ለአልሚዎች ከተሰጡ በኋላ ግንባታ ባልተጀመረባቸው ይዞታዎች ላይ በየዕለቱ የላስቲክና የቆርቆሮ ቤቶች ተሠርተውባቸው እንደሚያድሩ የገለፁት የቢሮ ኃላፊዉ፤ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ጋር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ከዚህ ቀደም የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት በወረዳ ደረጃ እንዳልነበረና አሁን በአዲስ መልክ መዋቀሩ ችግሩን ከስሩ ለመቅረፍ እንደሚያመች ሀላፊዉ አክለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደር አዲስ መዋቅር ዘርግቶ ችግሩን ለማስተካከል እተንቀሳቀሰ መሆኑ ጥሩ ቢሆንም፤ለዓመታት ተንሰራፍቶ የቆየው ሕገወጥ የመሬት ወረራ አዲስ አሰራርና አዲስ መዋቅር በመዘርጋት ብቻ መፈትሄ ሊያገኝ አይችልም፡፡ በመሆኑም መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሕጋዊ እርምጃ አለበት፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር የመራጮችን ድጋፍ ለማግኘት ተባሎ ሕገወጥ የመሬትን ወረራም ይሁን አላሰፈላጊ የከተማ ውስጥ እንቅስቃሴዎችን ባላዩ ማለፍ፤ ምንም ይሁን ምንም ውጤቱ አስደሳች ስለማይሆንና ቆይቶም ቢሆን ዋጋ ማስከፈሉ ስለማይቀረ፤ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ አስፈላጊዉን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡
የሀገሪቱ መንግስት መናገሻ ከተማ ከመሆን ባለፈ፤ የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆንችውን አዲስ አበባ፤ እንደስሟ ማድረግ ባቻል እንኳን በሕገወጥ የመሬት ወረራ በሚሰሩ ፕላን የለሽ የጨረቃ ቤቶች ገጽታዋ ሲበላሽ ዝም ብሎ መመልከት ከታሪክ ተወቃሽነትም ባለፈ የሕግ ተጠያቂነትንም ሊያስከትል ስለሚችል፤ ሕዝብ ለማገልገል በሕዝብ ወንበር ላይ ተቀምጠው ያሉ ኃላፊዎች በችግሩ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል፡፡ በአቅም ማነስ፤በግዴለሽነት፤ በውግንና፤ በአድር ባይነትና የጥቅም ተጋሪ በመሆን የሕዝብና የመንግስት ሀብት በሕገወጦች ሲመዘበር ባላዬ ማልፍ፤ቢያረፍድ እንጅ ማስጠየቁ ስለማይቀር ሕግን አክብሮ ማስከበር ሀገራዊ ግዴታም ጭምር ነው፡፡