ፖለቲካል ኢኮኖሚ በሃገር ውስጥ እና በሃገራት መካከል የሚታየውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ የግንኙነት የሚያጠናና የሚተነትን የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡ የዘርፋ ትኩረትም ሀብትንና በትረ-ስልጣንን የትኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ተቆጣጥረውታል? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መሻት ነው፡፡ የሀብት ክፍፍል በምንያህል ስፋትና መጠን እንደተያዘ ይተነትናል፡፡ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የመንግሥትና የዜጐችን ግንኙነት ያጠናል፡፡ የስልጣን ምንጭ የሆኑትን ዜጐች የተጠቃሚነት ሁኔታ ይተነትናል፡፡ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የመሬት፤ የጉልበትና የካፒታል ጥምረት ነው፡፡ የመሬትን ስርዓት በሀገራችን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ውስጥ ስንመለከት በርስት እና ጉልት ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ይህ ስርዓት በአገሪቷ አብዛኛው ክፍል አርሶ አደሩን የሚያገል ከመሆኑም በላይ የባለቤትነት መብትንም ሆነ የመጠቀም መብትን የማይሰጥ ነበር፡፡
በመሬት ላይ ይታይ የነበረውን ችግር አፄኃይለሥላሴ በትረስልጣኑን ሲይዙ ይስተካከላል ተብሎ ቢጠበቅም በሶስት ምክንያቶች ማሳካት አልቻሉም፡፡ አንደኛው ምክንያት ራሳቸው ንጉስነገስቱ እና ቤተሰቦቻቸው ሰፋፊ ጋሻ መሬት ባለቤት በመሆናቸው፤ ሁለተኛው ደግሞ የዘውድ ምክርቤቱ አባላት ከበርቴ ከመሬት ጋር የተገናኘ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያገኙ ስለነበሩ የምክር ቤቱን አባላት ጥቅም የሚነካ ህግ ማውጣት፤ ማለትም ለንጉሰ ነገስቱ የስልጣን አለመርጋጋት ስለሚያስከትል በመሬት ላይ የመድፈር ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት በማጣታቸው ሲሆን፤ ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ አፄኃይለሥላሴ የርስት መሬት ምዝገባና የመሬት ግብር ህግን ለማስፈፀም ሞክረው ባለርስቱ ዘንድ የመተባበር ፈቃደኝነት ባለማግኘታቸው ነበር፡፡ አፄኃይለሥላሴ በመሬት ላይ ባሳዩት ዝምታና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው በተማሪዎች ዘንድ አብዬትን አስከተለ፡፡ ለአብዬቱ መከሰት ሌሎች ምክንያቶች መዘርዘር አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ የከፍተኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለዓመታት “መሬት ላራሹ፤ ለላብ አፍሳሹ” የሚለውን መፈክር ዋና የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ ባካሄዱት አብዬት ንጉሰ ነገስቱን ከመንበረ ስልጣናቸው አስነሳቸው፡፡ ተማሪዎቹ በወቅቱ መሬት ላራሹ ሲሉ የጥያቄያቸው ዋና ጉዳይ የገጠር መሬት እንደነበር መፈክራቸው ይጠቁማል፡፡ የጥያቄው መንፈስ ሲታይ መሬት ለአርሶ አደሩ ይከፋፈል ከሚል ቅን ሃሳብ የተነሳ ይመስላል፡፡ ይኸ ደግሞ የባለቤትነት ጉዳይ በአርሶ አደሩ እጅ ይሁን ወደሚል ትርጓሜ ይገፋል፡፡ የማርክሲስት ፖለቲካ አቀንቃኝ የ1960ዎቹ ተማሪዎች ያነሱት የመሬት ላራሹ ጥያቄ፤ የከተማ መሬትን የሚያካትት አልነበረም፡፡ በወቅቱ የወጡ መፈክሮችም የፖለቲካ ሃሳቦች ስለከተማ መሬት ጉዳይ ያነሱት ነገር ስለመኖሩ የተፃፋ ሰነዶች አያስረዱም፡፡
ደርግ ስልጣኑን እንደያዘ በአዋጅ ቁጥር 31/1967 የገጠር መሬት ባለቤትነት ወደ መንግሥት በማዞር እና መሬቱን ለገበሬው በማከፋፈል፤ የመሬት ላራሹን ጥያቄ እንደመለሰ አስነገረ፡፡ በአዋጁ መሰረትም መሬት መሸጥ፣ መለወጥ፣ ማከራየት፣ መስጠት፣ በወለድ አገድ ማስያዝ ከለከለ፡፡ ደርግ በገጠር መሬት ላይ ያደረገውን የመውረስ ዘመቻ በአዋጅ ቁጥር 47/1967 አማካኝነት የከተማ መሬቶችን እና ትርፍ ቤቶችን ወደ መንግሥታዊ ንብረትነት የማጠቃለሉን ሥራ በማጠናከር በገጠርም ሆነ በከተማ ያለ መሬትን በቁጥጥር ሥር አዋለ፡፡ አንድ ግለሰብ አንድ መኖሪያ ቤት እንዲኖረው በማድረግ የመሬት ላራሹ ጥያቄ የቀደደው መንገድ ወደ ከተማ መሬት ዞሮ መሬት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር እንዲውል አደረገ፡፡ የተወረሱ የግለሰብ ቤቶችን የቀበሌ ቤት አስብሎ ለነዋሪው አደለ፡፡የሆነው ሆኖ ደርግ አርሶ አደሩን ከግል ገባርነት ወደ መንግሥት ገባርነት ስለአሽጋገረው የመሬት ጥያቄ በታሰበው እና በሚፈለገው ሁኔታ ተመልሶለታል ለማለት የማያስችሉ ሁኔታዎች ነበሩ ብሎ መግለፅ ይቻላል፡፡ የከተማ መሬት የዜጋው ጥያቄ ባልሆነበት ሁኔታ መመለሱም አግባብ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት ወደ ስልጣን እንደመጣ የአገሪቷን የመሬት ጉዳይ ያስተዳደረበትን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ በህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 40(3) ላይ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት የመንግሥትና የህዝብ መሆኑ ተገልፆል፡፡ መሬት የማይሸጥና የማይለውጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንበረት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ የገጠር መሬትን አስመልክቶም በአንቀፅ 40 ንዑስ አንቀፅ 4 እና 5 ላይ የአገሪቱን አርሶ እና አርብቶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ አርሶ አደሩ በደፈናው መሬት በነፃ የማግኘት መብት እንዳለው የሚደነግግ ሲሆን አርብቶ አደሮች ደግሞ ለግጦሽ እና ለእርሻ መሬት በነፃ እንደሚሰጣቸው በግልፅ ተቀምጧል፡፡ የከተማ መሬትን ስንመለከት ደግሞ በህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 40(6) ላይ የግል ባለሀብቶች (ኢንቨስተሮች) ከመንግሥት በህግ በሚወሰን ክፍያ መጠን መሬት እንደሚተላለፍላቸው ይገልፃል፡፡ ከዚህ አኳያ መሬት ለግል ባሀብቱ ይተላለፋል ሲል ታሳቢ ያደረገው መሬት ለሪል ስቴት አልሚ ባለሀብቶች በሊዝ በማስተላለፍ እነርሱ ደግሞ ቤት ገንብተው ለነዋሪ ያስተላለፋሉ የሚል እንድምታን የያዘ ይመስላል እንጂ፤ የከተማ ነዋሪ መሬት በምን መልኩ ሊያገኝ እንደሚችል ያስቀመጠ አይመስለኝም፡፡
የክልሎች ህገ-መንግሥቶችም በበኩላቸው መሬት የማይሸጥ የማይለውጥ መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ የመሬት ባለቤትነት የክልሉ ህዝብ የጋራ ንብረት መሆኑን አፅድቀዋል፡፡ እንደሚታወቀው ፖሊሲ ተለዋዋጭ እንደመሆኑ መጠን ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት መሬትን በህገ-መንግሥት እንዲታሰር ማድረጉ የመሬት ጉዳይ እንደተወሳሰበ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪም መሬትን በህገ-መንግሥቱ እንዲሰፍር መደረጉም ደርግ በአዋጅ ያስጀመረውን መሬትን ለፖለቲካ መሣሪያነት ለመጠቀም ይመስላል፡፡ በጥናት መረጋገጥ ያለበት ቢሆንም ማለት ነው፡፡
ህገ-መንግሥቱ በከተማ መሬት ላይ አዲስ ነገር ይዞ የመጣው የሊዝ ጉዳይን ነው፡፡ የከተማ መሬት ለግል ባለሀብቱ ከማስተላለፍ ጋር ተያይዞ የሊዝ ስርዓት በመደንገጉ ከመንግሥት ወደ ግለሰብ የማስተላለፍ ስሪት በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 721/2004 መግቢያ ላይ መሬት የመንግሥትና የህዝብ ንብረት ሆኖ የመሬት አጠቃቀም በህግ እንደሚወሰን በህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 40 በመደንገጉ፤ የከተማ ቦታን በሊዝ ለመያዝ የሚያስችል አዋጅ እንደወጣ ይገልፃል፡፡ እዚህላይ ህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 40(6) ላይ የከተማ መሬት ብሎ ያነሳው ለግል ባለሀብቱ መሬት በህግ በሚወሰን ክፍያ በሊዝ እንደሚተላለፍ ነው፡፡ ነገር ግን በአዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀፅ 11 ላይ በከተማ መሬት የሊዝ ጨረታ ላይ ማንኛውም መሳተፍ እንደሚችል ይገልፃል፡፡ ይህም ማለት የሊዝ ጨረታው ለግል ባለሀብቱ ብቻ አለመወሰኑን ያሳያል፡፡ ይሁንና በህገ-መንግሥቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎች መንግሥት በብቸኝነት በመሬት ላይ የመወሰን ሙሉ መብት እንዲኖረው አግዞታል፡፡ በመሬት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ወደፊት መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች አንደኛው፤ የከተማ መሬት ባለቤትነትን አስመልክቶ የተገለፀው ህገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ እንዲሻሻል ማድረግ ነው፡፡በህገ-መንግሥቱ ውስጥ መሻሻል ስላለባቸው አንቀጾች ማንሳቴ ካልቀረ አንቀፅ 3(1 እና 2)፤ አንቀፅ 5 (2)፤ አንቀፅ 39 (1)፤ አንቀፅ 40 (3)፤ አንቀፅ 46 (1እና 2)፤ አንቀፅ 47 (1 እና (2) እና አንቀፅ 49 (5) መሻሻል የሚያስፈልጋቸው አንቀፆች መሆናቸውን ማመላከት እፈልጋለሁ፡፡ ሁለተኛ ለጊዜውም ቢሆን የክልል መንግሥታት “ነባር” ህዝቦችን የመሬት ባለቤት የማድረግ፤ “መጤ” የሚሏቸውን መሬት አልባ የማድረግ አስተሳሰብና ድርጊት ካለ ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ ማድረግ ያሻል፡፡ ምክንያቱም “ነባርነት” እና መጤነት በራሱ ሌላ ትርጓሜ ያሻዋልና፡፡ እውነታው በታሪክም ሆነ በነባራዊ ሁኔታም የትኞቹ ህዝቦች “ነባር” የትኞቹ ደግሞ “መጤ” እንደሆኑ ግልፅ ስላልሆነ እና መልስ የሚሹ ቁልፍ ጥያቄዎች ስላሉ ነው፡፡ ለምሣሌ ከመቼ ጀምሮ የኖረ ነው ነባር የሚባለው? መጤስ?፤ መጤ የሚባለውስ በምን መስፈርት ነው? ሦስተኛ የሀገር ግንባታውን የበለጠ ለማጐልበት፤ ክልሎች የአስተዳደር ወሰን ብቻ ሆነው መኖሪያነታቸውና ባለቤትነታቸው ግን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ማድረግ፤ አራተኛ ፖሊሲ አውጭዎች ያለፉትን ሩብ ዓመታት የመሬት አስተዳደር ጉዞውን ቢገመግሙት ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የከተማ መሬት በመንግሥት እጅ በመሆኑ ያስገኘው ጥቅምና ጉዳት፣የመሬት ላራሹ ጥያቄ ተመልሷል? ወይስ አልተመለሰም? የሚሉት ጉዳዮች በጥልቀት ቢጠኑና ቢተነተኑ የዜጋውን እውነተኛ ሃሳብ እና ፍላጐት ለማወቅ ይረዳል፡፡ በፋና ወጊነት ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩቱ የጀመረው የውይይት መድረክም ሌሎች አካላትም ቢያጠናክሩት በመሬት ጉዳይ ላይ ያሉት ችግሮች ይቀንሳሉ፡፡
ፀሐፊው የመጀመሪ ያዲግሪያቸውን በታሪክ፤ሁለተኛዲግሪያቸውን በውጭ ፖሊሲና ዲኘሎማሲ እንዲሁም በመልቲ ካልቸራሊዝም ሰርተዋል፡፡ ጹሑፉ የጸሃፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለፅን በኢ-ሜል አድራሻቸው፡- [email protected] ማግኘትይቻላል፡፡