“በመልክዓ አፍሪቃ ላይ፣ እንደ አጎበሩ የወላድ እናት ጡቶች ጉብ ብላ፣ ለልምላሜና ለሥልጣኔ ምክንያት የሆነ ማየ ሐሊቧን [የወተት ውኃ] ወደታች እየረጨች በመኖሯ፣ ለለጋሥነቷ እንከን አይወጣላትም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ነባር ዘመናት ተለውጠው በአዲስ ዘመኖች በተተኩ ቁጥር፣ በአዲሱ ዘመን የሚገኝ ትውልድ ሁሉ ከአዲስ ፍላጎቶች ጋር የሚመጣ በመሆኑ፣ ነባር ልግሥናም ይዘቱን መቀየር ግድ ይሆንበታል፡፡ የአዲሱ ትውልዳችን አስተሳሰብና ዝንባሌ እጅግ ደርቆ የገረረም ባይሆን፣ እርጥብ አይደለም፡፡ እንደነዓባይ ያሉ የዓለሙ ቤተ ውኃዎች፣ ቀስ በቀስ የሞት አፍንጫ እያሸተቱ (ውኃቸው እያነሰ) እንደመጡ ግንዛቤ አለው፡፡ በኤፍራጥስና በጤግሮስ ጭን ስር ተሞላቃ ያደገችው ባቢሎን፣ በሥልጣኔ አብባ እንደ ነበር፣ ከታሪክ አንብቧል፡፡ የውኃ ማኅፀኖች ሥልጣኔን ሊወልዱ አንደሚችሉ ጠርጥሯል፡፡ ታድያንን የራሱ ዓባይ ዥረት ዝንተ ዓለም እየዘፈነና እያቅራራ፣ ደኑንና አረሁን ጥሶ ወደ ቆላ ሲወርድ ዝም ብሎ ማየት የሚዋጥለት አይሆንም፡፡ ስለሆነም ‹መላ በሉ› ማለቱ አልቀረም፡፡ የ‹እናስቀረው ያጣላል›ም ዚቅ፣ ሳይገባው አልቀረም፡፡ ‹ሰላም እንዳይኖረን› ካረጉን ምክንያቶችም አንዱ ነው ይል ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ፣ ‹አገር ያፈራውን ሲሳይ፣ የአገሩ ዜጋ የማይጠቀምበት ከሆነ፣ የአገር ሕዝብነት ትርጉም ምንድነው?› ብሎም ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ‹ውኃችን አፈር ይዞ እንዳይሄድ ወንፊት ይዤ ልቅረብም› ይል ይሆናል፡፡
የምድሪቱን ፀጋ፣ ውኃን ሆነ አየራት፣
ሣር ቅጠሉን ሳይቀር፣ ማዕድን ዕፀዋት፣
መጠቀም እንድንችል፣ በጋራ በኅብረት፣
ኧረ ሰዎች በሉ፣ ድረስ ነፊ ወንፊት
አገሩ ተዝቆ፣ ተንዶ ሳይሸፍት፣
ዶማና አካፋ፣ ያ ዓባይ ሆኖበት፣
እንደቡልዶዘርም፣ ነድሎ ገፎ ወስዶት፣
ራቁቱን ሳይቀር፣ ዓባይ ተወን በሉት!
አገር ባዶ ሳይሆን፣ አፈር አልባ ግተት
አፈሩን ማጋዙን፣ ቢተወው ምናልባት!!
አንድ ልዩ ዘዴ፣ መፈጠር አለበት!… እያለ የሚዘፍነውም፣ የዓባይ ዋልጌነት ቀስቅሶት ይሆናል፡፡ ከሌሎች አስተያየቶቹ ሁሉ፣ ይህን ሐሳቡን በሚገባ ሊያስተናግዱለት ይገባል፡፡ በጋርዮሽ ለመጠቀም የሚያስችል ዘዴ! በእርግጥ ይኼኛው አስተያየት ጥሩ አማራጭና አመርቂነትም ያለው ነው፡፡”
ይህ የመንደርደርያ ሐተታ ከሦስት አሠርታት በፊት በብዕር ስሙ “ገሞራው” ተብሎ የሚታወቀው ባለቅኔው ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ፣ በኖረበትና በዐፀደ ሥጋ በተለየባት በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ባሳተመው “እናትክን!” በሉልኝ! በተሰኘው ዓባይ ተኮር የግጥም መድበሉ ያሰፈረው ኃይለ ቃል ነው፡፡
ገሞራው በስደት ዓለም ውስጥ ሆኖ ለኢትዮጵያ ያልበጀውን ለባዕዳን ስለጠቀመው የዓባይ ወንዝ አረ እንዴት ነው ነገሩ ሲል አንጎራጉሯል፡፡ የውኃ ጥማት ለፈጀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሮሮአዊ ስንክሳር ነበር በክታቡ ያስገነዘበው፡፡
ገሞራው በዚህ አገላለጽ ብቻ አልተወሰነም፡፡ ፍኖተ ዓባይን፣ መልክአ ዓባይን እንዲህ በቁጭት ይፈክረዋል፡፡
“ቋጥኝና ገረገንብ በሚበዛበት አካባቢ ሁሉ፣ የዓባይ ወንዛዊ ጥልቀት እጅግ ቅርብ ነው፡፡ በአንፃሩ እንደዚያ ያለው አካባቢ ሁሉ፣ ጎናዊ የሆነ ስፋት አለው፡፡ አንድን ቋጥኝ አልፎ ቆልቋላማ ሥፍራ ባገኘበት ሥፍራ ሁሉ፣ ዓባይን ሲዘል ላየው ሰው ደራጎን ምሥጋና ይንሳው፡፡ በዚያም ወቅት፣ የሚከሰተው ድምፅና የውኃዎች ርጭት፣ ከሰማያዊ መብረቅና ነጎድጓድ በምንም አያንስም፡፡ በአንክሮ ለሚያው፣ እጅግ አስደናቂና አስደሳች ትርዒት ነው፡፡
“እንደ መቅደላ አፋፍ ባገጠጡ ቋጥኞች ላይ፣ እየተንደረደሩ የሚወርዱት የዓባይ ፏፏቴዎች፣ ልዩ ተዓምራት መሥራት የሚችሉ ጉልበታዊ ኃይሎች ነበሩ፡፡ ጉብታ መሬቶች ለማለፍ፣ እየተምዘገዘገ የሚወርደው የዓባይ ቁጡ የፏፏቴ ውኃ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኰረንቲ ወለድ ሻፍቶችን ማንቀሳቀስ የሚያስችል፣ የሚሊዮን ፈረሶች ጉልበት ኃይል አለው፡፡ ከዚያ ሁኔታ ላይ ሊፈጠር የሚችለው ኮረንቲያዊ የኃይል ምንጭ፣ በበኩሉ ማዕሠረ ድህነት ኢትዮጵያን በወራት ዕድሜ ብቻ መፍታት በቻለ ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ እነዚያን የኮረንቲ ኃይል ለማመንጨት፣ ከሚገደበው ግድብ ውስጥ የሚንጣለለው ውኃ በመስኖ የውኃ አከፋፈል ጥበብ ተገዶ፣ በየአካባቢው ክፍለ አገር ሊሠራጭ በሚችልበት ወቅት፣ ከሚፈጥረው የእርሻ ምርታዊ ውጤት ይልቅ፣ የልምላሜው ውበት ብቻ ስንት ተመልካቾችን ጭምር በሳበ ነበር፡፡ እርግጥ ‹‹ምድረ ገነት›› ይፈጥር ነበር! ዕሴቱማ አይነገር!!
ገሞራው (ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ) እንጉርጉሮውን ይቀጥላል፡፡ “በእርግጥም ዓባይ የሚያስቡትና የሚቀልቡት ድልብ ሠንጋና ቅልብ ሙክት አይደለም! በሰባና በደለበ ወቅት እንዲታረድ የሚጠበቅ እርድ!! እዚያ ምድራችን ላይ እየተወዛወዘ፣ የሆነ ሱፐርቡልዶዘር ይመስል፣ ለዘመናት ማርማ፣ ወተትማ ውኃችንን፣ ወርቅማ እቁማ አፈራችንን እንዳጋዘ ሊኖር? እንዲያ የለየለት ዋልጌ ሆኖ እንዳሾፈና እንዳላገጠ ሊኖር? አጠገቡ ሆኖ ‹የውኃ ያለህ!› እያለ ሲጮህ፣ ደራሽ ውኃ ያጣው ወገኑ እንደ ገረረ ጀንዲ ደርቆ ሲያልቅ፣ ለቀሪው ቋሚ ወገኑ ፈለገ ዓባይ የዘለዓለም መቆጫ (የሚቆጭበት) ምክንያት ትዝብት ሆኖ ሊኖር ነው፡፡
ገሞራው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ “ውኃችን አፈር ይዞ እንዳይሄድ ወንፊት ይዤ ልቅረብም” ይል ይሆናል ብሎ ያንፀባረቀው ከ23 ዓመታት በኋላ እርሱ በሕይወት እያለ ዕውን የሆነው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጉባ የመሠረት ድንጋይ መጣሉና ሥራው መጀመሩ ነው፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. “የሚሌኒየም ግድብ” (አስቀድሞ ሲጠነሰስ “ኤክስ ፕሮጀክት”) በሚል በፌዴራላዊ ሪፐብሊኩ የመጀመርያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካይነት የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የግድቡ ሥራ ዘጠነኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በመጋቢት አጋማሽ የወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው የግድቡ ፕሮጀክት ክንዋኔ 72 በመቶ ደርሷል፡፡
ሰሞኑን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ፣ ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ ሒደት እንዳስረዱት፣ 72 በመቶ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎቹም ከ42.3 በመቶ በላይ መድረሱን፣ የሲቪል ስትራክቸር የግንባታ ሒደትም ከ20 በመቶ በላይ አፈጻጸም አስመዝግቧል፡፡
ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ይፋ ያደረጉት ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ በዘንድሮ ክረምት የመጀመርያው ዙር የመጀመርያ ምዕራፍ ሙሌት እንደሚከናወንና በዚህም 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንደሚያዝ ይገልጻል።
ሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ በ2013 ዓ.ም. ክረምት እንደሚከናወንና 13.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ሜትር ውኃም በዚህ ወቅት እንዲሞላ ተደርጎ፣ የመጀመርያው ዙር ሙሌት እንደሚጠናቀቅ ሰነዱ ያስረዳል።

ዓባይ–ናይል
ገሞራው፣ ለመሆኑ ፈለገ ዓባይ ወይም ሪቨር ናይል፣ ምን ያህል በታሪክ የታወቀ ወንዝ ነው? በሺሕ ዘመናት በሚቆጠር የህላዌ ዕድሜው ምን ዓይነት ጠቀሜታ አበርክቷል? ባለበት ክፍለ ዓለም ውስጥስ በመከሰቱ፣ ምን ዓይነት ጣጣ አስከትሏል? ዛሬስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ብሎ ጠይቆ ስለ ዓባይ ማንነት ፈልቅቆ በማውጣት እንደሚከተለው ያስረዳል፡፡
ከጥንታዊው የግሪክ ቋንቋ ኔይሎስ ከሚለው ቃል ስሙን እንዳገኘ ሊቃውንት ይተርካሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከላቲን ቋንቋ ኒሉስ ከሚል ቃል የተገኘ ነው ይላሉ፡፡ ከግሪኩም ይሁን ከላቲኑ፣ ይህ ታላቅ አፍሪቃዊ ወንዝ ናይል የሚል ስያሜ እንደያዘ ለዘመናት ነበረ፣ አለ፣ ይኖራልም፡፡ በዓለም ያሳወቀው ሌላ ባሕርዩ ሳይሆን በቁመተ-ረዥምነቱ የዓለምን ታላላቅ ወንዞች ሁሉ ስለሚያስከነዳ ነው፡፡ ከመንታ ቦታዎች ምንጮች ተነስቶ፣ አራት ሰፋፊ አህጉራትን አቆራርጦ ማደርያ ቤቱ በሆነው የሜዲቴራንያን ባሕር እስኪደርስ ድረስ፣ 6,690 ኪሎ ሜትሮችን የሚጓዝ ማራቶናዊ ወንዝ ነው፡፡ ሜዲቴራንያን ባሕር ከመድረሱ በፊት፣ በተለይ ለሁለት ታላላቅ አገሮች-ኑብያና ምስር (ሱዳንና ግብፅ) ከፍተኛ የሲሳይ ድልብ አቅራቢ ሆኖ በቅንነት ሲያገለግል መኖሩ ይነገርለታል፡፡ ከዚህም የተነሳ ነው ‹ጥንታዊው የምድረ ግብፅ ሥልጣኔ ያለ ዓባይ (ናይል) ወንዝ ጭራሽ አይታሰብም› እየተባለ በየታሪኩ ገጾች የተመዘገበው፡፡ ምናልባትም በባሕረ ሜዲቴራንያን አካባቢ በመሥረጉ፣ አውሮፓንና መካከለኛ ምሥራቅን እያጣቀሰ፣ ካሮፓ ጣልያንን ከመካከለኛው ምሥራቅ ቱርክን ኮርኩሮ፣ በባለምንጮቹ አገሮች ላይ፣ ወስፈንጥር ሲቀስት ያስኖረው!!
ናይል የሚለው ቃል የሁለቱ አፍሪካውያን ወንዞች የወል ስም ነው፡፡ አንደኛው ናይል ነጭ ናይል የሚለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ዓባይ ብለን የምንጠራው ሰማያዊ ናይል (ጥቁር ናይል) ነው፡፡ ነጭ ናይል ካኔራ የሚባል ወንዝ ከሚመነጭበት ቦታ ፈልቆ፣ የቪክቶሪያን ሐይቅ ቆርጦ ሲመጣ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ከጣና ሐይቅ አጠገብ ከሚገኝ አንድ ምንጭ ፈልቆ፣ ሐይቀ ጣናን ሰንጥቆ፣ የሚውዘገዘገው ዓባይ ወንዝ ካርቱም ከተማ ላይ፣ ወንድሙን ነጭ ዓባይ ያገኘዋል፡፡
በውጮች ዘንድ የኢትዮጵያ ዓባይ ከጣና ሐይቅ የሚነሣውን ብሉ ናይል ከማዕከላዊ አፍሪካ የታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የሚወጣውን ኋይት ናይል ሲሉት ሁለቱ ወንዞች ሱዳን ካርቱም ተገናኝተው ወደ ግብፅ በሚያደርጉት ጉዞ ናይል በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ፡፡ ከግሪክ ኒሎስ የተገኘው ናይል ፍችውም የወንዝ ሸለቆ ማለት ነው፡፡
ለግብፃውያን ዓባይ ሕይወታቸውም መሠረታቸውም ነው፡፡ በጥንታዊው ታሪክ ጸሐፊ ሔሮዶቱስ እንደተገለጸው “ግብፅ የዓባይ ስጦታ” በመባል ትታወቃለች፡፡ በጥንታውያን ግብፃውያን ውኃ ኡዋት (Uat) ተብሎ ሲጠራ፣ ፍችውም አረንጓዴ ማለት ነው፡፡ ውኃና አረንጓዴ ተመሳሳይነት እንዳላቸውና የነፍስ መገለጫም እንደሆነ በአፈ ታሪክ ይነገራል፡፡ ሊዶር ከሮቭኪን፣ “የጥንቱ ዓለም ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው፣ ግብፃውያን የዓባይ ወንዝ ከየት እንደሚመነጭ ባለማወቃቸው የዓባይ አምላክ ከሰማይ በባልዲ እየቀዳ ቁልቁል ወደ መሬት እንደሚያንቆረቆርላቸውና የጐርፍ ማጥለቅለቅ የሚያጋጥመውም የሚንቆረቆርላቸው የውኃ መጠን ሲጨምር እንደሆነ ያምኑ ነበር፡፡ በመሆኑም ማሳቸውን ያለመልምላቸውና ሕይወታቸውን ይጠብቅላቸው ዘንድ ዓባይን ዘወትር ይማፀኑት፣ ምስጋናቸውን ይዘምሩለትና ውዳሴያቸውን ያቅራሩለት ነበር፡፡ ለዓባይ ወንዝ ይዘመር ከነበረው መዝሙር ከፊሉ እነሆ!
ለግብፅ ተሐድሶ ልትሰጥ ለመጣኸው ዓባይ፣
ክብርና ምስጋና ይገባሃል፣
ስትዘገይብን ሕይወት ሁሉ ቀጥ ይላል፣
ስትቆጣ ነጐድጓድ ያስገመግማል፡፡
ዓባይ ከተፍ ሲል መሬት በደስታ ትፈካለች፣
ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ በፍሥሐ ይፈነድቃሉ፡፡
የተትረፈረፈ ሲሳይ የምትመግበን አንተው ነህ፣
የተዋቡ ነገሮችን ሁሉ ታቀርብልናለህ፣
ወጣቶችና ሕፃናት በደስታ እየዘመሩ፣
ንጉሣችን ዓባይ እንኳን ደህና መጣህ ይሉሃል፡፡
ዓባይና ኢትዮጵያ
“የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው” የሚለው ብሂል ኢትዮጵያ በዓባይ ሀብቷ እስካሁን በምልዓት ላለመጠቀሟ በምሳሌነት ሲጠቀስ ኖሯል፡፡ እስካሁን የዓባይ ዙርያ ኅብረተሰብ በቂ የውኃ አቅርቦት በየደጃፉ እያገኘ አይደለም፡፡ የኤሌክትሪክ ብርሃንም እንዲሁ፡፡ መስኖአዊ እርሻንም እውን አላደረገም፡፡
እንደገሞራው አገላለጽ፣ እስከዚህኛው ዘመን ድረስ በዓባይ ወንዟ አንፃር፣ ሀገረ ኢትዮጵያ ለመንታ አፍሪካውያን አህጉራት [ሱዳንና ግብፅ] እህቶቿ ስትል፣ ከፍተኛ የዕርዳታ መስዋዕትነት ስትከፍል ኖራለች፡፡ መስዋዕት መባሉም፣ የራሷን ሕዝቦች እያስጠማች የለገሰችው በመሆኑ ነው፡፡ “ሥልጣኔ የመነጨው በውኃ ዳርቻ ላይ ነው” ቢባልም፣ የዓባይ ውኃ ምንጭ ባለቤት የሆነችዋ ኢትዮጵያ እንደሚፈስላቸው አገሮች ያሉ የፒራሚድ ሥልጣኔያዊ ትዕምርት አላነፀችም፡፡ የፈለገ ግዮን ልደቱም ሆነ መሠረቱ ምድረ ኢትዮጵያ በመሆኑ፣ በኢርቱዕ ንፃሬ ለታችኞቹ ሥልጣኔ ድርሻ ማበርከቱ የማይካድ ነው፡፡
“የብሩህ ተስፋና የሩቅ ምኞት አለኝታ ሆኖ፣ ለብዙኃን ኢትዮጵያውያን ወገኖች የህልውናቸው ዋስትና፣ የሕይወታቸው ኅብስተ መና ይሆናል ተብሎ እምነት የተጣለበት ዓባይ ወንዝ ነው፤” የሚለው ገሞራው በሌላው ገጹ እንዳሰመረበት፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብሯንና አገራዊ ይዘቷን ለማስከበር የሚያቅታት አይሆንም፡፡ ለዘመናት በዘፈቀደ ሲፈሱ የኖሩ ወንዞቿን ለማስከበር ልጆቿ ወደ ኋላ አይሉም፡፡
ሕዝቦቿ ይህን ነጥብ አስመልከተው፡
“በቆላው ሀገር ውስጥ ለሚቧርቅ ፈረስ፣
በታችኛው ምድር ለሚፈነጭ ፈረስ፣
እንደዠማ ውኃ በመስክ ለሚደንስ፣
ልጓሙ ደጋ ነው ከያዙት የማይፈስ…” እያሉ ቢዘምሩ ብሒላቸው ላያስደንቅ ነው፡፡
የገሞራው ጸሎት
ከቤተ ክርስቲያን የ”አባታችን ሆይ” ጸሎት በመነሳት በኢትዮጵያ “መሪዎች ነን” ባዮች ቅድመ አብዮት “አባታችን ብሬዥኔቭ ሆይ…”፣ ድኅረ አብዮትም “አባታችን ጆርጅ ቡሽ ሆይ…” የሚባል ጸሎት ማላዘናቸውን ያስታወሰው ገሞራው፣ “አማራጭና ተገቢ ጸሎት” ያለውንና በወንዘ ዓባይ ላይ ያቀናበረውን ከ31 ዓመታ በፊት እንዲህ ጸልዮታል፡፡ አስተጋብቶታልም፡፡

አማራጭና ተገቢ ጸሎት
አባታችን የዓባይ ወንዝ ፈጣሪ ሆይ!
በጣና ሐይቅና በሰሜን ኢትዮጵያ የምትኖር!
ስምህ ይቀደስ!
ፈቃድህ በምድረ ሱዳንና በምድረ ግብፅ እንደሆነ ሁሉ!
እንዲሁም በመላዋ ምድረ
ኢትዮጵያም ይሁን!
የዓመት የውኃ ጠለ ምሕረትህን ስጠን ዛሬ!
ለሚቀጥሉት ዓመታት በየግድቦቹና በየመስኖዎቹ ውስጥ አስቀምጥልን!
ከዝናብ ማጣትና ከአፈራችን መጋዝ ይቅር በለን!
የምንጠጣውም ውኃ ሆነ የምናበቅልበት አፈር የለንምና!
ከሀሩር ድርቀት አርቀን!
ወደ ምድረ በዳነት አታግባን!
አርጣቢዋ ውኃ የአንተ ናትና!
ኃይልና ሥልጣን ከነችሎታው!
ለዘለዓለም ይኑር!