በብዛት የአዲስ አበባ ጥግ ላይ ቆመው ሲተክዙ ይታያሉ፡፡ የሆነ ነገር በመጠበቅ ላይ ያሉም ይመስላሉ፡፡ እንቅስቃሴ የላቸውም በዚያው ተፈጥረው እዚያው ኖረው እዚያው የሚሞቱ ነው የሚመስሉት፡፡ ነገር ግን ሀቁ ሌላ ነው፡፡
ብዙ አገልግሎት ሰጥተውና ብዙ ተጎድተው የተጣሉ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ እንዲያውም ዝንብ እንደወረራቸው ነግቶ ይመሽባቸዋል፡፡ ፈረሶች ከቤት እንስሳት መሀል ይጠቀሳሉ፡፡ ሰፊ አገልግሎት በመስጠትም ይታወቃሉ፡፡ በተለይ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ መሠረት ናቸው፡፡
ለመጓጓዣና ለስፖርታዊ ውድድሮች፣ ለሰርግ ማድመቂያ አልፎም በጦርነት ከመሳተፍ ጀምሮ፣ ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች መሀል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ነገር ግን እኚህን እንስሳት ኅብረተሰቡ ከተገለገለባቸው በኋላ እንደ አሮጌ ዕቃ በየአስፋልቱና በየሰፈር ውስጥ ተጥለው ማየት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ የሚጣሉ ፈረሶች በዕድሜ የገፉ ናቸው፡፡ የጅብ ራት እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ እነዚህ እንስሳት መሞታቸው ላይቀር ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸዋል፡፡
ሸዋይነሽ አፈወርቅ (ዶ/ር) በጋማ እንስሳት ዙሪያ አተኩሮ በሚሠራው ብሩክ ኢትዮጵያ የደቡብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የእንስሳሳት ጤና አስተባባሪ ናቸው፡፡ ከላይ ለተጠቀሰው የእንስሳት ስቃይ ሳይንሳዊ መፍትሔ አለ ይላሉ፡፡ ይኼም ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንስሳቱን ማስወገድ ነው፡፡
ዩቲኔዥያ ወይም ሜርሲ ኪሊንግ ይሉታል፡፡ ይህም ማለት ያለ ምንም ስቃይ ማስወገድ ወይም መግደል ነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት እነዚህ እንስሳት መንገድ ላይ በሚቆሙ ጊዜ ከራሳቸው ስቃይ ባለፈ ለኅብረተሰቡም የጤና ጠንቅ ይሆናሉ ቁስል ስለሚኖራቸው ይሸታሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ለጉንፋንና ለተለያየ በሽታ ይዳርጋሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ ለትራፊክ አደጋም ምቹ አጋጣሚን ይፈጥራሉ ብለዋል፡፡
ሸዋይነሽ (ዶ/ር) እንደሚሉት ዩቲኔዥያ ለመጀመርያ ጊዜ የተተገበረው ሀላባ ከተማ ላይ ነው፡፡ ለመጀመራቸውም ምክንያት የነበረው የማኅበረሰቡ ልምድ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ ‹‹ልምዳቸው የነበረው የታመሙ እንዲሁም አገልግሎት ሰጥተው የደከሙ የጋማ ከብቶችን አውጥተው መጣል ነበር›› ይላሉ፡፡ አውጥተው በሚጥሏቸው ጊዜም ዕድላቸው በጅብ ተበልቶ መሞት ነበር፡፡ መሞታቸው ላይቀርም ይሰቃያሉ፡፡ ‹‹መሞታቸው ላይቀር ሳይሰቃዩ በአንድ ጊዜ ይረፉ የሚለው ሳይንስ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ወደ ሦስት ዓመት ያህል ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይት አደረግን፡፡ በመጀመሪያ የነበረው መልስ ፍፁም አይሆንም የሚል ነበር፡፡ እንዴት እንስሳ እንገላለን፣ ይኼ በፈጣሪም ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ ኃጢአት ነው በማለት አሻፈረኝ አሉ፤›› ይላሉ፡፡ ኋላ ግን መተማመን ላይ መድረሳቸውን አውስተዋል፡፡
በዚያን ወቅት በሀላባ ከተማ ከአሥር እስከ አሥራ አምስት የጋማ ከብቶችን በቀን ይጣሉ ነበር፡፡ ከተማው በጣም ይሸት ነበር፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር ግን መግባባት ሲጀመር ማዘጋጃ ቤትም ይህን ሐሳብ ሲቀበል ሕግ ወጣ፡፡ ሕጉም የተጣሉት እንስሶች በሰላሙ መንገድ እንዲያርፉ፣ ማዘጋጃ ቤቱም ኃላፊነቱን ወሰዶ የመቅበሪያ ቦታ እንዲያዘጋጅ ነው፡፡
ብሩክ ኢትዮጵያ የተባለው ግብረሰናይ ድርጅትም ይህን ኃላፊነት በመውሰድ ለመንግሥት ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠትና የመድኃኒት አቅርቦቱን መነሻ በመቻል ይህንን አገልግሎት አስጀመረ፡፡ በመቀጠልም ማዘጋጃ ቤቱ መድኃኒት በራሱ ወጪ እየገዛ እንስሳቱ እንዲወገዱ ተደርጎ ሀላባ ንፁህ ውብ ከተማ ልትሆን ትችላለች ብለዋል፡፡ ይህም ሥራ በሌሎች ከተሞችና አካባቢዎች ላይ እንዲስፋፋ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ሌላው ያነሱት በመንግሥትም ሆነ በግል ስለጋማ ከብት በቂ ትኩረት አለመኖሩንና በዚህም በቂ የመድኃኒት አቅርቦት አለመኖር ነው፡፡ በየጤና ኬላውና በየወረዳው የመድኃኒት አገዛዝ ሥርዓቱ የወደቀ ነው ይላሉ፡፡
‹‹ለነዚህ እንስሳት በቂ ትኩረት ካለመስጠት የተነሳ ለራሳቸው የሚሆን መድኃኒት ለማግኘት ባለመቻሉ የምንጠቀመው የሰው መድኃኒት ነው፡፡›› ከሰው ልጅ ጋር የሰውነት አወቃቀራቸው ተመሳሳይ በመሆኑ የሰው ልጅን መድኃኒት እንዲወስዱ የምናደርግ ቢሆንም ሁሉንም አይወስዱም ይላሉ፡፡
‹‹አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር ከውጭ የሚገባ የጋማ እንስሳት ላይ ትኩረት ያደረገ የመድኃኒት አቅርቦት ያለመኖሩ ነው፣ እዚህ ላይም ብሩክ ኢትዮጵያ እየሠራበት ይገኛል፤›› በማለት ለጊዜው ግን ከሰው መጋራት የሚቻለውን እየወሰድን እየሠራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ የሳንባ ምች፣ የዓይን በሽታ እንዲሁም “የአፍሪካ ፈረሶች በሽታ” የሚባሉት በሽቶች በአብዛኛው እንደሚያጠቃቸው ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ፈረሶች በሽታ መድኃኒት የለውም፡፡ በክትባት የሚከታተሉት የበሽታ ዓይነት ነው፡፡ መንግሥት ክትባቱን በነፃ ያቀርባል፡፡ በየጊዜው ጠብቆ የማሰከተብ ኃላፊነትም የማኅበረሰቡ ነው፡፡ ሌላው ክትባትም ሆነ ምንም መፍትሔ የሌለው ሉፈንጃይክስ የሚባል በሽታ ነው፡፡
ይህ የበሽታ ዓይነት ሰውነታቸውን በማቁሰል የሚያጠቃ ነው፡፡ የዚህ በሽታ ዋነኛ መተላለፊያ ዝንብ ነው፡፡ እነኚህ እንስሳት ሠራተኛ እንስሳት ስለሆኑ ከመጫኛም እንዲሁም ከተለያየ ነገር የተነሳ ይቆስላሉ፡፡ በሽታው ያለበት እንስሳ ላይ ያረፈ ዝንብ መጥቶ እነዚህ ፈረሶች ላይ ካረፈም ለዚህ በሽታ ይጋለጣሉ፡፡
ይህንንም ከመከላል አንፃር የተሻለ መጫኛ እንዲጠቀሙና እንሰሳው እንዳይጎዳ ብሩክ ኢትዮጵያ ትምህርት እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ ቁስል ሁሉ የማይድን ነው ማለት እንደማይቻል በመናገር ቁስል በቀላሉ በማጠብና ቫዝሊን በመቀባት ሊድን ይችላል ብለዋል፡፡
እኚህን እንስሳት ከመታደግ አንፃር ሁሉም ማኅበረሰብ የበኩሉን እንዲያደርግም ሸዋይነሽ (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል፡፡