በዓለም ላይ በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ ወረርሽኞች ተነስተው በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሰው ልጆች ሕይወትን ቀጥፈዋል፡፡ከሶስተኛው ክፍለዘመን ጀምር ተቀስቅሶ የነበረው የፈንጣጣ ወረርሽኝ፣ ከምድረገጽ እስከጠፋበት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕይወት ቀጥፏል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀውና የኅዳር ወር በገባ በ12ኛው ቀን ንጋት ላይ በየደጁም ሆነ በየአካባቢው ያለውን ቆሻሻ ሰብስቦ ያቃጥላል፡፡ ይህም “ሕዳር ሲታጠን” እየተባለ ከሚነገረው በቀር ምክንያቱ ያን ያህል ትኩረት ተሰጥቶት ሢነገር አይሰማም፡፡ዋናው ምክንያት ግን ከ100 ዓመታት በፊት በ1911 ዓ.ም ተከስቶ ከነበረ ወረርሽኝ ጋር የተያያዘ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያስርዳሉ፡፡ ወረርሽኑ በመነሻው ሃገር ስም ስያሜ ተሰጥቶት የነበረው “ስፓኒሽ ፍሉ” (የሕዳር ወረርሽኝ) ሲሆን በተለይ በአውሮፓ ከ50 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን መግደሉም ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያም በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከአስር ሺ በላይ ሰዎችን መግደሉም ይገለጻል፡፡ወረርሽኙ ሰው በተቀመጠበትና በተኛበት ይሞት እንደነበርና እጅግ አስከፊ ጊዜ እንደነበርም ይነገራል፡፡ይኸ አስከፊ ወረርሽኝ በተለይ በኢትዮጵያ በባህላዊ መድሃኒቶችና ድርጊቶች ሙሉ በሙሉ የጠፋበት ቀን ሕዳር 12 በመሆኑና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የዓለም ሕዝብ ያለቀበት ያልተመዘገበ የሰማዕታት ቀን በመሆኑ በየዓመቱ እየታሰበ ቀጥሏል፡፡ ከ100 ዓመታት በኋላ ዓለምን ያዳረሰና በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ መጋቢት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ከ30 ሺ በላይ ሰዎችን የገደለ ወረርሽኝ ተነስቶ ዓለምን ከፍተኛ ጭንቀት ውሰጥ ከቷታል፡፡
በታህሣሥ ወር መጨረሻ በቻይናዋ ሁቤ ግዛት ዉሃን ከተማ ምንነቱ ካልታወቀ መነሻ የተቀሰቀሰው ወረርሽኝ፣ መተንፈሻ አካልን በማጥቃት ለሰዎች ህመምና ሞት ምክንያት በመሆንየመከሰቱ ዜና ከተሰማ 90 ቀናትን ወይም ሦስት ወራትን አስቆጥሯል፡፡ ይህንን በሽታ ባለሙያዎች ኮቪድ-19 የሚል መጠሪያ የሰጡት ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ወረርሽኝ ብሎታል፡፡በአጭር ጊዜ ውስጥ የጉዳቱ ስፋትና ስርጭት በዓለም አገሮች በመዳረሱና የሰውን ዘር፣ ቀለም፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ የቴክኖሎጂ ልህቀት፣ ሀብት ወዘተ…ሳይመርጥና ሳይለይ እየፈጀ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የምድራችን ፈተና ሆኗል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ዓለም ላይ አደገኛ በሚባል ደረጃ መሰራጨቱን ተከቶሎ የዓለም የጤና ድርጅት በበሽታዉ መጠነ ሰፊ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ይፋ አድርጎ፤ የዓለም ሀገራት በሽታዉን ለመቆጣጠር በፍጥነትና በጥንካሬ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ እያሳሰባ ሲሆን፣ እስከ መጋቢት መካተቻ ድረስ በዓለም ደረጃ ከ600ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው፣ ከ134 ሺሕ በላይ ማገገም ሲችሉ፣ 30ሺሕ ገደማ በቫይረሱ ህይወታቸዉ ማለፉ ታውቋል፡፡ ምንም እንኳ ሰሞኑን የሀገራችን የባህልና የጤና ሳይንስ በጋራ ባደረጉት ምርምር የመጀመሪያውን ደረጃ ያለፈ መድሀኒት እያገኙ መሆኑና በመላዉ ዓለም የሚገኙ ተመራማሪዎች የተለያዩ ተስፋ ሰጭ ግኝቶችን ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም፤ ይህ የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት የሰውን ሕይወት የሚነጥቀው የኮሮና ቫይረስ እስካሁን ምንም አይነት ክትባትም ሆነ መድሀኒት አልተገኘለትም፡፡
ቫይረሱ የዓለማችንን ታላላቅ ሀገራትን ሳይቀር ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አደጋ እየዳረጋቸዉና አለምን በእጅጉ እየናጣት ይገኛል፡፡ ቫይረሱ በቻይና ሀገር የነበረዉ ስርጭት እየቀነሰ ቢሆንም እንደ ጣሊያን፤ኢራን፤ስፔን፤አሜሪካ፤ጀርመንና ከ46 በላይ የአፍሪካ አገራት ወረርሽኙ በፍጥነት አየተስፋፋና ከአንድ ሀገር ወደ ሌሎች ሀገራት በሚያቀኑ ተጓዦች አማካይት እየተሰራጨ እየገደለም ነው፡፡ አህጉራችን አፍሪካ ቫይረሱ ዘግይቶ የታየባት አህጉር ስትሆን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የቫይረሱ ተጠቂ የተገኘባት የአፍሪካ ሀገርም ግብፅ ነበረች፡፡ እስካሁን ባለዉ መረጃ መሰረት የኮሮና ቫይረስ በ47 አገሮች ውስጥ ሲሰራጭ ከ2000 በላይ ሰዎች በበሽታዉ ተጠቅተው በርካቶች ህይወታቸዉ አልፏል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጲያ በጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጲያ ህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲቲዩት ጥምረት አማካኝነት የተለያዩ የቅድመ መከላከያ ሥርዓት ዘርግታ ቫይረሱ እንዳይከሰት ተግባራትን ስታከናዉን ብትቆይም፤ ዘግይታም ቢሆን በኮሮና ቫይረስ ከመጠቃት አላመለጠችም፡፡መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚነስቴር በኢትዮጲያ የመጀመሪያዉ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ በአዲስ አበባ መገኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡መግለጫዉን ተከትሎም በመላ ሀገሪቱ አስደንጋጭ ስሜት ተፈጥሯል፡፡ በተለይ በመዲናች አዲስ አበባ በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የመረበሽና የመደናገጥ ስሜት ታይቶ ነበር፡፡በቀናት ዉስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ያሳየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጲያ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 19 መድረሳቸዉን የጤና ሚስቴር አስታውቋል፡፡ እስካሁን ባለዉ መረጃ መሰረት በሽዎች የሚቆጠሩ ናሙናዎች የCOVID-19 ላብራቶሪ ምርመራ ተደርጓል፡፡
መንግስት ስርጭቱን ለመግታት ሕዝቡ መውሰድ አለበት ያላቸውን ጥንቃቄዎች፤ መመሪያዎችን በማስተላለፍ፤ ዜጎች ራሳቸዉንና ቤተሰባቸዉን ከቫይረሱ አንዲጠብቁ በተለያዩ መንገዶች ቢያሳስብም፤በከተማዋ የሚስተዋሉ የዉሃና የመብራት አቅርቦት፤የህዝብ ትራንሰፖርት፤የዋጋ ንረት እና መሰል ችግሮች ከማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ተደምሮ የበሽታዉን ስርጭት የመከላከሉን ስራ በሚፈለገዉ ደረጃ ለማከናወን ግን እንቅፋት ገጥሞታል፡፡የበሽታውን መስፋፋት በፍጥነት ለመግታትና ሥርጭቱን ለመከታተል ይረዳ ዘንድም የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ትልልቅ ስብሰባዎችና ስፖርታዊ ክንዋኔዎች እንዲዘጉ፤በጣም ከሚፈለጉ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በስተቀር የመንግስትም ሠራተኞችም በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ በመንግስት ዉሳኔ የተላለፈ ሲሆን፤ ማናኛዉም ከዉጭ የሚመጣ ተጓዥ ለ14 ቀን በተዘጋጁ ሆቴሎችና ማቆያ ቦታዎች በራሱ ወጭና በመንግስት ወጪ ተለይቶ እንዲቆይም ተወስኗል፡፡ይሁን እንጅ በከተማዋ የቫይረሱን ስርጭት ከመግታት አንጻር እየታየ ያለዉ መዘናጋት የቫይረሱን ስርጭት ከቁጥጥር ዉጭ እንዲወጣ በማድረግ፤ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ እንዳያስከፍል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ እጅን መታጠብ ላይ የተሻለ ለውጥ ቢታይም፤አካላዊ ርቀትን መጠበቅ(Social distancing ፤እቤት መቆየት፤አላስፈላጊ መሰባሰብን ከማስዎገድና የህዝብ ትራንስፖርት አጠቃቀም ላይ ግን ከፍተኛ ክፍተት ይታያል፡፡በመንግስት ተቋማት ሳይቀር የሚካሄዱ ስብሰባዎችና መሰል ተግባራት ምንም አይነት ጥንቃቄ ሳይደረግባቸዉ ቀጥለው የነበረ ቢሆንም አሁን አሁነ የተሸለ ሁኔታ ይታያል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የበሽታዉን ስርጭት በተመለከተ እንዳስታወቁት
“አፍሪካውያን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ ሊከሰት ለሚችል የከፋ ሁኔታ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው”
ሲሉ መደመጣቸዉ በአህጉሪቱ እየተከናወነ ያለዉ የመከላከል ተግባርና ዝግጁነት ከቫይረሱ ባህሪና ስርጭት አንፃር እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነም ያመላከተ ነበር፡፡በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት በሚደረገዉ ጥረት ላይ እንቅፋት ከነበሩት ሁኔታዎች መካከል፤ ቫይረሱን በሚመለከት የሚተላለፉ የተዛቡ መረጃዎች በስፋት መሰራጨት ነበር፡፡ ስለ በሽታዉ አመጣጥ ከሚሰነዘሩ የተለያዩ መላምቶች (Conspiracies) አንስቶ ቫይረሱን ያድናሉ ተብለዉ ጥቅም ላይ እየዋሉ ስላሉ እፆች፤ በማህበራዊ ሚዲያዉ በስፋት እየተዘዋወሩ በርካቶቸን ላልተገባ መደናገር እየዳረጉ ይገኛል፡፡ በሀገራችንም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ባህላዊ መድሀኒቶች በመጠቀም ቫይረሱን ማዳን እንደሚቻል የሚገልጽ መረጃ በትስስር ገጾች በመሰራጨቱ በማህረሰቡ ዉስጥ ዉዥንብር ፈጥሯል፡፡ከማህበራዊ ሚዲያዉ በተጨማሪ አንዳንድ መገናኛ ብዙሀን ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ሳይቀሩ፤ ስለ ቫይረሱ የሚዘግቡበት መንገድ ህብረተሰቡን ወደ ባሰ ጭንቀትና ፍርሀት የሚያስገባ፤ ሀላፊነት የጎደለዉ አንደነበርም ተስተዉሏል፡፡ ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸዉ፤ስለ ወረርሽኙ መጥፎ ነገሮች ላይ ይበልጥ ያተኮሩ መረጃዎች የሚሰራጩበት ሁኔታም አለ፡፡ ከበሽታዉ ራስን በቀላሉ መጠበቅ ስለሚቻልባቸዉ የመከላከያ መንገዶችም ሆነ ከቫይረሱ አገግሞ መዳን የሚነገሩ ሳይንሳዊ መረጃዎች ብዙም ትኩረት እንዳልተሰጣቸዉም ይስተዋላል፡፡እንዲህ ያሉ አደጋዎቸ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ የሚኖረዉ ሚና የማይተካ መሆኑ ላይ አፅንዖት በመስጠት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡መረጃ ወረርሽኙን ለመከላከል ትልቅ ድርሻ አለዉ፡፡ ስለበሽታዉ የሚወጡ መረጃዎች የቫይረሱን ጉዳት በጣም የሚያካብዱ ወይንም ደግሞ ባልተፈለገ መልኩ አቅልለዉ የሚያሳዩ መሆን እንደሌለባቸዉ የዓለም ጤና ድርጅት ጀነራል ዳይሬክተር አሳስበዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ስርጭቱ እየጨመረ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያደርሰዉ ጉዳት በጤና ላይ ብቻ ተወስኖ እንደማይቀር የአለምአቀፉ ተሞክሮ አሳይቷል፡፡የቫይረሱ ስርጭት በተስፋፋባቸዉ በርካታ የዓለም ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡የምርት መቀነስ ችግር፤ የአቅርቦት ሰንሰለት እክል፤የወጭና የገቢ ንግድ ስራዎች መዳከም፤ የስራ አጥነት ችግር፤ የገቢ መቀነስ፤ የምርት አቅርቦት ችግር፤ የዋጋ ግሽበት መታየት በበርካታ ሀገራት እያጋጠሙ ካሉ የኢኮኖሚ ችግሮች ዉስጥ ጥቂቶቹ ናቸዉ፡፡
በኢትዮጲያ የመጀመሪያዉ የቫይረሱ ተጠቂ መገኘቱን ተከትሎ በተለይ በአዲስ አበባ ዜናዉ በተሰማ በጥቂት ሰዓታት ዉስጥ ፍርሀትና ድንጋጤ የገባቸዉ የከተማዉ ነዋሪዎች የምግብና የንፅህና ዕቃዎችን ለመግዛት፤ በሱፐር ማርኬቶችና በሱቆች በገፍ በመዉጣታቸው የታየዉ የዋጋ ማሻቀብ በርካቶችን ያስደነገጠ ነበር፡፡በድንጋጤ የወጣው ሕዝብና የተፈጸመው የገፍ ግዥ አንዳንድ ነጋዴዎች በምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዲያደርጉና የምርት እጥረት እንዲያጋጥም ምክኒያት ሆኗል፡፡ በየፋርማሲዉና በገበያ ቦታዎች ይታዩ የነበሩ ሰልፎችና ግርግሮች ቫይረሱ በቀላሉ እንዲዛመት አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡እንዲህ ያለዉ ክስተት ቫይረሱ በታየባቸዉ በርካታ የዓለም ሀገራት የታየ ሲሆን፤ መንግስታት ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስዱ ታይተዋል፡፡ በሀገራችንም በተለይ በአዲስ አበባ ለተከሰተዉ የዋጋ ጭማሪና ተፈጥሯዊ ያልሆነ የምርት ዕጥረት፤ በከተማ አስተዳደሩ የተወሰደዉ ፈጣን እርምጃ አበረታች ነበር፡፡ ችግሩ በታየ በቀናት ዉስጥ ብቻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በሽ የሚቆጠሩ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፈሰር የሆኑት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር)፤ አብዛኛዉን ዜጋ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኝባት ሀገር የወረርሽኙ ስርጭት ከጤና ጉዳይ በተጨማሪ የከፋ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረና በሽታ እየተስፋፋ ከሄደም በተጨማሪም፤ አምራቹ የህብረተሰብ ክፍል ላይ የሚያደርሰዉን ጉዳት ተከትሎ በተለያዩ አምራች ኢንደስትሪዎችም ይሁን በግብርናዉ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ የሆነ የምርት ማሽቆልቆልና የአቅርቦት ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ስጋታቸዉን ያስቀምጣሉ፡፡ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግስት መጠባበቂያ የሚሆን መሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችን ማከማቸትና ለህብረተሰቡ ፈጥኖ ተደራሽ የሚሆንበትን ስርዓት ከወዲሁ መዘርጋት፤ የአምራች ዘርፉን እንቅስቃሴ በቅርበት በመከታተል አስፈላጊዉን ድጋፍ መስጠት፤ ከተለያዩ ምንጮች የሚገኘዉን የገንዘብ ድጋፍ በብሔራዊ ደረጃ ወደ አንድ ቋት (ለምሳሌ FUND-COVID-19) በማሰባሰብ ፈንዱ ተጠያቂነት ባለዉ መልኩ ለሚፈለገዉ አላማ እንዲዉል ማድረግ ሊጋጥም የሚችለዉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና መቀነስ እንደሚቻል ለሪፖርተር መጽሄት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በሽታዉ በኢኮኖሚዉ ላይ ሊያስከትል የሚችለዉን ተፅዕኖ በዝርዝር ለመመልከትና ተገቢዉን እርምጃ ለመዉሰድ ጥናት እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ቀጥተኛ ተጠቂ ከሆኑት የሥራ ዘርፎች ዉስጥ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት አንዱ ነዉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ሆቴሎች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ለኪሳራ መዳረጋቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል ሀገራት ባወጡት የጉዞ ክልከላ ሳቢያ የቱሪዝም ፍሰት በማሽቆልቆሉ፤ ስብሰባዎች በመከልከላቸዉና የሰዎች እንቅስቃሴ በከፍተኛ መጠን በመቀነሱ፤የሆቴሎች ገበያ 50 በመቶ ያህል መቀነሱንም ይፋ አድርገዋል፡፡የወጪ ጫናቸውን ለመቀነስም ሠራተኞች የዓመት ዕረፍት እንዲወጡ እያደረጉ መሆኑንም አስታዉቀዋል ።
አቶ አዲስ አለማየሁ “251 ኮሙዩኒኬሽን” የተሰኘ የፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ፤ የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱን ተከትሎ ድርጅታቸዉ ሊያካሂዳቸዉ ተቆርጦላቸዉ የነበሩ ሁነቶችን ሙሉ በሙሉ መሰረዙን ይናገራሉ፡፡ በቫይረሱ ምክኒያት ሊፈጠር የሚችለዉ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት መታየት የሚጀምረዉ ከወራት በኋላ ቢሆንም፤እነሱ በተሰማሩበት የኤቨንትና የማርኬቲንግ የሥራ ዘርፍ ላይ ግን ተጽዕኖዉ በፍጥነት መታየት መጀመሩን ናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከ 80 በላይ መዳረሻዎቹን ወይም በረራዎቹን ለማቆም ተገዷል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ190 ሚሊዮን ዶላር በላይ መክሰሩን አስቴውቋል፡፡በአቬዬሽን ታሪክ ውስጥ እንዲህ አይነት የከፋ ችግር ታይቶ እንደማይታወቅም ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገበረማሪያም ተናገረዋል፡፡ ኢዮብ ተስፋዬ (ደ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚክስ ምሁር ናቸዉ፡፡የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ብሎም በዓለም ላይ የሚኖረዉ ስርጭትና ጉዳት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰዉን ጫና ለሪፖርተር መፅሔት እንደገለጹት፤ኢትዮጲያ ከቀሪዉ ዓለም ጋር በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት፤የአውሮፕላን በረራዎችን ጨምሮ በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች ከተቀረው ዓለም ጋር ትስስር ያላት ሃገር በመሆኗ፤ ወረርሽኙ በመላዉ አለም ባደረሰዉ ጉዳት መጠን በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረና የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት እንዲያሽቆለቁል እያደረገ ነዉ፡፡የዓለም የሸቀጦች አቅርቦት ሰንሰለቶች መቋረጥ፣ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን በነዳጅ፣ በቱሪዝም፤በአቬየሽንእና በውጪ ምንዛሪ ግኝት ረገድ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረም ገልፀዋል።ይባስ ብሎ በሽታዉ በሀገራችን መታየቱና መሰራጨት መጀመሩ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ እንዲወሳሰብ የሚያደርገዉ እንደሆነና የሀገር ዉስጥ ንግድ አለመጣጣም (trade deficit) እና የመንግስት በጀት እጥረት ሊጋለጥ አንደሚችል አስረድተዋል፡፡ሀገሪቱ ያለባትን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመጣጣም ለማስተካከል እየታገለች ባለችበት በዚህ ሰዓት፤ እንዲህ ያለ ያልታሰበ አደጋ ማጋጠሙ ችግሩን ይበልጥ ያከብደዋል ሲሉ ምሁሩ ይናገራሉ፡፡
በሽታው እያስከተለ የሚገኘው ቀውስ እያየለ በመምጣቱ በርካታ አምራቾችና ላኪዎች የገጠማቸውን የገበያ ቀውስ ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡ አበባ አምራቾችና ላኪዎች የአውሮፓ አገሮች ድንበሮቻቸውን በመዝጋታቸው፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ ገድበውና ከቤት እንዳይወጡ አግደው ምንም ዓይነት የግብይትም ሆነ የእንቅስቃሴ መስተጋብር እንዳይኖር በመከልከላቸው ሳቢያ፤ ከፍተኛ የአበባ ምርት ብልሽት በኢትዮጵያ ተከስቷል፡፡ ቡና ላኪዎችም ሳይወጣ የተከማቸ ቡና ገበያ የማጣቱ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
አምራቾች የገጠማቸው የገበያ ችግር ህልውናቸውን እንደሚፈታተነው በመግለጽ፣ ሠራተኞቻቸውን እንዳይበትኑ፣ የብድር ክፍያ ማራዘሚያ እንዲደረግላቸው፣ የሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲሰጣቸውና የብድር ወለድ እንዳይታሰብባቸው ጠይቀዋል፡፡ መንግሥትም በኢኮኖሚው ላይ ሊመጣ የሚችለውን ቀውስ፤ የአበባ ላኪዎችን ሥጋት በማዳመጥ የ15 ቢሊዮን ብር የኢኮኖሚ ማገገሚያ ድጋፍ እንዲደረግ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴርም ለአስፈላጊ ፍጆታዎችና ለምግብ ሸቀጦች ግዥ የሚውል የአምስት ቢሊዮን ብር በጀት እንዲያዘጋጅ ታዟል፡፡ በጠቅላላው ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የኮሮና ቫይረስ መከላከለያ በጀት መመደቡን መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡
አፍሪካ ከ10 እስከ 150 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ማስታወቋና ይህ ድጋፍም ከዓለም ኃያል አገሮች እንዲሰጣት መጠየቋ ይታወሳል፡፡ የቡድን 20 አገሮች ለዓለም ኢኮኖሚ ድጋፍ የሚውል የአምስት ትሪሊዮን ዶላር በጀት እንዲለቀቅ ሲስማሙ፣ አሜሪካ የጦርነት ጊዜ በጀት ያለችውን የ2.2 ትሪሊዮን ዶላር አስቸኳያ የድጋፍ ፓኬጅ አጽድቃለች፡፡
ምንም እንኳ እንዲህ ያሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚዉን ላይ ተጽዕኖ የሚያደርሱ አደጋዎችን በቀላሉ መመከት እንደ ኢትየጵያ ላለ ያልጠነከረ ኢኮኖሚ ፈታኝ ቢሆንም፤ ከአሁኑ ጀምሮ የዉጭ ምንዛሪን በአግባቡ በመጠቀም፤ ከለጋሽ ሀገራትና ከአበዳሪ ተቋማት የሚገኝን ገንዘብ በአግባቡ በማስተዳደር፤ ቅድሚያ ሊሰጡ ለሚገባቸዉ ተግባራት ማዋል በወረርሽኙ ሳቢያ ሊከሰት የሚችለዉን ኢሚኮኖሚዊ ጫና ለመቀነስ አንዱ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም መንግስት ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል፡፡
የዓለም ሀገራ በሽታዉን ለመግታት የተለያዪ ጥረቶችን ቢያደርጉም ከወረርሽኙ ፍጥነት አንጻር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ይህ ነዉ የሚባል ዉጤት ማስመዝገብ አልቻሉም፡፡ይሁን እንጅ ወረርሽኙ ከተነሳባት ቻይና በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ እንደ ሲንጋፖር፤ ሆንግ ኮንግና ታይዋን ያሉ የኤዥያ ሀገራት በወሰዷቸዉ ጠንካራ የመከላከል ርምጃዎች የቫይረሱን ስርጭት በሚደንቅ መልኩ መቀነስ እንደቻሉ ታይቷል፡፡ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ከገባንበት መደናገጥና ድንዛዜ በአፋጣኝ በመዉጣት የመከላከል ስራዉን ዉጤታማ በሆነ መልኩ ለመከወን መነሳት ይገባናል፡፡
በመንግስትም ሆነ በተለያዩ አካላት እየተካሄዱ ያሉ የመከላከል ተግባራት እንዳሉ ሆነዉ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንደሀገር የሚከናወኑ ተግባራት በተቀናጁና ሳይናሳዊ በሆኑ መንገዶች የተከተሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያመለክቱት በርካታ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸዉንና እንቅስቃሴ የሚበዛባቸውን(የእምነት ተቋማትን ጨምሮ) ለጊዜዉ ዝግ በማድረግ መቀነስ፤ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ሰራተኞች አስገዳጅ ካልሆነ በስተቀር በቤታቸዉ ሆነዉ እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የቫይረሱን ምርመራ በስፋት በማካሄድና ተጠቂዎችን በመለየት፤ ለህብረተሰቡ ወጥና በቂ የሆነ መረጃ በየጊዜዉ በመስጠት የቫይረሱን የስርጭት ፍጥነት መቀነስ ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ላይ የመጣ ትልቅ ፈተና መሆኑን በመረዳት፤ ሁሉም ዜጋ ሀላፊነት ተሰምቶት የበኩሉን ድርሻ መወጣት የሚስፈልግበት ጊዜ ነዉ፡፡በተለይ ወጣቱ በተስስር ገጾች የሚሰራጩትን “ሕጻናትንና ወጣቶችን አያጠቃም” የሚሉ የሃሰት ትርክቶችን ሳይከትል፤ጤና ሚኒስቴር፤ የሕብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲቲዩትና የዓለም ጤና ድርጅት የሚያስተላልፉትን መረጃ ብቻ በመከተል የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት፡፡ ለማንኛውመም የለውጥ ሂደት ቅርብና ዝግጁ ከመሆኑ አንጻር በየአካባቢው ያለውን ዜጋ መርዳትና ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ማስገንዘብ አለበት፡፡ የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) መነሻ የሆነችው ቻይናም ሆነች በስፋት የተሰራጨባቸው ሌሎች የዓለም ሀገራት ሆን ብለው ያመጡት በሽታ አይደለም፡፡በመሆኑም ወጣቱ በተልይ በኛ ኢትዮጵያውያን ያልተለመደና ነውር የሆነውን የማግለልና አካላዊ ጥቃት ከማድረስ አጸያፊ ተግባር መራቅና መጠየፍ አለበት፡፡ርቀትን ጠብቆ በመንቀሳቀስ፤ባለመጨባበጥና ባለመተቃቀፍ፤በቤት ውስጥ ሆኖ ሥራን በማከናወንና አጅን በሳሙና በመታጠብ፤ ኮሮና ቫይረስን መከላከል ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታም ነው፡፡