በመሐሪ መኰንን (ዶ/ር)
በሪፖርተር መጽሔት ቅጽ 1 ቁጥር 02 ስለሀገራችን የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት አንድ ጽሁፍ አቅርቤ ነበር፡፡ በዚህ ጽሁፍ የአንድ ሀገር የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት መለኪያ የሆኑትን የፋይናንስ ተቋማት እና የፋይናንስ ገበያን በአሰራር ጥልቀታቸው፣ በተደራሽነታቸው እና በቅልጥፍናቸው ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡በትንተናው አሁን በሀገራችን ያለው አጠቃላይ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት እምብዛም የሚመሰገን እንዳልሆነ ተገልቷል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት የሀገራችን ፋይናንስ ተቋማት ከፋይናንስ ገበያው በተሻለ ዕድገት እንዳሳዩም ተጠቁሟል፡፡ ይህ እድገት ከጠቅላላ የአፍሪካ ሀገራትም ሆነ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የፋይናንስ እንቅስቃሴ ዕድገት አንጻር ሲታይ እጅግ አነስተኛ እንደሆነም ተብራርቷል፡፡በሀገራችን በሰፊው የሚታወቁት የፋይናንስ ተቋማት ባንኮች፣ የመድን ድርጅቶች፣ ብድርና ቁጠባ ማህበራት እና አነስተኛ (ማይክሮ)የፋይናንስ ተቋማት ናቸው፡፡ከእነዚህ ውስጥ የገበያውን ሰፊ ድርሻ የያዙትን የባንኮችን እንቅስቃሴና ዕድገትን በሚመለከትም ተዳስሷል፡፡ የዛሬው ጽሁፌ ደግሞ ስለሀገራችን የመድን ገበያ እንቅስቃሴና ዕድገት የሚተነትን ይሆናል፡፡
የመድን ሥራ የሰው ልጆች የኑሮ ሥጋትን ለመከላከል ያቋቋሙት ሥርዓት ነው፡፡ በመጻሕፍት እንደተገለጸው የመድን ሥራ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ጥንት ከ4000 (ቅ.ክ) ዓመት በፊት ከፈርዖኖች ዘመን ይጀምራል፡፡ ሐሙራቢ 6ኛው የባቢሎን ንጉሥ(1792-1750) ለመድን ሥራ ሕግ ደንግጐ እንደነበርም ተጽፏል፡፡ በንጉሥ ሐሙራቢ ዘመን አንድ ዕቃ ቢሰረቅና ሌባው ባይያዝ፤ ሌባው በሚኖርበት አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ የተሰረቀውን ዕቃ እንዲተካ ይገደድ ነበር፡፡የመጀመሪያው የመድን ሽፋን ሥራ የተጀመረው በባህር ላይ ለሚደርስ ሥጋት እንደነበር ተጽፏል፡፡ ሮማውያን የሕይዎትና የህክምና መድን ሽፋን ስለመጀመራቸው ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ በዘመናዊነት ደረጃ የመጀመሪያው የመድን ሽፋን ሰነድ (የመድን ፖሊሲ) የተሸጠው እኤአ በ1547 በሎንደን እንደነበር ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡
በሀገራችን የመድን ስራ መጀመር የሚያያዘው ከጥንቱ የአቢሲኒያ ባንክ መመሰረት ጋር ነው (1905)፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አቢሲኒያ ባንክ ለውጭ ሀገር የመድን ኩባንያዎች ወኪል በመሆን የእሳት አደጋ ሥጋት እና የባህር ላይ አደጋ ሥጋት ሽፋን የመድን ሰነዶችን ይሸጥ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ እኤአ በ1923 ላ-ቮርሴ የተባለው የስዊዝ መድን ኩባንያ፤ ዊንስገር የተባለውን የኦስትሪያዊ ዜጋ ወደ ሀገራችን በመላክ የእሳት አደጋ ሥጋት የመድን ሰነዶች ይሸጡ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ከዚያ በኋላ የመድን ሥራ እየተለመደ ሄዶ እኤአ ከ1920-1950 ባሉት ጊዚያቶች 45 የውጭ ሀገር የመድን ኩባንያዎች በሀገራችን ይሰሩ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ሀገር በቀል የመድን ኩባንያ (ኢምፔሪያል የመድን ኩባንያ) በአንድ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ዶላርና በስድስት ባለአክሲዮኖች የተቋቋመው እኤአ በ1951 ነበር፡፡ እኤአ በ1960 የንግድ ህግ እና በ1970 የመድን ህግ (አዋጅ ቁጥር 281/1970) መደንገግ የመድን ንግድ ሥራ መሰረት እንዲኖረው አድርጐታል፡፡ የሶሻሊሰቱ ርዕዮተ-ዓለም እስከታወጀበት ጊዜ ድረስ 33 የውጭ ሀገርና እና 15 ሀገር በቀል በድምሩ 48 የመድን ኩባንያዎች በሀገራችን የመድን ገበያ ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡በርዕዮተ ዓለሙ የምጣኔ ኃብት ፖሊሲ ምክንያት እነዚህ ኩባንያዎች በአዋጅ ቁጥር 26/1975 እና 68/1975 በመንግስት ተወርሰው ወደ አንድ የመድን ኩባንያ ተጠቃለዋል፡፡ከ19 ዓመት በኋላ በአዋጅ ቁጥር 86/1986 እንደገና የመድን ስራ ለሁሉም በህግ የተፈቀደ ስራ ሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት ዛሬ በሀገራችን አንድ የመንግስትና 16 የግል በድምሩ 17 የመድን ኩባንያዎች እንዲሁም አንድ የጠለፋ-መድን ኩባንያ ተቋቁመው አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡
ከላይ እንደተገለጸው በሀገራችን የመድን ንግድ ስራ በኢትዮጵያውያን ከተጀመረ ወደ 70 ዓመት ሆኖታል፡፡ ሙያው የሀገራችንን ድንበር ዘልቆ ከገባ ግን ወደ 115 ዓመታት እየሆነው ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት የመድን ንግድ ስራ እንዴት አደገ? አሁን ምን ላይ ይገኛል? የሚሉትንና እና ተዛማጅ ጥያቄዎችን ማንሳት የግድ ይለናል፡፡
የባንክ ዕድገትን ባየንበት ሁኔታ የመድን ንግድ ሥራ ዕድገትም ሀገራችን ካሳለፈቻቸው የመንግሥታት መለዋወጥ ጋር ሲዋዥቅ የነበረ ነው፡፡ በቅድመ ኃይለ-ሥላሴ ተጀምሮ፤ በንጉሥ ኃይለ-ሥላሴ ዘመን ማደግ ሲጀምር በሶሻሊስቱ ሥርዓት ዕድገቱ ተገቶ ወደ አንድ የመንግስት የመድን ኩባንያ ተጠቃለለ፡፡ የ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ የታወጀው አዋጅ ቁጥር 86/1986 የመድን ንግድ ስራ እንደገና እንዲያንሰራራ አድርጐታል፡፡ በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት መጨረሻ በድምሩ 17 የመድን ኩባንያዎችና አንድ የጠለፋ-መድን ኩባንያ በገበያው ተሰማርተዋል፡፡ ከ50 ባላይ የመድን ደላሎች፣ 915 የመድን ሽያጭ ወኪሎችና አንድ የመድን ማህበር በገበያው ታቅፈዋል፡፡
እነዚህ የመድን ኩባንያዎች በድምሩ 568 ቅርንጫፎች ሲኖራቸው፤ 85 በመቶ በግል፤ ቀሪው 15 በመቶ ደግሞ በመንግስት የመድን ኩባንያ የተያዙ ናቸው፡፡ አምስቱ ከፍተኛ የቅርንጫፍ ብዛት ያላቸው መድን ኩባንያዎች 45 በመቶ ወይም 257 የሚሆነውን የቅርንጫፍ ብዛት የሚይዙት ዝርዝራቸው በሠንጠረዥ-1 ቀርቧል፡፡ በሀገር ደረጃ በቅርንጫፍ ብዛት የመንግሥቱ የመድን ድርጅት ቀዳሚ ነው፡፡
ሠንጠረዥ-1፡በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቅርንጫፍ ያላቸው የመድን ኩባንያዎች
|
እንደሌሎች የፋይናንስ ተቋማት የመድን ኩባንያ ቅርንጫፎችም በአብዛኛው የከተሙት በአዲስ አበባ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከጠቅላላው ቅርንጫፎች ውስጥ 54 በመቶ (8 በመቶ የመንግስት እና 92 በመቶ የግል) ወይም 305 ቅርንጫፎች የሚገኙት በአዲስ አበባ ነው፡፡ በአዲስ አበባ አምስቱ ከፍተኛ የቅርንጫፍ ብዛት ያላቸው መድን ኩባንያዎች 42 በመቶ (ወይም 128) ሲይዙ ዝርዝራቸው በሠንጠረዥ-2 ቀርቧዋል፡፡
ሠንጠረዥ-2፡ በአ.አ ከፍተኛ ቅርንጫፍ ያላቸው የመድን ኩባንያዎች
|
ባለፉት 15 ዓመታት (1997-2011) የመድን ቅርንጫፎች ብዛት በዓመት በአማካይ 11 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ የግል መድን ድርጅቶች በ11.7 በመቶ፤ የመንግሥት ደግሞ በ8.1 በመቶ እያደገ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ የ44 ዓመት የገበያ ተሞክሮ ቢኖረውም የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በቅርንጫፍ ዕድገት ምጣኔ አነስተኛ ነው፡፡
ሠንጠረዥ-3፡ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ካፒታል ያላቸው የመድን ኩባንያዎች (ሚሊ. ብር)
|
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተገኘው መረጃ መሰረት በ2010 ዓ.ም የመድን ኩባንያዎች ጠቅላላ ካፒታል ብር 8.188 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 68 በመቶ የሚሆነው ካፒታል በግል መድን ኩባንያዎች ሲያዝ ቀሪው 32 በመቶ በመንግሥት የመድን ኩባንያ የተያዘ ነው፡፡ አምስቱ ታላላቅ የመድን ኩባንያዎች 69 በመቶ (5.649 ሚሊዮን ብር) የሚሆነውን የካፒታል የያዙ ሲሆን ዝርዝሩ በሠንጠረዥ-3 ቀርቧል፡፡
በዓረቦን ድርሻም የመንግሥትና የግል መድን ኩባንያዎች ይለያያሉ፡፡ በ2012 ዓ.ም ግማሽ ዓመት የመንግሥት መድን ኩባንያ የዓረቦን የገበያ ድርሻ 53 በመቶ ሲሆን ሌሎች የግል መድን ኩባንያዎች ቀሪውን 47 በመቶ ይዘዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲገመገም የመንግሥት መድን ኩባንያ የዓረቦን የገበያ ድርሻ 8 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ የግሎቹ መቀዛቀዝ ታይቶባቸዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በግል ክፈለ-ኢኮኖሚው የታየው መቀዛቀዝ ለዚህ ዋናው ምክንያት እንደሚሆን ይገመታል፡፡
በአጠቃላይ የግል መድን ድርጅቶች ባለፉት አምስት ዓመታት 62 በመቶ የዓረቦን የገበያ ድርሻ እንደነበራቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በጠቅላላው የመድን ዓረቦን በየዓመቱ 21 በመቶ እያደገ ይገኛል (ሰዕል-1)፡፡የመድን ኩባንያዎች ትርፋማነት እንደየ መድን አገልግሎቱ ዓይነት፣ እንደ ኩባንያው የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት መጠን፣እንደ ኩባንያው የአስተዳደር ወጪ ምጣኔ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ለአንዳንድ የመድን ኩባንያዎች የሞተር ዘርፍ አክሳሪ ሲሆን ለሌሎች ግን አትራፊ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ኢንዱስትሪው አትራፊ መሆኑን ከስዕል-2 መገንዘብ ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ገበያ በተወሰኑ የመድን አገልግሎቶች ብቻ የተገደበ ነው፡፡ አገልግሎቱም በአብዛኛው በንግዱ ለተሰማራው የህብረተስበ ክፍል ያጋደለ ነው፡፡ በሰፊው የሚታወቁት ሞተር፣ ባሕር፣ እሳት አዳጋ፣የሠራተኞች ደሕንነት፣ የአቭየሽን እና የህይወት መድን 78 በመቶ የሚሆነውን ዓመታዊ ዓረቦን ይሸፍናሉ፡፡እኤአ ከ1980 እስከ 2019 በተወሰደ አማካይ የዓረቦን መረጃ፤ ሞተር (47 በመቶ)፣ ባሕር (10 በመቶ)፣ ሕይወትና ተዛማጅ (6 በመቶ)፣ እሳት አዳጋ (5 በመቶ)፣አቭየሽን (5 በመቶ)፣የሠራተኞች ደህንነት (3 በመቶ) እና ሌሎች (22 በመቶ) የገበያ ሽፋን ይዘዋል፡፡ በመደበኛው የመድን ገበያ አከፋፈል ሲታይ ደግሞ ጠቅላላ መድን አገልግሎት 94 በመቶ ሲይዝ የረጅም ጊዜ የመድን አገልግሎት የዓረቦን ሽፋን 6 በመቶ ይሆናል፡፡
የሀገራችን የመድን ገበያ በጣም ያላደገና ገና ብዙ የሚቀረው ነው፡፡ በኩባንያ ብዛት እንኳ አሁን ያለው ከሶሻሊስት አብዮት በፊት ከነበረው ጋር ሲወዳደር በ67 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ የዓረቦን ሽፋኑም እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሲነጻጸርም ገና ብዙ መልማት እንዳለበት መገንዘብ ይቻላል፡፡የተሰበሰበው የመድን ዓረቦን ለጠቅላላ ሀገሪቱ ዓመታዊ ምርት (ሀገራዊ ምርት) ያበረከተው አስተዋጽኦ እንደመለኪያ ይወሰዳል፡፡ በዚህ መሰረት እኤአ በ2019 ጠቅላላ የመድን ዓረቦን በዓለም ደረጃ 6 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ በአፍሪቃ 3 በመቶ፣ በምስራቅ አፍሪቃ 0.71 በመቶ፣ እና በኢትዮጵያ 0.40 በመቶ ለሀገራዊ ምርት አስተዋጽኦ እንደነበረው ተመዝግቧል፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የተመዘገበው በደቡብ አፍሪካ (14 በመቶ) ሲሆን በጎረቤት ኬንያ የተመዘገበው 2.6 በመቶ ነው፡፡የተሰበሰበው ዓረቦን ለሀገሩ ሕዝብ ሲካፈል የሚገኘው ስሌትም እንደ መድን ገበያ ዕድገት መለኪያ ይቆጠራል፡፡ በዚህም መሰረት በኬንያ $40 ሲመዘገብ በኢትዮጵያ $2.90 ተመዝግቧል፡፡
ለአንድ የተወሰነ ሥጋት የመድን ሽፋን የመግዛት አቅም ከሀገራዊ ቁጠባ ጋርም ይዛመዳል፡፡ ከፍተኛ የመቆጠብ አቅም ያላቸው ሀገሮች ሰፊ የመድን ሽፋን ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ የመድን ገበያ ዕድገት ከቁጠባ እድገታችን ጋር አልተጓዘም፡፡ ለምሳሌ እኤአ 2010 እስከ 2019 በነበረው ጊዜ ውስጥ ኢኮኖሚያችን በአማካይ ያደገው 9.61 በመቶ ሲሆን ቁጣባ ያደገው 20.27 በመቶ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከኬንያ (5.58 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት፤ 7.75 በመቶ የቁጠባ ዕድገት) እና ከታንዛኒያ (6.55 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት፤ 22.59 በመቶ የቁጠባ ዕድገት) ያነሰ የመድን ገበያ ዕድገት በኢትዮጵያ ተመዝግቧል፡፡እኤአ በ2019 በምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት መድን ገበያ ያለበትን ደረጃ በሠንጠረዥ-4 ቀርቧል፡፡
ሠንጠረዥ4፡ በምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት መድን ገበያ (2019)
ሀገር | ሕዝብ ብዛት (ሚሊዮን) | ሀገራዊ ምርት ቢሊየን$ | የሀገራዊ ምርት ዕድገት% | የመድን/የጠለፋመድንኩባንያ ብዛት | የመድንሽፋን % (2017) | ዓረቦን/ህዝብ ብዛት $ |
ኬንያ | 53 | 99.2 | 6.0 | 51 | 2.83 | 40.0 |
ሩዋንዳ | 13 | 10.2 | 7.8 | 15 | 1.74 | 6.0 |
ኡጋንዳ | 44 | 33.6 | 5.5 | 31 | 0.77 | 4.4 |
ታንዛኒያ | 58 | 61.0 | 6.6 | 28 | 0.68 | 6.0 |
ሱዳን | 43 | 31.5 | 3.6 | 20 | 0.57 | 9.0 |
ኢትዮጵያ | 112 | 91.0 | 8.2 | 17 | 0.43 | 2.9 |
ኤርትራ | 3 | 7.7 | 3.8 | 1 | 0.38 | 3.0 |
ጂቡቲ | 0.9 | 2.4 | 5.9 | 2 | 0.38 | 17.0 |
የሀገራችን የመድን ኩባንዎች የሚታወቁት በገበያው አለማደግ ብቻ ሳይሆን በመድን ቴክኖሎጂ ወደ ኋላ የቀሩ በመሆናቸውም ጭምር ነው፡፡ በሀገራችን የመድን ኩባንያዎች ቴክኖሎጂ ዋና የስራ መሳሪያ ሳይሆን አጋዥ መሳሪያ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ መለስተኛ ስሌቶችን እና የጽሁፍ ስራ ከመስራት የተለየ ተግባር ሲፈጸምበት አይታይም፡፡ በስራ ላይ ያሉት የመድን ኩንያዎች የጋራ የመረጃ ቋት (ለምሳሌ በሞተር መድን፡- የመኪና ዓይነት፣ባለቤት፣ ዕድሜ፣ መድን የተገባበት ዋጋ፣ መድን የሰጠው ኩባንያ፣የመኪናው የኋላ የሥጋት ታሪክ… ወዘተ)እስካሁን ለመገንባት አልቻሉም፤ የሞባይል፣ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂና ኢ-ኮሜርስ ለመድን ገበያው ማቀላጠፊያ ሲውልም አልተስተዋለም፡፡
የመድን ገበያ በአሁኑ ጊዜ በሰለጠነ ሁኔታ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ነው፡፡ የመድን ፖሊሲ ከመግዛት ጀምሮ እስከ ጉዳት ግመታና ካሳ ክፍያ በሞባይል/ኢንተርኔት ቴክኖሎጂ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ማኬንዚ እና ኩባንያው እኤአ በ2019 ባደረገው ጥናት የመድን ኩበንያዎች ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተለወጡ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡ እንደጥናቱ ከሆነ ለመድን ኩባንያዎች በአራት መስኮች ትራንስፎርሜሽን ያስፈልጋቸዋል፤ በስትራቴጂ፣ በአቅም ግንባታ፣በአሰራር መዋቅርና በአሠራር ዘይቤ፡፡ በዚህ መሰረት መድን ኩባንያዎች በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ፣ ፈጣን፣ በፈጠራ የታገዘና የእያንዳንዱን ደንበኛ ችግር የሚፈታ ግልጋሎት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ግልጋሎት ለመስጠት የመድን ኩባንያዎች የሚከተሉትን ስድስት ጉዳዮች ማከናወን እንዳለባቸው የማኬንዚ ተመራማሪ ያስረዳሉ፡፡ እነሱም ውሳኔ አሰጣጥን ለማቀላጠፍ የሙያ ስብጥር ያለው ቡድን መመስረት፤ቴክኖሎጂንና አሰራርን ማቀናጀት፤ ደንበኛ ተኮር በሆኑ ጉዳዮች ላይ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ፤ዋና ሥራ ያልሆኑ የስራ ዘርፎችን በሌሎች ማሰራት፤ልዩ ተሰጥዖ የሚታይባቸውን ስትራቴጂዎች መቀየስና የኩባንያን አቅም ማሳደግ፤የመረዳዳትና የመተጋገዝን ባህል መገንባትና ሠራተኞች ለአዲስ ነገር እንዲታትሩ ማድረግ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የመድን ኩባንያዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዛቸው ምክንያት የአገልግሎት ዋጋ ይቀንሳል፤የደንበኛ እርካታ ይጨምራል፡፡
ቴክኖሎጂ በመድን አገልግሎት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ በየአገልግሎቱ ዓይነት ይለያል፡፡ ከዚሀ አንጻር ቴክኖሎጂ በጠቅላላ መድን አገልግሎት ላይ የሚያስከተለው ተጽዕኖ ከረጅም ጊዜ የመድን አገልግሎት ጋር ሲነጻጸር እጅግ የላቀ ነው፡፡ አንዳንድ የሙያው ሊቃውንት “ቴክኖሎጂ ጠቅላላ መድን አገልግሎትን እየገደለው ነው” ይላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚከተሉት የቴክኖሎጂ ተጽዕኖ የጠቅላላ መድን አገልግሎትን ከገበያ እያስወጣው ይገኛል፡፡
የቴሌማቲክ አገልግሎቶች እየበረከቱ መምጣት የመረጃ ፍሰቱን ከማቀላጠፉም በላይ ሥጋትን በመተንተን፣ የዓረቦን ቅናሽ ያለውን ተወዳዳሪ የመድን ኩባንያ በቅንጣት-ሴኮንድ ለመለየት ያስችላል::ያለ-ሹፌር የሚነዱ መኪናዎች እየተፈለሰፉ መምጣትና በመንገድ ላይ መገኘት ነባሩን የሞተር መድን ተፈላጊነትን እያጠፋው ይገኛል፡፡ለአዳዲስ የመድን ኩባንያዎች የሞባይል ኢንተርኔት ግብይት መጀመር የመድን ሥራ መሰረተ ልማት ወጪን ስለሚቀንስ ዓረቦን ይቀንሳል፡፡ በዚህም ዓረቦን ምጣኔ እንዲወርድ አድርጐታል፡፡
የዓረቦን እና የመድን-ዕሴት ማወዳደሪያ ድረ-ገጾች መበራከት ደንበኞች የተለያዩ መድን ኩባንያዎችን በቀላሉ ለማወዳደርና ዝቅተኛ ዓረቦን የሚኖረውን ኩባንያ ለመምረጥ አስችሏቸዋል፡፡ደንበኞች በቡድን በመሆን፣ የመረብ ግንኙነትን በመጠቀምና ሥጋታቸውን በጋራ በማዋሀድ የራሳቸውን የመድን ስራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ አይነት ግብይት ከስርቆት የጸዳ፣ የግብይቱ ወጪ ቆጣቢና ይህ ነው የሚባል የመሰረተ ልማት ወጪ የሌለበት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ለቡድኑ አባላት የሚከፈለው ዓረቦን ከመደበኛ የመድን ኩባንያዎች ያነሰ ሆኗል፡፡ማህበራዊ ሜድያው በራሱ ማሕበራዊ የመድን ደላሎችን ፈጥሯል፡፡ ደላሎች ለተፈለገው የሥጋት ሽፋን ዝቅተኛ ዓረቦን ያላቸው የመድን ኩባንያዎቸን በቀላሉ መምረጥ አስችሏቸዋል፡፡በዚህ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ የመድን ሥራ ያለቴክኖሎጂ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በአፍሪካ የመድን ሥራንና ቴክኖሎጂን በማዋሃድ ደቡብ አፍሪካ በሰፊው ትታወቃለች፡፡ ጎረቤት ኬንያም ዓረቦን እና ካሳ ክፍያ በሞባይል ማከናወን ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
የመድን ሥራ ሥጋትን መቀነስ (ማካካስ) ነው፡፡ የመድን ሥራ የሀገር ምጣኔ ኃብት ለማሳደግ ከሚጠቅሙ የፋይናንስ ተቋማት አንዱ ነው፡፡ዋናው ዓላማ ግለሰቦች፣ ኩባንያዎችና መንግሥት በንብረትና በሕይወት ላይ ይከሰታል ተብሎ ለሚተነበየው ሥጋት ማካካሻ በማዘጋጀት፤ መድን ገዥው የህሊና ዕረፍት እንዲያገኝ ማስቻል ነው፡፡ የህሊና ዕረፍት ያለው የንብረት ባለቤት የተረጋጋ ኩባንያ ሊመራ እንደሚችል ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በሌላ በኩል የሚጠራቀመው ዓረቦን (በተለይ የረዥም ጊዜ መድንአገልግሎቶች) በትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ሊውል የሚችል ፋይናንስ ለማመንጨት ያስችላል፡፡ይህም የሀገር ምጣኔ ኃብትን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ የመድን ንግድ ሥራ ሥጋትን በጋራ በመከላከል አስተሳሰብ ላይ በመመስረቱ በግለሰቦች ላይ ሊከሰት የሚችልን ሥጋት ከመቀነሱም በላይ የመንግስትን ጫና ያቃልላል (እንደ ማሕበራዊ መድን ዓይነት አገልግሎቶች)፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የኢትዮጵያ የመድን ገበያ ገና ያላደገ የፋይናንስ ተቋም ነው፡፡ ሙያው ከተጀመረ ዕድሜው ረዥም ቢሆንም፤ የሚጠበቅበትን ያህል አላደገም፡፡ሁለቱን የመድን ዓይነቶች ለያይተን ስንመለከት (ጠቅላላ መድን እና የረዥም ጊዜ መድን) ደግሞ የረዥም ጊዜ መድን (ሕይወትና ሕይወት-ነክ አገልግሎቶች) እጅግ ኋላ ቀር ነው፡፡ አስካሁን ያለው የዓረቦን ድርሻ ከስድስት በመቶ አልበለጠም፡፡ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ የፋይናንስ ምንጭ የሚሆነው ደግሞ ይህኛው ያላደገው የመድን ዘርፍ ነው፡፡ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ንጽጽር ብቻ በማየት የእኛ የረዥም ጊዜ መድን እንዳላደገ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ መድን ኩባንያዎች ማሕበር እኤአ በ2018 ባወጣው ዓመታዊ መጽሔት ላይ የአህጉሩ የረዥም ጊዜ መድን 22 በመቶ በሞሮኮ፣ 15 በመቶ በግብፅ 11 በመቶ፤ በኬንያ ስምንት በመቶ፤ በሞሪሸየስ፣ ስድስት በመቶ፤ በዛምቢያና አንድ በኢትዮጵያ አንድ በመቶ እንደተያዘ ተመዝግቧል፡፡
ለኢትዮጵያ መድን ሥራ አለማደግ ብዙ ምክንያቶች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በየጊዜው የኢትዮጵያ መንግስታት ተለዋዋጭ መሆንና ከመንግስታቱ ጋር ተያይዞ የሚደነገጉት ሕጐች ለመድን ሥራ ትኩረት አለመስጠት፤ ራሱን የቻለ የመድን ሥራን የሚያበለጽግና የሚቆጣጠር የመንግስት ተቋም አለመኖር፤ የተቋቋሙት የመድን ኩባንያዎች ሙያውን እና ገበያውን ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት አናሳ መሆን፤ የትምህርት ተቋማት ለሙያው ብቁ የሆነ ሰው ማሰልጠን አለመቻላቸው፤ማሕበረሰቡ ስለመድን ጠቀሜታ ያለው ግንዛቤ ማነስ …ወዘተ ሊጠቀሱ ችላሉ፡፡ በመግቢያው እንደተገለጸው የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ነባራዊ ሁኔታውን መገምገምና የመድን የሥራ መስክ እንዲያድግ ሊደረግ ስለሚገባው ጉዳይ አስተያየት መስጠት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የመድን የሥራ ዘርፍ እንዲያድግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡
ለአንድ የሥራ ዘርፍ ራሱን የቻለ ጠንካራ የመንግሥት ተቋም መገንባት ለሥራው ትኩረት እንዲሰጠው ያደርጋል፡፡ አሁን ባለው አደረጃጀት የመድን ሥራ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስር እንደ አንድ ዘርፍ ሆኖ ይንቀሳቀሳል፡፡የመንግስት መ/ቤቶች ራሳቸውን ችለው ሲዋቀሩ የሚጠይቀው የመንግስት በጀት እንደሚጨመረው ሁሉ ለተቋሙም የትኩረት አቅም እንደሚጨምር ይገመታል፡፡ ላለፉት ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ራሱን ባልቻለ ሁኔታ ተመርቶ የመድን አንዱስትሪ የደረሰበትን ደረጃ ማየት ችለናል፡፡ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል አላደገም፣ በቴክኖሎጂ ኋላ ቀር ነው፣ የሰው ኃይሉም የመነመነ ነው፡፡ የመድን አገልግሎት ዓይነቶች ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት የነበሩት ናቸው፣…. ወዘተ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ራሱን የቻለ የመድን ተቋም ቢያቋቁም ዘርፉ የበለጠ ሊያድግ እንደሚችል ይገመታል፤
የመድን ኩባንያዎች ቀደም ብሎ በተፈጠሩ ገበያዎች ከሚያደርጉት ሽሚያ በስተቀር፣ አዳዲስ ገበያ ለመፍጠርና አዳዲስ አገልግሎቶችን ለህበረተሰቡ በማቅረብ አማራጭ መፍጠር አልቻሉም፡፡ ለምርምርና ስርጸት፣ ለሰው ኃይል ልማት፣ ለቴክኖሎጂ … ወዘተ የሚመድቡት መዋዕለ-ንዋይ ከሚጠበቀው በታች ነው፡፡ በተለይ የሰው ኃይል ዘርፉ ከባንክም በባሰ ሁኔታ እጀግ የተጐዳ ነው፡፡ እሰካሁንም ኩነቶችን አጥንቶና አስልቶ ዋጋ የሚተምነው አስሊ ከጐረቤት ሀገራት ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮንትራት የሚቀጠር ባለሙያ ነው፡፡የመድን ማህበራት በመንግሥትና በመድን ኩባንያዎች መካከል በመገኘት ለኢንዱሰትሪው አዳዲስ ሀሳብና ተሞክሮዎችን በማመንጨት፤ ለመንግሥት ግብዓት በማቅረብ እንደየሁኔታው በሕግም ሆነ በደንብ እንዲቀረጹ የሚታትሩ መሆን አለባቸው፡፡ በስራ ላይ ያለው ማህበር ብዙ ጐልቶ የወጣ ስራ ለማህበረሰቡ ሲያቀርብ አልታየም፡፡
የመድን ሙያ ትምህርት ከሌሎች በመደበኛነት ተቀርጸው ከሚሰጡ ሙያዎች ይለያል፡፡ የሙያው መሰረት በእጅ የማይዳሰስና ምናልባትም ወደ ፊት ሊከሰት የሚችልን ጉዳይ ዛሬ በመሸጥና በመለወጥ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የሚጠይቀው ክህሎት ከሌሎች ይለያል፡፡ ትንበያ፣ መረጃ የሚተነተንበትና ስሌት የሚበዛበት የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ ይህን ክህሎት ያለው ሰው ማስገኘት የከፍተኛ ትምህርት ተቋት ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ የመድን ሥራው የሚፈልጋቸው እንደ አስሊ (actuary)፣ጉዳት አስተካካይ (loss adjustor)፣ ጉዳት ገማች (loss assessor)፣ የመድን መርማሪ (insurance surveyor)፣ የመድን ወኪል (insurance agent)፣ የመድን ረዳት (insurance auxiliary)እና የመድን ደላላ (insurance broker) ሙያዎች ከተቋማት ሰልጥነውና ተመስክሮላቸው መውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ከላይ እንዳነሳነው በአንድ ሀገር ውስጥ 70 ዓመታት የቆየ የመድን ሥራ አንድ አስሊ እንኳ አለማስገኘት የሚያሳየን ሙያውን ለማሳደግ ገና ብዙ የቤት ስራ እንዳለብን ነው፡፡ማህበረሰቡ የመድን ትምህርት ያስፈልገዋል፡፡ በርግጥ የመድን ጠቀሜታን ለማስረዳት እንደሌላው ሙያ ቀላል ላይሆን ይቻላል፡፡ ይህን የማስተማር ኃላፊነት የሁሉም ሊሆን ይገባል፡፡ መንግስት ህግ በማውጣትና በሥርዓተ-ትምህርት በማካተት፤ የመድን ኩባንያዎች በወቅታዊ ማስታወቂያቸውና ወርክ-ሾፖችን በመደግፍ፣ በትምህርት ቤቶች ንግግር በማዘጋጀት፣ ስልጠና በመስጠት….፤ የመድን ማህበራት አባላትን በማስተባበርና በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ትምህርታዊ መርሐ-ግብሮችን በማዘጋጀት ማህበረሰቡን መስተማር ማንቃት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ፀሐፊው በፋይናንስና ኢንቨስትመንት ሙያ የሙሉ ጊዜ አማካሪ፤እንዲሁምበአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በድኅረ-ምረቃ ፕሮግራሞች አስተማሪ ሲሆኑ ጽሁፉ የፀሐፊውን አመለካክት ብቻ የሚያንጸባረቅ ሲሆን በ[email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡