አቶ ፊሊጶስ አይናለም
ስለ ጥቅም ሲነሳ ሊታሰቡ የሚችሉ የተለያዩ ዓይነት ጥቅሞች አሉ፡፡ የግል፤ የቡድ፤የሕዝብና የመንግስት ጥቅሞች ቅድሚያ የምንሰጣቸው ናቸው፡፡ ጥቅም የራሱ መገለጫና ዓይነት ቢኖረውም፤ በዋናነት የሕዝብ ጥቅም ግን ለየት ይላል፡፡ መክንያቱ ደግሞ ጥቅል ስለሆነና ምን ማለት እንደሆነ በሕግ በዝርዝር ባለመቀመጡ ነው፡፡ የሕዝብ ጥቅም ትርጉም ተሰጥቶት በግለጽ ባለመቀመጡ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑን በርካቶች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ የሕዝብ ጥቅም የሚለው በጥቅል በመቀመጡ፤ መንግስት የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ ዜጎችን ማሰሪያና መፍቻ በማድረግ እንደፈለገ እየተጠቀመበት ነው የሚሉም አሉ፡፡ ሪፖርተር መጽሔትም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙትንና ከ 30 ዓመታት በላይ በሕግ ኤክስፐርትነት፤በዳኝነት፤በዩኒቨርስቲ መምህርነት፤በጥብቅናና አማካሪነት ሰፊ ልምድ ያላቸውን፤ ታዋቂውን የሕግ ባለሙያ አቶ ፊሊጶስ ዓይናለምን “የሕዝብ ጥቅም ምንድን ነው ” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የአደባባይ አምዱ እንግዳ አድርጓቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3) ላይ፣ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የማቋረጥ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ክስ የማቋረጥ ሥልጣን መስጠት በመርህ ደረጃ ተገቢ ቢሆንም፣ ክስ እየተቋረጠና ፍርድ እየታገደ የወንጀል ተጠርጣሪዎችና ፍርደኞች የሚለቀቁበት አግባብ ግን እያነጋገረ ነው፡፡ ምንም እንኳን ተከሳሾችና ፍርደኞች ከእስር መለቀቃቸው ለእነሱና ለቤተሰቦቻቸው ደስታ የሚሰጣቸው ቢሆንም ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባልና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት›› በሚል ምክንያት ክስ ማቋረጥ ተገቢ እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ምክንያታቸውና የሚያነሱት ጥያቄ ደግሞ ‹‹የሕዝብ ጥቅም ማለት ምን ማለት ነው? የሚል ነው፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ፊሊጶስ፡- በመሠረቱ ‹‹የሕዝብ ጥቅም›› የሚለው በወንጀል ሕጉም ይሁን በፍትሐ ብሔር ሕግጋትም በሰፊው ተቀምጦ እናገኘዋለን፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ላይም ክስ የሚነሳውና ክስ የሚቋረጠው የሕዝብን መብት መሠረት አድርጎ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ክስን ለማቋረጥ በአዋጁ አንቀጽ 6(3) ላይ እንደተደነገገው፣ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌዴራል መንግሥትን በመወከል በወንጀል ጉዳዮች ላይ ክስ ይመሠርታል፣ ይከራከራል፣ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም›› አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክሱን ያነሳል፡፡ የተነሳ ክስንም እንዲቀጥል እንደሚያደርግና ጉዳዩ አገራዊ ይዘት ሲኖረው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከር ክስ ስለሚያነሳበት አግባብ መመርያ ማውጣት እንደሚችል ስልጣን ሰጥቶታል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹የሕዝብ ጥቅም የሚባለው ምንድነው?›› የሚለውን ብንመለከት፣ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ አንድ ላይ ተደንግጎ እንደሚገኘው፣ ማናቸውም የወንጀል ሕግ ዓላማ ሲተገበር፣ ክስ ሲነሳም ሆነ ሲቀርብ፣ ቅጣትም በፍርድ ቤት ሲወሰን፣ ፖሊስም ምርመራ ሲያደርግ፣ የወንጀልን ሕግ ዓላማና ግብ ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ ዓላማው ለጠቅላላው ሕዝብ ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግሥት፣ የሕዝቦችን ሰላም፣ ደኅንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ መሆኑም በወንጀል ሕጉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ መተግበር ያለበትም እነዚህን ባመጣጠነ መልኩ መሆን እንዳለበትም ከድንጋጌው መንፈስ መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹ሕዝብ›› የሚለው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥቱም ላይ ስናይ፣ ከአምስቱ የሕገ መንግሥት መሠረታዊ መርሆዎች መካከል በአንቀጽ ስምንት ላይ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆኑን ደንግጓል፡፡ ሕዝብ የሁሉም የበላይ እንዲሆን ሲደነገግ በ‹‹ሕዝብ›› ስም የሚፈጸሙ፣ የሕግ አወጣጥ፣ አፈጻጸምና አተረጓጎም ሒደቶች ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በሕግ ሥርዓታችን ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ‹‹የሕግ ጥቅም ሲባል ምን ማለት ነው?›› የሚለው ግልጽ የሆነ ትርጉም አልተሰጠውም፡፡ ነገር ግን ትርጉም ሊሰጠው ሲገባ አላግባብ በሥራ ላይ ውሏል፡፡
የፀረ ሽብር አዋጅና፤የሲቭል ማህበረሰብና በጎአድራጎት ድርጅቶች አዋጆችም ሥራ ላይ ሲውሉ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ›› ተብሎ ነው የወጡት፡፡ ነገር ግን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለሕዝብ እጅግ በጣም ብዙ ጥቅም የሚሰጡና በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ቢሆንም አዲስ የወጣው አዋጅ ድርጅቶቹን ሥራ የሚከለክል አዋጅ መሆኑ እየታወቀ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› ይባላል፡፡ በሠለጠነ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ፣ ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ አሉ፡፡ ሕግ አስፈጻሚው ማድረግ ያለበት ወይም የሚያስፈጽመው በሕጉ በተሰጠው ሥልጣን ልክ ነው፡፡ ሕግ አውጪውም ሥልጣን ሲሰጥ ዝም ብሎ ‹‹ድፍን›› ያለ፣ እንደፈለገ ሊደረግ የሚችልና አላግባብ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል መሆን የለበትም፡፡ ሕግ አውጭው፤ የአስፈጻሚ አካላትን ማቋቋሚያና ሥልጣን መደንገጊያ አዋጅ ላይ የተለያዩ ደንቦችን እያወጣ፤አስፈጻሚ አካላት ተቋማትን ማቋቋምና ማፍረስ እንደሚችሉ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ አስፈጻሚው ስልጣን ስለተሰጠው ደንቦችን ሲያወጣ ለራሱ በሚመቸው መልኩ አድርጎ ስለሚያወጣው ለመቆጣጠር አይችልም፡፡ ሦስቱ የመንግሥት አካላት እርስ በርስ መቆጣጠር (Check and Balance) የሚችሉትና በትክክል በተግባር ላይ ሊውል የሚችለው፤ ሕግ አውጪው ያወጣውን ሕግ፣ ሕግ አስፈጻሚው በአግባቡ ማስፈጸም ሲችል ብቻ ነው፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሊያስፈጽም የሚችለው ‹‹ እነማን ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ሊፍቱ ወይም ሊከሰሱ ይገባል?›› የሚለው በሕግ አውጭው በዝርዝር ተለይተው ከመቀመጣቸውም በተጨማሪ፤ በምሕረትና በይቅርታ አዋጆችም ሊደነገጉ ይገባል፡፡ ይኸ ባልሆነበት ሁኔታ የምሕረት አዋጁም ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ በይቅርታ አዋጁም በተመሳሳይ ሁኔታ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› ይላል፡፡ ‹‹ይህ የሕዝብ ጥቅም የስንት ሰው ጥቅም ነው? ሕክምናን ነው? ፍትሕን ነው? ፖለቲካን ነው? ኢኮኖሚን ነው? ማኅበራዊ ጉዳይን ነው? አንድ ሆቴል መሥራት ነው? አንድ የስፖርት ሜዳ መሥራት ነው? ምን እንደሆነ እንኳን ሕግ አውጪው ባወጣቸው ሕጎች ውስጥ ትርጉም አልሰጠበትም፡፡
የሕዝብ ጥቅም የሚባለው በሺዎችና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሊጠቀም የሚችል ፕሮጀክትን ወይም ሌላ ጠቃሚ ነገር እንጂ፣ አራት ኪሎና ካዛንችስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን መኖሪያ ቤት አፍርሶ፣ ሆቴል የሚሠራን ባለሀብት ለአሥር ዓመታት መጠበቅ አይደለም፡፡ የሚገርመው ነገር ይህም ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› ተብሎ መፍረሱ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የፍትሐ ብሔሩንና የወንጀል ሕጎችን ብንመለከት፣ የሕዝብ ጥቅምን ለመተርጎም የሞከረ አንድ አዋጅ እናገኛለን፡፡ ይህም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትና ለንብረት ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታን ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር 455/97 ነው፡፡ ይህም አዋጅ ‹‹የሕዝብ ጥቅም›› የሚለውን አልተረጎመውም፡፡ ‹‹መንግሥት ለሕዝብ አገልግሎት ለሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች መሬትን መጠቀም አስፈላጊ ሲሆን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንግድ በያዙት መሬት ላይ ያላቸውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በቀጣይነት ለማጎልበት አግባብ ያለው አካል በከተማ መዋቅራዊ ፕላን፤ በልማት ዕቅድ መሠረት የሕዝብ ጥቅም ብሎ የሚወስነው ነው›› ይላል፡፡ በዚህ ትልቅ የሕዝብ ጥቅም ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ሥልጣን የተሰጠው የበታች አካል፤ ወረዳ ወይም ክፍለ ከተማ መሆኑን ይናገራል፡፡ ለሕዝብ ጥቅም የሚወስነው ወረዳና ክፍለ ከተማ ነው፡፡ ገማች ራሱ፣ አስለቃቂና ውሳኔ ሰጭ ራሱ፣ ቅሬት ሰሚ ራሱ ሆኖ ሁሉን ነገር አንድ አካል የሚፈጸምን ውሳኔ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም›› መባሉ ተገቢ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ‹‹ለሕዝብ ጥቅም›› እየተባለ ከይዞታ ማፈናቀልና ወንጀል ሠርቶ የተከሰሰንና የተፈረደበትን ከእስር መልቀቅ ከጥቅሙ ይልቅ ሕዝብን መጉጃና መጨቆኛ የፖለቲካ መሣሪያ ሆኗል የሚሉ አሉ?
አቶ ፊሊጶስ፡- ትክክል ነው፡፡ በተለያየ መንገድና ሁኔታ የሰብዓዊ መብት የጣሱ፣ በግድያ የሚጠረጠሩ፣ በሙስና፣ በአራጣና በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የታሰሩና የተፈረደባቸው ሰዎች፤ ትክክለኛ ትርጉም ባልተሰጠው ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› በሚል ጥቅል አባባል፤ ክስ አቋርጦ መፍታት ትክክል አይደለም፡፡ ግብረ መልሱም መልካም አይሆንም፡፡ የሕግ ዋናውና መሠረታዊ ዓላማው ሁለት መሆኑን የሕግ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ የመጀመርያው በሕጎች መካከል ያለውን ግንኙነት በሥርዓት መምራት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የመንግሥት አካላትን ሥልጣን መገደብ ነው፡፡ ሕግ አውጪው ያወጣውን ሕግ፤ ሕግ አስፈጻሚው እንዴትና እስከ ምን ድረስ ማስፈጸም እንዳለበት ገደብ ሊያበጅለት ይገባል፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ ተወካይ ሕግ አውጪው በመሆኑ ጥቅሙንም የሚቆጣጠረው እሱ ነው፡፡ መቆጣጠር የሚችለውም ዝርዝር መቆጣጠሪያ መንገዶችን በዝርዝር በማስቀመጥና በመዘርጋት እንጂ፤ ድፍን ባለና ‹‹ለሕዝብ ጥቅም›› በሚል በቻ መነሻና መድረሻው በማይታወቅ ሁኔታ መሆን የለበትም፡፡ የመቶ አባወራዎችን ቤት አፍርሶ ለአንድ ሰው ሆቴል መሥሪያ መስጠት ለሕዝበ ጥቅም ነው አያስብልም፡፡ አንድ ሆቴል ገንብቶ ቢዝነስ መሥራት ለሕዝብ ጥቅም ነው ሊያሰኝ አይችልም፡፡ የሕዝብ ጥቅም ምን እንደሆነ በደንብ ዝርዝር ብሎ በሕግ አውጪው አካል ሊተረጎም ይገባል፡፡ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥልጣን ሲሰጠው፣ ምን ምን እና እስከ ምን ድረስ ማስፈጸም እንዳለበት መመርያ ጭምር ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ይቅርታ የሚደረግላቸውንና የማይደረግላቸውን፣ ክስ የሚቋረጥላቸውና የማይቋረጥላቸው እነማን እንደሆኑና ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› እንዴት ከእስር እንደሚፈቱ በዝርዝር አስቀምጦ መመሪያውን መስጠት አለበት፡፡ ትልቁ ስህተት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ድፍን ባለ ሁኔታ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› በሚል ገደብየለሽ ድንጋጌ ማስቀመጡ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በተለያዩ በርካታ አዋጆች ላይ ‹‹የሕዝብ ጥቅም›› የሚል ቢቀመጥም፣ ምን ምን እንደሚያካትት የተገለጸ ነገር ባለመኖሩ፣ አስፈጻሚው እንደፈለገ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ የአንድ ሕግ ዓላማ የሕዝብን ጥቅም ማስከበር ነው፡፡ የወንጀል ሕግ ዋና ዓላማው የግለሰብንና የቡድንን (የሕዝብን) መብት ማስከበር ነው፡፡ ቃሉን ብቻ የምንጠቀም ከሆነ፣ ‹‹ሕዝብ›› የሚለው ቃል ትርጉም ያጣል፡፡ አንድ ሰው ወንጀል ሠርቷል በሚል ጥርጣሬ ብቻ፣በምርመራ ሳይጣራበትና ትክክለኛ የሆነ ማስረጃ ሳይገኝበት ሊታሰር አይገባም፡፡ በተለይ ከ1997 ዓ.ም አገራዊ ምርጫ ወዲህ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› እየተባለ ሰው ይታሠራል፤ ይፈታል፡፡ ስለይቅርታ አሰጣጥ፣ ስለወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች፣ ስለግብርና ሌሎችም በርካታ አዋጆች ድንጋጌዎች ተጠቅሰው ክስ የተመሰረተባቸውና ቅጣት የተጣለባቸው ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› እየተባለ ከእስር ተፈትተዋል፡፡አዋጆቹ በሕዝብ ጥቅም ስም የሕዝብ መብት መጣሻ፤ ይቅርታ ማድረጊያና መፍቻ እየሆኑ ነው፡፡ ሕዝብን እየረበሸ፣ እየሰረቀ፣ እየገደለና ጉዳት እያደረሰ የታሰረው ሁሉ ነገ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› በማለት የሚፈታ ከሆነ፣ ነገ ተነገወዲያ የሕዝብ ጥቅም እየተጣሰ፣ የግለሰቦችና የቡድን መብቶች ማለትም የደህንነት፣ በሰላም የመኖር፣ ንብረት የማፍራትና በአጠቃላይ በሕገ መንግሥቱ የተከበሩ መብቶች መጣሳቸው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝብ መብት በልዩነት (Exception) መታየት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ ወንጀል ሠርቷል ተብሎ የሚጠረጠር ሰው የሚታሰረውና ክስ የሚመሰረትበት ለተጠረጠረበት ወንጀል በቂ የሆነ ማስረጃ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ ጥፋተኛ ወይም ነፃ መሆኑ የሚረጋገጠው በፍርድቤት ከሚደረገው ክርክር በኋላ መሆኑ እየታወቀ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› በሚል ክሰ ይቋረጥና ከእስር ይለቀቃል፡፡ ነገር ግን ሕዝብ አንድን ግለሰብ ‹‹ለጥቅሜ ሲባል ይታሰርልኝ›› ብሎ ቢጠይቅ ግለሰቡ ወንጀል ሳይሰራ ሊታሰር ይችላል?
አቶ ፊሊጶስ፡- ችግሩ ይኸው ነው፡፡ የሕዝብ ጥቅም የሚባለውን የሚወስነው ማነው? ኅብረተሰቡ በቀጥታ ሠልፍ ወጥቶ ነው? እንዴት ነው የሚሆነው? የሚለው መታየት አለበት፡፡ በመሠረቱ ኅብረተሰቡ ሕግ አውጪውን ወክሏል፡፡ ሕግ አውጪው ‹‹የሕዝብ ጥቅም ማለት ይህ ይህ ነው›› ብሎ በሕጉ ላይ ማስቀመጥ ነው፡፡ አለበለዚያ የሕግ የበላይነትን (Rule of Law) እየጣሰ ነው፡፡ ሕግ መከበር አለበት፡፡ ሕግን የጣሱ ተጠያቂዎች ‹‹ለሕዝብ ጥቅም›› በሚል የሚፈቱ ከሆነ፣ አደጋ ነው፡፡ ተጠርጣሪ የሚታሰረው፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ነው እንጂ ግለሰብን ለመበቀል አይደለም፡፡ ፖሊስ ምርመራ የሚጀምረውና የሚያስረው ከጥርጣሬ በላይ የሆነ ማስረጃ መኖሩን ሲያረጋግጥ ነው ፡፡ ዓቃቤ ሕግም ክስ የሚመሠርተው የፖሊስን የምርመራ መዝገብ በደንብ መርምሮና ክስ ለመመሥረት የሚያስችል ማስረጃ መኖሩን ሲያረጋግጥ መሆን አለበት፡፡ ካልሆነ ግን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 42 መሠረት ተጠርጣሪውን መልቀቅ አለበት፡፡ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› በማለት ክሳቸው እንዲቋረጥና እንዲፈቱ የሚደረገው፤ ያለ ምንም ማስረጃ በህገወጥ ሁኔታ የታሰሩ ናቸው፡፡ እንዲሁም ምንም እንኳን መሪዎች ‹‹የፖለቲካ እስረኛ የለም›› ቢሉም፤ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩትን ነው፡፡ የብዙ ሕዝብ መብትን የጣሰና ጥቅምን ያሳጣን ተጠርጣሪ ወይም ወንጀለኛ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ብሎ መፍታት አደጋ አለው፡፡ ከወንጀል ሕጉ ዓላማም ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ ይጣረሳልም፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን በወንጀል ተጠርጥረው የሚታሰሩ ቢኖሩም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ሊፈቱ የሚችሉ ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን መታየት ያለበት ከፖለቲካ አንጻር ብቻ ሳይሆን፤ በጠባቡ መሆን አለበት፡፡ ሐኪም፣ መምህር፣ ዳኛ፣ መሃንዲስና ፖለቲከኛ ከሆነ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መፍታት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ዝም ብሎ እያሰሩና እየከሰሱ መፍታት፣ አምባገነን የሆነ የመንግሥትን ባህሪ ሊያመጣ ስለሚችል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ ጭምር የሕዝብ ጥቅም የሚለው ግለጽ የሆነ ትርጉም ስላልተሰጠበት፣ ሕግ አውጪው አካል ራሱን የቻለ ሕግ ሊያወጣለት ይገባል፡፡ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› እየተባለ፤ ምንም ወንጀል ያልፈጸመን ተጠርጣሪ በማሰር፤ አሸባሪ ስላለመሆኑ የማስረዳት ሸክሙን በተጠርጣሪው ላይ በማድረግ፤ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲደርስ እንደነበር ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ሕዝብን የሚረብሽና የሚያስፈራራ አዋጅ እያወጡ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ነው›› ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ የሕዝብ ጥቅም ማለት ምን ማለት እንደሆነ መተርጎም አለበት፡፡ ከሳሽም፣ ፈችም ዓቃቤ ሕግ ከሆነ፤ የፍርድ ቤት ሚና ወይም ሕግን መተርጎም ዋጋ የለውም ማለት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም ‹‹ነገ ዓቃቤ ሕግ ስለሚፈታቸው ምን አለፋኝ›› በማለት ለሥራው ግዴለሽ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ለሙስናም መንገድ ይከፍታል፡፡
ሪፖርተር፡- ሕግ አውጪ አካል ክስ የማቋረጥና ፍርደኞችን የመፍታት ሥልጣን ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መስጠት አልነበረበትም፡፡ የተለጠጠ ሥልጣን ስለሆነ ሕዝብን ለመጥቀም ሳይሆን የፖለቲካ መሣሪያ ሆኗል የሚሉ አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ፊሊጶስ፡- አስተያየቱ ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ በእኔ እምነት ግን ‹‹ሥልጣኑ መሰጠት የለበትም ሳይሆን፣ እንደ ምሕረትና ይቅርታ አሰጣጥ አዋጆች፤ የተለያዩ አካላት አባል የሆኑበት ጠንካራ ኮሚቴ አቋቁሞ ዓቃቤ ሕግ የሚያቀርበውን የምሕረት፣ የይቅርታና ክስ የማቋረጥ ጥያቄ ከተመረመረ በኋላ መፈቀድ ወይም መከልከል አለበት፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩን ከምርመራ ጀምሮ እስከ ክስና ተከራክሮ እስከ ማስወሰን ድረስ ያለውን ሒደት የሚጫወተው ዓቃቤ ሕግ በመሆኑ፤ የማቋረጥ ሥልጣን ቢሰጠው ችግር የለውም፡፡ በእርግጥ ከሳሽም ፈችም ሲሆን የሥልጣን ግጭት (Conflict of Interest) ስለሚፈጥር፤ ልዩና ጠንካራ ኮሚቴ በማቋቋም ዓቃቤ ሕግ የሚያቀርበው ምክንያት እየተመረመረ ውሳኔ ቢሰጥ ጥሩ ነው፡፡ በመርህ ደረጃም ሥልጣን መስጠቱ ችግር የለውም፡፡ ሕግ አውጪ ዝርዝር አድርጎ ክስን ማቋረጥና ማስቀጠል የሚያስችሉ መስፈርቶችን በዝርዝር ማስቀመጥ አለበት፡፡ ሥልጣኑም መሰጠት ያለበት በጠባቡ ከሆነ ችግር የለውም፡፡ ዝም ብሎ የፈለጉትን ሰው ክስ ማንሳትና ያልፈለጉትን ክስ ማስቀጠል ለሌላው ዜጋ የሚያስተላልፈው መልዕክት ከባድ ስለሚሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- እስርዎ እንዳሉት በከባድ የሰው ግድያና የሙስና ወንጀል የተከሰሰን ግለሰብ ወይም ቡድን ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› ብሎ ክስ አቋርጦ መፍታት ከእስር ውጪ ላለው ዜጋ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድነው? ከሕግ የበላይነትና የፍትሕ ሥርዓቱን ከማስከበር አንጻርስ እንዴት ይታያል?
አቶ ፊሊጶስ፡- የሚያስፈራውና ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ይህ ነው፡፡ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› እየተባለ ሁለትና ሦስት ጊዜያት እየታሰሩ የሚፈቱ ይኖራሉ፡፡ የሕዝብ ጥቅም የሚባለውን ሕዝብ ሊያውቀው ይገባል፡፡ ‹‹እነ እከሌ የተፈቱት እኮ ለእኛ ተብሎ ነው›› ማለት አለበት፡፡ ለምሳሌ እንደነ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ዓይነት ሐኪም ቢፈታ ለሕዝብ ጥቅም ነው ያስብላል፡፡ ምክንያቱም በርካታ ሕሙማንን ስለሚያክሙ፡፡ እንደነ ኃይሉ ሻውል (ኢንጂነር)ና ታዬ ወልደሰማያት(ደ/ር) ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲ መሪና አመራር ቢፈታ ለሕዝብ ጥቅም ነው፡፡ ምክንያቱም፣ የሚከተላቸው በርካታ ሕዝብ አላቸው፡፡ “ስለዚህ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› የሚባለውን ጥቅም ሕዝብ ማወቅ አለበት፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በቀላል ወንጀል ተርጥረው ክስ የተመሰረተባቸውና መጠነኛ ቅጣት የተወሰነባቸው በፌደራል ማረሚያቤቶችየሚገኙ 4074 ግለሰቦች ከእስር እንዲፈቱ ያስተላለፉት ትዕዛዝ፤ ተገቢና እውነተኛ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የተደረገ ውሳኔ ነው፡፡ በክልሎች ማረሚያቤቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ በቀላል የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸውና ቀላል ቅጣት የተወሰነባቸው በርካታ ግለሰቦች እንዲፈቱ የተላለፈው ውሳኔም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የተሰጠ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሕዝብ ላይ ሊመጣ የሚችልን አደጋ መከላከል ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የተደረገ በመሆኑ የሚደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን በተለይ አስፈጻሚ አካላት ራሳቸው ተርጉመው፣ ራሳቸው እንዲፈጽሙት ማድረግ ከፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውጪ ነው፡፡ በሕዝብ ጥቅም መነሻ በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ ሲታወቅ፣ የተጀመረው ምርመራ እንዲቀጥል እንደሚያደርግና ምርመራው በሕጉ መሠረት መከናወኑን እንዲያረጋግጥ አዋጁ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ተገቢ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ‹‹የሕዝብ ጥቅም›› የሚለው ትርጉም ባልተሰጠበት ሁኔታ ወይም በአዋጁ ተዘርዝሮ ሳይቀመጥ፣ ሰው ገድሎ የታሰረውንም፣ በትንሽ ወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረውም፣ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የታሰሩትን ሁሉ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› በማለት ክስ ማንሳቱ እንደ አገር አደጋ አለው፡፡
ሪፖርተር፡- በበርካታ አዋጆች ላይ ‹‹የሕዝብ ጥቅም›› ብሎ ከመጥቀስ ውጭ፤ምን ምን እንደሆኑ ዝርዝር መስፈርቶች ባልተቀመጡበት ሁኔታ፤ ዓቃቤ ሕግና መርማሪ ከሳሽ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው መሥራት እንዳይችሉ ከማድረጉም በተጨማ የፖለቲካ መሣሪያ ሆኗል የሚሉ አሉ?
አቶ ፊሊጶስ፡- ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሹመት የፖለቲካ ሹመት ነው፡፡ በሙያ ብቻ ሳይሆን የሕግ ትምህርት የሌለው ሁሉ የተሾመበት ጊዜም ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም የካቢኔ አባላት ናቸው፡፡ ገለልተኛ እንዲሆኑ አልተፈለገም፡፡ ነገር ግን መሆን የነበረበት ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ ነበር፡፡ባየነው የ30 ዓመታት የሕግ ሥርዓት ውስጥ፤ የፍትሕ ሚኒስቴር/ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ በመሆኑም ከፖለቲካ ነጻ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ለዴሞክራሲ ግንባታና ለሰብዓዊ መብት መከበር ሲባል ገለልተኛ መሆን ነበረበት፡፡ ዜጎች ዝም ብሎ እንዳይታሰሩ፣ ሰብዓዊ መብታቸው እንዳይጣስ የፍትሕ አካሉ (ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) ከፍተኛ የሆነ ድርሻ አለው፡፡ ማንኛውም መብት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ መጣስ የለበትም፡፡ ከተጣሰም የሚጣሰው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ የግለሰቦችን መብት የጣሰ ሰውን ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› እያሉ ከመፍታት በፊት፣ ተጠቃሚው ሕዝብ ስንት ነው? የሚለውን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ የምሕረት አዋጁ ‹‹የሕዝብንና የመንግሥትን ጥቅም መሠረት በማድረግ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በራሱ ተነሳሽነት ወይም ከክልሎች በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት፤ ምሕረት የሚሰጥባቸውን ወንጀሎችና በወንጀል የተጠረጠሩ፣ የተከሰሱ ወይም የወንጀል ፍርድ የተላለፈባቸውን ለይቶ ለቦርዱ ያቀርባል›› ብሎ ደንግጓል፡፡ እዚህ ላይ ማየት ያለብን ‹‹መንግሥት የተለየ ጥቅም አለው ወይ?›› የሚለውን ነው፡፡ መንግሥት ይዞ የሚጓዘው ወይም የሚያስከብረው የሕዝብን ጥቅም ነው፡፡ ከሥልጣን አንጻር ካልሆነ በስተቀር መንግሥት የሕዝብ ተወካይ በመሆኑ የተለየ ጥቅም ሊኖረው አይችልም፡፡ ለፖለቲካው ከተባለም፣ በብዙ አገሮች የፖለቲካውን ሚና የሚጫወተው አስፈጻሚው አካል ነው፡፡ ይቅርታም፣ ምሕረትም፣ ክስ የማቋረጥም፣ ቅጣትን ማንሳትም ሆነ መክሰስም ለሕዝብ ጥቅም ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ተገማች የማይሆን የሕግ አፈጻጸምን የሚፈጠር መሆኑን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ጥቅም የሚለውን ሕግ አውጪው አካል ነገ ዛሬ ሳይል ማስተካከል አለበት፡፡ ለአስፈጻሚው ዝም ብሎ መተው የለበትም፡፡ መተርጎም አለበት፡፡ ለወረዳና ለክፍለ ከተማ ካድሬ በመተው የሕዝብን ጥቅም የሚያሳጣ ውሳኔ ማሳለፍ አንድ ቀን ተጠያቂነትን ያመጣል፡፡ በመሆኑም ዝርዝር መስፈርቶችን አስቀምጦ ለአስፈጻሚው አካል መሰጠት አለበት፡፡ ዝም ብሎ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ለሕዝብ ጥቅም›› እየተባለ ሕዝብን ማፈናቀል፣ ማሰርና መፍታት፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ሲያስነሳ እንጂ ‹‹ጥቅሜ ተከብሮልኛል አርፌ ልቀመጥ›› ሲል አልታየም፡፡ ዝም ብሎ ማሰርና ማፈናቀል በአዲስ አበባ ዙሪያና በኦሮሚያ ያስነሳውን ነገር ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ ‹‹መብቴ ተጥሷል›› እያለ ሕዝብ ሁከት እያስነሳ ባለበት ወቅት ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› እየተባለ የሚፈጸም ድርጊት፣ በነገው ትውልድ ላይ ሌላ ችግር ያስከትላል፡፡
ሪፖርተር፡- አገርን እንደ አገር ለማስቀጠል፣ ሕዝብን በሥርዓት ለመምራት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን የሕግ የበላይነትን ማክበር አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የፍትሕ ሥርዓቱ የተጣሰበትና ወደ ሥርዓት አልበኝነት የተገባበት ሁኔታዎች ታይተዋል፡፡ በተለይ ያለ ምክንያት ማሰርና ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› በማለት መፍታት ሕዝብ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሽር ከማድረጉም ሌላ ወደ አመጽ፤ሁከትና ሥርዓት አልበኝነት እየተቀየረ መምጣቱን የሚገልጹ አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ፊሊጶስ፡- ትክክል ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ላይ የብሔር ትኩሳት ያንዣበበበት ወቅት ነው፡፡ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ የአንድ ብሔር ከእስር ሲለቀቅ፣ ሌላው ብሔር ደግሞ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ነገ ስለምፈታ›› በሚል የበለጠ ሌላ ተጨማሪ ወንጀል እንዲፈጽሙ ያበረታታል፡፡ በተጎጂ በኩል ደግሞ ‹‹መንግሥት እንደሆነ ሕጉን አያስከብርም፡፡ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ወንጀል የፈጸመብኝ አካል በመለቀቁ እኔም በራሴ የጎበዝ አለቃ አቋቁሜ መብቴን አስከብራለሁ›› በሚል በመንግሥት ላይ አመጽ እንዲነሳ ያደርጋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ እያጣ መምጣቱን ነው፡፡ በፍርድ ቤት ላይም ‹‹ዛሬ ቢፈረድብኝ ነገ እወጣለሁ›› በማለትና በችሎት ዳኞች እንዲዘለፉና ፍትሕ ሰጪው አካል እንዲናቅ፣ ውሳኔ እንዳይከበርና አፈጻጸም እንዳይከናወን ያደርጋል፡፡ ወንጀል ፈጻሚው እንዲበረታታ ያደርጋል፡፡ የጎጂም ሆነ የተጎጂ አካል ‹‹ምን ይመጣል›› በማለት ነገ ሌላ ወንጀል እንዲፈጽሙ የሚያበረታታ ነው፡፡ በተለያዩ ክልሎች ያሉ ወጣቶች እየተሰበሰቡና የራሳቸውን ስያሜ እየሰጡ ሰውን እስከ መስቀል፣ እስከማቃጠልና መግደል የደረሱትም ምንም አይመጣም በሚል ነው፡፡ ይህ በቀጣይ ሰላም እንዳይኖር፣ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባና የወንጀል ሕግ ዓላማ እንዳይሳካ የሚያደርግ በመሆኑ ሊታሰብበትና ሊስተካከል ይገባል፡፡ መጠርጠርም፣ ማሰርም፣ መክሰስም፤ ተከራክሮ ፍርድ ማግኘትም፣ ክስ ማንሳትና ማቋረጥም ከወንጀል ዓላማ አኳያ መሆን አለበት፡፡ ለሕግ የበላይነት መከበር መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት አጥፍቶ የተከሰሰን ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› በማለት መፍታት ተገቢ ነው ይላሉ?
አቶ ፊሊጶስ፡- ሰውን የገደለና በመግደል የተጠረጠረ ሰው ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ነው›› ሊባል የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ሰውን ሆን ብሎ ወይም በቡድን ሆኖ ከገደለ ለሕዝብ ጥቅም ነው ሊባል አይችልም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ደረቅ ወንጀሎች፣ ከታክስ ጋር በተገናኘ በትንሽ ነገር ከሚታሰር፤ በገንዘብ ተቀጥቶ ቢፈታ ወጥቶ የሚሠራው ለሕዝብ ጥቅም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ግብር አለመክፈል የሕዝብ ጥቅም ስለሆነ ቀጥተኛ ጥቅም አለው፡፡ ከንብረት ጋር በተገናኘና በሙስና የታሰረ የወሰደውን ገንዘብ ከመለሰ ክሱ ቢነሳለት ወይም ቢቋረጥለት፣ በፖለቲካ ምክንያት የታሰረ ቢፈታ ለሕዝብ ጥቅም ሊባል ይችላል፡፡ ግለሰብንም ሆነ መሪን የገደለ ግን፣ መግደሉ እውነት መሆኑን አረጋጋጦ ተገቢውን ቅጣት መስጠትና ነገም ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይፈጽም ያግዛል፤ሌላውንም ያስተምራል እንጂ፤ በተለጠጠ ሥልጣን ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› ብሎ መፍታት ትክክል አይደለም፡፡ አስፈጻሚው በፈለገው መንገድ የሚያስርና የሚፈታ ከሆነ ሕግ ለምን ያስፈልጋል? አያስፈልግም፡፡ ስለዚህ ሕግ አውጪውም፣ ተርጓሚውም ሆነ ሕግ አስፈጻሚው አንዱ አንዱን እየጠበቀ (Check and Balance) መሄድ አለበት፡፡ የአንድ አገር የፍትሕ ሥርዓት እየተከበረ የሚሄደውም ተጠባብቆ መሥራት ሲቻልና ሕግና ሕጉን ብቻ በማስፈጸም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሕግ አውጪው አካል(የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) ሕግ ከማጽደቅ ባለፈ የወጣውን ሕግ አስፈጻሚው በተገቢው ሁኔታ እያስፈጸመ መሆኑን መከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን አስፈጻሚው ከሕግ ውጪ ሲንቀሳቀስ፣ ዕርምጃ ሲወስድ አይታይም፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ፊሊጶስ፡- ስህተቱ ከሕግ አውጪው ነው፡፡ ሕዝብን የወከለው (በበቂ ሁኔታ ይወክላል አይወክልም የሚለው እንዳለ ሆኖ) ሕግ አውጪው ነው፡፡ ‹‹የሕዝብ ጥቅም›› የሚለውን እንኳ በደንብ ተነጋግሮ ትርጉም ሳይሰጥ፣ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ከሆነ እሰረው፣ ፍታው›› የሚል ከሆነ ፤ለአስፈጻሚው የሚሰጠው ያልተገደበ ሥልጣን ነው፡፡ አብዛኛው አስፈጻሚ አካል ራሳቸው በሚመቻቸው አኳኋን ሕጉን አርቅቀው ያቀርባሉ፡፡ ያለምንም ተቃውሞ ይፀድቅለታል፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ አስፈጻሚ አካላት ሕግ አርቅቀው እንዲያቀርቡ መፈቀድ የለበትም፡፡
ሪፖርተር፡- ሕግ አውጪው ያፀደቀውን ሕግ አፈጻጸም፤ መከታተልና መቆጣጠር የለበትም?
አቶ ፊሊጶስ፡- አለበት፡፡ መጀመርያ ሕጉ ሲወጣ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያመች አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ መቆጣጠሪያ ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ መጠየቅ የለበት መጠየቅ አለበት፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን የሕዝብ ጥቅም ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚደነግግ አዋጅ መውጣት አለበት፡፡ ብዙ ሰዎች ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላና በሒደት ላይም እያለ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቤቱታ የሚያቀርቡት ጥቅማቸውን የሚያሳጣ ውሳኔ ስለሚሰጥባቸውና ክስም ስለሚቀርብባቸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ ሕግ እንዲወጣ ሲፈለግ ሐሳቡን ከማመንጨት እስከማርቀቅ ያለውን ሒደት አስፈጻሚው አካል መሥራት የለበትም፡፡ አስፈጻሚው ሐሳቡን አመንጭቶ ራሱ የሚያረቅ ከሆነ፤ ለራሲ አፈጻጸም በሚያመቸው አኳኋን ስለሚያዘጋጀው ሕግ ሳይሆን መጨቆኛ መሣሪያ ይሆናል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲደረግ የቆየው ይኸው በመሆኑ ሕዝብ ለተቃውሞና ሁከት እንዲነሳ ሆኗል፡፡ ኃላፊነቱን ወስዶ መሥራት ያለበት ሕግ አውጪ መሆን ሲገባው፤ የቀረበለትን ረቂቅ ሕግ በሙሉ ድጋፍ ከማጽደቅ ያለፈ ተግባር ሲፈጽም አለመታየቱንና ያላረቀቀውን ሕግ መቆጣጠር ስለማይችል ለሥርዓቱ መድከም ተጠያቂ ነው የሚሉ አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ፊሊጶስ፡- በመጀመርያ ‹‹ሕግ አስፈጻሚ አካላት እነማን ናቸው? ሕግ አውጪው አካልስ ማን ነው?›› የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለስሙ የሕዝብ ተወካይ ይባል እንጂ የአንድ ፓርቲ ተወካይ ነው፡፡ ሕግ አውጪም ሆነ አስፈጻሚው የአንድ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ የተወሰኑ ዓመታት ላይ በጣት የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ቢቀላቀሉም ድምፅ አልነበራቸውም፡፡ የፓርቲ ዲሲፒሊን የሚባል ነገር አለ፡፡ ፓርቲው የወሰነውን ነው የሚከተሉት፡፡ ሕግ አውጪውን ሲመራው የነበረው ሕግ አስፈጻሚው ነው፡፡ እንደፈለገው ሕጎችን ያመነጭና ያረቃል፡፡ ሁሉም ሕጎች ለሕግ አውጪው ቀርበው ከመጽደቃቸው በፊት በፍትሕ ሚኒስቴር/ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በኩል ማለፍ ሲገባቸው አስፈጻሚው እንደፍላጎቱና እንደሚፈልገው ሲያቀርብ በሙሉ ድምፅ ይፀድቅለታል፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ በመርህ ደረጃ መሆን የነበረበት፣ ምንም እንኳን በፓርቲ አባልነት የሚገናኙ ቢሆኑም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚው ያቀረበለትን ረቂቅ ሕግ በትክክል ለሕዝብ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለውን መመርመር አለበት፡፡ ካልጠቀመ ‹‹አይጠቅምም›› ብሎ ውድቅ ማድረግ አለበት፡፡ ነገር ግን እስካሁን ግን አንድም ረቂቅ ቀርቦ ውድቅ የተደረገ የለም፡፡ አሁን በሪፎርሙ ብዙ አዋጆች እንዲሻሻሉ ወይም እንደ አዲስ እንዲረቀቁ ቀርበዋል፡፡ ሕግ አውጪው ገለልተኛና ከአስፈጻሚው የተለየ መሆን አለበት፡፡ እስካሁን በሚታየው ሁኔታ የአብዛኞቹ ሕግ አውጪ አባላት አለቆቻቸው ሥራ አስፈጻሚው ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ለነገ ሹመት፣ በፖለቲካው ውስጥ ለመቆየትና የተሻለ የሥራ ቦታ ለመመደብ ሲሉ እውነተኛ ለሕዝብ ጥቅም የሚውል ሕግ ያወጣሉ ወይም የቀረበላቸውን ወገንተኛ ሕግ ውድቅ ያደርጋሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ የሚቀርበውን ያጋደለ ሕግ ‹‹አይሆንም ለማለት የፖለቲካ ባህሉም ሆነ ያላቸው እውቀት አልፈቀደላቸውም››፡፡ የሕዝብ ጥቅም የሚለውን ራሱ በፈለገው መንገድ ተርጉሞ እንዲጠቀምበት ለአስፈጻሚው መተው የሕግ የበላይነት እንዳይከበርና ሕዝብን ለአመጽ እንዲነሳሳ መፍቀድ ነው፡፡ ሕዝብን የሚያስለቅስና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽምን ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› ብሎ ክስ አንስቶና አቋርጦ መፍታት ውጤቱ የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ‹‹ለሕዝብ ጥቅምና ለልማት›› እየተባለ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው ይፈናቀላሉ፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎች ባህላዊ እሴቶቻቸውን አጥተውና ትተው ላላስፈላጊ እንግልት ሲዳረጉና ተገቢ የሆነ ካሳ እንኳን ሳይከላቸው ለችግር ተጋልጠው ተስተውለዋል፡፡ ነገር ግን አስፈጻሚው ይህንን የሚያደርገው በተጠናና ‹‹እውነትም ለሕዝብ ጥቅም ነው›› ከሚያሰኝ ይልቅ እስከ አሥር ዓመታትና ከዛም በላይ የፈረሱ ቦታዎች ታጥረው ይቀመጣሉ፡፡ የቆሻሻ መጣያ፣ የማጅራት መቺዎች መደበቂያና ሕገወጥ ድርጊት መፈጸሚያ ሆነው መታየታቸውን ከሕግ አንጻር እንዴት ይታያል? የመንግሥትስ ሥራ ከአልሚነት ይልቅ ምቀኝነት ሆኗል ለማለት አያስችልም?
አቶ ፊሊጶስ፡- በእኔ ዕይታ መንግሥት ሆን ብሎ ዜጋ እንዲጎዳ ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን አስፈጻሚው የሚያቀርበው የልማት ዕቅድና አሠራር በጥናት ላይ ያልተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያለምንም ፈቃድ ዝም ብሎ ሲፈርስ ይታያል፡፡ ግን ይህንን መወሰን ያለበት ማነው? ወረዳ ነው ክፍለ ከተማ ? ይህ መለየትና መታወቅ አለበት፡፡ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ቤታቸው ፈርሶ ሲንከራተቱ የሚሞቱ አሉ፡፡ ምንም ገቢ የሌላቸውና ያላቸውን አከራይተው ይኖሩ የነበሩ በወረዳ አስተዳዳሪና የክፍለ ከተማ ሹም ቤታቸው ፈርሶ ለድህነት የተጋለጡ፣ ለልመና የተቀመጡና የተጎሳቆሉትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ የሚሰጣቸው ካሳና ምትክ ቦታ ለምንም የሚጠቅም አይደለም፡፡ በቂ መሠረተ ልማት የሌለውና ለልጆቻቸው ትምህርት ቤትና ለሥራቸው አመቺ ያልሆነ ሩቅ ቦታ አሽቀንጥሮ ወርውሮ ‹‹ለሕዝብ ጥቅምና ልማት›› ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ሕዝብ የሚባለው ስንት ነው? አሥር ሰው፤ ሃምሳና መቶ ሰው ሕዝብ አይደለም? አሰራሩ ግልጽ አይደለም፡፡ በሌሎች አገሮች እንደሚታየው ለሕዝብ ጥቅም የሚባለው ሆስፒታል ለመገንባት፣ ዩኒቨርሲቲና መንገድ ለመገንባት ነው፡፡ ነገር ግን ለማን እንደሚሰጥና ምን እንደሚሠራበት ሳይታወቅ በልማት ስም ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀልና ችግር ላይ እንዲወድቁ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ በብስጭት፣ በጭንቀትና በችግር ስንት ሰው ሕይወቱን እንዳጣ ግምት ውስጥ አስገብቶ በቀጣይ አሠራር፣ ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡ እነ አክሊሉ ሀብተወልድ ሲገደሉ፣ ደርግ የኢሕአፓ አባላትን ሲገድል፣ መሬት ላራሹ ሲታወጅ፣ ሰው ገድሎ የታሰረ ሲፈታ ወዘተ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› እየተባለ ነው፡፡ ይህ ነገር ግን ለኢትዮጵያ ይጠቅማል? ሕዝብን ያገለገለ፣ አገሩን ያገለገለ፣ማኅበረሰብ ሲፈናቀልና ቤት አፍርሶ አጥር አጥሮ ለዓመታት ማስቀመጥ ለሕዝብ ጥቅም ሊሆን አይችልም፡፡ የፍትሐ ብሔሩም ሆነ የወንጀል ሕጉ እየተጣሰ ሕዝብ ከፍተኛ በደል እየደረሰበት ነው፡፡ ምንም ይሁን ምንም ለሕዝብ ጥቅም የተባለን ነገር እንዲያስፈጽም ለወረዳና ክፍለ ከተማ ካድሬ ሰጥቶ ሕዝብን ማማረር ውጤቱ የከፋ ስለሚሆን ‹‹የሕዝብ ጥቅም›› የሚባለው ነገር ሕግ ወጥቶለት በአግባቡ መፈጸም አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደሚሰማው ‹‹የፖለቲካ እስረኞች የሉም›› ይላል፡፡ በፖለቲካ አቋማቸውና በሚያራምዱት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የታሰሩ ሰዎች እንደሌሉ ቢናገርም፤ ክስ ሲያቋርጥና የተወሰነ ቅጣትን ሲያነሳ ደግሞ ‹‹ለፖለቲካው ምህዳር መስፋት ሲባል›› እያለ ከእስር ይፈታል፡፡ እርስ በርሱ አይጣረስም?
አቶ ፊሊጶስ፡- በትክክል ይጣረሳል፡፡ የ1997 ዓ.ም. ሁኔታን ብናስታውስ እንኳን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ሲያደርጉ በነበረው የፖለቲካ ፍጭት ምክንያት ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡ በወንጀል ሕጉ የፖለቲከኛ እስረኛ፣ የኢኮኖሚ እስረኛ ወይም ማኅበራዊ እስረኛ ማን እና ምን ዓይነት እንደሆነ የሚገልጽ ነገር የለም፡፡ ሕገ መንግሥቱንና ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመጣስ፤የኦነግ አባል በመሆኑ፣ መንግሥትን በኃይል ለመጣል በሚሉ ቃላቶችና ምክንያቶች ምንም ዓይነት ደረቅ ወንጀል መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሳይኖር፤ የፖቲካ አንድምታ ባላቸው ምክንያቶች ይታሰራሉ፡፡ ወይም ታስረው ነበር፡፡ በማንኛውም መለኪያ እስራቸው የሚያመለክተው ፖለቲካን እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ትልልቅ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን አስሮ ‹‹የፖለቲካ እስረኛ የለንም›› ማለት፣ ጭፍን የሆነ አመለካከትና የሚጎዳ ነው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ‹‹ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ሲባል›› ብሎ ከእስር መፍታት እርስ በርሱ የሚጣረስ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን፤ ማለትም በፖለቲካ አመለካከት፣ በሃይማኖት ልዩነትና ሐሳብን በግለጽ ማሰር ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ክልክል ስለሆነ፤ እነዚያን ድንጋጌዎች ለማለፍ ተብሎ ፖለቲከኛውን ‹‹በሠራው ወንጀል እንጂ በፖለቲካ አመለካከቱ የታሰረ ሰው የለም›› ማለት እውነታውን ለመሸሽ ከመሞከር ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ በመሠረቱ ሰው በፖለቲካ አመለካከቱ መታሰር የለበትም፡፡ ከታሰረ ደግሞ ለፖለቲካ ምህዳር መስፋት ተብሎም መፈታት የለበትም፡፡ ለአገር ሰላምና ደኅንነት እንጂ ከመቶ በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለቡት ሁኔታ፣ “ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ሲባል›› የሚለው አካሄድ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ከመጣሱም ሌላ ከሕገ መንግሥቱም ጋር አይሄድም፡፡