በወንጀል ህጉም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህጉ ተደንግጐ እንደሚገኘው፤ ጭካኔ የተሞላበት የግፍ አገዳደል ግድያ ከፈፀሙ፣ አካል ካጐደሉ፣ ህፃናትን አስገድደው ከደፈሩ፣ ዘር ለይተው ግድያ ከፈፀሙና ሌሎች ለሕዝብ ሞራል ተቃራኒ የሆኑ ተገባራትንና የወንጀል ድርጊቶችን ከፈፀሙ ተጠርጣሪ ተከሳሾችና ፍርደኞች በስተቀር፤ በሌሎች የወንጀል ጉዳዮች ተጠርጥረው የተከሰሱና የተፈረደባቸውን መንግስት በይቅርታና በምህረት እንዲፈታቸው እየተጠየቀ ነው።
ጥያቄው የቀረበበት ምክንያት፤ የፌዴራል መንግስትና የክልል መንግስትት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ፤ “ለህዝብ ጥቅምና ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ሲባል” እያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪ ተከሳሾችንና ፍርደኞችን ክስ በማቋረጥና በማንሳት ከእስር እንዲፈቱ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው። በእስር ላይ የሚገኙ ተከሳሾችና ፍርደኞች ቤተሰቦች፤ እንዲሁም የህግ ባለሙያዎችና ሌሎች የማህበረሰቡ አካላት በሚሰጡት አስተያየት “ወንጀል ትልቅም ይሁን ትንሽ ወንጀል ነው። ሁሉም በሰራው ወንጀል በህጉ ተደንግጐ የሚገኘውን ቅጣት ሊቀጣ ይገባል። ዛሬ የፈፀመው ወንጀል ‘ቀላል ወንጀል ነው’ ተብሎ አንድ ተጠርጣሪ ተከሳሽ ወይም ፍርደኛ በይቅርታና በምህረት ቢለቀቅ፤ ነገ በሺህ የሚቆጠሩ ተመሳሳይ ተግባር ፈፃሚዎችን ከማፍራት የዘለለ ውጤት ሊያመጣ አይችልም” ይላሉ። በመሆኑም ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉንም ተጠርጣሪ ተከሳሾችንና ፍርደኞች በይቅርታና በምህረት እንዲፈቱ ውሳኔ ሰጥቶ፤ የተጐጂ ወገኖችን ይቅርታ እንዲጠይቁ በማድረግ፤ሀገራዊ አርቅ ማውረድና የሀገርን ሠላም በማስፋት፤ በዓለም ደረጃ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በጋራ መከላከልና ሃገራዊ ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፤ መንግስት አቤቱታቸውን እንዲሰማቸው እየጠየቁ ነው።