ባለፉት ሶስት አሥርት አመታት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሀብታም ኢትዮጵያውያን ተፈጥረዋል። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ለወገናቸውና ለሀገራቸው ሊደርሱላቸው የሚገባው በዚህ በክፉ የወረርሽኝ ጊዜ በመሆኑ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሀገሪቱ መንግስት መቀመጫ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ (ኢንጂነር) አሳስበዋል።
መኖር፤ ማጌጥ፤ በሀብት ላይ ሀብት እያካበቱና እየተደሰቱ መቀጠል የሚቻለው ህዝብና ሀገር ሲኖሩ ብቻ በመሆኑ፤ በማንኛውም መንገድ ይሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ባለሀብት የሆኑ ኢትዮጵያውያን ለወገኖቻቸው ሊደርሱላቸው የሚገባው በዚህ ወቅት መሆኑን መሪዎቹ ተናግረዋል። ባለፉት ጥቂት ሣምንታት ውስጥ በተለያዩ የንግድ ሥራ፤ ኢንቨስትመንትና ሌሎች የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶች፣ የንግድ ተቋማት (እንደ የንግድ ባንኮች ያሉ)፣ የሙዚቃ ባለሙያዎችና በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን ለመርዳት ያደረጉት ርብርብ እጅግ በጣም የሚያኮራ ቢሆንም፤ ድምፃቸውን ያጠፉ በርካታ ባለሀብቶች መኖራቸውም ተጠቁሟል። ወገን ከሌለ ሀገር ሀገር ልትሆን ስለማትችል “አለንልህ” የሚሉበት ጊዜ አሁን በመሆኑ ሊተባበሩና ሊያግዙ እንደሚገባ መሪዎቹ ተናረዋል። በኮንስትራክሽን፣ በአበባ፣ በአዝዕርት፣ በፋብሪካና በተለያዩ ኢንዱስት የሥራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ በለሀብቶች ለወገናቸውና ለሀገራቸው አለኝታነታቸውን እንደሌሎቹ ባለሀብቶች ማሳየት እንደሚጠበቅባቸውና የውዳታ ግዴታም እንዳለባቸው ተገልጿል።
መኖሪያ ቤታቸውን፣ ሆቴላቸውን፣ የሥብሰባ አዳራሾቻቸውን፣ ትምህርት ቤቶቻቸውንና ተሽከርካሪዎቻቸውን በመለገስ ለወገኖቻቸው ቀናኢነታቸውን ያሳዩ በርካታ ኢትዮጵያውን ክብርና ምሥጋና እንደሚገባቸውም መሪዎቹ ተናግረዋል።