እ.አ.አ በታህሣሥ ወር 2019 መጨረሻ ላይ በቻይና አገር ሁቤ ግዛት ውሀን ከተማ የተነሳው ኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ፤ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ዓለምን በፍጥነት አዳርሷል፡፡ ወረርሽኙ ከአንዱ ወደ ሌላው መተላለፍና መዛመት ብቻ ሳይሆን ገዳይነቱም ፈጣን ነው፡፡ ወረርሽኙ በሶስት ወራት ውስጥ በመላው ዓለም ከ6ዐዐ ሺህ በላይ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ ከ3ዐ ሺህ በላይም የሚሆኑ ሰዎችም ህይወታቸው አልፏል፡፡ ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጠባቸው በኋላ ማገገም የቻሉት ከ134 ሺህ በላይ መሆናቸውንም እስከ መጋቢት 21 ቀን 2ዐ12 ዓ.ም የወጡ ዓለም አቀፍ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ዜጐቻቸው በብዛት ከሞቱባቸው መካከል ከፍተኛውን ቁጥር ያስመዘገቡት ከአውሮፓ አገሮች ውስጥ ጣሊያንና እስፔን ናቸው፡፡ ጣሊያን ከ1ዐ ሺህ በላይ፤ እስፔን ደግሞ ከ5 ሺህ በላይ ዜጐቻቸው ሞተውባቸዋል፡፡ ወረርሽኙ የተነሳባት ቻይና 81 394 ዜጐቿ በወረርሽኙ ተጠቅተውባት የነበረ ሲሆን 3,295ቱ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡ ወረርሽኙ በከፍተኛ ፍጥነት እተዛመተባትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ11ዐ ሺህ በላይ ዜጐቿ በቫይረሱ መጠቃታቸው የታወቀው አሜሪካ ስትሆን ከ2ዐዐዐ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ወረርሽኙ በ47 አፍሪካም አገራት የተሠራጨ ሲሆን እስከ መጋቢት 21 ቀን 2ዐ12 ዓ.ም ድረስ ከ3,800 በላይ ዜጎች በቫይረሱ የተጠቁ ሲሆን የሟቾችም ቁጥር 110 ደርሷል፡፡ በአልጄሪያ ከ25 በላይና በግብፅ ከ24 በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከአፍሪካ ሀገሮች ከ1100 በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ የተጠቁባት ሀገር ደቡብ አፍሪካ ስትሆን፤ ግብጽና አልጀሪያም ከ456 እና ከ367 በላይ ዜጎቻቸው ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ሌሎቹም የአፍሪካ አገራት ዜጎቻቸው በወረርሽኙ እየተጠቁና በሞት እየተነጠቁ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ግን በበሶስት ወራት ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የዜጐች ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቅርርብ ያላቸው በመሆኑ ማለትም በከፍተኛ ቅርርብና መጨባበጥ ሠላምታ መለዋወጥ፤ሲያስነጥሱ ጥንቃቄ አለማድረግ እንዲሁም እጅን በአግባቡ አለመታጠብ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያም ዜጐቻቸው በቫይረሱ ከተጠቁባቸው አገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡ ምንም እንኳን ሞት ያልተመዘገበባት እና የተጠቂ ሰዎች ቁጥር እስከ መጋቢት 21 ቀን 2ዐ1ዐ ዓ.ም ድረስ 21 ብቻ ቢሆንም፤ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያስፈልጋታል፡፡ መንግስና የጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የሚያስተላልፉትን ምከርና መመሪያ መፈፀም ለህይወት ዋስትና መስጠትና ወገኖችን መታደግም ጭምርም ነው፡፡ ምንም እንኳን ማህበራዊ ግንኙነቶች እጅግ የተወሳሰቡ፣ ሁሉንም ነገር ተነካክቶና ተጠጋግቶ የመፈፀም ልምድ ቢኖርም፤ አሁን ላይ ግን አካላዊ ርቀትን (Physical Distance) መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ በመተላለፊያ መንገዶች፣ ትራንስፖርት መጠበቂያ ቦታዎችና ፌርማታዎች፣ በርካታ ሰዎች የሚገናኙባቸው አደባባዮች፣ በተለይም በቤተ አምልኮ ስፍራዎች(የቤተክርስቲያናት ቅጥር ጊቢ) ያለው መጠጋጋትና እየተገፋፉ መንቀሳቀስ ያልቀረበት ሁኔታ ስላለ፤በራሳቸው እንዲያስተካክሉ ውይም ያ የማይሆን ከሆነ የመንግስት መመሪያን አስፈፃሚ አካላት እርምጃ በመውሰድ የማስፈጸም ግዴታ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ከአቅም በላይ የሆነና ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሲያጋጥም አስፈላጊውን እርምጃ ወስዶ ማዳን ኃላፊነት አለበት፡፡
ሕዝብን የማዳን ኃላፊነት የመንግስት ከመሆኑ አንፃር፤ ለሕዝቡ ደህንነት ሲባል ያወጣውን መመሪያ መተግበር ደግሞ የሕዝቡ ኃላፊነት መሆኑን ማወቅም ያስፈልጋል፡፡ ወረርሽኙን መከላከልና መግታት የሚቻለው፤ በጤና ባለሙያዎች የሚነገሩትን ወይም የሚተላለፉትን የጥንቃቄ መንገዶች መፍትሄዎች ማለትም በቤት ውስጥ በመቀመጥ፣ እጅን አዘውትሮ በመታጠብ፣ የአካል ርቀትን በመጠበቅ(Phisical Distance)፣ ባለመጨባበጥና የመንግሥትን መመሪያ በተግባር ላይ በማዋል ብቻ በመሆኑ; እነዚህን ተግባራት መፈፀም ግዴታም ጭምር ነው!