ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ እ.ኤ.አ. 2019 የዲሴምበር ወር መገባደጃ ላይ በቻይና ሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ ውስጥ ከአራት ወራት በፊት መከሰቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ 213 አገሮችና ግዛቶችን በማዳረስ የ302,493 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን፣ 4,444,670 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ማጥቃቱን፣ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ሪሶርስ ሴንተር የግንቦት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. የ8፡00 ሰዓት መረጃ ያሳያል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በቻይና ውሀን ከተማ ውስጥ መከሰቱ በተሰማ አጭር ጊዜ ውስጥ ዓለምን እያዳረሰ ቢሆንም፣ ቫይረሱ በ1937 መኖሩ በምርምር መረጋገጡን የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከእንስሳት ወደ ሰው እንደሚተላለፍ በ1960ዎቹ እንደታወቀና በ1970ዎቹ ደግሞ አራት ዝርያዎች እንዳሉት ታውቋል፡፡ ከቫይረሱ ዝርያዎች ውስጥ ቤታ የሚባለው ቫይረስ ከሰው ወደሰው በእስትንፋስ የሚተላለፍ፣ በመተንፈሻ አካላት ላይ ችግር የሚያመጣና ከሌሎቹ የቫይረሱ ክፍሎች የተለየ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የዓለም ከፍተኛ ሥጋት ሆኖ የሚገኘው ኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ቤታ የሚባለው ቫይረስ ዝርያ ሲሆን፣ መጠሪያውንም ያገኘው ከላቲን ነው፡፡ በአጉሊ መነፅር ሲታይ አክሊል (ዘውድ) የሚመስል ቅርፅ ስላለው ስያሜውን ማግኘቱን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ቫይረሱ አርኤንኤ (RNA) በመባልም እንደሚታወቅ፣ የሚተላለፈውም በእስትንፋስ ወይም ቫይረሱ ሙኮሳል (Mucosal) በሚባል የመተንፈሻ አካል ውስጥ ገብቶ ከተራባ በኋላ አልቬኦሊ (Alveoli) የሚባሉትን ቀጫጭን የመተንፈሻ መስመሮችን በማጥቃት የላይኛውንና የታችኛውን የሳንባ ክፍል በማጥቃት ስፖንጅ የነበረውን እንደሚያደርቀው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የላይኛው የሳንባ ክፍል በቫይረሱ ከተጠቃ መተንፈስ ስለማይቻል ታማሚው ወደ ሐኪም ቤት በመሄድ የኦክስጅን እገዛ ያገኛል፡፡ የታችኛው የሳንባ ክፍል ከተጠቃ ግን ሳንባ ሙሉ በሙሉ ስለማይሠራ ታማሚው በጽኑ ሕሙማን ክፍል (ICU) ውስጥ ሆኖ በመካኒካል ቬንቲሌተር እንዲተነፍስ እገዛ ይደረግለታል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባለፉት አራት ወራትና አሁንም ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ ወረርሽኙ እያደረሰ ስላለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ተያያዥ ጉዳይ በሚመለከት ሪፖርተር መጽሔት፣ በሙያቸው ጠቅላላ ሐኪም የሆኑትንና ፒፕል ቱ ፒፕል ዩኤስኤ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ክፍል ከፍተኛ አማካሪና በኮንቨርሴሽን ስሩ ኔትዎርክ (Conversation Through NetWork) የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑትን ዶ/ር ቅድስት ተሾመን የአደባባይ እንግዳ አድርገናቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኮረና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ በዓለም ደረጃ ከተከሰተ አራት ወራትን አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ አራት ወራት ውስጥ ከ290,000 በላይ ሰዎችን ገድሏል፡፡ ከ4.1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችም በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ ወረርሽኙ በዓለም ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ቀውሶችን አምጥቷል፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በጤና ባለሙያዎች ዕይታ ምን ማለት ይቻላል?
ዶ/ር ቅድስት፡- እንደ ጤና ባለሙያ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እየተናገርን ያለነው ነገር አለ፡፡ ትልቁና ዋናው ነገር ከጤና ጋር ያለው ቀውስ ነው፡፡ የወረርሽኙ ባህሪ በድንገት ተከስቶ የብዙ ሰዎችን ሕይወት የሚያጠፋ ነው፡፡ ብዙዎችንም የወረርሽኙ ተጠቂዎች ያደርጋል፡፡ በጠቀስካቸው ወራት ውስጥ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው ጠፍቷል፡፡ ቫይረሱ ጤነኛም ሆነ ሕሙማንን አይመርጥም፡፡ ጤነኛውን በቀናት ውስጥ ለሞት ሲዳርግ፣ የተለያዩ ሕመሞች ያሉባቸውን ወዲያውኑ ወደከፋ ሁኔታ ውስጥ ከመክተት አንስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት ይዳርጋል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ቀውስ ያመጣል፡፡ በመላው ዓለም የሚታየውን የመግደልና በፍትነት የመሠራጨት ሁኔታ ለመግታት ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ፣ እንዳይቀራረቡ፣ ሥራቸውን እንዲያቆሙ ያደረገና ሌሎችንም እንቅስቃሴዎች የገታ በመሆኑ ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው፡፡ ይኸ ወረርሽኝ እንኳን ቢያልፍ “Post traumatic disorder” [ድኅረ ጉዳት ጭንቀት] ያመጣል፡፡ ማለትም ለምሳሌ በጦርነት ላይ የተሰማሩ ሰዎች ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ከ”Post traumatic depression” [ድኅረ ጉዳት ድብርት] ውስጥ ቶሎ አይወጡም፡፡ ድንገት ያጋጠመን ፈተና አልፎ ወደ ነበረው ሕይወት ለመመለስ ከባድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ለሰው ልጆች ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ ሌላው ደግሞ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ቀውስ ነው፡፡ ኮሮና ቫይረስ በተለይ በዓለም ላይ ያሉ ትላልቅ የኢኮኖሚ ሴክተሮችና ሌሎችም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያም የጉዳቱ ሰለባ ከሆኑ አገሮች አንዷ ናት፡፡ የሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነትም እንዲገታ አድርጓል፡፡ ይኸም የራሱ የሆነ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ እንደጤና ባለሙያ ከላይ የጠቀስኳቸው ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ ትንንሽ መስለው ነገር ግን በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት (ተፅዕኖ) እያደረሱ ያሉ በርካታ ጉዳቶችም እንዳሉት እየተገነዘብን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያዩ አገሮች በተለይም በአፍሪካ ሀገሮች አደገኛ የተባሉ ወረርሽኞች፤ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ ቢሆንም፤ በጤና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች በሚደረግ የተፋጠነ የምርምር ሥራ ክትባት እየተገኘላቸው የከፋ ችግር ሳያደርሱ ለማስቆም ተችሏል፡፡ ኮሮና ቫይረስ ግን በጣም በፍጥነት ዓለምን ከማዳረሱም በተጨማሪ ገዳይም ነው፡፡ ቫይረሱ ከሌሎች አደገኛ ከሚባሉ ቫይረሶች ልዩ የሚያደረገው ምንድነው?
ዶ/ር ቅድስት፡- ጥያቄው ጥሩ ነው፡፡ በእርግጥ ይኼንን ጥያቄ ‹‹በዚህ ምክንያት ነው›› ብሎ ሊመልስ የሚችል ሐኪም ወይ የጥናት ባለሙያ የለም፡፡ ምክንያቱም ገና ብዙ ምርምሮችና ጥቶች እየተሠሩ ነው፡፡ ግን እስካሁን ባለው ሁኔታ የተለያዩ ሐሳቦችና ትንታኔዎች ተሰጥተዋል፡፡ በሽታው የተዛመተባቸው የአፍሪካና አውሮፓ አገሮችን ብንወስድ፣ ጥቃቱ ተመሳሳይ አይደለም፡፡ በመላው አፍሪካ በቫይረሱ የሞቱና የተያዙ ሰዎች ቁጥር በአውሮፓ፣ አሜሪካና እስያ ካሉ ከአንዱ አገር ያነሰ ነው፡፡ ለዚህ የተቀመጡ ትንታኔዎች አሉ፡፡ ግን ይኼ ትንታኔ ትክክለኛ ትንታኔና ግምት ነው የሚለው ድምዳሜ ላይ መድረስ የለብንም፡፡ ምክንያቱም እየተሰጡ ያሉ ግምቶችና መላምቶች ጥልቅ ጥናት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአፍሪካ አገሮች ላይ ለምን የሟቾችም ሆነ የተጠቂዎች ቁጥር ሊያንስ እንደቻለ የሚሰጠው ምላሽ፣ በአህጉሩ በተደጋጋሚ የተለያዩ ወረርሽኞች ከመከሰታቸው ጋር በተገናኘ ነው፡፡ በተደጋጋሚ አህጉሩ በወረርሽኝ መጠቃቱ ሕዝቡ ልምድ እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ አዲስ ወረርሽኝ ሲነሳ የመጀመርያ ዕርምጃቸው መከላከል (Prevention) ነው፡፡ አፍሪካውያን አዲስ ወረርሽኝ ሲከሰት የሚያርጉት ጥረት በሽታውን ማጥፋት ሳይሆን መጀመርያ እንዳይስፋፋ የመከላከል ሥራ ይሠራሉ፡፡ ከነዛ ልምዶች በመነሳት ኮሮና ቫይረስ ላይም ተመሳሳይ ድርጊት በማድረጋቸው በቀላሉ እንዳይዛመትና ሰዎችን እንዳይጎዳ አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ በተደጋጋሚ የተለያዩ ወረርሽኞች ላይ ባደረጉት የመከላከል ጥረት ያገኙት ምላሽ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ልምድ ሆኗቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ላይ በተደጋጋሚ ተላላፊ በሽታዎች (infectious diseases) ተከስተው ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ ኤችአይቪ ኤድስ፣ ቲቢ፣ ኮሌራ፣ “ጥቁር ሞት”፣ ስፓኒሽ ፍሉ ወዘተ ወረርሽኞች በአፍሪካም ላይ ተከስተው ያውቃሉ፡፡ እነዚህ ተላላፊ ወረርሽኞች የሰውን ልጅ አጥቅተው ሲድኑ፣ ተጠቂው በውስጡ የመቋቋም ችሎታ (Immunity) ያዳብራል፡፡ ይኼ ደግሞ እንደ ኮሮና ቫይረስ ዓይነት አዲስ ተላላፊ ወረርሽኞች በሚከሰቱ ጊዜ የመቋቋም ችሎታ እንዲኖረው ያርጋል፡፡ ሌላው ደግሞ ለአንዳንዶቹ ወረርሽኞች ክትባት ተገኝተዋል፡፡ ያ ክትባት ለተጠቂው ሰው ብቻ ሳይሆን ለጤነኛውም ሰው በክትባት መልክ ስለሚሰጥ፣ ወረርሽኙ ከአንዱ ወደ አንዱ እንዳይተላለፍ ያደርጋል፡፡ ሌላው ደግሞ ብዙ ሰዎች ከተጠቁ በኋላ ሲድኑ፣ ለወረርሽኙ መከላከያ የሚሆን በሰውነታቸው ውስጥ በሽታውን መከላከል የሚያስችላቸው ፀረ ባክቴሪያ (Anti-body) በሰውነታቸው ውስጥ ይፈጠራል፡፡ ይኸ ፀረ ባክቴሪያ ሌላ ወረርሽኝ ሲመጣ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ይከላከላል፡፡ ይኽ በመሆኑም በአፍሪካ አገሮች በተደጋጋሚ ተከስተው የነበሩ ወረርሽኖች ሕዝቡ ፀረ ባክተሪያ እንዲኖረው በማድረጋቸው አሁን ለተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገመታል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች በምርምር እስካልተረጋገጡ ድረስ ሙሉ በሙሉ ምላሽ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌላው በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ቢሲጂ ክትባት (BCG Vaccine) የሚባሉ ክትባቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ክትባቶች የሚሰጡት ከሳንባ ጋር ተያዞ ለሚመጡ ሕመሞች የሚሰጡ ናቸው፡፡ እነዚህን ክትባት በተለይ የአፍሪካ አገሮች በብዛት ወስደዋል፡፡ ሌሎች የአውሮፓ፣ አሜሪካና ሰሜን አሜሪካ አገሮች ግን ይኼንን ክትባት አልወሰዱም፡፡ በእርግጥ ይኼ ክትባት የሚያስወግደው ማይክሮ ባክትሬየም (Micro Bacterium) የሚባለውን ባክቴሪያ የሚያስወግድ ነው፡፡ ነገር ግን በአንድም ይሁን በሌላ በቀላሉ ሊፈጠር የሚችልን ባክቴሪያ ይከላከላል፡፡ ምክንያቱም ፀረ ባክቴሪያ መከላከያ ብቃት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ሊባል በሚቻል ደረጃ ይኼንን የቢሲጂ ክትባት ይወስዳሉ፡፡ ይኼም አዳዲስ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በመመከት ረገድ የራሱ የሆነ ሚና አለው የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ ሌላው ከአየር ንብረት ሁኔታ ጋር ተያይዞም ሲታይ፣ የአፍሪካ አገሮች የሙቀት መጠናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ተላላፊ በሽታዎች የሚቀሰቀሱት ቅዝቃዜን ተከትለው በክረምት ወቅት ነው፡፡ ይኼ በራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በኢትዮጵያም ብናይ፣ ወረርሽኙ መከሰቱ በተነገረበት ወቅት (መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከፍተኛ ሙቀት የነበረበት በመሆኑ በራሱ ያደረገው አስተዋጽኦ አለ የሚል ሐሳብ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሮና ቫረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ሙቀት መቋቋም ስለማይችል ከሰሃራ በርሃ በታች ባሉ አገሮች የመዛመት አቅም የለውም የሚባለው እውነት ነው ማለት ነው?
ዶ/ር ቅድስት፡- እንደ ጤና ባለሙያ በኅብረተሰቡ ላይ እንደዚህ ያለ አንድምታ እንዲፈጥር አንፈልግም፡፡ ትክክልም አይደለም፡፡ ምናልባትም ማብራሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ወረርሽኞች ሲቀሰቀሱ በቀላሉ በአንድ ጊዜ እንዲሠራጭ የሚያደርገው ቅዝቃዜ ነው፡፡ ያ ማለት ግን ሞቃት በሆኑ አገሮች የኮሮና ቫይረስ ይሞታል ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በጅቡቲና ሌሎች በጣም ሞቃት አገሮች ወረርሽኙ ተከስቷል፡፡ ከዚህ አንፃር በሌሎች ዓለማት አገሮች ወረርሽኙ ካደረሰው ጉዳት አንፃር በማወዳደር መላምቶችን ለመስጠት እንጂ፤ ሙሉ በሙሉ በሞቃታማ አገሮች ላይ አይከሰትም ወይም ሙቀት መቋቋም አይችልም ለማለት አይደለም፡፡ በአፍሪካ አገሮች ወረርሽኙ ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ ሥርጭቱ ከፍተኛ አለመሆኑ፣ የሕዝቡ አኗኗር የተራራቀና ገጠራማ (Rural) መሆኑ እንደሆነም ይነገራል፡፡ ብዙ ሰዎች ከከተማ ይልቅ በገጠር ይኖራሉ፡፡ ተጨናንቀው ሳይሆን ተበታትነው ይኖራሉ፡፡ ይኼም የራሱ አስተዋጽኦ አለው የሚል ግምት አለ፡፡ ለወረርሽኝ የማይመቸው ይኸው የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ያ ደግሞ በአፍሪካ ብቻ በመሆኑ ለአፍሪካውያኑ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ይገመታል፡፡
ሪፖርተር፡- ኮሮና ቫይረስ በአፍሪካውያን ላይ እንደ ሌሎቹ የዓለም አገሮች ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ ያልቻለው ካመጋገባቸው ጋር በተያያዘ መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡ በአብዛኛው ኦርጋኒክ ምግቦችን ስለሚያዘውትሩ በሽታዎችን የመከላከል አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ በቀላሉ ሊጠቁ እንደማይችሉም ይባላል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ቅድስት፡- ተላላፊ በሽታዎች በብዛት የሚስተዋሉት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ነው፡፡ ለእነዚህ ተላላፊ በሽታዎች በሚደረግ ሕክምና በሰውነት ውስጥ የሚፈጠር ፀረ ባክቴሪያ አለ፡፡ ያ ደግሞ በተላላፊው በሽታ በድጋሚ እንዳያዝ ይረዳዋል፡፡ ያ ማለት ግን ንጽህናን አለመጠበቅ ይጠቅማል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ንጽህና አለመጠበቅ በራሱ ከፍተኛ ችግር አለው፡፡ ንጽህና መጠበቅ የሚከሰቱ ሕመሞችን ለመከላከል የሚችል አቅም መፍጠር ነው፡፡ በሽታን የመከላከያ መንገድም ነው፡፡ ኮሮና ቫይረስ በመምጣቱና ሕዝቡ ንጽህናውን በመጠበቁ፤ በንጽህና ጉድለት የሚመጡ ሕመሞች ቀንሰዋል፡፡ እፍንፍን ብለው በሚኖሩ፣ ራሳቸውንና አካባቢያቸውን በጽዳት በማይጠብቁ ላይ ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ ስለሚዛመቱ፣ ፀረ ባክቴሪያ አለ ተብሎ ንጽህና አለመጠበቅ ከበሽታ አያድንም፡፡ የአካባቢን፣ የግልና የመጠቀሚያ ቁሳቁሶችን ንጽህና መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ለኮሮና ቫይረስ ትልቁ መከላከያ መንገድ እጅን ደጋግሞ መታጠብ ነው፡፡ እጅ በሰውነታችን ክፍሎች ላይ የሚያርፍ በተለይም በዓይን፣ አፍንጫና አፋችን ላይ የሚመላለስ በመሆኑ ደጋግሞ በመታጠብ ወረርሽኙን መከላከል ይቻላል፡፡ ሌሎችም ቫይረሶችና ቫይረስ አምራች ነገሮችን ለመከላከል እጅን መታጠብና አጠቃላይ ንጽህናን መጠበቅ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) በኢትጵያውያን ላይ ቢገኝም፣ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከሌሎች አገሮች በመጡ መንገደኞች ላይ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር እየነገረን ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየው ወረርሽኙ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ መሆኑን ነው የሚሉ አሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሕዝቡ ለፈጣሪው በሚያቀርበው ፀሎትና በሚመገቡት ኦርጋኒክ ምግብ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ቅድስት፡- ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ የኮቪድ-19 ተጠቂዎች ብዙዎቹ ከሌሎች አገሮች በሚመጡ ላይ ነው የተገኘው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከእነዚህ ተጠቂዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ናቸው፡፡ እውነትም ነው፡፡ ብዙ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች በአየር መንገድ የገቡ ናቸው፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና ከውጭ ከመጡ ሰዎችም ጋር ግንኙነት የሌላቸውም ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተው ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በተያያዘ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ምክንያቱን በመፈለግ ላይ በመሆኑና ምላሽም ያልሰጠ በመሆኑ መናገር አይቻልም፡፡ ወደ ማኅበረሰቡም ሰርጾ ገብቷል ወይም አልገባም ለማለትም የሚቻልበት ሁኔታ ገና አልታወቀም፡፡ ብዙ ቁጥጥር፣ ምርምርና ክትትል ተደርጎ ምን ያህል በአገሪቱ ላይ እንደተዳረሰ ካልታወቀ በስተቀር፤ በግምት መናገር አይቻልም፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ገብቷል ወይም አልገባም ለማለት የተሻለ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ እስካሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ግኝት መልካም ነገር አለው፡፡ አብዛኛው የቫይረሱ ተጠቂ ከውጭ አገሮች የመጡ መሆናቸው፣ ምንም እንኳን የመመርመርያ መሣሪያ በብዛት አለመኖርና ከሕዝቡ ብዛት አንፃር የተመረመረው ሕዝብ እጅግ በጣም ትንሽ ቢሆንም፤ እስካሁን በተደረገ ምርመራ እየተገኘ ያለው ውጤት ከሌሎች ከአውሮጳ፤አሜሪካ፤መካከለኛው ምስራቅ፤ኤዢያና ከአፍሪካ አገሮችም ጭምር የተሻለ ምላሽ አለው፡፡ ነገር ግን ምንም የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተው መገኘታቸው ‹‹ምናልባትም ወረርሽኙ በኮሚኒቲው ውስጥ ሰርጾ ገብቶ ሊሆን ይችላል›› የሚል ዕይታ እንዲኖር ያደርጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከእምነት (ሃይማኖት) እና ምግብ ጋር በተያያዘ የሚነገረውስ?
ዶ/ር ቅድስት፡- ኢትዮጵያ እኔንም ጨምሮ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የአማኞች (የሃይማኖተኞች) አገር ነች፡፡ እርግጥ ነው ፈጣሪ መልካም ነገርን እንደሚያደርግ እኔም አምናለሁ፡፡ በፈጣሪው ፊት ጥያቄውን የሚያቀርብ ጥሩ ምላሽ ያገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ አባቶችና ብዙ እናቶች የሚፀልዩባት የእምነት አገር ነች፡፡ ራስን ዝቅ አድርጎ ለሚደረግ ማንኛውም ነገር ፈጣሪ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ምናልባትም እግዚአብሔር በዚህ ጊዜ የምናሻሽለውና የምንወስደው ትምህርት ስላለ እንድንታረም የፈለገው ነገር ያለ ይመስላል፡፡ ነገር ግን በፈጣሪ ምላሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሮና ቫይረስ ጠፍቷል ወይም የለም የሚል ምላሽ ግን ልሰጥ አልችልም፡፡
ሪፖርተር፡- ነዋሪዎች ይኼንን ጥያቄ የሚያነሱት ወረርሽኙ በገባባቸው አገሮች የመዛመቱ ፍጥነት፤ እየገደለ ያለው የሰው ብዛትና በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ብዛት በጣም አስፈሪ ከመሆኑ ጋር በማነፃፀር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቫይረሱ መገኘቱ ከተረጋገጠ ሁለት ወራት ስላለፈውና የተጠቂዎችና የአገገሙ ሰዎች ቁጥር ተመጣጣኝ ከመሆኑ አንፃር፣ ወረርሽኙ ቢኖር ኖሮ የሟቾች ቁጥርና የተተቂዎች ቁጥር ሊበዛ ይችል ነበር ከሚል መነሻ ይመስላል?
ዶ/ር ቅድስት፡- ትክክል ነው፡፡ አንዱ በጎ ምላሽ (Positive response) የሚያስብለው ምክንያት፣ ይኼ ወረርሽኝ ከሌሎቹ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች የተለየ መሆኑ ነው፡፡ ይኼ ስያሜ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ የተሰጠ ነው፡፡ ቫይረሱ ብዙ ዝርያዎችም አሉት፡፡ ለምሳሌ አልፋ፣ ቤታ፣ ዴልታና ጋማ የሚባል መጠሪያ አላቸው፡፡ በፊት አራት ነበሩ፡፡ አሁን ወደ ሰባት እየደረሱ ነው፡፡ በመተንፈሻ አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያመጣው ቤታ ቫይረስ የሚባለው የኮሮና ቫይረስ ክፍል ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስም የሚመደበው በዚህ ውስጥ ነው ፡፡ ኖቭል ኮሮና ቫይረስ አዲስ የተፈጠረ ቫይረስ ቢሆንም፤ የቤታ ኮሮና ቫይረስ ዝርያ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ተመሳሳይነት አለው፡፡ ከዚህ በፊት መርስ የሚባል የኮሮና ቫይረስ በ2013 በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ተከስቶ ነበር፡፡ በ2003 ላይም ሳርስ የሚባል ኮሮና ቫይረስ ተከስቶ ነበር፡፡ ኮቪድ-19 ቫይረስን የሚያመጣው ቫይረስም “ሳርስ ኮቭቱ” ይባላል፡፡ ኮሮና ቫረስ-19 ለየት የሚያደረገው በጣም ዩኒክ የሆነ የመተላለፊያ ኃይል (ብቃት) ስላለው ነው፡፡ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ የመሠራጨት ባህሪ አለው፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰርጾ ገብቶ ቢሆን ኖሮ፤ ሰዎች በሆስፒታሎች ከመታደማቸውም ሌላ በርካቶች ሊሞቱ ይችሉ ነበር፡፡ ምክንያቱ አኗኗራችን በጣም የተጠጋጋና በአንድ ቤት እንኳን የሚኖረው የቤተሰብ ብዛት አንፃር ያለው ሁኔታ ግራ ሊያጋባ ይችላል፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ ምክንያቱን ለማወቅ ጥናት ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ወረርሽኙን በሚመለከት ቅድመ ትንበያ ሠርተናል ያሉ አካላት ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ28 ሚሊዮን እስከ 32 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቂ ይሆናሉ በማለት ሕዝቡን ሥጋት ውስጥ የከተቱበት ሁኔታም አለ፡፡ እንደ ጤና ባለሙያ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?
ዶ/ር ቅድስት፡- ወረርሽኝ በሚኖርበት ጊዜ ሞዴሊንግ የሚባል ነገር አለ፡፡ ማለትም በአንድ አገር ወረርሽኝ በገባ ጊዜ የተለያዩ ግብአቶችን (Personal protective equipment) ለጤና ባለሙያዎች የሚያስፈልጋቸውን፣ በኢኮኖሚም ደረጃ መዘጋጀት፤ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ማዘጋጀትና የጤና ባለሙያዎችም ነቅተው እንዲዘጋጁ ይደረጋል፡፡ ‹‹በዚህ ጊዜ ውስጥ ይኼንን ያህል ታማሚ እንጠብቃለን›› ተብሎ ጥናት ወይም ምርምር መደረጉ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በሁሉም አገር ሚደረግ ነው፡፡ በሐኪሞች፣ በመድኃኒት፣ በሕክምና መሳሪያዎች አቅርቦት፣ በኢኮኖሚ ዝግጅትና ከሌሎችም ዝግጅቶች አንፃር የሚጠቅም ነው፡፡ እንዳልከው በተቀመጠው ጊዜ ክልል ውስጥ ከ28 ሚሊዮን እስከ 30 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ እንደሚጠቁ ሞዴል ተደርጓል፡፡ ትንበያው ሙሉ በሙሉ ባይተገበርም፣ ከፍ ሊል ወይም ዝቅ ሊል ወይም ባስቀመጡት ልክ ላይሆን ይችላል፡፡ ሁሉጊዜ በተባለው ጊዜና መጠን ላይከሰት ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁንም ጥናትና ትንበያዎች እየተሠሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘቱ ይፋ ከተደረገበት ዕለት አንስቶ ሕዝቡ ብቻም ሳይሆን መንግሥትም ስላሳሰበው፣ እንዲሁም ሕዝቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚተላለፈውን ትምህርትና ምክር ተግባራዊ ሊያደርግ ባለመቻሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ ችሏል፡፡ ነገር ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስገዳጅ ድንጋጌዎች ቢኖሩትም፣ የሕዝቡን መቀራረብ ያስቀረው ወይም መከላከል የተቻለው ከእምነት ተቋማት እንጂ ከመገበያያ ቦታዎችና በመንገድ ላይ አየተገፋፉ ወይም መቀራረባቸውን ሊገታ አልቻለም፡፡ ሕዝቡም ወረርሽኙ የጠፋ እንጂ እየተባባሰ የሚሄድ አልመሰለውም፡፡ እዚሀ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
ዶ/ር ቅድስት፡- ትክክል ነው፡፡ በሕዝቡ ላይ የሚታየው ሁኔታ እንደመጀመርያው ጊዜ አይደለም፡፡ ነገር ግን አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ይኼ በሽታ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን ነው፡፡ ወረርሽኙ በኢትዮጵያ መኖሩ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ በመንግሥት ደረጃ የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም ያገባናል ያሉ ባለድርሻ አካላት፤ ኅብረተሰቡ መከተል ያለበትን የጥንቃቄ መስመሮች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና መንገዶች እየያስተላለፉ ነው፡፡ የባህሪ ለውጥ የሚጠበቀው ግን ከግለሰብ ነው፡፡ ይኸው ወረርሽኝ እንደ አገር የመጣብን ችግር ነው፡፡ አንዱ ሰው ራሱን ሲጠብቅ ሌላው ሰው ካልጠበቀ ዋጋ የለውም፡፡ምክንያቱም አንድ ሰው ለሁሉም ማዛመት ስለሚችል፡፡ ነገር ግን ይኼን ችግር በጋራ ተረዳድቶ ለማሸነፍ እያንዳንዱ ዜጋ የባህሪ ለውጥ ማምጣት አለበት፡፡ ለቤተሰብ፣ ለልጆች፣ ለአረጋውያንና ለአገር ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ኃላፊነትም ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ላይ ብዙ ሰዎችን እየጨረሰ እንዴት ኢትዮጵያ ውስጥ ቀላል ሊሆን እንደቻለ የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ጤና ሚኒስቴርም ሆነ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚሰጡት ምላሽ የአገሪቱ አቅም በቻለ መጠን ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ነው፡፡ የሚመረምሩትን የሰው ብዛትና ያገኙትን ውጤት በየቀኑ እያሳወቁ ነው፡፡ የምርመራው ግኝት ጥቂት መሆኑ ግን ሊያዘናጋ አይገባም፡፡ ካለን የሕዝብ ቁጥር አንፃር እየተመረመረ ያለው እጅግ በጣም ትንሽ ቢሆንም፣ ከመመርመር አቅም ጋር የተያያዘ በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻለም፡፡ አሁን ላይ ግን በክልሎችም ጭምር መመርመር በመጀመሩ በተሸለ ሁኔታ መመርመር እየተቻለ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሕዝቡ ቸልተኝነት እንዲያድርበት ያደረጉት በዋናነት ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የመጀመርያው ጤና ሚኒስቴር በየቀኑ የሚገልጸው ተጎጂዎች ወይም ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ከውጭ የገቡና በለይቶ ማቆያ የነበሩ መሆናቸውን መግለጹ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚ አለማድረጉ እንደሆነ የሚናገሩም አሉ፡፡ በተለይ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች ቁጥራቸውን ብቻ በመግለጽ የት እንደነበሩና ከየት እንደመጡ ባይገለጽ ሕዝቡ አይዘናጋም ነበር ይላሉ?
ዶ/ር ቅድስት፡- በእርግጥ የተነሱት ጥያቄዎች ትክክል ወይም ትክክል ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አንድን ትክክል የሆነ ሥራ ትክክል አይደለም ብሎ መናገር ተቀባይነት የለውም፡፡ ጤና ሚኒስቴር ስላደረገው ምርመራና ቫይረሱ ተገኘባቸው ያላቸው ሰዎች ከየት እንደመጡ መነገሩ ሊያዘናጋ አይገባም፡፡ ይኼ ወረርሽን ዛሬ ላይ በመከሰቱ አዲስ የሚሆነው ለዚህ ትውልድ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ሕዝብ የገደሉ እንደ ስፓኒሽ ፍሉ (የኅዳር በሽታ) ዓይነት ወረርሽኞች ከመቶ ዓመታት በፊት ተከስተው ያውቃሉ፡፡ ወረርሽኝ በሚቀጥሉትም ጊዜያት መከሰቱ ላይ መተማመን እስከተቻለ ድረስ፤ እንዴት መከላከል እንደሚቻል ባለሙያና መንግሥት የሚያስተላልፉትን መረጃ ተግባራዊ በማድረግ መጠንቀቅና የባህሪ ለውጥ ማምጣት ግዴታ ነው፡፡ ራስን እንዴት መጠበቅ እንደሚገባ በማሰብና ‹‹አታድርጉ›› ተባለውን በመተው ላይ ትኩረት ማድረግ እንጂ፣ የቫይረሱ ተጠቂዎች ኬት እንደመጡና ስንት እንደሆኑ ማወቅ ብቻ ሊያዘናጋ አይገባም፡፡ የሚነገሩትን የመከላከያ መንገዶች በአግባቡ ተግባራዊ ማድረጉ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡ ለአሁን ብቻ ሳይሆን ወደፊት ሌላ ወረርሽኝ ቢነሳ እንኳን ይጠቅማል፡፡ እኛ አገር ላይ ብዙ ሰው ጠዋት ከመኝታው ሲነሳ ወይም የከበደ ነገር ካልገጠመው በስተቀር እጁን የሚታጠበው ምግብ ከበላ በኋላ ነው፡፡ ሰላምታን ብንመለከት ቀደም ባሉት ዘመናት መጨባበጥ አልነበረም፡፡ አንገትን ዘለስ በማድረግና ከወገብ ሸብረክ ብሎ እጅ በመንሳት ነበር፡፡ ያ ቀርቶ በመጨባበጥ፣ በመሳሳምና በመተቃቀፍ የተቆየ ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ ወረርሽኙ ስለማይፈቅድ እንዲቆም ተባለ፡፡ ይኼንን መተግበር ከባድ አይደለም፡፡ በቀን በርካታ ጊዜ እጃችንን እየታጠብን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ጤና ጣቢያ በብዛት የሚያስኬዱን የተላላፊ በሽታዎች ተጠቂ የነበርን ሰዎች፣ እጅን በመታጠብ ከቆመ ይኼ ትልቅ የባህሪ ለውጥ ነው፡፡ ይኼነው ይኼነው እያልን ምክንያት በመስጠትና በማመካኘት ግዴለሽ መሆን ውጤቱ ጥሩ ስለማይሆን፤የሚተላለፉ ምክሮችንና መመርያዎችን ተግባራዊ ማድረጉ ተመራጭ ነው፡፡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ከየት አካባቢ እንደመጡ መግለጹ ኅብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ ይጠቅማል፡፡ አካባቢውን በቀላሉ ለማግኘት፣ በአካባቢው ቫይረሱ በብዛት ስለመሠራጨቱና አለመሠራጨቱ ለማወቅም ይረዳል፡፡ ራስን መጠበቅ ቤተሰብን፣ ጎረቤትን፣ አካባቢንና አገርንም መጠበቅ በመሆኑ በባህሪያችን ላይ ትኩረት አድርገን ለውጥ ብናመጣ የተሻለ ነው፡፡ እኔ በግሌ ኮሮና ቫይረስን እንደ ማንቂያ ደወልና የተስፋ ዕድል እንደሆነ አድርጌ አየዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ወደኋላ የቀረንባቸው ነገሮች እንድናይ ያደርገናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ችግር ፊት ለፊት ሲመጣ፣ ችግሩ በመምጣቱ ምክንያት ትናንትናና ከትናንት ወዲያ ልታድግበት የነበረውን ነገር ታየዋለህ፡፡ አማራጭ በማጣትህ ታድግበታለህ፡፡ ከእነዚህ ነገሮች አኳያ መጥፎ ጎኑን ብቻ ሳይሆን፣ ጨለማ ከሆነው ነገር ብርሃን ማግኘት እንደሚቻል አስተምሮ ያልፋል፡፡ ብዙ ቴክኖሎጂዎችን እንድንለምድና እንድንጠቀም፣ የመንግሥት ኃላፊዎች የሚሻሻሉበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ማድረጉ፣ በራሱ አገራችን እንድትነቃም ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በፖለቲካ አተያይና በዘር ተከፋፍሎ የነበረን ኅብረተሰብም አንድ አድርጓል፡፡ ወጣቱ፣ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የእምነት አባቶች አብረው እንዲሆኑና ለፈጣሪያቸው በአንድ ቋንቋ እንዲጸልዩ፣ እንዲያለቅሱ አድርጓቸዋል፡፡ ይኼ እንደኔ ዕይታ ቂም በቀል ትቶ ለአንድነት በአንድነት ተሠልፎ መገኘት በፈጣሪ ፊት ቀላል አይደለም፡፡ በጎ ፈቃደኞች በሌሎች አገሮች ትልቅ ተፅዕኖ የፈጠሩበት የትብብር ሥራ ነው፡፡ ይኼ ተግባር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በኢትዮጵያም እየተተገበረ በመሆኑ በጎ ተፅዕኖ ነው፡፡ ትናንትናና ከትናንት በስቲያ ማደግ ያልቻልንባቸውን ነገሮች፣ ዛሬ በተፈጠረብን ችግር ምክንያት ልናያቸው ይገባል፡፡ ከዚህ ወረርሽኝ በኋላም ጥሩ ጥሩውን ወስደን ማስቀጠል መቻል አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥትም ሆነ የጤና ባለሙያዎች አንዱ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ዘዴ በቤት ውስጥ ተቀምጦ መቆየት መሆኑን ደጋግመው እየተናገሩ ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮውን የሚገፋው በዕለት ሠርቶ በሚያገኘው መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቤት ውስጥ እንዲቆዩ የሚደረገው እስከ መቼ ነው? መፍትሔውስ ምን ይመስልዎታል?
ዶ/ር ቅድስት፡- የኮሮና ቫይረስን ለየት የሚያደርገው ነገር የመዛመቱ ዋና ምክንያት መቀራረብ ነው፡፡ የኛ ማኅበረሰባዊ ግንኙነታችን በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ ግለኝነት (Indvidualism) የሚባለውና በአውሮፓውያን የተለመደው ነገር በኛ አገር የለም፡፡ ይኼ ደግሞ ለኮሮና ቫይረስ መሠራጨት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ቫይረሱ ሲጠና በሁለት ሰዎች መካከል መኖር ያለበት ርቀት ሁለት ሜትር ወይም ስድስት ጫማ ወይም ሁለት የአዋቂ ዕርምጃ መሆን እናዳለበት ታውቋል፡፡ ቫይረሱ ከሁለት ሜትር በላይ እርቆ አይሄድም፡፡ አየር ላይ መቆየት አይችልም፡፡ አንድ ሰው ቢያስነጥስ ቫይረሱ ከተጠቀሰው ርቀት በላይ መሄድ ስለማይችል በዛ ርቀት ላይ ይወድቃል፡፡ ፈቀቅታ (Phisical Distance) እንዴት መተግበር እንዳለበት እየተሠራ ነው ያለው፡፡ ሰዎች በመገበያያ ቦታዎች፣ ትራንስፖርት መጠቀሚያ ቦታዎችና በማንኛውም ቦታ ያላቸው ቅርርብ ከሁለት ሜትር በታች መሆን የለበትም፡፡ ይኼንን ለጊዜውም ቢሆን ለመተግበር መንግሥት ሰው በቤቱ እንዲቆይ ተናግሯል፡፡ ይኼንን ማድረጉ በርካታ ሰዎች በጎዳና ላይ ሚያደርጉትን ጭንቅንቅ ያስቀራል፡፡ ነገር ግን እንደተባለው ብዙ ሰው ውሎ አደር በመሆኑ፤ “እንዴትና እስከመቼ ነው በቤት ውስጥ የሚቀመጠው?” የሚለው ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡ ይኼ ነገር በተለይ ላላደገ አገር ከባድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ግዴታ ካልሆነ በስተቀር ሕዝቡ ከቤት ውስጥ እንዳይወጣ›› በማለት እየተነገረ ያለው፡፡ ግዴታ የሆነባቸው ሰዎች ሲወጡ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ የፊት ማስክ፣ ሳኒታይዘር፣ ጓንትና ሌሎች መጠንቀቂያ ነገሮች በማድረግ በመውጣት ፈቀቅታቸውን ጠብቀው ሠርተው መግባት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል የተሸለ ነገር ያላቸው ለሌላቸውና በቤት ውስጥ ለተቀመጡ ወገኖች በመርዳት፤ በመንግሥት አስተባባሪነት የሚገኝን ዕርዳታ ደግሞ በአግባቡ በማድረስና ለችግረኞች በማካፈል ይኼንን አስቸጋሪ ጊዜ ማለፍ ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁኔታዎች በማገናዘብ በጤና ባለሙያዎችና በመንግሥት የተላለፉ ምክረ ሐሳቦችና መመርያዎችን አክብሮ በጥንቃቄ መቆየት ተገቢ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ከተማ “ትንሿ ኢትዮጵያ” የሚባል ስያሜ ተሰጥቷታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ዜጎች ሁሉ የሚያርፉባት ከተማ መሆኗ ነው፡፡ በመሆኑም በከተማው ውስጥ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች እንኳን ስለኮሮና ቫይረስ ቀርቶ ስለከተማዋም በቂ መረጃ የላቸውም፡፡ ትኩረታቸው የዕለት ጉርሳቸውን በሚያገኙበት ነገር ላይ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ለቫይረሱ ሥርጭት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ስለሚችል የኸንን ችግር ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ዶ/ር ቅድስት፡- ስለኮሮና ቫይረስ መኖርም ሆነ ስለሁኔታው ጭራሽ ግንዛቤው የሌለውን የማኅበረሰብ ክፍል በሚመለከት፣ ግንዛቤውን መፍጠር ያለበት የመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያ) መሆን አለበት፡፡ ሕዝቡ ምንም እንኳን ኑሮው ቢያባትለውም ዜና ይሰማል፡፡ ‹‹ምን አዲስ ዜና አለ?›› ብሎ እሱ ባይሰማም ሌላውን ይጠይቃል፡፡ በተሠሩ ጥናቶች ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ስለ ኮሮና ቫይረስ ግንዛቤው አለው፡፡ ስለዚህ ለታችኛውም ሆነ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በሚገባው ቋንቋ መረጃውን ማስተላለፉ ያስፈልጋል፡፡ “ኮቪድ 19 ምንድነው? ከየት ነው የመጣው? የሚያደርሰው ጉዳት ምን ህልና እስከምን ድረስ ነው? እንዴት ነው መከላከል የሚቻለው? መድኃኒት አለው ወይስ የለውም?›› የሚለውን ቀላል በሆነና በሚገባቸው ሁኔታ ማስተላለፍ አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመተባበር የሚያስፈልገውን ነገር በማቅረብና በመተባበር በስፋት እንዲሠራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንዱ ሌላውን በሚወቅስበት ሁኔታ ሳይሆን በመተጋገዝና በአገራዊው ስሜትና ወገንታዊነት መሥራት የግድ ነው፡፡ ወገንንና ሃገርን ማትረፍ የዜግነት ግዴታ መሆኑን ተረድተን መሥራት አለብን፡፡ ሳይንሱ እያደገ ቢመጣም፣ የምርምር ሒደቱ እየሰፋ ቢሆንም፣ የመተላለፊያ መንገዶቹ አልተለወጡም፡፡ ‹‹ታጠቡ፣ አትጨባበጡ፣ አካላዊ ፈቀቅታችሁን ጠብቁና ዓይን፣ አፍንጫና አፋችሁን በእጃችሁ አትንኩ፣ ስታስነጥሱ አፋችሁን በክንዳችሁ ሸፍኑ፣ በቤት ውስጥ ቆዩ›› በማለት የሕክምና ባለሙያዎች የሚያስተላልፉትን መተላለፊያ መንገዶች ደጋግሞ በመንገር የታችኛው የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚገባቸው ቋንቋና ቀለል ባለ ሁኔታ ደጋግሞ መናገር አስፈላጊ ነው፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች ለመምህራን፣ መምህራን ለተማሪዎች፣ ተማሪዎች ለቤተሰቦቻቸው፣ ቤተሰብ ለጎረቤት፣ ጎረቤት ለማኅበረሰቡ በመንገርና ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ሁሉም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ የድርሻውን ከሠራ ግንዛቤ በመፍጠር ይኼንን የወረርሽኝ ጊዜ ማለፍ ይቻላል፡፡ ግለሰቡ ለመለወጥ ዝግጁ እስከሆነ ድረስ ግንዛቤ መፍጠር ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ጤና ሚኒስቴር በኮሮና ቫይረስ ስለተያዙ ሰዎች በይፋ መናገር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ወዳገራቸው ከተመለሱት ሁለት ጃፓናውያንና ከሞቱት አምስት ኢትዮጵያውያን ጋር ተደምሮ 261 ደርሷል፡፡ ነገር ግን መንግሥት በብዙ ቦታዎች ለይቶ ማቆያ ቦታዎችን እያዘጋጀ ነው፡፡ ያገገሙና በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉት እኩል ለኩል ባሉበት ሁኔታ፣ ለለይቶ ማቆያ በሚል በርካታ አልጋዎችን ማዘጋጀቱ ለምን አስፈለገ? የተደበቀ ነገር አለ ወይስ ሌላ ሚስጥር አለው?
ዶ/ር ቅድስት፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በብዙ ሰዎች የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄውም ተገቢ ነው፡፡ ወረርሽኙ በምን መልኩ አጥቅቶና ጎድቶ እንደሚለቅ አይታወቅም፡፡ ወረርሽኝ ደግሞ ባህሪው ነው፡፡ በመሆኑም በወረርሽኝ ወቅት አንድ አገር በማንኛውም ሁኔታ ዝግጁ መሆንና መጠበቅ አለበት፡፡ ይጎዳል ወይም ጉዳት ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሞዴሊንግ ወይም ትንበያ አለ፡፡ የተከሰተውን ወይም ሊከሰት የሚችለውን ወረርሽኝ መሠረት አድርጎ ከዚህ እስከዚህ ድረስ ጉዳት ሊያደርስ ይችል ተብሎ ትንበያ ይቀመጣል፡፡ ጥናት ይደረጋል፡፡ በዚህ መሠረት ሆስፒታሎች፣ አልጋዎች፣ ዶክተሮችና መካኒካል ቬንቲሌተሮች፣ ኦክሲጅኖች፣ መድኃኒቶችና ሌሎች ተያያዥ ነገሮች እንዲዘጋጁ ይደረጋል፡፡ ይኼ በአንድ አገር ውስጥ ወረርሽኝ ሲገባ የሚደረግ ዝግጅት ነው፡፡ በኮሮና ቫይረስ የተጎዳው የሰው ብዛትና መንግሥት የሚያደርገው ዝግጅት ባይገናኝም፤ መዘንጋት ሌለብን ነነገር አለ፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊት ተከስቶ የነበረው ስፓኒሽ ፍሉ (የኅዳር በሽታ) ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ የታወቀው በመስከረም ወር ነበር፡፡ ለጊዜው ያደረሰው ጉዳት የከፋ ስላልነበረ ‹‹የለም የለም›› ተብሎ ሁሉም ሰው ዝም ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ በኅዳር ወርና በሁለተኛው ምዕራፍ (Phase II) ላይ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡ በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ በአየር ፀባይ ሁኔታና በተለያዩ ምክንያት በመጀመርያው ምዕራፍ (Phase I) የከፋ ጉዳት ባያደርስም፤ በሁለተኛው ምዕራፍ ግን ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት አይታወቅም፡፡ ኮሮና ቫይረስም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ የመጀመርያ ምዕራፍ (Phase I) ነው የሚሉ አሉ፡፡ ከሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ ያለው ጊዜ ምናልባት ሁለተኛው ምዕራፍ (Phase II) የሚባል ሲሆን፤በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚደርሰው ጉዳት ስለማይታወቅ ዝግጅት ማድረጉ አይከፋም፡፡ ችግሩ ሊደርስም ላይደርስም ስለሚችል መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ማዘጋጀት የሚገባውን ማንኛውንም ዓይነት ዝግጅት አሟልቶ መገኘት ግዴታው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተባቸው አገሮች፣ የወረርሽኙ መነሻ የሆነችው ቻይናና ደቡብ ኮሪያ ወረርሽኙን ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ ነገር ግን ከቫይረሱ ነፃ ተብለው የነበሩና ከሌላ ታማሚ ጋር ምንም ግንኙነት ሳይኖራቸው በድጋሚ በቫይረሱ መያዛቸው እየተነጋገረ ነው፡፡ ወረርሽኙ አይድንም? ያገረሻል ወይስ ሌላ የማይታወቅ ባህሪ አለው?
ዶ/ር ቅድስት፡- ጥያቄው ጥሩ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ እመልሰዋለሁ ማለት አልችልም፡፡ ወረርሽኞች ተላላፊ ሆነው በዓለም ላይ ሲመጡ፣ ብዙ ሰዎች ይጠ ቁና ይድናሉ፡፡ የዳኑት ሰዎች በሰውነታቸው ውስጥ ፀረ ተላላፊ (anti-body) መከላከያ ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን የኮሮና ቫይረስን አጥንቶ የጨረሰ የለም፡፡ ቫይረሱ አዲስ ከመሆኑ አንፃር በዓለም ላይ ያሉ ተመራማሪ ሳይንቲስቶች፣ ኤክስፐርቶችና ሌሎች የላብራቶሪ ባለሙያዎች አልደረሱበትም፡፡ ቫይረሱ ምናልባት (ሳርስ ኮቭዋን) ከሚባለው እ.ኤ.አ. በ2003 ተከስቶ ከነበረው ቫይረስ ጋር ትንሽ የመመሳሰል ባህሪ አለው የሚባል አንድምታ ከመኖሩ ውጭ ምንም የተገኘ ነገር የለም፡፡ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው ኖቨል የሚል ስያሜም የሰጡት፡፡ ቫይረሱ እያደገ በመሆኑ ትናንት የተነገረው ዛሬ፣ ዛሬ የተነገረው ነገ ይቀያየራል፡፡ ስለዚህ ሰዎችም ይኸንን ሲያዩ ለሳይንስ ክፍት መሆን አለባቸው፡፡ ጥናት ተጠንቶና ምንነቱ ተረጋግጦ ካልወጣ በስተቀር በእርግጠኝኘት መናገር አይቻልም፡፡ ማገርሸት አለማገርሸቱ ወይም ቫይረሱ በደም ውስጥ የመደበቅ ባህሪ ይኑረው አይኑረው ወይም ለሌላ ምክንያት መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ቫይረሱን ተሸካሚ የሆነ ሰው ሳል፣ ትኩሳት፣ አየር ማጠር፣ ማቅለሽለሽ፣ መድከም፣ ቁርጥማት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ መቅመስ አለመቻል፣ ማሽተት አለመቻል፣ ተቅማጥና ቁርጠት ዓይነት ምልክቶች አሉት፡፡ በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ምልክቶቹ ሳይታዩ ግን በቫይረሱ ተጠቅተው ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼ በጣም ያስፈራል፡፡ አንድ ሰው ምልክቱ ስላልታየበት በኮሮና ቫይረስ አልተጠቃም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ምርመራ ሳያደርግ አንድን ሰው ጤነኛ ወይም በቫይረሱ ተጠቂ መሆኑን መለየት አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው በተደጋጋሚ ርቀት ጠብቁ (Physical Distance) እየተባለ የሚነገረው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ብቸኛው መከላከያ መንገዶችን አታድርጉ የሚባለውን አለመጨባበጥ፣ እጅን ደጋግሞ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ ብቻ ናቸው፡፡ መጨነቅ ያለብን ስለመዳንና ማገገም ሳይሆን ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች መሆን አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ለኮሮና ቫይረስ መድኃኒት (ክትባት) ለማግኘት በኢትዮጵያ የሚገኙ ባህላዊ የሕክምና ባለሙያዎች በኢኖቪሽን ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከቻይና ባህላዊ ሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር እየተሠራ መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡ በምን ደረጃና ሁኔታ ላይ እንዳለ የሚታወቅ ነገር አለ?
ዶ/ር ቅድስት፡- ክትባት የራሱ የሆነ ፕሮቶኮል አለው፡፡ በአንድ ጊዜ ተዘጋጅቶ የሚሰጥ ነገር አይደለም፡፡ የራሱ ሒደት አለው፡፡ በጣም ፈጠነ ቢባል አንድ ዓመት ተኩል ይፈጃል፡፡ የራሱ መመርያ፣ ፕሮቶኮልና የሚያመጣው የጎንዮሽ ጉዳትና ሌሎችንም ሒደቶች አልፎ ስለሚወጣ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ለምሳሌ ክትባቱ መጀመርያ በእንስሳት ላይ ይሞከራል፡፡ ያንን ሙከራ ካለፈ ወደ ክሊኒካል ሙከራ ይተላለፋል፡፡ ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ ሲታወቅ በጥቅም ላይ ይውላል፡፡ የመርዛማነት አቅሙ (Level of Toxicity) ምን ያህል እንደሆነ ተሞክሮ እስከሚያልፍ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ከጀርመን፣ ከአውስትራሊያ፣ ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካ፣ ከእስራኤልና ከሌሎች አገሮች ላይ ክትባቱን ለማግኘት ከመጣጣር ባለፈ፣ የተጠቀሱትን ሒደቶች አልፈው ተግባራዊ ያደረጉ የሉም፡፡
ሪፖርተር፡- የሰው ልጅ የሚጠቃበት በሽታ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብቻ አይደለም፡፡ ጊዜ የማይሰጡ እንደ ካንሰር፣ ኩላሊት፣ ጉበት፣ ቲቢ፣ ደም ግፊት፤ ስኳርና ሌሎችም ሕመሞች የቅርብ ክትትል የሚያስፈልጋቸው የሕመም ዓይነቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ በአገር ውስጥ መከሰቱ ከተነገረ በኋላ፣ ትኩረት ሁሉ ወደሱ ሆኗል፡፡ እንደ ሕክምና ባለሙያነትዎ በዚህ ዙሪያ የሚሉት አለ?
ዶ/ር ቅድስት፡- እኔም እንደ ጤና ባለሙያነቴ ይኼንን በሚመለከት በሌላ መገናኛ ብዙኃን ላይ አንስቼው ነበር፡፡ አንተም ስላነሳኸው ደስ ብሎኛል፡፡ በጣም የሚያሳስበኝና ተገቢም ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት የእናቶችና ሕፃናት ጉዳይ ይረሳል፡፡ አጣዳፊ ሕመሞችም ችላ ይባላሉ፡፡ ይህ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ሥጋት የሆነው ኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ የእኛም ሥጋት ነው፡፡ ጤና ሚኒስቴር፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ሆኑ መንግሥት ሐሳባቸው ወረርሽኙን እንዴት ከአገር ማጥፋትና መከላከል ስለሚቻልበት ሁኔታ እንጂ ስለሌሎች ሕመሞች አያነሱም፡፡ በዚህ መካከል ግን የሚጎዱ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ መንግሥትም ሲረጋጋ ሐኪም ቤቶች ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰው ሕክምና መስጠት እንዳለባቸው የሰጠው ትዕዛዝ ባይሰጥ ኖሮ ሁኔታው አስፈሪ ነበር፡፡ በተለይ ወላዶች ምጥ ሲይዛቸው አምቡላንስ ያጡበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበርም መታወቅ አለበት፡፡ በመሆኑም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ከላይ ከጤና ሚኒስቴር እስከ ወረዳ ድረስ የተዘረጋ የጤና ኤክስቴንሽን ስላለ፣ በቋሚነት ሕክምና የሚከታተሉና ድንገተኛ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች በስልክ ጭምር እያገኙ ሕክምናውን እንዲያገኙ ማድረግና መርዳት አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ሕመም የሚሰማው ሰው በአብዛኛው ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት፣ የማንቀጥቀጥ፣ የመሳልና ሌሎች ስሜቶችንም ሊያሳይ ይችላል፡፡ ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ በኋላ ግን በዋናነት የሚነገረው ምልክት ትኩሳት ከመሆኑ አንፃር ብዙ ሰው ሌላ ሕመም ቢታመም እንኳን ‹‹ትኩሳት አለብህ ተብዬ ወደ ማግለያ እወሰዳለሁ›› በሚል ፍራቻ በቤቱ ውስጥ የሚቆይበትና በቀላሉ በሚድን በሽታ የሚሰቃይበት ሁኔታ እንዳለ ይሰማል፡፡ ታማሚውም ሆነ የሕክምና ባለሙያዎች በዚህ ላይ ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ?
ዶ/ር ቅድስት፡- ሕመም ያለባቸው ሰዎች ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ ሙቀታቸው ይለካል፡፡ ሙቀታቸው ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ ሲገኝ፣ የኮሮና ቫይረስ አንዱ ምልክት ሙቀት መጨመር በመሆኑ ወደተዘጋጀላቸው ክፍል መወሰዳቸው አይቀርም፡፡ ድርጊቱን መቃወም ሳይሆን እንደዛ የሚደረግበትን ዓላማ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ኳራንቲን የሚለውን ሲሰሙ ሰዎች የመበርገግ ስሜት ሲያሳዩ ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ጥሩ አይደለም፡፡ ትልቁ ችግር ግን ስለቫይረሱና አግልሎ ስለማቆየት የተነገረበት ሁኔታ የተዘበራረቀ መሆኑ ነው፡፡ “ኳራንቲን ምንድነው? ማግለል ማለት ምን ማለት ነው? ሰዎች የሚገለሉት ለምንድነው?፣ ከተገለሉ በኋላ ምንድነው የሚደረግላቸው?›› የሚሉትን በደንብ ማስረዳት ተገቢ ነበር፡፡ ያ አለመደረጉ የራሱን ችግር አምጥቷል፡፡ ስለአንድ ነገር ሲነገር በትይዩ ያለውን ጥቅምና ችግር ጎን ለጎን ማስረዳት ተገቢ ነው፡፡ ያ ባለመሆኑ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ቫይረሱ ባይኖርብህም ሙቀትህ ከፍ ያለበት ምክንያት ተመርምሮ እስከሚታወቅ ድረስ ተለይቶ መቀመጡ ለራስም ሆነ ለቤተሰብ ወይም ለማኅበረሰቡና ለአገርም ጥቅም እንዳለው ማወቁ ጥሩ ነው፡፡ ምንም ይሁን ምንም መፍራት አያስፈልግም፡፡ የኮቪድ-19 ቫይረስ ምልክቶቹም ሆኑ በሽታው ቀላል ነው፡፡ ሰዎች ሳይፈሩ የሚያስፈልገውን የሕክምናና ምክር በመተግበር አገግሞ መውጣት ይቻላል፡፡ መታወቅ ያለበት ግን ሙቀቱ ከፍ ያለበት ሰው ሁሉ ግን የኮቪድ-19 ታማሚ አለመሆኑን ነው፡፡ ምልክቱ ታይቶባቸው ሕመም የማይሰማቸውና 80 በመቶ የሚሆነው የሕመሙ ዓይነት ጉንፋን ዓይነት በመሆኑ፣ በቤታቸው ውስጥ ለብቻቸው በመሆንና አስፈላጊ ምግቦችን፣ ፈሳሾችንና ዕረፍት በማድረግ ድነው ይወጣሉ፡፡ ዋናው አስፈለጊ ነገር ቶሎ ብሎ ራስን ማወቅ ብቻ ነው፡፡ ይህ በውጭው ዓለም እየተደረገ ነው፡፡ በእኛ አገር ግን የአኗኗር ሥርዓታችን በአንድ ቤት ውስጥ ሰባት ስምንት ሰው ስለሚኖር ቤት ውስጥ ሆኖ ለማረፍ፣ ለመመገብና ተገቢ የሆኑ ፈሳሾችን ወስዶ ለመዳን አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሆኑም ሙቀታቸው ከፍ ብሎ የተገኙትን በለይቶ ማቆያ ሆነው ምልክቱን ሊያሳዩ ወይም ላያሳዩ ይችላሉ፡፡ ወይም የሌላ ሕመም መንስዔ መሆኑ በላቦራቶሪ ምርመራ ተረጋግጦ አንዱን ይይዛሉ ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከጥቂት ቀናት መገለል በኋላ ‹‹አገገሙ›› ይባላል፡፡ አገገሙ ማለት ምን ማለት ነው? ሙሉ በሙሉ ድነዋል ማለት ነው? ወይስ ቫይረሱ ቢኖርባቸውም እየዳኑ ነው ለማለት ነው?
ዶ/ር ቅድስት፡- አንድ ሰው በለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ከገባ በኋላ ከላይ የጠቀስናቸው እንክብካቤዎች ሁሉ ይደረጉለታል፡፡ ዓለም አቀፍ መረጃ እንደሚያሳየው በሦስት ደረጃ ከፋፍሎ አስቀምጧቸዋል፡፡ ማይልድ፣ ሲቬየርና ክሪቲካል ብሎ፡፡ ማይልድ የሚባሉት 80 በመቶ ጤናማ የሆኑ ሲሆን፣ 15 በመቶዎቹ ደግሞ ሲቬየር የሚባሉት ወይም ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸውና ሆስፒታል ገብተው የኦክስጅን ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ አምስት በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ክሪቲካል ውስጥ ያሉ ወይም በጽኑ ሕሙማን ክፍል (አይሲዩ) ውስጥ ሆነው ሰው ሠራሽ መተንፈሻ የሚገጠምላቸው ናቸው፡፡ አገግሟል የሚባለው ሰው በየትኛው ደረጃ ላይ የነበረና ምን ዓይነት ምልክቶች ያሉት እንደሆነ ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡
በኮረና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ወደ ሐኪም ቤት የገቡባቸው ደረጃዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ በገቡበት ደረጃ በሚሰጣቸው የሕክምና ድጋፍ በሚያመጡት ለውጥና ድጋፉ ሲቋረጥ፣ ምርመራ ተደርጎላቸው ሁሉ ነገራቸው እንደ ቀድሞ ሁኔታቸው ከተመለሱና ሲመረመሩ ነፃ ከሆኑ አገግመዋል ይባላል፡፡ ግን ነፃ ቢሆኑም ቫይረሱ ከሰውነት ቶሎ ስለማይወጣ፣ ነፃ ከተባሉ በኋላም የተወሰኑ ቀናት እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የሞቱ፣ ወደ አገራቸው የተመለሱ፣ ያገገሙና በለይቶ ማቆያና በጽኑ ሕሙማን ክፍል ያሉት ተደምረው ይህንን ያህል የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች አሉ ይባላል፡፡ የሌሎቹ ተቀንሰውና ተለይተው ለምን ዕርዳታ እየተደረገላቸው ያሉት ብቻ አይነገርም?
ዶ/ር ቅድስት፡- በዓለም ደረጃ ምን ያህል ሰው በኮሮና ቫይረስ እንደተጠቃ ለማወቅ መረጃው ስለሚያስፈልግ እንጂ ሌላ ምንም ዓይነት ነገር የለውም፡፡ ዳታው ስለሚያስፈልግ ብቻ ነው ሁሉም ተደምሮ የሚነገረው፡፡ በየአገሩ በቫይረሱ የተጠቃውን፣ የሞተውን ያገገመውንና ሙሉ በሙል የዳነውን ለማወቅ ስለሚረዳ ሁሉም ይመዘገባል፡፡ ተመዝግቦም ይቀመጣል፡፡