ዲፕሎማትና የእንግሊዝኛ አስተርጓሚ የነበሩት የቅርብ ወዳጃቸው አቶ ጳውሎስ መንአመኖ፣ በእርሳስና በቀለም የተጻፉትን ወረቀቶች ሲሰበስቧቸውና በ1914 ዓ.ም. ለልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን (የወደፊቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት) “ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የሚጠቅም ነገር አላቸው” ብለው እንዲታተም በልመና መልክ ደብዳቤ ሲልኩላቸው፣ በ1940ዎቹ ተፈጠረ የተባለውን በመዋቅራዊ ችግሮች ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ አተናተን (Structural economics)፣ በተለይም የፕሬቢሽ እና ሲንገርን ሥራዎች፣ ከፍ ሲል ደግሞ የልማት ምጣኔ ሀብታዊ አተናተንን ቀድመው ተረድተው እንደጻፉ፣ ለአገራቸው ብቻ ሳይሆን ለዓለም ፈር ቀዳጅ እንደነበር ያውቁ ይሆን?
ከጦር ጀግኖቻችን ባሻገር በኢኮኖሚው ዘርፍ፣ በሕክምና፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል አስተዋፅኦ ያደረጉ ሰዎቻችንን እንደ ብሔራዊ ጀግና መመልከት ላይ ደካሞች ነን፡፡ ዓለም እንደ ምልክት ከምትጠቀምባቸው ነገሮች አንዱ የገንዘብ ኖቶች ነው፡፡ ባደጉት አገሮች በተለይም በአውሮፓ የገንዘብ ኖቶቻቸው ምንም እንኳ በዘመን ቢቀያየሩም በሳይንቲስቶች፣ በሥነ ጽሑፍ ሰዎች፣ በሙዚቀኞች፣ በዴሞክራሲያዊ መሪዎች የተሞላ ነው፡፡ በተቃራኒው ያላደጉት አገሮች የገንዘብ ኖቶች በአምባገነን መሪዎቻቸው ምስል፣ ከቅኝ ግዛት ነፃ ያወጡ ጀግኖቻቸው፣ ከቅኝ ግዛት ነፃ አውጥተው በአምባገነንነት የመሩና የሚመሩ መሪዎች ምስል የያዙ ኖቶች መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1893 እስከ 1976 በሕይወት የቆዩት ሊቀመንበር ማኦ በቻይና ረሚኒቢ /Renminbi/፣ የፖለቲካና መንፈሳዊ መሪው ማህተመ ጋንዲ በህንድ ሩፒ /Rupee/፣ የፈርኦኖች ምስል በግብፅ ፓውንድ/pound/፣ እንዲሁም በ1979 የአብዮት መሪውና የመጀመሪያው የእስላማዊት አገሩ ታላቁ መሪ ሩሆላህ ሆሚኒ በኢራን ሪያል /rial/ የገንዘብ ኖቶች ትልቅ ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከነዚህ አገሮች በተለየ መልኩ በኖርዌይ ክሮን/Krone/ በ100 ክሮን የኦፔራ ሙዚቀኛዋ ክርስቲን ፍላግስታድ፣ በ200 ክሮን ኖት ሳይንቲስቱ ክርስቲያን ቢርከላንድ፣ በ500 ክሮኖ ኖት በ1928 የሥነ ጽሑፍ የኖቤል ተሸላሚው ሲግሪድ አንደስት እና ሌሎች ለአገሪቱ ጉልህ አበርክቶ ያላቸው ሰዎችን እንደምልክት በየገንዘብ ኖቶቻቸው መልካም ሐውልት አቁመውላቸዋል፡፡ የኛውን ሆድ ይፍጀው፡፡
የ“አጤ ምኒልክ እና ኢትዮጵያ” /በአጤ ምኒልክ መንግሥት ሥርዓት ላይ የተደረገ የሰላ ሒስ regime critics/ እና “የመንግሥት እና የሕዝብ አስተዳደር” ደራሲው ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ (1878-1911) ከጥቂት የጦር ጀግኖቻችን ባሻገር የኢኮኖሚ ምሁር ለሆኑት፡-
“. . . መከረ፣ ነገረ ለባለሥልጣናት፣
ሕዝቡን እንዲያወጡት ከድህነት ጥፋት
ሰሙት ሰሙትና ዕውነት ቢመስላቸው፣
ቀጠፉት ባጭሩ ምክሩ አሳስቧቸው፡፡” የሚለው ይህን ግጥም በኢኮኖሚው የምርምር መስክ አራት መጻሕፍትን እና በርከት ያሉ የምርምር ጽሑፎች ያሳተሙት የፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ነው፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ለምጣኔ ሀብት የሙያ ዘርፍ ለዓለምና ለአገራችን ያደረጉትን አስተዋፅኦ በማስተዋወቅ የመጽሐፍ ሐውልት አቁመውላቸል፡፡ ነጋድራስ ምንም እንኳ በሞያ ሐኪም ቢሆኑም በፍላጎትና በንባብ (ፈረንጆቹ interested in Economics እንደሚሉት) ከዘመኑ ምሁራን ሁሉ ልቀው የሚታዩ ኢኮኖሚስት እንደነበሩና የፖለቲካል ኢኮኖሚን አበጥረው በማወቅና ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር አዛምደው መተንተናቸውን ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983” በሚለው መጽሐፋቸው መስክረዋል፡፡
ፕሮፌሰር ዓለማየሁ እና አብርሃም ‘A Dynamic Modeling of Gebrehiwot Ideas’ በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው የነጋድራስን ሐሳብ ወደ ሒሳባዊ ሞዴል ቀይረው ያስረዱናል፡፡ ይህም የፍላጎት በገብረ ሕይወት ሞዴል፣ የአቅርቦት በገብረ ሕይወት ሞዴል፣ እና የገንዘብ ነክ እና የቀረጥ ነክ ፖሊሲ በገብረ ሕይወት ሞዴል ብለው ዘርዘር አድርገው ገልጸውታል፡፡ ለአንድ አገር ዕድገት እንደ ተግዳሮት የውስጥ ችግር (ግጭት ወይም ጦርነት) እና የውጪ የንግድ ሚዛን መዛባት ወሳኝ ሚና አላቸው ይላሉ፡፡ ይህንንም ፕሮፌሰር ዓለማየሁ “ገብረ ሕይወት የኢኮኖሚ ተዋናዮችን የሚመለከቷቸው በመደባዊ ይዘታቸው ነው፡፡ እነዚህ ተዋናዮች በተቋማት ላይ ያላቸውን አንድምታ በውሉ ተንትነዋል፤” በማለት ይገልጹታል፡፡
እኚህ አስተሳሰቦቹ በመዋቅራዊ ችግሮች ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ ሐቲት (Structural economics) እና የድኅረ ኬንስ ኢኮኖሚያዊ ሐቲት (Post Keynesian economics) የሚባሉትን የዛሬ ኢኮኖሚስ ትምህርት ፈርጆቹ ፋና ወጊ መሆናቸውን ቁልጭ አርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይህ ትንታኔያቸውም የመንግሥት የገንዘብና የቀረጥ ነክ ፖሊሲ ምን መሆን እንዳለበት አጥጋቢ በሆነ መልኩ ለማስረዳት መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡
በሌላ በኩል የውጭ ንግድ መዛባትን እንዲህ ይገልጹታል፡- “ኢትዮጵያ በውጭ ንግድ በኩል በተለይም ከአውሮፓ ጋር መከተል ያለባትን መንገድ ይተነትናል፡፡ ለምሳሌ አውሮፓና ኢትዮጵያ ሲነግዱ ያላደገው አገር እንደሚጎዳ ማስረዳቱ ላይ ነው፡፡ ለዚህም መሠረታዊው ምክንያት ያላደገው አገር ምርት ብዙ ዕውቀት የሌለበት ጥሬ ዕቃና የትራንስፖርት ወጪው ትልቅ ሲሆን፣ ያደገው አገር ዕቃ ደግሞ የተቃራኒውን ይዘት ይይዛል፡፡ ይህ ደግሞ ላልተመጣጠነ የንግድ ልውውጥ ብሎም ላላደገው አገር ድህነት መዳረግ ምክንያት ይሆናል፡፡” ሆኖም ይህ ሐሳብ ዓለም የሚያውቀው ‘የፕሬቢሽ ሲንገር’ እያለ እንደሆነ እና ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ግን ይህ ሐሳብ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ከ40 ዓመት በፊት ቀድመው አውቀውትና ጽፈውት ነበር ይሉናል፡፡
የ ‘ፕሬቢሽ-ሲንገር’ ሐሳባቸው ምን ነበር ለሚለው? የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እ.ኤ.አ. በ2013 ባሳተመው “Testing the Prebisch-Singer Hypothesis since 1650: Evidence from Panel Techniques that Allow for Multiple Breaks” በሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ በምጣኔ ሀብት በረጅም ጊዜ የመሠረታዊ ዕቃዎች ዋጋ በፋብሪካ ከሚመረቱ ዕቃዎች ካላቸው ግንኙነት ጋር ተያይዞ ዋጋቸው ይቀንሳል ብለው ፕሬቢሽ እና ሲንገር ይከራከራሉ። ይህም በኢኮኖሚው የመሠረታዊ ምርቶች ንግድ ማሽቆልቆል ያስከትላል ይላሉ። ከ2013 ወዲህ የወጡ ጥናቶችም ይህን ሐሳብ የሚደግፉ መሆናቸው ምሁራኑ ይጠቅሳሉ። ከ1940ዎቹ ጀምሮ በራስ ላይ የመመርኮዝ ሥነ ሐሳብ (dependency theory) እና የገቢ ንግድ መተኪያ ኢንዳስትራላይዜሽን (import substitution industrialization) የመሳሰሉ ፖሊሲዎችን ያቆመ ምሰሶ ሆኖ ማገልገሉንም ያብራራሉ።
በተቃራኒው ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ‘Gebrehiwot Baykedagn, Eurocentric and the decentering of Ethiopia’ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ነጋድራስ የአውሮፓን ሥልጣኔ በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን እንደሞከሩና ኢትዮጵያን በአውሮፓውያን ዓይን በማየት ለኢትዮጵያ ችግር የአውሮፓውያን መድኃኒት እንዳዘዙ አድርገው አቅርበውታል፡፡
ሆኖም ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የአውሮፓን ሥልጣኔ እንዳለ እንገልብጥ ሳይሆን እንዲያውም በተቃራኒው የኢትዮጵያ መንግሥት የጃፓን መንግሥት ያደረገውን እንዲከተል ይመክራሉ /ገጽ 28/፣ እንዲሁም በገጽ 37 እንዲህ ይላሉ፡፡ “. . . አንዱንም ሕዝብ የሚጠቅም ደንብ ሌላውን ሕዝብ ሳይጠቅም አይቀርም አያሰኝም፡፡ . . . ደንብ ሁሉ ምንም ቢጠቅም በተለየ ጊዜያት ውስጥ እና ለተለየ ሕዝብ ነው፤” በማለት ምንም ያክል ጥሩ አሠራሮች ወይም የዕድገት መንገዶች በአውሮፓና ጃፓን ውጤታማ ቢሆንም ለአገር በሚበጅ መልኩ ሊቀረፁ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የነጋድራስ የምጣኔ ሀብት ሐሳብ ለዚህ ዘመን ምኑ ነው?
ጽንሰ ሐሳቡ እንደመፍትሔ ከተተነተነ መቶ ዓመት ያለፈው ለዛሬው ዘመን እንዴት እንደ መፍትሔ መጠቀም እንችላለን? ለሚለው ዝናቡ ሳማሪኦ ረኪሶ የተባሉ ምሁር ‘Economics of Late Development and Industrialization: Putting Gebrehiwot Baykedgn (1886-1919) in Context’ በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው መከራከሪያቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ የኢኮኖሚ ልማት ለማረጋገጥ መንግሥት በተቀናጀ መልኩ በመሠረተ ልማት፣ በሰው ኃይል ልማት፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ ሥርፀትና ፈጠራ ማስተዋወቅ፣ የአገር ውስጥ ገበያ ማስፋፋት፣ የፋይናንስ ዘርፍ ልማትና የገቢ ንግድ ክልከላ፣ በሰፊው ጣልቃ በመግባት አቅጣጫ ማስቀመጥ እንዳለበት ያትታል። በታሪካዊና ጽንሰ ሐሳባዊ ማስረጃዎች መሠረት ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ የገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሐሳቦች ለዚህ ዘመን ልማታዊ ዓውድ ቅቡልና ትስስር ያላቸው መሆኑን ይከራከራል።
በተጨማሪም ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ‘Ethiopian Macroeconomic Modeling in Historical Perspective: Bringing Gebre-Hiwot and His Contemporaries to Ethiopian Macroeconomics Realm’ በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው፣ የነጋድራስ ምሁራዊ ጽሑፎች ድሮ ተሠርተው ታሪክ ሆነው የሚቀሩ ሐሳቦች እንዳልሆኑና የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች ብለው ምሁራዊ ትንታኔና የፖሊሲ አቅጣጫ ያሳዩባቸው ጉዳዮች በሚያሳዝንና በሚያሳፍር መልኩ ዛሬም ከኛ ጋር ያሉ፣ ዛሬም ምክራቸውን እንዳልተጠቀምንባቸው አመላክተዋል፡፡
ያልተቋረጠ የዘመናት አዙሪት
ዓመቱን ሙሉ የኢትዮጵያዊ የውዝግብ አስኳል አንድ ዓይነት ነው፡፡ እንደ አገር ሰብስበው ያስጠኑን ይመስላል፡፡ መስከረም ሲመጣ የዘመን አቆጣጠር የኔ ብሔር ነው ጀማሪው፣ የኔ ነው በሚል ዓመቱን አሐዱ ይላል፡፡ ብዙም ፈቅ ሳይል በማግስቱ በመስከረም ሁለት /የደርግ መንግሥት የድል በዓል/ የውዝግብ አጀንዳ ይሆናል፡፡ የኢሬቻ በዓል በመስከረም የመከራከርያ ሽፋን ከሚያገኙት ጉዳዮች ዋነኛው ነው፡፡ ጥቅምትን ስንይዝ ከወደ ሸዋ አፄ ምኒልክ ወደ ዓድዋ ለመዝመት የክተት አዋጅ ያስነገሩበት ወቅት ተንተርሶ፣ ለየካቲቱ የዓድዋ ድል ውዝግብ ማሟሟቅ ይጀምራል፡፡ በኅዳር 12 ታጥነን በብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለሌላ ፍልሚያ እንዘጋጃለን፡፡ ወርኃ ታኅሣሥ እንኳ እንዳያልፈን በዓሉን መሠረት አድርገን እንትን የሚባለውን ቢራ እንዳትጠጡ፣ የእንትን ብሔር አገልጋይ ነው የሚል ሙግት በማንሳት ያለጠብ የምናባክነው ወር እንደሌለ እናስመሰክራለን፡፡
ወርኃ ጥር ሲመጣ የአፄ ዮሐንስ ፬ኛ ንጉሠ ነገሥት ሆነው የነገሡበት ቀን የክርክር ሜዳ ይሆናል፡፡ ሌላም በጥቅምት የተጀመረው ማሟሟቅ ከፍ ብሎ የዶግዓሊ ድል የመናቆርያ አጀንዳ የሚሆነው በወርኃ ጥር ነው፡፡ ታላቁ የካቲት፣ ባለብዙ የመነታረክያ አጀንዳዎች ባለቤት ተረካቢው ወር ነው፡፡ በየካቲት አሥራ አንድ /የትግራይ ሕዝብ ትጥቅ ትግል የጀመረበት ዕለት/ ጀምሮ መንገዱን በየካቲት አሥራ ሁለት በፋሺስት ጣሊያን የተጨፈጨፉ ሰማዕታት ከማሰብ ይልቅ ባንዳ ጨፈጨፋቸው፣ አንተ ነህ ባንዳ አንተ ነህ በሚል ተቋስለን፣ ወደ የዓድዋ ድል ድል አይደለም፣ ድል ነው /ዛሬ ዛሬ ደግሞ የኛው ወገን ነው የበዛ አስተዋፅኦ ያረገው በሚለው ተተክቷል ጎን ለጎን/ በሚለው ተፋልመን በየካቲት ወር ማገባደጃ ላይ የካራማራ ጦርነት /በቅርቡ የተቀላቀለ ጮማ የመከራከሪያ አጀንዳ/ አዳሩን ያደርጋል፡፡ መጋቢት ሲብት በአፄ ዮሐንስ መስዋዕትነት ተጨቃጭቀን፣ በሚያዝያው የአርበኞች እና “ሜይ ደይ” ተዝናንተን ግንቦት ሃያ ላይ ለክርክር እንቀርባለን፡፡ ዝነኛው ነሐሴ ከነዝናዛ ዝናቡ ጋር ጮማ የመቧቀሻ አጀንዳውን ይዞ ይመጣል፡ አሸንዳ፣ አሸንድዬ እና ሶለል፡፡
ይህ ላለፉት ዓመታት የምናደርገው ቀድሞ የተጻፈ ፕሮግራማችን ነው፣ ቀድሞ ለሁላችን በጅምላ የታደለን መመሪያ፡፡ በዚህ መሃል በፌደራል መንግሥት፣ በክልል መንግሥታት፣ በማኅበራዊ ትስስር ዕውቅ ጸሐፊዎች፣ በሚዲያዎች የሚወረወሩ የቃላትና የድርጊት ትንኮሳዎች ቀድሞ ባጠናነው መሠረት እንፈርጃለን፣ እንከራከራለን፣ እንቧቀሳለን፣ እንለያያለን፡፡ አዲስ ዓመት ግን በአንድ ዓይነት አጀንዳዎች መቋሰሉ ይቀጥላል፡፡ አዲስ ዓመት ነባር ቁስል፣ አዲስ ዓመት ነባር ምስል፣ አዲስ ዓመት የነበር ታሪክ. . . ያልተቋጨ የዘመናት አዙሪት፡፡
የዚህ አዙሪት ዘዋሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ የታሪክ ጸሐፊዎቻችን፣ የሚዲያ አካላት፣ የኪነት ሰዎች፣ ምሁራን ይህን መመሪያ በጥብቅ ይከተላሉ፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የታሪክ ጸሐፊዎቻችንን በሁለት ይከፍሏቸዋል፡፡ አንዱ ዓይነት የቤተ መንግሥት ሊቃውንት ይባላሉ፡፡ እንጀራን ሲፈልጉ ንጉሡ ያዘዛቸውን የራሱን ውዳሴ፣ ታሪክ ብለው ጽፈው ለሁዋላው ትውልድ የሚያቆዩ አቆላማጮች፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ግን መነኮሳት ናቸው፡፡ እነሱም የሚጽፉት ታሪክ አድልዎ ይበዛበታል፡፡ . . . ከድንቁርና ወጥቶ ከፍ ባለ ህሊና ተመርቶ ስለዜጎች ልማት የሚጥርን ግን ርኩስ ይላሉ በማለት ይገልጿቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ታሪክ ከተረከብን በኋላ ይህንኑ ለዓመታዊው አዙሪታችን እንጠቀምበታለን፡፡
ዋናው የአዙሪት መንገዳችን የተቃኘው በታሪክ ጸሐፊዎቻችን ነው፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ለታሪክ ጽሑፍ ተመልካች ልቡና የተደረገውን ለማስተዋል፣ የማያዳላ አዕምሮ በተደረገው ለመፍረድ፣ የጠራ የቋንቋ አገባብ እንደሚያስፈልግ ይገልጹና ለዚህ የአዙሪት ሰለባ በምሳሌነት የአፈወርቅ ገብረየሱስን የታሪክ አጻጻፍ መንገድ በአፄ ምኒልክ እና ኢትዮጵያ መጽሐፋቸው፣ “ዳግማዊ ምኒልክን ለማመስገን አፄ ዮሐንስን ማንቋሸሻቸውን” ስህተት እና ከርሳቸው እንደማይጠበቅ ይገልጻሉ፡፡ በአገራችን አንዳንዴ ከተጻፈው ታሪክ ይልቅ ትንሿን ነገር እንዴት በኪነት እንደምናጋንን ግሁድ ነው፡፡ እንዲያውም ከታሪክ ጸሐፊዎቻችን ይልቅ የኪነት ሰዎች የአዙሪታችን አምበል ናቸው፡፡
ሌላው የዓመት የክርክር ድጎማችንን ከሃይማኖት እንቀበላለን፡፡ ነጋድራስ በመጽሐፋቸው፣ “አሁን በ19 መቶ ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በሁዋላ አልፈን በሃያኛው መቶ ዓመት ስንጀምር አንድ ሰው የተዋሕዶን ሃይማኖት ቢነቅፍ ከአዲስ አበባ ገበያ ላይ በድንጊያ አልተቀጠቀጠምን?” የአሁኑን ዘመን ታዝቦ የጻፉት ይመስላል፡፡ የሃይማኖት አዙሪት፡፡ የኔ ሃይማኖት ይበልጣል፣ የክርስትና ደሴት፣ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች እያልን የምናበላልጠውን እና ከራሳችን ይልቅ የሰውን ሃይማኖት በመንቀፍ የምናሳልፈውን አዙሪታችንን ነጋድራስ (በገጽ 28) “ሃይማኖቱ ተዋሕዶ ያልሆነ ሰው ሁሉ እንደ ርኩስ ይቆጠራል፡፡ ይህም በእጅጉ ያስቃል፡፡ አዕምሮ የሌለው ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሳያውቅ የእግዚአብሄር ጠበቃ ሊሆን ይወዳል፤” ይላል፡፡ አሁንም በፅንፈኞች አብያተ ክርስቲያን ይቃጠላሉ፣ መስጊዶች ይጋያሉ፣ ምዕመናን ይገለላሉ፣ ይሰደዳሉ፣ ለአዙሪቱ ትልቅ ግብዓት፣ የዓመት ስንቅ ይሆናል፡፡
አሁንም ከዘመናት ችግራችን ጋር ነን፣ አሁንም ከዘመናት መድኃኒት ያልጎበኘው ቁስላችን ጋር ነን፣ አሁንም ትናንት ላይ ነን፣ ትናንት ነን፣ ክፉ የአዙሪት ስቃይ፡፡ አይነኬ የሚመስሉንን ነገሮች በቅንነት ለመንቀፍ ስንነሳ እንኳ ከሐሳባችን ይልቅ ከየት እንደመጣን አጣርቶ ይወቅሰናል፡፡ ስለዚህም ፍርሃቱ ከኛ ጋር ነው፡፡ በጊዜው ‘ባለጊዜ’ የሚባሉትን የሸዋ ሰዎች ሊወቅስ ሲነሳ ነጋድራስ ፍርሃት እንደተሰማቸው በገጽ 12 “እንግዲህ ከጸሐፊው ልብ ውስጥ ፍርሃት ተነሳ፣ የሸዋዎቹን ሐሳብ ሊመረምር ነውና፡፡ ዘመናይ ሁሉ ሊያመሰግኑት እንጂ ሊወቅሱት አይወድም፡፡ ስለዚህ ብዙ የሸዋ ሰው ሳይቆጣ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ሰውን ፈርቶ እውነቱን የሚሸሽግ ሰው እንደ ጀግና ይቆጠራልን? መንግሥቱንም የሚወድ ሰው ያ ቅዱስ ቅዱስ የሚለው አይደለም፣ ጥፋቱን ይገልጽለታል እንጂ፡፡” በማለት የመፍትሔ ሐሳቡን ያስቀምጣል፡፡
ከአዙሪቱ ለመውጣት አዙሪት ውስጥ እንዳለን ማመን ይቀድማል፡፡ ያለፈውን ዓመት እንዴት አሳለፍን? ዘንድሮስ እንዴት እያሳለፍነው ነው? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ መነታረኩን በመተው እንደዝንባሌያችን “የኔ” የምንላቸውን የጦር ጀግኖቻችን በየፊናችን በመከባበር እያነገሥን በሌላ በኩል እንደ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ዓይነቱን ጉምቱ የቀለም ቀንድ በጋራ ጀግና ይዘን ብንጓዝ ከአዙሪታችን ለመውጣት ይረዳናልና በጋራ ጀግኖቻችን እንምከር፣ አስተምህሮቶቻቸውንም እንጠቀምበት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአፈር ሳይንስ የማስተር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪ ያላቸውና ተመራማሪ መሆናቸውን፣ ጽሑፉም የእሳቸውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ እሳቸውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡