Ethiopian Reporter Magazine
Wednesday, March 29, 2023
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት
Ethiopian Reporter Magazine
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
Ethiopian Reporter Magazine
ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ

ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

በ ሔኖክ ያሬድ
May 2020
ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት
44
ያጋሩ
1.9k
ዕይታዎች
Share on FacebookShare on Twitter

“በሳል፣ በጉንፋን የምትሞተውን ሞት ከሩቅ አገር እኛን ለማጥቃት ለመጣው ጠላታችን ባገርህና በርስትህ በቤትህ ላይ ሁነህ መመከት አቅቶህ ላገርህ ኢትዮጵያ ሞት ብትነፍጋት፣ ደምህንም ሳታፈስ ብትቀር በፈጣሪህ የምትወቀስበት በዘርህ የምትረገምበት ነውና የተለመደ የጀግንነት ልብህን ሳታበርድ፣ ወደፊት የሚቆይህን ታሪክህን እያሰብህ ጠንክረህ ለመዋጋት ቆርጠህ ተነሣ”

ይህ ከላይ የሰፈረው ኃይለ ቃል፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሰማንያ አራት ዓመታት በፊት ፋሺስት ጣሊያን በሰሜን በኩል መረብን ተሻግሮ ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ፣ ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት ብለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዓርብ መስከረም 23 ቀን 1928 ዓ.ም. ባስታወቁበት ወቅት ያስተላለፉት አዋጅ ነበር፡፡

ይህቺ ታሪካዊት ቀን ለአፍሪካውያን እንደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ይቆጥሯታል፡፡ የታሪክ ምሁራኑ ፍሬድሪክ ኩፐር ሆነ ጥላሁን ጣሰው አገላለጽ፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረው ጣሊያን ኢትዮጵያን በ1928 ዓ.ም. በወረረችበት ጊዜ ሲሆን አጠቃላይ ጦርነቱ ያበቃው በ1937 ዓ.ም. ነበር፡፡

የፋሺስት ጣሊያን ጦር ወረራውን ረቡዕ መስከረም 21 ቀን መፈጸሙን ተከትሎ ሕዝበ ኢትዮጵያ ለቀረበለት የክተት ጥሪ ሳያወላውል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፎች

አርበኞች ሽለላና ፉከራ ሲያሰሙ

May 2021
ደም የተከፈለበት ባርነት፤ የኤርትራ አብዮት ህልሞችና ውድቀት።

እውነትና ንጋት… (የመጽሐፍ ቅኝት)

August 2020

“ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም” ዓውደ ጥናት ሊካሄድ ነው

June 2020

ዓባይ የህልውና ዋስትና የሕይወት ኅብስተ መና

April 2020

ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

April 2020

ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

February 2020

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን (1888 ዓ.ም.) ዓድዋ ላይ ድል የተመታው የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት ከ40 ዓመታት ቆይታ በኋላ በፋሺስቱ ቤኔቶ ሙሶሎኒ አማካይነት ኢትዮጵያን መውረሩና በተለይ በዓለም የተከለከለው የመርዝ ጋዝ በመጠቀም በ1928 ዓ.ም. ጥፋትና ዕልቂት በተምቤን፣ በሐሸንጌ፣ በዑጋዴን፣ ወዘተ አድርሷል፡፡ 

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ነፃነትና ክብርን የሚሹ የጀግንነት መንፈስን የሰነቁ እርመኛ አርበኞችና ሕዝቡ በስምንቱ ማዕዝናት ተነስተው የአባቶችና የእናቶችንም የጀግንነት ጋሻ በማንገብ ከአምስት ዓመታት ተጋድሏቸው በኋላ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ድላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በእርመኛ አርበኝነታቸው የድሉን ሰንደቅ ከፍ ካደረጉት መካከልም ሴት አርበኞች ይገኙበታል፡፡

ሴቶችና ተጋድሏቸው

‹‹ሰንበሌጥ [ለቤት ክዳን የሚሆን ሳር] ውስጥ ሆኖ ሲተኩስ አየው ነበር፡፡ ድንገት ፊቱን ወደኔ መለስ አደረገ፣ ወደቀም፡፡ እኔም የያዝኩትን ቦታ ለቅቄ ወደ እሱ ሄድኩኝ፤ ሞቶ ነበር፡፡ በወንዙ ሌላኛው አቅጣጫ በጎን በኩል የጠላት ወታደሮች ተጠግተው ነበር፡፡ ከነበርኩበት ቦታ ከማፈግፈጌ በፊት ወደ ወንዙ አቅጣጫ ተኩስ ከፈትኩ፣ ሦስት ሰዎችንም ገደልኩ፡፡ ከዚያም የባሌን አስከሬኑንና መሣሪያውን እየተጎተትኩ ወደ ኋላ አፈገፈኩ፤ የተቀሩትና ከኔ ጎን ተሠልፈው የነበሩት ሁሉ ግን ደህና ነበሩ፡፡ ወደ ጦር ሠፈሩ ተመለስኩ፡፡ በማግሥቱም አስከሬኑን በዲርማ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስቀበርኩ፡፡››

ከባላቸውና ከልጃቸው ጋር የዘመቱት አርበኛዋ ወ/ሮ ልኬለሽ በያን በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ባለቤታቸው ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ያዩትንና እሳቸው የፈጸሙትን ጀብዱ ማመልከታቸውን ፀሐይ ብርሃነ ሥላሴ፣ ኖርዝኢስት አፍሪካን ስተዲስ ባሳተመው መድበል ውስጥ “Women guerrilla fighters” በሚለው መጣጥፋቸው ገልጸውታል፡፡

ከቁርጠኛ ጀግኖች አንዷ ልዕልት ከበደች ሥዩም መንገሻ
ከቁርጠኛ ጀግኖች አንዷ ልዕልት ከበደች ሥዩም መንገሻ

በሰሜን የማይጨው ግንባር ከዘመቱት ሴቶች መካከል ከአርሶ አደር ቤተሰብ እስከ ልዕልታቱ ይገኙባቸዋል፡፡ “Africa and World War II” በሚል ርዕስ በአሜሪካ ካምብሪጅ ፕሬስ በታተመውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ስለነበረው አፍሪካዊ ገጽታ በሚተነትነው የጥናት መድበል ውስጥ ዶ/ር ኃይሉ ሀብቱ፣ “Fighting Fascism Ethiopian Women Patriots 1935 – 1941” በሚለው ጥናታቸው እንደጠቀሱት፣ ወ/ሮ ዘነበች ወልደየስ ባለቤታቸውን ተከትለው የዘመቱት አርበኛ ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙ ሲሆኑ፣ ሌላዋ ዘማች ልዕልት ሮማነ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ ከባለቤታቸው ከባሌው ገዢ ጋር አብረው ከትተዋል፡፡ በተመሳሳይም የሸዋው ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ ልጅ ወ/ሮ ላቀች ደምሰው ከባለቤታቸው ደጃዝማች መንገሻ አቦዬ ጋር የወንድ ልብስ ለብሰው ሽጉጣቸውን ታጥቀው ዘምተዋል፡፡ ወ/ሮ ዘነበች ወልደየስ ከባለቤታቸው ከራስ አበበ አረጋይ፣ ወ/ሮ ሸዋነሽ አብርሃ አርአያ ከባለቤታቸው ከደጃዝማች ኃይሉ ከበደ (ሌተና ጄኔራል) ጋር እንዲሁ ከትተዋል፡፡

ወ/ሮ ሸዋነሽ አባታቸው ደጃዝማች አብርሃ አርአያ የአፄ ዮሐንስ አጎት የራስ አርአያ ድምፁ ልጅ ናቸው፡፡ ባለቤታቸው ደጃዝማች/ዋግ ሹም ኃይሉ ከበደ እንደ አፄ ዮሐንስ አንገታቸውን በኢትዮጵያ ጠላቶች የተሰየፉ ናቸው፡፡ ፋሺስቶች ከሰየፏቸው በኋላ ጭንቅላታቸውን ወደ ሮም መስደዳቸው ይወሳል፡፡

 አንዳንድ ሴቶች አባቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውንም ተከትለዋል፡፡ ሴቶች ከባለቤታቸው ጋር ቢዘምቱም የግድ በነሱ እዝ ውስጥ መዋሉን አይመርጡም ነበር፡፡ አንዱ ማሳያ የደጃዝማች ሀብተ ሚካኤል ባለቤት የወሰዱት ቆራጥ ዕርምጃ ነው፡፡ ሰው ተጎድቶባቸው ነበርና በዶሎ ግንባር የመጣውን የጣሊያን ጦር ለመግጠም ያመነቱትን ባለቤታቸው ደጃዝማች ሀብተ ሚካኤል አቋም ባለመቀበል 150 ወታደሮች ይዘው ክተት ያሉት በቅሎ ላይ ፊጥ ብለው ነበር፡፡ የጣሊያንን ሠራዊት ገጥመው ሠራዊታቸው በርካታ የፋሺስት ወታደሮችን ገድሏል፡፡ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ማርኳል፡፡ ስማቸው በውል ባለመገለጹ አንዳንድ ጸሐፍት ‹‹ስሟ ያልታወቀው›› እያሉ ይጠቅሷታል፡፡

ሌላዋ አርበኛ ወ/ሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ ተመሳሳይ ርምጃ ወስደዋል፡፡ ባላቸው በ1929 ዓ.ም. ወደ ጣሊያኖች ቢገቡም በርሳቸው ሥር የነበሩትን አርበኞች ይዘው ወደ ኬንያ ማፈግፈጋቸው ተጽፏል፡፡

የአፄ ዮሐንስ የልጅ ልጅ ልጅ፣ የልዕልት ከበደች ሥዩም መንገሻ ባለቤት ደጃዝማች አበራ ካሳ፣ ለፋሺስቶች እጅ መስጠትና መገደል፣ ልዕልት ከበደችን ከተዋጊነት አልመለሳቸውም፡፡ አርባ ወታደሮችን ይዘው ከሌሎች ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር ፍልሚያውን ተቀላቅለውታል፡፡

ስመ ጥር አርበኛውና ታሪክ ጸሐፊው አቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ፣ በ1948 ዓ.ም. በጻፉት “ሀገሬ የሕይወቴ ጥሪ” መጽሐፋቸው የአርበኛዋን ልዕልት ከበደች ሥዩምን ገድል ከዘረዘሩ በኋላ ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር ያስተሳስራቸዋል፡፡ “የሸዋን ቤተ መንግሥት መሥርተው ያቋቋሙ፣ በዓድዋም የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት እንዲነሣ ያደረጉና ድልም የመቱን እኒያ ደፋር በኃይለኝነታቸው የሚያንቀጠቅጡት ሴት እቴጌ ጣይቱ ናቸው” ብሎ ኮንተ አንቶነሊ ራሱ ጠላታቸው መሰከረላቸው፡፡ እንደዚሁ የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ጀግንነት የወረሱ ደፋር የሴት አርበኛ ወይዘሮ ከበደች ሥዩም መንገሻ ናቸው፡፡”

ከቆፍጣና ጀግኖች አንዷ ወ/ሮ ልኬለሽ በያን (ከመሀል)
ከቆፍጣና ጀግኖች አንዷ ወ/ሮ ልኬለሽ በያን (ከመሀል)

በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ ከአምስት አሠርታት በፊት በተጻፈው የአርበኞች ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ፣ ስማቸው ጎልቶ የተጠቀሰው ሴት አርበኛ ወ/ሮ አበባ በላቸው ናቸው፡፡ ወ/ሮ አበባ  ከባለቤታቸው ከሜታ ሮቢ ባላባት ልጅ ስመ ጥሩው አርበኛ ከልጅ ገርቢ ቡልቶ ጋር አራት ዓመት ከነራስ አበበ፣ ከነልጅ ኃይለ ማርያም ማሞ ጋር እስከ 5,000 በተቆጠሩ ወታደሮች ጋር ሆነው በመዘዋወር ጀብዱ የሠሩ ናቸው፡፡ የጀግንነት ቦታቸውም በሜታ ሮቢ፣ በዱላ ቆርቻ፣ በሰላሌ፣ በወሊሶና ዓባይ ዳር ነው፡፡ በአንድ ቀን 16 ጣሊያን ከባለቤታቸው ጋር አብረው ማርከው አስረክበዋል ይላል የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፡፡

የጠላትን ሁኔታ ለመሰለል፣ ምስጢራዊ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ፤ ሴቶች ከወንዶች የተሻለ ችሎታ ለማሳየታቸው አንዷ ተጠቃሽ የውስጥ አርበኛዋ ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ተድላ ዘገየ እንደጻፉት፣ አርበኞች የአዲስ ዓለምን ምሽግ ደጋግመው ለማጥቃትና ለመጨረሻም ለማስለቀቅ የቻሉት በቆፍጣናዪቷ ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ ድጋፍ ጭምር ነው፡፡

በሕክምና ሥራም የረዱ ብዙ ናቸው፡፡ ሰው በቆሰለ ጊዜ ደሙን አጥበው፣ መግሉን አጥበው፣ የተገኘውን የአገር ባህል መድኃኒት አድርገው፣ መግበውና ውኃ አጠጥተው ያድናሉ፡፡ የሞተባቸውም እንደሆነ ለማያውቁት ሰው ጭምር እርር ብለው አልቅሰው ቀባሪ ለምነው ያስቀብራሉ፡፡

ሕክምናን በተመለከተ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩና ወ/ሮ ጽጌ መንገሻ ተጠቃሽ ናቸው፡፡  ‹‹ኢጣልያ በኢትዮጵያ – ከወልወል እስከ ጎንደር›› በተሰኘው የአቶ ተድላ ዘገየ መጽሐፍ እንደሚያብራራው፣ ወይዘሪት ስንዱ በአዲስ አበባ ከአባታቸው ከከንቲባ ገብሩ ጋራ ጎሬ ከተማ ገቡ፡፡ ወይዘሪት ጽጌ መንገሻ ደግሞ ከወንድማቸው ከአቶ ይልማ መንገሻ ጋር አምቦ ከተማ፣ ከጥቁር አንበሳ ጦር ጋር ተቀላቀሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ወጣቶች ጎሬ ካለው ሐኪም ቤት ያገኙትን ያህል መድኃኒት ወስደው ጦሩ በየሄደበት ቦታ ሁሉ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት እስከ መጨረሻው አገልግለዋል፡፡ ደንበኛውን የቀይ መስቀል መለዮ አድርገው፣ እንደ ወንድ ኮትና ሱሪ ለብሰው፣ ቡሽ ባርኔጣ አድርገው በጦርነት ጊዜ የቆሰለውንና የታመመውን በማከም ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ወ/ሮ ስንዱ ባርበኝነት ጉዟቸው ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋራ በጣሊኖች እጅ ከወደቁ በኋላ ለሁለት ዓመት ተኩል በጣሊያን ተግዘው ቆይተዋል፡፡ ከድል በኋላ በኢትዮጵያ ፓርላማ ለሕግ መምርያ ምክር ቤት ለሕዝብ እንደራሴነት በአዲስ አበባ ለጉለሌ አካባቢ ተወዳድረው በማሸነፍ ያገለገሉ ሲሆን እስከምክትል ፕሬዚዳንትነትም ደርሰዋል፡፡

በአምስቱ ዘመን በተለያዩ ግንባሮች በውጊያው አውድማ ውስጥ ከዘመቱት በሺዎች ከሚቆጠሩት ሴቶች መካከል ፊታውራሪ በላይነሽ ገብረ አምላክ አንዷ ናቸው፡፡ ከ14 ዓመት በፊት የ90 ዓመት አረጋዊት ሳሉ ያነጋገራቸው ሺበሺ ለማ እንደጻፈው፣ በ1928 ዓ.ም. ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወር ባለቤታቸው በጅጅጋ በኩል ወደ ጅቡቲ ለስድስት እንዲሄዱ ቢገፋፏቸው አገራቸውን ትተው እንደማይሄዱ ተጋድሏቸውን እንደሚቀጥሉ ነግረዋቸው ተለያይተዋል፡፡ በምሥራቅ ግንባር ሰርጎ የገባው የፋሺስት ወራሪን ሱሪ ታጥቀው፣ ዝናር ታጥቀው ብረት አንግተው ተፋልመዋል፡፡ ከወረራው 10 ዓመት በፊት ያረፉትን የአባታቸውን ፊታውራሪ ገብረአምላክ ውብነህ ማዕረግን የያዙት ፊታውራሪ በላይነሽ፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለኢትዮጵያ ድል 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ ያሳተመው ‹‹እኔ ለአገሬ›› መጽሔት የፊታውራሪ በላይነሽን ገድል ዘርዝሮታል፡፡

‹‹ጣሊያን አሁንም ዋጩ በሚባል አገር ለአሰሳ መጣ፡፡ ኃይለ ማርያም መብረቁ ለሚባሉ አርበኛ ወረቀት ጻፍኩና፣ ‹‹ኑ ዕርዱኝ›› አልኩ፡፡ እኔን ለመርዳት ብዙዎች ብረት ይዘው መጡልኝ፡፡ ለጋራሙለታው ሰው ለፊታውራሪ ሺመልስ ሀብቴም ወረቀት ጽፌ መሣሪያ ይርዱኝ ብዬ ላኩባቸው፡፡ እሳቸውም አንድ መትረየስና 15 ጠመንጃ ላኩልኝ፡፡ ከዚህ በኋላ አርበረከቴ የነበረውን ጣሊያንን እንዲህ እያልን እያቅራራን እንወጋው ጀመር፡፡

እናንተም ወዲህ ኑ እኛም

እንመጣለን

አረበረከቴ ላይ እንገናኝ፡፡

ተጋዳይ፣ ተጋዳይ፣ ተጋዳይ አርበኛ

ገዳይ እቁኒ ላይ ሾላ መገናኛ፡፡

ምናባቱ ፋሽስት፣ ምናባቱ

በረዢም ቁመቱ፣

በደንዳና ባቱ፣

እንወጋዋለን በገዛ ብረቱ፡፡

‹‹ጣሊያን መልሶ ማጥቃት ሲያረግብን ቦረዳ የሚባል አካባቢ ሄደን ተዋጋን፡፡ ከዚያም ከሺመልስ ሀብቴ ጋር ሆነን ወደ ሸዋ አቅጣጫ ውጊያ ጀመርን፡፡ እስከ አርባጉጉ ድረስ እየተዋጋን ቀጠልን፡፡ ነገር ግን በዚያ መቆየት ስላልቻልን ወደ ባሌ ተጓዝን፡፡ ጣሊያንም እዚያ ድረስ ተከታትሎን መጣ፡፡ እኛም መልሰን ወጋነው፤ ፊታውራሪ ሺመልስ ሲዋጉ፣ ሲዋጉ ቆይተው ሲዳሞና ባሌ ጠረፍ ላይ ሞቱ፡፡ የጣሊያን ኃይል እያየለ በመምጣቱና በሌሎቹም ችግሮች ምክንያት አቅማችን ስለተዳከመ መበታተን የግድ ሆነብን፡፡ እኔም ወደ ሸዋ መጣሁ፡፡

‹‹ሸንኮራ፣ ደጃዝማች ፍቅረማርያም የሞቱበት አገር እንዳለሁ፣ አሁንም ጣሊያን ተከትሎኝ መጣ፡፡ እጄን ሳልሰጥ ስዋጋ ቆይቼ ወደ አድአ አፈገፈግሁ፡፡ ጣሊያንም እንደገና ዱካዬን አፈንፍኖ መጣ፣ ቢሾፍቱ ቡርቃ የሚባል፣ ምንጃር ቡልጋ የሚገኝበት ቦታ ጦርነት ገጠምነው፡፡

‹‹እዚያ በጥይት ተመትቼ ቆሰልኩ፡፡ ከዚያም ብረቴን ቀብሬ ቁጭ አልኩ፡፡ እዚያ እየበላሁ፣ እየጠጣሁ፣ ባንዳው እንዳያሳብቅብኝ፣ ጣሊያንም እንዳያገኘኝ ጎፈሬዬንም ተቆርጬ  እያለሁ የጃንሆይን ወደ አገር መግባት ሰማሁ፡፡ የእሳቸውን መምጣት ስንሰማ አዲስ አበባ ለመቀበል መጣን፡፡ ግን አልመጡም አሉን፡፡ ገሚሱ እሳቸውን ለመቀበል ጎጃም ሄደ፣ እኔ ተመለስኩ፡፡

‹‹ጃንሆይ ከገቡ በኋላ እንደገና መጣሁና እየፎከርን ገብተን ጃንሆይን አገኘናቸው፡፡ እኔ ቀሚስ ለብሼ ከአርበኞቹ ተለይቼ ጃንሆይን እጅ ነሳሁ፡፡ የእኔ ዝና ቀድሞውንም ተሰምቶ ነበርና፣ ደጃዝማች ይገዙ ሀብቴ እጄን ይዘው ለጃንሆይ ፣ ‹ጉድ ላሳይዎት› ብለው አቀረቡኝ፡፡ እኔም ቆንጆ ሆኜ የከተማ ሰው መስዬ ነበር የቀረብኩት፡፡

‹‹ጄኔቭ በነበርንበት ጊዜ፣ በላይነሽ የምትባለው ሴት ትዋጋለች እየተባለ የምንሰማው እሷን ነው?› ብለው ጠየቁ፡፡ ደጃዝማች ይገዙም ‹አዎ› ብለው አቀረቡኝ፡፡ ጃንሆይም በፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡ ‹አለሽ እንዴ! ማን ትባያለሽ?› አሉኝ፡፡ እኔም፣ ‹ፊታውራሪ በላይነሽ ነኝ› አልኳቸው፡፡ ‹በስምሽ ተጠሪበት› ብለው ሹመቱን አፀደቁልኝ፡፡››

 ‹‹እስከዳር››

በስም ከሚታወቁት ውጪ ሱሪ ታጥቀው ጠመንጃ አንግተው ፍልሚያውን የተቀላቀሉ በርካታ ሴቶች ነበሩበት፡፡ ከነዚህ በስም ከማይታወቁት ሴቶች መካከል ስለ አንዷ እንስት ታዋቂው ደራሲና አርበኛ፣ ሚኒስትርና ዲፕሎማት አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ ‹‹ትዝታ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ከገጽ 84 እስከ 86 ሐተታ ታሪክ ጽፈውላት ነበር፡፡ ይህን ታሪክ ያነበቡት ባሕር ማዶ የሚገኙት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ስሟ ላልተጠቀሰው አርበኛ ‹‹እስከዳር›› የሚል መጠርያ በመሰጠት ታሪካዊ ልብ ወለድ ጽፈው በ2002 ዓ.ም. አሳትመውላታል፡፡ ደራሲው ዳዊት በመግቢያቸው ላይ እንዲህ ከትበውላታል፡፡

‹‹[አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ] ከገጽ 84 እስከ 86 ስለአንዲት ሴት የጻፉት ለብዙ ጊዜ በሐሳቤ ውስጥ ሲንገዋለል ቆይቷል፡፡ በሐሳቤ ‹ይህች ሴት ማን ትሆን? ከየት ነው የመጣችው? ትውልዷ ምንድነው? እንዴት እዚህ እሳት ውስጥ ገባች?› እያልኩ ራሴን ስጠይቅ ቆይቼ ዛሬ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞከርኩኝ፡፡ ይህችን ስም ያልነበራትን ሴት ስም ሰጠኋት፡፡ እስከዳር አልኳት፡፡ ታሪክ አበጀሁላት፡፡ በኢትዮጵያ የሴት አርበኞች ያሸበረቀ ታሪክ ውስጥ አስቀመጥኳት፡፡ ይኸ መጽሐፍ የወይዘሪት እስከዳር ልብ ወለድ ታሪክ ነው፡፡››

እዚች መጣጥፍ ላይ ልብወለዱን ሳይሆን የምናነሣው አቶ ሐዲስ ስለእርመኛዋ አርበኛ በደራሲ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ስያሜ ‹‹እስከዳር›› ያወጉትን ነው፡፡

‹‹ያንለትና ከዚያ በፊት በነበረው ሌሊት ከዚህ በላይ ባጭሩ እንደ ተረክሁት፣ መንገድ ለመንድ ይታይ የነበረውን የመከራና የስቃይ ትርዒት ሳስታውስ ከሁሉም ጎልቶ ባይነ ህሊናዬ ፊት የሚታየኝ ባንድ ሴት ላይ ሲደርስ ያየሁት ነው፡፡ አንድ ያይሮፕላን ቡድን ደብድቦን ካለፈ በኋላ ዛፍና ቁዋጥኝ ወይም ሌላ ተገን ወዳለበት መሸሹን ያልረሳን ሰዎች ከየተሸሸግንበት ወጥተን ስንሄድ እንደቆየን አይሮፕላኖች ከኋላችን እንደገና ቦምብ እየጣሉ ሲመጡ ሰማን፡፡ ያን ጊዜ የደረስንበት ቦታ የዘንባባ ዛፎችና ሌሎች ዛፎች አለፍ አልፍ ብለው የበቀሉበት ስለነበረ መንገዱን ይዞ ከሚጉዋዘው ሠራዊት መካከል ጥቂታችን ዛፎች ወዳሉበት እየሸሸን ተጠጋን፡፡ በበቅሎ ተቀምጣ ከሠራዊቱ ጋር የምትሄድ አንድ ሴት ነበረች፡፡

ይች ሴት ባለማኅደር ዳዊት ባንገቷ አግብታ ካንድ ብብትዋ ሥር አንጠልጥላ አንድ አጭር ዲሞትፈር ጠመንጃ እንዲሁ ባንገቷ አግብታ በጀርባዋ አዝላ ባንድ እጇ የተቀመጠችበትን በቅሎ ዛብ በሌላ እጇ የተጫነች አጋሰስ በረዥም ላኰ ይዛ ከኋላዋ እየሳበች ትሄድ ነበር፡፡ በክፉ አጋጣሚ አይሮፕላኖች እዚያ ቦታ ሊደርሱ ሲቃረቡ አጋሰስዋ ገረገረችባት (ቆማ ወደ ኋላ ሳበቻት)፡፡ ዘወር ብትል ያጋሰስዋ ጭነት ባንድ ወገን አጋድሎ ከጀርባዋ ወደ ሆዷ ወርዷል፡፡ ከዚያ ሴትዮዋ ከበቅሎ ወርዳ ያጋደለውን ጭነት ወዳጋሰሷ ጀርባ መልሳ ለመጫን ትታገል ጀመር፡፡ ያን ጊዜ ሁላችንም ያይሮፕላኖችን መድረስ አይተን ‹ሴትዮ አይሮፕላኖች መጡብሽ በቅሎዎችን ተይና ነይ! እባክሽ ተያቸውና ወዲህ ነይ!› እያልን ከያለንበት ጮህን፡፡ እሷ የእኛን ጩኸትም ሆነ በምብ እየጣሉ የመጡትን አይሮፕላኖች አታይም አትሰማም ነበር፡፡ ዓይኗንም፣ ጆሮዋንም፣ አሳቧንም ሁሉ ተሰብስቦ ያተኮረው ያን ያጋደለ ጭነት መልሳ ለመጫን በጀመረችው ትግል ላይ ብቻ ነበር፡፡ ከየዛፉና ከየቁዋጥኙ ሥር ስንጮህ ከነበርነው መካከል አንድ ሰው ሴትዮዋን ለማዳን ወደሷ ሮጦ ነበር፡፡ ነገር ግን አይሮፕላኖች ስለቀደሙት ከመሀል መንገድ ወደ መሸሸጊያው ተመለሰ፡፡ ያች ሴት እንዲያ ካጋሰስዋ ጭነት ጋር በመታገል ላይ እንዳለች አይሮፕላኖች ከጣሉዋቸው ቦምቦች አንዱ እስዋና በቅሎዎችዋ በቆሙበት መሀል ወደቀ፡፡ ወዲያው ያ የቆሙበትና በዙሪያው የነበረው መሬት ሁሉ ተጎርዶ ብዙ ሜትር ወደ ሰማይ ሲነሳ የስዋና የበቅሎዎችዋ፣ የመሬቱ፣ የድንጋዩ፣ የሳሩና የቁጥቁዋጦው ብጥስጣሽ ባንድነት ተደባልቆ ባየር ውስጥ ከጓነ በኋላ ተመልሶ ቦምቡ መሬቱን ጎርዶ ሲያስነሳው እስር ተቆፍሮ በቀረው ሰፊ ጉድጉዋድ ዙሪያ ተበተነ፡፡ ታዲያ የሚያስገርመው አይሮፕላኖች እዚያ ባጠገባችን በጣሉት ብዙ ቦምብ ከዚያች ሴትና ከበቅሎዎቹ በቀር ከዚያ ሁሉ ሠራዊት ሞቶ ወይም ቆስሎ ሲወድቅ ያየነው አልነበረም፡፡

የሕክምና ነርስነት አገልግሎት ከሰጡ አርበኞች አንዷ ወሮ ስንዱ ገብሩ
የሕክምና ነርስነት አገልግሎት ከሰጡ አርበኞች አንዷ ወሮ ስንዱ ገብሩ
የውስጥ አርበኛዋ ወሮ ሸዋረገድ ገድሌ
የውስጥ አርበኛዋ ወሮ ሸዋረገድ ገድሌ

‹‹አይሮፕላኖች ከሄዱልን በኋላ ከየዛፉ ስር ወጥተን መንገዳችንን ስንቀጠል ሴትዮዋን ለማዳን  ሩጫ ጀምሮ የነበረው ሰው እንደነገረን ያቺ ሴት ያንድ መኰንን በጣም የሚዋደዱት የጭን ገረድ ኖራለች፡፡ ከሁለት ቀን በፊት የመኰንኑ አሽከሮች እጦርነቱ ውስጥ አልቀው እሳቸውም ክፉኛ ሲቆስሉ ከሞትም ከመቁሰልም የዳኑ እስዋና አንድ ወንድ አሽከራቸው ብቻ ኖረዋል፡፡ ጌትየው በጽኑ ቆስለው በጣእር ውስጥ እንዳሉ እስዋ ባጠገባቸው ሆና ስታስታምማቸው እንደማይተርፉ ተረድተውት ኖሮ ‹አንቺና ተስፋ (ወንዱ አሽከራቸው) ከሞት ተርፋችሁ አገራችሁ ለመግባት የበቃችሁ እንደሆነ፤ መሣሪያየንና አባቴ ሲሞቱ ለመታሰቢያቸው የሰጡኝን ዳዊቴን ለልጄ ለንጋቱ እንድታደርሱልኝ አደራ፡፡ እሱ እስኪያድግ የናቱ ወንድም ብላታ በየነ ባላደራ ሆነው ይጠብቁለት፤› ብለው ተናዘው ሞተዋል፡፡ እንግዲህ ይቺ፣ ሰው ሁሉ ነፍስዋን እንድታድን ያን ያክል ሲማፀናት ዓይኗን እያየ በቦምብ ተቃጥላ የሞተች የወዳጇን ያደራ ኑዛዜ ለመፈጸም ኖሮዋል! ምን ዓይነት እስከ ሞት የሚያደርስ ታማኝነት፣ ምን ዓይነት ኃያል ፍቅር ቢሆን ነው? ‹‹ለሃይማኖትዋ ብላ ለማተብዋ ብላ እንዲያ ተቃጥላ ሞተች!›› አለ ሰውየው የሴትየዋን ታሪክ ከተረከልን በኋላ እየተከዘ፡፡

‹‹እንዴት ለሃይማኖትዋ ብላ? ያይሮፕላን ቦምብ ስንቱን አቃጥሎ ሲጨርስ እያየች ካጋሰስ ጭነት ጋር ስትታገል መሞትዋ ‹ሃይማኖተኛ› የሚያሰኛት መስሎዋት ነው? እንዲህ ያለው ሞኝነት ወይም እብደት ነው እንጂ ሃይማኖተኛነት አይደለም!›› አለ ጤናው ከማዘኑ የተነሳ ቆጣ ብሎ ግን ኃያል ፍቅር ሞኝም፣ እብድም፣ ሃይማኖተኛም ሁሉንም ያደርጋልኮ!››

Share44TweetShare

ተዛማጅ Posts

አርበኞች ሽለላና ፉከራ ሲያሰሙ
ታሪክ

በ ሔኖክ ያሬድ
May 2021
0

ኢትዮጵያ በወራሪው የፋሺስት ጣሊያን ሠራዊት ላይ ድል የተቀዳጀችበት ሰማንያኛ ዓመት ረቡዕ ሚያዝያ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. አክብራለች፡፡ በተለይ በዓሉ በአዲስ አበባ ከተማ በአራት ኪሎው የሚያዝያ 27 አደባባይ፣ የጥንት አርበኞችና...

ተጨማሪ ያንብቡ
ደም የተከፈለበት ባርነት፤ የኤርትራ አብዮት ህልሞችና ውድቀት።

እውነትና ንጋት… (የመጽሐፍ ቅኝት)

August 2020
“ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም” ዓውደ ጥናት ሊካሄድ ነው

“ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም” ዓውደ ጥናት ሊካሄድ ነው

June 2020
ከህዳሴው ግድብ ድርድር በስተጀርባ

ዓባይ የህልውና ዋስትና የሕይወት ኅብስተ መና

April 2020
ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

April 2020
ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

ፖለቲካ እና ኩሽ ኩሸቲክ

February 2020
ለቅዱስ ያሬድ ሐውልት ማቆም ያለበት ማን ነው?

ለቅዱስ ያሬድ ሐውልት ማቆም ያለበት ማን ነው?

February 2020

በብዛት በመነበብ ላይ ያሉ መጣጥፎች

ዶ/ር ቅድስት

“አንድ ሰው ምልክቱ ስላልታየበት በኮሮና ቫይረስ አልተጠቃም ብሎ መደምደም አይቻልም”

May 2020
C:\Users\IT\Documents\A01\pics

የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውኃ ሙሌትና መቆሚያ ያጣው የግብፅ ሩጫ

July 2020
የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ

የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ

May 2020
ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

May 2020
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ

ከጦር ጀግኖች ባሻገር . . .

May 2020

Follow us on Facebook

  • ዶ/ር ቅድስት

    “አንድ ሰው ምልክቱ ስላልታየበት በኮሮና ቫይረስ አልተጠቃም ብሎ መደምደም አይቻልም”

    384 shares
    Share 384 Tweet 0
  • የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውኃ ሙሌትና መቆሚያ ያጣው የግብፅ ሩጫ

    21 shares
    Share 21 Tweet 0
  • የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ

    0 shares
    Share 0 Tweet 0
  • ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

    44 shares
    Share 44 Tweet 0
  • ከጦር ጀግኖች ባሻገር . . .

    169 shares
    Share 169 Tweet 0
Ethiopian Reporter Magazine

ሪፖርተር ሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተር

(+251) 116 61 61 81

(+251) 116 61 61 85

[email protected]

የኢትዮጵያ ሪፖርተር መጽሔት

የኢትዮጵያ ሪፖርተር መጽሔት በሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ ሴንተር እየታተመ የሚወጣ ወርኃዊ መጽሔት ሲሆን፣ የሚያተኩረውም በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር መጽሔት በ ኢሜይል ለማግኘት

  • Ethiopian Reporter
  • The Reporter Ethiopia
  • Reporter Tenders
  • Ethiopian Reporter Jobs

© 2020 Ethiopian Reporter Magazine - By Media And Communications Center.

ውጤት የለም
ሁሉንም ውጤት ይመልከቱ
  • የፊት ገጽ
  • ከሪፖርተር
  • ምን ከበር አለ?
  • አንኳር
  • አደባባይ
  • ምጣኔ ሀብት
  • ማኀበረ ሰብ
  • የሕግ ነገር
  • ጥበብ እና ባህል
  • እንዴት ነው ነገሩ?
  • ሰበዝ
  • ሠገነት
  • ስፖርት

© 2020 Ethiopian Reporter Magazine - By Media And Communications Center.

Login to your account below

Forgotten Password?

Fill the forms bellow to register

All fields are required. Log In

Retrieve your password

Please enter your username or email address to reset your password.

Log In