ከአምስት ዓመታት በፊት በ2ዐዐ7 ዓ.ም. በተደረገው አምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ፣ መቶ በመቶ አሸናፊ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞከራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላው ከሁለት ጊዜ በላይ ካቢኔውን ቢቀያይርም አገሪቱን በተረጋጋ ሁኔታ መምራት ባለመቻሉ የበላይ አመራሩ በ2ዐ1ዐ ዓ.ም. መጋቢት ወር መገባደጃ ላይ ተቀይሯል፡፡
በአምስተኛው አገራዊ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርገው የተሾሙትን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በመተካት ወንበሩን የተቆጣጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን በያዙ በቀናት ውስጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ኢሕአዴግ በሕዝቡና በአገር ላይ የፈጸማቸውን ጥፋቶችና ስህተቶች በማመን ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ ከሰኔ 16 ቀን 2ዐ1ዐ ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ ተግዳሮቶች የገጠማቸውም ቢሆንም፣ ይቅርታውን ተስፋ አድርገው የተከተሏቸው በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገሮች የነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ሳያሰሙ የየራሳቸውን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ወደ አገር ቤትም እንደገቡ በደጋፊዎቻቸው አማካይነት በርካታ ጥፋቶች ሲፈጸሙ ኃላፊነት ወስደው ሕዝቡን ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ፣ እንደ ጀብዱና ማስፈራሪያ አድርገው የወሰዱት ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ነበሩ፡፡ የእነዚህ የተወሰኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ በአክራሪ አክቲቪስቶች እገዛ ያደረጉት ዘርን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ያሳዩትን የዴሞክራሲ ጭላንጭል ወደ ማጥፋት ወስዶታል፡፡ በመሆኑም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ደጋፊዎች ተቃውሞአቸውን መሰንዘር ጀምረዋል፡፡ ምንም እንኳን ጥቂት የተፎካካሪ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ተቃውሞአቸውን በመቀጠል የተለያዩ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ለመፈፀም ባደረጉት እንቅስቃሴ በሰው ሕይወት፣ በሃይማኖት ተቋማትና የተለያዩ ንብረቶች ላይ የማይተካ ጉዳት ቢያደርሱም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልፎ አልፎ በስብሰባዎችና በጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ከሚያስተላልፉት ማስጠንቀቂያና ምክር በስተቀር ዕርምጃ አልወሰዱም፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢሕአዴግን በሚመለከት ባደረጉት ጠቅላላ ስብሰባ “ኢሕአዴግ” የሚለውን ለ31 ዓመታት የቆየውን ስያሜ ወደ ብልጽግና ፓርቲ እንዲቀየር አድርገዋል፡፡ ከሕወሓት በስተቀር ሁሉም ክልላዊ ፓርቲዎች በመደገፋቸውና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ተመዝግቦ ዕውቅና በማግኘቱ ሥራውን ቀጥሏል፡፡
ፓርቲው የ2ዐ12 አገራዊ ምርጫ መደረግ አለበት በማለት ከጥቂት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይ አቋም በመያዝ፣ አብዛኛዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባይስማሙም ምርጫውን ነሐሴ 23 ቀን 2ዐ12 ዓ.ም. ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀጠሮ ይዞ የተለያዩ የምርጫ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ሽር ጉድ ማለት ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን መድኃኒት የለሹና ዘር፤ ቀለምና ማንነትን የማይለየው ኖብል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ በመከሰቱ፣ አገራዊ ምርጫ 2ዐ12 አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ወረርሽኙ በከፍተኛ ፍጥነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በመግደልና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን የቫይረሱ ሰለባ በማድረግ ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም አገሮችን ሥጋት ላይ ጥሏል፡፡ በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫው እንዲካሄድ ማድረግ እንደማይችል ለፓርላማው አሳውቋል፡፡
መንግሥትም ወረርሽኙን በጋራ ለመከላከል እንዲያመቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ ይህ ሁሉ ተደምሮ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማድረግ እንደማይችል ያቀረበው ጥያቄ በፓርላማው ተቀባይነት በማግኘቱ፣ በቀጣይ ምን መደረግ እንዳለበት ጉዳዩን አስጠንቶ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ኃላፊነቱን ለሕግ፣ ለፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶለት ነበር፡፡ ኮሚቴውም ያቀረበው ሐሳብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን እንዲተረጐም የሚል ነው፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ሕገ መንግሥቱን ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተረጉም እንጂ ከወር በኋላ የምርጫ ጊዜያቸውን ስለሚያጠናቅቁት የምክር ቤት አባላትም ሆነ የገዥው መንግሥትን ዕጣ ፈንታ በሚመለከት ያለው ነገር አልነበረም፡፡ የምክር ቤቱም የቀረበውን “ሕገ መንግሥቱ ይተርጐም” ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ወስኖ አሳልፏል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ የደነገገውን በመተላለፍ ምክር ቤቱ የሥራ ዘመኑን በሕገ ወጥ መንገድ ማራዘም እንደማይችልና ምንም የሚተረጐም ነገር እንደሌለ ከሕወሓት አባላትና አንዳንድ የተፎካከሪ ፓርቲዎች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የቋሚ ኮሚቴውን ሐሳብ በመደገፍ ሕገ መንግሥቱ እንዲተርጐም ተስማምተዋል፡፡ ሕወሓት የትግራይ ሕዝብን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለማስጠበቅ እንደሚሠራ፣ ምርጫም እንደሚያካሂድና መሰል አጀንዳ ከሚያካሂዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ማኒስትር ዓብይ፣ ሚያዝያ 29 ቀን 2ዐ12 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ደግሞ ተቃውሞ ያነሱትን ተፎካካሪ ፓርቲዎችና አንዳንድ “ተሰሚነት አለን” የሚሉ አክቲቪስቶችን አስጠንቅቀዋል፡፡ ስለ ሕገ መንግሥት መተርጐም በሌሎችም አገሮች ተመሳሳይ ልምድ መኖሩንና ያለውን ጥቅም፣ እንዲሁም የሽግግር መንግሥት የማያስፈልግ መሆኑን አስረድተው፣ “ሕዝብ ለአደጋ ተጋልጦ ባለበት ጊዜ ሥልጣንን ያለ ምርጫ ከሕግ አግባብ ውጭ በሁከትና ብጥብጥ ካልሰጣችሁኝ፣ አገር አተራምሳለሁ የሚለውን ማንኛውንም ኃይል አንታገስም፡፡ በቂ ዝግጅትም አለን፤” በማለት ከመስከረም 3ዐ ቀን 2ዐ13 ዓ.ም. በኋላ “ማንም አካል ሥልጣን የለውም ሁላችንም እኩል ነን፡፡ መከላከያውንም ሆነ ደኅንነቱን የሚያዝ ማንም የለም፤” በማለት የተከራከሩ አካላትን አስጠንቅቀዋል፡፡ ቀጣይ የምርጫ ሁኔታ በምን መልኩ እንደሚደረግና ከመቼ እስከ መቼ እንደሚደረግ የሚተነትነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉምና ዝርዝር ሁኔታ ከተገለጸ በኋላ ምን ሊያስከትል እንደሚችልም እየተጠበቀ ነው፡፡